አጠቃላይ ጉባኤ
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ተዓምራት
የጥቅምት 2021 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


9:13

የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ተዓምራት

የእርሱ ወንጌል ተስፋን፣ ሰላምን እና ደስታን ሊያመጣልን እንደሚችል፣ ያም አሁን ብቻ እንዳልሆነ ፣ በሚቀጥሉት ትውልዶች ውስጥም ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሌሎችንም እንደሚባርክ አውቃለሁ።

ማቡሃይ!! ከፊሊፒንስ አስደናቂ ቅዱሳን ፍቅር እና ሞቅ ያለ ፈገግታ አምጥቼላችኋለሁ። የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን ወደ ፊሊፒንስ ደሴቶች ከገቡ በዚህ ዓመት 60 ዓመት ሆኖቸው። ዛሬ 23 ሚስዮኖች እና በ 123 ካስማዎች ከ 800,000 በላይ የቤተክርስቲያን አባላት አሉ። አሁን በስራ ላይ፣ በግንባታ ላይ ያሉ፣ ወይም ይፋ የተደረጉ ሰባት ቤተመቅደሶች አሉ ። ይህ በእውነት ተአምር ነው። በ 2 ኔፊ 10፥21 ውስጥ የሚገኘውን: “በባሕር ደሴቶች ላይ ላሉት የጌታ ተስፋዎች ታላቅ ናቸው” የሚለውን የትንቢት ፍጻሜ እያየን ነው።

ፕሬዚዳንት ሂንክሊ በፊሊፒንስ

ይህ ተአምር ያኔ በ 1961 (እ.አ.አ)በማኒላ ውስጥ በሽማግሌ ጎርደን ቢ ሂንክሊ ጸሎት ለተሰጠው ትንቢትም ፍጻሜ ነው። በዚያ ጸሎት ውስጥ፣ ሽማግሌ ሂንክሊ እንዲህ ብለዋል፦ “በዚህ ምድር ላይ ያሉ ሰዎች እዚህ ለሚመጡ ሰዎች ወዳጅነት፣ እንግዳ ተቀባይነት እና ደግነት እንዲያሳዩ እንዲሁም ሞገስ እንዲኖራቸው በረከቶችህን እንለምናለን፣ እንዲሁም ብዙዎች፣ አዎን፣ ጌታ ሆይ፣ ይህን መልእክት የሚቀበሉ እና በእሱ የሚባረኩ ብዙ ሺዎች እንዲሆኑ እንጸልያለን። በተቀባይ አእምሮ እና በሚያስተውል ልብ፣ እንዲሁም ለመቀበል ባለ እምነት እንዲሁም የወንጌልን መርሆዎች ለመኖር ድፍረት እንዲኖራቸው ባርካቸው”(በአሜሪካ ጦርነት የመታሰቢያ መቃብር፣ ፊሊፒንስ፣ ኤፕሪል 28፣ 1961)(እ.አ.አ) የተደረገ የምረቃ ጸሎት።

የሬቪሎ ቤተሰብ

በብዙ ሺዎች ከሚቆጠሩ ታማኝ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ባሻገር ፣ የወንጌሉ ተአምር በሀገሪቱ እና በሕዝቧ ላይ አዎንታዊ ለውጦችን አምጥቷል። ለዚህ ሕያው ምስክር ነኝ። ወላጆቼ በደቡባዊው ሚንዴኔዮ ደሴት ቤተክርስቲያኗን ሲቀላቀሉ የስድስት ዓመት ልጅ ነበርኩ። በዚያን ጊዜ በመላ አገሪቱ ውስጥ የነበረው አንድ ሚስዮን ብቻ ሲሆን ምንም ካስማዎች አልነበሩም። ወላጆቼ አዳኝን ለመከተል ለነበራቸው ድፍረት እና ቁርጠኝነት ለዘላለም አመሰግናቸዋለሁ። እነርሱን እና በፊሊፒንስ ውስጥ ያሉትን የቤተክርስቲያን ፈር ቀዳጅዎቹ ሁሉ አከብራለሁ። ተተኪዎቹ ትውልዶች እንዲባረኩ መንገድ ጠርገዋል።

ንጉስ ቤንጃሚን በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ እንዲህ አለ፣ “እናም በተጨማሪ ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዛትን የሚጠብቁትን የተባረከና አስደሳቹን ሁኔታ እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ። እነሆም እነርሱ በሁሉም ነገሮች፣ ለጊዜያዊም ሆነ ለመንፈሳዊ፣ የተባረኩ ናቸውና ” (ሞስያ 2፥41)።

የወንጌልን መርሆች እና ሥርዓቶች ስንኖር እና ስንታዘዝ፣ ይበልጥ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንሆን ዘንድ ተባርከናል እንዲሁም ተለውጠናል። ወንጌሉ ቤተሰቦቼን ጨምሮ የፊሊፒንስ ቅዱሳንን የለወጠው እና የባረከው እንደዚያ ነበር። ወንጌል በእውነት የደስታ፣ የተትረፈረፈ ሕይወት መንገድ ነው።

የወንጌሉ የመጀመሪያ መርህ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው። ብዙ ፊሊፒናውያን በእግዚአብሔር ላይ ተፈጥሯዊ እምነት አላቸው። በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እና ለጸሎቶቻችን መልስ ማግኘት እንደምንችል ማወቅ ለእኛ ቀላል ነው።

የኦቤዶዛ ቤተሰብ

የኦቤዶዛ ቤተሰብ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። በወጣትነት ዕድሜዬ ወንድም ኦቤዶዛ የቅርንጫፌ ፕሬዚዳንት ነበር። የወንድም እና የእህት ኦቤዶዛ ትልቁ ፍላጎት በማኒላ ቤተመቅደስ ውስጥ ከቤተሰባቸው ጋር መታተም ነበር። ከማኒላ 1000 ማይሎች(1,600 ኪ.ሜ) ርቃ በምትገኘው ጄኔራል ሳንቶስ ከተማ ውስጥ ይኖሩ ነበር። ዘጠኝ አባላት ላሉት ቤተሰብ ፣ ወደ ቤተመቅደስ ጉዞ ማድረግ የማይቻል ይመስል ነበር። ነገር ግን ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ አንድ ውድ የሆነ ዕንቁ እንደገዛው ነጋዴ ሁሉ (ተመልከት ማቴዎስ13:45–46), እነዚህ ባልና ሚስት ለጉዞው ለመክፈል ቤታቸውን ለመሸጥ ወሰኑ። ተመልሰው የሚገቡበት ቤት ስለሌላቸው እህት ኦቤዶዛ ተጨንቃለች። ወንድም ኦቤዶዛ ግን ጌታ እንደሚሰጣት አረጋገጠላት።

በ 1985 (እ.አ.አ) በቤተመቅደስ ውስጥ ለጊዜ እና ለዘለአለም እንደቤተሰብ ታተሙ። በቤተመቅደስ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ደስታ ማለትም ውድ ዕንቁዎቻቸውን አገኙ። እናም በወንድም ኦቤዶዛ ቃላት የተነገሩት እውነት ሆነው፣ ጌታ በርግጥ ሰጥቷል። ከማኒላ ሲመለሱ የሚያውቋቸው ደግ ሰዎች ማረፊያ ቦታ ሰጧቸው፤ በመጨረሻም የራሳቸውን ቤት አገኙ። በእርሱ ላይ እምነታቸውን የሚያሳዩትን ጌታ ይንከባከባቸዋል።

ሁለተኛው የወንጌል መሰረታዊ መርሆ ንስሀ መግባት ነው። ንስሐ ከኃጢአት መራቅና ይቅርታ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው። የአስተሳሰብና የልብ ለውጥ ነው። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንደሚያስተምሩት፣ “በየቀኑ ማድረግ እና ትንሽ መሻሻል” ነው (“የተሻለ መስራት እና የተሻለ መሆን እንችላለን,” ሊያሆና, ግንቦት 2019 እ.አ.አ ፣ 67)።

ንስሐ ልክ እንደሳሙና ነው። ወጣት የኬሚካል መሐንዲስ እያለሁ በፊሊፒንስ ውስጥ በሳሙና ፋብሪካ ውስጥ እሠራ ነበር። ሳሙናን እንዴት መስራት እንደሚቻል እና የሚሰራበትን ሂደት ተማርኩ። ዘይቶች ከአልካላይን ቤዝ ጋር ስትቀላቅሉ እና ፀረ ባክቴሪያዎችን ስትጨምሩ ባክቴሪያዎችን እና ቫይረሶችን ሊያስወግድ የሚችል ኃይለኛ ንጥረ ነገር ይፈጥራል። ልክ እንደ ሳሙና፣ ንስሐም ማጽጃ ነው። “ርኩስ ነገር ሁሉ [የእግዚአብሔርን] መንግሥት ሊወርስ ስለማይችል” ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን ብቁ እንድንሆን ርኩስዎቻችንን እና አሮጌ ፍርስራሾችን ለማስወገድ እድሉን ይፈቅድልናል። (አልማ 11:37).

በንስሐ አማካኝነት የኢየሱስ ክርስቶስን የማንጻት፣ የመቀደስ ኃይል እናገኛለን የመለወጥ ሂደት ቁልፍ አካል ነው። በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ በአንቲ-ኔፊ-ሊሂዎች ላይ የሆነው ይህ ነው። እነሱ ሙሉ በሙሉ የተለወጡ ላማናውያን ስለነበሩ “መንገዳቸውን አልሳቱም ነበር” ( አልማ 23:6–8ይመልከቱ)። የጦር መሣሪያዎቻቸውን ቀብረው እንደገና አላነሱም። ያንን ቃል ኪዳን ከማፍረስ ሞትን ይመርጣሉ። እናም አረጋገጡት። የከፈሉት መስዋዕትነት ተአምራት እንዳመጣ እናውቃለን፤ ከእነርሱ ጋር የተዋጉ በሺዎች የሚቆጠሩ መሣሪያዎቻቸውን ወርውረው ተለወጡ። ከዓመታት በኋላ እንደኃያል ወጣት ተዋጊዎች የምናውቃቸው ልጆቻቸው በሚያስደንቅ ሁኔታ ከጦርነት ተጠበቁ!

(ሽማግሌ ሬቪሎ አባት

ቤተሰቤ እና ብዙ የፊሊፒንስ ቅዱሳን በተመሳሳይ የመቀየር ሂደት ውስጥ አልፈዋል። የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ስንቀበል እና ቤተክርስቲያንን ስንቀላቀል፣ ከወንጌል ጋር ለመስማማት መንገዳችንን እና ባህላችንን ለወጥን። የተሳሳቱ ወጎችን መተው ነበረብን። ከወንጌል ተምሮ ንስሐ ሲገባ ይህን በአባቴ ውስጥ አየሁት። እሱ ከባድ አጫሽ ነበር፣ ሆኖም ሲጋራዎቹን ጣላቸው እንደገና አንድም አልነካም። ለመለወጥ ባደረገው ውሳኔ ምክንያት ከእሱ የወጡ አራት ትውልዶች ተባርከዋል።

የሬቪሎ ቤተሰብ ትውልዶች

ንስሐ በቅዱስ ሥርዓቶች አማካኝነት ቃል ኪዳኖችን ወደመፈጸም እና ወደመጠበቅ ይመራናል። የመዳን እና ከፍ ከፍ የማለት የመጀመሪያው ስርዓት ለኃጢአት ስርየት ውሃ ውስጥ በመጥለቅ የሚደረግ ጥምቀት ነው። ጥምቀት የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ለመቀበል እና ከጌታ ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት ያስችለናል። በየሳምንቱ ቅዱስ ቁርባንን ስንወስድ ይህንን የጥምቀት ቃል ኪዳን ማደስ እንችላለን። ይሄም ተአምር ነው!

ወንድሞች እና እህቶች፣ ይህንን ተአምር ወደ ሕይወታችሁ እንድታመጡ እጋብዛችኋለሁ። ወደኢየሱስ ክርስቶስ ኑ፤ እንዲሁም በእሱ ላይ ያላችሁን እምነት ማሳየትን ምረጡ፤ ንስሃ ግቡ እና በመዳን እና ከፍ ከፍ በማለት ሥርዓቶች ውስጥ ያሉትን ቃል ኪዳኖች አድርጉ እንዲሁም ጠብቁ።። ይህ ከክርስቶስ ጋር እንድትጣመሩ እና የአምላካዊነትን ኃይል እና በረከቶች እንድትቀበሉ ያስችላችኋል ( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84:20ይመልከቱ).

ስለኢየሱስ ክርስቶስ እውነታ እና ህልውና እንዲሁም እያንዳንዳችንን ስለመውደዱ እመሰክራለሁ። የእርሱ ወንጌል ተስፋን፣ ሰላምን፣ እና ደስታን ሊያመጣልን እንደሚችል አውቃለሁ፤ አሁን ብቻ ሳይሆን፣ በሚቀጥሉት ትውልዶች ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎችንም ይባርካል። የፊሊፒንስ ቅዱሳን ቆንጆ እና ሞቅ ያለ ፈገግታ ምክንያት ያ ነው። የወንጌል ተአምር እና የክርስቶስ ትምህርት ነው። ይህንን በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም እመሰክራለሁ፣ አሜን።