አጠቃላይ ጉባኤ
ወደ አዳኙ መቅረብ
የጥቅምት 2022 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


15:4

ወደ አዳኙ መቅረብ

አዳኙን ለማወቅ እና ለመውደድ እየፈለግን፣ ከእግዚአብሔር ጋር በገባነው ቃል ኪዳን፣ የተለየ፣ ያልተለመደ እና ልዩ በመሆን፣ እራሳችንን ከሌሎች በተለየ መንገድ ከሚያምኑት ሳንነጥል፣ ራሳችንን ከአለም እንለያለን።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በዚህ ምሽት ትሁት እና ታማኝ የሆኑ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮችን አነጋግራለሁ። የህይወታችሁን መልካምነት እና በአዳኛችን ያላችሁን እምነት በዚህች ሀገር እና በአለም ላይ ባሉ አገራት ውስጥ ስመለከት፣ የበለጠ እወዳችኋለሁ።

ወደ አገልግሎቱ መጨረሻ አካባቢ፣ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት “የመምጣ[ቱ]ና የዓለም መጨረሻ ምልክ[ት] ምንድን”1 እንደሆነ እንዲነግራቸው ጠየቁት።

ከእርሱ ዳግም መመለስ በፊት ስለሚኖሩ ሁኔታዎች ነገራቸው እና እንዲህ በማወጅ ፈጸመ፣ “ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ።”2

ባለፈው አጠቃላይ ጉባኤ ላይ፣ የፕሬዘዳንት ሔንሪ ቢ. አይሪንግን ቃላት በጥሞና አዳመጥኳቸው፦ “እያንዳንዳችን፣ የትም ብንሆን፣ ይበልጥ አደገኛ በሆነ ጊዜ ውስጥ እንደምንኖር እናውቃለን። … ማንም የዘመኑን ምልክቶች ለማየት አይን ያለው እና የነቢያትን ቃላት ለመስማት ጆሮ ያለው ይህ እውነት መሆኑን ያውቃል።”3

ጀግናዎቹን ደቀመዛሙርቱንም አዳኙ እንዲህ ሲል አመሰገናቸው፦ “ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን [ናችሁ]።”4 በዚህ ጉባኤ በነቢያቱ እና በሌሎች በኩል የሚመጡትን የጌታ ቃላት አጥብቀን ስናዳምጥ፣ ይህ በረከት ለእኛ ይሁን።

ስንዴ እና እንክርዳድ

ጌታ ከመምጣቱ በፊት ባለው በዚህ የመጨረሻ ጊዜ፣ “የመንግስት ልጆች” ብሎ የገለጻቸው “ስንዴ”5 “ከእንክርዳዱ” ወይም እግዚአብሔርን ከማይወዱ ወይም ትእዛዙን ከማይጠብቁት ጋር ጎን ለጎን እንደሚበቅሉ ገልጿል። “ሁለቱም” ጎን ለጎን “አብረው ያድጋሉ”6

ይህም አዳኝ እስከሚመለስ ድረስ፣ በሁለቱም በኩል መልካምም መጥፎም ጎን ለጎን የሚገኙበት አለማችን ይሆናል።7

አንድ አንድ ጊዜ እንደ ጠንካራ የስንዴ ዛላ ላይሰማችሁ ይችላል። በራሳችሁ ትእግስተኛ ሁኑ! ጌታም ስንዴው የሚለመልሙ ቅጠሎችን እንደሚያካትት ተናገረ።8 ሁላችንም የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ነን፣ እናም ለመሆን የምንፈልጋቸውን ሁሉ ባንሆንም የእርሱ እውነተኛ ደቀመዛሙርት ለመሆን ባለን ፍላጎት ቀልድ አናውቅም።

በኢየሱስ ክርስቶስ ያለ እምነትን ማጠንከር

በአለም ላይ ክፋት እየጨመረ በሄደ ቁጥር የእኛ መንፈሳዊ ህልውና እና የምንወዳቸው ሰዎች መንፈሳዊ ህልውና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት የበለጠ ሙሉ በሙሉ እንድንንከባከብ፣ እንድንከላከል እና እንድናጠናክር እንደሚጠይቅ እንገነዘባለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአዳኝ ባለን ፍቅር እና እርሱን ለመከተል ባለን ቁርጠኝነት ሥር እንድንሰደድ፣9 መሠረት እንድንሆን እና እንድንቆም10 መክሮናል። ዛሬ እና ወደፊት ያሉት ቀናት፣ ከመንገድ ከመውጣት እና ከግድየለሽነት ለመጠበቅ፣11 የበለጠ ትኩረት እና የተጠናከረ ጥረትን ይጠይቃሉ።

ነገር ግን በዙሪያችን እየጨመረ የመጣውን ዓለማዊ ተጽዕኖ መፍራት አይገባንም። ጌታ የቃል ኪዳኑን ሕዝብ ፈጽሞ አይጥልም። ለጻድቃን የመንፈሳዊ ስጦታዎች እና የመለኮታዊ መመሪያ ማካካሻ ኃይል አለ።12 ሆኖም ይህ የተጨመረው የመንፈሳዊ ሃይል በረከት የዚህ ትውልድ አካል ስለሆንን ብቻ በእኛ ላይ አያርፍም። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ስናጠናክር እና ትእዛዛቱን ስንጠብቅ እርሱን ስናውቅ እና ስንወድ ይመጣል። ኢየሱስ እንደጸለየው፣ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንክ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስ ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ህይወት ነች።”13

ጠንቅቀን እንደምናውቀው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት መኖር እና እውነተኛ ደቀ መዝሙር መሆን ከአንድ ጊዜ ውሳኔ በላይ—ከአንድ ጊዜ ክስተት በላይ ነው። በህይወታችን ወቅቶች ውስጥ የሚያድግ እና የሚሰፋ፣ በእግሩ ስር እስክንበረከክ ድረስ የሚቀጥል፣ የተቀደሰ ቀጣይ ሂደት ነው።

በዓለም ውስጥ ስንዴው በእንክርዳድ መካከል እያደገ ሲሄድ፣ በመጪው ጊዜያት ለአዳኝ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳደግ እና ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

ሶስት ሀሳቦች እነሆ፦

እራሳችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ማድረግ

በመጀመሪያ፣ በኢየሱስ ህይወት፣ በትምህርቶቹ፣ በግርማዊነቱ፣ በኃይሉ፣ እና በኃጢያት ክፍያው ውስጥ የበለጠ ሙሉ በሙሉ ራሳችንን ማጥለቅ እንችላለን። አዳኙ፣ “ባሰባችሁት ነገር ሁሉ ወደ እኔ ተመልከቱ።”ብሏል14 ሐዋርያው ዮሀንስ፣ “እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።” ሲል ያስታውሰናል።15 ፍቅሩን በተሻለ ሁኔታ በተለማመድን መጠን፣ የበለጠ እንወደዋለን እናም በርግጥ፣ በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን በመውደድ እና በመንከባከብ የእርሱን ምሳሌ እንከተላለን። በእያንዳንዱ የጽድቅ እንቅስቃሴ ወደ እርሱ ስንቀርብ፣ የበለጠ በግልጽ እናየዋለን።16 እርሱን በጣም እንወዳለን እንዲሁም በትንንሽ መንገዶቻችን እርሱን ለመምሰል እንሞክራለን።17

ቃልኪዳኖችን ከጌታ ጋር ማድረግ

ቀጥሎም፣ አዳኙን በደንብ ስናውቀው እና ስንወደው፣ ታማኝነታችንን እና መታመንን የበለጠ ለእርሱ ለመስጠት እንፈልጋለን። ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን እንገባለን። በጥምቀት ጊዜ በምንገባቸው ቃል ኪዳኖች እንጀምራለን፣ እናም በየቀኑ ንስሀ ስንገባ፣ ይቅርታ ስንጠይቅ እና በየሳምንቱ ቅዱስ ቁርባንን ለመቀበል በጉጉት ስንጠብቅ እነዚህን እና ሌሎችንም ቃል ኪዳኖች እናረጋግጣለን። “[ሁልጊዜ እሱን ለማስታወስ ትእዛዙንም ለመጠበቅ]” ቃል እንገባለን።18

ዝግጁ ስንሆን፣ የቤተመቅደስን ስርዓቶች እና ቃል ኪዳኖች እንቀበላለን። በጌታ ቤት ውስጥ በተቀደሰው ጸጥታ በሰፈነበት ጊዜያችን ውስጥ የዘለአለም ተጽዕኖ እየተሰማን፣ ከእግዚአብሔር ጋር በደስታ ቃል ኪዳን እንገባለን እንዲሁም እነዚህን ለመጠበቅ ያለንን ውሳኔ እናጠናክራለን።

ቃል ኪዳኖችን መግባት እና መጠበቅ የአዳኙ ፍቅር በልባችን ውስጥ የበለጠ ሰርጎ እንዲገባ ያስችለዋል። በዚህ ወር ሊያሆናውስጥ፣ ፕሬዘደንት ረስልኤም. ኔልሰን እንዳሉት፦ “[የእኛ] ቃል ኪዳን(ዎች) ወደ እርሱ የበለጠ ወደመቅረብ ይመ(ራ)ሩናል። … እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዲህ ያለውን ግንኙነት የፈጠሩትን አይተውም።”19 ፕሬዝዳንት ኔልሰን ደስ በሚል ሁኔታ ዛሬ ጠዋት እንዳሉት፣ “በእያንዳንዱ አዲስ ቤተመቅደስ ቡራኬ ሊያጠነክረን እና የጠላትን ሙከራዎች ሊቃረን ተጨማሪ የእግዚአብሔር ኃይል ወደ ዓለም ይመጣል።”20

ጌታ ለምን ቅዱሳን ቤተመቅደሶችን ወደ እኛ እንዲያቀርብ እና ብዙ ጊዜ በቤቱ መሆን እንድንችል ነቢዩን እንደሚመራው እንረዳለን?

ወደ ቤተመቅደስ ስንገባ፣ የህይወታችንን አላማ እና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ስለቀረቡልን ዘለአለማዊ ስጦታዎች ስንማር፣ ከሚያጨናነቁን የአለም ተጽዕኖዎች ለተወሰነ ጊዜ ነፃ እንወጣለን።

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን መጠበቅ

በመጨረሻም፣ ሦስተኛው ሀሳቤ፦ በዚህ የተቀደሰ ፍለጋ፣ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እናከብራለን፣ እንጠብቃለንም። ፕሬዝዳንት ኤም.ረስል ባላርድ በፊት እና ሽማግሌ ኬቨንደብሊው. ፒርሰን በቅርቡ የፕሬዝዳንት ኔልሰን የትንቢት ማስጠንቀቂያ ተናገሩ እኔም እደግመዋለው፦ “በሚመጡት ቀናት ያለ መንፈስ ቅዱስ መመሪያ፣ ምሪት፣ መጽናኛ እና ቋሚ ከሆነ ተጽዕኖ በመንፈሳዊነት ተቋቁመን ለመቀጠል አይቻልም።”21 ከዋጋ በላይ የሆነ ስጦታ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ተጽዕኖ በእኛ ላይ ይኖር ዘንድ የዕለት ተዕለት ልምዶቻችንን ለመጠበቅ የተቻለንን እናደርጋለን። እኛ ለዓለም ብርሃን ነን፣ አስፈላጊ ሲሆንም በፈቃደኝነት ከሌሎች የተለየን ለመሆን እንመርጣለን። ፕሬዘደንት ዳሊን ኤች ኦክስ በቅርቡ ወጣት ጎልማሶችን እንዲህ ሲሉ ጠይቀዋል፦ “‘የተለያችሁ ለመሆን ትደፍራላችሁ?’ … [በተለይ] በግል ህይወታችሁ ውስጥ የምታደርጓቸው ምርጫዎች አስፈላጊ ናቸው። … የዓለምን ተቃውሞ በመቃወም ወደ ፊት እየሄዳችሁ ናችሁን?”22

ከዓለም የተለያችሁ ለመሆን ምረጡ

በቅርብ ጊዜ በማህበራዊ ድረ ገጽ ባወጣሁት ጽሁፍ ላይ፣ እንደ እኔ ደቀ መዛሙርት የሆኑትን ከአለም የተለዩ እንዲሆኑ ያደረጓቸውን ምርጫዎች እንዲያካፍሉ ጠየኳቸው። በመቶዎች የሚቆጠሩ መልሶች ደርሰውኛል።23 ጥቂቶቹን ብቻ እነሆ፦

አማንዳ፦ እኔ በአካባቢው እስር ቤት ውስጥ የምሰራ ነርስ ነኝ። ክርስቶስ እንዳደረገው እስረኞችን ለመንከባከብ እሞክራለሁ።

ሬቸል፦ እኔ የኦፔራ ዘፋኝ ነኝ፣ እና ምንም አይነት ጨዋነት ሳይለይ የተሰጠኝን ልብስ መልበሴ ብዙ ጊዜ እንደ ቀላል ይቆጠራል። [የቤተመቅደስ መንፈሳዊ ስጦታ ስለተቀበልኩኝ፣] ልብሱ [ልከኛ] መሆን እንዳለበት ለ[አዘጋጆቹ] ነገርኳቸው። ደስተኛ አልነበሩም … ግን ሳይወድዱ ለውጦችን አድርገዋል። በማንኛውም ጊዜ የክርስቶስ ምስክር ሆኖ በመቆም የሚገኘውን ሰላም በምንም አልለውጥም።

ክሪስ፦ እኔ (በማገገም ላይ ያለሁ) የመጠጥ ሱሰኛ፣ ቤተመቅደስ ለመግባት ብቁ የሆንኩ፣ የቤተክርስቲያኗ አባል ነኝ። በሱስ ምክንያት ስላጋጠሙኝ ተሞክሮዎች እና ስለ [ኢየሱስ ክርስቶስ] የኃጢያት ክፍያ ስላለኝ ምስክርነት ዝም አልልም።

ሎረን፦ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከክፍል ጓደኞቼ ጋር ትወና በመጻፍ ላይ ነበር። የእኔ ጸጥ ያለ እና ቁጥብ ባህርይ በድንገት ሃይማኖታዊ ስነምግባር የሌለው እንዲሆን ፈለጉ። እነሱ ይገፋፉኝ ነበር፣ እኔ ግን እምቢ አልኩና ግፊታቸውን ተቋቋምኩኝ።

አዳም፦ ብዙ ሰዎች የንጽህና ህግን እጠብቃለሁ እንዲሁም ከብልግና ምስሎች መራቅን እመርጣለሁ ስላቸው አያምኑኝም። ይህ የደስታ እና የአእምሮ ሰላም ጥቅም እንደሚሰጠኝን አልገባቸውም።

ኤላ፦ አባቴ የኤልጂቢቲኪው ማህበረሰብ አባል ነው። የክርስቶስ ምስክር ሆኜ ስቆም እና ለማምንበት ነገር ታማኝ ስሆን ሁልጊዜ የሌሎች ሰዎችን ስሜት ግምት ውስጥ ለማስገባት እሞክራለሁ።

አንድራዴ፦ ቤተሰቤ እስከመጨረሻው ላለመሄድ ሲወስኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ለመቀጠል ወሰንኩ።

እና መጨረሻ፣ ከሼሪ፦ በገዥው መኖሪያ ቤት አንድ ዝግጅት ላይ ነበርን። “የመልካም ምኞት ጽዋ” ለማንሳት ሻምፓኝ ማደል ጀመሩ። ሰራተኞቹ የሚያናድድ ነገር ነው ቢሉኝም ውሃ ስጡኝ በማለት አጥብቄ ጠየቅኩ። ገዥውን የመልካም ምኞት ጽዋ አነሳንለት፣ እናም የውሃ ብርጭቆዬን ከፍ አድርጌ ያዝኩት! ገዥው አልተናደደም።

ፕሬዘደንት ኔልሰን እንዲህ ብለዋል፣ “አዎ፣ የምትኖሩት በአለም ላይ ነው፣ ነገር ግን የአለምን እድፍ እንድታስወግዱ ከአለም በጣም የተለየ መስፈርት አላችሁ።”24

በዩክሬን የምትኖር አናስታሲያ የተባለች ወጣት እናት ባለፈው የካቲት ወር በኪየቭ የቦምብ ጥቃት ሲጀምር ገና ወንድ ልጅ ወልዳ ሆስፒታል ውስጥ ነበረች። አንዲት ነርስ የሆስፒታሉን ክፍል በር ከፍታ በቸኮለ ድምፅ፣ “ልጅሽን ያዢ በብርድ ልብስ ጠቅልይውና ወደ አዳራሹ ግቢ!” አለቻት።

በኋላ አናስታሲያ ይህን አስተያየት ሰጠች፦

“የመጀመሪያው የእናትነት ዘመኖቼ በጣም ከባድ ይሆናሉ ብዬ አስቤ አላውቅም፣ ነገር ግን ባየኋቸው በረከቶች እና ተአምራት ላይ እያተኮርኩ ነኝ።

“አሁን፣ ብዙ ውድመት እና ጉዳት ያደረሱትን ይቅር ማለት የማይቻል ሊመስል ይችላል ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ይቅር ለማለት እንደምችል እምነት አለኝ።…

“ወደፊት የሚሆነውን ሁሉ አላውቅም፣ ነገር ግን ቃል ኪዳናችንን መጠበቅ መንፈሱ ያለማቋረጥ ከእኛ ጋር እንዲሆን እንደሚያስችለው፣ … በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳን ደስታ እና ተስፋ እንዲሰማን እንደሚያደርግ አውቃለሁ።”25

የዘላለም ሕይወት እና የሰለስትያል ክብር ቃልኪዳን

ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ የውድ አዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር በብዛት ለመቀበል ተባርኬያለው። ህያው እንደሆነ እና ቅዱስ ስራውን እንደሚመራ አውቃለሁ። ለእርሱ ያለኝን ፍቅር መግለፅ የሚችሉ ሙሉ ቃላት የሉኝም።

የጌታችንን እና የመድኃኒታችንን የከበረ ዳግመኛ ምጽአት እየጠበቅን ያለን በቁጥር በሚሊዮን የምንቆጠር በየአህጉሩ፣ በየሀገሩ እና በብዙ ባህሎች ውስጥ በምድር ላይ ተሰራጭተን የምንገኝ “የቃል ኪዳኑ ልጆች” ነን። በዙሪያችን ላሉ ሰዎች እንደ ብርሃን እየበራን፣ ምኞቶቻችንን፣ አስተሳሰቦቻችንን፣ ምርጫዎቻችንን እና ድርጊቶቻችንን ሆን ብለን እንቀርጻቸዋለን። አዳኙን ለማወቅ እና ለመውደድ በሙሉ ልባችን እየፈለግን፣ ከእግዚአብሔር ጋር በገባነው ቃል ኪዳን፣ የተለየ፣ ያልተለመደ እና ልዩ በመሆን እሱን እና ትምህርቶቹን ስናከብር፣ እራሳችንን ከሌሎች በተለየ መንገድ ከሚያምኑት ሳንነጥል፣ ራሳችንን ከአለም እንለያለን።

በእንክርዳዱ መካከል ስንዴ የመሆን፣ አንዳንዴም በልብ ህመም በተሞላበት፣ ነገር ግን ሁልጊዜ በእምነታችን ብስለት እና ማረጋገጫ የምንረጋጋበት ድንቅ ጉዞ ነው። ለአዳኙ ያላችሁ ፍቅር እና ለእናንተ ያለው ፍቅር በልባችሁ ውስጥ ሰርጎ እንዲገባ ስትፈቅዱ፣ የህይወትህን ፈተናዎች ለመጋፈጥ የሚያስችል በራስ መተማመንን፣ ሰላምን እና ደስታን እንደምትጨምሩ ቃል እገባለሁ። እናም አዳኙ እንዲህ ቃል ገባልን፦ “በስንዴዎች እና እንክርዳዶች ምሳሌ መሰረት፣ ስንዴዎች በጎተራው እንዲሰበሰቡ እና የዘለአለም ህይወት ያገኙ ዘንድ፣ እና በሰለስቲያል ክብር አክሊል [በመስጠት]፣ ህዝቤን [እሰበስባለሁ]።”26 በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ማቴዎስ 24፥3

  2. ማቴዎስ 24፥33

  3. ሔንሪ ቢ. አይሪንግ፣ “በአውሎ ንፋስ ውስጥ መረጋጋት፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2022 (እ.አ.አ)፣ 27።

  4. ማቴዎስ 13፥16፤ ትኩረት ተጨምሮ።

  5. ማቴዎስ 13፥38

  6. ማቴዎስ 13፥30

  7. ሽማግሌ ኔል ኤ. ማክስዌል እንዳሉት፦ “የቤተክርስትያን አባላት በዚህ የስንዴ-እና እንክርድድ ሁኔታ እስከ አንድ ሺህ አመት ድረስ ይኖራሉ። አንዳንድ እውነተኛ እንክርዳዶች እንደ ስንዴ ያስመስላሉ” (“Becometh as a Child,” Ensign, May 1996፣ 68)።

  8. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 86፥4፣ 6 ተመልከቱ።

  9. ቆላስያስ 2፥7 ተመልከቱ።

  10. ቆላስይስ 1፥23 ተመልከቱ፤ ደግሞም ኤፌሶን 3፥17፤ ኒል ኤ. ማክስዊል፣ “Grounded, Rooted, Established, and Settled” [Brigham Young University devotional፣ መስከረም 15፣ 1981 (እ.አ.አ)]speeches.byu.edu።

  11. ማቴዎስ 13፥22 ላይ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል “ቃሉን እንዳያንቁት” እና መንፈሳዊ እድገታቸውን እንዲያቆሙ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። “ቃሉን ያንቃል” የሚለውን ሐረግ በዮሐንስ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውስጥ “መጀመሪያ ቃል ነበር ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበር” ከሚለው ቃሉ ኢየሱስ መሆኑን ከተናገረበት ጋር ማያያዝ እወዳለሁ።… ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም”(ዮሀንስ 1፥1፣ 3)። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት፣ እርሱን ለመከተል ያለን ቁርጠኝነት፣ ለአዳኝ ያለን ፍቅር ከመንፈሳዊ ብርሃን እና ምግብ ከተነፈገ ሊታፈን ወይም እንዳያድግ ሊደረግ ይችላል (አልማ 32፥37–41 ይመልከቱ)።

  12. See Neil L. Andersen, “A Compensatory Spiritual Power for the Righteous” (Brigham Young University devotional, Aug. 18, 2015), speeches.byu.edu.

  13. ዮሐንስ 17፥3

  14. ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 6፥36

  15. 1 ዮሐንስ 4፥19

  16. ሽማግሌ ዴቭድ ቢ ሀይት እንዲህ አሉ፦

    “እውነት ነው አንዳንዶች አዳኙን አይተዋል፣ ነገር ግን አንድ ሰው መዝገበ ቃላትን ላይ ማየት የሚለው ቃል ሲመረምር፣ እርሱን ማወቅ፣ እሱን ማስተዋል፣ እርሱን እና ስራውን በእይታ ማወቅን፣ አስፈላጊነቱን በማስተዋል፣ ወይም እርሱን ለመረዳት መምጣትን የመሳሰሉ ሌሎች ብዙ የቃሉ ትርጉሞች እንዳሉ ይማራል።

    እንደዚህ አይነት ሰማያዊ መገለጥ እና በረከቶች ለእያንዳንዳችን ይገኛሉ” (“Temples and Work Therein,” Ensign, Nov. 1990, 61)።

  17. ሞዛያ 5፥13ን ይመልከቱ።

  18. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፥77

  19. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ዘለአለማዊ ቃል ኪዳን፣” ሊያሆና፣ ጥቅምት 2022 (እ.አ.አ)።

  20. ራስል ኤ. ኔልሰን፣ “እውነት ምንድን ነው፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2022 (እ.አ.አ)፣ 29።

  21. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “Revelation for the Church, Revelation for Our Lives፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2018 (እ.አ.አ)፣ 96።

  22. ዳለንኤች. ኦክስ፣ “Going Forward in the Second Century፣” (የብሬገም ያንግ ዩኒቨርስቲ መንፈሳዊ ስብሰባ፣ መስከረም 13፣ 2022 እ.አ.አ)፣ speeches.byu.edu. ፕሬዝዳንት ኦክስ “ልዩ ለመሆን መድፈር” የሚለውን ሃረግ በ ዴዘረት መጽሔት ውስጥ በሽማግሌ ክላርክጂ. ጊልበርት ከተፃፈን ፅሁፍ እንዳገኙት ተናገሩ፣ የቤተክርስቲያን ትምህርት ሲስተም ኮሚሽነር፣ የሐይማኖት ማንነትን በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ መጠበቅ (“ልዩ ለመሆን መድፈር” ዴዘረት መጽሔት፣ ጥቅምት 2022 እ.አ.አ፣ deseret.com)።

  23. ከአለም እንዴት እንደሚለዩ አስተያየት ከሰጡን መማር ከፈለጋችሁ በፌስቡክ ላይ የሰጡትን አስተያየት ማንበብ ትችላላችሁ (ኒልኤል. አንደርሰን፣ ፌስቡክ፣ ሐምሌ 18, 2022 (እ.አ.አ)፣ facebook.com/neill.andersen) ወይም በኢንስታግራም (ኒልኤል. አንደርሰን፣ ኢንስታግራም፣ ሐምሌ 18፣ 2022 (እ.አ.አ)፣ instagram.com/neillandersen).ይመልከቱ)።

  24. ረስልኤም ኔልሰን፣ “Hope of Israel” (ዓለም አቀፋዊ የወጣቶች አምልኮ፣ ሰኔ3፣ 2018 እ.አ.አ)፣ HopeofIsrael.ChurchofJesusChrist.org።

  25. አናሳሲያ ኮቼቫ፣, “Facing the Conflict in Ukraine, Healing the Conflict in My Heart፣” YA Weekly፣ ግንቦት 2022 (እ.አ.አ)።

  26. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 101፥65