መፅሐፈ ኢኖስ
ምዕራፍ ፩
ኢኖስ በኃይል ፀለየ እናም ለኃጢአቱ ስርየትን አገኘ—ለላማናውያን ወደፊት በሚመጣው ደህንነታቸው ተስፋ ያለው የጌታ ድምፅ ወደ አዕምሮው መጣ—ኔፋውያን ላማናውያንን ለመመለስ ጣሩ—ኢኖስ በቤዛው ይደሰታል። ከ፬፻፳ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እነሆ፣ እንዲህ ሆነ እኔ ኢኖስ አባቴ ፃድቅ ሰው እንደነበር ስለማውቅ—በራሱም ቋንቋ እናም ደግሞ በጌታ አስተዳደግና ተግሳፅ ስላስተማረኝ፣ እናም ለዚህ የአምላኬ ስም የተባረከ ይሁን—
፪ እናም ለኃጢአቴ ስርየትን ከማግኘቴ በፊት በእግዚአብሔር ፊት ስለነበረኝ ትግል እነግራችኋለሁ።
፫ እነሆ፣ አራዊትን ለማደን ወደጫካው ሄድኩ፤ እናም አባቴ ዘለዓለማዊ ህይወትንና የቅዱሳንን ደስታ በተመለከተ ሁልጊዜ ሲናገር የምሰማቸው ቃላት ወደልቤ ጠልቀው ገቡ።
፬ እናም ነፍሴ ተራበች፤ በፈጣሪዬም ፊት ተንበረከክሁ፣ እናም ለነፍሴ በሀይለኛ ፀሎትና ልመና ወደእርሱ ጮህኩኝ፣ እናም ቀኑን ሙሉ ወደ እርሱ ጮህኩኝ፤ አዎን፣ ምሽቱ ሲመጣ ድምፄን ሰማይ እስከሚደርስ ከፍ አደረግሁት።
፭ እናም ድምፅ ወደእኔ መጣ፣ እንዲህም አለኝ፥ ኢኖስ ኃጢያትህ ይቅር ተብሎልሃል እናም አንተ ትባረካለህ።
፮ እናም እኔ ኢኖስ እግዚአብሔር ሊዋሽ እንደማይችል አውቃለሁ፤ ስለሆነም፣ በደሌ ተወግዶልኛል።
፯ እናም ጌታ፣ ይህ እንዴት ሆነ? አልኩት።
፰ እናም እርሱም አለኝ፥ ባላየኸውና ሰምተህ በማታውቀው በክርስቶስ ባለህ እምነት ምክንያት ነው። እናም እራሱን በአካል ከመግለፁ በፊት ብዙ አመታት ያልፋሉ፤ ስለሆነም፣ ሂድ እምነትህ አድኖሃል።
፱ አሁን፣ እንዲህ ሆነ እነዚህን ቃላት በምሰማ ጊዜ ለኔፋውያን ወንድሞቼ ደህንነት ማሰብ ጀመርኩ፤ ስለሆነም፣ ለእነርሱ ነፍሴን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር አፈሰስኩ።
፲ እናም እንደዚህ በመንፈስ በምታገልበት ጊዜ፣ እነሆ፣ የጌታ ድምፅ በአዕምሮዬ በድጋሚ መጥቶ እንዲህ አለኝ፤ ወንድሞችህ ትዕዛዛቴን ለመጠበቅ ባላቸው ትጋት መሰረት እጎበኛቸዋለሁ። ለእነርሱም ይህን ምድር ሰጥቻቸዋለሁ፣ ይህችም ቅዱስ ምድር ናት፤ በክፋት የተነሳ ካልሆነ በቀር አልረግማትም፤ ስለሆነም፣ በተናገርኩት መሰረት ወንድሞችህን እጎበኛቸዋለሁ፤ እናም መተላለፋቸውን በራሳቸው ላይ በሀዘን አወርዳለሁ።
፲፩ እናም እኔ ኢኖስ፣ እነዚህን ቃላት ከሰማሁ በኋላ እምነቴ በጌታ የማይናወጥ ሆነ፤ እናም ለወንድሞቼ ላማናውያን በብዙ ረጅም ትግል ወደ እርሱ ፀለይኩ።
፲፪ እናም እንዲህ ሆነ ባለኝ በሙሉ ትጋት ከሰራሁና ከፀለይኩ በኋላ፣ ጌታም አለኝ፥ በእምነትህ የተነሳ እንደተመኘኸው መሰረት እሰጥሀለሁ።
፲፫ እናም አሁን እነሆ፣ ከእርሱ የፈለግሁት ፍላጎት ይህ ነበር—የእኔ ህዝብ ኔፋውያን በመተላለፋቸው መውደቅ ካለባቸውና በምንም አይነት መጥፋትም ቢኖርባቸው፣ ላማናውያንም መጥፋት ከሌለባቸው፣ ጌታ አምላክ የህዝቤን የኔፋውያን ታሪክ እንዲጠብቅ ዘንድ፤ እንዲሁም፣ በቅዱስ ክንዱ ኃይልም እንኳን ቢሆን፣ ይህም ወደፊት አንድ ቀን ለላማናውያን ይመጡ ዘንድ፣ ምናልባት ወደ ደህንነት ይመጡ ዘንድ—
፲፬ ለጊዜው እነርሱን ወደ እውነተኛው እምነት የመመለሱ ትግል ከንቱ ነበር። እናም ታሪካችንና እኛን፣ ደግሞም የአባቶቻችንን ባህል ሁሉ የሚቻላቸው ከሆነ ያጠፉ ዘንድ በቁጣቸው ማሉ።
፲፭ ስለሆነም፣ ጌታ እግዚአብሔር ታሪካችንን ማስቀመጥ እንደሚቻለው ስለማውቅ፣ ያለማቋረጥ ወደ እርሱ ጮህኩኝ፣ እርሱም እንዲህ ብሎኛልና፥ በክርስቶስ ስም እንደምትቀበል ካመንህ ምንም ነገር በእምነት ብትጠይቅ ትቀበላለህ።
፲፮ እናም እኔ እምነት ነበረኝ፣ እናም መዝገቦቹን እንዲያስቀምጥ ወደ እግዚአብሔር ጮህኩ፤ በእርሱ ዘመን ለላማናውያን እንደሚያመጣውም ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባ።
፲፯ እናም እኔ ኢኖስ፣ በገባው ቃል ኪዳን መሰረት እንደሚሆን አውቃለሁ፤ ስለዚህ ነፍሴም እረፍትን አገኘች።
፲፰ እናም ጌታ አለኝ፥ አባቶችህም ደግሞ ስለዚህ ነገር ከእኔ ይፈልጉ ነበር፤ እናም ለእነርሱ እንደእምነታቸው ይደረግላቸዋል፤ እምነታቸው ልክ እንደአንተው ነበርና።
፲፱ እናም አሁን እንዲህ ሆነ እኔ ኢኖስ፣ የሚመጡትን ነገሮች በመተንበይ በኔፋውያን ህዝብ መካከል ተጓዝኩ፣ እናም የሰማኋቸውንና ያየኋቸውን ነገሮች መሰከርኩ።
፳ እናም የኔፊ ህዝብ ላማናውያንን ወደ እውነተኛው የእግዚአብሔር እምነት እንዲመልሱ በትጋት እንደሚመክሩ እመሰክራለሁ። ነገር ግን ስራችን ከንቱ ነበር፤ ጥላቻቸው የፀና ነበር፣ እናም በመጥፎ ተፈጥሮአቸው ተመርተው ስለነበር አረመኔ፣ አስፈሪም፣ ደም የተጠማ ህዝብና፣ ጣኦትን አምላኪና ርኩሳን ሆኑ፤ የታደኑ አውሬዎችን በመመገብ፤ በድንኳን መኖርና፣ በምድረበዳ ውስጥ አጭር የቆዳ ግልድም አገልድመው እራሳቸውን ተላጭተው ተዘዋወሩ፤ እናም ችሎታቸውም ስለቀስትና ደጋን እንዲሁም ምሳር ነበር። እናም ብዙዎች ከጥሬ ስጋ በስተቀር ምንም አይበሉም ነበር፤ እናም እነሱ ያለማቋረጥ እኛን ለማጥፋት ይፈለጉ ነበር።
፳፩ እናም እንዲህ ሆነ የኔፊ ህዝብ መሬትን ያርሱ ነበር፣ እናም ሁሉንም አይነት እህልና ፍራፍሬ ያበቅሉ፣ የከብት መንጋዎችን፣ ከሁሉም የከብት አይነት መንጋዎችን፣ ፍየሎችን፣ የሜዳ ፍየሎችን፣ እናም ደግሞ ብዙ ፈረሶችን ያረቡ ነበር።
፳፪ እናም ከእኛ መካከል እጅግ ብዙ ነቢያት ነበሩ። እናም ህዝቡ ለመረዳት የሚያስቸግር አንገተ ደንዳና ነበር።
፳፫ እናም እጅግ አስከፊ ከሆነው የጦርነት ሰበካና ትንቢት፣ እናም ፀብና ጥፋት፣ እንዲሁም ያለማቋረጥ ሞትን ከሚያስታውሳቸውና፣ ከዘለዓለማዊ ጊዜ፣ ፍርድና ከእግዚአብሔር ኃይል፣ በጌታ ፍርሃት ያለማቋረጥም ይጠበቁ ዘንድ ካነሳሳቸው በስተቀር ምንም የለም። ከእነዚህ ነገሮችና እጅግ ታላቅ የሆነው ግልፅ ንግግር በስተቀር ወደ ጥፋት በፍጥነት ከመሄድ የሚጠብቃቸው ምንም ነገር አልነበረም እላለሁ። እናም በእንደዚህ አይነት እነሱን በተመለከተ እፅፋለሁ።
፳፬ እናም በጊዜዬ በኔፋውያንና በላማናውያን መካከል ጦርነቶችን ተመልክቻለሁ።
፳፭ እናም እንዲህ ሆነ እየሸመገልኩ ሄድኩ፣ እናም አባታችን ሌሂ ኢየሩሳሌምን ለቆ ከወጣ አንድ መቶ ሰባ ዘጠኝ አመታት አለፉ።
፳፮ እናም በእግዚአብሔር ኃይል ለዚህ ህዝብ መስበክና እንድተነብይ፣ እናም በክርስቶስ ባለው እውነት መሰረት ቃሉን እንድናገር እንደተገፋፋሁ በቶሎ ወደ መቃብሬ መሄድ እንዳለብኝ ተመለከትኩ። እናም በዘመኔ ሁሉ ተናግሬዋለሁ፣ በዚህም ከዓለም በላይ ተደስቼበታለሁ።
፳፯ እናም ከቤዛዬ ጋር ወደሆነው ማረፊያዬ በቶሎ እሄዳለሁ፤ በእርሱ እንደማርፍ አውቃለሁና። እናም የሚሞተው የማይሞተውን በሚተካበትና፣ በእርሱ ፊት በምቆምበት ቀን እደሰታለሁ፤ ከእዚያም ፊቱንም በደስታ አያለሁ፣ እርሱም ይለኛል፥ የተባረከው ወደ እኔ ና፣ በአባቴም ቤት የተዘጋጀልህ ቦታ አለ። አሜን።