አምላካችን ሆይ፣ የሚሰቃዩትን ቅዱሳንህን አስታውስ
ቃል ኪዳኖችን መጠበቅ የኢየሱስ ክርስቶስን የኃጢያት ክፍያ መሥዋዕት ኃይል ይከፍታል፣ እናም በመከራን ለምትሰቃዩት እንኳን ደስታን ይሰጣል።
የሰማይ አባት የደስታ እቅድ ሁሉም ልጆቹ የሚፈተኑበት እና ሙከራዎችን የሚያዩበትን የሟች ልምድን ያካትታል። 1 ከአምስት ዓመት በፊት ካንሰር ተገኘብኝ። የቀዶ ጥገናዎች፣ የጨረር ሕክምናዎች እና የመድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳቶች አካላዊ ሥቃዮች ተሰማኝ አሁንም ይሰማኛል። በሚያሰቃዩ እንቅልፍ የለሽ ምሽቶች ውስጥ የስሜታዊ ትግሎች አጋጥመውኛል። የሕክምና መረጃ እንደሚያመለክተው ምናልባት፣ ሁሉንም ነገር የሆኑትን ቤተሰብ ትቼ፣ እኔ ከጠበቅሁት ቀደም ብዬ ሟችነትን ለቅቄ እንደምሄድ ነበር።
የትም ብትኖሩ፣ ከተለያዩ ፈተናዎች እና ሟች ድክመቶች የተነሳ አካላዊ ወይም ስሜታዊ ሥቃይ፣ የሕይወታችሁ አካል ነበረ፣ አሁንም ነው፣ ወይም አንድ ቀንም ይሆናል።
አካላዊ ሥቃይ በተፈጥሮ እርጅና፣ ባልተጠበቁ በሽታዎች፣ ባልተጠበቀ አደጋዎች፤ በረሃብ ወይም ቤት አልባነት፣ ወይም በበደል፣ በጠበኛ ድርጊቶች እና በጦርነት ሊመጣ ይችላል።
የስሜት ሥቃይ፣ ከጭንቀት ወይም ከስጋት፤ የትዳር ጓደኛ፣ ወላጅ ወይም የታመነ መሪ ክህደት፤ የሥራ ወይም የገንዘብ መቀልበስ፤ በሌሎች ፍትሃዊ ያልሆነ ፍርድ፤ የጓደኞች፣ ልጆች ወይም የሌሎች የቤተሰብ አባላት ምርጫዎች፤ በብዙ መልኩ ባለው በደል፤ ያልተፈጸሙ የጋብቻ ወይም የልጆች ህልሞች፤ የምንወዳቸው ሰዎች ከባድ ህመም ወይም ቀደምት ሞት፤ ወይም በጣም ብዙ ሌሎች ምንጮች አማካኝነት ሊነሳ ይችላል።
በእያንዳንዳችን ላይ የሚደርሰውን ልዩ እና አንዳንድ ጊዜ የሚያዳክም መከራን እንዴት መቋቋም ትችላላችሁ?
ምስጋና ይግባውና፣ ተስፋ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ውስጥ ይገኛል፣ እናም ተስፋም የሕይወታችሁ አካል ሊሆን ይችላል። ዛሬ ከቅዱሳት መጻህፍት፣ ከትንቢታዊ ትምህርቶች፣ ከብዙ የአገልጋይ ጉብኝቶች እና ከራሴ ቀጣይ የጤና ፈተና የተውጣጡ አራት የተስፋ መርሆችን እጋራለሁ። እነዚህ መርሆዎች በሰፊው የሚተገበሩ ብቻ ሳይሆኑ በጥልቅ ግላዊ ናቸው።
በመጀመሪያ፣ መከራ ማለት እግዚአብሔር በሕይወታችሁ አልደሰተም ማለት አይደለም። ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንድ ዓይነ ስውር በቤተመቅደስ ውስጥ አይተው እንዲህ ጠየቁ፣ “መምህር ሆይ፣ ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጥያት የሠራው ይህ ሰው ወይም ወላጆቹ ናቸው?”
ደቀ መዛሙርቱ፣ ልክ ዛሬ እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች እንደሚያምኑት፣ በሕይወታቸው ውስጥ ያሉት ችግሮች እና መከራዎች ሁሉ የኃጥያት ውጤቶች ናቸው ብለው በስህተት የሚያምኑ ይመስላሉ። ነገር ግን አዳኙ “የእግዚአብሔር ሥራዎች በእርሱ እንዲገለጡ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ አልበደሉም” ሲል መለሰ። 2
የእግዚአብሔር ስራ የእኛን ህያውነት እና ዘለአለማዊ ህይወት ለማምጣት ነው። 3 ነገር ግን ፈተናዎች እና መከራዎች—በተለይም በሌላ ሰው ኃጥያታዊ ነጻ ምርጫ 4 መሰቃየት ሲመጣ፣ እንዴት የእግዚአብሔር ሥራ ወደፊት እንዲገፋ ያደርጋሉ?።
ጌታ ለቃል ኪዳኑ ሕዝቡ እንዲህ ነገራቸው፣ “እኔ አነጻኋችሁ … ፤ በመከራ እቶን ውስጥ መርጫችኋለሁ።” 5 የመከራችሁ ምክንያቶች ምንም ይሁን ምን፣ አፍቃሪ የሰማይ አባታችሁ ነፍሳችሁን እንዲያጠሩ ሊመራቸው ይችላል። 6 የተጣሩ ነፍሳት የሌሎችን ሸክም በእውነተኛ ርህራሄ ሊሸከሙ ይችላሉ። 7 “ከታላቅ መከራ” የወጡ የተጣሩ ነፍሳት በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም በደስታ ለመኖር ተዘጋጅተዋል፣ እናም “እግዚአብሔር እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል”። 8
ሁለተኛ፣ የሰማይ አባት ስቃያችሁን በቅርበት ያውቃል። በፈተናዎች መካከል ሳለን፣ እግዚአብሔር ሩቅ ነው እና ስለ ህመማችን ግድ የለውም ብለን በስህተት ልናስብ እንችላለን። ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንኳ ይህንን ስሜት በሕይወቱ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ገልፀዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ከቤታቸው እየተባረሩ ሳሉ፣ እና በሊበርቲ እስር ቤት ውስጥ ታስሮ፣ ጆሴፍ በጸሎት እንዲህ በማለት መረዳትን ፈለገ፣ “እግዚአብሔር ሆይ፣ የት ነህ?” እና የተሰወርክበትን ስፍራ የሚሸፍነው ድንኳን የት ነው?” “አምላካችን ሆይ፣ የሚሰቃዩትን ቅዱሳንህን አስታውስ” በማለት በዚህ ልመና አበቃ። 9
የጌታ መልስ ጆሴፍንና የተሰቃዩትን ሁሉ አረጋ፦
“ልጄ፣ ለነፍስህ ሰላም ይኑርህ፤ ጭንቀትህ እና ስቃይህ ለጥቂት ጊዜ ቢሆን ነው፤
“ከዚያም፣ በመልካም ይህን ብትጸና፣ እግዚአብሔርም ወደ ላይ ዘለአለማዊ ክብር።” 10
ብዙ መከራ የደረሰባቸው ቅዱሳን በፈተናዎቻቸው ወቅት የእግዚአብሔር ፍቅር ምን እንደተሰማቸው ለእኔ አካፍለውኛል። ዶክተሮች የአንድ ከባድ ህመም መንስኤዎችን ገና ባላወቁበት ጊዜ በአንድ ወቅት በካንሰር ውጊያዬ ውስጥ የራሴን ተሞክሮ በደንብ አስታውሳለሁ። በምሳችን ላይ መደበኛ በረከትን ለመስጠት በማሰብ ከባለቤቴ ጋር ተቀመጥኩ። ይልቁንም እኔ ማድረግ የምችለው በቀላሉ ማልቀስ ብቻ ነበር፣ “የሰማይ አባት፣ እባክህ እርዳኝ። በጣም ታምሜያለሁ።” ለሚቀጥሉት ከ20 እስከ 30 ሰከንዶች በፍቅሩ ተከብቤ ነበር። ለበሽታዬ ምንም ምክንያት አልተሰጠኝም፣ የመጨረሻውን ውጤት አመላካች እና ከህመሙ እፎይታ አላገኘሁም። እኔ የሱ ንፁህ ፍቅሩ ተሰማኝ፣ እናም ያ በዚያም እና አሁንም በቂ ነው።
የአንዲት ድንቢጥ እንኳን መውደቅን የሚያስተውለው የሰማዩ አባታችን መከራችሁን እንደሚያውቅ እመሰክራለሁ። 11
ሦስተኛ፣ መከራችሁን በጥሩ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንዲኖራችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱን ኃይል ይሰጣል። ይህ የሚያስችል ኃይል የሚገኘው በእርሱ የኃጢያት ክፍያ በኩል ነው። 12 በጣም ብዙ የቤተክርስቲያኗ አባላት ትንሽ ከጠነከሩ በራሳቸው ማንኛውንም ሥቃይ መቋቋም እንደሚችሉ ያስባሉ ብዬ እፈራለሁ። ይህ ለመኖር አስቸጋሪ መንገድ ነው። የእናንተ ጊዜያዊ ጥንካሬ ነፍሳችሁን ለማጠንከር ከአዳኙ ከማያልቅ የኃይል አቅርቦት ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር አይችልም። 13
መፅሐፈ ሞርሞን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለመርዳት ህመሞቻችንን፣ እና ድክመቶቻችንን “በእርሱ ላይ” እንደሚወስድ ያስተምራል። 14 በመከራ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተን ለመርዳት እና ለማበረታታት የሚሰጣችሁን ኃይል እንዴት ልትጠቀሙ ትችላላችሁ? ቁልፉ ከእሱ ጋር የገባችሁትን ቃል ኪዳኖች በመጠበቅ እራሳችሁን ከአዳኝ ጋር ማሰር ነው። የክህነት ስርዓቶችን ስንቀበል እነዚህን ቃል ኪዳኖች እናደርጋለን። 15
የአልማ ሕዝብ ወደ ጥምቀት ቃል ኪዳን ገቡ። በኋላ በባርነት ተሰቃዩ እና በአደባባይ እንዳያመልኩ ወይም ጮክ ብለው እንዳይጸልዩ ተከለከሉ። ሆኖም በልባቸው ውስጥ በዝምታ በመጮህ ቃል ኪዳናቸውን በተቻለ መጠን ጠብቀዋል። በዚህ ምክንያት መለኮታዊ ኃይል መጣ። “ሸክማቸውን በቀላሉ እንዲሸከሙ ጌታ አበረታታቸው።” 16
በዘመናችን፣ አዳኙ “በእያንዳንዱ ሀሳብ ወደ እኔ ተመልከቱ፤ አትጠራጠሩ፣ አትፍሩ።” በማለት ይጋብዛል። 17 እርሱን ሁል ጊዜ ለማስታወስ የቅዱስ ቁርባን ኪዳኑን ስንጠብቅ፣ መንፈሱ ከእኛ ጋር እንደሚሆን ቃል ገብቷል። መንፈስ ፈተናዎችን እንድንቋቋም እና በራሳችን ማድረግ የማንችለውን እንድናደርግ ብርታት ይሰጠናል። መንፈስ ሊፈውሰን ይችላል፣ ሆኖም ግን ፕሬዘደንት ጄምስ ኢ. ፋውስት እንዳስተማሩት፣ “አንዳንድ ፈውስ በሌላ ዓለም ውስጥ ሊከናወን ይችላል።” 18
እንዲሁም “የአምላካዊነት ኃይል በሚገለጥበት” 19 ፣ በቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች እና ሥርዓቶች ተባርከናል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ሴት ልጇን በአሰቃቂ አደጋ ያጣችውን፣ ከዚያ በኋላ ባሏን በካንሰር ምክንያት ያጣችውን ሴት ጎበኘሁ። እንዲህ ያለውን ማጣት እና መከራ እንዴት እንደምትቋቋም ጠየቅኳት። እርሷም ጥንካሬው የመጣው በመደበኛ የቤተመቅደስ አምልኮ ወቅት ከተቀበለችው የዘለአለማዊ ቤተሰብ መንፈሳዊ ማረጋገጫዎች እንደሆነ ተናገረች። ቃል እንደተገባው፣ የጌታ ቤት ሥርዓቶች በእግዚአብሔር ኃይል አስታጥቀዋታል። 20
አራተኛ፣ በየቀኑ ደስታን ለማግኘት ምረጡ። የሚሠቃዩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሌሊቱ እንደቀጠለ እና የቀን ብርሃን በጭራሽ እንደማይመጣ ይሰማቸዋል። ማልቀስ ችግር የለውም። 21 ሆኖም፣ እራሳችሁን በመከራ ጨለማ ምሽቶች ውስጥ ካገኛችሁ፣ እምነትን በመምረጥ ወደ ብሩህ የደስታ ማለዳ መንቃት ትችላላችሁ። 22
ለምሳሌ ከሕመምና ከፀጉር ማጣት ባሻገር፣ በወንበሯ ላይ ግርማ ሞገስ እያሳየች ተቀምጣ፣ ለካንሰር ሕክምና እየተደረገላት ያለች አንዲት ወጣት እናትን ጎበኘሁ። በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ባልና ሚስት ልጆችን ለመፀነስ ባይችሉም በደስታ የወጣት መሪ ሆነው ሲያገለግሉ አገኘኋቸው። ከጥቂት ቀናት በኋላ ከህይወት ከምታልፍ፣ ግን በቤተሰብ እንባቸው መካከል ሳቅና የሀሴት ትዝታዎች በሚገገኝባት፣ ወጣት አያት፣ እናት እና ባለቤት ከሆነች ውድ ሴት ጋር ተቀመጥኩኝ።
እነዚህ መከራዎች ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን ያስተማሩትን በምሳሌአዊነት ያሳያሉ፦
“የሚሰማን ደስታ ካሉን የህይወታችን ሁኔታዎች ጋር ግንኘነት አነስተኛ ነው እናም በህይወታችን ትኩረት ከምንሰጠው ነገር ጋር ያላቸው ተዛምዶ ታላቅ ነው።
የህይወታችን ትኩረት በእግዚአብሔር የደህንነት እቅድ …እና በኢየሱስ ክርስቶስና በወንጌሉ ላይ ሲሆን፣ በህይወታችን ከተከሰተውም ወይም—ካልተከሰተውም—ሁኔታ ባሻገር ደስታ ሊሰማን ይችላል።” 23
የሰማዩ አባታችን በመከራ ላይ ያሉ ቅዱሳኑን እንደሚያስታውስ፣ እንደሚወዳችሁ፣ እና እናንተን በቅርበት እንደሚያውቅ 24 እመሰክራለሁ። ምን እንደሚሰማችሁ አዳኛችን ያውቃል። “በእውነት ስቃያችንን ተቀበለ፤ እናም ሀዘናችንን ተሸከመ” 25 በየእለቱ ተቀባይ በመሆኔ፣ 26 —ቃል ኪዳኖችን መጠበቅ የኢየሱስ ክርስቶስን የኃጢያት ክፍያ መሥዋዕት ኃይልን ይከፍታል፣ እናም በመከራ ለምትሰቃዩት እንኳን ደስታን ይሰጣል።
ለሚሰቃዩ ሁሉ፣ “በልጁም ደስታ አማካኝነት ሸክማችሁን እንዲቀልልላችሁ እግዚአብሔር ይፍቀድላችሁ” ብዬ እጸልያለሁ። 27 በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።