ምዕራፍ ፳፪
እስራኤላውያን በምድር ሁሉ ገፅ ላይ ይበተናሉ—በመጨረሻው ቀናት አህዛብ እስራኤላውያንን በወንጌል ያጠቧቸዋልም ይመግቧቸዋልም—እስራኤላውያን ይሰበሰባሉ፣ ይድናሉም እናም ኃጢአተኞች እንደአገዳ ይነዳሉ—የዲያብሎስ መንግስት ይጠፋል፣ እንዲሁም ሰይጣን ይታሰራል። ከ፭፻፹፰–፭፻፸ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም አሁን እንዲህ ሆነ፣ እኔ ኔፊ በነሀስ ሰሌዳዎች ላይ የተፃፉትን ነገሮች ካነበብኩ በኋላ ወንድሞቼ ወደ እኔ መጡና እንዲህ አሉኝ—እነዚህ ያነበብካቸው ነገሮች ምን ማለታቸው ነው? እነሆ እንደስጋ ሳይሆን በመንፈስ እንደሚሆኑት ነገሮች መሰረት መገንዘብ የሚቻሉ ናቸው?
፪ እናም እኔ፣ ኔፊ፣ እንዲህ ስል ተናገርኳቸው—እነሆ እነርሱ በመንፈሱ ድምፅ ለነቢዩ ተገልፀዋል፤ ለሰዎች ልጆች በስጋ መሰረት የሚመጡት ሁሉም ነገሮች ለነቢያት በመንፈስ እንዲያውቁት ይደረጋሉና።
፫ ስለዚህ ያነበብኳቸው ነገሮች ከጊዜያዊና መንፈሳዊ ነገሮች ጋር የተገናኙ ናቸው፤ የእስራኤል ቤት በቅርቡ ወይም በኋላ፣ በምድር ገፅ ላይ ሁሉ እናም ደግሞ በሁሉም ሀገሮች መካከል ሲበተኑ ይታያል።
፬ እናም እነሆ በኢየሩሳሌም ውስጥ ካሉት እውቀት ብዙዎቹ ጠፍተዋል። አዎን ከሁሉም ነገዶች ብዙዎች ተሰደዋል፤ እናም በባህሩ ደሴቶች ላይ ወዲህና ወዲያ ተበትነዋል፤ እንዲሁም የት እንዳሉ ማናችንም አናውቅም፣ ነገር ግን ሁላችንም የምናውቀው እነርሱ መሰደዳቸውን ነው።
፭ እናም ስለተሰደዱ፣ እነርሱን በተመለከተና ደግሞ በእስራኤል ቅዱስ ምክንያት ከእዚህ በኋላ ለሚበተኑትና ከሌሎች ሀገሮች ጋር የሚቀላቀሉትን በተመለከተ እነዚህ ነገሮች ተተንብየዋል፤ ምክንያቱም በእርሱ ላይ ልባቸውን ያጠጥራሉና፤ ስለዚህ በሁሉም ህዝቦች መካከል ይበተናሉ፣ እንዲሁም በሁሉም ህዝቦች ይጠላሉ።
፮ ይሁን እንጂ፣ በኋላም በአህዛብ ያጠቧቸዋል፣ እና ጌታ በአህዛብ ላይ እጁን ያነሳል፤ እንደአርማም ያቆማቸዋል፤ ልጆቻቸውንም በክንዶቻቸው ላይ ይሸከሟቸዋል፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም በትከሻቸው ይሸከማሉ፣ እነሆ የተነገሩት እነዚህ ነገሮች ጊዜያዊ ናቸው፤ ጌታ ከአባቶቻችን ጋር የገባቸው ኪዳን እንደዚህም ናቸውና፤ እናም ይህም በሚመጣው ጊዜ እኛንና፣ ደግሞም የእስራኤል ቤት የሆኑት ወንድሞቻችንን ሁሉ ያመለክታል።
፯ እናም ይህ ሁሉም የእስራኤል ቤት ከተበተኑና ከተቀላቀሉ በኋላ፣ አዎን ጌታ እግዚአብሔርም በዚህች ምድር ገፅ ላይ በአህዛብ መካከል ኃያል ህዝብን የሚያስነሳበት ጊዜ ይመጣል፤ እና በእነርሱም ዘሮቻችን ይበተናሉ ማለት ነው።
፰ እናም ዘሮቻችን ከተበተኑ በኋላ ጌታ እግዚአብሔር በአህዛብ መካከል ለዘሮቻችን ታላቅ ጥቅም የሚሆኑ ድንቅ ስራ መስራቱን ይቀጥላል፤ ስለዚህ ይህም በአህዛብ እንደተጠበቁና በክንዶቻቸውና በትከሻቸው እንደተሸከሟቸው ጋር ተመሳስሏል።
፱ እናም ይህ ደግሞ ለአህዛብ ጥቅም ይኖረዋል፣ እናም ለአህዛብ ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ለእስራኤል ቤት ሁሉና፣ በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ በማለት የሰማይ አባት ከአብርሃም ጋር የገባው ቃልኪዳኖች ለማሳወቅ ነው።
፲ እናም ወንድሞቼ ጌታ ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ካልገለጠ በስተቀር የምድር ወገኖች ሁሉ መባረክ እንደማይችሉ እንድታውቁ እፈልጋለሁ።
፲፩ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር ቃልኪዳኑን እና ወንጌሉን በእስራኤል ቤት ውስጥ ላሉት በመስጠት ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት መግለጥን ይቀጥላል።
፲፪ ስለዚህ ከምርኮ እንደገና ያወጣቸዋል፣ እናም በአንድ ላይ በርስት ምድራቸው ላይ ይሰበሰባሉ፤ ከጨለማና ከጭጋግም ይወጣሉ፤ እናም ጌታ አዳኛቸውና ቤዛቸው የእስራኤልም ኃያል መሆኑን ያውቃሉ።
፲፫ እናም የምድር ሁሉ ጋለሞታ የሆነችው ታላቋና የርኩሰት ቤተክርስቲያን ደም በእራሳቸው ላይ ይመለሳል፤ ምክንያቱም በመካከላቸው ጦርነት ይሆናል፣ እና በእጆቻቸው ያሉ ጎራዴዎቻቸውም በራሳቸው ላይ ይወድቃሉ፣ በራሳቸውም ደም ይሰክራሉ።
፲፬ እናም የእስራኤል ቤት ሆይ፣ በአንቺ ላይ ለጦርነት የሚነሳ እይስንዳንዱ ሀገር እርስ በራስ ይቃወማሉ፣ እናም እነርሱ የጌታን ህዝቦች ለማጥመድ በቆፈሩት ጉድጓድ ይወድቃሉ። እናም ፅዮንን የሚዋጉ ሁሉ ይጠፋሉ፣ ትክክለኛውን የጌታን መንገድ የምታስተው ታላቋ ጋለሞታም፤ አዎን ታላቋና የርኩሰት ቤተክርስቲያን ወደ አፈር ትወድቃለች፤ እንዲሁም ውድቀቷ ታላቅ ይሆናል።
፲፭ እነሆም ሰይጣን በሰዎች ልጆች ልብ ላይ ኃይል የሚያጣበት ጊዜ በፍጥነት ይመጣል ብሎ ነቢዩ ተናግሯል፤ የሚኮሩ እና ኃጢያትን የሚሰሩ ሁሉ እንደ አገዳ የሚሆኑበት ጊዜ ቀኑ በቅርቡ ይመጣልና፤ እና መቃጠል የሚገባቸው ጊዜም ይመጣል።
፲፮ በሰዎች ልጆች ላይ ሁሉ የእግዚአብሔር ቁጣ የሚወርድበት ጊዜ በቅርቡ ይመጣል፤ ምክንያቱም ኃጢአተኞች ፃድቃኖችን እንዲያጠፉ እርሱ አይፈቅድምና።
፲፯ ስለዚህ እርሱ በኃይሉ ፃድቃንን ይጠብቃል፣ ምንም እንኳን የቁጣው ሙላት መምጣት ቢኖርበትም እናም ጠላቶቻቸውን እንኳ በእሳት እስከማጥፋት ድረስ ፃድቃኖች ይጠበቃሉ። ስለዚህ ፃድቃኖች መፍራት የለባቸውም፤ ምክንያቱም ከእሳትም እንኳን ቢሆን ይድናሉ ብሎ ነቢዩ ተናግሯልና።
፲፰ እነሆ ወንድሞቼ፣ እነዚህ ነገሮች በቅርቡ መሆን አለባቸው እላችኋለሁ፤ አዎን ደምና እሳት፣ እንዲሁም የጭስ ጭጋግ እንኳን መምጣት አለባቸው፤ እናም ይህ በዚህች ምድር ገፅ ላይ መሆን አለበት፤ እናም እነርሱ በእስራኤል ቅዱስ ላይ ልባቸውን ካጠጠሩ ይህም ለሰዎች በስጋ መሰረት ይመጣል።
፲፱ እነሆ ፃድቃኖች አይጠፉም፤ ከፅዮን ጋር የሚዋጉ የሚጠፉበት ጊዜ በእርግጥ መምጣት አለበት።
፳ እናም ሙሴ፥ ጌታ የእናንተ አምላክ እኔን አይነት አንድ ነቢይ በመካከላችሁ ያስነሳል፤ ለእናንተ በሚናገራችሁ በሁሉም ነገሮች እናንተ ስሙት ብሎ የተናገራቸው ቃላት ይሟሉ ዘንድ፣ በእርግጥ ጌታ ለህዝቡ መንገድን ያዘጋጃል። እናም እንዲህ ይሆናል ያንን ነቢይ የማይሰማ ከህዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል።
፳፩ እናም አሁን እኔ ኔፊ እናንተን የምናገራችሁ ይህ ሙሴ ስለእርሱ የተናገረለት ነቢይ የእስራኤል ቅዱስ ነው፤ ስለዚህ እርሱ በፅድቅ ይፈርዳል።
፳፪ እናም ፃድቃን መፍራት የለባቸውም፣ ምክንያቱም እነርሱ የሚደባለቁ አይደሉምና። ነገር ግን ይህ በሰዎች ልጆች መካከል የተመሰረተው የዲያብሎስ መንግስት ነው፣ መንግስቱም በስጋ በተሸፈኑት መካከል የተመሰረተው ነው—
፳፫ ሀብትን ለማግኘት የተመሰረቱት ቤተክርስቲያኖች ሁሉ፣ የስጋ ኃይልን ለማግኘት የተመሰረቱት ሁሉ፣ እናም በዓለም ዐይናት ታዋቂ ለመሆን የተመሰረቱትና፣ የስጋቸውን ፍላጎት ለማርካትና የዓለምን ነገሮች ለሚሹ፣ እንዲሁም ሁሉንም አይነት ኃጢያት ለማድረግ ለሚሹ ጊዜው በፍጥነት ይመጣል፤ አዎን በአጠቃላይ በዲያብሎስ መንግስት አባል የሆኑት ሁሉ ሊፈሩ፣ ሊንቀጠቀጡና ሊናወጡ ይገባቸዋል፤ እነርሱም መዋረድ ያለባቸው ናቸው፣ እነርሱም እንደአገዳ መንደድ ያለባቸው ናቸው፣ እናም ይህ እንደነቢዩ ቃላት ነው።
፳፬ እናም ፃድቃኖች እንደሰባ እምቦሳ የሚመሩበትና፣ የእስራኤል ቅዱስ በበላይነት በስልጣንና በኃይል፣ እንዲሁም በታላቅ ክብር የሚነግስበት ጊዜ በፍጥነት ይመጣል።
፳፭ እናም እርሱ ልጆቹን ከአራቱም የምድር ማዕዘናት ይሰበስባል፤ እናም በጎቹንም ይቆጥራል፣ እነርሱም ያውቁታል፤ እናም አንድ መንጋና አንድ እረኛ ይሆናሉ፤ እርሱም በጎቹን ይመግባል፣ እነርሱም በእርሱ ሰማሪያ ያገኛሉ።
፳፮ እናም በህዝቦቹ ፅድቅ ምክንያት ሰይጣን ኃይል የለውም፤ ስለዚህ ለብዙ ዓመታት ሊፈታ አይችልም፤ ምክንያቱም እርሱ በሰዎች ልብ ላይ ስልጣን የለውም፣ እነርሱ በፅድቅ ይኖራሉ፣ እናም የእስራኤል ቅዱስ ይነግሳልና።
፳፯ እናም አሁን እኔ ኔፊ እንዲህ እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በስጋ መምጣት አለባቸው።
፳፰ ነገር ግን እነሆ ሁሉም ሀገሮች፣ ነገዶች፣ ቋንቋዎችና፣ ህዝቦች ንስሀ ከገቡ ከእስራኤል ቅዱስ ጋር በደህንነት ይኖራሉ።
፳፱ እናም አሁን እኔ ኔፊ አቆማለሁ፤ ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች በተመለከተ አሁን ከዚህ የበለጠ ለማለት አልደፍርም።
፴ ስለዚህ ወንድሞቼ በነሀስ ሰሌዳዎቹ ላይ የተፃፉት ነገሮች እውነት እንደሆኑ እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤ እናም እነርሱ ሁሉም ሰው ለእግዚአብሔር ትዕዛዛት ታዛዥ መሆን እንዳለበት ይመሰክራሉ።
፴፩ ስለዚህ እናንተ እኔና አባቴ ብቻ ይህንን የመሰከርን፣ እናም ደግሞ ስለ እነርሱ ያስተማርን ነን በማለት ማሰብ የለባችሁም። ስለዚህ እናንተ ለትዕዛዛቱ ታዛዥ ከሆናችሁና እስከመጨረሻው ከፀናችሁ በመጨረሻው ቀን ትድናላችሁ። እናም እንዲህም ነው። አሜን።