አጠቃላይ ጉባኤ
“ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?”
የጥቅምት 2021 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


13:6

“ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?”

ጌታን መጀመሪያ እንደምትወዱ ለማሳየት በግል ሕይወታችሁ ውስጥ ምን ዓይነት ነገሮችን ልታደርጉ ትችላላችሁ?

በህዳር 2019 (እ.አ.አ.) ጓደኛዬ እና እኔ የተቀደሰችዋን ምድር ጎበኘን። እዛ እያለን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የሚናገሩትን ቅዱሳት መጻህፍት ከለስን እና አጠናን። በአንድ ጥዋት ኢየሱስ ከትንሳኤው በኋላ ደቀመዛሙርቱን ያገኘበት በሚመስለው ቦታ በሰሜን ምዕራባዊ የገሊላ ባሕር ዳርቻ ላይ ቆምን።

ከኢየሱስ ትንሳኤ በኋላ፣ በዮሐንስ ምዕራፍ 21 ውስጥ ስናነብ፣ ጴጥሮስ እና ሌሎቹ ደቀመዛሙርት ምሽቱን በሙሉ ያለምንም ስኬት አሳ ማጥመዳቸውን ቀጠሉ። 1 በጥዋትም በጀልባዋ ሌላኛው አቅጠጫ በኩል መረባቸውን እንዲጥሉ የነገራቸውን አንድ ሰው በባሕሩ ዳርቻ ላይ ቆሞ ተመለከቱ። ለእነሱ በሚያስገርም ሁኔታ መረቡ በተዓምራት በአሳዎች ተሞላ። 2

ሰውዬው ጌታ እንደሆነ ወዲያውኑ ተገነዘቡና ሰላምታ ሊሰጡት ተጣደፉ።

በአሶች የተሞላውን መረብ ወደ ዳርቻው ሲጎትቱ፣ ኢየሱስ ፣ “ኑ፣ ምሳ ብሉ” አለ። 3 ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ዘገበ፣ “ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፣ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው።” 4

በዛው የባሕር ዳርቻ ላይ ቆሜ ሳለሁ፣ የአዳኙ ጥያቄ የሆነ ቀን ከሚጠይቀኝ በጣም አስፈላጊ ጥያቄዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ተገነዘብኩኝ። የእርሱ ድምፅ እንዲህ ብሎ ሲጠይቀኝ ይሰማኛል፣ “ራስል፣ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?”

ጴጥሮስን “ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” ብሎ ሲጠይቅ ኢየሱስ ስለ ምን እየተናገረ እንደሆነ ታስባላችሁን?

ይህንን ጥያቄ ከቀናችን ጋር ስናነፃፅር፣ እንዴት በስራ እንደተጠመድን እና ብዙ አወንታዊ እና አሉታዊ ተፅዕኖዎች ትኩረታችንን እና ጊዜያችንን ለማግኘት እየተሻሙ እንደሆነ ጌታ እየጠየቀን ይሆናል። ከዚህ ዓለም ነገሮች በላይ እንደምንወደው እያንዳንዳችንን እየጠየቀን ይሆናል። ይህም በሕይወት ውስጥ በእርግጥ ለምን ዋጋ እንደምንሰጥ፣ ማንን እንደምንከተል እና ከቤተሰብ አባላት እና ከጎረቤቶች ጋር ያለንን ግንኙነት እንዴት እንደምንመለከት የሚጠይቅ ጥያቄ ሊሆን ይችላል። ወይም ምናልባት በእርግጥ ምን ደስታ እና ሃሴት አንደሚያመጣልን እየጠየቀን ይሆናል።

የዚህ ዓለም ነገሮች አዳኙ ለደቀመዛሙርቱ የሰጠውን እና ለእኛ የሚሰጠውን ደስታ፣ ሃሴት እና ሰላም ያመጡልናልን? ስንወደው እና ትምህርቶቹን ስንከተል እርሱ ብቻ ነው ደስታን፣ ሃሴትን እና ሰላምን ሊያመጣልን የሚችለው።

“ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” የሚለውን ጥያቄ እንዴት አንመልሰዋለን?

የዚህን ጥያቄ ሙሉ ትርጉም ስንረዳ፣ የተሻልን የቤተሰብ አባል፣ ጎረቤቶች፣ ዜጎች፣ የቤተክርስቲያን አባሎች እና የእግዚአብሔር ወንድ እና ሴት ልጆች መሆን እንችላለን።

በእድሜዬ፣ በብዙ የቀብር ስነ-ስርዓቶች ላይ ተገኝቻለሁ። ያስተዋልኩትን ነገር ብዙዎቻችሁ እንደተገነዘባችሁት እርግጠኛ ነኝ። የአንድን የሞተ የቤተሰብ አባል ወይም ጓደኛ ሕይወት ስንዘክር፣ ስለ ሰውዬው የመኖሪያ ቤት መጠን፣ የመኪና ብዛት ወይም የባንክ አካውንት የገንዘብ መጠን መናገር የተለመደ አይደለም። ስለማህበራዊ ሚዲያ ተሳትፎዎች ብዙ ጊዜ አይናገሩም። በነበርኩባቸው ብዙ የቀብር ስነ-ስርዓቶች ላይ፣ ከሚወዱት ሰዎች ጋር ስለነበራቸው ግንኙነቶች፣ ለሌሎች ስላበረከቱት አገልግሎት፣ በሕይወት ስለተማሩት ትምህርቶች እና ልምዶች እንዲሁም ለኢየሱስ ክርስቶስ ባላቸው ፍቅር ላይ ያተኩራሉ።

አባባሌ ግር አይበላችሁ። የጥሩ ቤት ወይም የጥሩ መኪና ባለቤት መሆን ስህተት ነው እያልኩኝ ወይም ማህበራዊ ሚዲያን መጠቀም መጥፎ ነው እያልኩኝ አይደለም። እኔ እያልኩኝ ያለሁት በመጨረሻ ላይ እነዚያ ነገሮች አዳኙን ከመውደድ ጋር ሲነፃፀሩ ብዙም ጥቅም የላቸውም።

እርሱን ስንወደው እና ስንከተለው፣ በእርሱ እምነት አለን ማለት ነው። ንስሀ እንገባለን። የእርሱን ምሳሌ እንከተላለን እናም እንጠመቃለን ከዚያም መንፈስ ቅዱስን እንቀበላለን። እሰከመጨረሻ እንፀናለን እናም በቃል ኪዳኑ መንገድ ላይ እንቆያለን። የያዝነውን ቂም ትተን የቤተሰብ አባላትን እና ጎረቤቶችን ይቅር እንላለን። የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ለመጠበቅ በትጋት እንጥራለን። ታዛዥ ለመሆን እንጥራለን። ቃል ኪዳኖችን እንገባለን እናም እንጠብቃለን። አባቶቻችንን እና እናቶቻችንን እናከብራለን። የዓለምን አሉታዊ ተፅዕኖዎች ወደ ጎን እንተዋለን። ለእርሱ ዳግም ምፅዓት እራሳችንን እናዘጋጃለን።

በ“ህያዉ ክርሰቶስ፦ የሐዋርያት ምስክር፣” ውስጥ እንደምናነበው፣ “[ኢየሱስ] አንድ ቀን ወደ ምድር ይመለሳል። … የነገስታት ንጉሥ እና የጌቶች ጌታ በመሆን ይገዛል እና እያንዳንዱ ጉልበት ይሰግዳል እናም በእርሱ ፊት በአምልኮ የእያንዳንዱ አንደበት ይናገራል። እንደስራዎቻችን እና እንደ ልቦቻችን መሻት እያንዳንዳችን በእርሱ ሊፈረድብን እንቆማለን።” 5

“ህያው ክርስቶስ” የሚለውን ሰነድ ከፈረሙት ሐዋርያቶች አንዱ እንደመሆኔ፣ ኢየሱስ “የዓለም ብርሃን፣ ህይወት እና ተስፋ” 6 እንደሆነ ማወቄ በየቀኑ እርሱን የበለጠ ለመውደድ ታላቅ ፍላጎትን ይሰጠኛል ማለት እችላለሁ።

የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው እንደሆኑ እመሰክራለሁ። እኛን እንደሚወዱን እመሰክራለሁ። ቅዱሳት መጻህፍት እንዲህ ያስተምሩናል፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” 7 ቅዱሳት መጻህፍት ስለኢየሱስም እንዲህ ይናገራሉ፣ “ያመኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ አለምን በመውደድ እርሱ ህይወቱን አሳልፎ ሰጠ።” 8

የሰማይ አባት እኛን በጣም ከመውደዱ የተነሳ አዳኝን ማዕከል ያደረገ የደህንነት ዕቅድን አዘጋጀ። ኢየሱስ እኛን በጣም ከመውደዱ የተነሳ፣ የሰማይ አባት “ማንን ልላክ?” ብሎ በጠየቀበት በሰማይ ውስጥ በነበረው በታላቁ ምክር ላይ፣ የሰማይ አባት የመንፈስ ልጆች የበኩር ልጅ የሆነው ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰ፣ “እዚህ አለሁ፣ እኔን ላከኝ።” 9 ለአብ እንዲህ አለ፣ “አባት ሆይ፣ ፈቃድህ ይፈጸም፣ እናም ክብርም ለዘለአለም ያንተ ይሁን።” 10 እንደእነርሱ መሆን እንችል ዘንድ እና ወደ እነርሱ መገኛ መመለስ እንችል ዘንድ ኢየሱስ የእኛ አዳኝ እና ቤዛ ለመሆን ፈቃደኛ ሆነ።

እነዚህ ሁለት ጥቅሶች ወደ እነርሱ መገኛ ለመመለስ ማመን እንደሚገባን ያስተምራሉ። በኢየሱስ እና በእግዚአብሔር የደስታ ዕቅድ ላይ ማመን ይኖርብናል። ምንም እንኳን በፈተናዎች እና ግጭቶች ውስጥ ብንሆንም ማመን ማለት አዳኛችንን መውደድ እና ትዕዛዛቱን መከተል ማለት ነው።

የዛሬው ዓለም ያልተረጋጋች ነች። ቅሬታ፣ አለመስማማት፣ ጭንቀት እና መዘናጋት አሉ።

ፕሬዝዳንት ዳለን ኤች. ኦክስ በ2017 (እ.አ.አ) ንግግር ሲያደርጉ ይህንን አስገነዘቡ፦ “እነዚህ በጦርነት እና የጦርነት ወሬዎች፣ በተላላፊ የወረርሽኝ በሽታዎች፣ በድርቆች፣ በጎርፎች እና በዓለም አየር ሙቀት ታላቅ ጭንቀት የተሞሉ አስቸጋሪ ጊዜያት ናቸው።” 11

ከመጠን በላይ የሆኑ ችግሮች ቢያጋጥሙንም እንኳን በኢየሱስ ያለንን ፍቅር እና ተስፋ ማጣት የለብንም። የሰማይ አባት እና ክርስቶስ በምንም አይረሱንም። ይወዱናል።

ባለፈው ጥቅምት ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን የሰማይ አባትን እና ኢየሱስ ክርስቶስን በሕይወታችን ውስጥ የማስቀደምን ጥቅም አስተማሩን። ፕሬዚዳንት ኔልሰን የእስራኤል አንደኛው ትርጉም “እግዚአብሔር እንዲያሸንፍ” መፍቀድ እንደሆነ አስተማሩን። 12

እሳቸው አያንዳንዳችንን ይህንን ጥያቄ ጠየቁን፦ “እግዚአብሔር በህይወታችሁ እንዲያሸንፍ እናንተ ፍቃደኞች ናችሁን? እግዚአብሔር በህይወታቸው በጣም ሃይለኛ ተጽዕኖ እንዲሆን እናንተ ፈቃደኞች ናችሁን? የእርሱ ቃላት፣ ትዕዛዛት፣ እና ቃል ኪዳኖች በየዕለቱ በምታደርጉት ነገር ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ ትፈቅዳላችሁን? ድምጹ ከሌሎች ድምጽች በላይ ቅድሚያውን እንዲይዝ ትፈቅዱለታላችሁን? እርሱ እንድታደርጉ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ከሌላው ግብ ሁሉ በፊት ለማስቀደም ፈቃደኞች ናችሁን? የእናንተ ፍላጎት በእርሱ ውስጥ እንዲዋጥ ፍቃደኞች ናችሁን?” 13

የእኛ ትክክለኛ ደስታ የሚወሰነው ከእግዚአብሔር፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከእያንዳንዳችን ጋር ባለን ግንኙነት እንደሆነ ሁሌም ማስታወስ ይኖርብናል።

ፍቅራችንን የምናሳይበት አንዱ መንገድ እርስ በእርስ በተሻለ ሁኔታ አገልግሎት ለመስጠት የሆኑ ትንንሽ ነገሮችን ለማድረግ ቤተሰብን፣ ጓደኞችን እና ጎረቤቶችን በመቀላቀል ነው። ይህንን ዓለም የተሻለ ቦታ የሚያደርጉ ነገሮችን አድርጉ።

ጌታን መጀመሪያ እንደምትወዱ ለማሳየት በግል ሕይወታችሁ ውስጥ ምን ዓይነት ነገሮችን ልታደርጉ ትችላላችሁ?

ጎረቤቶቻችንን እርሱ እንደወደዳቸው መውደድ ላይ ስናተኩር፣ በዙሪያችን ያሉትን በእርግጥ መውደድ እንጀምራለን። 14

በድጋሜ እጠይቃለሁ፣ “ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” የሚለውን ጥያቄ እንዴት ትመልሱታላችሁ?

እኔ እንዳደረኩት ይህን ጥያቄ ስታስቡ፣ ከዚህ በፊት ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ እንደመለሰው እንድትመልሱ እጸልያለሁ፣ “አዎን ጌታ ሆይ፣ እንድምወድህ አንተ ታውቃለህ፣” 15 እና ከዚያም በኋላ ይህን እግዚአብሔርን እና በዙሪያችሁ ያሉትን በመውደድ እና በማገልገል አሳዩ።

የምንኖርበትን መንገድ እና እርስ በእርስ እንዴት መንከባከብ እንዳለብን እንዲመራን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ስላለን እንደተባረክን እመሰክራለሁ። በእርሱም እያንዳንዳቸው የእግዚአብሔር ወንድ እና ሴት ልጆች ለእርሱ ውድ እንደሆኑ ለማወቅ እንችላለን።

ኢየሱስ ክርስቶስ ውዱ ቤዛችን እንደሆነ እመሰክራለሁ። የእግዚአብሔር አንድያ ልጅም ነው። ይህን ምስክርነት የምሰጠው በትህትና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው አሜን።