አጠቃላይ ጉባኤ
የመንፈሳዊ ፍጥነት ሃይል
የሚያዝያ 2022 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


17:18

የመንፈሳዊ ፍጥነት ሃይል

አዎንታዊ የመንፈሳዊ ፍጥነትን ለመጠበቅ የሚረዱንን አምስት የተለዩ ተግባራት ለመጠቆም እወዳለሁ።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ እወዳችኋለሁ። ዛሬ እናንተን ለማነጋገር ያገኘሁትን እድል ከፍ አድርጌ እመከተዋለሁ። ከጠላት ሃይለኛ ጥቃቶች ትጠበቁ ዘንድ እንዲሁም በሚያጋጥሟችሁ ፈተናዎች ወደፊት ለመግፋት የሚያስችል ጥንካሬ እንዲኖራችሁ በየቀኑ እጸልያለሁ።

አንዳንድ ፈተናዎች ሌላ ማንም ሊያያቸው የማይችላቸው የግል ሸክሞች ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ዓለም እያየ የሚከናወኑ ናቸው። በምስራቅ አውሮፓ የሚካሄደው ወታደራዊ ግጭት ከእነዚህ ውስጥ ይመደባል። ወደ ሩሲያ እና ዩክሬን ብዙ ጊዜ ሄጃለሁ። እነዚያን አገራት፣ ህዝቦች፣ እና ቋንቋቸውን እወዳለሁ። በዚህ ግጭት ስለተጎዱት ሁሉ አለቅሳለሁ እንዲሁም እጸልያለሁኝ። በቤተክርስቲያን ደረጃ በስቃይ ላይ ያሉትን እና በህይወት ለመቆየት የሚታገሉትን ለመርዳት የተቻለንን ያህል በማድረግ ላይ እንገኛለን። በዚህ አደጋ እየተጎዱ ላሉ ሰዎች ሁሉ እያንዳንዱ ጾም እና ጸሎት በማድረግ እንዲቀጥል እንጋብዛለን። ማንኛውም ጦርነት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የቆመለትን እና ያስተማረውን ነገር ሁሉ በአስፈሪ ሁኔታ መጣስ ነው።

ማንኛችንም ሃገራትን ወይንም የሌሎችን ድርጊቶች ወይንም የራሳችንን ቤተሰብ አባላት እንኳን መቆጣጠር አንችልም። ነገር ግን ራሳችንን መቆጣጠር እንችላለን። ውድ ወንድሞች እና እህቶች ዛሬ የማቀርብላችሁ ጥሪ በእናንተ ልብ በእናንተ ቤት እና በእናንተ ህይወት ውስጥ እየተነሱ ያሉትን ግጭቶች እንድታስወግዱ ነው። ያ ዝንባሌ ቁጣም ቢሆን፣ የሚወጋ አንደበት ወይም በጎዳችሁ ሰው ላይ የያዛችሁት ቂም ማንኛውንም እንዲሁም ሁሉንም ዝንባሌዎች ቅበሩ። አዳኙ ሌላኛውን ጉንጫችንንም እንድናዞር፣1 ጠላታችንን እንድንወድ እንዲሁም ለሚበድሉን እንድንጸልይ አዞናል።2

ተገቢ እንደሆነ የሚሰማንን ቁጣ መተው በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል። አፍራሽ ድርጊቶቻቸው ንጹሃንን የጎዳውን ይቅር ማለት የማይቻል ሊመስል ይችላል። ሆኖም አዳኙ “ሁሉንም ይቅር እንድንል”3ምክር ሰጥቶናል።

የሰላሙ ልዑል ተከታዮች ነን። ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን እርሱ ብቻ የሚያመጣውን ሰላም እንፈልጋለን። በግለሰብ ደረጃ ሰላምን እና ስምምነትን ሳንፈልግ በዓለም ሰላም እንዲሰፍን እንዴት መጠበቅ እንችላለን። ወንድሞች እና እህቶች፣ እየጠቆምኳችሁ ያለሁት ነገር ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ። ሆኖም የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች አለም ሁሉ ሊከተለው የሚገባ ምሳሌ መተው ይኖርባቸዋል። በልባችሁ እና በህይወታችሁ ውስጥ በአሁኑ ወቅት እየተነሱ ያሉትን የግል ግጭቶች ለማስወገድ ማድረግ የምትችሉትን ሁሉ እንድታደርጉ እማጸናችኋለሁ።

በቅርብ ጊዜ የቅርጫት ኳስ ጨዋታ እየተመለከትኩኝ ሳለሁ የታወሰኝን ሃሳብ በመግለጽ ለዚህ የድርጊት ጥሪ አጽንዖት ልስጥ።

በዚያ ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ወደፊት ወደኋላ እያሉ በየተራ ሲመሩ የታዩበት ነበር። ከዚያም በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ አምስት ሴኮንዶች ውስጥ በአንደኛው ቡድን ውስጥ ያለ ተከላካይ አንድ ቆንጆ ባለ ሶስት ነጥብ ጎል አስቆጠረ። አንድ ሰከንድ ብቻ ሲቀርም ጨዋታው ከእንደገና ሲጀመር የቡድን አጋሩ የተወረወረውን ኳስ ቀምቶ ባለቀ ሰዓት ሌላ ነጥብ አስቆጠረ!። ስለዚህም ያ ቡድን በአራት ነጥብ እየመራ ሊታይ በሚችል መልኩ ፍጥነቱን በመጨመር ወደ ልብስ መቀየሪያ ክፍል ገባ። በሁለተኛው አጋማሽም ያንን ፍጥነት ማስቀጠል እንዲሁም ማሸነፍ ችለው ነበር።

ፍጥነት ሃይለኛ ጽንሰ ሃሳብ ነው። እኛ ሁላችንም በአንድ ወይም በሌላ መልኩ አይተነዋል—ለምሳሌ ፍጥነቱን እየጨመረ የሚመጣ መኪናን በምናይበት ጊዜ ወይንም አለመግባባት በአንዴ ወደክርክር ሲያመራ።

ስለዚህ እንዲህ ስል እጠይቃለሁ መንፈሳዊ ፍጥነትንየሚያቀጣጥለው ምንድነው? የአዎንታዊ እና የአሉታዊ ፍጥነትን ምሳሌዎች ተመልክተናል። የተለወጡ እና በእምነት ያደጉ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮችን እናውቃለን። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ቁርጠኛ የነበሩ ዛሬ ወደኋላ ሰስለቀሩትም እናውቃለን። ፍጥነት በየትኛውም አቅጣጫ ሊሄድ ይችላል።

አሁን የሚያስፈልገንን ያህል አዎንታዊ መንፈሳዊ ፍጥነት እንደዛሬ አስፈልጎን አያውቅም። አዎንታዊ መንፈሳዊ ፍጥነት በወረርሽኝ፣ በሱናሚ፣ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች እና በመሳሪያ በታገዙ ግጭቶች መካከል ወደፊት እንድንገፋ ይረዳናል። መንፈሳዊ ፍጥነት የጠላትን የማያቋርጡ ክፉ ጥቃቶች እንድንቋቋምና የግል መንፈሳዊ መሠረታችንን ለመሸርሸር የሚያደርገውን ጥረት ለማምከን ሊረዳን ይችላል።

ብዙ ተግባራት አዎንታዊ መንፈሳዊ ፍጥነትን ሊያቀጣጥሉ ይችላሉ። ታዛዥነት፣ ፍቅር፣ ትህትና፣ አገልግሎት እና አመስጋኝነት4 ጥቂቶቹ ናቸው።

ዛሬ አዎንታዊ መንፈሳዊ ፍጥነትን ለመጠበቅ ልንፈጽም የምንችላቸውን አምስት የተለዩ ተግባራት ለመጠቆም እወዳለሁ።

አንደኛ፦ ወደቃል ኪዳኑ መንገድ ግቡና በዚያው ቆዩ።

ብዙም አልቆየም፣ ከብዙ ሰዎች ጋር የተገናኘሁበት ግልፅ ህልም አየሁኝ። ብዙ ጥያቈዎች ጠየቁኝ፣ ከእነዚህም የተደጋገመው የቃል ኪዳኑን መንገድ የተመለከተ ሲሆን እንዲሁም ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ነበር።

በህልሜም ወደ ቃል ኪዳን መንገድ የምንገባው በመጠመቅ እና የመጀመሪያውን ቃል ኪዳናችንን ከእግዚአብሔር ጋር በመግባት ነው ብዬ ገለፅኩኝ።5 ቅዱስ ቁርባንን በተካፈልን ቁጥር፣ የአዳኙን ስም በራሳችን ላይ ለመውሰድ፣ እርሱን ለማስታወስ እና ትዕዛዛቱን ለመጠበቅ እንደገና ቃል እንገባለን።6 በምላሹም መንፈሱ ሁሌም ከእኛ ጋር እንደሚሆን እግዚአብሔር ያረጋግጥልናል።

በኋላም የበለጡ ተስፋዎችን በምንቀበልበት በቤተመቅደስ ውስጥ ተጨማሪ ቃልኪዳኖችን እንገባለን። ስርዓቶች እና ቃልኪዳኖች የአምላካዊ ኃይል ተደራሽነትን ይጨምራሉ። የቃል ኪዳኑ መንገድ ከፍ ወዳለ ክብር እና ወደዘለለማዊ ህይወት የሚመራ ብቸኛው መንገድ ነው።

በህልሜ፣ አንዲት ሴት ቃል ኪዳኖቹን/ቿን ያፈረሰ/ሰች እንዴት በዚያ መንገድ ለመመለስ እንደሚችሉ ጠየቀችኝ። የዚህ ጥያቄ መልስ ወደ ሁለተኛው ጥቆማዬ ይመራል፦

በየቀኑ በንስሃ ደስታን አግኙ።

ንስሃ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? አልማ “ንስሃን እና በጌታ ላይ እምነትን ካልሆነ በቀር ምንም እንዳ[ንሰብክ]”7አስተምሯል። እያንዳንዱ ተጠያቂነት ያለበት እና ዘላለማዊ ክብርን የሚፈልግ ንስሃ ያስፈልገዋል።8 ልዩ ሁኔታዎች የሉም። ለነብዩ ጆሴፍ ስሚዝ በተሰጠው ራዕይ ውስጥ፣ ጌታ ለልጆቻቸው ወንጌልን ላላስተማሩ የቤተክርስቲያን መሪዎችም ተግሳጽ ሰጥቷቸዋል።9 ንስሃ የእድገት ቁልፉ ነው። ንጹህ እምነት በቃል ኪዳኑ መንገድ ላይ ወደፊት እንድንጓዝ ያደርገናል።

እባካችሁን ንስሃ መግባት አትፍሩ ወይም ንስሃችሁን አታዘግዩት። ሰይጣን በሃዘናችሁ ይደሰታል። አጭር አድርጉት። ተጽዕኖውን ከህይወታችሁ ውስጥ አስወጡ! ተፈጥሯዊውን ሰው በማውለቅ የሚገኘውን ደስታ ዛሬውኑ ጀምሩ።10 አዳኙ ሁል ጊዜ ይወደናል በተለይ ንስሃ ስንገባ። “ተራሮች ይፈልሳሉ፥ ኮረብቶችም ይወገዳሉ … ቸርነቴ ግን ከአንቺ ዘንድ አይፈልስም” ሲል ተስፋ ሰጥቶናል።11

ከቃል ኪዳኑ መንገድ በጣም እንደራቃችሁ ወይም የመመለሻ መንገድ እንደሌላችሁ ከተሰማችሁ በቀላሉ ያ እውነት አይደለም።12 እባካችሁ ከኤጲስ ቆጶሳችሁ ወይም ከቅርንጫፍ ፕሬዘደንታችሁ ጋር ተነጋገሩ። እርሱ የጌታ ወኪል ነው እናም ደስታን እና እፎይታን እንድታገኙ ይረዳችኋል።

አሁን ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ አለ፦ ወደ ቃል ኪዳኑ መንገድ መመለስ ማለት ህይወት ቀላል ይሆናል ማለት አይደለም። ይህ መንገድ በጥብቅ የሚተገበር ነው እናም አንዳንድ ጊዜ አቀበትን እንደመውጣት ሊሰማ ይችላል።13 ሆኖም ይህ የአቀበት ጉዞ የተዘጋጀው እኛን ለመፈተን እና ለማስተማር፣ ተፈጥሯችንን ይበልጥ እንድናስተካክል እንዲሁም ቅዱሳን እንድንሆን ለመርዳት ነው። ይህም ወደ ዘለአለማዊ ህይወት የሚመራ ብችኛ መንገድ ነው። አንድ ነቢይ14 “የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁትን የተባረከና አስደሳቹን ሁኔታ [ገልጿል]። እነሆም እነርሱ በሁሉም ነገሮች፣ በስጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ፣ የተባረኩ ናቸውና፤ እናም እስከ መጨረሻው በታማኝነት ከዘለቁ፣ ለዘለአለም በማያልቀው ደስታ ከእግዚአብሔር ጋር ይኖሩ ዘንድ፣ መንግስተ ሰማይ ትቀበላቸዋለች።15

በቃል ኪዳኑ መንገድ መጓዝ ከእለት ተዕለት ንስሃ ጋር ሲጣመር አዎንታዊ መንፈሳዊ ፍጥነትን ያቀጣጥላል።

ሶስተኛው ጥቆማዬ፦ ስለእግዚአብሔር እንዲሁም ስለአሰራሩ ተማሩ።

ዛሬ ካሉብን ታላላቅ ፈተናዎች አንዱ በእግዚአብሔር እውነቶች እና በሰይጣን እውነት መሳይ ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ነው። ለዚህ ነው ጌታ “ድል [እና]ደርግ ዘንድ፤ አዎን፣ ሰይጣንን ድል [እና]ደርግ ዘንድ፣ እናም የእርሱን ስራ ከሚደግፉት የሰይጣን አገልጋዮች እጆች [እና]መልጥ ዘንድ ዘወትር ጸል[ዩ]።” ሲል ያስጠነቀቀው።16

ሙሴ በአምላክና በሰይጣን መካከል ያለውን ልዩነት ለመገንዘብ በማስተዋል ረገድ እጅግ በጣም ጥሩ ምሳሌ ነው። ሰይጣን ሊፈትነው ሲመጣ ሙሴ ማታለል መሆኑን አወቀ፤ ምክንያቱም ገና ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ መመለሱ ነበርና። ስለዚህ ሙሴ በፍጥነት ሰይጣን ማን እንደሆነ ተገነዘበ እንዲሁም ከእርሱ እንዲለይ አዘዘው።17 ሰይጣን በጸና ጊዜ ተጨማሪ እርዳታ ለማግኘት እግዚአብሔርን እንዴት መጥራት እንዳለበት ሙሴ አወቀ። ሙሴ ከአምላክ ጥንካሬን ተቀበለ እናም ክፉውን በድጋሚ“ሰይጣን ከእኔ ዘንድ ሂድ፣ የክብር አምላክ የሆነውን ይህን አንድ እግዚአብሔርን ብቻ አመልካለሁና።”18ሲል ገሰጸው።

እኛም ያን ምሳሌ መከተል ይገባናል። ሰይጣን በህይወታችሁ ላይ ያለውን ተጽዕኖ አስወግዱ! እባካችሁ“ ወደባህረሰላጤ እና መጨረሻ ወደሌለው ዋይታ አትከተሉት።”19

በየቀኑ “ከእግዚአብሔር መልካም ቃል”20 ያልተመገበ ምስክርነት በሚያስፈራ ፍጥነት ሊፈርስ ይችላል። ስለዚህ የሰይጣን እቅድ እንይዳይሰራ የማድረጊያው መድሃኒት ግልጽ ነው፦ ጌታን የማምለክ እና ወንጌሉን የማጥናት የእለት ተእለት ልምዶች ያስፈልጉናል። እግዚአብሔር በህይወታችሁ እንዲያሸንፍ እንድትፈቅዱ እማጸናችኋለሁ። የጊዚያችሁን ተገቢ ድርሻ ስጡት። ይህንን ስታደርጉ አዎንታዊ መንፈሳዊ ፍጥነታችሁ ላይ ምን እንደሚከሰት ልብ በሉ።

ጥቆማ 4፦ ተዓምራትን እሹ እንዲሁም ጠብቁ።

ሞሮኒ “እግዚአብሔር የተዓምራት አምላክ መሆኑን አላቆመም“ ሲል አረጋግጦልናል21እያንዳንዱየቅዱሳት መጻሕፍት መጽሐፍ ጌታ በእርሱ በሚያምኑት ሕይወት ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ምን ያህል ፈቃደኛ እንደሆነ ያሳያሉ።22 ለሙሴ ቀይ ባህርን ከፈለ፣ ኔፊ የነሃስ ሰሌዳዎቹን እንዲያወጣ ረዳው እንዲሁም በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካኝነት ቤተክርስቲያኑን ዳግም መለሰ። እያንዳንዳቸው እነዚህ ተአምራት ጊዜ ወስደዋል እንዲሁም ግለሰቦቹ አስቀድመው ጌታን የጠየቁት ነገሮች ላይሆኑ ይችላሉ።

በተመሳሳይ መንገድ ”ሳትጠራጠሩ”ብታምኑጌታ በሚያስፈልጓችሁ ተዓምራት እናንተንይባርካችኋል።23 ተዓምራትን ለመሻት መንፈሳዊ ስራን ስሩ። ያን አይነት እምነት እንዲኖራችሁ ይረዳችሁ ዘንድ እግዚአብሔርን በጸሎት መንፈስ ጠይቁ። ኢየሱስ ክርስቶስ “ለደካማ ኃይልን [እንደሚሰጥ]፤ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን [እንደሚጨምር] በራሳችሁ ማወቅ እንደምትችሉ ቃል እገባላችኋለሁ።”24 ጌታ በህይወታችሁ ያለን ተራራ እንድታንቀሳቅሱ እየረዳችሁ መሆኑን ከማወቅ የበለጠ ጥቂት ነገሮች መንፈሳዊ ፍጥነታችሁ እየጨመረ እንዲሄድ ያደርጋሉ።

ጥቆማ ቁጥር 5፦ ከግል ህይወታችሁ ውስጥ ግጭትን አስወገግዱ

ከእናንተ ህይወት ውስጥ ግጭትን እንድታስወገዱ ያደረገግኩትን ጥሪ እደግምላችኋለሁ። ይቅርታ ለማድረግ እና ይቅር ለመባል የሚያስፈልጉትን ትህትናን፣ ድፍረትን እና ጥንካሬን በተግባር ላይ አውሉ። አዳኙ “[እኛ] የሌሎችን መተላለፍ ይቅር ካልን፣ [የእኛ]የሰማይ አባት ደግሞ [እኛን] ይቅር ይለናል።” ሲል ቃል ገብቶልናል።25

የዛሬ ሁለት ሳምንት ፋሲካን እናከብራለን። ከአሁን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ ሸክም የሆነባችሁን የግል ግጭት እንድታስወግዱ እጋብዛችኋለሁ። ለኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ይበልጥ ተስማሚ የሆነ የምስጋና ተግባር ሊኖር ይችላል? አሁን ይቅር ለማለት የማይቻል መስሎ ከተሰማችሁ አርዳታ ለማግኘት ለሃጢያት በተከፈለው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም በኩል ተማጸኑ። ይህንን ስታደርጉ አዎንታዊ መንፈሳዊ ፍጥነታችሁ ላይ ምን እንደሚከሰት ልብ በሉ።

አዳኙ ለሁሉም የሰው ልጆች የሃጢያት ክፍያውን በፈጸመ ጊዜ እርሱን የሚከተሉት የመፈወስ፣ የማጠንከር እና የቤዛነት ሃይሉን ማግኘት እንዲችሉ መንገዱን ከፈተ። እነዚህን መንፈሳዊ እድሎች እሱን ለመስማት እና ለመከተል የሚሹ ሁሉ ያገኟቸዋል።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ ወደቃልኪዳኑ መንገድ እንድትገቡ እና በዚያው እንድትቆዩ በሙሉ ልቤ እማጸናችኋለሁ። በየቀኑ ንስሃ በመግባት ደስታን አግኙ። ስለእግዚአብሔር እንዲሁም ስለአሰራሩ ተማሩ። ተዓምራትን እሹ እንዲሁም ጠብቁ። በህይወታችሁ ውስጥ ያለውን ግጭት ለማስወገድ ጣሩ።

በእነዚህ ግቦች ላይ ተግባራዊ እርምጃ ስትወስዱ ምንም አይነት መሰናክል ቢገጥማችሁም በጨመረ ፍጥነት በቃል ኪዳኑ መንገድ ላይ ወደፊት እንደምትገፉ ቃል እገባላችኋለሁ። እንዲሁም ፈተናን የመቋቋም የበለጠ ጥንካሬ፣ የበለጠ የአዕምሮ ሰላም እና ከፍርሃት ነጻነት እንዲሁም በቤተሰቦቻችሁ መካከል የበለጠ ህብረት እንደምታገኙ ቃል እገባላችኋለሁ።

እግዚአብሔር ህያው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ነው! እርሱ ህያው ነው። እርሱ ይወደናል እንዲሁም ይረዳናል። ይህንንም የምመሰክረው በቤዛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. 3 ኔፊ 12፥39 ይመልከቱ።

  2. 2 ኔፊ 12፥44 ይመልከቱ።

  3. ትምህርተ እና ቃል ኪዳኖች 64፥10፤ ደግሞም ቁጥር 9 ይመልከቱ።

  4. ሃዋርያው ጳውሎስ እንዳለው፣ “በሁሉ አመስግኑ” (1 ተሰሎንቄ 5፥18።) ተስፋ መቁረጥ፣ ተነሳሽነት ማጣት እንዲሁም መንፈሳዊ ሃይል እና ፍላጎት ማጣት ከሚወገዱበት የተረጋገጡ መፍትሄዎች አንዱ አመስጋኝነት ነው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ልናቀርብ ከምንችልባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ነገሮች ምን ምን ናቸው? ስለምድር ውበት፣ ስለተመለሰው ወንጌል፣ እርሱ እና ልጁ ኃይላቸውን እኛ በዚህ ምድር ያለን እንድንጠቀምበት ስላደረጉልን ስፍር ቁጥር የሌላቸው መንገዶች አመስግኑት። ስለቅዱሳት መጻህፍት፣ እርዳታ ለማግኘት ለእግዚአብሔር ለምናቀርበው ተማጽኖ ምላሽ ስለሚሰጡን መላዕክት፣ ስለራዕይ እና ስለዘላለማዊ ቤተሰቦች አመስግኑት። ከሁሉም በላይ ወደምድር የተላክንበትን ተልዕኮ እንድናሳካ ስላስቻለን ስለልጁ ስጦታ እና ስለኢየሱስ ክርስቶስ የሃጢያት ክፍያ እግዚአብሔርን አመስግኑት።

  5. የቃልኪዳን መንገዱን ለመረዳት ቃልኪዳን በሁለቱ ወገኖች መካከል ይኸውም በእግዚአብሔር እና ከልጆቹ መካከል ከአንዱ ጋር የሚደረግን ስምምነት የሚያካትት መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። በቃል ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር የቃል ኪዳኑን ቅድመ-ሁኔታ ይሰጣል፣ እኛም ለእነዚህ ቅድመ-ሁኔታዎች ተገዢ ለመሆን እንስማማለን። በምላሹም እግዚአብሔር ተስፋን ይሰጠናል። ብዙ ቃልኪዳኖች ምስክሮች ባሉበት በምንሳተፍበት በውጫዊ ምልክቶች ወይም በቅዱስ ስርዓቶች ይታጀባሉ። ለምሳሌ ጥምቀትን ብንወስድ እየተጠመቀ ያለው ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመጠበቅ ቃል ኪዳን እየገባ እንደሆነ ለጌታ ምልክት ነው።

  6. ሞሮኒ 4፥35:2ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 20፥77፣ 79.ይመልከቱ።

  7. ሞዛያ 18፥20

  8. ሙሴ 6፥50፣57ይመልከቱ።

  9. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 93፥40–48ይመልከቱ።

  10. ሞዛያ 3፥19ይመልከቱ።

  11. ኢሳይያስ 54፥10፤ ትኩረት ተጨምሮበታል፤ ደግሞም 3 ኔፊ 22፥10ይመልከቱ። ደግነትየሚለው ቃል ሄሴድከሚል ደግነትን፣ ይቅርታን፣ ቃልኪዳንን፣ ፍቅርን እና ሌሎችንም አጠቃልሎ ከሚይዝ ጥልቅ ትርጉም ካለው ሃይለኛ የዕብራይስጥ ቃል የተተረጎመ ነው።

  12. ለአንዳንድ ኃጢአቶች ማካካሻ በማድረግ ወደነበሩበት መመለስ ይቻላል፤ ለሌሎች ግን አይቻልም። አንድ ሰው የሌላውን ሰው ንጽህና ካፈረሰ ወይም አንድ ሰው የሌላን ሰው ህይወት ካጠፋ የተሟላ ማካካሻ ማድረግ አይቻልም። በእነዚያ ሁኔታዎች ውስጥ ያለ ኃጢአተኛ የቻለውን ሁሉ ብቻ ነው የሚያደርገው፣ እናም ሚዛን የሚደፋው የሚቀረው በግል ንስሃ አማካኝነት ነው። ጌታ ከሚዛኑ ያለፈውን ይቅር ለማለት ካለው ፍላጎት የተነሳ የቱንም ያህል ከመንገዱ ርቀን ብንሄድ ወደ እሱ ተመልሰን መምጣት እንችላለን። ከልብ ንስሃ ሰንገባ ይቅር ሊለን ይችላል። በሃጢያታችን እና ማካካሻ ለማድረግ ባለን አቅም መካከል ልዩነት ካለ ማካካሻውን መክፈል የሚቻለው የይቅርታን ስጦታ መስጠት የሚችለውን የኢየሱስ ክርስቶስን የሃጢያት ክፍያ በመጠቀም ብቻ ነው። ከሚዛኑ ያለፈውን ይቅር ለማለት ያለው ፍላጎት በዋጋ የማይተመን ስጦታ ነው።

  13. 2 ኔፊ 31፥18–20 ይመልከቱ።

  14. የኔፋውያን ነቢይ ንጉስ ቢንያም

  15. ሞዛያ 2፥41.

  16. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 10፥5፤ አትኩሮት ተጨምሮበታል።

  17. ሙሴ 1፥16፤ ደግሞም ቁጥር 1–20 ይመልከቱ።

  18. ሙሴ 1፥20

  19. ሔላማን 5፥12

  20. ሞሮኒ 6፥4

  21. ሞርሞን 9፥15፤ ደግሞም ቁጥር 19 ይመልከቱ።

  22. ሃዋርያው ዮሃንስ “ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ እናምን ዘንድ “የአዳኙን ተዓምራት እንደመዘገበ ተናግሯል።(ዮሃንስ 20፥31)

  23. ሞርሞን 9፥21

  24. ኢሳይያስ 40፥29

  25. ማቴዎስ 6፥14