አጠቃላይ ጉባኤ
ለጌታ ጊዜ ስጡ
የጥቅምት 2021 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


5:49

ለጌታ ጊዜ ስጡ

በሕይወታችሁ ውስጥ በየእለቱ ለጌታ ጊዜ በመስጠት የዓለምን ማታለያ እንድትቃወሙ ዛሬ እማጸናኋለሁ።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እርሱ ምን እንዲናገሩ እንደሚፈልግ ለማወቅ በትጋት በፈለጉ የጌታ አገልጋዮች ለሁለት ቀናት በደንብ ተምረናል።

ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚሆን ሙላትን ተቀብለናል። አሁን የሚጠየቀው ጥያቄም፣ በሰማነው እና በተሰማን ምክንያት እንዴት ልዩ እንሆናለን? የሚለው ነው

ወረርሽኙ አንዳንድ ጊዜ ከቁጥጥራችን በላይ በሆኑ ሁኔታዎች ሕይወት ምን ያህል በፍጥነት እንደሚለወጥ አሳይቷል። ሆኖም፣ ልንቆጣጠራቸው የምንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እኛ ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች እናስቀምጣለን እና ጉልበታችንን፣ ጊዜያችንን እና መንገዶቻችንን እንዴት እንደምንጠቀም እንወስናለን። እርስ በእርስ እንዴት እንደምንንከባከብ እንወስናለን። እኛ ለእውነት እና ለመመሪያ የምንዞርባቸውን ሰዎች እንመርጣለን።

የዓለም ድምፆች እና ግፊቶች አሳታፊ እና ብዙ ናቸው። ነገር ግን በጣም ብዙ ድምፆች አታላይ፣ አሳሳች ናቸው፣ እና ከቃል ኪዳኑ መንገድ ሊያወጡን ይችላሉ። የሚከተለውን እና የማይቀረውን የልብ ስብራት ለማስወገድ፣ በሕይወታችሁ ውስጥ በየእለቱ ለጌታ ጊዜ በመስጠት የዓለምን ማታለያ እንድትቃወሙ ዛሬ እማጸናችኋለሁ።

አብዛኛው የምታገኙት መረጃ ከማህበራዊ ወይም ከሌላ ሚዲያ ከሆነ፣ የመንፈስን ሹክሹክታ የመስማት ችሎታችሁ ይቀንሳል። በየዕለቱ በጸሎት እና በወንጌል ጥናት ጌታን የማትፈልጉ ከሆነ፣ ቀልብ ለሚስቡ ግን እውነት ላልሆኑ ፍልስፍናዎች ተጋላጭ ትሆናላችሁ። ታማኝ የሆኑት ቅዱሳን እንኳን በማይቋረጠው በባቢሎን ባንድ የከበሮ ድለቃ ሊሳሳቱ ይችላሉ።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ለጌታ ጊዜ እንድትሰጡ እማጸናችኋለሁ! መንፈስ ቅዱስ ሁል ጊዜ፣ ከእናንተ ጋር እንዲኖር የሚፈቅዱትን ነገሮች በማድረግ፣ የራሳችሁን መንፈሳዊ መሠረት ጽኑ እና የጊዜን ፈተና መቋቋም የሚችል አድርጉ።

ጥልቅ የሆነውን እውነት በጭራሽ ዝቅ አድርጋችሁ አትገምቱ፣ ይህም “መንፈስ ቅዱስ ነገሮች በእርግጥ እንዳሉ፣ እናም ነገሮች በእርግጥ እንደሚሆኑ ይናገራል።” 1 እርሱም “ማድረግ ያለባችሁን ሁሉ ያሳያችኋል።” 2

ትኩረታችሁን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ከማስተካከል የበለጠ መንፈስን የሚጋብዝ ነገር የለም። ስለ ክርስቶስ ተናገሩ፣ በክርስቶስ ደስ ይበላችሁ፣ በክርስቶስ ቃሎች ላይ ተመገቡ፣ እናም በክርስቶስ ጽናት ወደፊት ቀጥሉ። 3 እርሱን በማምለክ፣ ቅዱስ ቁርባንን በመካፈል፣ እና ቀኑን ቅዱስ አድርጋችሁ በመጠበቅ ሰንበታችሁን አስደሳች አድርጉ። 4

ዛሬ ጠዋት እንደገለጽኩት፣ እባካችሁ ለጌታ በቅዱስ ቤቱ ውስጥ ጊዜ ስጡ። እንደ ቤተመቅደስ አገልግሎት እና የቤተመቅደስ አምልኮ መንፈሳዊ መሠረታችሁን የሚያጠናክር ምንም ነገር የለም።

በአዲሱ ቤተመቅደሶቻችን የሚሰሩትን ሁሉ እናመሰግናለን። በመላው ዓለም እየተገነቡ ናቸው። ዛሬ በሚቀጥሉት ቦታዎች ወይም በአጠገባቸው ተጨማሪ ቤተመቅደሶችን ለመገንባት ያለንን እቅድ ሳሰተዋውቅ በደስታ ነው፦ ካኦሺንግ፣ ታይዋን፤ ታክሎባን፣ ፊሊፒንስ፤ ሞንሮቪያ፣ ላይቤሪያ፤ ካናንጋ፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፤ አንታናናሪቮ፣ ማዳጋስካር፤ ኩሊያካን፣ ሜክሲኮ፤ ቪቶሪያ፣ ብራዚል፤ ላ ፓዝ፣ ቦሊቪያ፤ ሳንቲያጎ ምዕራብ፣ ቺሊ፤ ፎርት ዎርዝ፣ ቴክሳስ፤ ኮዲ፣ ዋዮሚንግ፤ ሬክስበርግ ሰሜን፣ አይዳሆ፤ ሄበር ቫሊ፣ ዩታ፤ እንዲሁም የኦረም ዩታ ቤተመቅደስ ከተመረቀ በኋላ የፕሮቮ ዩታ ቤተመቅደስ ይታደሳል።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች እወዳችኋለሁ። ጌታ ያውቃችኋል እንዲሁም ይወዳችኋል። አዳኛችሁ እና ቤዛችሁ ነው። እርሱ ቤተክርስቲያኑን ይመራል። እናንተ በሕይወታችሁ ውስጥ ለእሱ ጊዜ በየዕለቱ ስትሰጡ በግል ሕይወታችሁ ውስጥ ይመራችኋል።

እንደገና እስክንገናኝ ድረስ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆን ዘንድ የምጸልየው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።