የክርስቶስ ሰላም ጠላትነትን ያጠፋል
የክርስቶስ ፍቅር ሕይወታችንን ሲሸፍን፣ አለመግባባቶችን በየዋህነት፣ በትዕግስት እና በደግነት እንመለከታለን።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ የውጥረት ምርመራ ወቅት፣ የልብ ሥራ ጫና ይጨምራል። መራመድ የሚችሉ ልቦች ሽቅብ የመሮጥ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ሊቸገሩ ይችላሉ። በዚህ መንገድ፣ የውጥረት ምርመራው በሌላ መልኩ በግልጽ የማይታየውን በሽታ ሊያሳይ ይችላል። ማንኛቸውም የተገኙ ችግሮች በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ከባድ ችግሮችን ከመፍጠራቸው በፊት ሊታከሙ ይችላሉ።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በእርግጥም ዓለም አቀፍ የውጥረት መለኪያ ሆኗል! ምርመራው ድብልቅ ውጤቶችን አሳይቷል። አስተማማኝ እና ውጤታማ ክትባቶች ተዘጋጅተዋል። 1 የህክምና ባለሙያዎች፣ መምህራን፣ ተንከባካቢዎች እና ሌሎችም በጀግንነት መስዋእትነት ከፍለዋል —አሁንም በመክፈል ላይ ይገኛሉ። ብዙ ሰዎች ልግስና እና ደግነት አሳይተዋል—አሁንም በማሳየት ላይ ይገኛሉ። ሆኖም፣ መሠረታዊ ድክመቶች ተገልጠዋል። ለአደጋ የተጋለጡ ግለሰቦች ተጎድተዋል—እንዲሁም በመጎዳት ላይ ይገኛሉ። እነዚያ መሰረታዊ እኩል ያለመሆንን ችግሮች ለመቅረፍ የሚሰሩ ሊበረታቱ እና ሊመሰገኑ ይገባል።
ወረርሽኙ ለአዳኙ ቤተክርስቲያን እና ለአባላቱ የመንፈሳዊ ውጥረት መመርመሪያም ነው። ውጤቱም እንዲሁ ድብልቅ ነው። ሕይወታችን “ከፍ ባለ እና በተቀደሰ መንገድ፣” በማገልገል፣ 2 በ ኑ፤ ተከተሉኝሥርዓተ-ትምህርት፣ እና በቤት-ተኮር፣ በቤተክርስቲያን የተደገፈ የወንጌል ትምህርት ተባርኳል። በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ብዙዎች ርህራሄ የተሞላበት እርዳታን እና ማጽናኛን ሰጥተዋል፣ አሁንም በማድረግ ላይ ይገኛሉ። 3
ሆኖም፣ በአንዳንድ አጋጣሚዎች፣ የመንፈሳዊ ውጥረት ምርመራው የክርክር እና የመለያየት ዝንባሌዎችን አሳይቷል። ይህም ልባችንን ለመለወጥ እና እንደ አዳኙ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት አንድ ለመሆን የምንሠራው ሥራ እንዳለ ይጠቁማል። ይህ አዲስ ፈተና አይደለም፣ ግን ወሳኝ ነው። 4
አዳኙ ኔፋውያንን ሲጎበኝ፣ ይህንን አስተማረ “በመካከላችሁ ክርክር አይኖርም። … እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ የፀብ መንፈስ ያለበት፣ የፀብ አባት ከሆነ እናም የሰዎችን ልብ እርስ በርስ እንዲጣሉ በቁጣ ከሚያነሳሳው ከዲያብሎስ እንጂ፤ ከእኔ አይደለም።” 5 በቁጣ እርስ በርሳችን ስንጣላ ሰይጣን ይስቃል የሰማይ አምላክ ያለቅሳል። 6
ሰይጣን የሚስቀው እና እግዚአብሔር የሚያለቅሰው ቢያንስ ለሁለት ምክንያቶች ነው። በመጀመሪያ፣ ክርክር ለኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ያለንን የጋራ ምስክርነት እና በእሱ “መልካም ሥራ፣ … ምህረትና ፀጋ” 7 ፣ በኩል የሚመጣውን ቤዛ ያዳክማል። አዳኙ እንዲህም አለ፣ “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። … እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” 8 ተገላቢጦሹም እውነት ነው— እርስ በርሳችን ፍቅርን ሳናሳይ ስንቀር፣ ሁሉም የእሱ ደቀ መዛሙርት አለመሆናችንን ያውቃል። በደቀ መዛሙርቱ መካከል ክርክር ወይም ጠላትነት ሲኖር ፣ 9 የኋለኛው ቀን ሥራው ይስተጓጎላል። 10 ሁለተኛ፣ ክርክር ለእኛ እንደግለሰብ በመንፈሳዊ ጤናማ አይደለም። ሰላምን፣ ደስታን እና ዕረፍትን እንነፈጋለን፣ እንዲሁም መንፈስን የመሰማት ችሎታችን ይስተጓጎላል።
እየሱስ ክርስቶስ ፣ “ሰዎችን አንዳቸውን ከሌላኛው ልባቸውን ለቁጣ የሚያነሳሳ ይህ የእሱ ትምህርት [እንዳልሆነ]፤ ነገር ግን እንደነዚህ ያሉ ነገሮች እንዲወገዱ ማድረግ ይህ [የእሱ] ትምህርት [እንደሆነ] ገልጿል።” 11 እኔ ቁጡ በመሆን ወይም ፍርድ በመስጠት በአመለካከት ልዩነት ላይ ቅሬታ የሚሰማኝ ወይም ምላሽ ለመስጠት ፈጣን ከሆንኩኝ፣ እኔ የመንፈሳዊ ውጥረት ምርመራን “ወድቄያለሁ”። ይህ ያልተሳካ ምርመራ ተስፋ የለኝም ማለት አይደለም። ይልቁንም መለወጥ እንዳለብኝ ይጠቁማል። እናም የንን ማወቅ ጥሩ ነው።
አዳኙ አሜሪካን ከጎበኘ በኋላ ሕዝቡ አንድ ሆነ፤ “በምድሪቱ ሁሉ ጠብ አልነበረም” 12 ሰዎቹ አንድ ስለነበሩ ወይም የሐሳብ ልዩነት ስላልነበራቸው አንድ ሆነዋል ብላችሁ ታስባላችሁን? ያንን እጠራጠራለሁ። ይልቁንስ፣ ክርክር እና ጠላትነት ጠፋ ምክንያቱም የአዳኙን ደቀ መዝሙርነት ከምንም በላይ ከፍ አድርገው ስለያዙ ነው። ለአዳኙ ካላቸው የጋራ ፍቅር ጋር ሲነፃፀር ልዩነቶቻቸው አይታዩም፣ እናም እነሱ “የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች” በመሆን አንድ ሆነዋል። 13 በውጤቱም፣ “በእግዚአብሔር እጅ ከተፈጠሩት ሰዎች መካከል እንደዚህ ያለ ደስተኛ ሊሆን የቻለ ህዝብ አልነበረም።” 14
አንድነት ጥረት ይጠይቃል። 15 በልባችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ፍቅር ስናዳብር፣ 16 እና በዘላለማዊ ዕጣ ፈንታችን ላይ ስናተኩር ያድጋል። 17 እንደ እግዚአብሔር ልጆች የጋራችን በሆነው ዋነኛ ማንነታችን 18 እና ለተመለሰው ወንጌል እውነቶች ባለን ቁርጠኝነት አንድ ሆነናል። በምላሹም፣ ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር እና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆናችን ለሌሎች እውነተኛ ተቆርቋሪነትን ይፈጥራል። ለሌሎች የተለያዩ ውስብስብ ባህሪዎች፣ አመለካከቶች እና ተሰጥኦዎች ዋጋ እንሰጣለን። 19 የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርትነታችንን ከግል ፍላጎቶች እና አመለካከቶች በላይ ማድረግ ካልቻልን፣ ቅድሚያ ስለምንሰጣቸው ነገሮች እንደገና መመርመር እና መለወጥ አለብን።
“በእርግጥ እርስዎ ቢስማሙኝ፣ አንድነትን ማግኘት እንችላለን!” ለማለት እንፈልግ ይሆናል። የተሻለው አቀራረብ “አንድነትን ለማሳደግ ምን ማድረግ እችላለሁ? ይህ ሰው ወደ ክርስቶስ እንዲቀርብ ለመርዳት እንዴት ምላሽ መስጠት እችላለሁ? ክርክርን ለመቀነስ እና ሩህሩህ እና አሳቢ የቤተክርስቲያን ማህበረሰብን ለመገንባት ምን ማድረግ እችላለሁ?” ብሎ መጠየቅ ነው።
የክርስቶስ ፍቅር ሕይወታችንን ሲሸፍን፣ 20 አለመግባባቶችን በየዋህነት፣ በትዕግስት እና በደግነት እናያቸዋለን። 21 ስለራሳችን ስሜታዊነት ሳንጨነቅ ስለ ጎረቤታችን የበለጠ እንጨነቃለን። ”ለማስማማት እና አንድ ለመሆን እንሻለን።” 22 እኛ “በአጠራጣሪ ክርክሮች” ውስጥ አንገባም፣ ባልተስማማናቸው ሰዎች ላይ አንፈርድም ወይም እንዲሰናከሉ ለማድረግ አንሞክርም። 23 ይልቁንም፣ እኛ የማንግባባቸው ሰዎች ባገኙት የሕይወት ልምዶች የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው ብለን እንገምታለን።
ባለቤቴ ከ20 ዓመታት በላይ በህግ ሙያ ውስጥ ሰርታለች። እንደ ጠበቃ፣ ብዙውን ጊዜ ተቃራኒ አመለካከቶችን በግልጽ ከሚደግፉ ከሌሎች ጋር ትሠራ ነበር። እሷ ግን ሰውን ሳታስቀይም ወይም ሳትናደድ አለመስማማትን ተማረች። ለተቃዋሚዎችዋም እንዲህ ትላለች፣ “በዚህ ጉዳይ ላይ እንደማንስማማ ይታየኛል። እወድዎታለሁ። አስተያየትዎን አከብራለሁ። እርስዎም በተመሳሳይ ጨዋነት እንደሚይዙኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ” ብዙውን ጊዜ ልዩነቶች ቢኖሩም ይህ እርስ በእርስ መከባበርን እና አልፎ ተርፎም ጓደኝነትን ይፈጥራል።
የቀድሞ ጠላቶች እንኳን በአዳኙ ደቀ መዛሙርትነታቸው አንድ ሊሆኑ ይችላሉ። 24 እ.ኤ.አ. በ 2006 ፊንላንድ ውስጥ ወደ ቤተክርስቲያኗ የተቀላቀሉትን አባቴን እና አያቶቼን ለማክበር በሄልሲንኪ ፊንላንድ ቤተመቅደስ ምረቃ ላይ ተገኝቼ ነበር። ፊንላንዳውያን፣ አባቴን ጨምሮ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊንላንድ ውስጥ ቤተመቅደስ እንዲኖር ሲመኙ ኖረዋል። በወቅቱ የቤተመቅደስ አውራጃው ፊንላንድን፣ ኢስቶኒያን፣ ላትቪያን፣ ሊቱዌኒያን፣ ቤላሩስ እና ሩሲያን ያጠቃልል ነበር።
በምረቃው ወቅት አንድ አስገራሚ ነገር ተማርኩ። አጠቃላይ ስራው ሲጀመር የመጀመሪያው ቀን፣ የሩሲያ አባላት የቤተመቅደስ ሥርዓቶችን እንዲፈጽሙ ተይዞ ነበር። ይህ ምን ያህል አስገራሚ እንደነበረ ለማብራራት አስቸጋሪ ነው። ሩሲያ እና ፊንላንድ ባለፉት ዘመናት ብዙ ጦርነቶችን አድርገዋል። አባቴ ሩሲያን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሩሲያውያንን አያምንም እንዲሁም አይወድም ነበር። እንዲህ ዓይነት ስሜቱን ስሜታዊ ሆኖ ይገልጽ ነበር፣ እናም ይህም ፊንላንዳውያን ለሩሲያውያን ያላቸው የተለመደ የጠላትነት ስሜት ነበር። በ19 ኛው ክፍለ ዘመን በፊንላንዳውያን እና በሩሲያውያን መካከል የነበረውን ጦርነት የሚዘክሩ ግጥሞችን በቃሉ ሸምድዶ ነበር። ፊንላንድ እና ሩሲያ እንደገና ተቃዋሚዎች ሲሆኑ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ያጋጠሙት ተሞክሮዎች አስተያየቱን ለመለወጥ ምንም አልረዱም።
የሄልሲንኪ ፊንላንድ ቤተመቅደስ ከመመረቁ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ፣ የፊንላንድ አባላትን ብቻ ያካተተ የቤተመቅደሱ ኮሚቴ በምረቃ ዕቅዶች ላይ ለመወያየት ተሰብስበው ነበር። በስብሰባው ወቅት፣ አንድ ሰው የሩሲያውያን ቅዱሳን በምረቃው ላይ ለመገኘት ብዙ ቀናት እንደሚጓዙ እና ወደ አገራቸው ከመመለሳቸው በፊት የቤተመቅደስ በረከቶቻቸውን ለመቀበል ተስፋ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተመለከተ። የኮሚቴው ሊቀመንበር ወንድም ስቨን ኤክሉንድ፣ ሩሲያውያን በቤተመቅደስ ውስጥ የቤተመቅደስ ሥርዓቶችን ለመፈጸም የመጀመሪያዎቹ አባላት መሆን እንዳለባቸው እና ፊንላንዳውያን ደግሞ ትንሽ መጠበቅ እንደሚችሉ ሐሳብ አቀረበ። ሁሉም የኮሚቴ አባላት ተስማሙ። ታማኝ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ፊንላንዳውያን የሩሲያ ቅዱሳንን በማስቀደም የራሳቸውን የቤተመቅደስ በረከቶች አዘገዩ።
በዚያ የቤተመቅደስ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የተገኙት የአከባቢው ፕሬዚዳንት፣ ሽማግሌ ዴኒስ ቢ ኑዌንስሽዋንደር፣ በኋላ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፣ “እኔ ከዚህ ቅጽበት በበለጠ በፊንላንዳውያን ላይ ኩራት ተሰምቶኝ አያውቅም። ፊንላንድ ከምስራቃዊ ጎረቤቷ ጋር ያላት አስቸጋሪ ታሪክ … እና በመጨረሻ በአገራቸው ላይ [ቤተመቅደስ] በመገንባቱ የነበራቸው ደስታ ሁሉም ወደ ጎን ተደረጉ። ሩሲያውያን በመጀመሪያ ወደ ቤተመቅደስ እንዲገቡ መፍቀድ የፍቅር እና የመሥዋዕትነት መግለጫ [ነበር]። 25
ይህንን ደግነት ለአባቴ ስገልጽ ልቡ ቀለጠ እናም አለቀሰ፣ ለዚያ ልበ ጠጣራ ፊንላንዳዊ በጣም ያልተለመደ ክስተት ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሦስት ዓመት በኋላ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ስለሩሲያ ሌላ አሉታዊ ስሜትን በጭራሽ አልገለጸም ነበር። የእርሱ በሆኑት ፊንላንዳውያን ምሳሌ በመነካት፣ አባቴ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙርነትን ከሌሎች ነገሮች ሁሉ በላይ አድርጎ መረጠ። ፊንላንዳውያን ከፊንላንዳዊነታቸው ፈቀቅ አላሉም፤ ሩሲያውያን ከሩሲያውያንነታቸው አልጎደሉም። ሁለቱም ቡድኖች ጠላትነታቸውን ለማስወገድ ባህላቸውን፣ ታሪካቸውን ወይም ልምዶቻቸውን አልተዉም። አያስፈልጋቸውም ነበር። ይልቁንም፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ደቀመዝሙርነት ቀዳሚ አሳባቸው ማድረግን መርጠዋል። 26
እነሱ ማድረግ ከቻሉ እኛም እንዲሁ ማድረግ እንችላለን። ቅርሶቻችንን፣ ባህላችንን እና ልምዶቻችንን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ማምጣት እንችላለን። ሳሙኤል ከላማናዊ ርስቱ አልራቀም፣ 27 ሞርሞንም ከኔፋዊነቱ አላፈገፈገም። 28 ነገር ግን እያንዳንዳቸው የአዳኙን ደቀ መዝሙርነት አስቀድመዋል።
አንድ ካልሆንን የእርሱ አይደለንም። 29 ግብዣዬም፣ ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር እና የአዳኙን ደቀመዝሙርነት ከሌሎች ጉዳዮች ሁሉ በማስቀደም ጀግኖች እንድንሆን ነው። 30 በደቀ መዛሙርትነታችን ውስጥ ያለውን አንድ የመሆን ቃል ኪዳን እንጠብቅ።
የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመሆን በተሳካ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ ያሉትን ቅዱሳን ምሳሌ እንከተል። በመካከላችን ያለውን የመከፋፈል ግድግዳ ባፈረሰው፣ “በእርሱ [የኃጢያት ክፍያ መሥዋዕት] ጠላትነትን ባስወገደው” በኢየሱስ ክርስቶስ መታመን እንችላለን። 31 ለአለም የምንሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነታችን ይጠናከራል እንዲሁም በመንፈሳዊ ጤነኛ ይሆናል። 32 “ክርክርን ስንቃወም” እና “ከጌታ ጋር በፍቅር እና በአንድነት በእምነት አንድ” ስንሆን፣ 33 ሰላሙ የእኛ እንደሚሆን እመሰክራለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።