ቅዱስ ቁርባን እኛ ቅዱስ እንድንሆን ሊረዳን ይችላል
ቅዱስ በሆነው የቅዱስ ቁርባን ስርዓት ላይ የሁልጊዜ ተሳትፎዋችንን ተፅእኖ እና ሀይል ለማሳደግ አምስት መንገዶችን አስቡ።
ከትውስታዎቼ መካከል ቀደምት የሆነው በቤታችን በዋርናምቡል፣ አውስትራሊያ የተካሄዱት የቅዱስ ቁርባን ስብሰባዎች ናቸው። ከ10 እስከ 15 የሚጠጉ ሰዎች የእኛ ቅርንጫፍ ላይ ይካፈሉ ነበር፣ እናም ከሶስቱ የክህነት ተሸካሚዎች መካከል የሆነው፣ አባቴ፣ ቅዱስ ቁርባንን የመባረክ ተደጋጋሚ እድል ነበረው። የቅዱስ ቁርባን ፀሎት ቃላቶችን በትህትና እና በጥንቃቄ ሲያነባቸው እኔ የነበረኝን ስሜት አስታውሳለሁ። መንፈስ ቅዱስ ሲሰማው አብዛኛውን ጊዜ ድምፁ ይንቀጠቀጥ ነበር። እንዳንዴ ፀሎቱን ከመጨረሱ በፊት ስሜቶቹን ለመቆጣጠር ማንበቡን ቆም ያረግ ነበር።
የአምስት አመት ልጅ እንደመሆኔ መጠን፣ ሲነገር እና ሲደረግ የነበረውን ነገር ሙሉ ትርጉም መረዳት አልችልም ነበር፤ ቢሆንም፣ የሆነ የተለየ ነገር እየተከሰተ እንደነበር አውቅ ነበር። አባቴ የአዳኝን ፍቅር ለእኛ ሲያሟላ የሚያረጋጋውን እና የሚያፅናናውን የመንፈስ ቅዱስ ተፅእኖ ይሰማኝ ነበር።
አዳኝ እንዲህ ሲል አስተማረ፣ “እናም ይህን ንስሀ ለገቡት እናም በስሜ ለተጠመቁት ሁልጊዜ ታደርጉታላችሁ። እናም ለእናንተ ያፈሰስኩትን ደም ለማሰብ፣ እኔን ሁልጊዜ እንደምታስታውሱኝ ለአብ ለመመስከር ታደርጉታላችሁ። እናም ሁልጊዜም የምታስታሱኝ ከሆነ መንፈሴ ከእናንተ ጋር ይሆናል” (3 ኔፊ 18፥11)።
ቅዱስ እንድንሆን እኛን በሚረዳው የተቀደሰ የቅዱስ ቁርባን ስርዓት ላይ ያለንን የሁልጊዜ ተሳትፎ ተጽእኖ እና ሀይል ለማሳደግ አምስት መንገዶችን ሁላችንም እንድናስብ እጋብዛለሁ።
1. እስቀድሞ መዘጋጀት
የቅዱስ ቁርባን ዝግጅታችንን የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት አስቀድመን መጀመር እንችላለን። መንፈሳዊ እድገታችንን እና ዝግታችንን ለማሰላሰል ቅዳሜ ጥሩ ቀን ሊሆን ይችላል።
ልክ እንደ ሰማይ አባታችን የመሆን ጉዟችን ላይ ሟችነት ጠቃሚ ስጦታ ነው። እንድንለወጥ እና እንድናድግ እድል የሚሰጡንን ፈተናዎችን እና መከራዎችን ማካተቱ ግድ ነው። ንጉስ ቢንያም እነዲህ ሲል አስተማረ፣ “ተፈጥሮአዊው ሰው ለእግዚያብሔር ጠላት የነበረ ሲሆን፣ እርሱም ቅዱስ የሆነውን መንፈስ ወደራሱ ካልጋበዘ፣ እናም ስጋዊ ሰውነቱን ካልቀየረ እናም በጌታ ክርስቶስ የሀጢያት ክፍያ ቅዱስ አማካኝነት ቅዱስ ካልሆነ፣” (ሞዛያ 3፥19)። በቅዱስ ቁርባን ስርዓት ላይ መሳተፍ ልቦቻችን እና ነፍሶቻችን በተሻለ ሙላት ለእግዚያብሔር ለመሰጠት እድልን ይሰጠናል።
በዝግጅታችን ውስጥ፣ ለክርስቶስ ቤዛነት ምስጋናን ስንገልፅ፣ ለስህተታችን እና ለጉድለታችን ንስሀ ስንገባ፣ እንዲሁም እንደ እርሱ የመሆን ቀጣይነት ጉዟችን ላይ የአባትን እርዳት ስንጠይቅ ልቦቻችን የተሰበሩ ይሆናሉ። ከዛም የእርሱን መስዋትነት ለማስታወስ እና ለገባናቸው ቃልኪዳኖች ሁሉ መሰጠታችንን ለማደስ ቅዱስ ቁርባን የሚያዘጋጅልንን እድል መመልከት እንችላለን።
2. በጊዜ መድረስ
ከስብሰባው በፊት በጣም ቀደም ብለን ስንደርስ እና በፒያኖው ላይ የተጫኑትን መዝሙሮች በሚሰሙ ጊዜ ስናሰላስል የቅዱስ ቁርባን ልምዳችን ማደግ ይጀምራል።
ፕሬዘዳንት ቦይድ ኬ. ፓከር እንዳስተማሩት፥ “በእርጋታ የሚጫወተው የፒያኖው መዝሙር፣ ለመንፈስ ምግብ ነው። መነሳሳትን ይጋብዛል።”1 ፕሬዘዳንት ሩስል ኤም. ኔልሰን እንዲህ አብራሩ፣ “የመነጋገሪያ ወይም መልእክቶችን የምንቀባበልበት ጊዜ አይደለም፣ ነገር ግን መሪዎችን እና አባላትን ለቅዱስ ቁርባን መንፈሳዊ ዝግጅት ሲያደርጉ በፀሎት መንፈስ የምናሰላስልበት ጊዜ ነው።”2
3. ከቅዱስ ቁርባን መዝሙር ቃላቶች ላይ መዘመር እና መማር
የቅዱስ ቁርባን መዝሙር በቅዱስ ቁርባን ልምዳችን ውስጥ በተለየ መልኩ ጠቃሚው ክፍል ነው። መዝሙር ሀሳባችንን እና ስሜታችንን ከፍ ያደርጋል። ቃላቶቹ እና ሀይል ያላቸው አስተምሮቶቹ ላይ ስናተኩር የቅዱስ ቁርባን መዝሙር ወጥ የሆነ ታላቅ ተፅዕኖ አለው። ከእነኚህ አይነት ቃላቶች ብዙ እንማራለን “ለእኛ ተጎዳ፣ ተሰበረ፣ ተሰቃየ፣”3 “ልቦቻችን እና እጆቻችን የፀዱ እና ንፁህ መሆናቸውን እናስታውስ እና እናረጋግጥ፣”4 ፍትህ፣ ፍቅር፣ እና ምህረት በመለኮታዊ ስምምነት የሚገናኙበት ቦታ!”5
ቅዱስ ቁርባን በመውሰድ ዝግጅት ውስጥ መዝሙር ስንዘምር፣ ቃላቶቹ የገባናቸውን ቃልኪዳኖች የመሰጠት አካል መሆን ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ይህን አስቡበት፥ “ጌታ እንወድሀለን፣ ልቦቻችን ሙሉ ናቸው። አንተ በመረጥከው መንገድ እንጓዛለን።”6
4. በቅዱስ ቁርባን ፀሎቶች ላይ በመንፈሳዊ መልኩ ተሳተፉ (ሞሮኒ 4–5 ተመልከቱ)
የተለመዱትን ቅዱስ ቁርባን ፀሎት ቃላትን በጥሞና ከማዳመጥ ይልቅ፣ በቅዱስ ቁርባን ፀሎት ላይ የተካተቱትን መሰጠቶች እና የተያያዙትን በረከቶች በማሰብ በመንፈሳዊነት ስንካፈል፣ በተሸለ መልኩ እንማራለን እናም ይሰማናል።
ለነፍሳችን ዳቦው እና ውሃው ተባርከዋል እናም ተቀድሷል። የአዳኝን መስዋት እና እርሱ እኛ ቅዱስ እንድንሆን መርዳት እንደሚችል ያስታውሱናል።
ዳቦውን የምንወስደው ሁሉንም ሰው ለትንሳኤ ብቁ ለማድረግ የሰጠውን የልጁን ስጋ ለማሰብ እንደሆነ እናም ውሃውን የምንጠጣው፣ ንስሀ የምንገባ ከሆነ ሊያድነን ዘንድ በነፃ ያፈሰሰውን የልጁን ደም ለማሰብ እንደሆነ ፀሎቶቹ ያብራራሉ።
ፀሎቶቹ “ፈቃደኛ ይሆኑ ዘንድ” (ሞሮኒ 4፥3) የሚለው የቃል ኪዳን ሀረግ ያስተዋውቃሉ። ይህ ሀረግ ለእኛ በጣም አቅም ያለው ሀይል አለው። ለማገልገል እና ተሳትፎ ለማድረግ ፈቃደኞች ነን? ለመለወጥ ፈቃደኞች ነን? ድካማችን ላይ ለመስራት ፈቃደኞች ነን? ለሌሎች ለመድረስ እና ለመባረክ ፈቃደኞች ነን? አዳኝ ላይ እምነታችንን ለማድረግ ፈቃደኞች ነን?
ቃልኪዳኖቹ ሲገለፁ እና እኛም ስንካፈል፣ እነዚህን ለማድረግ ፈቃደኞች እንደሆንን በልባችን እናረጋግጣለን፤
-
በላያችን ላይ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ለመውሰድ።
-
የእርሱን ትእዛዛት በሙሉ ለመጠበቅ ለመጣር።
-
ሁሌም እርሱን ለማስታወስ።
ፀሎቱ ልብ በሚነካ ግብዣ እና ቃል በመግባት ይጠናቀቃል፤ “መንፈሱ ሁልግዜም ከእነርሱ ጋር ይሆን ዘንድ” (ሞሮኒ 4፥3)።
ጳውሎስ እንዲህ ሲል ፃፈ፣ “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትእግስት፣ ቸርነት፣ ነጎነት፣ የዋህነት፣ ራስን መግዛት ነው” (ገላትያ 5፥22–23)። ቃል ኪዳናችንን ስንጠብቅ የሚያምሩ በረከቶች እና ስጦታዎችን እናገኛለን።
5. ቅዱስ ቁርባን በሚታደልበት ሰዓት ስለ እርሱ አሰላስሉ እናም አስታውሱት።
የክህነት ተሸካሚዎች ቅዱስ ቁርባኑን በሚያሳልፉበት ሰዓት ያለው የፅሞና ወቅቶች ለእኛ የተቀደሱ መሆን ይችላሉ።
ዳቦው ሲታደል፣ አዳኝ “ህዝቡን ያሰረውን የሞት እስር ይፈታ ዘንድ ሞትን በራሱ ላይ ይወስዳል” የሚለው እርሱ ለእኛ ያለው የመጨረሻ የፍቅር ድርጊት፣ እንደሆነ ልናሰላስል እንችላለን። (አልማ 7፥12)።
እንዲህ የሚለው ታላቅ የትንሳኤ በረከት ልናስታውስ እንችላለን፣ “ለሁሉም ይሆናል ለሽማግሌዎች እና ለወጣቶች፣ ለታሰሩ እና ነፃ ለሆኑትም፣ ለሴትና ለወንድ፣ ለኃጢያተኛ እና ለፃድቃን፣ እናም እንዲሁም የራስ ፀጉራቸው እንኳን አይጠፋም።” (አልማ 11፥44)።
ውሃው ሲታደል፣ የአዳኝን ተማፅኖ ልናስታውስ እንችላለን፤
“እነሆም እኔ፣ አምላክ፣ ንስሀ ከገቡ እነሱ እንዳይሰቃዩ ዘንድ፣ እነኚህን ነገሮች ለሁሉም ተሰቃይቻለሁ፤ …
“ይህንን ስቃይ እኔን፣ እነሆም የሁሉም ታላቅ የሆንኩትን አምላክን፣ በህመሙ ምክንያት እንድንቀጠቀጥ፣ እና ከእያንዳንዷ የቆዳ ቀዳዳ እንድደማ፣ እንዲሁም በአካል እና በመንፈስ እንድሰቃይ ምክንያት ሆነ— እናም መራራውን ፅዋ እንዳልጠጣ እና እንዳላፈገፍግ አደረገኝ” (ት. እና ቃ. 19፥16፣ 18)።
“ይህን ማድረጉን እናስታውሳለን በስጋ አንጀቱ በምህረት የሞላ ዘንድ፣ ድካማችንን በራሱ ላይ አደረገ እናም በስጋ ህዝቡን ከድካሙ እንዴት እንደሚረዳ ያውቅ ዘንድ ይህንን ያደርጋል” (አልማ 7፥12)።
የቅዱስ ቁራባን ልምዳችንን ከግንዛቤ ውስጥ ስናስገባ፣ እንዲህ ብለን እራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን፤
-
ለቅዱስ ቁርባን በተሻለ መልኩ ለመዘጋጀት በዚህ ሳምንት ምንድን ነው የማደርገው?
-
ከቅዱስ ቁርባን ስብሰባ አጀማመር ጋር አብርው መሄድ በሚችሉት ፅሞና እና መገለጥ ላይ የራሴን አስተዋፅኦ መጨመር እችላለውን?
-
በቅዱስ ቁርባን መዝሙር ውስጥ ምን አይነት ትምህርት ነው የተሰጠው?
-
የቅዱስ ቁርባን ፀሎቶቹን በማዳምጥ ጊዜ የሰማሁት እና የተሰማኝ ምንድን ነው?
-
ቅዱስ ቁርባን ሲታደል ስለ ምን እያሰብኩ ነበር?
ሽማግሌ ዴቪድ ኤ. ቤድናር እንዳስተማሩት፥ “የቅዱስ ቁርባን ስነስርዓት ቅዱስ እና ከልብ ንሰሀ ለመግባት እና መንፈሳዊ እድሳት ለማድረግ ተደጋጋሚ ግብዣ ነው። ቅዱስ ቁርባንን የመካፈል ድርጊት ብቻ፣ በራሱ የሀጢያት ስርየትን አያመጣም። ነገር ግን በተሰበረ ልብ እናመ በተዋረደ መንፈስ በቅዱስ ቁርባን ስርዓት ላይ በጥንቃቄ ስንዘጋጅና ስንካፈል፣ ከዚያ ቃልኪዳኑ የጌታ መንፈስ ሁሌም ከእኛ ጋር እንደሚኖር ነው። እናም የእኛ ቋሚ ጓደኛ በሆነው በሚያነፃው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በኩል፣ የሀጢያቶቻችንን ስርየት ሁሌም ማቆየት እንችላለን።”7
በቅዱስ ቁርባን ስርዓት ላይ ዝግጅታችንን እና መንፈሳዊ ተሳትፏችንን ስናደርግ፣ ለእኛ ስለተቀመጡት እጅግ በጣም በርካታ በረከቶች እመሰክራለሁ። እነኚህ በረከቶች ለእኛ የተቀመጡት በሰማይ አባት ፍቅር እና በተወደደው ልጁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ማብቂያ በሌለው የሀጢአት ክፍያ መስዋእት ምክንያት እንደሆነ በተጨማሪ እመሰክራለሁ። በተቀደሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።