አጠቃላይ ጉባኤ
እንደገና መተማመን
የጥቅምት 2021 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


13:7

እንደገና መተማመን

በእግዚአብሄር እንዲሁም እርስበርስ መተማመን የሰማይን በረከቶች ያመጣል።

አንድ ጊዜ ትንሽ ብላቴና ሳለሁ፣ ለአፍታ ከቤት ስለመጥፋት አሰብኩ። አንድ ብላቴና በሚያስብበት መንገድ ማንም ሰው እንደማይወደኝ ተሰማኝ።

እያየችኝ የነበረችው እናቴ ሰማችኝ እንዲሁም አረጋገጠችልኝ። እቤት በሰላም እኖር ነበር።

ከቤት እየጠፋችሁ የሆነ ያህል ተሰምቷችሁ ያውቃል? ብዙውን ጊዜ ከቤት መጥፋት ማለት ከራሳችን ጋር፣ እርስ በርሳችን ወይም ከእግዚያብሄር ጋር ያለው መተማመን ተበላሽቷል ወይም ፈርሷል ማለት ነው። መተማመን ተግዳሮት ሲገጥመው እንዴት እንደገና መተማመን እንችላለን ብለን እንጨነቃለን።

የዛሬው መልእክቴ፣ ወደ ቤት እየመጣንም ይሁን ወደ ቤት እየሄድን እግዚአብሔር ሊያገኘን ይመጣል። 1 እንደገና መተማመን እንችል ዘንድ በእርሱ እምነትንና ድፍረትን፣ ጥበብንና ማስተዋልን ማግኘት እንችላለን። ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣም ሆንን ተመልሰን የመጣን የእርሱ ቤተክርስቲያን ምቾት የሚሰጠን ቦታ ሊሆን ይችል ዘንድ እርስ በርሳችን እንድንደጋገፍ፣ የበለጠ ይቅር ባይ እንድንሆን እንዲሁም በራሳችን ላይም ሆነ አንዳችን በሌላው ላይ አብዝተን እንዳንፈርድ ይጠይቀናል።

“መተማመን የእምነት ተግባር ነው። እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለውን እምነት ይጠብቃል። ሆኖም የሰዎች እምነት በሚከተሉት ሁኔታዎች ምክንያት ሊዳከም ወይም ሊፈርስ ይችላል፦

  • ጓደኛ፣ የንግድ ሸሪክ ወይም የምናምነው ሰው ታማኝ ሳይሆን ሲቀር፣ ሲጎዳን ወይም ሲጠቀምብን። 2

  • የትዳር ጓደኛ እምነት ሲያጎድል።

  • ምናልባት ሳይታሰብ የምንወደው ሰው ሲሞት፣ ጉዳት ሲያጋጥመው ወይም ሲታመም።

  • ያልተጠበቀ የወንጌል ጥያቄ ሲገጥመን፣ ምናልባትም የቤተክርስቲያኗን ታሪክ ወይም የቤተክርስቲያን ፖሊሲን የሚመለከት አንድ ነገር ሲኖር እንዲሁም አንድ ሰው ቤተክርስቲያናችን በሆነ መንገድ እውነትን ደብቃለች ወይም እውነትን አልተናገረችም ብሎ ሲናገር።

ሌሎች ሁኔታዎች ብዙ የተለዩ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ሆኖም በእኩል ደረጃ አሳሳቢ ሊሆኑ ይችላሉ።

ምናልባት ራሳችንን ቤተክርስቲያን ውስጥ አንመለከትም፣ ብቁ እንደሆንን አይሰማንም፣ ሌሎች እንደሚፈርዱብን ይሰማንም ይሆናል።

ወይም የሚጠበቅብንን ሁሉ የሰራን ቢሆንም ነገሮች ገና አልተስተካከሉም። ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የግል ተሞክሮዎች ቢኖሩንም፣ እግዚአብሔር ሕያው እንደሆነ ወይም ወንጌል እውነት እንደሆነ እንደምናውቅ ገና ላይሰማን ይችላል።

ዛሬ ብዙዎች በሰዎች ግንኙነቶች እና በዘመናዊው ህብረተሰብ መካከል መተማመንን መልሶ የማምጣት ታላቅ አስፈላጊነት ይሰማቸዋል። 3

በመተማመን ላይ ስናሰላስል እግዚአብሔር የእውነት አምላክ እደሆነ እና “ሊዋሽ እንደማይችል” እናውቃለን። 4 እውነት ነገሮች እንዳሉ፣ እንደነበሩ፣ እናም ወደፊት እንደሚሆኑ ያለው እውቀት እንደሆነ እናውቃለን። 5 የማያቋርጥ መገለጥ እና መነሳሳት የማይለዋወጥ እውነትን ከሚለዋወጡ ሁኔታዎች ጋር እንደሚያስማማ እናውቃለን።

የፈረሱ ቃልኪዳኖች ልብ እንደሚሰብሩ እናውቃለን። “የማይሆኑ ነገሮችን አደረኩኝ?” አለ። “ይቅርታ ልታደርጊልኝ ትችያለሽ?” እንደገና ለመተማመን ተስፋ በማድረግ ባልና ሚስቱ እጅ ለእጅ ይያያዙ ይሆናል። በሌላ ሁኔታ አንድ የእስር ቤት ታራሚ “የጥበብ ቃልን ጠብቄ ቢሆን ኖሮ እዚህ አልገኝም ነበር” ሲል ያስባል።

በጌታ የቃል ኪዳን መንገድ ላይ ደስታን እናውቃለን፤ እንዲሁም በእርሱ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለማገልገል የሚሰጡ ጥሪዎች እግዚአብሔር ለእኛ እንዲሁም አንዳችን ላንዳችን እምነት እና ፍቅር እንዲሰማን የቀረቡ ግብዣዎች ናቸው። ነጠላ አዋቂዎችን ጨምሮ የቤተክርስቲያን አባላት በመላ ቤተክርስቲያኗ እና በማህበረሰባችን ውስጥ በቋሚነት ያገለግላሉ።

አንድ ኤጲስ ቆጶስ ወጣት ጥንዶችን በአጥቢያ የትንንሽ ልጆች ክፍል እንዲያገለግሉ በመንፈስ አነሳሽነት ይጠራል። መጀመሪያ ላይ ባልየው ተነጥሎ እና ርቆ ጥግ ላይ ይቀመጣል። ቀስበቀስ ከልጆቹ ጋር ፈገግታ መለዋወጥ ይጀምራል። በኋላም ጥንዶቹ ምስጋናቸውን ይገልጻሉ። ቀደም ብሎ ሚስት ልጆችን ፈለገች፤ ባል አልፈለገም ይላሉ። አሁን ማገልገል ለውጧቸዋል እንዲሁም አንድ አድርጓቸዋል። በልጆች የሚገኝን ደስታ ወደ ትዳራቸው እና ወደ ቤታቸውም አምጥቷል።

በሌላ ከተማ ውስጥ ትናንሽ ልጆች ያሏት አንዲት ወጣት እናት እና ባለቤቷ ተገረሙ እንዲሁም ከመጠን በላይ ተጨናነቁ፤ ነገር ግን የአጥቢያ የሴቶች መረዳጃ ማህበር ፕሬዝዳንት ሆና እንድታገለግል ስትጠራ ተቀበለች። ብዙም ሳይቆይ የበረዶ አውሎ ነፋስ የመደብር መደርደሪያዎችን ባዶ አድርጎ እና ቤቶችን እንደበረዶ መያዣ ሳጥን አቀዝቅዞ የኤሌክትሪክ ኃይልን አቋረጠ። ኃይል እና ሙቀት ስለነበራቸው ይህ ወጣት ቤተሰብ ማዕበሉን እንዲቋቋሙ ለበርካታ ቤተሰቦች እና ግለሰቦች ቤታቸውን በደግነት ከፈቱ።

ከባድ ነገሮችን በእምነት ስናደርግ መተማመን እውን ይሆናል። አገልግሎት እና መስዋዕትነት አቅምን ይጨምራሉ እንዲሁም ልብን ያጠራሉ። በእግዚአብሄር እንዲሁም እርስበርስ መተማመን የሰማይን በረከቶች ያመጣል።

አንድ ታማኝ ወንድም ከካንሰር ከተረፈ በኋላ በመኪና ተገጨ። ለራሱ ከማዘን ይልቅ “ከዚህ ተሞክሮ ምን እማራለሁ?” ሲል ጠየቀ። በጽኑ ህሙማን ማቆያ ክፍሉ ውስጥ ሆኖ ስለባሏ እና ስለልጇ የተጨነቀችውን ነርስ እንዲያስተውል የመነሳሳት ስሜት ተሰማው። የህመም ስሜት እየተሰማው ያለ አንድ ህመምተኛ በእግዚአብሔር ሲታመን እና ሌሎችን ሲረዳ መልሶችን ያገኛል።

ከፆታዊ ብልግና ሥዕሎች ጋር የተያያዘ ችግር ያለበት አንድ ወንድም ከቢሮው ውጭ እየጠበቀ ሳለ የካስማ ፕሬዚዳንቱ እንዴት መርዳት እንዳለበት ለማወቅ ጸለየ። “በሩን ክፈትና ወንድምን አስገባው“ የሚል ግልጽ መልዕክት መጣ። በእምነት እና በመተማመን እግዚአብሄር ይረዳል፤ የክህነት መሪው በሩን ከፈተና ይህን ወንድም አቀፈው። እያንዳንዳቸው የሚለውጥ ፍቅር እና በእግዚአብሄር እንዲሁም እርስበርስ የመተማመን ስሜት ተሰማቸው። ብርታት አግኝቶ ይህ ወንድም ንስሐ መግባት እና መለወጥ መጀመር ይችላል።

የግል ሁኔታዎቻችን የግል መሆናቸው እንዳለ ሆኖ የወንጌል መርሆዎች እና መንፈስ ቅዱስ በሌሎች ላይ እንደገና መታመን ይኖርብን እንደሆነ እና እንዳልሆነ፣ ከሆነስ እንዴት እና መቼ እንደሚሆን ለማወቅ ይረዱናል። መተማመን ሲፈርስ ወይም ክህደት ሲፈጸም ንዴት እና ብስጭት ይከሰታሉ፤በሰዎች ግንኙነት ውስጥ እምነት እና ድፍረት በድጋሚ ለመታመን መቼ ብቁ እንደሚሆኑ የማስተዋል አስፈላጊነትም እንዲሁ ነው።

ሆኖም የእግዚያብሄርን እና የግል መገለጥን በተመለተ ፕሬዚዳንት ረስል ኤም. ኔልሰን “ማንን ያለስጋት ማመን እንደምትችሉ ማሰብ አይኖርባችሁም” ሲሉ ማረጋገጫ ይሰጣሉ። 6 ሁሌም በእርሱ መታመን እንችላለን። ጌታ ራሳችንን ከምናውቀው እና ከምንወደው በላይ የተሻለ ያውቀናል እንዲሁም የበለጠ ይወደናል። ማለቂያ የሌለው ፍቅሩ እና ስላለፈው፣ ስላሁኑ እና ስለወደፊቱ ያለው ፍጹም እውቀት ቃልኪዳኖቹን እና ተስፋዎቹን ዘላቂ እና የተረጋገጡ ያደርጋቸዋል።

ቅዱሳን ጽሁፎች “ከብዙ ዘመንም በኋላ“ ብለው የሚጠሩትን እመኑ። 7 ከጌታ በረከት ጋር፣ ከዘመን በኋላ እንዲሁም ከቀጣይ እምነት እና ታዛዥነት ጋር መፍትሄ እና ሰላም ማግኘት እንችላለን።

ጌታ እንዲህ ሲል ያጽናናል፦

“ልቅሶ ማታ ይመጣል፥ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል።” 8

“ትካዜህን በጌታ ላይ ጣል በማያቋርጥ እንክብካቤውም ታመን።” 9

“ሰማይ መፈወስ የማይችለው ሀዘን ምድር የላትም።” 10

በእግዚአብሄር እና በተዓምራቱ ታመን። 11 እኛ እና ግንኙነቶቻችን ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ በጌታ በኢየሱስ የሃጢያት ክፍያ አማካኝነት ስግብግቡን የተፈጥሮ ማንነታችንን ማውለቅ እንችላለን እንዲሁም የዋህ፣ ትሁት፣ በእምነት የተሞላ እና ተገቢ እምነት ያለን የእግዚአብሄር ልጆች መሆን እንችላለን፡፡ 12 ንስሃ ስንገባ፣ ሃጢያቶቻችንን ስንናዘዝ እና ስንተዋቸው ጌታ ከእንግዲህ አላስታውሳቸውም ብሏል፤ እኛም ማስታወስ አይገባንም፡፡ 13 እርሱ ይረሳል ማለት አይደለም። ከዚያ ይልቅ በሚያስደንቅ ሁኔታ እነሱን ላለማስታወስ ይመርጣል ማለት ነው እንጂ፤ እኛም ማስታወስ አያስፈልገንም።

በጥበብ ለማስተዋል በእግዚአብሄር መነሳሳት ታመኑ። ጌታ አድርጉ እንዳለው በትክክለኛው ጊዜ እና መንገድ ሌሎችን ይቅር ለማለት እንችላለን 14 እሱንም “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች” በመሆን። 15

አንዳንድ ጊዜ ልባችን የተሰበረ እና የተዋረደ ሲሆን ከመንፈስ ቅዱስ መጽናናትን እና ምሪትን ለማግኘት እጅግ ዝግጁ እንሆናለን። 16 ወቀሳም ሆነ ይቅርታ ሁለቱም የሚጀምሩት ስህተት እንደተፈጠረ እውቅና በመስጠት ነው። አብዛኛውን ጊዜ ወቀሳ ትኩረቱን የሚያደርገው ባለፈ ነገር ላይ ነው። ይቅርታ በመጪው ጊዜ ነፃ ለመውጣት አሻግሮ ይመለከታል። “ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።” 17

ሃዋርያው ጳውሎስ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? ሲል ይጠይቅና፣ “ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ” ሲል ይመልሳል። 18 ሆኖም ከእግዚአብሔር እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ሊለየን የሚችል አንድ ሰው አለ—ያም ሰው እኛው እራሳችን ነን። ኢሳይያስ እንዳለው “ነገር ግን በደላችሁ በእናንተ እና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች።” 19

በመለኮታዊ ፍቅር እና ህግ ለምናደርጋቸው ምርጫዎች እና ለምንወስዳቸው ድርጊቶች ሃላፊነት አለብን። ነገር ግን የአዳኛችን የሃጢያት ክፍያ ፍቅር “መጨረሻ የሌለው እና ዘላለማዊ” ነው። 20 ወደቤት ለመምጣት ስንዘጋጅ “በጣም ሩቅ” 21 ብንሆንም እንኳን እግዚአብሔር ያለውን ምርጡን በደስታ በመስጠት በታላቅ ርኅራሄ ሊቀበለን ዝግጁ ነው። 22

ፕሬዝዳንት ጄ. ሩበን ክላርክ “ሰማያዊ አባት ሁሉንም ልጆቹን ለማዳን እንደሚፈልግ አምናለሁ፣ … በፍትሁ እና በምሕረቱ ለድርጊቶቻችን ከፍተኛውን ሽልማት እንደሚሰጠን፣ ሊሰጠን የሚችለውን ሁሉ እንደሚሰጠን እንዲሁም በተቃራኒው ሊጥልብን ከሚችለው ቅጣት አነስተኛውን እንደሚጥልብን አምናለሁ” 23 ብለዋል።

በመስቀል ላይ ሆኖ አዳኛችን ለአባቱ ያቀረበው የምሕረት ልመና “አባት ሆይ፣ ይቅር በላቸው” የሚል ምንም ቅድመ ሁኔታ የሌለው አልነበረም፤ ከዚያ ይልቅ “አባት ሆይ፣ ይቅር በላቸው የሚያደርጉትን አያውቁምና” ሲል ነበር ያቀረበው። 24 ስለማንነታችን፣ ስለምናውቀው እና ስለምናደርገው ነገር በእግዚአብሔር እና በራሳችን ፊት ተጠያቂ ስለሆንን የፈለግነውን መምረጥ መቻላችን እና ነፃነታችን ትርጉም አላቸው። ደስ የሚለው ነገር የእኛን ዓላማዎች እና ድርጊቶች በትክክል ለመዳኘት ባለው የእግዚአብሔር ፍጹም ፍትሕ እና ፍጹም ምሕረት መተማመን እንችላለን።

በእግዚአብሔር ርህራሄ ወደ እርሱ እና አንዳችን ወዳንዳችን ቤት ስንመጣ—እንደጀመርን እንጨርሳለን።

ሁለት ወንዶች ልጆች ስለነበሩት አንድ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ምሳሌ ታስታውሳላችሁ? 25 አንድ ልጅ ከቤት ኮበለለና ውርሱን አባከነ። ወደራሱ ሲመለስ ይህ ልጅ ወደ ቤት ሊመጣ ፈለገ። ሌላኛው ልጅ “ይህን ያህል አመት” ትዕዛዛቱን ሲጠብቅ እንደነበረ ስለተሰማው ወንድሙን ሊቀበለው አልፈለገም። 26

ወንድሞች እና እህቶች፣ እባካችሁ ኢየሱስ ልባችንን፣ ማስተዋላችንን፣ ርህራሄያችንን እና ትህትናችንን እንድናሳይ እና ራሳችንን በሁለቱም ቦታ አድርገን እንድናይ እየጠየቀን እንደሆነ ታስባላችሁን?

እንደመጀመሪያው ወንድ ወይም ሴት ልጅ ልንኮበልል እና በኋላም ወደቤት ለመመለስ እንፈልግ ይሆናል። እግዚአብሄር ሊቀበለን ይፈልጋል።

እንዲሁም ልክ እንደሌላው ወንድ ወይም ሴት ልጅ እያንዳንዳችን ወደቤት ወደ እርሱ ስንመጣ እግዚአብሔር አብረን ደስ እንዲለን ቀስ ብሎ በአጽንኦት ይማጸናል። ጉባኤዎቻችንን፣ ቡድኖቻችንን፣ የክፍል ትምህርቶቻችንን እና እንቅስቃሴዎቻችንን ክፍት፣ እውነተኛ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ—አንዳችን ላንዳችን መኖሪያ እንድናደርግ ይጋብዘናል። በደግነት፣ በመግባባትና በመከባበር እያንዳንዳችን በትህትና ጌታን እንሻለን፤ የተመለሰው የወንጌሉ በረከቶች ለሁሉም እንዲደርሱ እንጸልያለን እንዲሁም እንቀበላለን።

የሕይወት ጉዞዎቻችን የግል ናቸው፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር፣ አንዳችን በሌላችን እንዲሁም በራሳችን በመታመን እንደገና ወደ እግዚአብሔር አባታችን እና ወደተወዳጅ ልጁ መመለስ እንችላለን። 27 “እመኑ ብቻ እንጂ፣ አትፍሩ” ሲል ይጋብዘናል። 28 ልክ ነብዩ ጆሴፍ ተስፋ ሳይቆርጥ እንዳደረገው በሰማይ አባታችን ጥበቃ እንታመን። 29 ውድ ወንድም፣ ውድ እህት ውድ ጓደኛ እባካችሁ ዛሬ ቃል የገባላችሁን ተዓምር—እምነትን እና መታመንን እንደገና ፈልጉ። በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም፣ አሜን።