አጠቃላይ ጉባኤ
ቀንበሩም ልዝብ ሸክሙም ቀሊል ነው።
የጥቅምት 2022 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


10:39

ቀንበሩም ልዝብ ሸክሙም ቀሊል ነው።

በምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው የሰማይ አባት ልጅ እንደሆነ እና እርሱም እያንዳንዱን እንደሚወድ እናስታውስ።

ታሪኩ ካሲ የተባለች ተወዳጅ ወፍ አዳኝ ውሻ ስለነበረችው ጃክ ስለተባለ አንድ ሰው የሚናገር ነው። ጃክ በካሲ በጣም ኩራት ይሰማው ነበር እንዲሁም ብዙ ጊዜ ብቃት ያላት ውሻ እንደሆነች በኩራት ይናገር ነበር። ይህንን በተግባር ለማሳየት ጃክ አንዳንድ ጓደኞቹን ካሲ ስራዋን እንዴት እንደምትሰራ እንዲመለከቱ ጋበዛቸው። ጃክ ወደ አደን ክለቡ ከደረሰ በኋላ ለመመዝገብ ወደ ውስጥ ሲገባ ካሲ ዞር ዞር እንድትል ለቀቃት።

የፕሮግራሙ መጀመሪያ ሰዓት ሲደርስ ጃክ የካሲን አስደናቂ ችሎታዎች ለማሳየት ቋምጦ ነበር። ነገር ግን ካሲ እንግዳ ባህርይ እያሳየች ነበር። ብዙውን ጊዜ በፈቃደኝነት እንደምታደርገው የትኛውንም የጃክ ትዕዛዛት አልታዘዘችም ነበር። ማድረግ የፈለገችው ነገር ቢኖር አጠገቡ መሆን ብቻ ነበር።

ጃክ በካሲ ተስፋ ቆረጠ እንዲሁም ሃፍረት እና ንዴት ተሰማው፤ ብዙም ሳይቆይ እንዲሄዱ ሐሳብ አቀረበ። ካሲ ወደ ጭነት መኪናው ላይ እንኳን አልዘለለችም ነበር፣ ስለዚህም ጃክ ትዕግሥት በማጣት ብድግ አድርጎ ከኋላዋ ወደ ውሻ ቤቱ ውስጥ ገፋት። አብረውት የነበሩት በውሻው ባህሪ የተነሳ እቤት እስኪደርስ ድረስ ስለተሳለቁበት በንዴት ጦፈ። ካሲ ለምን መጥፎ ባህሪ እያሳየች እንደነበር ጃክ ሊረዳ አልቻለም ነበር። በደንብ ሰለልጥና ነበር እንዲሁም የቀድሞ ሙሉ ፍላጎቷ እሱን ማስደሰትና ማገልገል ነበር።

ሁል ጊዜ እንደሚያደርገው እቤት እንደደረሱ ጃክ የተጎዳችው፣ የተፋቀችው ነገር እንዳለ ወይም መዥገር ይዟት እንደሆነ ለማየት ካሲን ማገላበጥ ጀመረ። እጁን በደረቷ ላይ ሲያደርግ እርጥበት ያለው ነገር ተሰማው እንዲሁም እጁ በደም እንደተሸፈነ አወቀ። በካሲ የደረት አጥንት በሰተቀኝ ረጅም እና ሰፊ የሆነ ቁስል ሲያገኝ ኀፍረት እና ጥልቅ የሆነ ድንጋጤ ተሰማው። በቀኝ የፊት እግሯ ላይም ሌላ አገኘ፤ ይህም እንዲሁ አጥንቷ ላይ ነው።

ጃክ ካሲን አቅፎ ማልቀስ ጀመረ። የተሳሳተ ፍርድ በመስጠቱ እና እንደዚያ ስላያት የተሰማው ሃፍረት ከባድ ነበር። ካሲ ጉዳት ደርሶባት ስለነበር በቀኑ መጀመሪያ ላይ ያልተለመደ ድርጊት ስታደርግ ነበር። ህመሟ፣ ስቃይዋ እና ቁስሏ በባህርይዋ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር። ጃክን የመታዘዝ ፍላጎት ከማጣት ወይም ለእሱ ፍቅር ካለመኖር ጋር ምንም ግንኙነት አልነበረውም።1

ይህንን ታሪክ የሰማሁት ከዓመታት በፊት ነበር እናም በፍጹም አልረሳሁትም። ምን ያህል የቆሰሉ ግለሰቦች በዙሪያችን አሉ። በደንብ ገብቶን ቢሆን ኖሮ በምንሰጠው ፍርድ ሸክማቸው ላይ ከመጨመር ይልቅ ርህራሄ ለማሳየት እና ለመርዳት የምንፈልጋቸው የነበሩ በውጫዊ መልካቸው እንዲሁም ባደረጉት ወይም ባላደረጉት ድርጊት ላይ ተንተርሰን ሌሎች ላይ ምን ያህል ጊዜ እንፈርዳለን?

በዚህ ጉዳይ በሕይወቴ ብዙ ጊዜ አጥፍቻለሁ፣ ነገር ግን በግል ተሞክሮዎቼ አማካኝነት እና የብዙ ሰዎችን የሕይወት ልምድ ሳዳምጥ ጌታ በትዕግስት አስተምሮኛል። ብዙ ጊዜውን ሌሎችን በፍቅር በማገልገል ያሳለፈውን የውድ አዳኛችንን ምሳሌ የበለጠ አድንቂያለሁ።

የሁሉም ታናሽ የሆነችው የሴት ልጄ የሕይወት ተሞክሮ ትንሽ ልጅ እያለች ጀምሮ የነበሩባትን ስሜታዊ የጤና ችግሮች ያካትትታል። በመላው ህይወቷ ወደፊት መቀጠል እንደማትችል ሆኖ የተሰማት ብዙ ጊዜያት ነበሩ። በእነዚያ ጊዜያት ከአጠገቧ በመቀመጥ፣ እርሷን በማዳመጥ፣ ከእርሷ ጋር በማልቀስ፣ እንዲሁም ልዩ ስጦታዎችን፣ መንፈሳዊ ግንዛቤዎችን እና የጋራ የፍቅር ግንኙነቶችን በማጋራት ከአጠገቧ ለነበሩት ምድራዊ መላዕክት ለዘላለም አመስጋኞች ነን። በእንደዚህ ዓይነት አፍቃሪ ሁኔታዎች ውስጥ ብዙውን ጊዜ ከሁለቱም በኩል ሸክሞች ይቃለላሉ።

ሽማግሌ ጆሴፍ ቢ. ዊርትሊን 1ኛ ቆሮንቶስን በመጥቀስ እንዲህ ብለዋል፦l”በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ።”2

ቀጥለውም፦

“ጳውሎስ ለዚህ አዲስ የቅዱሳን አካል ያስተላለፈው መልእክት ቀላል እና ቀጥተኛ ነበር፦ፍቅር ከሌላችሁ የምታደርጓቸው ማናቸውም ነገሮች ብዙ ለውጥ አያመጡም። በልሳን ልትናገሩ ትችላላችሁ፣ ትንቢትም ቢኖራችሁ፣ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ብታውቁ…ተራሮችንም እስክታፈልሱ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖራችሁ ፍቅር ግን ከሌላችሁ ከንቱ ናችሁ።

“‘ልግስና የክርስቶስ ንፁህ ፍቅር ናት’ [ሞሮኒ 7፥47]። አዳኙ ያንን ፍቅር በምሳሌ አሳይቷል።”3

በዮሃንስ ወንጌል እንደምናነበው፣ “ እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”4

ልግስናን፣ አንድነትን፣ ፍቅርነን፣ ደግነትን፣ ርህራሄን፣ ይቅርታን እና ምሕረትን የተመለከቱ ብዙ ንግግሮች በቤተክርስቲያናችን መሪዎች ተሰጥተዋል። አዳኙ ከፍ ያለ እና የተቀደሰ መንገድ5—በርግጥ ሁሉም የዚህ አካል እንደሆኑ እና እንደሚያስፈልጉ እንዲሰማቸው የሚያስችል የእርሱን የፍቅር መንገድ እንድንኖር እየጋበዘን እንደሆነ አምናለሁ።

የታዘዝነው ሌሎችን እንድንወዳቸው 6 እንጂ እንድንፈርድባቸው 7 አይደለም። ያንን ከባድ ሸክም ከላያችን ላይ እናውርድ እርሱን መሸከም የእኛ ሥራ አደለም።8 ከዚያ ይልቅ የአዳኙን የፍቅር እና የርህራሄ ቀንበር ማንሳት እንችላለን።

“እናንተ ደካሞች ሸከማችሁ የከበደ ሁሉ፤ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ።

ቀንበሬንም በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፤

“ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”9

አዳኙ ኃጢአትን አይቀበልም ነገር ግን ፍቅሩን ይሰጠናል እንዲሁም ንስሐ ስንገባ ይቅርታ ያደርጋል። ምንዝር ስትፈጽም የተያዘችውን ሴት እንዲህ አላት “ እኔም አልፈርድብሽም፤ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ሀጢአት አትስሪ።“10 እርሱ የነካቸው ፍቅሩተሰምቷችዋል፣ እንዲሁም ፍቅሩ አክሟቸዋል፤ ለውጧቸዋል። የእርሱ ፍቅር ህይወታቸውን ለመለወጥ እንዲፈልጉ አነሳስቷቸዋል። በእርሱ መንገድ መኖር ደስታን እና ሰላምን ያመጣል፤ እንዲሁም ሌሎችንም ወደዚያ በየዋህነት፣ በደግነት እና በፍቅር የመኖር መንገድ ጋብዟል።

ሽማግሌ ጋሪ ኢ. ስቲቨንሰን እንዲህ ብለዋል “የህይወትን ንፋስ እና ወጀብ፣ ህመም እና ጉዳቶች ስንጋፈጥ፣ እረኛችን፣ ተንከባካቢያችን የሆነው ጌታ በፍቅር እና በደግነት ይመግበናል። ልባችንን ይፈውሳል፤ ነፍሳችንንም ይመልሳል።”11 እንደኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይነታችን እንዲሁ ማድረግ የለብንም?

አዳኙ ከእርሱ እንድንማር11 እና እርሱ ሲያደርግ ያየናቸውን ነገሮች እንድናደርግ ይጠይቀናል።13 እርሱ የንፁህ ፍቅር የልግስና አካላዊ መገለጫ ነው። በግዴታ ወይም ልንቀበላቸው ከምንችላቸው በረከቶች አንጻር ሳይሆን ለእርሱ እና ለሰማይ አባታችን14 ካለን ንጹህ ፍቅር ብቻ ተነስን እርሱ የሚጠይቀንን ለማድረግ መማርን በየጊዜው ስናሳድግ ፍቅሩ በእኛ ውስጥ ይፈስሳል እንዲሁም የሚለምነውን ሁሉ የሚቻል ማድረግ ብቻ ሳይሆን በመጨረሻም በጣም ቀላል 15 እና ልንገምተው ከምንችለው በላይ አስደሳች ያደርገዋል። ልምምድ ይጠይቃል፤ እኔን እንደወሰደብኝ ዓመታትን ሊወስድ ይችላል፤ ነገር ግን ፍቅር ማበረታቻ ሃይላችን እንዲሆን ስንፈልግ ያን ፍላጎት፣16 ያንን ዘር ወስዶ በጣም ጣፋጭ ፍሬ ወደሞሉበት ወዳማረ ዛፍ ሊለውጠው ይችላል።17

ከምንወዳቸው መዝሙሮች አንዱ የሆነውን ይህንን እንዘምራለን “ፍጽምና በጎደለው መንገድ እየሄድኩኝ በሌላው ላይ የምፈርድ እኔ ማን ነኝ? ጸጥ ባለው ልብ ውስጥ ዓይን የማያየው ሐዘን ተደብቋል።”18 ከእኛ መካከል የተደበቀ ሐዘን ሊኖረው የሚችለው ማን ነው? አመጸኛ የሚመስለው ጎረምሳ፣ ወላጆቻቸው በፍቺ የተለያዩባቸው ልጆች፣ ነጠላ እናት ወይም አባት፣ የአካል ወይም የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸው፣ እምነታቸውን የሚጠራጠሩ፣ አረጋውያን፣ ከአናሳ ዘር የወጡ፣ ብቻቸውን እንደሆኑ የሚሰማቸው፣ ሊያገቡ የሚፈልጉ፣ የማያስፈልግ ሱስ ያለባቸው እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ከሆኑ ፈታኝ የህይወት ገጠመኞች ጋር የሚኖሩ—ብዙውን ጊዜ ህይወታቸው ከላይ ከላይ ፍጹም የሆነ መስለው የሚታዩት።

ማናችንም ብንሆን ፍጹም ህይወትም ሆነ ፍጹም ቤተሰቦች የሉንም፤ በእርግጠኝነት እኔ የለኝም። ሌሎች ተግዳሮቶች እና ጉድለቶች ካጋጠሟቸው ጋር ለማዘን ስንሻ፣ በችግሮቻቸው ውስጥ ብቻቸውን እንዳልሆኑ እንዲሰማቸው ሊረዳቸው ይችላል። እያንዳንዱ በእውነት የዚህ ክፍል እንደሆነ እና በክርስቶስ አካል ውስጥ እንደሚያስፈልግ ሊሰማው ያስፈልጋል።19 የሰይጣን ታላቅ ፍላጎቱ የእግዚያብሄርን ልጆች መከፋፈል ነው እናም በጣም ተሳክቶለታል፤ ነገር ግን በህብረት ውስጥ ታላቅ ሃይል አለ።20 እናም በዚህ አስቸጋሪ ምድራዊ ጉዞ ላይ ምንኛ እጅ ለእጅ ተያይዘን መሄድ ያስፈልገናል!

ነቢያችን ፕሬዚዳንት ራስል.ኤም. ኔልሰን እንዲህ ብለዋል፣ “በብሔር፣ በዘር፣ በፆታዊ ማንነት፣ በጾታ፣ በትምህርት ደረጃ፣ በባህል ወይም በሌሎች ጉልህ መለያዎች ምክንያት በሌላው ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ወይም ጭፍን ጥላቻ ፈጣሪያችንን የሚያስቆጣ ነው! እንዲህ ያለው ግፍ እንደቃል ኪዳኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ከሚጠበቅብን ደረጃ በታች እንድንኖር ያደርገናል!”21

ፕሬዘደንት ኔልሰን ሁሉም ወደ አዳኛችን እና ወደሰማይ አባታችን ወደሚመራው የቃል ኪዳን መንገድ እንዲመጡ እና በዚያ እንዲቆዩ ሲጋብዟቸው የሚከተለውን ምክርም ሰጥተዋል፦“ጓደኞች እና ቤተሰብ… ከቤተክርስቲያን ቢወጡም እነርሱን መውደዳችሁን ቀጥሉ። ታማኝ በመሆናችሁ ልትተቹ የማይገባችሁን ያህል በሌላው ምርጫ ላይ መፍረድ አትችሉም።”22

ጓደኞች፣ በዚህች ምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው የሰማይ አባት ልጅ 23እንደሆነ እና እርሱም እያንዳንዱን እንደሚወድ24 እናስታውስ። በእናንተ መንገድ ላይ ልትፈርዱባቸው የምትፈልጓቸው ሰዎች አሉ? ካሉ እነዚህ አዳኙ እንደሚወደው መውደድን የምንለማመድባቸው አስደናቂ እድሎች መሆናቸውን አስታውሱ።25 የእርሱን ምሳሌ ስንከተል ከእርሱ ጋር እንጣመራለን እንዲሁም በሁሉም የአባታችን ልጆች ልብ ውስጥ የፍቅርን እና የመካተትን ስሜት በማሳደግ እንረዳለን።

“እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።”26 በአዳኙ ፍቅር ስንሞላ ቀንበሩ በእውነት ልዝብ ሊሆን ይችላል ሸክሙም ቀሊል ሊሆንይችላል27 ስለዚህ የምመሰክረው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. See Jack R. Christianson, Healing the Wounded Soul (2008), 27.

  2. 1 ቆሮንቶስ 13:1ሞሮኒ 7:44–48 ይመልከቱ.

  3. ጆሴፍ ቢ. ዊርዝሊን፣ “The Great Commandment፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2007 (እ.አ.አ)፣ 28።

  4. ዮሃንስ 13:35፣ ትኩረት ተጨምሮበታል፣ እንዲሁም ቁጥር 34 ይመልከቱ።

  5. ራስል ኤም ኔልሰን “የመክፈቻ ንግግርሊያሆና ህዳር 2018 (እ.አ.አ) 6–8 ይመልከቱ፡፡

  6. ማቴዎስ 22፥36–40ሉቃስ 10፥34–35 ይመልከቱ።

  7. ማቴዎስ 7:1–4፤ ዳይተር ኤፍ አክዶርፍ. “The Merciful Obtain Mercy፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2012,(እ.አ.አ) 70–77፤ በተጨማሪም ሮበረርት ሲ.ጌይ “Taking upon Ourselves the Name of Jesus Christ፣” ሊያሆና፣ህዳር. 2018(እ.አ.አ)፣ 97–100.ይመልከቱ።

  8. ኤጲስ ቆጶሳትና የካስማ ፕሬዘዳንቶች አይመለከታቸውም። “እያንዳንዱ ኤጲስ ቆጶስ እና የካስማ ፕሬዘዳንት ‘የእስራኤል ዳኛ‘ ነው” (ትምህርተ እና ቃል ኪዳኖች 107፥72 )። በዚህ ስልጣን አባላት ከሃጢያታቸው ንስሃ እንዲገቡ እና ሃጢያትን ይቅር ወደሚለው ወደክርስቶስ እንዲመጡ ይረዳሉ (32.1 እና 32.3 ይመልከቱ)” (General Handbook፥ Serving in The Church of Jesus Christ of Latter-day Saints, 31.1.7, ChurchofJesusChrist.org)።

  9. ማቴዎስ 11፥28–30፤ ትኩረት ተጨምሮበታል።

  10. ዮሃንስ 8፥11፤ ትኩረት ተጨምሮበታል፣ እንዲሁም ቁጥር 3–10 ይመልከቱ።

  11. ጌሪ ኢ. ስቲቨንሰን፣“Hearts Knit Together፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2021 (እ.አ.አ)፣ 23።

  12. ማቴዎስ 11፥29 ይመልከቱ።

  13. 3 ኔፊ 27፥21–22 ይመልከቱ።

  14. ማቴዎስ 22፥37–39 ይመልከቱ።

  15. ሞዛያ 24፥15 ይመልከቱ።

  16. አልማ 32፥27 ይመልከቱ።

  17. አልማ 32፥41 ይመልከቱ።

  18. “Lord, I Would Follow Thee,” መዝሙር፣ ቁ. 220።

  19. 1 ቆሮንቶስ 12:12–27; በተጨማሪም ጀፍሪ አር. ሆላንድ፣ “Songs Sung and Unsung,” ሊያሆና፣ ግንቦት 2017(እ.አ.አ)፣ 49–51.ይመልከቱ

  20. Sharon Eubank, “By Union of Feeling We Obtain Power with God,” Liahona, Nov. 2020, 55–57; see also Dale G. Renlund, “The Peace of Christ Abolishes Enmity,” Liahona, Nov. 2021, 83–86; Sharon Eubank, “Turning Enemies into Friends” (Brigham Young University devotional, Jan. 23, 2018), speeches.byu.edu.ይመልከቱ

  21. Russell M. Nelson, “Choices for Eternity” (worldwide devotional for young adults, May 15, 2022), broadcasts.ChurchofJesusChrist.org.

  22. Russell M. Nelson, “Choices for Eternity,” broadcasts.ChurchofJesusChrist.org.

  23. ሮሜ 8፥16 ይመልከቱ።

  24. ኢሳይያስ 49፥16ሮሜ 8፥35, 38–39ይመልከቱ።

  25. ሉቃስ 6፥31–38 ይመልከቱ።

  26. 1 ዮሐንስ 4፥19። “እየተነጋገርን ያለነው ለሰብዓዊው ቤተሰብ ስለተሰጠው ስለመጀመሪያው ታላቅ ትዕዛዝ ነው—በሙሉ ልብ ወይም ያለጥርጥር ወይም ቅድመ ሁኔታ ሳናስቀምጥ እግዚአብሔርን በሙሉ ልብ መውደድ ያም ማለት በሙሉ ልብ፣ ሀይል፣ አዕምሮ፣ እና ጥንካሬ እግዚአብሄርን መውደደ ነው። እግዚአብሄርን መውደድ በዓጽናፈ ዓለሙ የመጀመሪያው ታላቅ ትዕትዛዝ ነው። ነገር ግን ከፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ የመጀመሪያው ታላቅ እውነት እግዚአብሔር እኛን በዚያ መንገድ መውደዱ ነው—በሙሉ ልብ ወይም ያለጥርጥር ወይም ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጥ፣ በሙሉ ልቡ፣ ሀይሉ፣ አዕምሮው፣ እና ጥንካሬው” (Jeffrey R. Holland፣ “ The Greatest Possession፣” Liahona፣ Nov. 2021(እ.አ.አ) 9)።

  27. ማቴዎስ 11፥28-30 ይመልከቱ።