አጠቃላይ ጉባኤ
በእርሱ አማካኝነት ከባድ ነገሮችን ማከናወን እንችላለን
የጥቅምት 2022 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


በእርሱ አማካኝነት ከባድ ነገሮችን ማከናወን እንችላለን

በአስቸጋሪ ጊዜያት በጌታ ላይ እምነትን ከተለማመድን በደቀመዝሙርነታችን እናድጋለን።

አዳኙ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ዓይነ ስውር የነበረን ሰው ተመለከተ። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲህ ጠየቁ፣ “መምህር ሆይ፣ ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጥያት የሠራው ይህ ሰው ወይም ወላጆቹ ናቸው?”

የአዳኙ ጽኑ፣ አፍቃሪ እና ትሁት ምላሽ ችግሮቻችንን እንደሚውቅ ያረጋግጥልናል፦“የእግዚአብሔር ሥራዎች በእርሱ እንዲገለጡ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ አልበደሉም።”1

አንዳንድ ፈታኝ ሁኔታዎች ሆነ ብሎ ባለመታዘዝ ምክንያት ሊመጡ የሚችሉ ሲሆን አብዛኞቹ የሕይወት ፈተናዎች የሚመጡት በሌሎች ምክንያቶች እንደሆነ እናውቃለን። የፈተናዎቻችን ምንጮች ምንም ይሁኑ ምን ወርቃማ የማደግ እድል ሊሆኑ ይችላሉ።

ቤተሰባችን ከህይወት መከራ አልዳነም። በማደግ ላይ ሳለሁ ትልልቅ ቤተሰቦችን አደንቅ ነበር። በተለይ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል እያለሁ በእናቴ በኩል አጎቴ በሆነው በሳርፎና በሚስቱ አማካኝነት በታኮራዲ ጋና ውስጥ ቤተክርስቲያኗን ባገኘሁበት ጊዜ እንደዚህ አይነት ቤተሰቦች ይማርኩኝ ነበር።

ሃና እና እኔ ትዳር በመሰረትን ጊዜ ብዙ ልጆችን በመውለድ እንደምንባረክ የሚጠቁመውን የፓትርያርክ በረከታችንን ፍጻሜ ፈልገን ነበር። ሆኖም ሶስተኛው ወንድ ልጃችን ከመወለዱ በፊት ሃና ሌላ ልጅ ልትወልድ እንደማትችል በህክምና ተረጋገጠ። ደግነቱ ኬኔት የእርሱንም ሆነ የእናቱን ሕይወት አደጋ ውስጥ በሚከት ሁኔታ ውስጥ ቢወለድም በሰላም ወደዚህ ዓለም መጣ፤ እናቱም አገገመች። በቤተክርስቲያን መሳተፍን፣ የዕለት ተዕለት ጸሎትን፣ የቅዱስ ጽሁፍ ጥናትን፣ የቤት ምሽትን እና ሁሉን ዓቀፍ በሆኑ የመዝናኛ እንቅስቃሴዎች መሳተፍን ጨምሮ በቤተሰባችን ህይወት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ መሳተፍ ቻለ።

ከአንድ ትልቅ ቤተሰብ በምንጠብቀው ነገር ላይ ማስተካከያ ማድረግ የነበረብን ቢሆንም ተወዳጅ ከሆኑት ሦስት ልጆቻችን ጋር “ቤተሰብ፦ ለዓለም የተላለፈ አዋጅ” የሚለውን ትምህርት ተግባራዊ ማድረጋችን የሚያስደስት ነበር። እነዚያን ትምህርቶች መከተሌ እያደገ ለመጣው እምነቴ ትልቅ ትርጉም ሰጥቶኛል።

አዋጁ እንደሚለው “በወንድ እና በሴት መካከል የሚደረግ ጋብቻም ለዘላለማዊ እቅዱ በጣም አስፈላጊ ነው። ልጆችም በጋብቻ ጥምረቶች ውስጥ የመወለድ፣ እናም የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን በሙሉ ታማኝነት በሚያከብሩ አባት እና አናት የማደግ መብት አላቸው።”2 እነዚህን መርሆዎች በተግባር ላይ ስናውል፣ እንባረከ ነበር።

ነገር ግን በአንድ የሳምንቱ መጨረሻ የእረፍት ቀን የካስማ ፕሬዘዳንት ሆኜ ሳገለግል በነበረበት ወቅት ምናልባት ወላጆች ሊያጋጥማቸው ከሚችለው ሁሉ የከፋ ፈተና አጋጠመን። ቤተሰባችን ከቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ መልስ ለምሳ ተሰብስበን ነበር። ከዚያም ሦስቱ ወንድ ልጆቻችን በግቢያችን ውስጥ ሊጫወቱ ወጡ።

ባለቤቴ የሆነ ችግር ተፈጥሮ ሊሆን እንደሚችል በተደጋጋሚ ተሰምቷት ነበር። እቃዎቹን እያጠብን እያለን ልጆቹን ወጣ ብዬ እንዳይ ጠየቀችኝ። ሲጫወቱ የሚያወጡት የደስታ ድምፅ ይሰማን ስለነበር ደህና እንደሆኑ ተሰምቶኝ ነበር።

በመጨረሻ ሁለታችንም ልጆቻችንን ለማየት ስንሄድ የ18 ወሩ ትንሽ ልጅ ኬኔት ወንድሞቹ ሳያዩት በባልዲ ውሃ ውስጥ ራሱን ማዳን በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ገብቶ አገኘነውና ደነገጥን። በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ወሰድነው ሆኖም ህይወቱን ለማትረፍ የተደረገው ሙከራ ሁሉ አልተሳካም ነበር።

በዚህ ምድራዊ ህይወት ውስጥ ውድ ልጃችንን የማሳደግ እድል ስለማይኖረን ጥልቅ ሃዘን ገባን። ኬኔት ለዘለአለም የቤተሰባችን አካል እንደሚሆን ብናውቅም ጥሪዬን ለማጉላት የምችለውን ያህል እያደረኩ እያለሁ አምላክ ይህ አሳዛኝ ነገር በእኔ ላይ እንዲደርስ ለምን እንደፈቀደ ራሴን ስጠይቅ አገኘሁት። ቅዱሳንን የማገልገል አንዱን ግዴታዬን ተወጥቼ ገና ወደ ቤት መምጣቴ ነበር። እግዚአብሔር አገልግሎቴን አይቶ ልጃችንን እና ቤተሰባችንን ከዚህ አሳዛኝ ክስተት ማዳን ያልቻለው ለምንድነው? ስለእሱ ይበልጥ ባሰብኩኝ ቁጥር ይበልጥ መራር እየሆንኩኝ ሄድኩኝ።

ባለቤቴ ለተሰማት የመንፈስ ምሪት ቶሎ ምላሽ ባለመስጠቴ በፍጹም አልወቀሰችኝም። ነገር ግን ህይወትን የሚቀይር ትምህርት ተማርኩኝ እንዲሁም መቼም የማይሻሩ ሁለት ደንቦችን አወጣሁኝ።

ደንብ 1፦ የባለቤትህን የመንፈስ ምሪት አዳምጥ እንዲሁም ተከተል።

ደንብ 2፦ በማንኛውም ምክንያት እርግጠኛ ካልሆንክ ደንብ 1ን ተመልከት።

ምንም እንኳን ልምዳችን ቅስም ሰባሪ ቢሆንና ማዘናችንን ብንቀጥልም ሸክማችን ከጊዜ በኋላ ተቃሏል።3 እኔና ባለቤቴ ከደረሰው ጥፋት የተለየ ትምህርት ተምረናል። በቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖቻችን አንድነት እና ጥምረት ተሰምቶናል፤ በቃል ኪዳኑ ውስጥ ስለተወለደ በመጪው ዓለም ኬኔት የእኛ ነው ማለት እንደምንችል እናውቃለን። በተጨማሪም ሌሎችን ለማገልገል እና በህመማቸው ላይ አጽንዖት ለመስጠት የሚያስችል አስፈላጊ ልምድ አግኝተናል። በጌታ ላይ እምነትን በመለማመዳችን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምሬታችን እንደጠፋ እመሰክራለሁ። ልምዳችን ከባድ እንደሆነ ነው፤ ሆኖም ትኩረታችንን በእርሱ ላይ ካደረግን “[ሃይልን በሚሰጠን] በክርስቶስ ሁሉን ማድረግ እንደምንችል” እንደሃዋርያው ጳውሎስ ተምረናል።4

ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ “የህይወታችን ትኩረት በእግዚአብሔር የደህንነት እቅድ … እና በኢየሱስ ክርስቶስና በወንጌሉ ላይ ሲሆን፣ በህይወታችን ከተከሰተውም ወይም ካልተከሰተውም ሁኔታ ባሻገር ደስታ ሊሰማን ይችላል።” አክለውም “ደስታ ከሱና በሱ ምክንያት ይመጣል” ብለዋል።5

በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ስንሆን ደስ ሊለን እና በሰላም ልንሞላ እንችላለን። በአዳኙ እና በኃጢያት ክፍያው ሳቢያ የሚሰማን ፍቅር በፈተናችን ጊዜያት ታላቅ ጉልበት ይሆነናል። “በህይወት ሚዛናዊ ያልሆኑ [እና አስቸጋሪ] ነገሮች በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በኩል ትክክል ለመሆን ይችላሉ።”6 እንዲህም አዝዟል፣ “በአለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ አለምን አሸንፌዋለሁ።”7 በምድራዊ ህይወት ማንኛውም ዓይነት ህመም፣ በሽታ እና ፈተናዎች ቢገጥሙን እንድንጸና ሊረዳን ይችላል።

እንደኤርምያስ፣ ኢዮብ፣ ጆሴፍ ስሚዝ እና ኔፊ ስላሉ ከምድራዊ ቸግሮች እና ፈተናዎች ስላልዳኑ ታላላቅ እና የተከበሩ መሪዎች ብዙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ታሪኮችን እናገኛለን። አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳን ጌታን መታዘዝን የተማሩ ስጋ ለባሽ ነበሩ።8

በሊበርቲ እስር ቤት በነበረበት አስፈሪ ቀናት ጆሴፍ ስሚዝ “እግዚአብሔር ሆይ፣ የት ነህ? እና የተሰወርክበትን ስፍራ የሚሸፍነው ድንኳን የት ነው?”9ሰሲለል ተጣርቷል። ጌታ በመልካም መጽናትን ለጆሴፍ አስተማረው10 እንዲሁም ቢጸና እነዚህ ነገሮች ሁሉ ልምድ አንደሚሰጡት እና ለእርሱም መልካም እንደሚሆንለት ቃል ገባለት።11

ስለራሴ ልምዶች ሳስብ አንዳንድ ምርጥ ትምህርቶቼን የተማርኩት በሕይወቴ ውስጥ ከምቾት ክልሌ ባወጡኝ አስቸጋሪ ጊዜያት ሳቢያ እንደሆነ እገነዘባለሁ። አዲስ እንደተለወጠ ሰው በሴሚናሪ ስለቤተክርስቲያኗ እየተማርኩኝ በነበረበት በወጣትነቴ እና በሙሉ ጊዜ የሚስዮናዊ አገልግሎቴ ወቅት ያጋጠሙኝ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዲሁም በትምህርቴ፣ ጥሪዎቼን ለማጉላት ጥረት በማደርግበት እና ቤተሰብ በማስተዳድርበት ወቅት ያጋጠሙኝ ተግዳሮቶች ለወደፊቱ ጊዜ አዘጋጅተውኛል። በጌታ በማመን ለአስቸጋሪ ሁኔታዎች ይበልጥ በደስታ ምላሽ በሰጠሁ ቁጥር በደቀመዝሙርነቴ አድጋለሁ።

በቀጭኑና በጠባቡ መንገድ ከገባን በኋላ በሕይወታችን ውስጥ ያሉ ከባድ ነገሮች ሊያስደንቁን አይገባም።12 ኢየሱስ ክርስቶስ “ከተቀበለው መከራ መታዘዝን“ ተማረ።13 በተለይም በአስቸጋሪ ጊዜያችን እርሱን ስንከተል ይበልጥ እርሱን ወደመምሰል ማደግ እንችላለን።

በቤተመቅደስ ውስጥ ከጌታ ጋር ከምንገባቸው ቃል ኪዳኖች አንዱ የመስዋዕት ህግን መኖር ነው። መስዋዕት ሁልጊዜም የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ክፍል ነበር። እስከዛሬ በምድር ላይ ለኖሩት ወይም ወደፊት ለሚኖሩት ሁሉ የቀረበውን ታላቁን የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕት የሚያስታውስ ነው።

ምስል
የሽማግሌ ሞሪሰን ሚስዮኖች

ጌታ ሁል ጊዜ የጽድቅ ፍላጎታችንን እንደሚሰጠን አውቃለሁ። በፓትርያርክ በረከቴ ውስጥ ቃል የተገቡልኝን ብዙ ልጆች ታስታውሳላችሁ? ያ በረከት እየተፈፀመ ነው፡፡ ባለቤቴ እና እኔ ከ25 ከሚበልጡ አገራት ከመጡ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሚስዮናውያን ጋር በጋና ኬፕ ኮስት ሚስዮን አገልግለናል፡፡ ቃል በቃል ከአብራካችን የወጡ ልጆቻችን የሆኑ ያህል ለእኛ ውድ ናቸው።

በአስቸጋሪ ጊዜያት በጌታ ላይ እምነትን ከተለማመድን በደቀመዝሙርነታችን እንደምናድግ እመሰክራለሁ። ይህን ስናደርግ በምህረቱ ያበረታናል፤ እንዲሁም ሸክማችንን እንድንሸከም ይረዳናል። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

አትም