ብቁነት እንከን አልባነት አይደለም
መሞከርን ለመቀጠል ብዙ ጊዜ እንደምትወደቁ ሲሰማችሁ፣ የክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ እና የሚቻለውን ጸጋ እውን እንደሆኑ አስታውሱ።
አንድ ጊዜ በስልኬ ላይ ያለውን ድምጽ ወደ ጽሁፍ መቀየርያን በመጠቀም ለሴት ልጄ እና ለአማቼ መልዕክት ላኩኝ። እንዲህም አልኳቸው፣ “ሰላም ለእናንተ። በእርግጥ እወዳችኋለሁ።” እነሱ የደረሳቸው “ሁለታችሁን እጠላችኋለሁ። መውደድ አለብኝ” የሚል ነበር። በመልካም እና ቀና አላማ የተላከ መልዕክት በቀላሉ እንዴት አለመግባባትን ሊያመጣ መቻሉ አይገርምም? አንዳንድ ጊዜ በእግዚአብሔር የንስሃ እና ብቁነት መልዕክት ላይ ይህ ይከሰታል።
አንዳንዱ ንስሃ እና ለውጥ አስፈላጊ እንዳልሆኑ በስህተት መልዕክት ይቀበላሉ። የእግዚአብሔር መልዕክት ግን ይህ አስፈላጊ እንደሆነ ነው። 1 ነገር ግን እግዚአብሔር የሚወደን ከነእንከኖቻችን አይደለምን? ትክክል ነው! በፍጹምነት ይወደናል። የልጅ ልጆቼን ከነእንከናቸው እወዳቸዋለሁ፣ ነገር ግን ይህ ማለት እንዲሻሻሉ እና መሆን የሚችሉትን ሁሉ እንዲሆኑ አልፈልግም ማለት አይደለም። እግዚአብሔር ባለንበት ይወደናል ሆኖም ግን ባለንበት እንዳይተወን እጅግ አድርጎ ይወደናል። 2 የምድር ላይ ኑሮ ሁሉ ወደ ጌታ ስለማደግ ነው። 3 የክርስቶስ የኃጥያት ክፍያ ትኩረት ለውጥ ብቻ ነው። ክርስቶስ ከሞት ማስነሳት፣ ማንጻት፣ ማጽናናት እና መፈወስ ብቻ ሳይሆን በዚህ ሁሉ ውስጥ ይበልጥ እርሱን እንድንመስል ሊለውጠን ይችላል። 4
አንዳንዱ ንስሃ የአንድ ጊዜ ድርጊት እንደሆነ በስህተት መልዕክት ይቀበላል። ፕሬዘዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ የእግዚአብሔር መልዕክት፣ “ንስሃ … ሂደት [እንደሆነ] ነው።” 5 ንስሃ መግባት ጊዜን ይፈጃል እናም ተደጋጋሚ ጥረት ያስፈልገዋል፣ 6 ስለዚህ ኃጥያትን መተው 7 እና “ያለማቋረጥ መልካምን መስራት እንጂ ኃጥያት ለመፈጸም ምንም ፍላጎት ማጣት” 8 የእድሜ ልክ ስራዎች ናቸው። 9
ህይወት እንደ ሃገር አቋራጭ የመንገድ ጉዞ ነው። መድረስ ያለብን ቦታ በአንድ የነዳጅ ጋን መድረስ አንችልም። ጋኑን በተደጋጋሚ መሙላት ይኖርብናል። ቅዱስ ቁርባንን መቀበል ነዳጅ ማደያ ጋ እንደማቆም ነው። ንስሃ ስንገባ እና ቃል ኪዳናችንን ስናድስ፣ ትዕዛዛቱን ለመጠበቅ በፈቃደኝነት እንስማማለን፤ እግዚአብሔር እና ክርስቶስም በመንፈስ ቅዱስ ይባርኩናል። 10 በአጭሩ፣ መንገዳችንን ለመቀጠል ቃል እንገባለን፤ እግዚአብሔር እና ክርስቶስ ደግሞ ጋናችንን ይሞሉልናል።
አንዳንዶቹ ከመጥፎ ልማዶች ነጻ ስላልሆኑ፣ በወንጌል ላይ ሙሉ በሙሉ ለመሳተፍ ብቁ እንዳልሆኑ የተሳሳተ መልዕክት ይደርሳቸዋል። የእግዚአብሔር መልዕክት ግን ብቁነት እንከን አልባነት እንዳልሆነ ነው። 11 ብቁነት ሐቀኛ መሆን እና መጣር ማለት ነው። እኛ ለእግዚአብሔር፣ ለክህነት መሪዎች እና ለሚወዱን ለሌሎች እውነተኞች መሆን አለብን፣ 12 እንዲሁም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ለመጠበቅ መጣር እና ስለተንሸራተትን ብቻ ተስፋ መቁረጥ የለብንም። 13 ሽማግሌ ብሩስ ሲ. ሃፍን እንዳሉት፣ የክርስቶስ አይነት ባህርይን ማዳበር “ከእንከን አልባነት ይልቅ ትዕግስት እና ጽናትን ይጠይቃል።” 14 ጌታም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች “ለሚወዱኝ እና ሁሉንም ትዕዛዜን ለሚጠብቁ እንዲሁም ለመፈጸም ለሚፈልጉ ጥቅም የተሰጡ ናቸው” ብሏል። 15
አንድ ወጣት ልጅ፣ ዴመን ብዬ እጠራዋለሁ፣ “ሳድግ በአጸያፊ ምስሎች እቸገር ነበር። ነገሮችን ማስተካከል ባለመቻሌ ሁልጌዜ እጅግ በጣም አፍርም ነበር።” ዴመን በተንሸራተተ ቁጥር የጸጸት ህመም ከፍ እያለ በመምጣቱ ራሱን ለየትኛውም አይነት ጸጋ፣ ይቅርታ ወይም ከእግዚአብሔር ተጨማሪ እድል እንደማያስፈልገው አድርጎ ያስብ ነበር። እንዲህም አለ፦ “ሁል ጊዜም መጥፎ ስሜት መሰማት እንደሚገባኝ ወሰንኩ። ጠንክሬ ለመስራት እና ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ይህን ነገር ለመቆጣጠር ፈቃደኛ ባለመሆኔ ምናልባት እግዚአብሔር እንደሚጠላኝ አሰብኩ። ለሳምንት ያህል አንዳንዴም እስከ ወር እቆያለሁ፣ ነገር ግን እንደገና ወደኋላ ተመልሼ ‘እኔ መቼም ብቁ አልሆንም፣ ስለዚህ ሙከራዬ ምን ጥቅም አለው?’ ብዬ አስባለሁ።”
እንደዚህ ባለ አንድ የወረደ ወቅት ዴመን ለክህነት መሪው እንዲህ አለ፦ “ምናልባት ቤተክርስትያን መምጣት ማቆም አለብኝ። ግብዝ መሆን ሰልችቶኛል።”
መሪውም እንዲህ በማለት መለሰለት፦ “ለመተው እየጣርክ ያለ መጥፎ ልማድ ስላለህ ግብዝ አትሆንም። አንተ ግብዝ የምትሆነው ከደበከው፣ ስለነገሩ ከዋሸህ ወይም ቤተክርስትያኗ እንዲህ አይነት ከፍ ያለ ስርዓት ስላላት ችግር አለባት ብለህ ካሰብክ ነው። ስለ ምግባርህ ሃቀኛ መሆን እና ወደፊት ለመቀጠል እርምጃ መውሰድ ግብዝነት አይደለም። ደቀመዝሙር መሆን ማለት ነው።” 16 ይህ መሪ የጠቀሰው ሽማግሌ ሪቻርድ ጂ. ስኮት እንዲህ ብለው ያስተማሩትን ነበር፦ “ጌታ ድክመትን ከአመጻ በተለየ መልኩ ይመለከታል። … ጌታ ስለ ድክመት የሚያወራው ሁል ጊዜ ከምህረት ጋር ነው።” 17
ያ እይታ ለዴመን ተስፋ ሰጠው። እግዚአብሔር ከላይ ሆኖ “ዴመን እንደገና አበላሸ” እያለው እንዳልሆነ ተረዳ። በምትኩ ምናልባት “ዴመን ምን ያህል እንደተሻሻለ ተመልከቱ” እያለ ይሆናል። ይህ ወጣት በሃፍረት ወደታች ማየት ወይም ለሰበብ እና ለምክንያት ወደጎን ማየቱን በስተመጨረሻ አቆመ። ለመለኮታዊ እርዳታ ወደላይ ተመለከተ እናም አገኘ። 18
ዴመንም እንዲህ አለ፦ “ከዚህ ቀደም ወደ እግዝአብሔር እዞር የነበረው ለይቅርታ ብቻ ነበር፣ አሁን ግን በተጨማሪ ጸጋውን—የእርሱን ‘የማስቻል ሃይል’ እጠይቃለሁ [Bible Dictionary (የመፅሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃል)፣ “ጸጋ”]። ከዚህ በፊት እንደዛ አድርጌ አላውቅም። አሁን ላይ ላደረኩት ነገር ራሴን በመጥላት እጅግ ያነሰ ጊዜ አሳልፋለሁ፥ ብዙውን ጊዜ ደግሞ ላደረገልኝ ነገር ኢየሱስን ይበልጥ በመውደድ አሳልፋለሁ።”
ዴመን ለምን ያህል ጊዜ እንደተቸገረ ስናስብ፣ እሱን የሚረዱ ወላጆች እና መሪዎች በችኮላ “ሁለተኛ አልደግምም” እንዲል ማድረግ ወይም “ብቁ” ተብሎ እንዲታሰብ የመታቀብ ስርዓትን ማስቀመጥ የማይረዳ እና ተጨባችነት የሌለው ነው። በምትኩ በትንሽ የሚቻሉ ግቦች ጀመሩ። እነርሱ ግትር የሆነ ግምታቸውን በማስወገድ እና ትኩረታቸውን በሚጨምር እድገት ላይ አደረጉ፤ ይህም ዴመን በውድቀት ፈንታ ስኬት እንዲገነባ ረድቶታል። 19 እሱም ባርነት ላይ እንደነበሩ ሊምሂ ህዝቦች “ቀስ በቀስ መበልጸግ” እንደሚችል ተማረ። 20
ሽማግሌ ዲ. ቶድ ክርስቶፈርሰን እንዲህ በማለት መክረዋል፦ “በጣም ትልቅ ነገርን ለመቋቋም፣ በትንሽ በትንሽ፣ በዕለታዊ ደጊቶች፣ መሥራት ያስፈልገን ይሆናል። … አዲስ እና ጤናማ ልምዶችን በባህሪያችን ውስጥ ማካተት ወይም መጥፎ ልምዶችን ወይም ሱሶችን ማሸነፍ [ብዙውን] ጊዜ ዛሬ ጥረትን ሌላ ነገን ከዚያም ሌላን ፣ ምናልባትም ለብዙ ቀናት ፣ ወሮችን እና ዓመታትን እንኳን መሞከር ማለት ነው። ነገር ግን ልናደርገው እንችላለን ምክንያቱም እግዚአብሔርን በየእለቱ ለሚያስፈልገን እርዳታ … መጠየቅ ስለምንችል ነው።” 21
አሁን፣ ወንድሞች እና እህቶች፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለማንም ቀላል አልነበረም፣ ነገር ግን ለይቶ ማቆያ ጋር የተያያዘው መለየት ከመጥፎ ልማድ ጋር ያሉትን ህይወት ከባድ አድርጓል። ለውጥ የሚቻል እንደሆነ አስታውሱ፣ ንስሃ ሂደት ነው እናም ብቁነት እንከን አልባነት አይደለም። እግዚአብሔር እና ክርስቶስ እዚህ እና አሁን ሊረዱን ፈቃደኛ እንደሆኑ አስታውሱ። 22
አንዳንዶች እግዚአብሔር ሊረዳቸው የሚጠብቅው ንስሃ ከገቡ በኋላ እንደሆነ በስህተት መልዕክት ይቀበላሉ። የእግዚአብሔር መልዕክትም ንስሃ እየገባን ሳለ እንደሚረዳን ነው። “በመታዘዝ መንገድ ላይ የትም ብንሆን” ጸጋው ለእኛ አለ። 23 ሽማግሌ ዲይተር ኤፍ. ኡክዶርፍ እንዲህ ብለዋል፦ “እግዚአብሔር እንከን የሌላቸውን ሰዎች አይፈልግም። እርሱ የሚፈልገው ‘ልባቸውን የሚሰጡትንና ፈቃደኛ የሆነ አዕምሮን ያላቸውን’ [ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 64፥34) ነው፣ እናም እርሱ ‘በክርስቶስ ፍጹም’ [ሞሮኒ 10፥32–33] ያደርጋቸዋል።” 24
ብዙዎች በተሰበሩ እና በተጨናነቁ ግንኙነቶች ተጎድተዋል፣ ስለዚህ በእግዚአብሔር ርህራሄ እና ትዕግሥት ማመን ለእነሱ ከባድ ነው። እግዚአብሔር በችግራችን የሚያገኘን አፍቃሪ አባት እንደሆነ 25 እና “ለሚለምኑት መልካም ነገር መስጠት” 26 የሚያውቅ እንደሆነ ለማየት ያስቸግራቸዋል። ጸጋው ብቁ ለሆነ ብቻ የሚሰጥ ሽልማት አይደለም። እርሱ የሚሰጠን “መለኮታዊ እርዳታ” ነው ብቁ እንድንሆን የሚረዳን። ጻድቅ ለሆነው ብቻ የሚሰጥ ሽልማት አይደለም። እርሱ የሚሰጠው “የሃይል ስጦታ” ነው ጻድቅ እንድንሆን የሚረዳን። 27 እኛ ወደ እግዚአብሔር እና ክርስቶስ ብቻ እየተራመድን አይደለንም። እኛ ከእነሱ ጋር እየተራመድን ነን። 28
በቤተክርስትያኗ ውስጥ ወጣቶች የወጣት ሴቶች እና አሮናዊ ክህነት ሸንጎ ጭብጥ መልዕክትን ደጋግመው ያነባሉ። ከኒውዚላንድ እስከ ስፔን ከኢትዮጵያ እስከ ጃፓን ወጣት ሴቶች፣ “እኔ የንስሃን ስጦታ አከብራለሁ” ይላሉ። ከቺሊ እስከ ጓቲማላ እስከ ሞሮኒ፣ ዩታም ወጣት ወንዶች፣ “ለማገልገል ስጥር፣ እምነትን ስለማመድ እና በየቀኑ ስሻሻል የቤተመቅደስ ስጦታዎችን እና ዘላቂ የወንጌል ደስታን ለመቀበል ብቁ እሆናለሁ” ይላሉ።
እነዚያን በረከቶች እናም ያ ደስታ እውነተኛ እና ሁሉንም ትዕዛዛት ለሚጠብቁ እናም “ይህን ለማድረግ ፈቃድ ላላቸው” ተደራሽ እንደሆነ ቃል እገባለሁ። 29 መሞከርን ለመቀጠል ብዙ ጊዜ እንደምትወደቁ ሲሰማችሁ፣ የክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ እና የሚቻለውን ጸጋ እውን እንደሆኑ አስታውሱ። 30 የእርሱ “የምህረት ክንዶች ወደ [እናንተ] ተዘርግተዋል”። 31 እናንተ የተወደዳችሁ ናችሁ—ዛሬም፣ በ20 አመት ውስጥ እና ለዘለአለምም። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።