በደመና እና በጸሃይ ብረሃን ጌታ ከእኔ ጋር ሁን!
“በደመና እና በጸሃይ ብረሃን” ጌታ አብሮን እንደሚሆን “ስቃይ በክርስቶስ ፍቅር እንደሚዋጥ” እመሰክራለሁ።
ከተወደዱ መዝሙሮቻችን አንዱ “በደመና እና በጸሃይ ብረሃን ጌታ ከእኔ ጋር ሁን!” የሚለውን ልመና ይገልጻል።1 በአንድ ወቅት ወደ ትልቅ ማዕበል እየተጠጋ በነበረ አውሮፕላን ወስጥ ነበርኩ። በመስኮት ወደ ውጭ ስመለከት ጥቅጥቅ የደመና ክምር አየሁ። እየጠለቀ የነበረው ጸሃይ ጨረር በደመናት ላይ በማንጸባረቅ በሃይል እንዲበሩ አደረገ። ወድያው ግን አውሮፕላኑ በጥቅጥቅ ደመና መሃል ወረደ እናም ሁላችንም በድንገት በድቅድቅ ጨለማ ተከበብን እናም ከቅጽበት በፊት ተመልክተን የነበረውን ሃይለኛ ብርሃን አጠፋብን። 2
እነዚህ ጥቁር ደመናዎች በህይወታችን ሊፈጠሩ ይችላሉ። የእግዝአብሄርን ብረሃን እንዳናይ እና ያ ብርሃን መኖሩን እንኳን እንድንጠራጠር ያደርጋሉ። ድብታ ፣ ስጋት እና ሌሎች የአዕምሮና የስሜት መከራዎች ከነዚያ ደመናት መሃል የተወሰኑት ናችው። ራሳችንን፣ ሌሎችን እንዲሁም እግዚአብሔርን የምንረዳበትን መንገድ ሊያዛቡብን ይችላሉ። በሁሉም የአለም ጥግ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶችና ወንዶችን ያጠቃሉ።
ስሜት እንድናጣ የሚያደርጉ ፈተናዎች ያላጋጠማቸውን ሌሎችን ሊያጠቃ የሚችል ጥርጣሬ እንደዚሁ ሊጎዳ ይችላል። ልክ እንደማንኛውም የሰውነት ክፍል አዕምሯችን ለበሽታ፣ ለአደጋ እና የኬሚካል አለመመጣጠን ሊያጋጥመው ይችላል። ለአካላዊ ህመም እንደምናደርገው ሁሉ ከእግዚአብሔር፣ በአካባቢያችን ከሚገኙ ሰዎች እና ከጤናና የአዕምሮ ህክምና ባለሙያዎች እርዳታን መፈለግ አለብን።
‘የሰው ልጆች በሙሉ —ወንድና ሴቶች —በእግዚአብሔር አምሳል ነው የተፈጠሩት። እያንዳንዱ በሰማይ ወላጆች የተወደዱ የመንፈስ ሴት እና ወንድ ልጆች ናቸው፣ እናም… እያንዳንዱ መለኮታዊ ተፈጥሮ እና ፍጻሜም አላቸው።”3 እንደ ሰማይ ወላጆቻችን እና አዳኛችን አካላዊ ሰውነት አለን።4 እናም ስሜቶችን እንለማመዳለን።5
ውድ እህቶቼ ለተወሰነ ጊዜ ማዘን ወይም መጨነቅ ጤናማ ነገር ነው። ሃዘን እና ስጋት ተፈጥሯዊ የሰው ስሜቶች ናቸው።6 ነገር ግን ሁልጊዜ የምናዝን ከሆነ እና ህመማችን ጥልቅ ሆኖ የሰማይ አባታችን እና የልጁ ፍቅር ፣ መንፈስ ቅዱስ እንዳይሰማን የሚከለክል ከሆነ የድብታ፣ የስጋት ወይም የስሜት ችግር ተጠቂ ልንሆን እንችላለን።
አንዴ ልጄ እንዲህ ብላ ጽፋ ነበር “ ዘወትር እጅግ አዝን የነበረ ጊዜ ነበረ። ሃዘን የሚታፈርበት ነገር እና የድክመት ምልክት እንደሆነ አድርጌ ሁልጊዜ አስብ ነበር። ስለዚህ ሃዘኔን ለራሴ ያዝኩት ።… ፍጹም የማልረባ እንደሆንኩ ተሰማኝ።”7
አንድ ጓደኛ እንዲህ ስትል ገልጻው ነበር ”ከልጅነቴ ጀምሮ የተስፋ ቢስነት፣ የጨለማ ፣የብቸኝነት እና የፍርሃት እንዲሁም የተሰበርኩ ወይም ጎዶሎ እንደሆንኩ ከሚሰሙኝ ስሜቶች ጋር የማያቋርጥ ውግያ ውስጥ ነበርኩ። ህመሜን ለመደበቅ የተቻለኝን ሁሉ አደርግ ነበር እና እያደኩና ጠንካራ እንደሆንኩ ብቻ እንድመስል እፈልግ ነበር።8
ውድ ጓደኞቼ በማናችንም ላይ ሊከሰት ይችላል - በተለይም እንደ ደስታ እቅድ አማኞች አሁን ላይ ፍጹማን ለመሆን በማሰብ አላስፈላጊ ሸክም በራሳችን ላይ ስናስቀምጥ። እንደነዚህ አይነት ሃሳቦች ስሜትን የሚጎዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ፍጹምነት በህይወት ዘመናችን ሙሉ እና ከዚያም በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ አማካኝነት ብቻ የሚሳካ ሂደት ነው። 9
በአንጻሩ ፍጹማን እንዳልሆንን በማመን ስለ ስሜታዊ ፈተናዎቻችን ስንናገር ሌሎች የራሳቸውን ትግል እንዲያካፍሉ ፈቃድ ይሰጣቸዋል። በአንድነትም ተስፋ እንዳለና ብቻችንን መሰቃየት እንደሌለብን እንገነዘባለን።10
እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርትነት “አንዳችን የአንዳችንን ሸክም ለመሸከም” እና “ከሚያዝኑት ጋር ለማዘን” ከእግዚአብሔር ጋር ቃልኪዳን ገብተናል።11 ይህም ስለስሜታዊ ህመም ማወቅ፣ እነዚህን ችግሮች ተደራሽ ለማድረግ የሚረዱ አስፈላጊ ነገሮችን መፈለግ፣ በመጨረሻም ራሳችንን እና ሌሎችን ወደ ዋነኛው ፈዋሽ ወደ ክርስቶስ ማምጣትን ያካትታል።12 ምንም እንኳን ሌሎች እያለፉ ያለበትን ነገር መረዳት ባንችል እንኳን ህመማቸው እውነተኛ እንደሆነ እውቅና መስጠት መረዳትን እና ፈውስን የመፈለግ አስፈላጊ የመጀመርያ እርምጃ ነው። 13
በአንዳንድ ሁኔታዎች የድብታ ወይም የስጋት ምክንያት ይታወቃል። በሌሎች ጊዜዎች ለመረዳት ሊከብድ ይችላል። 14 አዕምሯችን አንዳንድ ጊዜ በአመጋገብ፣ በእንቅልፍ እና በአካል እንቅስቃሴ ሊስተካከል በሚችል ጭንቀት 15ወይም በሚያንገዳግድ ድካም 16ሊሰቃይ ይችላል። በሌሎች ጊዜያት በህክምና ወይም በሰለጠነ ባለሙያ መሪነት መድሃኒት ሊያስፈልግ ይችላል።
ህክምና ያልተደረገለት የአዕምሮ ወይም የስሜት በሽታ ከሌሎች መለየት ፣ አለመግባባት፣ የተሰበሩ ግንኙነቶች፣ ራስን መጉዳት እንዲሁም ራስን ወደማጥፋት ሊመራ ይችላል። ከብዙ አመታት በፊት የገዛ አባቴ ራሱን በማጥፋቱ ይህን በቀጥታ አውቃለሁ። የሱ ሞት ለኔ እና ለቤተሰቤ አስደንጋጭና ልብ የሚሰብር ነበር። ከሃዘኔ ለመውጣት ብዙ አመት ወስዶብኛል። እናም ራስን ስለማጥፋት በትክክለኛ መንገድ ማውራት ከማበረታታት ይልቅ እንደሚከላከል የተማርኩት በቅርቡ ነው። 17 አሁን ላይ ስለአባቴ ሞት ከልጆቼ ጋር በግልጽ ተወያይቻለሁ። እናም አዳኙ በሁለቱም መጋረጃዎች በኩል ሊሰጥ የሚችለውን ፈውስ መስክሪያለሁ።18
በሚያሳዝን ሁኔታ በከባድ ድብታ የተጠቁ ሰዎች ራሳችውን ከቅዱሳን ያርቃሉ። ምክንታቱም አንድ ምናባዊ ቦታ የሚገጥሙ መስሎ ስለማይሰማቸው ነው። በርግጥም ከኛ ጋር መሆን እንዳለባቸው እንዲሰማቸው እና እንዲያውቁ መርዳት እንችላለን። ድብታ የድክመት ውጤት ወይም ሃጥያትን ተከትሎ የሚመጣ እንዳልሆነ መረዳት አስፈላጊ ነው።19 “በድብቅ ይዳብራል ፤ ነገር ግን የሰውን ችግር እንደራስ በማየት ይሟሽሻል።” 20 በአንድነት የማግለልና የመጥፎን ስም ደመናት ሰብረን እናልፋለን፤ የሃፍረት ሸክም ይነሳል እናም የፈውስ ተአምር ሊከሰት ይችላል።
በምድራዊ አገልግሎቱ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የታመሙትንና የተጠቁትን ፈውሷል። ነገር ግን እያንዳንዳቸው ፈውሱን ለማግኘት በእርሱ እምነት እንዲኖራቸው እና እንዲተገብሩ አስፈልጓቸዋል። በርሱ ለመፈወስ አንዳንዶቹ ረጅም መንገድ ተጓዙ፣ ሌሎች እጃቸውን ዘርግተው ልብሱን ነኩ እናም ሌሎች ሰዎች ተሸክመው አመጧቸው።21 ስለፈውስ ሲታሰብ ሁላችንም አጥብቀን እርሱን አንፈልገውምን? “ሁላችንም ለማኞች አይደለንምን?”22
እስቲ የአዳኙን መንገድ እንከተል እና ርህራሄን እንጨምር፣ የመፍረድ ዝንባሌያችንን እንቀንስ እናም የሌሎችን መንፈሳዊነት ተቆጣጣሪ መሆንን እንተው። በፍቅር ማዳመጥ የምንወዳቸውን ሰዎች ወይም ጓደኞቻችንንየሚያፍኑ ጥቅጥቅ ደመናዎች ለመሸከም ወይም ለማንሳት ልንሰጥ የምንችለው ታላቅ ስጦታ ነው 23 ፤ በመሆኑም በኛ ፍቅር አማካኝነት ዳግም መንፈስ ቅዱስ ሊሰማቸው እና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚወጣውን ብርሃን መመልከት ይችላሉ።
ዘወትር ”በጨለማ ጭጋግ”24 የምትከበቡ ከሆነ ወደ ሰማይ አባት ተመለሱ። የትኛውም አይነት ያጋጠማችሁ ነገር የሱ ልጅ የመሆናችሁን ዘላለማዊ እውነት እና እንደሚወዳችሁ ሊቀይር አይችልም።25 ክርስቶስ አዳኛችሁ እና የሚቤዣችሁ ነው።እናም .እግዚአብሔር አባታችሁ እንደሆነ አስታውሱ። ይረዳሉ፡፡ አጠገባችሁ ሆነው ሲያዳምጧችሁ እና ድጋፍ ሲሰጧችሁ ሳሉ። 26 “በመከራችሁ ያጽናኗችኋል” 27 የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ እናም በጌታ የሃጢያት ክፍያ ጸጋም እመኑ።
ትግሎቻችሁ እናንተን አይወስኑም ነገር ግን ሊያነጥሯችሁ ይችላሉ።28 “በስጋ መውጊያ”29 ምክንያት ለሌሎች የበለጠ ርህራሄ ሊሰማችሁ ይችል ይሆናል። በመንፈስ ቅዱስ በመመራት “ደካሞችን ለመርዳት፣ የወረዱ እጆችን ወደ ላይ ለመደገፍ እና የደከሙ ጉልበቶች ለማጠንከር” 30 ታሪካችሁን ለሌሎች አካፍሉ።
በአሁን ሰአት እየታገልን ላለን ወይም እየታገለ ያለን ሰው እየረዳን ያለን መንፈሱ ሁልጊዜ ከኛ ጋር እንዲሆን የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ለመከተል ፍቃደኞች እንሁን።31 መንፈሳዊ ጥንካሬ የሚሰጡንን “ትንሽና ቀላል ነገሮች”32 እንስራ። ፕሬዝደንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳሉት“እንደ ከፍ ያለ ንጽህና፣ ትክክለኛ መታዘዝ፣ በቅንነት መፈለግ፣ በመጽሃፈ ሞርሞን ዉስጥ ባለው የክርስቶስ ቃል መመገብ የሰማያትን መስኮት የሚከፍት የለም” ብለዋል።33
አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ በስጋ አንጀቱ በምህረት ይሞላ ዘንድ፣ ድካማችንን በራሱ ላይ አደረገ እናም በስጋ ህዝቡን ከድካሙ እንዴት እንደሚረዳ ያውቅ ዘንድ ይህንን እንዳደረገ” እናስታውስ።34 እሱ “ልባቸው የተሰበረውን ይጠግን ዘንድ … የሚያለቅሱትንም ሁሉ ያጽናና ዘንድ … በአመድ ፋንታ አክሊልን፣ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት ፣በሃዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጎናጸፍያ ይሰጣቸው ዘንድ” መጥቷል። 35
“በደመና እና በጸሃይ ብረሃን” ጌታ አብሮን እንደሚሆን እመሰክራለሁ፤ “ስቃይ በክርስቶስ ፍቅር እንዲዋጥ”36እናም “በጸጋ የምንድነው ምንችለውን ካደረግን በኋላ እንደሆነ እናውቃለንና።” 37 ክርስቶስ “ፈውስ በክንፎቹ ዉስጥ” 38ይዞ እንደሚመለስ እመሰክራለሁ። በመጨረሻም እርሱ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻችን ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ …ኀዘንም አይሆንም።” 39 “ወደ ክርስቶስ ለሚመጡ እና በሱ ፍጹማን ለሚሆኑ” 40 “እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃን ይሆናል የለቅሶም ወራት ታልቃለች … ጸሃይ ከዚያ በኋላ አትጠልቅም።41 በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።