2010–2019 (እ.አ.አ)
ጥንቃቄ እና ቸልተኝነት
የሚያዝያ 2019 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


ጥንቃቄ እና ቸልተኝነት

የዓለም ተጽዕኖዎች ይበልጥ ክፋትን እያካተቱ በመሄዳቸው፣ ወደአዳኛችን በሰላም በሚመራን መንገድ ላይ በጽናት ለመቀጠል ያላሰለሰ ጥረት ለማድረግ በብርቱ መታገል አለብን።

በአንድ ወቅት “ደስታ በ15 ብር“ የሚል ጽሁፍ የተለጠፈበት አንድ መደብር ተመለከትኩ። በ15 ብር ምን ያህል ደስታ መግዛት እችል እንደሆነ ለማወቅ ስለጓጓሁ ለማየት ወደውስጥ ገባሁ። ያገኘሁት ነገር ቢኖር ብዛት ያላቸው ርካሽ ጌጣጌጦችን እና ማስታወሻዎችን ነበር—ጽሁፉ የሚያመላክተውን የደስታ አይነት ሊያስገኝ የሚችል አንድም ነገር አላየሁም ነበር። በአመታት ውስጥ ስለዚያ ምልክት እና ርካሽ እና ጊዜያዊ በሆኑ ቁሳቁስ ውስጥ ደስታን መፈለግ እንዴት ቀላል ሊሆን እንደሚችል ብዙ ጊዜ አስቤአለሁ። እንደ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት፣ እንዴት እና መቼ እውነተኛ ደስታን እንደምናገኝ በማወቅ ተባርከናል። የሚገኘውም በጌታችን እና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተቋቋመውን ወንጌል በጥንቃቄ በመኖር እና ይበልጥ እንደእርሱ ለመሆን በመጣር ነው።

የባቡር መሃንዲስ የሆነ አንድ ውድ ጓደኛ አለን። አንድ ቀን በመንገዱ ላይ ባቡር እየነዳ በነበረበት ጊዜ ከፊት ለፊቱ በሃዲዱ ላይ የቆመ መኪና ተመለከተ። መኪናው መንቀሳቀስ አለመቻሉን እና ሃዲዱን ለማቋረጥም በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ እንደነበረ በፍጥነት ተገነዘበ። በፍጥነትም ባቡሩን ወደ ድንገተኛ ሁኔታ ውስጥ አስገባው ይህም ከሞተሩ ወደኋላ ሶስተኛ ማይል (1.2 ኪ.ሜ) በሚረዝሙት እና 6500 ቶን (5,900 ሜትር ቶን) በተሸከሙት በእያንዳንዱ ፉርጎዎች ላይ ያሉትን የባቡሩን ፍሬኖች እንዲይዙ አደረጋቸው። ባቡሩ መኪናውን ከመግጨቱ በፊት ሊቆም የሚችልበት እድል አልነበረም፤ እናም የሆነውም ይኸው ነበር። እንደ እድል ሆኖ፣ መኪናው ውስጥ የነበሩት ሰዎች የባቡሩን የማስጠንቀቂያ ፊሽካ ሰምተው ከመገጨታቸው በፊት ከመኪናው ውስጥ ወጡ። መሃንዲሱ ከመርማሪ ፖሊስ መኮንኑ ጋር እየተነጋገረ እያለ አንዲት የተናደደች ሴት ቀረበቻቸው። ሁሉንም ክስተቶች አይታ እንደነበር እየጮኸች ተናገረች እንዲሁም መሃንዲሱ መኪናውን ላለመግጨት መስመሩን ለመቀየር እንኳን ሙከራ እንዳላደረገ መሰከረች።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መሃንዲሱ አደጋን ለማስቀረት መንገዱን መቀየር እና ሃዲዱን መለወጥ ችሎ ቢሆን ኖሮ እሱ እና መላ ባቡሩ ሃዲድን የመሳት አደጋ ላይ ይወድቁ ነበር፣ እንዲሁም የባቡሩ የወደፊት ግስጋሴ በቅጽበት ሊቆም ይችል ነበር። እድሉ ሆኖ፣ ባቡሩ ሲሄድባቸው የነበሩት የሃዲዶቹ መደገፊያዎች የባቡሩን ጎማዎች በምቹ ሁኔታ በመያዝ በመንገዱ ላይ ምንም አይነት እንቅፋት ቢገጥመውም በፍጥነት ወደመድረሻቸው እንዲሄዱ አድርጓቸዋል። ለእኛም እንደ እድል ሆኖ፣ እኛም ተጠምቀን የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል ስንሆን በገባነው የቃል ኪዳን መንገድ ሃዲድ ላይ ነን። ምንም እንኳን በመንገዱ ላይ አልፎ አልፎ እንቅፋቶች ሊያጋጥሙን ቢችሉም፣ ይህ መንገድ ጸንተን ከቆየንበት ወደ ውድ ዘለአለማዊ ፍጻሜአችን እንድንጓዝ ያደርገናል።

የሌሂ የህይወት ዛፍ ራዕይ

የቸልተኝነት ውጤቶች ከቃል ኪዳኑ መንገድ እንዴት እንደሚያርቁን የህይወት ዛፍ ራዕይ ያሳየናል። የብረት ዘንጉን እና የጠበበውን እና ቀጭኑን መንገድ ወይም በአዳኛችን እና በኃጢያት ክፍያው አማካኝነት ለታማኞቹ ወደተዘጋጀው ወደ ህይወት ዛፍ የሚመራውን የቃል ኪዳኑን መንገድ አስቡ። በራዕዩ ውስጥ የአለምን ቆሻሻነት የሚወክል የወንዝ ውሃም ታይቶ ነበር። የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅሶችም ይህ ወንዝ በመንገዱ ትይዩ “ይወርድ” እንደነበር ሆኖም ወደ ዛፉ ሳይሆን “በአቅራቢያው” ብቻ እንደሚያልፍ ይገልጻሉ። ቃል ኪዳናቸውን በመኖር ረገድ ቸልተኞች እንዲሆኑ እያደረገ፣ ይህ አለም ምርጦቹን እንኳን ሊያታልሉ በሚችሉ ትኩረት ወሳጅ ነገሮች ተሞልቷል—በዚህም ወደ ዛፉ ሳይሆን ወደ አቅራቢያው ይመራቸዋል። ቃል ኪዳኖቻችንን በትክክል ለመኖር ጥንቃቄ ካላደረግን የቸልተኝነት ድርጊቶቻችን በመጨረሻ ወደተከለከሉ መንገዶች ሊመሩን ወይም ወደትልቁ እና ሰፊው ህንጻ ቀድመው ከገቡት ጋር እንድንቀላቀል ሊያድርጉን ይችላሉ። ጥንቃቄ ካላደረግን፣ በጥልቅ ቆሻሻ ወንዝ ውስጥ ልንሰምጥም እንኳን እንችላለን።1

ወንጌልን መኖርን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ለማድረግ የጥንቃቄ እና የቸልተኝነት መንገድ አለ። ለአዳኙ ያለንን ቁርጠኝነት ስናስብ ጠንቃቃ ነን ወይስ ቸልተኛ? በስጋዊ ተፈጥሮአችን ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ድርጊታችንን በግራጫው ውስጥ እንደሆንን በመጥቀስ ወይም ጥሩ ካልሆነ ጥሩ ነገርን ጥሩ ካልሆነ ጋር በማደባለቅ ባህሪያችንን አንዳንድ ጊዜ ምክንያታዊ ማረጋገጫ እናቀርባለን። በማንኛውም ጊዜ፣ የነቢያት መሪዎቻችንን ስለመከተል ወይም ወንጌልን በጥንቃቄ ስለመኖር የሚሰጠንን ምክር “ሆኖም፣” “ከ… በስተቀር፣” ወይም “ነገር ግን“ የምንል ከሆነ፣ በእርግጥ “ይህ ምክር በእኔ ላይ አይሰራም” እያልን ነው። ለምንፈልገው ነገር ሁሉ ምክንያታዊነቱን ማሳየት እንችላለን፣ እውነታው ግን የተሳሳተን ነገር የማድረግ ትክክለኛ መንገድ የለም!

የ2019 (እ.አ.አ) የወጣቶች ጭብጥ ጌታ “ብትወዱኝ ትዕዛዜን ጠብቁ“ ብሎ ከሚያስተምርበት ከዮሐንስ 14፥15 የተወሰደ ነበር። የምንናገረውን ያህል የምንወደው ከሆነ፣ ትዕዛዛቱን በመጠበቅ ረገድ ይበልጥ ጠንቃቃ በመሆን ፍቅሩን ማሳየት አንችልምን?

በወንጌል ውስጥ በመኖር ረገድ ጠንቃቃ መሆን ማለት የግድ መደበኛ ወይም ግትር መሆን ማለት አይደለም። ያም ማለት እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርነታችን በአስተሳሰባችን እና በባህርያችን የተገባ መሆን ማለት ነው። በጠንቃቃ እና በቸልተኛ ወንጌል አኗኗራችን መካከል ያለውን ልዩነት ስናሰላስል ከግምት ውስጥ የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች እነሆ፥

በየሳምንቱ በሰንበት ቀን አከባበራችን እና ቅዱስ ቁርባንን ለመካፈል በምናደርገው ዝግጅት ጠንቃቆች ነን?

በጸሎቶቻችን እና በቅዱስ መጻህፍት ጥናታችን ይበልጥ ጠንቃቃ ለመሆን ወይም በ ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች ጥናት ይበልጥ በንቃት ተሳታፊ መሆን እንችላለን?

በቤተመቅደስ አምልኳችን፣ እንዲሁም በጥምቀት እና በቤተመቅደስ የገባናቸውን ቃል ኪዳኖች በጥንቃቄ እና አስበንበት በመተግበር ረገድ ጠንቃቆች ነን? በአቀራረባችንም ሆነ በአለባበሳችን ረገድ ጠንቃቆች ነን፣ በተለይ በተቀደሱ ቦታዎች እና ሁኔታዎች ላይ? የተቀደሱ የቤተመቅደስ ልብሶችን በምናደርገው አለባበስ ረገድ ጠንቃቆች ነን? ወይንስ የአለም ፋሽኖች ይበልጥ ቸልተኛ ዝንባሌ እንዲኖረን ያደርጉናልን?

ሌሎችን በማገልገል እና የቤተክርስቲያን ጥሪያችንን በመፈጸም ረገድ ጠንቃቆች ነን ወይስ ለአገልግሎት ጥሪያችን ምንም የማይገደን ወይም ቸልተኞች ነን?

በምናነበው እና በቴሌቪዥን እና በእጅ ስልኮቻችን በምናየው ነገር ጠንቃቆች ነን ወይስ ቸልተኞች? በቋንቋ አጠቃቀማችን ጠንቃቆች ነን? ወይንስ ያልታረሙ እና የስድበት ቃላትን በቸልተኝነት እናካትታለን?

ለወጣቶች ጥንካሬ የተሰኘው አነስተኛ መጽሄት በጥንቃቄ ከተከተልናቸው ብዙ በረከቶችን የሚያመጡ እንዲሁም በቃል ኪዳኑ መንገድ ላይ እንድንቆይ የሚረዱ መስፈርቶች አሉት። ለወጣቶች ጥቅም የተጻፈ ቢሆንም፣ ከወጣት ወንዶች እና ከወጣት ሴቶች ፕሮግራሞች ስንወጣ መስፈርቶቹ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አያልፍም። ለእኛ ለሁላችን በምን ጊዜም ይሰራሉ። እነዚህን መስፈርቶች መከለስ ወንጌልን ስንኖር ይበልጥ ጠንቃቃ ልንሆን የምንችልባቸውን ሌሎች መንገዶች ሊያነሳሳ ይችላል።

ከሁኔታዎች ጋር ለመስማማት ወይንም ሌላ ሰው ምቾት እንዲሰማው ለማድረግ ስንል መስፈርቶቻችንን ዝቅ አናደርግም። እኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ነን፣ ስለሆነም አላማችን ሌሎችን ከፍ ወዳለ፣ ታላቅ በረከቶችን ወደሚያጭዱበት የተቀደሰ ስፍራ ለማንሳት ነው።

ከቃል ኪዳኖቻችን ጋር ይበልጥ በጥንቃቄ ተስማምተን ለመሄድ ምን ማስተካከያ እንደሚያስፈልገን ማወቅ እንድንችል የመንፈስ ቅዱስን ምሪት እንድንፈልግ እያንዳንዳችንን እጋብዛለሁ። በተመሳሳይ ጉዞ ላይ ባሉ በሌሎች ላይ ፈራጅ እንዳትሆኑም እማጸናችኋለሁ። “ጌታ ፍርድ የእኔ ነው ብሏል።”2 እኛ እያንዳንዳችን በእድገት እና በለውጥ ሂደት ላይ ነን።

በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የተነገረው የከሃዲ አማለካውያን ታሪክ ይስበኛል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከእንግዲህ ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ለሌሎች እንደማሳያ መንገድ የተለየ ቀይ ምልክት ሁሉም እንዲያዩት በግንባራቸው ላይ ያደርጉ ነበር።3 በተቃራኒ መንገድ እና እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት፣ እራሳችን ላይ ምልክት የምናደርገው እንዴት ነው? ሌሎች ምስሉን በቀላሉ በፊታችን ለመመልከት እና ህይወታችንን በጥንቃቄ በምንመራበት መንገድ በመነሳት ማንን እንደምንወክል ማወቅ ይችላሉን?

የቃል ኪዳን ህዝብ እንደመሆናችን መጠን ከቀረው አለም ጋር መቀላቀል አይኖርብንም። “የተለየ ህዝብ”4 ተብለን ተጠርተናል—እንዴት ያለ ምስጋና ነው! የዓለም ተጽዕኖዎች ይበልጥ ክፋትን እያካተቱ በመሄዳቸው ወደ አዳኛችን በሰላም በሚመራን መንገድ ላይ በጽናት ለመቀጠል እንዲሁም ቃል ኪዳናችንን በመኖራችን እና በአለማዊ ተጽዕኖዎች መካከል ያለውን ርቀት ለማስፋት ያላሰለሰ ጥረት ለማድረግ በብርቱ መታገል አለብን።

ዘላቂ ሰላም ስለማግኘት ስናገር አንዳንድ ጊዜ እራሳችንን በማያስደስት ሁኔታ ውስጥ ልናገኘው እንደምንችል እገነዘባለሁ። በቃል ኪዳኑ መንገድ ስንጓዝ የጭለማ ጭጋጎች የማይቀሩ ናቸው። ፈተና እና ቸልተኝነት በረቀቀ ዘዴ መንገዳችንን ወደ አለም ጭለማ እና ከቃል ኪዳኑ መንገድ በተለየ አቅጣጫ ለመምራት ምክንያት ሊሆኑብን ይችላሉ። እንዲህ ሊሆኑ በሚችሉባቸው ጊዜያት ተወዳጁ ነቢያችን ፕሬዘዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን ወደ ቃል ኪዳኑ መንገድ በፍጥነትም እንድንመለስ በጥብቅ አሳስበውናል። ለንስሃ ስጦታ እና ለአዳኛችን የኃጥያት ክፍያ ሃይል እንዴት አመስጋኝ ነኝ።

ፍጽምና ያለው ህይወት መኖር አይቻልም። በዚህ ተለስቲያል አለም ላይ አንድ ሰው ብቻ ነበር በፍጽምና መኖር የቻለው። ያም ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። ፍጹም ልንሆን ባንችልም፣ ወንድሞች እና እህቶች፣ ብቁ ልንሆን እንችላለን፥ ከቅዱስ ቁርባኑ ለመካፈል፣ ለቤተመቅደስ በረከቶች እና የግል መገለጦችን ለመቀበል ብቁ ልንሆን እንችላለን።

ንጉስ ቢንያም አዳኙን በጥንቃቄ ለሚከተሉ ስለሚመጡት በረከቶች እና ደስታ መስክሯል፣ “እናም በተጨማሪ፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁትን የተባረከና አስደሳቹን ሁኔታ እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ። እነሆም እነርሱ በሁሉም ነገሮች፣ ለጊዜያዊም ሆነ ለመንፈሳዊ፣ የተባረኩ ናቸውና፤ እናም እስከ መጨረሻው በታማኝነት ከዘለቁ፣ ለዘለአለም በማያልቀው ደስታ ከእግዚአብሔር ጋር ይኖሩ ዘንድ፣ መንግስተ ሰማይ ትቀበላቸዋለች።5

ደስታ በ15 ብር ሊገዛ ይችላልን? በፍጹም አይቻልም። ጥልቅ እና ዘላቂ ደስታ የሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በዓላማ እና በጥንቃቄ በመኖር ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።