ምድራዊ መጋቢነታችን
ምድርን እንዲሁም ወንዶች እና ሴቶች ጓደኞቻቸውን ለሚወዱ እና ለሚንከባከቡ የታላቅ መንፈሳዊ በረከቶች ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል።
እኔና ባለቤቴ የትውልድ አገራችንን ፈረንሳይን እየጎበኘን በነበርንበት ጊዜ በቅርቡ ጥቂት የልጅ ልጆቻችንን ይዘን በትንሿ ጊቨርኒ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን አስደናቂ የአትክልት ስፍራ በመጎብኘት ተዝናንተን ነበር። የሚያማምሩ የአበባ መደቦችን፣ የውሃ ላይ አበቦችን እና በኩሬዎቹ ላይ እየበራ የነበረውን ብርሃን በማድነቅ በመንገዱ ላይ መጓዛችን አስደስቶናል።
ይህ አስደናቂ ቦታ የአንድ ሰው ጠንካራ የፈጠራ ስሜት ውጤት ነው፦ታላቁ ሰአሊ ክላውድ ሞኔት ለ40 አመታት የአትክልት ስፍራውን በፍቅር የቀረጸው እና ያለማው የስዕል መስሪያ ቦታው ለማድረግ ነበር። ሞኔት በተፈጥሮ ግርማ ውስጥ እራሱን ሰወረ፤ ከዚያም በቀለም ብሩሹ ቀለምን እና የብርሃን ጭረትን በመጠቀም የተሰማውን ግንዛቤ አስተላልፏል። ለዓመታት ከአትክልቱ ስፍራ መነሳሳትን በማግኘት በመቶዎች የሚቆጠሩ እጅግ አስደናቂ የሥዕሎች ስብስብን ፈጥሯል።
ወንድሞች እና እህቶች፣ በዙሪያችን ከሚገኙ የተፈጥሮ ውበቶች ጋር ያሉን መስተጋብሮች በህይወታችን ውስጥ በጣም የሚያነሳሱ እና አስደሳች ልምዶችን ሊያስገኙ ይችላሉ። የሚሰሙን ስሜቶች ይህችን አስደናቂ ምድር ከተራሮቿ እና ከጅረቶቿ፣ ከተክሎቿ እና ከእንሳሳቶቿ እንዲሁም ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ጋር ለፈጠሯት ለሰማይ አባታችን እና ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥልቅ የሆነ የምስጋና ስሜት በውስጣችን ያጭራሉ።1
የፍጥረት ስራ በራሱ የመጨረሸው ግብ አይደለም። እግዚአብሔር ለልጆቹ ያለው እቅድ ዋና ክፍል ነው። ዓላማው፣ ወንዶች እና ሴቶች አንድ ቀን ወደ ፈጣሪያቸው ፊት ተመልሰው የዘላለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ የሚፈተኑበትን፣ የመምረጥ ነጻነታቸውን የሚለማመዱበትን፣ ደስታን የሚያገኙበትን እንዲሁም የሚማሩበትን እና የሚያድጉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።
እነዚህ አስደናቂ ፍጥረታት የተዘጋጁት ሙሉ ለሙሉ ለእኛ ጥቅም ሲባል በመሆኑ ፈጣሪ ለልጆቹ ያለውን ፍቅር የሚያሳዩ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው። ጌታ ሲናገር ”አዎን፣ በጊዜአቸው በምድር ላይ የሚያድጉት ነገሮች የተፈጠሩት ለሰው ጥቅም፣ አይንን እና ልብን ለማስደሰት ነውና” ብሏል።2
ነገር ግን የፍጥረት መለኮታዊ ስጦታ ያለ ግዴታዎች እና ኃላፊነቶች አይመጣም። እነዚህ ግዴታዎች መጋቢነትበሚለው ጽንሰ-ሐሳብ በተሻለ ሁኔታ ይገለጻሉ። በወንጌል አገላለጽ መጋቢነት የሚለው ቃል ተጠያቂ የምንሆንበትን የእግዚአብሔር የሆነውን ነገር የመንከባከብ የተቀደሰ መንፈሳዊ ወይም ስጋዊ ኃላፊነትን ይወክላል።3
ቅዱሳን መጻህፍት ሲያስተምሩ ምድራዊ መጋቢነታችን የሚከተሉትን መርሆዎች ያካትታል።
የመጀመሪያ መርህ፦መላው ምድር እና በውስጧ የያዘቸው ህይወት ሁሉ የእግዚአብሄር ናቸው።
ፈጣሪ የምድርን ሃብቶች እና ሁሉንም የህይወት አይነቶች እንድንጠብቅ ለእኛ አሳልፎ በሃላፊነት ሰጥቶናል፤ነገር ግን ባለቤትነቱ ሙሉ በሙሉ የእርሱ ነው። እንዲህ ብሏል ”እኔ ጌታ የእውነት የእጄን ስራ ሰማያትን ዘረጋሁ፣ እና ምድርንም መሰረትሁ፤ እና በዚህ ያሉት ነገሮች ሁሉ የእኔ ናቸው።”4 ቤተሰቦች፣ ስጋዊ አካላችን እና ህይወታችን እንኳን ሳይቀር በምድር ላይ ያሉት ነገሮች በሙሉ የእግዚአብሄር ናቸው።5
ሁለተኛ መርህ፦ የእግዚአብሄር ፍጥረታት መጋቢ እንደመሆናችን እነርሱን የማክበር እና የመንከባከብ ግዴታ አለብን።
የእግዚአብሄር ልጆች እንደመሆናችን መጋቢ፣ ተንከባካቢ እና ጠባቂ እንድንሆን ትዕዛዝ ተቀብለናል። ጌታ እንዲህ ብሏል ”እያንዳንዱ ሰው ለፍጥረቶቼ ለሰራሁት እና ላዘጋጀሁት የምድር በረከቶች በመጋቢነት ተጠያቂ ይሆንም ዘንድ ፍቃዴ ነውና።”6
የሰማይ አባታችን ምድራዊ ሃብቶችን በራሳችን ነጻ ምርጫ መሰረት እንድንጠቀም ፈቅዷል። ሆኖም ነጻ ምርጫችን የዚህን ዓለም ሀብት ያለ ጥበብና ገደብ ለመጠቀም እንደተሰጠ ፈቃድ ሊወሰድ አይገባም። ጌታ ይህንን ምክር ሰጥቷል “እናም እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለሰው ስለሰጠ እግዚአብሔርን ያስደስተዋል፤ በብልጫ ወይም በግድ ሳይሆን፣ በጥበብ እንደዚህ እንዲጠቀሙባቸው ነውና የተፈጠሩት።”7
ፕሬዚዳንት ራስል ኤም.ኔልሰን በአንድ ወቅት አስተያየት ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል “የመለኮታዊ ፍጥረቱ ተጠቃሚዎች እንደመሆናችን ምን እናድርግ? ምድርን ልንከባከባት፣ ጥበበኛ መጋቢ ልንሆንላት እና ለወደፊቱ ትውልድ ልንጠብቃት ይገባል።”8
ለምድር እና ለተፈጥሮ አካባቢያችን እንክብካቤ ማድረግ እንዲያው ሳይንሳዊ ወይም ፖለቲካዊ አስፈላጊነት ያለው ነገር ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሄር የተሰጠን የተቀደሰ ኃላፊነትም ነው። የደቀመዝሙርነታችን ዋና ክፍልም ነው። ፍጥረቶቻቸውን ሳናከብር እና ሳንወድ የሰማይ አባታችንን እና ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ማክበር እና መውደድ እንችላለን?
ጥሩ መጋቢዎች ለመሆን በጋራ እና በግለሰብ ደረጃ ልናደርጋቸው የምንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። የእኛን የግል ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት እያንዳንዳችን የምድርን የተትረፈረፉ ሀብቶች ይበልጥ በአክብሮት እና በጥንቃቄ ልንጠቀምባቸው እንችላለን። ምድርን ለመንከባከብ ጥረት የሚያደርጉ ማህበረሰቦችን መደገፍ እንችላለን። የእግዚአብሔርን ፍጥረታት የሚያከብሩ የግል የአኗኗር ዘይቤዎችን እና ባህሪያትን መከተል እንዲሁም የራሳችንን የመኖሪያ አካባቢ ይበልጥ የተስተካከለ፣ የሚያምር እና የበለጠ የሚያነሳሳ ማድረግ እንችላለን።9
በእግዚአብሄር ፍጥረታት ላይ ያለብን የመጋቢነት ትልቁ ደረጃ፣ ምድርን ከእኛ ጋር በጋራ የሚጠቀሙትን የሰው ልጆች ሁሉ የመውደድ፣ የማክበር እና የመንከባከብ የተቀደሰ ግዴታን ያካትታል። የእግዚአብሔር ወንድ እና ሴት ልጆች፣ እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን ናቸው እንዲሁም የእነርሱ ዘላለማዊ ደስታ የፍጥረት ስራ ትልቁ አላማ ነው።
ደራሲው አንትዋን ደ ሴንት-ኤክሱፔሪ የሚከተለውን ተናግሯል፦አንድ ቀን በባቡር እየተጓዘ በነበረበት ጊዜ ራሱን ከስደተኞች መካከል ተቀምጦ አገኘው። በአንድ ትንሽ ልጅ ፊት ላይ ባየው የተስፋ መቁረጥ ስሜት በጣም ተነክቶ እንዲህ ብሎ ጮኸ፣ “አዲስ ጽጌረዳ በመራባት በአትክልት ስፍራው ውስጥ ሲበቅል ሁሉም አትክልተኞች ይደሰታሉ። ጽጌረዳውን ይለዩታል፣ ይንከባከቡታል እንዲሁም ያሳድጉታል። ነገር ግን ለሰዎች አትክልተኛ የለም።10
ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ለወንዶች እና ለሴቶች ጓደኞቻችን አትክልተኞች መሆን አይገባንምን? የወንድማችን ጠባቂ አይደለንምን ኢየሱስ ባልንጀሮቻችንን እንደራሳችን እንድንወድ አዝዞናል። 11 ከቃላቱ መረዳት እንደሚቻለው ባልንጀራ የሚለው ቃል የሚያመለከተው የቦታ ቅርበትን ብቻ አይደለም፤ የልብ ቅርበትንም እንጂ። መኖሪያቸው በአቅራቢያችንም ሆነ በሩቅ አገር፣ የፈለቁበት፣ አስተዳደጋቸው ወይም ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን የዚህችን ፕላኔት ነዋሪዎች ሁሉ ያቅፋል።
እንደክርስቶስ ደቀመዝሙርነታችን ሁሉም የምድር ሕዝቦች ሰላምና ስምምነት ይኖራቸው ዘንድ ያለመታከት በጥልቅ ቅንነት የመሥራት ግዴታ አለብን። ዓቅመ ደካሞችን፣ ችግረኞችን እና በስቃይ ላይ ያሉትን ወይም የተጨቆኑትን ሁሉ ከጉዳት ለመከላከል እና መፅናናትን እንዲያገኙ ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን። ከሁሉም በላይ ለሰዎች ልንሰጥ የምንችለው ትልቁ የፍቅር ስጦታ የወንጌልን ደስታ ለእነርሱ ማካፈል እና የተቀደሱ ቃል ኪዳኖችን እና ስርዓቶችን በመፈጸም ወደ አዳኛቸው እንዲመጡ መጋበዝ ነው።
ሶስተኛ መርህ፦ በፍጥረት ስራ እንድንሳተፍ ተጋብዘናል።
መለኮታዊው የፍጥረት ሂደት ገና አልተጠናቀቀም። የእግዚአብሔር ፍጥረታት በየቀኑ ማደጋቸውን፣ መስፋፋታቸውን እና መብዛታቸውን ይቀጥላሉ። የሰማይ አባታችን በመፍጠር ስራው እንድንሳተፍ ግብዣ ማቅረቡ እጅግ በጣም የሚደንቅ ነገር ነው።
ለአምላክ ፍጥረታት አክብሮት እስካሳየን ድረስ ምድርን በምናርስበት ጊዜ ሁሉ ወይም በዚህ ዓለም ላይ የራሳችንን ግንባታዎች ስንጨምር በፍጥረት ሥራ እየተሳተፍን ነው። የእኛ አስተዋፅኦ ፕላኔታችንን የሚያስጌጡ፣ የስሜት ህዋሳቶቻችንን የሚያነቁ እና ህይወታችንን ብሩህ የሚያደርጉ የኪነጥበብ፣ የአርክቴክቸር፣ የሙዚቃ፣ የስነ-ጽሁፍ እና የባህል ስራዎችን በመፈጠር ሊገለጽ ይችላል። ምድርን እና በላዩዋ ላይ ያለውን ህይወት ከጉዳት የሚጠብቁ ሳይንሳዊ እና የህክምና ግኝቶችን በማበርከትም እንሳተፋለን። ፕሬዚዳንት ቶማስ ኤስ. ሞንሰን ይህንን ሃሳብ በነዚህ በሚያምሩ ቃላት አጠቃለውታል፦“ሰው የመፍጠርን ደስታ እና ክብር ያውቅ ዘንድ እግዚአብሔር ሰው ባለው ክህሎት እንዲሰራ … አለምን ሳይጨርስ ተወው።”12
ኢየሱስ ስለመክሊት በተናገረው ምሳሌ ውስጥ ጌታው ከጉዞው ሲመለስ፣ ያተረፉትን እና መክሊታቸውን ያበዙትን ሁለቱን አገልጋዮች አወድሶ ሸልሟል። በተጻራሪው ልዩ መክሊቱን “ያለትርፍ” መሬት ውስጥ የቀበረውን ባሪያ ጠራና ተቀብሎት የነበረውንም ወሰደበት።13
በተመሳሳይም በምድር ፍጥረታት ላይ ያለብን የመጋቢነት ሚና እነርሱን መንከባከብ ወይም መጠበቅ ብቻ አይደለም። ጌታ ለእኛ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ለመባረክ ሲባል በእርሱ መንፈስ ቅዱስ እንደተመራን የሰጠንን ሀብቶች ለማሳደግ እና ለማሻሻል በትጋት እንድንሰራ ይጠብቅብናል።
ከሁሉም የሰው ልጆች ስኬቶች መካከል እንደ ወላጅም ሆነ እንደአስተማሪ፣ ወይም እንደመሪ፣ ወይም በማንኛውም በሌላ ሚና፣ ሕይወትን በመስጠት ወይም ልጅን እንዲማር፣ እንዲያድግ እና እንዲበለጽግ በመርዳት ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ የመፍጠርን ተሞክሮ የሚያክል የለም። ከፈጣሪያችን ጋር በመተባበር ለመንፈሣዊ ልጆቹ ሥጋዊ አካልን ከመስጠት እና ከዚያም ወደ መለኮታዊ አቅማቸው እንዲደርሱ ከመርዳት የበለጠ የተቀደሰ፣ ይበልጥ የሚያስደስት ሆኖም የበለጠ አስቸጋሪ የሆነ መጋቢነት የለም።
አብሮ የመፍጠር ሃላፊነት ህይወት እና የእያንዳንዱ ሰው አካል የተቀደሰ መሆኑን፣ ከእግዚአብሔር በቀር የማንም እንዳልሆነ እንዲሁም እንድናከብረው፣ ከጉዳት እንድንጠብቀው እና እንድንንከባከበው ጠባቂዎች እንዳደረገን ቋሚ አስታዋሽ ሆኖ ያገለግላል። የመዋለድን እና የዘላለም ቤተሰቦችን የመመስረትን ኃይሎች የሚመሩት የእግዚአብሔር ትእዛዛት ለእቅዱ በጣም አስፈላጊ በሆነው በዚህ ቅዱስ መጋቢነት ይመሩናል።
ወንድሞቼ እና እህቶቼ የስጋዊ ሕይወታችንን ገጽታዎች ጨምሮ ሁሉም ነገሮች ለጌታ መንፈሳዊ መሆናቸውን ልናውቅ ይገባል። ምድርን እንዲሁም ወንዶች እና ሴቶች ጓደኞቻቸውን ለሚወዱ እና ለሚንከባከቡ የታላቅ መንፈሳዊ በረከቶች ቃል ኪዳን እንደተገባላቸው እመሰክራለሁ። በዚህ የተቀደሰ መጋቢነት ታማኝ ስትሆኑና ዘላለማዊ ቃል ኪዳኖቻችሁን ስትጠብቁ፣ በእግዚአብሔር እና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ታድጋላችሁ እንዲሁም ፍቅራቸው እና ተፅእኗቸው በህይወታችሁ ውስጥ በብዛት ይሰማችኋል። ይሄ ሁሉ ከእነሱ ጋር ለመኖር እና በሚመጣው ህይወትም ተጨማሪ የመፍጠር ሀይልን14 ለመቀበል ያዘጋጃችኋል።
በዚህ ስጋዊ ህልውና መጨረሻ፣ መምህሩ የእርሱን ፍጥረታት እንዴት እንደተንከባከብን እንዲሁም ስለተቀደሰው መጋቢነታችን ገለጻ እንድንሰጥ ይጠይቀናል። ያን ጊዜ “መልካም፣ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፥ በጥቂቱ ታምነሃል፣ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” የሚሉትን የእርሱን አፍቃሪ ቃላት ለልባችን ሲያንሾካሹክ እንድንሰማ እጸልያለሁ።15 በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።