አጠቃላይ ጉባኤ
ዕለታዊ ተሀድሶ
የጥቅምት 2021 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


ዕለታዊ ተሀድሶ

የማያቋርጥ፣ ዕለታዊ የሰማይ ብርሃን ፍሰት ያስፈልገናል። “የመታደስ ዘመናት” ያስፈልጉናል። የግል ተሀድሶ ዘመናት።

እኛ ስለ ክርስቶስ ለመናገር፣ በወንጌሉ ለመደሰት፣ እና በአዳኛችን “መንገድ” ስንሄድ እርስ በእርስ ለመረዳዳት እና ለመደጋገፍ በዚህ ውብ የሰንበት ጠዋት እንሰበስባለን። 1

የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት እንደመሆናችን፣ ለዚህ ዓላማ በያንዳንዱ የሰንበት ቀን፣ ዓመቱን በሙሉ እንሰበስባለን። የቤተክርስቲያኗ አባል ካልሆናችሁም፣ እኛ በጣም በደስታ እንቀበላችኋለን እንዲሁም አዳኝን ለማምለክ እና ከእሱ ለመማር ከእኛ ጋር ስለተቀላቀላችሁ እናመሰግናለን። እንደ እናንተም፣ እኛ ፍፁም ባንሆንም—የተሻሉ ወዳጆች፣ ጎረቤቶች እና የሰው ልጆች ለመሆን እየጣርን ነው፣ 2 እናም የእኛን አርአያ ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተል ይህንን ለማድረግ እንፈልጋለን።

ምስል
አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ

የምሥክራችን ልባዊነት እንደሚሰማችሁ ተስፋ እናደርጋለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው ነው! እርሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው፣ እናም በእኛ ዘመን በምድር ላይ ነቢያትን ይመራል። ሁሉም እንዲመጡ፣ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲሰሙ እና ከቸርነቱ እንዲካፈሉ እንጋብዛለን! እግዚአብሔር በመካከላችን መሆኑን እና ወደ እሱ ለሚቀርቡት ሁሉ በእርግጥ እንደሚቀርብ የግል ምስክርነቴን እሰጣለሁ። 3

በመምህር ጠባብ መንገድ እና በደቀ መዝሙርነት ጎዳና ከእናንተ ጋር መጓዝን እንደ ክብር እንቆጥረዋለን።

በቀጥታ መስመር የመራመድ ጥበብ

የሚሄዱበት የጠፋባቸው ሰዎች በክብ ይዞራሉ የሚል ተደጋጋሚ ጽንሰ-ሀሳብ አለ።. በቅርብ ጊዜ፣ በማክስ ፕላንክ ኢንስቲትዩት የባዮሎጂ ሳይበርኔቲክስ ተቋም ሳይንቲስቶች ያንን ጽንሰ -ሀሳብ ሞክረዋል። ተሳታፊዎችን ጥቅጥቅ ወዳለ ጫካ ወስደው “ቀጥ ባለ መስመር ላይ ተጓዙ” የሚል ቀላል መመሪያ ሰጧቸው። ምንም የሚታዩ የመንገድ ምልክቶች አልነበሩም። የፈተናው ተሳታፊዎች በአቅጣጫ ስሜታቸው ላይ ብቻ መተማመን ነበረባቸው።

እነሱስ እንዴት ያደረጉ ይመስላችኋል?

የሳይንስ ሊቃውንቱም፣ “ሰዎች በእውነቱ የመራመጃ አቅጣጫቸው አስተማማኝ ፍንጮች በሌሉበት በክብ ይዞራሉ” ብለው ደመደሙ። 4 ከዚያ በኋላ ሲጠየቁ፣ አንዳንድ ተሳታፊዎች በጥቂቱ እንኳ አላፈነገጥንም ብለው በራስ በመተማመን ተናግረዋል። ከፍተኛ የመተማመን ስሜት ቢኖራቸውም የጂፒኤስ መረጃ እንደሚያሳየው እስከ 20 ሜትር ዲያሜትር ድረስ ባለው ቀለበት ውስጥ መሄዳቸውን ያሳያል።

ቀጥታ መስመር ላይ ለመጓዝ ለምን እንደዚህ ይከብደናል? አንዳንድ ተመራማሪዎች ትንሽ፣ ብዙም የማይመስል ከመንገድ ላይ መሳት፣ ልዩነት ይፈጥራል ብለው ይገምታሉ። ሌሎች ደግሞ ሁላችንም ከሌላው በመጠኑ ጠንካራ የሆነ አንድ እግር እንዳለን አመልክተዋል። ሆኖም፣ “አብልጦ ሊሆን የሚችለው፣” በቀጥታ ወደ ፊት ለመሄድ እንቸገራለን “[ምክንያቱም] በቀጥታ ወደ ፊት የት እንደሆነ እርግጠኛ አለመሆን እየጨመረ ስለሚሄድ ነው።” 5

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ የሰው ተፈጥሮ ነው አስተማማኝ ምልክቶች ከሌሉ፣ ከትክክለኛው መንገድ እንርቃለን።

ከመንገዱ መራቅ

ትንሽ፣ አነስተኛ የሚመስሉ ምክንያቶች በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማምጣት መቻላቸው የሚያስገርም አይደለም?

እኔ ይህንን ከፓይለትነት የግል ተሞክሮዬ አውቃለሁ። የአውሮፕላን ማረፊያ መቅረብ በጀመርኩ ቁጥር፣ አብዛኛው ቀሪ ሥራዬ አውሮፕላኑን በደህና ወደሚፈለገው ማረፊያ አውራ ጎዳናችን ለመምራት የማያቋርጥ ጥቃቅን የአቅጣጫ እርማቶችን እንደሚያካትት አውቃለሁ።

ተሽከርካሪ መኪና በምትነዱበት ጊዜ ተመሳሳይ ተሞክሮ ሊኖራችሁ ይችላል። ንፋስ፣ የመንገድ መዛባት፣ ያልተስተካከለ የጎማ አቀማመጥ፣ ትኩረተቢስ የሆኑ—የሌሎች አሽከርካሪዎች ድርጊቶችን ሳንጨምር፣ ሁሉም ከታሰበው መንገድ ሊያወጧችሁ ይችላሉ። ለእነዚህ ምክንያቶች ትኩረት መስጠት ከተሳነን፣ መጥፎ ቀን ሊያጋጥማችሁ ይችላል። 6

ምስል
መኪና በመዋኛ ውስጥ

ይህ በስጋዊ አካል ለእኛ ይሠራል።

በመንፈሳዊነትም ላይ ይሰራል።

አብዛኛዎቹ ለውጦች በመንፈሳዊ ሕይወታችን ውስጥ—አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ—ቀስ በቀስ፣ ደረጃ በደረጃ ይከሰታሉ። እንደ ማክስ ፕላንክ ጥናት ተሳታፊዎች፣ እኛ ከመንገዳችን ስንወጣ ላናስተውል እንችላለን። በቀጥታ መስመር እየተጓዝን ስለመሆናችን ከፍተኛ እምነት ሊኖረንም ይችላል። እውነታው ግን፣ እኛን ለመምራት ከተቀመጡት የመንገድ ምልክቶች ዕርዳታ ውጪ ከትክክለኛው አቅጣጫ እንርቃለን እንዲሁም እንሆናለን ብለን ካላሰብንበት ቦታ ላይ መሆናችን የማይቀር ነው።

ይህ ለግለሰቦች እውነት ነው። ለማህበረሰቦች እና ለአገሮችም እውነት ነው። ቅዱሳት መጻህፍት በምሳሌ የተሞሉ ናቸው።

መጽሐፈ መሳፍንት ኢያሱ ከሞተ በኋላ “ጌታን የማያውቅ፣ ለእስራኤልም ያደረገውን ስራዎች የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሳ።” 7

በሙሴ እና በኢያሱ የሕይወት ዘመን የእስራኤል ልጆች አስገራሚ የሰማይ ጣልቃ ገብነቶች፣ ጉብኝቶች፣ ማዳን እና ተአምራዊ ድሎች ቢኖሩም፣ በአንድ ትውልድ ዘመን ውስጥ ሕዝቡ መንገዱን ትቶ እንደ ፍላጎቱ መራመድ ጀመረ። እና በእርግጥ፣ ለዚያ ባህሪ ዋጋ ለመክፈል ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም።

አንዳንድ ጊዜ ይህ እምነትን መተው ከትውልዶች በኋላ ይከሰታል። አንዳንድ ጊዜ በዓመታት ወይም በወራት ጊዜ ውስጥ ይከሰታል። 8 ነገር ግን ሁላችንም ተጋላጭ ነን። ቀደም ባሉት ጊዜያት መንፈሳዊ ልምዶቻችን የቱንም ያህል ጠንካራ ብንሆንም፣ እንደሰው ወደ መንከራተት እናዘነብላለን። ከአዳም ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የሆነው ይኸው ነው።

መልካም ዜናው ይኸውና

ነገር ግን ሁሉም አልጠፋም። ከሚንከራተቱ የጥናት ተሳታፊዎች በተቃራኒ፣ አካሄዳችንን ለመገምገም የምንጠቀምባቸው አስተማማኝ፣ የሚታዩ የመንገድ ምልክቶች አሉን።

ታዲያ እነዚህ የመንገድ ምልክቶች ምንድናቸው?

በእርግጥ እነዚህ ዕለታዊ ጸሎትን እና ቅዱሳት መጻህፍትን ማሰላሰልን እንዲሁም እንደ ኑ፣ ተከተሉኝ፣ ያሉ በመንፈስ አነሳሽነት የቀረቡ መሳሪያዎችን መጠቀምን ያካትታሉ። በየቀኑ፣ በትሕትና እና በሐቀኝነት ወደ እግዚአብሔር ዙፋን መቅረብ እንችላለን። ፈቃዳችንን እና ፍላጎታችንን ከእሱ አንፃር ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ድርጊቶቻችንን ማሰላሰል እና የቀናችንን አፍታዎች መገምገም እንችላለን። ከመንገድ ከወጣን፣ እግዚአብሔር እንዲመልሰን እንለምነዋለን፣ እንዲሁም የተሻለ ለማድረግ ቃል እንገባለን።

ምስል
አዳኝ በጉን ሲመራ

ይህ የውስጥ እይታ ጊዜ እንደገና የማስተካከል እድል ነው። በሰማይ አባታችን በጽሑፍ እና በመንፈስ በተገለጠው ቃል ከጌታ ጋር አብረን የምንሄድበት፣ የምንማርበት፣ የምንታነጽበት እና የምንጸዳበት የነፀብራቅ የአትክልት ስፍራ ነው። የዋህ የሆነውን ክርስቶስን ለመከተል፣ እድገታችንን ስንገመግም እና እግዚአብሔር ለልጆቹ ከሰጣቸው መንፈሳዊ ምልክቶች ጋር እራሳችንን የምናስተካክልበት ቃል ኪዳኖቻችንን የምናስታውስበት ቅዱስ ጊዜ ነው።

እንደ ግል ዕለታዊ ተሀድሶአድርጋችሁ አስቡት። በክብር መንገድ ጉዟችን ላይ እንደ መንፈሳዊ ተጓዥ፣ መውደቅ ምን ያህል ቀላል እንደሆነ እናውቃለን። ነገር ግን ጥቃቅን ነገሮች ከአዳኙ መንገድ ሊያወጡን እንደሚችሉ፣ እንዲሁ ትናንሽ እና ቀላል የማስተካከያ ድርጊቶች በእርግጠኝነት ይመልሱናል። ብዙ ጊዜ እንደሚያደርገው፣ ጨለማው በሕይወታችን ውስጥ ዘልቆ ሲገባ፣ ዕለታዊ ተሀድሶአችን ልባችንን ለሰማያዊ ብርሃን ይከፍታል፤ ጥላዎችን፣ ፍርሃቶችን እና ጥርጣሬዎችን አባርሮ ነፍሳችንን ያበራል።

ትናንሽ መሪዎች፣ ትላልቅ መርከቦች

እኛ ከፈለግነው በእርግጥ “እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ፣ አዎን፣ በማይነገር የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ለእኛ እውቀትን ይሰጠናል።” 9 በጠየቅን ቁጥር እርሱ መንገድን ያስተምረናል እንዲሁም እንድንከተለው ይረዳናል።

በእርግጥ ይህ በእኛ በኩል የማያቋርጥ ጥረትን ይጠይቃል። ቀደም ባሉት መንፈሳዊ ልምዶች ልንረካ አንችልም። የማያቋርጥ መንፈሳዊ ክትትል ያስፈልገናል።

በሌሎች ምስክርነቶች ላይ ለዘለአለም መተማመን አንችልም። የራሳችንን መገንባት አለብን።

የማያቋርጥ፣ ዕለታዊ የሰማይ ብርሃን ፍሰት ያስፈልገናል።

“የመታደስ ዘመናት” 10 ፣ ያስፈልጉናል። የግል ተሀድሶ ዘመናት።

“የሚንከባለል ውሃ” ለረጅም ጊዜ “ቆሽሾ ሊቆይ አይችልም።” 11 ሀሳቦቻችንን እና ድርጊቶቻችንን ንፁህ ለማድረግ፣ መንከባለላችንን መቀጠል አለብን!

ለነገሩ የወንጌሉ እና የቤተክርስቲያኑ ዳግም መመለስ አንድ ጊዜ የተፈጸመ እና ያለቀ ነገር አይደለም። ቀጣይነት ያለው ሂደት ነው—አንድ ቀን በአንድ ጊዜ፣ አንድ ልብ በአንድ ጊዜ።

ቀኖቻችን በገፉ ቁጥር፣ እንዲሁ የእኛ ሕይወት ይሄዳል። አንድ ደራሲ እንዲህ በማለት አስቀምጦታል፤ “አንድ ቀን እንደ ሙሉ ሕይወት ነው። አንድ ነገር ማድረግ ትጀምራላችሁ፣ ግን ሌላ ነገር በማድረግ ትጨርሳላችሁ፣ አንድ ስራ ለመስራት አቅዳችሁ፣ ግን እዚያ አትደርሱም። … እና በሕይወታችሁ መጨረሻ ላይ፣ የእናንተ ሕልውና እንዲሁ ተመሳሳይ የዘፈቀደ ባህሪ አለው። መላ ሕይወታችሁ እንደ አንድ ቀን ተመሳሳይ ቅርፅ አለው።” 12

የህይወታችሁን ቅርፅ መለወጥ ትፈልጋላችሁን?

የቀናችሁን ቅርፅ ለውጡ።

ቀናችሁን መለወጥ ትፈልጋላችሁን?

በዚህ ሰዓት ተለወጡ።

በዚህ ቅጽበት ሃሳባችሁን፣ ስሜታችሁን እና ድርጊታችሁን ለውጡ።

ትንሽ መሪ፣ ትልቅ መርከብን ማሽከርከር ይችላል። 13

ትናንሽ ጡቦች አስደናቂ መኖሪያ ቤቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

ትናንሽ ዘሮች ከፍተኛ ቁመት ያላቸው ዛፎች ሊሆኑ ይችላሉ።

በጥሩ ሁኔታ ያጠፋናቸው ደቂቃዎች እና ሰዓታት በጥሩ ሁኔታ የሕይወት መኖሪያ መገንቢያ ብሎኬቶች ናቸው። እነዚህም መልካምነትን ሊያነሳሱ፣ ፍጹም ካለመሆን ጉድለቶች ምርኮ ሊያወጡን እና ወደ ይቅርታ እና ወደ ቅድስና ቤዛነት ጎዳና ወደላይ ሊመሩን ይችላሉ።

የአዲስ ጅማሬ አምላክ

ከእናንተ ጋር፣ ለአዲስ ዕድል፣ ለአዲስ ሕይወት፣ ለአዲስ ተስፋ አስደናቂ ስጦታ ልቤን በአመስጋኝነት ከፍ አደርጋለሁ።

የተትረፈረፈውን እና ይቅር ባይ አምላካችንን ለማመስገን ድምፃችንን ከፍ እናደርጋለን። በእርግጥም፣ እርሱ የአዲስ ጅማሬ አምላክ ነው። የድካሙ ሁሉ የላቀ ፍጻሜ፣ እኛ ልጆቹ፣ ወደ አለመሞት እና የዘላለም ሕይወት ፍለጋችን ውስጥ ስኬታማ እንድንሆን መርዳት ነው። 14

በክርስቶስ አዲስ ፍጥረታት ልንሆን እንችላለን፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር “ሕዝቤ ንስሐ በገባ ቁጥር በደላቸውን በእኔ ላይ ይቅር እላለሁ” 15 ሲል ቃል ገብቷል እና “ደግሜም አላስታውሰውም።” 16

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ውድ ጓደኞቼ፣ ሁላችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እንንሸራተታለን።

ግን ወደ መንገዳችን መመለስ እንችላለን። በዚህ ህይወት ጨለማ እና ፈተናዎች ውስጥ መንገዳችንን ማሰስ እና እርሱ የሰጣቸውን መንፈሳዊ ምልክቶች ከፈለግንና ከተቀበልን፣ የግል መገለጥን ከተቀበልን፣ እና ለዕለታዊ ተሀድሶ፣ ከጣርን ወደ አፍቃሪው የሰማይ አባታችን የምንመለስበትን መንገድ ማግኘት እንችላለን። ለምንወደው አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት የምንሆነው በዚህ መንገድ ነው።

ይህን ስናደርግ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ፈገግ ይላል። “አምላካችሁ እግዚአብሔርም በሚሰጣችሁ ምድር ይባርካችኋል። ጌታ ለራሱ ቅዱስ ሕዝብ ያቆማችኋል።” 17

ዕለታዊ ተሐድሶን የምንፈልግ እና በኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ለመጓዝ ያለማቋረጥ የምንታገል እንድንሆን ጸሎቴ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ኢየሱስም አስተማረ፣ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ።”(ዮሀንስ 14፥6). የየኤንአይቪ የመጀመሪያ ክፍለ ዘመን ጥናት መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ማብራሪያ ይዟል-“በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመንገድ ምስል ወይም መንገድ ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ወይም ትምህርቶች ለመጠበቅ የቆመ ነው። ምሳሌ 1፥116፥11; 86፥11 ተመልከቱ]። ይህ በእምነቶች፣ ትምህርቶች ወይም ልምዶች ስብስብ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ የተለመደ ጥንታዊ ዘይቤ ነበር። የዴድ ባሕር ጥቅልሎች ማኅበረሰብ ራሳቸውን ‹የመንገድ› ተከታዮች ብለው ይጠሩ ነበር፣ ይህም ማለት እግዚአብሔርን በሚያስደስ መንገድ የራሳቸው ትርጓሜ ተከታዮች ናቸው ማለታቸው ነው። ጳውሎስና የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እራሳቸውን ‘የመንገዱ ተከታዮች’ ብለው ይጠሩ ነበር የሐዋርያት ሥራ 24፥14፣ ይመልከቱ]” (in “What the Bible Says about the Way, the Truth, and the Life,” Bible Gateway, biblegateway.com/topics/the-way-the-truth-and-the-life)።

    በ1873 (እ.አ.አ)፣ ቁስጥንጥንያ በሚገኘው የኢየሩሳሌም ፓትርያርክ ቤተ-መጽሐፍት ውስጥ ዲዳክ የሚል ጥንታዊ መጽሐፍ ተገኘ። ብዙ ምሁራን የተጻፈው እና ጥቅም ላይ የዋለው በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ (ከ80-100 ዓ.ም) እንደሆነ ያምናሉ። ዲዳኩ በእነዚህ ቃላት ይጀምራል፤ “ሁለት መንገዶች አሉ፣ አንዱ የሕይወት እና የሞት፣ ግን በሁለቱ መንገዶች መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። እንግዲህ የሕይወት መንገድ ይህች ናት፤ በመጀመሪያ የፈጠረህን አምላክ ውደድ፤ ሁለተኛ፣ ጎረቤትህን እንደራስህ ”(የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ትምህርት፣ ትራንስ. ሮስዌል ዲ ሂችኮክ እና ፍራንሲስ ብራውን [1884 እ.አ.አ] ፣ 3)።

    እንደ The Expositor’s Bible Commentary፣ ያሉ ሌሎች ምንጮች “በቤተክርስቲያኗ መጀመሪያ ላይ የኢየሱስን መሲሕነት የተቀበሉ እና ጌታቸው ነው ብለው የጠየቁት ሰዎች ራሳቸውን‹ የመንገዱ ›ብለው ይጠሩ ነበር። [የሐዋርያት ስራ 19፥9፣ 23; 22፥424፥14፣ 22 ተመልከቱ]” (ed. Frank E. Gaebelein and others [1981], 9:370)።

  2. ሞዛያ 2፥17፣ ይመልከቱ።

  3. ትምህርት እና ቃል ኪዳን 88፥63 ተመልከቱ።

  4. “Walking in Circles,” Aug. 20, 2009, Max-Planck-Gesellschaft, mpg.de.

  5. “በክብ መዞር፣” mpg.de። ይህ ምስል በጥናቱ ውስጥ አራት ተሳታፊዎችን የጂ.ፒ.ኤስ መከታተልን ያሳያል። ሦስቱም በደመናማ ቀን ተጓዙ። ከመካከላቸው አንዱ (ኤስ.ኤም.) ፀሐይ በደመና ተሸፍኖ ሳለ መራመድ ጀመረ፣ ግን ከ 15 ደቂቃዎች በኋላ ደመናዎቹ ተበተኑ፣ እና ተሳታፊው የፀሐይ ፍንጭዎችን ማየት ይችላል። ፀሐይ አንዴ ከተገለጠ በኋላ ተጓዥው በቀጥታ መስመር በመራመድ እንዴት የበለጠ እንደተሳካለት ልብ በሉ።

  6. በሁለት ዲግሪ ብቻ የመንገድ ስህተት አንድ የመንገደኛ አውሮፕላን በአንታርክቲካ ኤሬቡስ ተራራ ላይ ተከስክሶ 257 ሰዎችን እንደገደለ የሚያሳይ አንድ አሳዛኝ ምሳሌ፣ ዲተር ኤፍ ኡክዶርፍን፣ “የጥቂት ዲግሪዎች ጉዳይ፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2008 እ.አ.አ፣ 57–60 የሚለውን ይመልከቱ።

  7. መሣፍንት 2፥10

  8. ክርስቶስ አሜሪካን ከጎበኘ በኋላ፣ ሕዝቡ በእውነት ከኃጢአታቸው ተጸጽተው፣ ተጠምቀዋል፣ እና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። በአንድ ወቅት ተከራካሪ እና ትህምከተኛ ሕዝብ በነበሩበት፣ አሁን “በመካከላቸው ጠብ እና ክርክር አልነበረም፣ እና እያንዳንዱ ሰው እርስ በርሱ በፍትሐዊነት ይሠራል” (4 ኔፊ 1፥2)። ኩራት ሰዎችን ከመንገድ እንዲስቱ ከማድረጉ በፊት ይህ የጽድቅ ዘመን ለሁለት መቶ ዓመታት ያህል ቆየ። ሆኖም፣ መንፈሳዊ መንሸራተት እንዲሁ በበለጠ ፍጥነት ሊከሰት ይችላል። እንደ ምሳሌ፣ ከብዙ አሥርተ ዓመታት በፊት፣ በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ በዳኞች ዘመን በ 50 ኛው ዓመት፣ በሕዝቡ መካከል “ቀጣይ ሰላም እና ታላቅ ደስታ” ነበር። ነገር ግን በቤተክርስቲያኒቱ አባላት ልብ ውስጥ ኩራት በመግባቱ የተነሳ፣ ከአራት ዓመት አጭር ጊዜ በኋላ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ አለመግባባቶች ነበሩ፣ እንዲሁም በሕዝቡ መካከል ጠብ ነበር፣ ብዙ ደም መፋሰስ” (ሔለማን 3፥32–4፥1 ተመልከቱ)።

  9. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥26

  10. የሐዋሪያት ስራ 3፥19

  11. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥33።

  12. Michael Crichton, Jurassic Park (2015), 190.

  13. “መርከቦችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ምንም እንኳን በጣም ትልቅ ቢሆኑ እና በኃይለኛ ነፋሶች ቢነዱም፣ ፓይለቱ መሄድ ወደሚፈልግበት በጣም ትንሽ በሆነ የበትር መሪ ይመራሉ ”(ያዕቆብ 3፥4፣ ኒው ኢንተርናሽናል እትም)።

  14. ሙሴ 1፥39 ይመልከቱ።

  15. ሞዛያ 26፥30

  16. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 58፥42

  17. ዘፍጥረት 28፥8–9፤ ደግሞም ቁጥሮች 1–7 ይመልከቱ።

አትም