አጠቃላይ ጉባኤ
የክርስቶስ ተከታይ መሆን
የጥቅምት 2021 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


የክርስቶስ ተከታይ መሆን

የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት ድርጊቶቻችንን፣ ምግባራችንን እና ህይወታችንን ከአዳኙ ጋር ለማጣጣም መጣር ማለት ነው።

በቅዱሳት መጻህፍት የግል ጥናቴ ውስጥ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጸው በኋላ ጳውሎስ በመባል የታወቀው የጠርሴሱ ሳውል መለወጥ አስደንቆኝ ነበር።

ጳውሎስ ቤተክርስቲያኗን እና ክርስቲያኖችን በማሳደዱ ድርጊት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ሰው ነበር። ነገር ግን በሰማይ ኃይል እና በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ምክንያት፣ እሱ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ፣ እናም ከታላላቅ የእግዚአብሔር አገልጋዮች አንዱ ሆነ። የሕይወት ምሳሌው አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር።

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ባስተማራቸው ትምህርቶች ውስጥ እርሱ ራሱ የክርስቶስ ተከታይ እንደመሆኑ የእርሱ ተከታዮች እንዲሆኑ ጋብዟቸዋል ( 1 ቆሮንቶስ 11፥1ን ይመልከቱ)። ይህም ከጳውሎስ ጊዜ እስከ አሁን ድረስ ልባዊ እና ተገቢ የሆነ ግብዣ ነው፦ የክርስቶስ ተከታይ መሆን።

የክርስቶስ ተከታይ መሆን ምን ትርጉም እንዳለው ማሰላሰል ጀመርኩኝ። እና ከሁሉም በላይ፣ እንዲህ በማለት መጠየቅ ጀመርኩኝ፣ “በምን መንገድ እርሱን መምሰል አለብኝ?”

የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን ድርጊቶቻችንን፣ ምግባራችንን እና ህይወታችንን ከአዳኙ ጋር ለማጣጣም መጣር ነው። ይህም በጎነትን ማግኘት ነው። ይህም እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ነው።

የአዳኝን ሕይወት አንዳንድ ገጽታዎች አጥንቻለሁ፣ እናም ዛሬ እንደ መልዕክቴ አካል፣ እሱን ለመምሰል የምሞክራቸውን እና ከእናንተ ጋር የምጋራቸውን አራት ባህርያቱን ጠብቄአለሁ።

የአዳኙ የመጀመሪያ ባህርይ ትሕትና ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድመ ምድራዊ ሕይወት ጀምሮ በጣም ትሁት ነበር። በሰማይ በነበረው ሸንጎ፣ ለሰው ልጅ በተዘጋጀው የደህንነት ዕቅድ ውስጥ የእግዚአብሔር ፈቃድ ማሸነፍ እንዳለበት አወቀ እናም ፈቀደ። እንዲህም አለ፣ “አባት ሆይ፣ ፈቃድህ ይፈጸም፣ እናም ክብርም ለዘለአለም ያንተ ይሁን” (ሙሴ 4፥2)።

ኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናን እንዳስተማረ እና አባቱን ለማክበር ራሱን ዝቅ እንዳደረገ እናውቃለን።

በትህትና እንኑር፣ ይህም ሰላምን ያመጣልና ( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 19፥23ን ይመልከቱ)። ትህትና ክብርን ይቀድማል፣ እናም የእግዚአብሔርን ሞገስ በእኛ ላይ ያመጣል፦ “አዎን፣ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፣ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሁታን ግን ጸጋን ይሰጣል” (1 ጴጥሮስ 5፥5)። ትህትና ረጋ ያለ መልሶችን ያመጣል። የጻድቅ ባህርይ ምንጭ ነው።

ሽማግሌ ዴል ጂ. ሬንለንድ እንዳስተማሩት፦

ከእግዚአብሔር ጋር በትህትና የሚጓዙ ግለሰቦች የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ ለእነሱ ምን እንዳደረጉላቸው ያስታውሳሉ።

“በትህትና ከእግዚአብሔር ጋር ስንጓዝ አብረነው በክብር እንተገብራለን” [“በትክክል ተግብሩ፣ ምህረትን ውደዱ እና ከእግዚአብሔር ጋር በትህትና ተጓዙ፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2020 (እ.አ.አ)፣ 111፣ 109]።

የአዳኙ ሁለተኛ ባህርይ ድፍረት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስን በ12 ዓመቱ በህግ ባለሙያዎች መካከል በእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ውስጥ ተቀምጦ መለኮታዊ ነገሮችን ሲያስተምራቸው ሳስበው፣ እርሱ አስቀድሞ በሕይወቱ መጀመሪያ ላይ ጥሩ የድፍረት ስሜት፣ ልዩ ድፍረት እንደነበረው አመለክታለሁ። ብዙዎች ወጣቱ ልጅ በህግ ባለሙያዎች ሲማር ለማየት ቢጠብቁም፣ እርሱ “እየሰሙት ፣ እየጠየቁትም” ያስተምራቸው ነበር (የጆሴፍ ስሚዝ ትርጉም፣ ልኡቃስ 2፥46 [በ ሉቃስ 2፥46ውስጥ፣ የግርጌ ማስታወሻ )።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሙቡጂ-ማዪ ሚስዮን ከ2016 (እ.አ.አ) እስከ 2019 (እ.አ.አ) ድረስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አገለገልን። በሚስዮኑ ውስጥ ከአንድ ዞን ወደ ሌላው የሚኬደው በመንገድ ነበር። በዚያ አካባቢ አንድ ክስተት ተከስቷል፣ ስለት የታጠቁ ሽፍቶች መንገዶችን ሰብረው የመንገደኞችን እንቅስቃሴ ማወክ ጀምረው ነበር።

የዝውውሩ አካል የነበሩ ከአንድ ዞን ወደ ሌላው የሚጓዙ አምስት ሚስዮናውያን የእነዚህ ብጥብጦች ሰለባዎች ነበሩ። እኛ ራሳችን አንዳንድ ጊዜ የዚህ ክስተት ሰለባዎች በመሆናችን፣ ሚስዮናውያንን ለመጎብኘት እና በዞን ጉባኤዎች ለመሳተፍ በእነዚህ መንገዶች ላይ ለመጓዝ እንኳን በመጠራጠር ስለሁላችን ሕይወት እና ደህንነት መፍራት ጀመርን። ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አናውቅም ነበር። መንገዱ ሚስዮናውያኖቻችንን ለመድረስ ያለው ብቸኛ ዘዴ በመሆኑ መጓዙን ለመቀጠል ያለኝን የፍርሃት ስሜት በመግለጽ ለአካባቢው አመራር የላኩትን አንድ ሪፖርት አዘጋጀሁ።

የአፍሪካ ደቡብ ምስራቅ አካባቢ ፕሬዚዳንታችን የነበሩት ሽማግሌ ኬቨን ሃሚልተን በመልሳቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጻፉልኝ፦ “ምክሬ የምትችሉትን ሁሉ እንድታደርጉ ነው። ጥበበኛ ሁኑ እና ጸልዩ። እያወቅክ ራስህን ወይም ሚስዮናውያኖችህን አደጋ ላይ አትጣል፣ ቢሆንም በእምነት ወደፊት ሂድ። “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንም (2 ጢሞቴዎስ 1፥7)።”

ይህ ማበረታቻ በእጅጉ አጠናክሮናል እንዲሁም ሚስዮናችን እስኪያበቃ ድረስ በጉዞው እንድንቀጥል እና በድፍረት እንድናገለግል ፈቅዶልናል፣ ምክንያቱም በዚያ የቅዱስ ጽሁፍ ጥቅስ ውስጥ የሰማይ አባታችንን መመሪያን ሰምተናል።

በዘመናዊ ቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ፣ የጌታን ማበረታቻ የሚያንጸባርቁትን የነብዩ ጆሴፍ ስሚዝን ቃላት እናነባለን፦ “ወንድሞች፣ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ ተልእኮ ላይ መሳተፍ አይኖርብንም? ወደኋላ ሳይሆን ወደፊት ሂዱ። በርቱ፣ ወንድሞች፤ እና ወደ ድል ሂዱ!” (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 128፣22)።

እምነታችንን ለመከላከል እና በእምነት ለመተግበር ሲባል ተወዳጅ ባይሆንም ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለማድረግ ድፍረት ይኑረን። በየቀኑ ንስሐ ለመግባት፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመቀበል እና ትእዛዛቱን ለመታዘዝ ድፍረት ይኑረን። በጽድቅ ለመኖር እና በተለያዩ ኃላፊነቶቻችን እንዲሁም የስራ መደባችን ከእኛ የሚጠበቀውን ለማድረግ ድፍረቱ ይኑረን።

የአዳኙ ሶስተኛ ባህርይ ምህረት ነው። በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት፣ አዳኙ በዝሙት ተይዛ የነበረች አንዲት ሴት በድንጋይ እንዳትወግር ከልክሏል። እርሷንም “ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ” ብሎ አዘዛት (ዮሀንስ 8፥11)። ይህም ወደ ንስሀ እናም በመጨረሻም ወደ ምህረት እንድትሄድ አነሳሳት፣ ቅዱሳት መጻህፍት እንደመዘገቡት፣ “እና ሴቲቱ ከዛ ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔርን አከበረች እናም በስሙም አመነች” (የጆሴፍ ስሚዝ ትርጉም፣ ዮሀንስ 8፥11 [በ John 8:11ውስጥ የግርጌ ማስታወሻ )።

በታህሳስ 2018 (እ.አ.አ) በገና በዓል አምልኮ ወቅት፣ ውድ ፕሬዘዳንታችን ረስል ኤም. ኔልሰን ከአዳኙ ስለተቀበልናቸው አራት ስጦታዎች ተናገሩ። አዳኙ የሚያቀርበው አንድ ስጦታ ይቅርየማለት ችሎታን ነው ብለዋል።

“በእሱ ማለቂያ በሌለው የኃጢያት ክፍያ በኩል፣ እናንተን የጎዱትን እና በእናንተ ላይ ላደረጉት ጭካኔ ሃላፊነትን በጭራሽ የማይቀበሉትን ይቅር ማለት ትችላላችሁ።

“ብዙውን ጊዜ ይቅርታችሁን ከልብ እና በትህትና ለሚፈልግ ይቅር ማለት ቀላል ነው። ነገር ግን አዳኙ በማንኛውም መንገድ የበደላችሁን ማንኛውንም ሰው ይቅር ለማለት ችሎታ ይሰጣችኋል።” (“Four Gifts That Jesus Christ Offers to You” [First Presidency Christmas devotional, Dec. 2, 2018], broadcasts.ChurchofJesusChrist.org)።

የአብን ይቅርታ ለማግኘት እርስ በርሳችን ከልባችን ይቅር እንባባል። ይቅርታ ነፃ ያወጣናል እና በየሳምንቱ እሁድ ከቅዱስ ቁርባን ለመካፈል ብቁ ያደርገናል። በእውነት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ይቅርታ ከእኛ ይፈለጋል።

የአዳኙ አራተኛ ባህርይ መስዋዕት ነው። ይህም የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ክፍል ነው። እኛ እንድንድን አዳኙ የሕይወቱን ከፍተኛ መሥዋዕት ለእኛ ሰጥቶናል። የመሥዋዕት ሥቃይ ስለተሰማው፣ አባቱን ጽዋውን እንዲያርቅለት ጠየቀው፣ ሆኖም ወደ ዘለአለማዊ መሥዋዕት መጨረሻ ሄደ። ይህም የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ነው።

ፕሬዚዳንት ኤም. ረስል ባለርድ ይህን አስተምረዋል፦ “መስዋዕት [የ]ንጹህ ፍቅር ማመልከቻ ነው። ለጌታ፣ ለወንጌል እና ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር መጠን ለእነርሱ ለመሠዋት ፈቃደኛ በሆንነው ሊለካ ይችላል” [“የመስዋዕት በረከቶች፣” ኢንሳይን፣ ግንቦት 1992 (እ.አ.አ)፣ 76]።

አገልግሎትን ለማከናወን፣ ሌሎችን ለማገልገል፣ መልካም ለማድረግ፣ የቤተሰብ ታሪክ ስራን ለመስራት እና የቤተክርስቲያናችንን ጥሪ ለማጉላት ጊዜያችንን መስዋእት ማድረግ እንችላለን።

የእግዚአብሔርን መንግሥት በምድር ላይ ለመገንባት አሥራት፣ የጾም ቁርባን እና ሌሎች መዋጮዎችን በመክፈል የገንዘብ አቅማችንን መስጠት እንችላለን። ከአዳኙ ጋር የገባናቸውን ቃል ኪዳኖች ለመጠበቅ መስዋዕትነት ያስፈልገናል።

ጸሎቴ ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተል እና የኃጢያት ክፍያው በረከቶችን በመጠቀም፣ የበለጠ ትሁት እንድንሆን፣ የበለጠ ደፋሮች እንድንሆን፣ ብዙ ይቅር እንድንል እና ለመንግስቱ የበለጠ መስዋዕት እንድናደርግ ነው።

የሰማይ አባታችን ሕያው መሆኑን እና እያንዳንዳችንን እንደሚያውቅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን፣ ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰ ዛሬ የእግዚአብሔር ነቢይ እንደሆኑ እመሰክራለሁ። የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በምድር ላይ ያለች የእግዚአብሔር መንግስት እንደሆነች እና መፅሐፈ ሞርሞን እውነት እንደሆነ እመሰክራለሁ። በቤዛችን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

አትም