አጠቃላይ ጉባኤ
የመጠየቅ እምነት እና በሚሰጠው መልስ ላይ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ
የጥቅምት 2021 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


15:37

የመጠየቅ እምነት እና በሚሰጠው መልስ ላይ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ

በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት የእውነት መገለጥን ለመቀበል ቁልፍ ነው።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በአጠቃላይ ጉባኤው በዚህ የቅዳሜ ምሽት ክፍለ ጊዜ እናንተን ለማነጋገር ላገኘሁት እድል አመስጋኝ ነኝ። በዚህ ጠዋት የጉባዔው የመግቢያ ንግግራቸው ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን “በልባችሁ ለሚመላለሱ ጥያቄዎች የሚመጣው ንጹህ መገለጥ ይህንን ጉባዔ አብዝቶ የሚሸልም እና የማይረሳ ያደርገዋል” ብለዋል። በእነዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ጌታ እንዲሰማችሁ የሚረዳችሁን የመንፈስ ቅዱስን አገልግሎት ገና እየለመናችሁ ካልሆናችሁ፣ አሁን እንድታደርጉ እጋብዛችኋለሁ። ከእናንተ ጋር ለሚኖረኝ ለእዚህ ጉብኝት መገለጥን ለመቀበል ስዘጋጅ ያንን በረከት ለማግኘት ጸልያለሁ። ያንን መገለጥ ከእግዚአብሔር ትቀበሉ ዘንድ ጥብቅ ጸሎቴ ነው።

ከእግዚአብሔር መገለጥን የመቀበያው መንገድ በአዳም እና ሔዋን ጊዜ ከነበረው አልተቀየረም። ለሁሉም የተጠሩ የጌታ አገልጋዮች ከመጀመሪያው ጀምሮ እስካሁኑ ቀን ድረስ ያው ነው። ለእናንተም ሆነ ለእኔ ተመሳሳይ ነው። ሁልጊዜም ቢሆን የሚደረገው እምነትን በመለማመድ ነው። 2

በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ይገኝ የነበረው ጆሴፍ ስሚዝ እግዚአብሔር ልባዊ ፍላጎቱን እንደሚመልስለት ስላመነ እግዚአብሔርን ጥያቄ ለመጠየቅ የሚያስችል በቂ እምነት ነበረው። የመጣው ምላሹም አለምን ቀየረ። ከኃጥያቱ ለመንጻት የቱን ቤተክርስቲያን መቀላቀል እንደሚገባው ለማወቅ ፈለገ። ያገኘው ምላሽም ሁልጊዜ የተሻሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ እንዲቀጥል እንዲሁም ገና መጀመሩ በነበረው የመገለጥ ፍሰት ላይ ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስድ አበረታቶታል። 3

በዚህ ጉባኤ የእናንተም ተሞክሮ ተመሳሳይ ሊሆን ይችል ይሆናል። መልስ የምትፈልጉላቸው ጥያቄዎች አሏችሁ። በአገልጋዮቹ አማካኝነት መልሶችን ከጌታ እንደምትቀበሉ ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል ቢያንስ በቂ እምነት አላችሁ። 4 ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ ከተናጋሪዎቹ መልሱን ለመጠየቅ እድል አታገኙም፣ ሆኖም አፍቃሪ አባታችሁን በጸሎት መጠየቅ ትችላላችሁ።

ፍላጎቶቻችሁን የሚያሟሉ እና ለመንፈሳዊ ዝግጅታችሁ የሚሆኑ መልሶች እንደሚመጡ ከልምድ አውቃለሁ። ለእናንተ ወይም ለሌሎች ዘለአለማዊ ደህንነት የሚጠቅም መልስ የምትፈልጉ ከሆነ የዚያ መልስ የመምጣት እድሉ ሰፊ ነው። ሆኖም፣ ያኔም እንኳ፣ እንደ ጆሴፍ ስሚዝ ታጋሽ የመሆንን መልስ ልትቀበሉ ትችላላችሁ። 5

በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላችሁ እምነት በኃጥያት ክፍያው ተጽዕኖ አማካኝነት ወደተለሳለሰ ልብ አምርቶ ከሆነ፣ ለጸሎቶቻችሁ መልስ የሚያመጣው የመንፈስ ሹክሹክታ ይበልጥ ሊሰማችሁ ይችላል። ውስጣዊ ጸጥታ እና ለጌታ ፈቃድ የመገዛት ስሜት ሲሰማኝ፣ እውን የሆነው ትንሹ ለስላሳ ድምጽ ግልጽ እና በአእምሮዬ የማስተውለው መሆኑ የግል ተሞክሮዬ ነው። ያ የትህትና ስሜት “የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ” 6 ፣ በሚል በተሻለ ሁኔታ ሊገለጽ ይችላል።

በዚህ ጉባኤ ውስጥ ያሉ ተናጋሪዎች የክርስቶስ ትምህርት ተብሎ የሚጠራውን ሲያስተምሩ የምትሰሙት በዚህ የመገለጥ ሂደት ምክንያት ነው። 7 መገለጥ ወደእኛ የሚመጣው የክርስቶስን ትምህርት ወደ ልባችን ለመውሰድና በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ በፈለግነው መጠን ነው።

በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት መኖር የእውነት መገለጦች መቀበያ ቁልፍ እና አዳኙ የሚሰጠውን መመሪያ እየተከተልን እንደሆነ በራስ መተማመን እንዲኖረን የሚያስችል ቁልፍ መሆኑን ኔፊ በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ እንዳስተማረን ታስታውሳላችሁ። ኔፊ እነዚህን ቃላት ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጽፏል፦

“መላዕክት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይናገራሉ፤ ስለዚህ፣ የክርስቶስን ቃል ይናገራሉ። ስለሆነም፣ የክርስቶስን ቃል ተመገቡ እላችኋለሁ፤ እነሆ የክርስቶስ ቃል ማድረግ ያለባችሁን ነገሮች በሙሉ ይነግራችኋልና።

“ስለሆነም፣ አሁን እነዚህን ቃላት ከተናገርኩ በኋላ፣ መረዳት ካልቻላችሁ፣ ይህም ስላልጠየቃችሁ፣ ወይም ስላላንኳኳችሁ ነው፤ ስለሆነም፣ ወደ ብርሃኑ አልመጣችሁም፣ ነገር ግን በጨለማው ትጠፋላችሁ።

“እነሆም፣ በድጋሜ እላችኋለሁ በመንገዱ የምትገቡ፣ እናም መንፈስ ቅዱስን የምትቀበሉ ከሆነ፣ ማድረግ ያለባችሁን ነገሮች ሁሉ ያሳያችኋል።

“እነሆ፣ ይህ የክርስቶስ ትምህርት ነው፣ እናም ለእናንተ በስጋ እራሱን እስከሚገልፅ ድረስ ሌላ ትምህርት አይሰጥም። እናም እርሱ ራሱን በስጋ ለእናንተ በሚገልፅበት ጊዜ፣ የተናገራችሁን ነገሮች በትጋት ታደርጋላችሁ።” 8

ጌታ በነቢያቱ አማካኝነት ነገሮችን ዛሬ እና በሚመጡት ቀናት ለእናንተና ለእኔ ይናገራል። ምን ምን ነገሮችን ማድረግ እንዳለብን ይነግረናል፡፡ 9 አዳኙ ለእኔ እና ለእናንተ ትዕዛዛትን በጩኸት አይናገርም። ኤልያስ እንዳስተማረውም፦

“እርሱም፦ ውጣ፣ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፣ በእግዚአብሔር ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮችን ሰነጠቀ ዓለቶችንም ሰባበረ፣ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፣ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም፤

“ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፣ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምጽ ሆነ።” 10

ያን ድምፅ ማድመጥ የሚመጣው በእርሱ ባለን እምነት ነው። በቂ እምነት ይዘን ለመሄድና የሚጠይቀንን ሁሉ ለማድረግ መመሪያ እንጠይቃለን። 11 የሚጠይቀው ነገሮች ሁሉ ሌሎችን እንደሚባርክ ለማወቅ እምነትን እናዳብራለን፣ እንዲሁም በሂደቱ ለእኛ ባለው ፍቅር ምክንያት ልንነጻ እንችላለን።

በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት አብን መልስ ወደ መጠየቅ ሲመራን፣ ያው እምነት ደግሞ የእርሱን መመሪያ ለመስማት እና ለመታዘዝ ቆራጥ እና ጉጉ እንሆን ዘንድ የአዳኙን የደግነት ተግባር ያመጣል። ከዚያም ስራው ከባድ ቢሆንም “ሥራው ጣፋጭ ነው፣ አምላኬ፣ ንጉሴ” እያልን የመዝሙሩን ቃላት በደስታ እንዘምራለን። 12

በሕይወታችን እና በልባችን ውስጥ የክርስቶስ ትምህርት ይበልጥ በኖረ መጠን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኝን በረከት አግኝተው ለማያውቁ ወይም ያንን ጠብቀው ለማቆየት ለሚቸገሩ የበለጠ ፍቅር እና ርህራሄ ይሰማናል። ያለእምነት እንዲሁም በእርሱ ላይ መታመን ሳይኖር የጌታን ትእዛዛት መጠበቅ ከባድ ነው። አንዳንዶች በአዳኙ ላይ ያላቸውን እምነት ሲያጡ፣ መልካሙን መጥፎ እያሉ እና ክፉውን መልካም እያሉ ምክሩን እንኳ ሊያጠቁ ይችላሉ። 13 ይህንን አሳዛኝ ስህተት ለማስወገድ፣ እኛ የምናገኘው ማንኛውም የግል መገለጥ ከጌታ እና ከነቢያቱ ትምህርት ጋር የሚስማማ መሆኑ ወሳኝ ነው።

ወንድሞች እና እህቶች፣ ለጌታ ትዕዛዛት ታዛዥ መሆን እምነትን ይጠይቃል። ሌሎችን በእርሱ ስም ለማገልገል በኢየሱስ ክርስቶስ እምነትን ይጠይቃል። የእርሱን ወንጌል ለማስተማር ለመሄድ እንዲሁም የመንፈስ ድምጽ ለማይሰማቸው ወይም የመልዕክቱን እውነታ ለሚክዱ ሰዎች ለማቅረብ እምነት ይጠይቃል። ነገር ግን በክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ስንለማመድ—እንዲሁም ህያው ነቢያቱን ስንከተል—በዓለም ዙሪያ እምነት ይጨምራል። በተክኖሎጅይ ምክንያት፣ ምናልባት በታሪክ ውስጥ ካሉ ከማንኛውም ሌሎች ሁለት ቀናት ይልቅ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ብዙ የእግዚአብሔር ልጆች የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማሉ እንዲሁም ያውቃሉ።

በምድር ያለች የጌታ ቤተክርስቲያን እና መንግስት ስለመሆኗ ያላቸው እምነት በመጨመሩ፣ ብዙ አባላት አስራት ይከፍላሉ እንዲሁም እነዚህ አባላት የራሳቸውን ፈተናዎች እየተጋፈጡም ቢሆን የተቸገሩትን ለመርዳት ይለግሳሉ። በኢየሱስ ክርስቶስ እንደተጠሩ ባላቸው እምነት በአለም ዙሪያ የሚገኙ ሚስዮናውያን በወረርሽኙ ምክንያት የተፈጠሩትን ፈተናዎች የሚያሸንፉባቸውን መንገዶችን አግኝተዋል—ይህንንም በድፍረት እና በደስታ አድርገዋል። እንዲሁም ባደረጉት ተጨማሪ ጥረት እምነታቸው ይበልጥ ጠንክሯል።

ተቃውሞ እና ፈተናዎች ለረዥም ጊዜ እምነት የሚሳድጉ ለም መሬት ናቸው። በተለይም በዳግም መመለሱ መጀመሪያ አካባቢ ላይ እንዲሁም ከጌታ ቤተክርስቲያን መቋቋም ጀምሮ ያ ሁል ጊዜ እውነት ነው። 14

ፕሬዘዳንት ጆርጅ ኪው. ካነን ከረዥም ጊዜ በፊት የተናገሩት ዛሬም እውነት ነው፣ እንዲሁም አዳኙ ቤተክርስቲያኑን እና ህዝቡን ለመምራት በግል እስኪመጣ ድረስም እንዲሁ ነው፦“ለወንጌሉ መታዘዝ [ሰዎች] ከጌታ ጋር በጣም የጠበቀ ዝምድና እንዲኖራቸው ያደርጋል። በምድር ላይ ባሉ ሰዎች እና በሰማይ በሚኖረው በታላቁ ፈጣሪያችን መካከል የቅርብ ግንኙነት እንዲመሰረት ያደርጋል። በሃያሉ አምላክ እና በእርሱ የሚታመኑትን ሰዎች ትሁት ልመናዎች ለማዳመጥ እንዲሁም ለመመለስ ባለው ፈቃደኝነት ላይ ፍጹም የመተማመንን ስሜት ወደ ሰው አእምሮ ያመጣል። በፈተናዎች እና በአስቸጋሪ ጊዜያት ይህ መተማመን በዋጋ ከሚታመነው በላይ ነው። ችግር በግለሰብ ወይም በሰዎች ላይ ሊመጣ ይችላል፤ አደጋ ስጋት ሊፈጥር ይችላል፤ የእያንዳንዱ ሰው ተስፋም የጨለመ ሊመስል ይችላል። ሆኖም፣ ሰዎች ወንጌልን መታዘዝ ለሚያመጣቸው መብቶች ራሳቸውን ሲያዘጋጁ የተረጋገጠ የመቆሚያ ስፍራ አላቸው፤ እግሮቻቸውም በማይነቃነቅ አለት ላይ ናቸው።” 15

የቆምንበት ዓለት ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን እንደሚመሰክርልን፤ ይህች ራሱ የሚመራት ቤተክርስቲያኑ እንደሆነች፤ እንዲሁም ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን በህይወት ያሉ የእርሱ ነቢይ እንደሆኑ ምስክርነቴ ነው።

ፕሬዘዳንት ኔልሰን ከጌታ ዘንድ መመሪያ ይጠይቃሉ እንዲሁም ይቀበላሉ። እሳቸው ለእኔ ያንን መመሪያ ለመከተል ቁርጠኛ በመሆን የመጠየቅ ምሳሌዬ ናቸው። ለጌታ መመሪያ ለመታዘዝ ያለው ያው ቁርጠኝነት በቤተክርስቲያኑ አጠቃላይ ጉባኤ ውስጥ በተናገሩ ወይም ገና በሚናገሩ፣ በሚጸልዩ ወይም በሚዘምሩ ሁሉ ልብ ውስጥ ነው።

በምድር ዙሪያ ያሉ ይህንን ጉባኤ የሚመለከቱ ወይም የሚያዳምጡ ሁሉ ጌታ ለእነሱ ያለው ፍቅር ስሜት ይኖራቸው ዘንድ እጸልያለሁ። ቢያንስ አዳኙ ለእናንተ እንዲሁም የሰማይ አባታችን ለሆነው ለሰማይ አባቱ ያለውን ፍቅር ትንሽ ክፍል እንኳ ይሰማኝ ዘንድ ያቀረብኩትን ጸሎቴን የሰማይ አባት መልሶልኛል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው እንደሆነ እመሰክራለሁ! እሱ አዳኛችን እና ቤዛችን ነው። ይህች የእርሱ ቤተክርስቲያን ናት። እርሱም የእርሷ ራስ ነው። እርሱ ከሰማይ አባት ጋር ኒው ዮርክ በሚገኝ ቅዱስ ጥሻ ውስጥ ለጆሴፍ ስሚዝ ተገልጧል። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና ክህነቱ በሰማያዊ መልዕክተኞች ዳግም ተመልሷል። 16 በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያ እውነት እንደሆነ አውቃለሁ።

ያው ተመሳሳይ እምነት ይኖራችሁም ዘንድ እጸልያለሁ። መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር እንዲሆን የሚያስችሏችሁን ቃል ኪዳኖች ለመግባት እና ለመጠበቅ በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት እንዲኖራችሁ የሰማይ አባትን እንድትለምኑ እጸልያለሁ። ፍቅሬን እና ምስክርነቴን የምሰጣችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።