አጠቃላይ ጉባኤ
ፅዮን ሆይ፣ ሀይልሽን ልበሺ
የጥቅምት 2022 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


13:57

ፅዮን ሆይ፣ ሀይልሽን ልበሺ

እያንዳንዳችን በስጋዊ እና በመንፈሳዊ ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች በቅንነት እና በጸሎት መንፈስ መገምገም አለብን።

ምሳሌዎች የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ የተዋጣላቸው የማስተማሪያ አቀራረቦቸ የተለዩ መገለጫዎች ናቸው። በቀላሉ ለመግለጽ የአዳኙ ምሳሌዎች መንፈሳዊ እውነቶችን ከቁሳዊ ነገሮች እና ከምድራዊ ተሞክሮዎች ጋር ለማነጻጸር የሚያገለግሉ ታሪኮች ናቸው። ለምሳሌ የአዲስ ኪዳን ወንጌሎች የእግዚአብሄርን መንግስት ከሰናፍጭ ፍሬ፣1 ዋጋዋ እጅግ ከበዛ ዕንቁ፣2 ከወይን አትክልት ሰራተኞች እና ከባለቤቱ፣3 ከአስር ደናግላን4 እና ከሌሎች ከብዙ ነገሮች ጋር በሚያመሳስሉ ትምህርቶች የተሞላ ነው። ጌታ በገሊላ በሰጠው ከፊል አገልግሎቱ ወቅት “ያለምሳሌ ግን [እንዳልነገራቸው]”5ቅዱሳት መጻህፍት ይህን ያመለክታሉ።

ሊተላለፍ የታሰበው የምሳሌው ትርጉም ወይም መልዕክት በተለምዶ እንደሚደረገው በግልጽ አልተቀመጠም። ከዚያ ይልቅ ታሪኩ ተቀባዩ በእግዚአብሔር ላይ ባለው ወይም ባላት እምነት፣ የግል መንፈሳዊ ዝግጅት እና ለመማር ባለ ፍላጎት ልክ መለኮታዊ እውነትን ያስተላልፋል። |ስለዚህ አንድ ግለሰብ ምሳሌው የያዛቸውን እውነቶች ለማወቅ የመምረጥ ነጻነትን መጠቀም እና በንቃት “መጠየቅ፣ መፈለግ እና ማንኳኳት”6 አለበት።

አሁን ንጉሡ ስላዘጋጀው የጋብቻ ስነሥርዓት ድግስ ምሳሌ ጠቀሜታ ስናስብ መንፈስ ቅዱስ ለእያንዳንዳችን እንዲገልጥልን አጥብቄ እጸልያለሁ።

ንጉሡ ያዘጋጀው የጋብቻ ስነሥርዓት ድግስ

“ኢየሱስም … በምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ፣

“መንግስተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉስን ትመስላለች።

“የታደሙትንም ወደ ሰርጉ ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ ሊመጡም አልወደዱም።

“ደግሞ ሌሎቹንም ባሮቹን ልኮ፥ የታደሙትን፥ እነሆ ፥ድግሱን አዘጋጀሁ፥ ኮርማዎቼን እና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፥ ሁሉም ተዘጋጅቷል ፥ወደ ሰርጉ ኑ፥ በሏቸው አለ።

“እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ።”7

በጥንት ጊዜ፥ በአይሁድ ሕይወት ውስጥ በጣም አስደሳች ከሆኑት ወቅቶች አንዱ፥ ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንታት የሚቆየው የሰርግ በዓል ነበር። እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ሰፊ እቅድ ማውጣትን ይጠይቃል፤ ስለዚህም እንግዶች በጣም ቀደም ብሎ ተነግሯቸዋል፤ በበዓሉ መክፈቻ ቀንም አስታዋሽ ተልኳል። ንጉሥ ለአገሩ ሰዎች እንዲህ ባለው ሠርግ ላይ እንዲገኙ የሚያደርገው ግብዣ በመሠረቱ እንደ ትዕዛዝ ይቆጠር ነበር። ሆኖም፣ በዚህ ምሳሌ ውስጥ ከተጠቀሱት እንግዶች አብዛኞቹ አልመጡም።8

“በንጉሱ ድግስ መካፈልን አሻፈረኝ ማለት በሉዓላዊ አገዛዙ እና በልጁ ንጉሳዊ ስልጣን እና በግል ክብራቸው ላይ ሆን ተብሎ የተደረገ አመጽ ነው። አንዱ ሰው ወደ እርሻው እንዲሁም ሌላው ወደ [ንግድ ፍላጎቱ]9 መመለሳቸው ቅድሚያ ስለሚሰጣቸው ነገሮች ያላቸውን የተሳሳተ አረዳድ እና የንጉሱን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ችላ ማለታቸውን ያሳያል።10

ምሳሌው ይቀጥላል።

“በዚያን ጊዜ ባሮቹን፥ ሰርጉስ ተዘጋጅቷል፥ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ።

“እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያው ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ፥ አለ።

“እነዚያም ባሮች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንም በጎዎችንም ሰበሰቡ፥ የሰርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት”11

በዚያ ዘመን በነበረው ልማድ መሰረት የሠርጉ ድግስ አዘጋጅ —በዚህ ምሳሌ ውስጥ ንጉሡ—ለሠርጉ እንግዶች ልብስ ይሰጥ ነበር። እነዚህ የሠርግ ልብሶች ሁሉም ተሳታፊዎች የሚለብሷቸው ሲሆን ቀላል እና የመሳብ ባህርይ የሌላቸው ልብሶች ነበሩ። በዚህ መንገድ የማዕረግ እና የኑሮ ደረጃ ልዩነቶች ይወገዱ ነበር እንዲሁም በበዓሉ ላይ ያሉ ሁሉም ሰዎች እኩል የሆኑ ያህል መቀላቀል ይችሉ ነበር።12

በሠርጉ ላይ እንዲገኙ ከመንገዱ የተጋበዙት ሰዎች ለዝግጅቱ የሚሆን ተገቢ ልብስ ለመግዛት ጊዜም ሆነ ገንዘብ አያገኙም ነበር። በዚህም ምክንያት ንጉሱ ከራሱ አልባሳት ውስጥ ለእንግዶቹ የሰጠ ሳይሆን አይቀርም። እያንዳንዱ ሰው የንጉስ ልብስ የመልበስ ዕድል ተሰጥቶት ነበር።13

ንጉሱም ወደ ሰርጉ አዳራሽ እንደገባ ታዳሚውን ቃኘት ቃኘት አደረገ በዚያው ቅጽበትም አንድ ጎልቶ የሚታይ እንግዳ የሰርግ ልብስ እንዳልለበሰ አስተዋለ። ሰውየውን ወደፊት አመጡት፤ ከዚያም ንጉሱ “ወዳጄ ሆይ፥ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? ሲል ጠየቀ። እርሱም ዝም አለ።”14 በመሰረቱ ንጉሱ “የተሰጠህን የሠርግ ልብስ ለምን አልለበስክም?” ሲል ነበር የጠየቀው።15

ሰውየው በግልጽ ለዚህ ልዩ ዝግጅት የሚገባውን ዓይነት ልብስ አልለበሰም ነበር፤ “እናም እርሱም ዝም አለ” የሚለው ሃረግ ሰውየው የሚያመካኝበት ነገር እንዳልነበረው ያሳያል።16

ሽማግሌ ጄምስ ኢ. ታልማጅ ስለሰውየው ድርጊት አስፈላጊነት ይህንን አስተማሪ አስተያየት ሰጥተዋል፦ “ልብስ ያልለበሰው እንግዳ በቸልተኝነት፣ ሆን ብሎ አክብሮት በማጓደል ወይም ሌላ የባሰ ጥፋት በማጥፋቱ እንደሆነ ከሁኔታው ግልጽ ነው። መጀመሪያ ላይ ንጉሱ በቅንነት ስላሰበ ነበር ሰውዬው የሰርግ ልብስ ሳይለብስ እንዴት እንደገባ ብቻ የጠየቀው። ሰውየው ለየት ስላለው አለባበሱ ማስረዳት ቢችል ወይም ተገቢ የሆነ ምክንያት ቢኖረው ኖሮ በእርግጠኝነት ይናገር ነበር፤ ነገር ግን ዝም እንዳለ ተነግሮናል። የንጉሱ ጥሪ አገልጋዮቹ አግኝተዋቸው ለነበሩት ሁሉ በነጻነት ተላልፎ ነበር፤ ሆኖም እያንዳንዳቸው ወደንጉሳዊው ቤተመንግስት በበሩ መግባት ነበረባቸው፤ እንዲሁም ንጉሡ በአካል በሚገኝበት እግብዣው ክፍል ከመድረሳቸው በፊት፣ እያንዳንዳቸው በተገቢ ሁኔታ ይለብሳሉ፤ ሳያሟላ በሌላ መንገድ የገባ ሰው ግን በመግቢያው ላይ ባሉት ጠባቂዎች በኩል ስላላለፈ ሰርጎ ገብ ይሆን ነበር።”17

ክርስቲያን ደራሲ የሆኑት ጆን ኦ. ሪድ፣ ሰውዬው የሠርግ ልብሱን ለመልበስ አሻፈረኝ ማለቱ “ለንጉሱም ሆነ ለልጁ በግልጽ አክብሮት ያለመኖር“ ባህርይ ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል። በቀላሉ፣ የሰርግ ልብስ አጥቶ አልነበረም፤ ከዚያ ይልቅ አለመልበስን መርጧል። በዓመፀኝነት ለዝግጅቱ ተገቢ የሆነ ልብስ መልበስን አሻፈረኝ ብሏል። የንጉሱ ምላሽ ፈጣን እና ቆራጥ ነበር፦“እጁን እና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”18

ንጉሱ በሰውየው ላይ ያሳለፈው ፍርድ በዋነኝነት የተመሰረተው የሠርግ ልብስ አለመኖሩ ላይ አልነበረም—ነገር ግን “በርግጥ እርሱ ላለመልበስ ወስኖ የነበረ በመሆኑ ነው። ሰውዬው … በሠርጉ ድግስ ላይ የመገኘትን ክብርን ፈልጎ የነበረ ቢሆንም የንጉሡን ልማድ መከተል ግን አልፈለገም ነበር። ነገሮችን በራሱ መንገድ ማድረግ ፈልጎ ነበር። ተገቢ ልብስ አለመኖሩ በንጉሱ እና በመመሪያዎቹ ላይ ያለውን ውስጣዊ አመጽ ይገልጻል።”19

ብዙዎች ተጠርተዋል፣ ግን የተመረጡት ጥቂቶች ናቸው።

ከዚያም ምሳሌው “ብዙዎች ተጠርተዋል፣ ግን የተመረጡት ጥቂቶች ናቸው” በሚለው ሰርስሮ የሚገባ ጥቅስ ያጠቃልላል።20

ጆሴፍ ስሚዝ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ በሚገኘው በዚህ የማቴዎስ ወንጌል ጥቅስ ላይ የሚከተለውን ማሻሻያ ማድረጉ የሚስብ ነው፦ “ብዙዎች ተጠርተዋል፣ ግን የተመረጡት ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ ሁሉም የሠርጉ ልብስ የላቸውም።”21

በሠርጉ ላይ ለመታደም የቀረበው ግብዣ እና በድግሱ ላይ ለመካፈል የሚደረገው ምርጫ ተያያዥነት አላቸው ሆኖም የተለያዩ ናቸው። ግብዣው የተደረገው ለሁሉም ወንዶች እና ሴቶች ነው። አንድ ግለሰብ ግብዣውን ተቀብሎ በበዓሉ ላይ ሊታደምም ይችላል—ሆኖም ለመታደም ያልተመረጠ ሊሆንም ይችላል፤ ምክንያቱም እሱ ወይም እሷ በጌታ በኢየሱስ እና በመለኮታዊ ፀጋው እምነትን የመለወጥ ተስማሚ የሰርግ ልብስ የላቸውም። ስለዚህ የእግዚአብሔር ጥሪም ለዚያ ጥሪ የምንሰጠው ግለሰባዊ ምላሽም አለን፤ እናም ብዙዎች ተጠርተዋል፣ ግን የተመረጡት ጥቂቶች ናቸው።22

መመረጥ ለእኛ ብቻ ተለይቶ የተሰጠ አይደለም። ከዚያ ይልቅ እናንተ እና እኔ በመጨረሻ የመምረጥ ነጻነታችንን በጽድቅ በመጠቀም የተመረጥን ለመሆን መምረጥ እንችላለን።

እባካችሁ በሚከተለው የተለመደ የትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ጥቅስ ውስጥ የተመረጡት የሚለውን ቃል አጠቃቀም አስተውሉ፦

“እነሆ፣ ብዙዎች ተጠርተዋል፣ ነገር ግን የተመረጡትጥቂቶች ናቸው። እና ያልተመረጡትስለምንድን ነው?

“ምክንያቱም ልባቸውን በአለም ነገሮች ላይ ስለሚያደርጉ እና በሰዎች ይሞገሱ ዘንድ ስለሚነሳሱ [ነው]።”23

እነዚህ ጥቅሶች ያላቸው አንድምታ በጣም ቀጥተኛ እንደሆነ አምናለሁ። እግዚአብሔር አንድ ቀን ስማችንን እንዲያካትት ተስፋ ልናደርግ የሚገባን የተወዳጆች ስም ዝርዝር የለውም። እሱ “የተመረጡትን” በጥቂቶች ብቻ የተገደበ እንዲሆን አያደርግም። ከዚያ ይልቅ፣ የእኛ ልቦች፣የእኛ ፍላጎቶች፣የእኛ የቅዱስ ወንጌሉን ቃል ኪዳኖች እና ስርዓቶች ማክበር፣የእኛ ትእዛዛትን መታዘዝ እንዲሁም ከሁሉም በላይ የአዳኙ የቤዛነት ጸጋ ከእግዚአብሔር የተመረጡት ውስጥ እንደ አንዱ መቆጠር አለመቆጠራችንን ይወስናል።24

“ለመጻፍ፣ ልጆቻችንን እናም ደግሞ ወንድሞቻችንን በክርስቶስ እንዲያምኑና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ለማሳመን በትጋት እንሰራለንና፤ ምክንያቱም በጸጋ የምንድነው የምንችለውን ካደረግን በኋላ እንደሆነ እናውቃለንና።”25

በእለት ተእለት ሩጫ የበዛበት ህይወታችን እና በምንኖርበት በአሁኑ አለም ሁካታ ውስጥ ደስታን፣ ብልጽግናን፣ ታዋቂነትን እና እውቅናን ዋነኛ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች በማድረግ በጣም አስፈላጊ ለሆኑት ዘላለማዊ ነገሮች ትኩረት ልንነፍግ እንችላለን። ለአጭር ጊዜ “በዓለም ነገር” እና “በዓለም ክብር” መጠመዳችን የመንፈሳዊ ብኩርና መብታችንን ከምስር ወጥ ባነሰ ነገር እንድናጣ ወደማድረግ ሊመራን ይችላል።26

የተስፋ ቃል እና ምስክርነት

በብሉይ ኪዳን ነቢይ በሐጌ አማካኝነት ጌታ ለሕዝቡ የሰጠውን ምክር እደግመዋለሁ፦አሁንም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ።”27

የሰማይ አባት እና አዳኙ ሊሰጡን ፍቃደኛ የሆኑትን የተትረፈረፉ በረከቶች እንዳናገኝ በህይወታችን ውስጥ እንቅፋት የሆኑብንን ነገሮች ለመለየት እያንዳንዳችን በስጋዊ እና በመንፈሳዊ ቅድሚያ ስለምንሰጣቸው ነገሮች በቅንነት እና በጸሎት መገምገም አለብን። መንፈስ ቅዱስ ራሳችንን፥ በትክክል እንደሆንነው አድርገን እንድናይ ይረዳናል።28

የሚያይ ዓይን እና የሚሰማ ጆሮ የመንፈሳዊ ስጦታን በተገቢ ሁኔታ ስንፈልግ29 ከህያው ጌታ ጋር ያለንን የቃል ኪዳን ግንኙነት አቅም እና አስተዋይነት በማጠናከር በረከት እንደምናገኝ ቃል እገባለሁ። በተጨማሪም በሕይወታችን እግዚአብሄርን የመፍራት ኃይል እንቀበላለን፤26—በመጨረሻም በጌታ ድግስ ላይ እንጠራለን ከዚያም እንመረጣለን።

“ፅዮን ሆይ ንቂ፣ ንቂ ሀይልሽን ልበሺ።“31

“ፅዮን በውበት፣ እና በቅድስና፣ ልትልቅ ይገባል፤ ድንበሮችዋም ሊሰፉ፣ ካስማዎቿም ሊጠናከሩ፣ አዎን፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ፅዮን ልትነሳ እና የውበት ልብሷን ልትለብስ ይገባል።“32

የዘላለም አባታችንን የእግዚአብሔርን እና የተወደደ ልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት እና ሕያውነት እውነታ ምስክርነቴን በደስታ እናገራለሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እና ቤዛችን እንደሆነ እንዲሁም ህያው እንደሆነ እመሰክራለሁ። በተጨማሪም አብ እና ወልድ ለወጣቱ ጆሴፍ ስሚዝ እንደተገለጡለት ያም በኋለኛው ቀናት የአዳኙን ወንጌል ዳግም መመለሰ እንዳስጀመረ እመሰክራለሁ። የሚያዩ ዓይኖችን እና የሚሰሙ ጆሮዎችን እንድንሻ በእነሱም እንድንባረክ እፀልያለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም፣ አሜን።