አጠቃላይ ጉባኤ
በሚያስቸግሩ ጊዜዎች ውስጥ የግል ሰላም
የጥቅምት 2021 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


በሚያስቸግሩ ጊዜዎች ውስጥ የግል ሰላም

ግላዊ ሰላምን መሻት እንደዚህ የበለጠ ጠቃሚ ሆኖ አያውቅም።

በቅርቡ የታሪካዊውን ናቩ የተወሰነ ክፍል ለመባረክ ተመድቤ ነበር። እንደ ምደባዬ አካል በምዙሪ ውስጥ የሊበርቲ እስር ቤትን ለመጎብኘት ቻልኩኝ። እስር ቤቱን ስመለከት የቤተክርቲያኗ ታሪክ አስፈላጊ አካል ያደረጉትን ክስተቶች አሰላሰልኩኝ። በምዙሪ አስተዳዳሪ በወጣው የድምሰሳ ትዕዛዝ መሰረት የቅዱሳኑ ሕይወት አደጋላ ላይ ወድቆ ነበር። በተጨማሪም ነቢዩ ጆሴፍ እና የተወሰኑ የተመረጡ ጓዶች በሊበርቲ እስር ቤት ውስጥ አግባብ በሌለው መልኩ ታስረው ነበር። አባሎቻችን ያጋጠማቸው ጠብ ያለው ተቃውሞ ምክንያት አንዱ አብዛኞቹ ባርነትን ይቃወሙ ስለነበረ ነው። 1 ይህ የጆሴፍ ስሚዝ እና ተከታዮቹ ከባድ ስደት በጻድቃን ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል ጽድቅ ያልሆነ የነፃ ምርጫ ልምምድ እጅግ ምሳሌ ነው። በሊበርቲ እስር ቤት ውስጥ የጆሴፍ ጊዜ መከራ በጌታ ፊት ሞገስን ማጣት ወይም የእርሱን በረከቶቹ የማንሳት ማረጋገጫ እንዳልሆነ ያሳያል።

ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በሊበርቲ እስር ቤት ውስጥ ሳለ እንዲህ ብሎ ያወጀውን ሳነብ በጥልቅ ስሜት ተነካው፣ ““እግዚአብሔር ሆይ፣ የት ነህ?? እና የተሰወርክበትን ስፍራ የሚሸፍነው ድንኳን የት ነው?” 2 የጌታ ህዝቦች እስከ መቼ ድረስ “እነዚህን ክፋቶችን እና ህጋዊ ያልሆኑትን ጭቆናዎችን ይሰቃዩ” ብሎ ጆሴፍ ጠየቀ። 3

ምስል
ሽማግሌ ኩክ ሊብረቲ እስር ቤትን ሲጎበኙ

በሊበርቲ እስር ቤት ውስጥ ቆሜ ሳለሁ፣ የጌታን መልስ ሳነብ በጥልቅ ስሜት ተነካሁ፦ “ልጄ፣ ለነብስህ ሰላም ይኑርህ፤ ጭንቀትህ እና ስቃይህ ለጥቂት ጊዜ ቢሆን ነው፤ ከዚያም በመልካም ይህን ብትፀና፤ እግዚአብሔር ወደ ላይ ዘላለማዊ ክብር ይሰጥሀል።” 4 ተቃውሞ ለዘላለሙ የሰለስቲያል ክብር መድረሻ እንደሚያስተካክለን ግልፅ ነው። 5

“ልጄ፣ ለነብስህ ሰላም ይኑርህ” የሚሉት የአዳኙ ውድ ቃላት 6 በግሌ ውስጥ ያስተጋባል እና ለቀናችን ትልቅ ጥቅም አለው። በምድራዊ አገልግሎቱ ውስጥ ለደቀመዛሙርቱ ያስተማረው የእርሱን ትምህርቶች አስታወሱኝ።

ክርስቶስ በጌተሰማኒ የአትክልት ስፍራ እና በመስቀል ላይ ከመሰቃየቱ በፊት፣ “እኔ እንደወደድኳችሁ፣ እርስ በእርስ ተዋደዱ” በማለት ሐዋርያቱን አዘዘ 7 እና በእነዚህ ቃላት አፅናናቸው፦ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።” 8

የጌታችን እና የአዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ ክብር የተሰጠው ሰም “የሰላም ልዑል” የሚለው ነው። 9 በመጨረሻ መንግሥቱ ሰላምን እና ፍቅርን ያጠቃልላል። 10 የመሲሁን የሺህ ዓመታት ንግሥ በጉጉት እንጠብቃለን።

ምንም እንኳን የዚህን የሺህ ዓመታት የንግሥ እይታ ቢኖረንም፣ የዓለም ሰላም እና መስማማት በቀናችን ውስጥ በመስፋፋት እንደማይገኙ እናውቃለን። 11 በሕይወት ዘመኔ፣ እንደዚህ ዓይነት ታላቅ የትህትና እጦትን አይቼ አላውቅም። እኛ በቁጣ፣ በክርክር ቋንቋ እና በቀስቃሽ፣ አጥፊ ድርጊቶች ሰላምን እና መረጋጋትን በሚያበላሹ ድርጊቶች እየተጨናነቅን ነን።

የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት እስከሚከናወን ድረስ ሰላም በዓለም ውስጥ እንደሚገኝ ቃል አልተገባም ወይም አልተረጋገጠም። አዳኙ ምድራዊ ተልዕኮው ሁለንተናዊ ሰላምን እንደማያስገኝ ሐዋርያቱን አስተምሯል። እንዲህ አስተማረ፣ “በምድር ላይ ሰላምን ላመጣ የመጣው አይምሰላችሁ።” 12 የዓለም አቀፍ ሰላም የአዳኙ የመጀመሪያ ምድራዊ አገልግሎት አካል አልነበረም። የዓለም አቀፍ ሰላም ዛሬ የለም።

ይሁን እንጂ፣ ንዴት፣ ግጭት እና ክፍፍል ዓለማችንን ዛሬ ቢያደብዝዟት እና ቢበክሏትም ግላዊ ሰላም ሊገኝ ይችላል። ግላዊ ሰላምን መሻት እንደዚህ የበለጠ ጠቃሚ ሆኖ አያውቅም። “ሰላም በክርስቶስ” ተብሎ የሚጠራው ለዛሬዎቹ ወጣቶች በወንድም ኒክ ደይ የተፃፈው ደስ የሚለው እና አዲሱ መዝሙር እንዲህ ይላል፣ “በምድር ላይ ሰላም ሳይኖር ሲቀር፣ በክርስቶስ ሰላም አለ።” 13 ከዓለም አቀፉ የኮቨድ-19 ወረርሽኝ በፊት ይህን መዝሙር ስላገኘን ተባርከናል።

ይህ መዝሙር በሚያምር መልኩ የሰላምን ምኞት ያንፀባርቃል እናም ሰላም በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት እና ተልዕኮ ውስጥ ስር እንደሰደደ ተገቢ በሆነ መልኩ ያተኩራል። ፕሬዘደንት ጆሴፍ ኤፍ. ስሚዝ እንዲህ አወጁ፣ “የሰው ዘር የእግዚአብሔርን እውነታ እና የእግዚአብሔርን መልዕክት እስካልተቀበለ ድረስ … እና መለኮታዊ የሆነውን የእርሱን ሀይል እና ስልጣን እስካልተቀበለ … ያ የሰላም እና የፍቅር መንፈስ ወደ ዓለም ሊመጣ አይችልም።” 14

የዓለም ሰላምን ከማሳካት ጥረቶች በፍፁም ወደ ኋላ ሳንሸሽ፣ ክርስቶስ እንዳስተማረው ግላዊ ሰላም ሊኖረን እንደሚችል ተረጋግጦልናል። ይህ መርሆ በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ውስጥ እንዲህ ተቀምጥዋል፦ “ነገር ግን የፅድቅን ስራ የሚሰራው ደመወዙን፣ እንዲሁም በዚህ አለም ሰላም፣ እና በሚመጣው አለምም ዘለአለማዊ ህይወትን ይቀበላል።” 15

ሙግቶችን እና ክርክሮችን ለመቀነስ በዚህ ዓለም ውስጥ ሰላምን እንድናገኝ የሚረዱን የተወሰኑት “የጽድቅ ስራዎች” ምንድን ናቸው? ሁሉም የክርስቶስ ትምህርቶች ወደዚህ አቅጣጫ ይጠቁማሉ። ጠቃሚ ናቸው ብዬ የማምናቸውን የተወሰኑትን እጠቅሳለሁ።

አንደኛ፦ እግዚአብሔርን መውደድ፣ ትዕዛዛቱን መጠበቅ እና ሁሉንም ይቅር ማለት

ፕሬዘዳንት ጆርጅ አልበርት ስሚዝ በ1945 (እ.አ.አ) የቤተክርቲያኗ ፕሬዘዳንት ሆኑ። በእድሜያቸው ሐዋርያ ሆነው ሳሉ እንደ ሰላም ፈላጊ መሪ ታዋቂ ነበሩ። ፕሬዘዳንት ከመሆናቸው በፊት ለ15 ዓመታት፣ ዓለም አቀፍ የሆነ ታላቅ የኢኮኖሚ ውድቀት ችግሮች እና ፈተናዎች፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሞት እና ውድመት በመከተል ሰላም አልባ ሆኗል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መደምደሚያ ላይ፣ በጥቅምት 1945 (እ.አ.አ) ፕሬዝዳንት በነበሩበት የመጀመሪያ አጠቃላይ ጉባኤ ወቅት፣ ፕሬዝዳንት ስሚዝ ጎረቤቶቻቸውን እንዲወዱ እና ጠላቶቻቸውን ይቅር እንዲሉ የአዳኙን ግብዣ ለቅዱሳኑ አስገነዘቡ እናም እንዲህ አስተማሩ፣ “አንደ ቀን በእርሱ መገኛ ለመቆም እና ክብራዊ እንኳን ወደ ቤት በደህና መጣችሁ ከእጁ ለመቀበል ተስፋ የሚያደርጉ ከሆነ፣ ሁሉም የኋለኛው ቀን ቅዱሳን እንዲኖራቸው ሊሹት የሚገባ መንፈስ ያ ነው።” 16

ሁለተኛ፦ የመንፈስ ፍሬዎችን መሻት

ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላቲያኖች በፃው ደብዳቤ የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ ብቁ በሚያደርግ የጽድቅ ስራዎች እና ካለ ንስሃ ብቁ በማያደርጉን ስራዎች መካከል ያለውን ልዩነት አስቀመጠ። ብቁ ከሚያደርጉን ነገሮች መካከል አንዱ የመንፈስ ፍሬዎች ናቸው፣ እነሱም “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ እርጋታ፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ትህትና [እና] ቁጥብነት” ናቸው። 17 ጳውሎስ የእርስ በእርስ ሸክሞችን መሸከም እና መልካምን በማድረግ አለመድከምን እንዲሁም አከለ። 18 ጽድቅ ካልሆኑ ስራዎች መካከል ጥላቻ፣ ቁጣ እና ጠብ ይካተታሉ። 19

በብሉይ ኪዳን ጊዜ ውስጥ ከታላቅ ትምህርቶች መካከል አንዱ ከአባት አብርሐም ጋር ይዛመዳል። አብርሐም እና የወንድሙ ልጅ ሎጥ ሃብታሞች ነበሩ፣ ነገር ግን አብረው መኖር እንደማይችሉ ተረዱ። ጠብን ለማስወገድ ሎጥ የፈለገውን መሬት እንዲመርጥ አብርሐም ፈቀደለት። ሎጥ በደንብ የተጠበቀውን እና ያማረውን የዮርዳኖስን ሜዳ መረጠ። አብርሐም በደንብ ያልለማውን የመምሬን ሜዳ ወሰደ። መጽሐፍ ቅዱሳት አብርሐም ድንኳኑን እንደተከለ እና “መሰዊያን ለጌታ” እንደገነባ ይናገራሉ። 20 ሎጥ በሌላ መልኩ “ድንኳኑን ወደ ሶዶም አዙሮ ተከለ።” 21 ትምህርቱ ግልፅ ነው፣ ሰላማዊ ግንኙነቶች እንዲኖረን ጽድቅን የማያካትቱ የጠብ ነገሮችን ለማስማማት እና ለማስወገድ ፍቃደኛ መሆን አለብን። ንጉሥ ቢኒያም እንዲህ አስተማሩ፣ “እርስ በእርስ ለመቆሳሰል አታስቡም፣ ነገር ግን በሰላም መኖርን እንጂ።” 22 ነገር ግን ከጽድቅ ጋር በሚዛመድ ተግባር እና ትምህርታዊ ትዕዛዛት ላይ፣ ፅኑ እና የማናወላውል መሆን አለብን።

የጽድቅ ስራዎች ሽልማት የሆነውን ሰላም ከፈለግን፣ ድንኳናችንን ወደ ዓለም አዙረን መቼም አንተክልም። ድንኳናችንን ወደ ቤተመቅደሱ አዙረን እንተክላለን።

ሶስተኛ፦ ነፃ ምርጫን በጽድቅ ለመምረጥ መለማመድ

ሰላም እና ነፃ ምርጫ በደህንነት ዕቅድ ውስጥ እንደ አስፈላጊነት እርስ በእርስ የተወሳሰቡ ናቸው። በ“ነፃ ምርጫ እና ሃላፊነት፣” በወንጌል እርዕሶች ውስጥ እንደተገለፀው “ነፃ ምርጫ ለራሳችን ለመምረጥ እና ተግባራዊ ለማድረግ እግዚአብሔር የሚሰጠን ችሎታ እና መብት ነው።” 23 ስለዚህ አዳኙን ስንከተል በሚባርከን የግል እድገት እና ልምምድ ላይ ነፃ ምርጫ ማዕከላዊ ነው። 24

ነፃ ምርጫ “በሰማይ ከሕይወት በፊት ምክክር” እና በሴጣን ተከታዮች እና ክርስቶስን ለመከተል በመረጡ መካከል ባለው ግጭት ውስጥ ታላቅ ጉዳይ ነበር። 25 ኩራትን እና መቆጣጠርን መተው እና አዳኙን መምረጥ የእርሱን ብርሃን እና ሰላም እንዲኖረን ይፈቅድልናል። ነገር ግን ሰዎች ነፃ ምርጫቸውን በሚጎዳ መልኩ ሲለማመዱ የግል ሰላም ፈተና ይገጥመዋል።

በልቦቻችን ውስጥ የተሰማን ሰላማዊ ማረጋገጫ የዓለም አዳኝ በእኛ ፈንታ ምን እንደሚያሳካ ባለን እውቀት እንደጠነከረ እተማመናለሁ። ይህ ደስ በሚል ሁኔታ በ ወንጌሌን ስበኩ ውስጥ እንዲህ ተቀምጥዋል፦ “በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ላይ ስንመካ፣ በችግሮቻችን፣ በህመሞቻችን፣ እና በስቃያችን መፅናት እንድንችል ይረዳናል። በደስታ፣ በሰላም፣ እና በመፅናኛ ለመሞላት እንችላለን። በህይወት ሚዛናዊ ያልሆኑ ነገሮች በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በኩል ትክክል ለመሆን ይችላሉ።” 26

አራተኛ፦ ፅዮንን በልቦቻችን እና በቤቶቻችን ውስጥ መገንባት

የእግዚአብሔር ልጆች እና የቤተሰቡ አካል ነን። የተወለድንበት ቤተሰብ አካልም ነን። የቤተሰብ መዋቅር ለደስታ እና ለሰላም መሰረት ነው። በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ቤት ተኮር የሆነው በቤተክርቲያን የተደገፈው የሐይማኖት አከባበር “…[የእኛን] ቤታ[ችንን] ወደ እምነት መቅደስ ለመለወጥ የቤተሰቦችን ኃይል እንደሚለቅ” እንደተማርን ፕሬዘዳንት ረስል ኤም. ኔልሰን አስተምረውናል። 27 በቤታችን ውስጥ ይህ የሐይማኖት አከባበር ካለን፣ የአዳኙ ሰላምም ይኖረናል። 28 ብዙዎቻችሁ የፃድቅ ቤቶች በረከቶች እንደሌላችሁ እና ፃድቅ ያልሆነን ነገር ከሚመርጡ ሰዎች ጋር በተደጋጋሚ እንደምትጋጩ እንገነዘባለን። ከሕይወት መዓበሎች ወደ ደህንነት እና መጠለያ ሊመራችሁ አዳኙ በመጨረሻ ጥበቃ እና ሰላምን መስጠት ይችላል።

በሚዋደዱ ፃድቅ ቤተሰቦች ውስጥ ያለ ደስታ፣ ፍቅር እና የማሟላት ስሜት ሰላምን እና ደስታን እንደሚያመነጭ አረጋግጥላችኋለሁ። ጽዮንን በልቦቻችን እና በቤቶቻችን ውስጥ ለማድረግ ፍቅር እና ደግነት ማዕከላዊ ናቸው። 29

አምስተኛ፦ የነቢያችንን ወቅታዊ ማሳሰቢያ መከተል

የጌታን ነብይ፣ ፕሬዘዳንት ራስል ኤም. ኔልሰንን ስንከተል ሰላማችን የበለጠ ይሻሻላል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከእሳቸው የመስማት እድሉን ታገኛላችሁ። ለዚህ ጥሪ ዓለም ከመመስረቷ በፊት ተዘጋጅተዋል። የእሳቸው ግላዊ ዝግጅት የበለጠ አስደናቂ ሆኗል። 30

እንደ አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሆን የበለጠ ስንጥር፣ “በሁከት ጊዜያትም እንኳን የሚፀና ሰላም እና ደስታ ሊሰማን” እንደሚችል አስተምረዋል። 31 “በየቀኑ ንስሃ እንድንገባ”፣ የጌታን የሚያነፃ፣ የሚፈውስ እና የሚያጠነክር ኃይል እንድንቀበል መክረውናል። 32 ከሰማይ በውድ ነቢያችን ራዕይ እንደሚቀበሉ እና እየተቀበሉ እንዳሉ ግላዊ ምስክር ነኝ።

እንደ ነቢያችን ስናከብራቸው እና ስንደግፋቸው የሰማይ አባታችንን እና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እናመልካለን። በመንፈስ ቅዱስ ተገልግለናል።

የዓለም አዳኝ እና ቤዛው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በዳግም የተመለሰውን ቤተክርሰቲያኑን እንደሚመራ ግላዊ የሐዋርያ ምስክርነቴን እሰጣለው እንዲሁም እመሰክራለው። ሕይወቱ እና የሃጢያት ክፍያው ተልዕኮ እውነተኛ የሰላም ምንጭ ናቸው። እርሱ የሰላም ልዑል ነው። እርሱ ህያው እንደሆነ እርግጠኛ እና የከበረ ምስክርነቴን እመሰክራለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. “በኢንድፐንደንስ ውስጥ ያሉ ሰዎች ቅዱሳን ለሕንዶች መስበካቸውን እና ባርነትን አለመቀበላቸውን አልወደዱም” ( ቅዱሳን፤ የኋለኛው ቀን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ታሪክ ፣ መጽሃፍ 1፣ የእውነት መስፈርት፣ 1815–1846 (እ.አ.አ) [2018 (እ.አ.አ)]፣ 172)።

  2. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥1

  3. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥3

  4. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥7-8

  5. 2 ኔፊ 2፥11–15 ተመልከቱ።

  6. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥7

  7. ዮሐንስ 13፥34

  8. ዮሐንስ 14፥27

  9. ኢሳይያስ 9፥62 ኔፊ 19፥6። አዳኙ በብልጽግናዎቹ እንዲህ አስተማረ፣ “የሚያስተራርቁ ብፁአን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (ማቴዎስ 5፥9)።

  10. “እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ” (ኢሳይያስ 9፥6–72 ኔፊ 19፥6–7ን ተመልከቱ፤ በተጨማሪም ገላትያ 5፥22 ን ተመልከቱ)።

  11. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥35ን ይመልከቱ። ፕሬዘደንት ዊልፈርድ ዉድረፍ በ1894 (እ.አ.አ) እና እንደገናም በ1896 (እ.አ.አ) ይህን አወጁ (The Discourses of Wilford Woodruff፣ ዕትም ጂ. ሆመር ዱርሃም (1946 እ.አ.አ)፣ 251-52፤ እንዲሁም ማሪየን ጂ. ራምኒ፣ በጉባኤ ሪፖርት ውስጥ፣ ሚያዚያ 1967 (እ.አ.አ)፣ 79-82፤ እዝራቲ. ቤንሰን፣ “The Power of the Word፣” ኢንሳይን፣ ሚያዝያ 1986 (እ.አ.አ)፣ 79፤ ዳለንኤች. ኦክስ፣ “Preparation for the Second Coming፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2004 (እ.አ.አ)፣ 9 ይመልከቱ።

  12. ማቴዎስ 10፥34

  13. Nik Day, “Peace in Christ,” 2018 Mutual theme song, Liahona, Jan. 2018, 54–55; New Era, Jan. 2018, 24–25. “ሰላም በክርስቶስ” የሚባለው መዝሙር እንህ ያስተምራል፦

    እርሱ በኖረበት ስንኖር፣

    በክርስቶስ ሰላም አለ።

    ተስፋ ይሰጠናል

    ተስፋ በጠፋበት።

    ጥንካሬ ይሰጠናል

    መሄድ ሲያቅተንም።

    መጠለያ ይሰጠናል

    በህይወት አውሎ ንፋስም።

    በምድር ላይ ሰላይ በማይገኝበትም፣

    በክርስቶስ ሰላም አለ።

  14. Teachings of Presidents of the Church: Joseph F. Smith (1998), 400.

  15. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 59፥23

  16. ጆርጅ አልበርት ሰሚዝ፣ በጉባኤ ሪፖርት ውስጥ፣ ጥቅምት 1945 (እ.አ.አ)፣ 169–70 ተመልከቱ።

  17. ገላትያ 5፥22–23

  18. ገላትያ 6፥2፣ 9 ይመልከቱ።

  19. ገላትያ 5፥20

  20. ዘፍጥረት 13፥18

  21. ዘፍጥረት 13፥12

  22. ሞዛያ 4፥13

  23. የወንጌል ርዕሶች፣ “ነፃ ምርጫ እና ሃላፊነት፣” topics.ChurchofJesusChrist.org።

  24. እኛ “ሁሉን ሰው በሚማልደው አማካኝነት ነፃነትን ወይም ዘለዓለማዊ ህይወትን ለመምረጥ … ነጻ” ነን (2 ኔፊ 2፥27)። ነፃ ምርጫ የሌሎች አጥፊ መጥፎ ምርጫዎች ህመምን እና ስቃይን፣ አንዳንዴ ደግሞ ሞትን እራሱ መንስኤ እንዲሆን ይፈቅዳል። ሰው መልካምን ወይም መጥፎን መምረጥ እንዲችል ጌታ እግዚአብሔር ነፃ ምርጫን እንደሰጠ ቅዱሳት መጻህፍት ግልፅ ያደርጉታል (2 ኔፊ 2፥16ን ተመልከቱ)።

  25. የወንጌል ርዕሶች፣ “ነፃ ምርጫ እና ሃላፊነት፣” topics.ChurchofJesusChrist.org።

  26. ወንጌሌን ስበኩ፥ ለሚስዮን አገልግሎት መመሪያ (2019 እ.አ.አ)፣ 52፣ ChurchofJesusChrist.org.።

  27. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “አርአያ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን መሆንሊያሆና፣ ህዳር 2018 (እ.አ.አ)፣ 113።

  28. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 19፥23ን ይመልከቱ።

  29. ሰላም በሰፈነበት እቤት ውስጥ በማደጌ እድለኛ ነበርኩኝ። ይህ የሆነበት አንደኛው ምክንያት የቤተክርቲያን አማኝ አባል በነበረችው በእናታችን ተፅዕኖ ነበር። አባቴ በሁሉም ነገር በጣም የሚገርም ነበር፣ ነገር ግን ቤተክርሰቲያን አይሄድም ነበር። እማዬ አባታችንን አከበረች እና ክርክርን አስወገደች። ልጅ ሳለን መጸለይን እና ቤተክርሲያን መሳተፍን አስተማረችን። እርስ በእርስ እንድንዋደድ እና እንድናገለግልም አስተማረችን (ሞዛያ 4፥14–15 ይመልከቱ)። በእንደዚህ ዓይነት ቤት ውስጥ ማደጌ ሰላምን ሰጠኝ እናም በሕይወቴ ውስጥ ታላቅ በረከት ሆነኝ።

  30. ራስል ኤም. ኔልሰን ከዩታ ዩኒቨርሲቲ ከህክምና ትምህርት ቤት በ22 ዓመታቸው ከክፍላቸው አንደኛ ሆነው ተመረቁ። ለረጅም ጊዜ ቀዶ ጠጋኝ ለመሆን ፈልገው ነበር እና በታላቅ የህክምና ተቋሞች ውስጥ የሚገኙ ምርጥ ስልጠናን ተቀበሉ። በኮሪያ እና ጃፓን ውስጥ የውትድርና ሃላፊነታቸውን በታማኝነት አከናወኑ። ለብዙ ዓመታት በልብ ቀዶ ጥገና መስራች ነበሩ እናም በዓለም አቀፍ ታዋቂ ነበሩ። በህክምና ክህሎታቸው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎችን ለመባረክ ያለው ዝግጁነት አስደናቂ እንደመሆኑ መጠን፣ የፕሬዘዳንት ኔልሰን መንፈሳዊ ዝግጁነት የበለጠ ጠቀሜታ ነበረው። የትልቅ ቤተሰብ ልጆች፣ የልጅ ልጆች እና የልጅ ልጅ ልጆች አባት ናቸው። በመላ ሕይወታቸው ቤተሰባቸውን እና ቤተክርቲያንን በታማኝነት አገልግለዋል።

  31. ረስልኤም. ኔልሰን፣ “መክፈቻ ንግግር፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2020 (እ.አ.አ)፣ 6፤ እንዲሁም ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ደስታ እና መንፈሳዊ ደህንነት፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2016 (እ.አ.አ)፣ 81-84።

  32. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “መክፈቻ ንግግር፣” 6።

አትም