በክርስቶስ በማመን መንፈሳዊ አውሎ ነፋሳችንን መጋፈጥ
በክርስቶስ በማመን እና ትእዛዛቱን በመጠበቅ መንፈሳዊ ማዕበሎቻችንን ከሁሉም በተሻለ ሁኔታ እንጋፈጣለን።
ላለፉት ስድስት ዓመታት ባለቤቴ አን እና እኔ አንዳንድ ታላላቅ የባህር አውሎ ነፋሶች አሜሪካን በመቱበት፣ ከፍተኛ ውድመት አልፎ ተርፎም የሕይወት መጥፋትን ባስከተሉበት በቴክሳስ ባሕረ ሰላጤ ጠረፍ አቅራቢያ ኖረናል ። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ የቅርብ ወራቱም እንደዚህ ላሉት አስከፊ ክስተቶች እንግዳ አልነበሩም። ፍቅራችን እና ጸሎቶቻችን በማንኛውም መንገድ ለተጎዱ ሁሉ ይዘልቃል። በ2017 (እ.አ.አ) እስከዛሬ ከተመዘገበው የበለጠ እስከ 60 ኢንች (150 ሴ.ሚ.) የሚደርስ ዝናብ ያስከተለውኸሪኬን ሃርቬይ እኛም አጋጥሞናል።
የተፈጥሮ ሕጎች የባህር አውሎ ነፋሶች መፈጠርን ይወስናሉ። የውቅያኖሱ ሙቀት ቢያንስ 80 ዲግሪ ፋራናይት (27 ሴንቲ ግሬድ) መሆን አለበት፣ ይህም ከውቅያኖሱ ወለል በታች እስከ 165 ጫማ (50 ሜትር) መዝለቅ አለበት። ነፋስ ከሞቃታማው የውቅያኖስ ውሃ ጋር ሲገናኝ፣ ውሃው ተንኖ ወደፈሳሽነት ወደሚቀየርበት ወደ ከባቢ አየር ከፍ እንዲል ያደርገዋል። ከዚያም ደመናዎች ይፈጠራሉ፣ እናም ነፋሶች በውቅያኖሱ ወለል ላይ ጠመዝማዛ ግድግዳን ይፈጥራሉ።
አውሎ ነፋሶች በመጠን ግዙፍ ናቸው፣ እስከ 50,000 ጫማ (15,240 ሜትር) ወይም ከዚያ በላይ ወደ ከባቢ አየር የሚደርሱ እና ቢያንስ ከዳር እስከዳር 125 ማይል ( 200 ኪሎ ሜትር) የሚዘልቁ ናቸው። የሚገርመው፣ የባህር አውሎ ነፋሶች መሬት ሲደርሱ፣ ለጥንካሬያቸው ጉልበት ከሚሰጠው የሞቀ ውሃ በላይ ስላልሆኑ መዳከም ይጀምራሉ። 1
አውዳሚ አካላዊ አውሎ ነፋስ በጭራሽ ላያጋጥማችሁ ይችላል። ሆኖም ግን፣ እያንዳንዳችን ሰላማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ እና እምነታችንን የሚፈትኑ መንፈሳዊ አውሎ ነፋሶች አጋጥመውናል፣ እናም ያጋጥሙናል። በዘመናዊው ዓለም፣ እነዚህ በድግግሞሽ እና በጥንካሬ እየጨመሩ ይመስላል። ደስ የሚለው፣ ጌታ በደስታ የምናሸንፍባቸውን አስተማማኝ መንገድ ሰጥቶናል። የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በመኖር፣ “የጨለማ የመከራ ደመናዎች በላያችን ላይ ሲያንዣብቡ እና ሰላማችንን ለማጥፋት ሲያስፈራሩ፣ በፊታችን ተስፋ በብሩህ ፈገግታ ይገኛል”። 2
ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዲህ ገልጸዋል፦
“ቅዱሳን በማንኛውም ሁኔታ መደሰት ይችላሉ። መጥፎ ቀን፣ መጥፎ ሳምንት፣ ወይም መጥፎ አመት ቢያጋጥመን እንኳ ደስታ ሊሰማን እንችላለን።
“… የሚሰማን ደስታ፣ ካሉን የህይወታችን ሁኔታዎች ጋር ያለው ግንኘነት አነስተኛ ነው እንዲሁም በህይወታችን ትኩረት ከምንሰጠው ነገር ጋር ያላቸው ተዛምዶ ታላቅ ነው።
“የህይወታችን ትኩረት … በኢየሱስ ክርስቶስና በወንጌሉ ላይ ሲሆን፣ በህይወታችን እየተከሰተ ካለው ወይም ሳይከሰት ከቀረው ሁኔታ ባሻገር ደስታ ሊሰማን ይችላል።” 3
የተፈጥሮ ሕጎች አካላዊ አውሎ ነፋሶችን እንደሚወስኑ ሁሉ፣ መለኮታዊ ሕጎች በመንፈሳዊ አውሎ ነፋሳችን ወቅት እንዴት ደስታ እንደሚሰማን ይወስናሉ። የህይወት ማዕበሎችን ደፍረን ስንጋፈጥ የሚሰማን ደስታ ወይም ሰቆቃ እግዚአብሔር ካወጣቸው ሕጎች ጋር የተሳሰሩ ናቸው። ፕሬዚዳንት ኔልሰን፣ “እነዚህም ትዕዛዛት ተብለው ይጠራሉ፣ ግን ልክ እንደ ነገሮችን ማንሳት ሕግ፣ የስበት ሕግ [እና] የልብ ምትን እንደሚቆጣጠረው ሕግ እውነት ናቸው” ሲሉ አካፍለዋል።
ፕሬዚዳንት ኔልሰንም፣ “ይህም ቀለል ያለ ቀመር ይሆናል - ደስተኛ ለመሆን ከፈለጋችሁ፣ ትእዛዛቱን ጠብቁ” 4 ሲሉ ይቀጥላሉ።
ጥርጣሬ የእምነት እና የደስታ ጠላት ነው። ሞቃታማ የውቅያኖስ ውሃ ለባህር አውሎ ነፋሶች መፈጠር አመቺ ሁኔታ እንደሆነ ሁሉ ጥርጣሬም ለመንፈሳዊ አውሎ ነፋሶች መፈጠር አመቺ ሁኔታ ነው። እምነት ምርጫ እንደሆነ ሁሉ ጥርጣሬም እንዲሁ ምርጫ ነው። መጠራጠርን በምንመርጥበት ጊዜ፣ ለጠላት ኃይልን በመስጠት፣ እርምጃ እንዲወሰድብን እንመርጣለን፣ በዚህም ደካማ እና ተጋላጭ ያደርገናል። 5
ሰይጣን ለጥርጣሬ መፈጠር አመቺ ወደሆነ ሁኔታ ሊመራን ይፈልጋል። እንዳናምን ልባችንን ሊያደነድን ይፈልጋል። 6 ጥርጣሬን ለመፍጠር አመቺ የሆነ ሁኔታ የሚጋብዝ ይመስላል፣ ምክንያቱም ሰላማዊ የሚመስለው፣ ሞቅ ያለው ውሃ “ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ” 7 ፣ እንድንኖር አይጠብቅብንም። በእንደዚህ ዓይነት ውሃዎች ውስጥ ሰይጣን መንፈሳዊ ንቃታችንን እንድናላላ ይፈትነናል። ያ ግድየለሽነት “ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ” 8 ፣ ያልሆንበትን መንፈሳዊ እምነት ማጣት ሊያስከትል ይችላል። በክርስቶስ ላይ ካልተጣበቅን፣ ጥርጣሬ እና ወጥመዶቹ፣ ተአምራትን፣ ዘላቂ ደስታን ወይም “ለነፍሳችን ዕረፍትን” ወደማናገኝበት ግድየለሽነት ይወስዱናል።” 9
አውሎ ነፋሶች በመሬት ላይ እንደሚዳከሙ ሁሉ፣ መሠረታችንን በክርስቶስ ላይ ስንገነባ ጥርጣሬ በእምነት ይተካል። ከዚያም መንፈሳዊ አውሎ ነፋሶችን በተገቢው አኳኋን ማየት እንችላለን፣ እናም እነሱን ለማሸነፍ አቅማችን እየሰፋ ይሄዳል። ከዚያም፣ “ዲያብሎስ ኃይሉን ንፋሱን፣ አዎን፣ በአውሎ ነፋስ እንደሚወረወር ዘንጉን በላከ ጊዜ፣ … እርግጠኛ መሰረት በሆነው ሰዎች ከገነቡበት ሊወድቁበት በማይችሉበት አለት ላይ ስለገነባችሁ እናንተን ወደ ስቃይና ወደባህር ስላጤና መጨረሻ ወደሌለው ዋይታ ጎትቶ ለመጣል ኃይል አይኖረውም።” 10
ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፦
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለ እምነት የሁሉም እምነት መሠረት እና የመለኮታዊ ኃይል መተላለፊያ ነው።
ጌታ ከእርሱ ፍጹም ሀይል እንድንካፈል ከእኛ ፍጹም እምነትን አይጠብቅም። ነገር ግን እንድናምን ይጠይቀናል።” 11
ከሚያዚያ አጠቃላይ ጉባኤ ጀምሮ፣ እኔና ቤተሰቦቼ “ፈተናዎቻችንን አቻ ወደማይገኝለት እድገትና እና ዕድል ለመቀየር” 12 ፣ እንዲረዱን በኢየሱስ ክርስቶስ እና በኃጢያት ክፍያው ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከር እየፈለግን ነበር።
የልጅ ልጃችን ሩቢ በጠንካራ፣ ኃላፊነት የመውሰድ ፍላጎት ተባርካለች። በተወለደች ጊዜ የምግብ መውረጃ ቧንቧ ከሆዷ ጋር አልተያያዘም ነበር። ገና ሕፃን በነበረችበት ጊዜ እንኳ ሩቢ በወላጆቿ እርዳታ ይህንን ፈተና ባልተለመደ ቁርጠኝነት ተጋፈጠችው። ሩቢ አሁን አምስት ዓመቷ ነው። እሷ ገና በጣም ልጅ ብትሆንም ሁኔታዎ ደስታዋን እንዲወስኑ ባለመፍቀድ ጠንካራ ምሳሌ ናት። እሷ ሁል ጊዜ ደስተኛ ናት።
ባለፈው ግንቦት፣ ሩቢ በሕይወቷ ውስጥ ተጨማሪ አውሎ ነፋስን በእምነት ተጋፈጠች። እርሷም የማስተካከያ ቀዶ ጥገና ከሚያስፈልገው ሙሉ በሙሉ ካልዳበረ እጅ ጋርም ነበር የተወለደችው። ከዚህ በጣም ውስብስብ ከሆነ ቀዶ ጥገና በፊት፣ ጎበኘናትና የሕፃን እጅ የአዳኝን እጅ ሞቅ ባለ ሁኔታ እንደያዘች በሚያምር ሁኔታ የሚያሳይ ሥዕል ሰጠናት። እሷ ፈርታ እንደሆነ ስንጠይቃት፣ “አልፈራሁም፣ ደስተኛ ነኝ!” ብላ መለሰች።
ከዚያ እኛም “ሩቢ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?” ብለን ጠየቅናት።
ሩቢም በልበ ሙሉነት “ምክንያቱም ኢየሱስ እጄን እንደሚይዝ አውቃለሁ” አለች።
የሩቢ ማገገም ተዓምራዊ ሆኗል፣ እናም ደስተኛ መሆኗን ቀጥላለች። እያደግን ስንሄድ በተደጋጋሚ ሊፈትነን ከሚችለው የጥርጣሬ ሞኝነት ጋር ሲነጻጸር የልጅ እምነት ንጽህና እንዴት ይቃረናል! 13 ግን ሁላችንም እንደ ትንሽ ልጆች መሆን እና አለማመናችንን ወደ ጎን ለመተው መምረጥ እንችላለን። ቀላል ምርጫ ነው።
አሳቢ አባት አዳኙን በትጋት እንዲህ በማለት ተማጸነ፣ “ቢቻልህ ግን… እርዳንም አለው” 14
ጌታም እንዲህ አለው፥
“ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል።
“ወዲያውኑ የብላቴናው አባት ጮኸ፣ አምናለሁ፣ አለማመኔን እርዳው።” 15
ይህም ትሁት አባት ከጥርጣሬ ይልቅ በክርስቶስ ያለውን እምነት በጥበብ መርጧል። ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዳካፈሉት፣ “ የእናንተ አለማመን ብቻ ነው እግዚአብሔር በእናንተ ህይወት ውስጥ ያሉትን ተራራዎች ለማነቃነቅ በሚያስችሉ ተዓምራት መባረኩን የሚገድበው። 16
መንጠራሪያ ዘንጉን በእውቀት ደረጃ ሳይሆን በእምነት ደረጃ ማድረጉ እግዚአብሔር ለእኛ ምን ያህል መሐሪ ነው!
አልማ እንደሚከተለው ያስተምራል፦
“በእግዚአብሔር ቃል ያመነ፣ እርሱ የተባረከ ነው።” 17
“እግዚአብሔር በስሙ ለሚያምኑት ሁሉ መሃሪ መሆኑን እንድታስታውሱም እፈልጋለሁ፤ ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ በእርሱ እንድታምኑ፤” 18
አዎን፣ በመጀመሪያ፣ እግዚአብሔር በእርሱ እንድናምን ይፈልጋል።
እኛ በክርስቶስ በማመን እና ትእዛዛቱን በመጠበቅ መንፈሳዊ ማዕበሎቻችንን ከሁሉም በተሻለ ሁኔታ እንጋፈጣለን። “እምነታችን እና መታዘዛችን በሕይወታችን ውስጥ “[ማንኛውንም] የሚሆነውን ወይም የማይሆነውን” ለማሸነፍ ከራሳችን በላይ ካለው ኃይል ጋር ያገናኘናል።” 19 አዎን፣ እግዚአብሔር በማመናችን እና በመታዘዛችን “ወዲያውኑ [ይባርከናል]”። 20 በእርግጥ፣ በእርሱ ላይ ያለንን እምነት ስንለማመድ እና ትእዛዛቱን ስንጠብቅ ሁኔታችን ወደ ደስታ ይለወጣል እንዲሁም “በክርስቶስ ሕያዋን እንሆናለን።” 21
ወንድሞች እና እህቶች፣ ዛሬ “መጠራጠርን ሳይሆን፣ ግን ማመንን” እንመርጥ። 22 “ትክክለኛው መንገድ በክርስቶስ ማመን ነው፤” 23 “እኛን [በእጁ] መዳፍ [ቀርፆናል]።” 24 በራችን ላይ ቆሞ የሚያንኳኳ አዳኛችን እና ቤዛችን ነው። 25 በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።