ቅደም ተከተል ስርዓት ያለው ቤት
“የቅደም ተከተል ስርዓት” ጌታ እኛን እንደ ልጆቹ ጠቃሚ መርሆዎችን የሚያስተምርበት ቀላል፣ ተፈጥሮአዊ እና ውጤታማ መንገድ ነው።
በሙያዊ ሕይወቴ እና በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ባገለገልኩት አገልግሎት፣ ይህንን ብዙ ሺህ ጊዜ አድርጌያለሁ—ግን ከኋላዬ ከተቀመጡት 15 ሰዎች በፊት በጭራሽ አላደረኩም። የእናንተ እና የእነርሱ ጸሎት ይሰማኛል።
ወንድሞች እና እህቶች፣ በደቡብ ፓስፊክ ውስጥ የቶንጋ መንግስት ተወላጅ ነኝ፣ ነገር ግን በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ነው ያደኩት። ወረርሽኙ በመቶዎች ምናልባት በሺዎች የሚቆጠሩ በዓለም ዙሪያ በማገልገል ላይ የነበሩ ወጣት ቶንጋውያን ሚስዮናውያንን በተዘጉ ድንበሮቹ ምክንያት ወደ ውድ አገራቸው እንዳይመለሱ አስቀርቷል። የተወሰኑ ቶንጋውያን ሽማግሌዎች ለሶስት ዓመታት እና እህቶች ደግሞ ለሁለት ዓመታት በሚስዮናቸው ቆይተዋል። የእኛ ህዝቦች በሚታወቁበት በእምነት በትዕግስት ይጠብቃሉ። ይሁን እና በአጥቢያችሁ እና በካስማችሁ ውስጥ እያገለገሉ ያሉ የተወሰኑት የበለጠ—በእድሜ እና በሽበት እኔን እየመሰሉ ከመጡ በጣም እንዳትደናገጡ። በሁሉም ቦታ ላሉ ሚስዮናውያን በወረርሽኙ ምክንያት ካሰቡት በላይ ረጅም ወይም አጭር ቢሆንም ስለአገልግሎታቸው አመስጋኞች ነን።
ዲያቆን በነበርኩኝ ሰዓት በአንድ እሁድ፣ የሆነች ሴት ወደ ህንፃው ውስጥ ገና በገባችበት ጊዜ በመተላለፊያው ውስጥ የቅዱስ ቁርባን ውኃን በማሳለፍ ላይ ነበርኩኝ። በታዛዥነት መንፈስ ቀረብኳት እና ውኃውን አቀበልኳት። እራሷን በማነቃነቅ፣ ፈገግ በማለት ውኃን ወሰደች። በጣም ስላረፈደች ዳቦውን ለመውስድ አልቻለችም። ይሄ ከተከሰተ ከትንሽ ጊዜ በኋላ፣ የቤት ለቤት አስተማሪዬ ኔድ በሪምሊ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ብዙ ሁኔታዎች እና በረከቶች ለእኛ በቅደም ተከተል ስርዓት እንደሚሰጡን አስተማረኝ።
በዛ ሳምንት መጨረሻ ላይ ኔድ እና የእሱ ጓደኛ የማይረሳ ትምህርት ይዘው ወደ ቤታችን መጡ። እግዚአብሔር ምድርን ሲፈጥራት የቅደም ተከተል ስርዓት እንደነበረው ኔድ አስታወሰን። ምድርን በምን ቅደም ተከተል ስርዓት እንደፈጠራት ጌታ ለሙሴ ለመግለፅ ጊዜውን ወሰደ። መጀመሪያ፣ ብርሃንን ከጨለማ፣ ከዛ ውኃን ከደረቅ መሬት በመከፋፈል ጀመረ። ታላቁን ፍጥረቱን ማለትም የሰው ዘርን ከአዳም እና ከሔዋን ጀምሮ አዲስ ከተፈጠረችው ፕላኔት ጋር ከማስተዋወቁ በፊት የእፅዋቶችን እና የእንስሳቶችን ሕይወት ጨመረ።
“እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው”። …
“እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበር” (ዘፍጥረት 1፥27፣ 31)።
ጌታ ተደሰተ። እናም በሰባተኛውም ቀን ከስራው አረፈ።
ምድር የተፈጠረችበት ተከታታይ ቅደም ተከተል ለእግዚአብሔር በጣም አስፈላጊ የሆነውን ብቻ ሳይሆን ምድርን ለምን እና ለማን እንደፈጠረ ፍንጭ ይሰጠናል።
ኔድ ብሪምሊ የተነሳሳ ትምህርቱን ቀላል በሆነ ዓረፍተ ነገር እንደዚህ ቋጨ፦ “ቫይ፣ የእግዚአብሔርም ቤት ስርዓት ያለው ነው። ሕይወትህን በስርዓት እንድትኖሩ ይፈልጋል። ተገቢ በሆነ ቅደም ተከተል። ከማግባትህ በፊት ሚስዮን እንድታገለግል ይፈልጋል።” ይህን አስመልክቶ፣ የቤተክርስቲያን መሪዎች በወቅቱ ይህን ያስተምራሉ፣ “እያንዳንዱ የሚችል ወጣት ወንድ ለማገልገል እንዲዘጋጅ ጌታ ይጠብቃል። … ወጣት ሴቶች … ለማገልገል የሚፈልጉ መዘጋጀትም አለባቸው” (General Handbook: Serving in The Church of Jesus Christ of Latter-day Saints [ጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ፦ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማገልገል]፣ 24.0፣ ChurchofJesusChrist.org ይመልከቱ)። ወንድም ብሪምሊ እንዲህ ቀጠለ፣ “ልጆች ከመውለዳችሁ በፊት እንድትጋቡ እግዚአብሔር ይፈልጋል። ትምህርት ስታገኙ ችሎታችሁን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንድታዳብሩ ይፈልጋል። ሕይወታችሁን ከቅደም ተከተል ውጪ ለመኖር ከመረጣችሁ፣ ሕይወትን የበለጠ አስቸጋሪ እና የተመሰቃቀለ ሆኖ ታገኙታላችሁ።
በሃጢያት ክፍያው አማካኝነት፣ በእራሳችን ወይም በሌሎች ጥሩ ያልሆኑ ምርጫዎች ሳቢያ የተመሰቃቀለ ወይም ቅደም ተከተል የሌለው ሕይወታችንን ወደ ቅደም ተከተል ለመመለስ አዳኙ እንደሚረዳንም ወንድም ብሪምሊ አስተማረን።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፣ “ለቅደም ተከተል ስርዓት” አግራሞት አለኝ። በሕይወት እና በወንጌል ውስጥ የቅደም ተከተል ንድፎችን የመፈለግ ልምድን አካበትኩኝ።
ሽማግሌ ዴቪድ ኤ. ቤድናር ይህን መርሆ አስተማሩ፣ “የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ስናጠና፣ ስንማር እና ስንኖር፣ ቅደም ተከተል ብዙ ጊዜ አስተማሪ ይሆናል። ምሳሌ ፣ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የአዳኝ ወንጌል ሙላት ሲታደስ ከተከሰቱት ዋና ዋና ክስተቶች ቅደም ተከተል ስለ መንፈሳዊ ቅድሚያ ስለምንማረው ትምህርቶች እንመልከት።”
ሽማግሌ ቤድናርም የመጀመሪያውን ራዕይ እና በመጀመሪያ ለጆሴፍ ስሚዝ የተገለጠበትንምወጣት ልጅ ነቢይን መጀመሪያየእግዚአብሔርን ተፈጥሮ እና ባህሪ፣ ቀጥሎም በዚህ በመጨረሻው ክፍለ ዘመን ውስጥ መጽሐፈ ሞርሞን እና ኤሊያስ እስራኤሎችን በመጋረጃው ሁሉቱም ክፍል በመሰብሰብ ላይ ስለሚጫወቱት ሚና በማስተማር እንደተጠቀመ ዘርዝረዋል።
ሽማግሌ ቤድናር እንዲህ ደመደሙ፣ “ይህ የሚያነሳሳ ቅደም ተከተል ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ያለው የመለኮት ከፍተኛ ቅደም ተከተል ምን እንደሆነ አስተማሪ ነው” (”The Hearts of the Children Shall Turn፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2011 እ.አ.አ)።
ያደረኩት አንዱ ምልከታ “የቅደም ተከተል ስርዓት” ጌታ እኛን እንደ ልጆቹ ጠቃሚ መርሆዎችን የሚያስተምርበት ቀላል፣ ተፈጥሮአዊ እና ውጤታማ መንገድ መሆኑን ነው።
በሌላ መንገድ የማይገኘውን ለመማር እና ልምድን ለማግኘት ወደ ምድር መጥተናል። የእኛ እድገት ለእያንዳንዳችን በግል ልዩ ነው እና የሰማይ አባታችን ዕቅድ ጠቃሚ አካል ነው። የእኛ አካላዊ እና መንፈሳዊ እድገት በደረጃዎች ይጀምራል እናም በቅደም ተከተል ልምድን ስናገኝ ቀስ እያለ ያድጋል።
አልማ በእምነት ላይ—የፍሬን ምሳሌ በመስጠት ማለትም ከተንከባከብነው እና በትክክል ከመገብነው፣ ከትንሽ ጣፋጭ ፍሬዎችን ወደሚያፈራ ትልቅ ዛፍ እንደሚቀየር ኃይለኛ ስብከትን ይሰጣል ( አልማ 32፥28–43ን ይመልከቱ)። ትምህርቱ ለፍሬው—ወይም ለእግዚአብሔር ቃል—በልባችሁ ውስጥ ቦታ ከሰጣችሁት እና ከመገባችሁት እምነታችሁ ይጨምራል ማለት ነው። የእግዚአብሔር ቃል “በደረታሁ ውስጥ ማደግ” ሲጀምር እምነታችሁ ይጨምራል (ቁጥር 28)። ያም “በፋፋና በበቀለ፣ እናም ማደግ በጀመረ ጊዜ” (ቁጥር 30) እይታዊ እና አስተማሪ ነው። ቅደም ተከተልም አለው።
ጌታ እንደአቅማችን እንዲሁም በምንማርበት መንገድ በግል ያስተምረናል። እድገታችን የሚወሰነው በፈቃደኝነታችን፣ በተፈጥሮአዊ የማወቅ ጉጉት፣ በእምነት መጠን እና በመረዳት ላይ ነው።
ኔፊ፣ ጆሴፍ ስሚዝ በከርትላንድ ኦሃዮ ውስጥ ከ2,300 ዓመታት በኋላ የሚማረውን ነገር ተምሮ ነበር፦ “እነሆም፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለሰው ልጆች በትዕዛዝ ላይ ትዕዛዝ፣ በስርዐት ላይ ስርዐት፣ ጥቂት በዚህ፣ ጥቂት በዚያ እሰጣለሁ፤ ትምህርቴን የሚሰሙ፣ እናም ምክሬን የሚያደምጡ የተባረኩ ናቸው፣ ጥበብን ይማራሉና” (2 ኔፊ 28፥30)።
ያ “በትዕዛዝ ላይ ትዕዛዝ፣ በስርአት ላይ ስርአት፣ ጥቂት በዚህ፣ ጥቂት በዚያ” የምንማረው ነገር ቅድም ተከተልን የጠበቀ ነው።
በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ጊዜ የሰማናቸውን የሚከተሉትን ዓረፍተ-ነገሮች አስቡ፦ “የመጀመሪያ ነገር መጀመሪያ ነው” ወይም “ከስጋ በፊት ወተት መግቧቸው።” “ከመሮጣችን በፊት መራመድ አለብን” የሚለውስ? እያንዳንዱ እነዚህ አባባሎች ቅደም ተከተል የሆነ ነገርን ይገልፃሉ።
ታዓምራት በቅደም ተከተል ስርዓት መልኩ ነው የሚሰሩት። ታዓምራት የሚከሰቱት እምነትን ስንለማመድ ነው። እምነት ታዓምራትን ይቀድማል።
ወጣት ወንዶች በአሮናዊ የክህነት ክፍሎች የሚሾሙት በቅደም ተከተል መሰረት ነው፣ ማለትም የሚሾመውን ግለሰብ እድሜ አስመልክቶ ነው፦ ዲያቆን፣ አስተማሪ እና ከዚያም ካህን።
የደህንነት እና ከፍ ከፍ የማለት ስርዓቶች በተፈጥሮ ቅደም ተከተላቸውን የጠበቁ ናቸው። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ከመቀበላችን በፊት እንጠመቃለን። የቤተመቅደስ ስርዓቶች በተመሳሳይ መልኩ ቅደም ተከተላቸውን የጠበቁ ናቸው። በእርግጥ፣ ጓደኛዬ ኔድ ብሪምሊ በጥበብ እንዳስተማረኝ፣ ቅዱስ ቁርባን ቅደም ተከተሉን የጠበቀ ነው—ማለትም በዳቦው ይጀምራል ከዚያም ውኃው ይከተላል።
“ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና አላቸው፣ እንካችሁ፣ ብሉ ይህ አካሌ ነው።
“ከዛም በወይን የተሞላው ጽዋን አንስቶ አመሰገነ እና ጽዋውን ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ አለ፤
“ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።” (ማቴዎስ 26፥26–28).
በኢየሩሳሌም እና በአሜሪካ ውስጥ አዳኙ ቅዱስ ቁርባንን ተመሳሳይ በሆነ ስርዓት አበረከተ።
“እነሆ፣ ቤቴ የስርዓት ቤት ነው፣ ይላል ጌታ አምላክ፣ እና የግራ መግባት ቤት አይደለም።” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 132፥8)።
ንስሀ ቅደም ተከተሉን የጠበቀ ነው። የሚጀምረው በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት ነው ትንሽም ብትሆን እንኳን። እምነት “የተሰበረ ልብ እና የተዋረደ መንፈስ” እንዲኖር አስፈላጊ የሆነውን ትህትናን ይፈልጋል (2 ኔፊ 2፥7)።
በእርግጥ፣ የወንጌል የመጀመሪያ አራቱ መርሆዎች ቅደም ተከተላቸውን የጠበቁ ናቸው። “የወንጌሉ ቀዳሚ መሰረታዊ መርሆችና ስነ ስርዓቶች፥ አንደኛ፣ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት፤ ሁለተኛ፣ ንስሐ መግባት፤ ሶስተኛ፣ ለኃጥያት ስርየት በማጥለቅ መጠመቅ፤ አራተኛ፣ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ለመስጠት እጆችን መጫን እንደሆኑ እናምናለን” (የእምነት አንቀፅ 1፥4)።
ንጉሥ ቢኒያም ህዝቦቹን ይህን ጠቃሚ እውነታ እንዲህ አስተማረ፦ “እናም እነዚህ ነገሮች ሁሉ በጥበብና በዕቅድ እንደተደረጉ ተመልከቱ፣ ሰው ከአቅሙ በላይ ፈጥኖ መሮጡ አስፈላጊ አይደለምና። እናም እንደገና፣ ሽልማቱን ያሸንፍ ዘንድ ትጉህ መሆኑ አስፈላጊ ነው፣ ስለዚህ፣ ሁሉም ነገሮች በስርዓት መደረግ አለባቸው” (ሞዛያ 4፥27)።
ሕይወታችንን በቅደም ተከተል እንኑር እና ጌታ የሰጠንን ቅደም ተከተል ለመከተል እንሻ። ጌታ ለእርሱ ምን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስተምርባቸውን መንገዶች እና ቅደም ተከተሎች ስንሻ እና ስንከተል እንባረካለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም፣ አሜን።