ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፭


ምዕራፍ ፭

ኔፋውያን እራሳቸውን ከላማናውያን ለዩ፣ የሙሴን ህግ ጠበቁ፣ እናም ቤተመቅደስ ሰሩ—ላማናውያን ባለማመናቸው ከጌታ ፊት ተለዩ፣ ተረገሙ፣ እናም ለኔፋውያን እንደ ጅራፍ ሆኑ። ከ፭፻፹፰–፭፻፶፱ ም.ዓ. ገደማ።

እነሆ፣ እንዲህ ሆነ፣ እኔ ኔፊ፣ በወንድሞቼ ቁጣ የተነሳ ወደ ጌታ አምላኬ በጣም ጮህኩ።

ነገር ግን እነሆ፣ እነርሱ ህይወቴን ለማጥፋት እስከመፈለጋቸው ድረስ በእኔ ላይ ቁጣቸው በርትቶ ነበር።

አዎን፣ በእኔ ላይ እንዲህ ሲሉ አጉረመረሙ—ታናሽ ወንድማችን በእኛ ላይ ገዢ ለመሆን ያስባል፤ እናም እኛ በእርሱ ምክንያት ብዙ ችግር አጋጥሞናል፤ ስለዚህ፣ በእርሱ ቃል የተነሳ በተጨማሪ አንዳንሰቃይ አሁን እንግደለው። እነሆም እርሱ ገዢያችን እንዲሆን አንፈቅድም፤ ምክንያቱም ታላቅ ወንድሞቹ የሆንነው በዚህ ህዝብ ላይ መግዛት የሚገባን እኛ ነንና።

አሁን በእነዚህ ሰሌዳዎች ላይ በእኔ ላይ ያጉረመረሙትን ቃል ሁሉ አልፅፍም። ነገር ግን እነርሱ ህይወቴን ሊያጠፉ ፈልገዋል የሚለውን ብቻ ማለት ይበቃኛል።

እናም እንዲህ ሆነ፣ እኔ ኔፊ፣ እንዲሁም ከእኔ ጋር የሚሄዱት ሁሉ፣ ከእነርሱ መሸሽና ወደ ምድረበዳው መሄድ እንዳለብን ጌታ አስጠነቀቀኝ

ስለዚህም፣ እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ ቤተሰቤን፣ እናም ደግሞ ዞራምንና ቤተሰቡን፣ እናም ታላቅ ወንድሜን ሳምንና ቤተሰቦቹን፣ እናም ያዕቆብን እና ዮሴፍን፣ ታናናሽ ወንድሞቼን እናም ደግሞ እህቶቼን፣ እና ከእኔ ጋር የሚሄዱትን ሁሉ ወሰድኩ። እናም ከእኔ ጋር የሚሄዱት ሁሉ የእግዚአብሔርን ማስጠንቀቂያዎችንና ራዕይ ያመኑ ነበሩ፤ ስለዚህ፣ የእኔን ቃል አዳመጡ።

እናም ድንኳናችንንና ለመውሰድ የምንችለውን ማናቸውንም ነገሮች ወሰድንና፣ በምድረበዳ ውስጥ ለብዙ ቀናት ተጓዝን። እናም ለብዙ ቀናት ከተጓዝን በኋላ ድንኳኖቻችንን ተከልን።

እናም ህዝቤ የቦታውን ስም ኔፊ ብለን እንድንጠራው ፈለጉ፤ ስለዚህም ኔፊ ብለን ጠራነው።

እናም ከእኔ ጋር የነበሩ ሁሉ እራሳቸውን የኔፊ ህዝብ ብለው ለመጥራት ወሰኑ።

እናም በሁሉም ነገሮች ፍርዱን፣ ስርአቱንና፣ የጌታን ትዕዛዝ በሙሴ ህግ መሰረት በትጋት ለመጠበቅ ተቀበልን።

፲፩ ጌታም ከእኛ ጋር ነበር፣ እናም እጅግ በለፀግን፤ እህል ዘርተናል፣ እናም እንደገና በብዛት ሰብስበናልና። እናም የበግና የከብት መንጋንና ከሁሉም አይነት እንስሳት ማርባት ጀመርን።

፲፪ እናም ደግሞ እኔ ኔፊ በነሀስ ሰሌዳዎች ላይ የተቀረፁትን መዝገቦች፣ እናም ደግሞ እንደተፃፈው ለአባቴ በጌታ እጅ የተዘጋጀውን ኳስ ወይም ኮምፓሱን አመጣሁ።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ እኛ በይበልጥ መበልፀግ እንዲሁም በምድሪቱ ላይ መብዛት ጀመርን።

፲፬ እናም አሁን ላማናውያን ተብለው የሚጠሩት ህዝቦች በማንኛውም ሁኔታ እንዳይመጡብንና እኛን እንዳያጠፉን ዘንድ፣ እኔ ኔፊ፣ የላባንን ጎራዴ ወሰድኩና በእርሱ አይነት ብዙ ጎራዴዎችን ሰራሁ፤ ምክንያቱም እነርሱ ወደ እኔና ልጆቼ እናም ህዝቤ ተብለው ወደተጠሩት ያላቸውን ጥላቻ አውቃለሁና።

፲፭ እናም ህዝቤን በብዛት ከሁሉም አይነት እንጨትና ብረት፣ እናም መዳብና ነሀስ፣ እና ብረትና ወርቅ፣ እና ብርና ከከበሩ የብረት አፈር ህንፃ እንዲሰሩ አስተማርኳቸው።

፲፮ እናም እኔ ኔፊ ቤተመቅደስን ሰራሁ፤ ከብዙ ከከበሩ ነገሮች የተገነባ ባይሆንም፣ እንደ ሰለሞን ቤተመቅደስ አይነት ነበር የሰራሁት፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች በምድሪቱ ላይ አልተገኙም ነበርና፣ ስለዚህ፣ እንደ ሰለሞን አይነት ቤተመቅደስ መስራት አልተቻለም። ነገር ግን የቤተመቅደሱ አሰራር ከሰለሞን ቤተመቅደስ ጋር ተመሳሳይ ነበር፤ እናም አሰራሩ እጅግ ያማረ ነበር።

፲፯ እናም እንዲህ ሆነ፣ እኔ ኔፊ፣ ህዝቤ ታታሪ እንዲሆኑና በእጃቸውም እንዲሰሩ አደረግሁ።

፲፰ እናም እንዲህ ሆነ፣ እነርሱ እኔ ንጉሳቸው እንድሆን ፈለጉ። ነገር ግን እኔ ኔፊ፣ ለእነርሱ ንጉስ እንዲኖራቸው አልፈለግሁም፤ ይሁን እንጂ፣ በውስጤ ባለው ኃይል መሰረት ለእነርሱ አደረግሁ።

፲፱ እናም እነሆ፣ እኔ የእነርሱ ገዢና አስተማሪ እሆን ዘንድ ወንድሞቼን በተመለከተ ጌታ የተናገራቸው ቃላት ተፈፅመዋል። ስለዚህ፣ በጌታ ትዕዛዝ መሰረት እነርሱ ህይወቴን ለማጥፋት እስከሚያስቡበት ድረስ ገዢያቸውና አስተማሪያቸው ነበርኩኝ።

ስለሆነም፣ ጌታ እንዲህ ያለኝ ቃሉ ተፈፅሟል—እነርሱ የአንተን ቃል እስካላዳመጡ ድረስ ከጌታ ፊት ይለያሉ። እናም እነሆ፣ እነርሱ ከፊቱ ተለይተው ነበር።

፳፩ እናም እርሱ በኃጢአታቸው የተነሳ እርግማን፣ አዎን፣ እንዲያውም ከባድ እርግማን፣ በእነርሱ ላይ እንዲመጣ አድርጓል። እነሆም በእርሱ ላይ ልባቸውን አጠጠሩ፣ እንደ ድንጋይም ሆኑ፤ ስለዚህ፣ እነርሱ ነጭ እና ቆንጆ እንዲሁም ያማሩ ስለነበሩ ለህዝቤ የሚስቡ እንዳይሆኑ ጌታ እግዚአብሔር በቆዳቸው ላይ ጥቁረት እንዲመጣባቸው አደረገ።

፳፪ እናም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አለ—ለክፋቶቻቸው ንስሀ ካልገቡ በስተቀር ለህዝብህ የሚያስጠሉ እንዲሆኑ አደርጋቸዋለሁ።

፳፫ እናም ከእነርሱ ዘር ጋር የተቀላቀለው ዘር የተረገመ ይሆናል፤ እነርሱ በእንደዚህ አይነት እርግማን ይረገማሉ። እናም ጌታ ተናግሮታል፣ ይህም ተደርጓል።

፳፬ እናም በእነርሱ ላይ ባለው እርግማን የተነሳ ሰነፍ፣ አጭበርባሪዎችና በተንኮል የረቀቁ እንዲሁም በምድረበዳ ውስጥ አራዊቶችን የሚያድኑ ህዝቦች ሆነዋል።

፳፭ እናም ጌታ እግዚአብሔር አለኝ፥ እኔን ያስታውሱ ዘንድ ለማነሳሳት ለዘሮችህ እንደ ጅራፍ ይሆናሉ፤ እናም እኔን ካላስታወሱኝና፣ ቃሌንም ካላዳመጡ፣ እስከሚጠፉ ድረስ ይቀጧቸዋል።

፳፮ እናም እንዲህ ሆነ፣ እኔ ኔፊ፣ ያዕቆብንና፣ ዮሴፍን በህዝቤ ምድር ላይ ካህናትና መምህራን ይሆኑ ዘንድ ቀባኋቸው

፳፯ እናም እንዲህ ሆነ አስደሳች ህይወት ኖርን።

፳፰ እናም ኢየሩሳሌምን ለቀን ከወጣን ሠላሳ ዓመታት አለፉ።

፳፱ እናም እኔ ኔፊ፣ ህዝቤን በተመለከተ በሰራሁት በሰሌዳዎች ላይ እስከዚያ ያለውን ታሪክ ጽፌ ጠበቅሁ።

እናም እንዲህ ሆነ ጌታ እግዚአብሔር አለኝ፥ ሌሎች ሰሌዳዎችን ስራ፤ እናም ለህዝብህ ጥቅም በእኔ አመለካከት መልካም የሆኑትን ብዙ ነገሮች በእነዚህ ላይ ትፅፋለህ።

፴፩ ስለሆነም፣ እኔ ኔፊ፣ ለጌታ ትዕዛዛት ታዛዥ ለመሆን፣ ሄድኩ፣ እናም እነዚህን ነገሮች የፃፍኩበትን እነዚህን ሰሌዳዎች ሰራሁ።

፴፪ እናም እግዚአብሔርን የሚያስደስተውን ቀረፅኩኝ። እናም ህዝቤ በእግዚአብሔር ነገር የሚደሰት ከሆነ በእነዚህ ሰሌዳዎች ላይ እኔ በቀረፅኩት ይደሰታሉ።

፴፫ እናም ህዝቤ የህዝቤን ታሪክ በጥልቀት ለማወቅ ከፈለጉ፣ የእኔን ሌሎች ሰሌዳዎች ማጥናት አለባቸው።

፴፬ እናም አርባ ዓመታት ዓለፉ ማለት ለእኔ በቂ ነው፣ እናም ከወንድሞቻችን ጋር በጦርነትና ፀብ አሳልፈናል።