ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፴፫


ምዕራፍ ፴፫

የኔፊ ቃላት እውነት ናቸው—ስለክርስቶስ ይመሰክራሉ—በክርስቶስ የሚያምኑ በፍርድ ወንበር ፊት ምስክር ሆኖ በሚቆመው በኔፊ ቃላት ያምናሉ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን እኔ ኔፊ፣ በህዝቤ መካከል የተነገሩትን ትምህርቶች በሙሉ መፃፍ አልችልም፤ እንደመናገሬ አይነት በፅህፈት ጎበዝ አይደለሁም፤ ምክንያቱም ሰው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲናገር የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው ወደ ሰዎች ልጆች ልብ የሚያደርሰው።

ነገር ግን እነሆ፣ በቅዱስ መንፈስ ላይ ልባቸውን አጠጥረው በእነርሱ ውስጥ ቦታ የሌላቸው ብዙዎች አሉ፣ ስለዚህ እነርሱ የፃፉትንና ጠቃሚ አይደለም ብለው የገመቱአቸውን ብዙ ነገሮች ይጥላሉ።

ነገር ግን እኔ ኔፊ፣ መፃፍ ያለብኝን ፅፌአለሁ፣ እና ይህም በልዩ ለህዝቤ ታላቅ ዋጋ አለው ብዬ የምገምተው ነው። በእነርሱ የተነሳ ያለማቋረጥም በቀን እፀልያለሁ፣ እናም በሌሊት እምባዬ ትራሴን ያረጥባል፤ ወደ ጌታም በእምነት እጮሀለሁ፣ ጩኸቴንም እንደሚሰማ አውቃለሁ።

እናም ጌታ እግዚአብሔር ፀሎቴን ለህዝቤ ጥቅም እንደሚቀድሰው አውቃለሁ። እናም በድካም የፃፍኳቸው ቃላትም በእነርሱ ዘንድ ብርቱ ይሆናሉ፤ መልካምም ያደርጉ ዘንድ ያሳምናቸዋልና፤ ስለአባቶቻቸውም ያሳውቃቸዋል፤ ስለክርስቶስም ይናገራል፤ እናም ዘለዓለማዊ ህይወት በሆነው በእርሱ እንዲያምኑና፣ እስከመጨረሻውም እንዲፀኑ ያሳምናቸዋል።

እናም በእውነት በግልፅነት መሰረት፣ ስለኃጢያት በፅኑ በመቃወም ይናገራል፤ ስለዚህ፣ ከዲያብሎስ መንፈስ ካልሆነ በቀር እኔ በፃፍኩት ቃላት የሚናደድ ማንም ሰው አይኖርም።

በግልፅነት እደሰታለሁ፤ በእውነት እደሰታለሁ፣ በእኔ ኢየሱስ እደሰታለሁ፣ ነፍሴን ከሲኦል አድኗታልና

ለህዝቤ ልግስና፣ እናም በፍርድ ወንበር ብዙ እንከን የለሽ ነፍሳት እንደማገኝ በክርስቶስ ታላቅ እምነት አለኝ።

ለአይሁድ ልግስና አለኝ—አይሁድ እላለሁ፣ ምክንያቱም እኔ የመጣሁበትን ዘር ማለቴ ነው።

ለአህዛብም ደግሞ ልግስና አለኝ። ነገር ግን እነሆ፣ በክርስቶስ ካልታረቁ፣ እናም በጠባቡ በር ካልገቡ፣ እናም ወደ ህይወት በሚያመራው በቀጭኑ ጎዳና ካልተራመዱ፣ እናም እስከሙከራ ቀናቸውም መጨረሻ ድረስ በጎዳናው ጉዞአቸውን ካልቀጠሉ፣ በማናቸውም ላይ ተስፋ አላደርግም።

እናም አሁን፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እናም ደግሞ አይሁድና፣ በምድር ዳርቻ ያላችሁ ሁሉ፣ እነዚህን ቃላት አድምጡም፣ በክርስቶስም እመኑ፤ እንዲሁም በእነዚህ ቃላት የማታምኑ ከሆነ በክርስቶስ እመኑ። እናም በክርስቶስ የምታምኑ ከሆነ በእነዚህ ቃላት ታምናላችሁ፣ እነርሱ የክርስቶስ ቃላት ናቸውና፣ እነርሱንም ለእኔ ሰጠኝ፤ እናም ሰዎች ሁሉ መልካም እንዲሰሩ ያስተምራሉ

፲፩ እናም የክርስቶስ ቃላት ካልሆኑም ፍረዱ—በመጨረሻው ቀን የእርሱ ቃል መሆናቸውን ክርስቶስ በኃይልና በታላቅ ክብር ያሳያችኋል፤ እናም እኔና እናንተ በፍርድ ወንበር ፊት ለፊት እንቆማለን፤ እናም ምንም እንኳን ደካማ ብሆንም እነዚህን ነገሮች እንድፅፍ በእርሱ እንደታዘዝኩ ታውቃላችሁ።

፲፪ እናም ሁላችንም እንኳን ባንሆን ብዙዎቻችን በታላቁና በመጨረሻው ቀን በመንግስቱ እንድን ዘንድ በክርስቶስ ስም ለአብ እፀልያለሁ።

፲፫ እናም አሁን፣ የእስራኤል ቤት ሁሉ የሆናችሁ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እናም በምድር ዳርቻ ያላችሁ ሁሉ፣ ከመሬት እንደሚጮህ ድምፅ እናገራችኋለሁ፥ ያ ታላቁ ቀን እስኪመጣ መልካም ይሁንላችሁ።

፲፬ እናም ከእግዚአብሔር ቸርነት የማትካፈሉ፣ እናም የአይሁዶችንም ቃላት፣ ደግሞም የእኔን ቃላት፣ እንዲሁም ከእግዚአብሔር በግ አፍ የሚወጣውን ቃል የማታከብሩ፣ እነሆ፣ ዘለዓለማዊ ስንብት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ቃላት በመጨረሻው ቀን ይኮንኗችኋልና

፲፭ በምድር ያተምሁት፣ በፍርድ ወንበር በእናንተ ላይ ይቀርባል፤ ጌታ እንዲህ አዞኛልና፣ መታዘዝ አለብኝ። አሜን።