በገለዓድ የሚቀባ መድሃኒት የለምን?
የአዳኙ የፈውስ ኃይል አካላችንን የመፈወስ ችሎታው ብቻ ሳይሆን ምናልባትም የበለጠ አስፈላጊ የሆነውን ልባችንን የመፈወስ ችሎታው ነው.
ከሚስዮናዊ ተልእኮዬ እንደተመለስኩ ብዙም ሳይቆይ፣ በብሪገም ያንግ ዩኒቨርሲቴ ተማሪ ሳለሁ፣ ከአባቴ የስልክ ጥሪ ደረሰኝ። የጣፊያ ካንሰር እንደተገኘበትና እና ምንም እንኳን ጥሩ የመዳን እድል ባይኖረውም፣ ለመዳን እና ወደ መደበኛ የሕይወት እንቅስቃሴው ለመመለስ ቆርጦ እንደተነሳ ነገረኝ። ያ የስልክ ጥሪ ለእኔ አስጨናቂ ጊዜ ነበር። አባቴ፣ ኤጲስ ቆጶሴ፣ ጓደኛዬ እና አማካሪዬ ነበር። እኔ፣ እናቴ፣ ወንድሞቼና እህቶቼ ስለወደፊቱ ስናሰላስል፣ የጨለመ ተስፋ ቢስ ይመስል ነበር። ታናሽ ወንድሜ ዴቭ በኒው ዮርክ ሚስዮን እያገለገለ ነበር እናም በእነዚህ አስቸጋሪ የቤተሰብ ክስተቶች ውስጥ በረጅም ርቀት ላይ ሆኖ እተሳተፈ ነበር።
የዚያን ጊዜ የሕክምና አገልግሎት ሰጪዎች የካንሰርን ስርጭት ለመግታት ቀዶ ጥገና ለማድረግ ሐሳብ አቀረቡ። ቤተሰባችን ተአምር ለማግኘት አጥብቆ ጾመ እና ጸለየ። አባቴ እንዲፈወስ የሚያስችል በቂ እምነት እንደነበረን ተሰማኝ። ቀዶ ጥገናው ከመደረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ እኔና ታላቅ ወንድሜ ኖርም ለአባቴ በረከት ሰጠነው። ባለን እምነት ሁሉ እንዲፈወስ ጸለይን።
ቀዶ ጥገናው ለብዙ ሰዓታት እንዲቆይ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዶክተሩ ከቤተሰባችን ጋር ለመገናኘት ወደ ማረፊያ ክፍል መጣ። ቀዶ ጥገናውን እንደጀመሩ ካንሰሩ በአባቴ አካል ውስጥ ተሰራጭቶ እንደነበር ማየት እንደቻሉ ነገረን። እነሱ በተመለከቱት መሠረት፣ አባቴ የሚኖረው ለጥቂት ወራት ብቻ ነበር። በጣም አዘንን።
አባቴ ከቀዶ ሕክምናው እንደነቃ፣ ሂደቱ የተሳካ እንደነበር ለማወቅ ጓግቶ ነበር። አስከፊውን ዜና ለእሱ ነገርን።
እኛ ተአምር ለማግኘት መጾማችንን እና መጸለያችንን ቀጠልን። የአባቴ ጤንነት በፍጥነት እያሽቆለቆለ ሲመጣ፣ ከሕመም ነፃ እንዲሆን መጸለይ ጀመርን። በመጨረሻ፣ የእሱ ሁኔታ እየተባባሰ ሲሄድ፣ በፍጥነት እንዲያልፍ ጌታን ጠየቅነው። የቀዶ ጥገና ሐኪሙ እንደተነበየው ከቀዶ ጥገናው ከጥቂት ወራት በኋላ አባቴ አረፈ።
ከአጥቢያ አባላት እና ከቤተሰብ ጓደኞች ብዙ ፍቅር እና እንክብካቤ በቤተሰባችን ላይ ፈሰሰ። የአባቴን ሕይወት ያከበረ ውብ የቀብር ሥነ ሥርዓት አደረግን። ይሁን እንጂ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አባቴን በማጣታችን ምክንያት ስቃይ ይሰማን ጀመር እናም አባቴ ለምን እንዳልተፈወሰ መገረም ጀመርኩ። እምነቴ ጠንካራ ባይሆን ይሆን ብዬ አሰብኩ። አንዳንድ ቤተሰቦች ለምን ተአምር ተቀበሉ፣ የእኛ ቤተሰብ ግን ለምን አልተቀበለም? መልስ ለማግኘት ወደ ቅዱሳት መጻህፍት ዞር ማለት እንዳለብኝ ከሚስዮን አገልግሎቴ ተምሬአለሁ፣ እናም በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ መፈለግ ጀመርኩ።
ብሉይ ኪዳን በገለዓድ ከሚበቅል ቁጥቋጦ ስለተሠራ ቁስልን ለመፈወስ ስለሚያገለግል ጥሩ መዓዛ ስላለው ቅመም ወይም ቅባት ያስተምራል። በብሉይ ኪዳን ዘመን ይህ ቅባት “የገለዓድ መድሃኒት” በመባል ይታወቅ ነበር።” 1 ነቢዩ ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል ባያቸው አደጋዎች በማዘን ፈውስ እንዲመጣ ተስፋ አደረገ። ኤርሚያስም እንዲህ ብሎ ጠየቀ፣ “በገለዓድ የሚቀባ መድኃኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን?” 2 በአስደናቂው የመፈወስ ኃይሉ ምክንያት፣ አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ በስነ ጽሑፍ፣ በሙዚቃ እና በሥነ ጥበብ ውስጥ ብዙውን ጊዜ የገለዓድ መድሃኒት ተብሎ ይጠራል። ልክ እንደ ኤርምያስ፣ “በገለዓድ ለኒልሰን ቤተሰብ መድሃኒት የለምን?” ብዬ አስቤ ነበር።
በአዲስ ኪዳን በማርቆስ ምዕራፍ 2 አዳኙን በቅፍርናሆም ሆኖ እናገኘዋለን። የአዳኙ የመፈወስ ኃይል ወሬ በመላ አገሪቱ ተሰራጭቶ ነበር፣ እናም ብዙ ሰዎች በአዳኙ ለመፈወስ ወደ ቅፍርናሆም ተጓዙ። አዳኙ በሚገኝበት ቤት ዙሪያ ብዙዎች ተሰብስበው ስለነበር ሁሉንም የሚቀበልበት ቦታ አልነበረውም። አራት ሰዎች የታመመውን ሽባ ሰው አዳኙ እንዲፈውሰው አመጡት። በሕዝቡ መካከል መጓዝ አልቻሉም እናም የቤቱን ጣሪያ ከፍተው ከአዳኙ ጋር ይገናኝ ዘንድ ሰውየውን ወደ መሬት አወረዱት።
ይህን ታሪክ ሳነብ፣ አዳኝ ከዚህ ሰው ጋር እንደተገናኘ “ልጅ ሆይ፣ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ” ብሎ በተናገረው ነገር ተገረምኩ። 3 ይህን ሰው ከተሸከሙት ከአራቱ ሰዎች አንዱ ብሆን ኖሮ አዳኙን “በእውነት እንዲፈወስ እዚህ ያመጣነው እኛ ነን” እንደምለው አሰብኩኝ። አዳኙ “እኔ ፈውሼዋለሁ” ብሎ የሚመልስ ይመስለኛል። የአዳኙ የፈውስ ኃይል ሰውነታችንን የመፈወስ ችሎታው ብቻ ሳይሆን ምናልባትም የበለጠ አስፈላጊ የሆነውን ልባችንን እና የተሰበረውን የቤተሰቤን ልብ የመፈወስ ችሎታው እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አልተረዳሁኝ ይሆን?
የዚህን ሰው አካል በመጨረሻ ሲፈውስ በዚህ ተሞክሮ አማካኝነት አዳኙ አንድ አስፈላጊ ትምህርት አስተማረ። የእርሱ መልእክት ዓይነ ስውር የሆኑትን ዓይኖች መዳሰስ እንደሚችል እና እነርሱም ማየት እንደሚችሉ ግልጽ ሆነልኝ። መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ጆሮ ሊዳስስ እንደሚችልና እነርሱም ሊሰሙ እንደሚችሉ፣ መራመድ ያልቻሉትን እግሮች መንካት እንደሚችልና እነርሱም መራመድ እንደሚችሉ መሆኑ ግልጽ ሆነልኝ። እርሱ ዓይኖቻችንን እና ጆሮዎቻችንን እና እግሮቻችንን ሊፈውስ ይችላል፣ ግን ከሁሉም በላይ፣ እርሱ ከኃጢአት ሊያነጻን እና በአስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ ልባችንን ሊፈውስ ይችላል።
አዳኙ በመጽሐፈ ሞርሞን ውስጥ ከትንሣኤው በኋላ ለሕዝቡ ሲገለጥ፣ ስለፈውስ ኃይሉ እንደገና ተናገረ። ኔፋውያን “ እፈውሳችሁ፣ ዘንድ ለኃጥያታችሁ ንስሃ ገብታችሁ እናም ተለውጣችሁ አሁን ወደ እኔ አትመለሱምን?” ሲል ድምጹን ከሰማይ ሰሙ።” 4 በኋላም፣ አዳኙ እንዲህ አስተማረ፣ “ለእነዚህ አይነት ለማገልገል መቀጠል አለባችሁ፤ ምክንያቱም አንድ ቀን እንደሚለወጡና ንሰሃ እንደሚገቡ እናም በልባቸው ሙሉ አላማ ወደ እኔ እንደሚመጡ አታውቁምና፣ እናም እፈውሳቸዋለሁ።” 5 አዳኙ የሚያመለክተው ሥጋዊ ፈውስን ሳይሆን የነፍሳቸውን መንፈሳዊ ፈውስ ነው።
ሞሮኒ የአባቱን የሞርሞንን ቃላት በማጋራት ተጨማሪ ግንዛቤን ይሰጣል። ሞርሞን ስለ ተዓምራት ከተናገረ በኋላ ይህንን ገለጸ፣ “እናም ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፥ በእኔ እምነት ካላችሁ እኔ አስፈላጊ የሆነውን ማንኛውንም ነገር ለመስራት ኃይል ይኖራችኋል።” 6 የእምነቴ አላማ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆን እንዳለበት ፣ እናም በእሱ ላይ እምነት በማኖር በእርሱ ዘንድ ያለውን አስፈላጊ ነገር መቀበል እንደሚያስፈልገኝ ተማርኩኝ። የአባቴ በህይወት ማለፍ ለእግዚአብሔር ዕቅድ አስፈላጊ መሆኑን አሁን ተረድቻለሁ። አሁን፣ በረከት ለመስጠት እጆቼን በሌላ ሰው ራስ ላይ ስጭን፣ እምነቴ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነው እንዲሁም ክርስቶስ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ይህ ሰው በአካል ሊድን እንደሚችል ወይም እንደሚድን ተረድቻለሁ።
የሚያድን እና የሚያስችል ኃይሉን የሚሰጠን የአዳኙ የኃጢያት ክፍያ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁሉም የሰጠው ዋናው በረከት ነው። በሙሉ ልብ ዓላማ ንስሐ ስንገባ፣ አዳኝ ከኃጢአት ያነጻናል። እጅግ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን ፈቃዳችንን ለአብ ስናቀርብ፣ አዳኝ ሸክማችንን ያነሳል እና ቀላል ያደርጋቸዋል። 7
ግን እኔ የተማርኩት ትልቁ ትምህርት ይህ ነው። የአዳኝ የፈውስ ኃይል ለቤተሰቤ አልሰራም ብዬ በስህተት አምኜ ነበር። አሁን በበሰለ እይታ እና ልምድ ወደ ኋላ ዞር ብዬ ስመለከት፣ የአዳኙ የፈውስ ኃይል በእያንዳንዱ የቤተሰብ አባሎቼ ሕይወት ውስጥ ግልፅ ሆኖ አየሁ። እኔ በአካላዊ ፈውስ ላይ በጣም አተኩሬ ስለነበር የተፈጸሙትን ተአምራት ማየት አልቻልኩም። ጌታ በዚህ አስቸጋሪ ፈተና እናቴን ከአቅሟ በላይ አበረታትና አነሳት፣ እርሷም ረጅም እና ፍሬያማ ሕይወት ኖራለች። በልጆቿ እና በልጅ ልጆቿ ላይ አስገራሚ አዎንታዊ ተፅእኖ ነበራት። ጌታ እኔን እንዲሁም ወንድሞቼን እና እህቶቼን ዛሬም የሕይወታችን አስፈላጊ አካል ሆኖ በቀጠለው ፍቅር፣ አንድነት፣ እምነት እና ጽናት ባረከን።
ነገር ግን አባቴስ? እንደማንኛውም ንስሐ እንደሚገቡ ሁሉ፣ በአዳኝ የኃጢያት ክፍያ ምክንያት ለሁሉም የሚገኙትን በረከቶች በፈለገ እና በተቀበለ ጊዜ በመንፈሳዊ ተፈውሷል። ለሃጥያቱ ስርየትን ተቀብሏል እንዲሁም አሁን የትንሳኤን ተዓምር በመጠበቅ ላይ ይገኛል። ሃዋርያው ጳውሎስ “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።” ብሎ አስተምሯል፡፡” 8 አያችሁ፣ እኔ ለአዳኙ፣ “አባቴን ለመፈወስ ወደ አንተ አመጣን” እያልኩት ነበር፣ እናም አዳኙ በርግጥ እንደፈወሰው አሁን ግልፅ አድርጎልኛል። የገልዓድ መድሃኒት ለኒልሰን ቤተሰብ ሰራ—እኛ ባሰብነው መንገድ ባይሆንም፣ የበለጠ ጉልህ በሆነ መንገድ ሕይወታችንን ባረከ እንዲሁም መባረኩን ቀጠለ።
በአዲስ ኪዳን በ ዮሃንስ ምእራፍ 6 አዳኙ በጣም አስገራሚ ተአምር አድርጓል። በጥቂት ዓሳ እና በጥቂት እንጀራ ብቻ አዳኙ 5000 ሰዎችን መግቧል። ይህንን ታሪክ ብዙ ጊዜ አንብቤያለሁ፣ ነገር ግን ከዚህ በፊት ያልጨበጥኩት አንድ ክፍል አሁን ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው። አዳኙ 5 ሺህ ሰዎችን ከመገበ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን 12 ቅርጫት የሞሉትን የተረፉትን ቍርስራሶች እንዲሰበስቡ ጠየቀ። ያን ለማድረግ አዳኝ ለምን ያንን ጊዜ እንደወሰደ አስቤአለሁ። ከዚያ ታሪክ የምንማረው አንድ ትምህርት፣ እርሱ 5,000 ሰዎችን መመገብ እንደሚችልና ከዚያም በላይ ትርፍራፊ እንደሚኖር ለእኔ ግልጽ ሆኖልኛል። “ጸጋዬ ለሁሉም ሰው በቂ ነው።” 9 የአዳኙ የመዋጀት እና የመፈወስ ኃይል ማንኛውንም ኃጢአት፣ ቁስል፣ ወይም ፈተና ምንም ያህል ትልቅ ወይም ከባድ ቢሆን ሊሸፍን ይችላል፣ እንዲሁም ይትረፈረፋል። ጸጋው በቂ ነው።
በዚያ እውቀት፣ አስቸጋሪ ጊዜዎች ሲመጡ፣ በእርግጥም መምጣታቸው አይቀርም፣ ወይም ኃጢአት ሕይወታችንን ሲሸፍን፣ አዳኙ “በክንፎቹ ፈውስ” 10 በመቆም፣ ወደ እርሱ እንድንመጣ ይጋብዘናል።
የገለዓድ መድሃኒት ስለሆነው፣ ስለአዳኛችን ስለኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለቤዛችን እና ስለአስደናቂው የመፈወስ ኃይሉ ምስክርነቴን እሰጣችኋለሁ። እናንተን ለመፈወስ ስላለው ፍላጎት ምስክርነቴን እሰጣለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።