መንፈሳዊ ጡንቻዎቻችንን መጠቀም
ልክ ስለ ጡንቻ ማንበብና መማር ጡንቻን ለመገንባት በቂ እንዳልሆነ ሁሉ፣ ስለ እምነት ማንበብና መማር ብቻውን ተግባር ካልተጨመረበት በስተቀር እምነትን ማሳድግ አይችልም፡፡
ድንቅ በሆነው የሰማያዊ አምላካችን የስጋዊ አካል ስጦታ ስለተባረኩኝ አመስጋኝ ነኝ፡፡ አካላቶቻችን 600 ያህል ጡንቻዎች አሏቸው1 ብዙዎቹ ጡንቻዎች የእለት ተእለት ተግባራቸውን ማከናወን የሚያስችላቸው አቋም ላይ እንዲሆኑ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅቸዋል፡፡ ሰለጡንቻዎቻችን አእምሮአዊ ጥረታችንን ተጠቅመን ማንበብና መማር እንችላለን ነገር ግን ይህን ማድረጋችን ጡንቻችንን ጠንካራ ያደርጋል ብለን ካሰብን ግን በጣም እናዝናለን፡፡ ጡንቻዎቻችን የሚያድጉት ስንጠቀምባቸው ብቻ ነው፡፡
መንፈሳዊ ስጦታዎችም በብዙ ነገሮች ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ባህሪ እንዳላቸው ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ ማደግ እንዲችሉ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው። የእምነት መንፈሳዊ ስጦታ ለምሳሌ ዝም ብሎ የሆነ ስሜት ብቻ አይደለም በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ “ልምምድ“ ከሚለው ግስ ጋር ተያይዞ የሚገኝ አንድ የተግባር መርህ ነው2 ልክ ስለ ጡንቻ ማንበብና መማር ጡንቻን ለመገንባት በቂ እንዳልሆነ ሁሉ፣ ስለ እምነት ማንበብና መማር ብቻውን ተግባር ካልተጨመረበት በስተቀር እምነትን ማሳድግ አይችልም፡፡
እኔ የ16 አመት ልጅ ሳለሁ 22 አመቱ የነበረው የሁላችን ታላቅ ወንድም ኢቫን አንድ ቀን ወደቤት መጣና አንድ ዜና ለቤተሰቡ ተናገረ፡፡ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የእየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ለመጠመቅ ወስኖ ነበር፡፡ ወላጆቻችን በጥርጣሬ መልክ ተመለከቱት ፤ እናም ትዝ ይለኛል ምን እየተካሄደ እንደነበር ሙሉ በሙሉ አልገባኝም ነበር፡፡ ከአመት ምናምን ገደማ በኋላ ይበልጥ ያልተጠበቀ ዜና ነገረን-—የቤተክርስቲያኗ ሚስዮናዊ ሆኖ ለማገልገል ወስኖ ነበር፤ ይህም ማለት ለቀጣዮቹ ሁለት አመታት አናየውም ማለት ነበር፡፡ ወላጆቼ በዚህ ዜና አልተደሰቱም ነበር ፤ ይሁን እንጂ ለእርሱ እና ላሳለፈው ውሳኔ ያለኝን አድናቆት ከፍ ያደረገ የማያሻማ ቁርጠኝነት አይቼበታለሁ፡፡
ከወራት በኋላ ኢቫን ሚስዮናዊ አገልግሎት ላይ እያለ ከጥቂት የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋር ሽርሽር ለመሄድ የማቀድ አጋጣሚን አግኝቼ ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታችን መጠናቀቁን በማስመልከት ለመዝናናት እና በውሃው ዳርቻ ለጥቂት ቀናት ለማሳለፍ ፈልገን ነበር፡፡
የበጋውን የሽርሽር እቅዴን በመጥቀስ ለሚስዮናዊ ወንድሜ ደብዳቤ ጻፍኩለት፡፡ እርሱ የሚያገለግልበት ከተማ ወደ እኔ መዳረሻ ስሄድ በማልፍበት መንገድ ላይ እንደሚገኝ ጻፈልኝ፡፡ እዚያ ብወርድና ብጎበኘው ጥሩ ሃሳብ እንደሚሆን ወሰንኩኝ፡፡ እሰከዛ ጊዜ ድረስ ሚስዮናውያን በቤተሰብ መጎብኘት እንደማይችሉ አላውቅም ነበር፡፡
ዝግጅቴን በሙሉ አጠናቀኩኝ፡፡ በዚያ ውብ ጸሃያማ ቀን ኢቫንና እኔ በምን በምን መዝናኛዎች ልንዝናና እንደምንችል እያሰብኩኝ በአውቶብሱ ውስጥ መቀመጤ ትዝ ይለኛል፡፡ ቁርሳችንን እንበላለን፣ እናወራለን፣ አሸዋው ላይ እንጫወታለን፣ ጸሃይ እንሞቃለን-—አቤት እንዴት ያለ ምርጥ ጊዜ እንደምናሳልፍ!
አውቶቡሱ መጨረሻው ላይ እንደደረሰ ኢቫንን ከሌላ አንድ ወጣት ልጅ ጋር ቆሞ አየሁት ፤ ሁለቱም ነጭ ሸሚዝ ለብሰዋል ፤ ከረባትም አስረዋል፡፡ ከአውቶብሱ ወረድኩኝ ፤ ተቃቀፍን ከዚያም ሚስዮናዊ ጓደኛውን አስተዋወቀኝ፡፡ ምንም ተጨማሪ ደቂቃ ሳላባክን ስለዚያን ቀን ያለኝን እቅድ ለወንድሜ ነገርኩት ነገር ግን ኢቫን ምን አቅዶ እንደነበር ብዙም አላውቅም ነበር፡፡ አየኝና ፈገግ አለ ከዚያም “ጥሩ! ነገርግን በመጀመሪያ አንዳንድ ስራዎችን መስራት አለብን፡፡ ከእኛ ጋር ትመጣለህ?” ከዚያ በኋላ በውሃ ዳርቻው ለመዝናናት በቂ ጊዜ እንደሚኖረን አሰብኩና ተስማማሁኝ፡፡
የዚያን ቀን ከአስር ለሚበልጡ ሰአታት ከወንድሜ እና ከሚስዮናዊ ጓደኛው ጋር በዛ ከተማ መንገድ ላይ ተጓዝኩኝ ፡፡ ቀኑን ሙሉ ለሰዎች ፈገግ ስል ዋልኩኝ፡፡ በህይወቴ አግኝቼ የማላውቃቸውን ሰዎች ሰላምታ አቀረብኩላቸው፡፡ ከሁሉም ሰው ጋር ተነጋገርን ፣ የማናውቃቸውን ሰዎች በር አንኳኳን ፣ ወንድሜ እና ሚስዮናዊ ጓደኛው የሚያስተምሯቸውን ሰዎችም ጎበኘን፡፡
እንደዚህ ካሉት ጉብኝቶች ባንዱ ወንድሜ እና ሚስዮናዊ ጓደኛው ስለእየሱስ ክርስቶስ እና ስለደህንነት እቅዱ እያስተማሩ ነበር፡፡ በድንገት ኢቫን ቆም አደረገና ተመለከተኝ፡፡ ይድነቅህ ብሎ እየተሰጠ ስለነበረው ትምህርት ያለኝን ሃሳብ እንዳካፍል በትህትና ጠየቀኝ፡፡ ክፍሉ በጸጥታ ተዋጠ ፤ እና ሁሉም አይኖች እኔ ላይ ነበሩ፡፡ ትንሽ ተደናገርኩኝ ፤ በመጨረሻም ቃላቶቹ መጡልኝ እና ስለአዳኙ የነበረኝን ስሜት አካፈልኩኝ፡፡ ያካፈልኩት ነገር ልክ ይሁን አይሁን አላወኩም ነበር፡፡ ወንድሜም አላረመኝም ነበር፤ እንዲያውም በተቃራኒው ሃሳቤንና ስሜቴን ስላካፈልኩኝ አመሰገነኝ፡፡
አብረን በነበርንባቸው በነዛ ሰአታት ውስጥ ወንድሜ እና ሚስዮናዊ ጓደኛው አንድም ደቂቃ ምንም ትምህርት እኔን በተለይ አላስተማሩኝም፡፡ነገር ግን እስከዚያ ቀን ድረስ ከእርሱ ጋር ከነበሩን የቀድሞ ውይይቶች የተሸለ እውቀትን አገኘሁኝ‹፡፡ ሰዎች በህይወታቸው መንፈሳዊ ብርሃን ሲቀበሉ የንግግር አገላለጻቸው ምን ያህል እንደሚለወጥ አይቻለሁ፡፡ አንዳንዶች እንዴት በመልዕክቱ ተስፋ እንዳገኙ አየሁ፤ እራሴንና የግል ፍላጎቶቼን ወደጎን በማድረግ እንዴት ሌሎችን ማገልገል እንደሚቻል ተምሪያለሁ፡፡ “ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ቢኖር እራሱን ይካድ፡፡“ የሚለውን አዳኙ ያስተማረውን ነበር እያደረኩኝ የነበረው፡፡3
ዞር ብዬ ወደኋላ ስመለከት እምነቴ የዛን ቀን አንደጨመረ እገነዘባለሁ ምክንያቱም ወንድሜ እምነቴን ወደተግባር የምለውጠበትን አጋጣሚ ስለፈጠረልኝ ነው፡፡ ከቅዱሳን ጽሁፎች የምናነበውን ያንኑ ተግባር ላይ አዋልኩኝ ፤ የማስተምራቸውን ሰዎች ስፈልግ ዋልኩኝ ፣ ምስክርነት ሰጠሁኝ ፣ ሌሎችን አገለገልኩኝ ፣ እንዲሁም የመሳሰሉትን ... የዚያን ቀን ጸሃይ ለመሞቅ አልወጣንም ይሁን እንጂ ልቤ ከሰማይ ከመጣ ብርሃን ሙቀት አግኝቶ ነበር፡፡ በውሃው ዳርቻ አንዲት ቅንጣት አሸዋ አላየሁም ነበር ነገር ግን እምነቴ እንደ አንዲት የሰናፍጭ ፍሬ ቅንጣት ሲያድግ ተሰማኝ፡፡4 ጸሃያማውን ቀን እንደ አንድ ቱሪስት አላሳለፍኩትም ነገርግን አስደናቂ ተመክሮዎችን አግኝቼበታለሁ ፤ እናም ሳላስበው ሚስዮናዊ ሆኔ ነበር-ያውም የቤተክርስቲያኗ አባል ሳልሆን!
መንፈሳዊ ጡንቻዎችን ለማጠንከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎች
ዳግም ለተመለሰው ወንጌል ምስጋና ይግባውና የሰማዩ አባታችን መንፈሳዊ ስጦታዎችን እንዴት ልናዳብር እንደምንችል እንደሚረዳን ልንገነዘብ እንችላለን፡፡ ያለምንም መንፈሳዊና አካላዊ ጥረት ዝም ብሎ ከሚሰጠን ይልቅ እነዚያኑ ስጦታዎች ልናዳብር የምንችልበትን አጋጣሚዎች የሚሰጥበት ሰፊ እድል አለ፡፡ ከመንፈሱ ጋር ስምም ከሆንን እነዚያን አጋጣሚዎች ለማወቅ ከዚያም አርምጃ ለመውሰድ እንማራለን፡፡
ብዙ ትእግስት ካስፈለገን ራሳችንን ትእግስትን በተግባር በማዋል ለማሳየት በመፈለግ ላይ ሆነን ልናገኘው እንችላለን ምላሽ እስክናገኝ ድረስ፡፡ ለጎረቤታችን የላቀ ፍቅር እንዲኖረን ከፈለግን ቤተክርስቲያን ውስጥ ከአንድ አዲስ ሰው አጠገብ በመቀመጥ ኮትኩተን ልናሳድገው እንችላለን፡፡ እምነትም እንደዚያው ነው-ጥርጣሬዎች ወደ አእምሯችን ሲመጡ በጌታ ተስፋዎች ላይ እምነት ማሳደር ወደፊት ለመራመድ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ መንገድ መንፈሳዊ ጡንቻዎቻችንን እናለማምዳቸዋለን ፤ እንዲሁም በህይወታችን የጥንካሬ ምንጮች ወደመሆን እናሳድጋቸዋለን፡፡
መጀመሪያ ላይ ምናልባት ቀላል ላይሆን ይችላል ፤ እንዲያውም ትልቅ ፈተና ሊሆንብን ይችላል፡፡ በነቢዩ ሞሮኒ በኩል የተነገሩት የጌታ ቃላት በዚህ ዘመን ለኛም ይሆናሉ—“እናም ሰዎች ወደኔ የሚመጡ ከሆነ ድክመታቸውን አሳያቸዋለሁ፡፡ ሰዎች ትሁት እንዲሆኑ ድካምን እሰጣቸዋለሁ፤ እናም ፀጋዬም እራሳቸውን በፊቴ ዝቅ ላደረጉ ሁሉ በቂ ነው ፤ እነርሱም በፊቴ እራሳቸውን ዝቅ ካደረጉ ፣ እናም በእኔም እምነት ካላቸው ፣ ከዚያም ደካማ የሆኑትን ለእነርሱ ጠንካራ እንዲሆኑ አደርጋለሁ።”5
ወንጌልን ለኔ ማካፈል ብቻ ሳይሆን በተዘዋዋሪ እንድኖረውም እንዲሁም ድክመቶቼን እንድገነዘብ ለጋበዘኝ ስለወንድሜ ኢቫን አመስጋኝ ነኝ ፡፡ የጌታን ግብዣ እንድቀበል ረድቶኛል-“ኑ፤ ተከተሉኝ“ 6—ጌታ አንደተመላለሰው ለመመላለስ ፣ ጌታ እንደሻተው ለመሻት ፣ እንዲሁም ጌታ እንደወደደን እኛም ለመውደድ፡፡ የሚስዮናዊ አገልግሎትን ተመክሮ ካየሁኝ ከወራት በኋላ ለመጠመቅ እና የራሴን ሚስዮናዊ አገልግሎት ለመስጠት ወሰንኩኝ፡፡
የፕሬዚደንት ረሰል ኤም. ኔልሰንን ግብዣ እንቀበል እና 7ብዙ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የሚያስፈልጋቸውን እነዚያን ጡንቻዎች በመለየት እና ልናንቀሳቅሳቸው በመጀመር ወደ ጌታ እንምጣ፡፡ ይህ የአጭር ሳይሆን የረዥም ርቀት የማራቶን ውድድር ነው ስለዚህ እነዚያን አስፈላጊ መንፈሳዊ ጡንቻዎች የሚያጠነክሩ ትንንሽ ነገር ግን የማይቀሩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አትርሱ፡፡ እምነታችንን ማሳደግ የሚያስፈልገን ከሆነ እምነትን የሚጠይቁ ነገሮችን እናድርግ፡፡
የአፍቃሪ ሰማያዊ አባት ልጆች እንደሆንን ምስክርነቴን እሰጣለሁ፡፡ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ይወደናል። መንገዱን ሊያሳየን ወደዚህ ምድር መጥቷል ከዚያም ለኛ ተስፋ ሊሰጠን ህይወቱን በፈቃደኝነት ሰጥቷል፡፡ አደኙ ፍጹም ምሳሌውን እንድንከተል ፣ በእርሱ እና በሃጢያት ክፍያው ላይ ያለንን እምነት በተግባር እንድናሳይ ፣ እንዲሁም የተሰጡንን የመንፈስ ስጦታዎች እንድናስፋፋ ጋብዞናል፡፡ እርሱ መንገድ ነው፤ ይህ ምስክርነቴ ነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን።