መልሱ ኢየሱስ ነው።
ፈተናዎቹ የቱንም ያህል ከባድ ወይም ግራ የሚያጋቡ ቢሆኑ መልሱ ሁልጊዜ ቀላል እንደሆነ ማስታወስ ትችላላችሁ፤ ሁሌም ኢየሱስ ነው።
በዚህ ስብሰባ ለእናንተ ንግግር ማድረግ ምን ያህል ክብር ነው። ዛሬ ጓደኞች እያልኩኝ እጠራችኋለሁ። በዮሃንስ ወንጌል ውስጥ አዳኙ የሚጠይቀንን ነገር የምናደርግ ከሆነ ጓደኞቹ እንደሆንን አስተምሯል።1
እኛን በአንድ ላይ የሚያስተሳስረን ለአዳኙ ያለን የግል እና የጋራ ፍቅር እንዲሁም ከእርሱ ጋር የገባነው ቃል ኪዳን ነው። ፕሬዚዳንት አይሪንግ እንዳስተማሩት፦ “ጌታ ምን ያህል እንደሚወዳችሁ እና እንደሚያምናችሁ ለእናንተ መናገር እፈልጋለሁ። እንዲሁም፣ ከዚህም በላይ ምን ያህል በእናንተ ላይ እንደሚተማመን ልነግራችሁ እፈልጋለሁ።”2
በፕሬዚዳንት ኔልሰን እንደ አጠቃላይ ባለስልጣን ተደርጌ ስጠራ በስሜቶች ተጥለቅልቄ ነበር። ከዓቅም በላይ ነበር። ባለቤቴ ጁሊ እና እኔ የጠቅላላ ጉባኤ የቅዳሜ ከሰአት በኋላ ክፍለ ጊዜን በጉጉት ስንጠብቅ ነበር። ከተሰብሳቢው ድጋፍን ማግኘት ዝቅ እንድል የሚያስገድድ ነበር። ገና በመጀመሪያው ምድቤ እንዳልወድቅ፣ እርምጃዎቼን በጥንቃቄ እየቆጠርኩኝ ተለይቶ ወደተዘጋጀልኝ ቦታ ሄድኩኝ።
በዚያ ክፍለ ጊዜ መደምደሚያ ላይ በእኔ ላይ ታላቅ ተጽዕኖ ያሳደረ አንድ ነገር ሆነ። የሸንጎው አባላት በሰልፍ ሆነው ለአዲሶቹ አጠቃላይ ባለስልጣናት አንድ በአንድ ሰላምታ አቀረቡ። እያንዳንዱም ፍቅራቸውን እና ድጋፋቸውን ገለጹ። ከልባቸው በማቀፍ፣ “አይዟችሁ፣ የዚህ አካል ናችሁ” አሉ።
ከአዳኙ ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ እርሱ ልባችንን ይመለከታል፤ “ለሰዎችም አያዳላም።”3 ሃዋርያቱን እንዴት እንደመረጠ አስቡ። ለኑሮ ደረጃ ወይም ለሃብት ትኩረት አልሰጠም፡፡ እንድንከተለው ይጋብዘናል፤ የእርሱ አካል መሆናችንን እንደሚያረጋግጥልንም አምናለሁ።
ይህ መልዕክት በተለይ ለቤተክርስቲያኗ ወጣቶች ይሆናል። ፕሬዚዳንት ኔልሰን በእናንተ ውስጥ የተመለከቱን እኔም እመለከታለሁ። እንዲህ ብለዋል፣ “ይህ ወጣት ትውልድ የማይካድ ልዩ ነገር አለው። የሰማይ አባታችሁ እናንተን በዚህ ጊዜ ወደ ምድር መላኩ በእናንተ ላይ በጣም እንደሚተማመን ያሳያል። ታላቅ እንድትሆኑ ነው የተወለዳችሁት!”4
ከወጣቶች ስለምማረው ነገር አመስጋኝ ነኝ። ልጆቼ ስለሚያስተምሩኝ ነገር፣ ሚስዮናውያን ስለሚያስተምሩኝ ነገር እንዲሁም የእህቴ እና የወንድሜ ልጆች ስለሚያስተምሩኝ ነገር አመስጋኝ ነኝ።
ብዙም አልቆየም፤ ከወንድሜ ልጅ ከናሽ ጋር በእርሻ ቦታችን ላይ እየሰራሁኝ ነበር፡፡ ስድስት ዓመቱ ሲሆን ልቡም ንጹህ ነው፡፡ ከሁሉም አስበልጬ የምወደው የወንድሜ ልጅ ነው፣ ስሙም ናሽ ይባላል እንዲሁም ዛሬ በኮንፈረንስ ውስጥ እናገራለሁ ከሁሉም አስበልጦ የሚወደኝ አጎቱ እንደሆንኩ አምናለሁ።
ለፕሮጀክታችን መፍትሄ እንዳገኝ ሲረዳኝ እንዲሀ አልኩት፣ “ናሽ ያ ጥሩ ሃሳብ ነው“። እንዴት እንዲህ ብልህ ልትሆን ቻልክ?” “አጎቴ ራያን የዚህን ጥያቄ መልስ እንዴት አታውቅም? በሚል የዓይን አገላለጽ አየኝ።
በቀላሉ፣ ትከሻውን ሰበቀ፣ ፈገግ አለና በልበ ሙሉነት “ኢየሱስ” አለ።
የዚያን ቀን፣ ናሽ ያንን ቀላል ነገር ግን ጥልቅ የሆነ ትምህርት አስታወሰኝ። በጣም ቀላል የሆኑ ጥያቄዎችም ሆኑ በጣም ውስብስብ የሆኑ ጥያቄዎች መልሳቸው ሁል ጊዜ አንድ ነው። መልሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እያንዳንዱ መፍትሄ በእርሱ ዘንድ ይገኛል።
በዮሃንስ ወንጌል ውስጥ አዳኙ ለደቀ መዛሙርቱ ቦታ እንደሚያዘጋጅላቸው ነግሯቸዋል። ቶማስ ግራ ተጋብቶ ነበር እናም አዳኙን እንዲህ አለው፦
“ጌታ ሆይ ወደምትሄድበት አናውቅም እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን?
“ኢየሱስም እንዲህ አለው፣ እኔ መንገድና፣ እውነት ህይወትም ነኝ፦ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።”5
አዳኙ “መንገድ፣ እውነት፣ እና ህይወት” እንደሆነ ለደቀ መዛሙርቱ አስተማራቸው። እርሱ እንዴት ወደ አብ መምጣት ይቻላል ለሚለው ጥያቄ መልስ ነው። እርሱ በህይወታችን ውስጥ ስላለው መለኮታዊ ሚና ምስክርነት ማግኘትን በወጣትነቴ የተማርኩት ነገር ነበር።
በአርጀንቲና ውስጥ ሚስዮናዊ በመሆን እያገለገልኩኝ በነበረበት ጊዜ፣ ፕሬዚዳንት ሃዋርድ ደብሊው.ኸንተር በህይወቴ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ያለው ነገር እንድናደርግ ጋብዘውን ነበር። እንዲህ አሉ፦ “ኢየሱስን ከምናውቀው የበለጠ ልናውቀው ይገባል፤ ከምናስታውሰው የበለጠ በተደጋጋሚ ልናስታውሰው ይገባል፤ ከምናገለግለው የበለጠ በጀግንነት ልናገለግለው ይገባል።”6
በዚያን ጊዜ፣ እንዴት የተሻልኩኝ ሚስዮናዊ መሆን እንደምችል ያሳስበኝ ነበር። መልሱ ይህ ነበር፦ ክርስቶስን ማወቅ፣ እርሱን ማስታወስ እና እርሱን ማገልገል። በአለም ዙሪያ ያሉ ሚስዮናውያን በዚህ አላማ አንድ ናቸው፦ “ሌሎች በእርሱ እና በሀጢያት ክፍያው በማመን፣ ንስሀ በመግባት፣ በመጠመቅ፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን በመቀበል እና እስከመጨረሻው በመጽናት የተመለሰውን ወንጌል እንዲቀበሉ በመርዳት ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ መጋበዝ ነው።”7 ሚስዮናውያንን እያዳመጡ ላሉ ጓደኞቻችንን ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ ግብዣዬን አክላለሁ፡፡ እርሱን ለማወቅ፣ እርሱን ለማስታወስ እና እርሱን ለማገልገል በአንድነት እንጥራለን።
ሚስዮናዊ አገልግሎት የሰጠሁበት ጊዜ የህይወቴ የተቀደሰ ጊዜ ነበር። የሙሉ ጊዜ ሚስዮናዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ በነበርኩበት ጊዜ ከእርሳቸው ጋር ባደረግሁት የመጨረሻ ውይይት ፕሬዚዳንት ብሌር ፒንኮክ፣ እሳቸው እና ባለቤታቸው አገልግሎታቸውን ወደ ማጠናቀቅ እንደደረሱና በሚስዮን መሪዎች ላይ ስለሚደረጉት ለውጦች ተናግረዋል። ሁለታችንም በጣም የምንወደውን ነገር ትተን ልንሄድ በመሆናችን አዝነናል። በቃ ከእንህዲህ የሙሉ ጊዜ ሚስዮናዊ አልሆንም የሚለውን ሃሳብ በማሰብ እንደተጨነኩኝ ማየት ችለው ነበር። ታላቅ እምነት የነበራቸው ሰው ነበሩ እንዲሁም ላለፉት ሁለት አመታት ሲያደርጉት እንደነበረው በፍቅር አስተማሩኝ። ከጠረጴዛው በላይ ወደተሰቀለው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስል እየጠቆሙ፣ “ሁሉም መልካም ይሆናል ምክንያቱም የእርሱ ስራ ነው።” አሉኝ። በምናገለግልበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከፈቀድንለት አዳኙ ሁልጊዜም እንደሚረዳን በማወቄ ተረጋጋሁ።
እህት ፒንኮክ የስፓንኛ ሀረጎችን ከልቧ አስተምራናለች። “ሄሱክሪስቶ ቢቤ፣” ስትለን እንዳለ እና እውነት እንደሆነ አውቃለሁ። “ኤልደሬስ ኢ ሄርማናስ ሌስ አሞ፣” ስትል እንደምትወደን እና አዳኙን እንድንከተል እንደምትፈልግ አውቃለሁ።
በቅርቡ ባለቤቴ እና እኔ የሚስዮን መሪዎች በመሆን በማገልገል በኡራጓይ ካሉ ድንቅ ሚስዮናውያን ጋር አብረን በመስራት ተባርከናል። እነዚህ የዓለማችን ምርጥ ሚስዮናውያን ነበሩ እላለሁ፤ እያንዳንዱ የሚስዮን መሪ እንደዚያ እንደሚሰማውም አምናለሁ። እነዚህ ደቀ መዛሙርት አዳኙን ስለመከተል በየቀኑ አስተምረውናል።
በአንድ መደበኛ የውይይት ወቅት ጎበዝ ከተባሉት ሚስዮናውያን አንዷ ወደ ቢሮው ገባች። ውጤታማ ሚስዮናዊ፣ ምርጥ አሰልጣኝ እና ቁርጠኛ መሪ ነበረች። በጓደኞቿ ዘንድ እንደ መረጃ ምንጭ ትታያለች በሰዎችም ዘንድ ተወዳጅ ነበረች። ታዛዥ፣ ትሁት እና ልበ ሙሉ ነበረች። የቀድሞዎቹ ጉብኝቶች ትኩረታቸውን ያደረጉት በአካባቢዋ እና በምታስተምራቸው ሰዎች ላይ ነበር። ይህ ጉብኝት የተለየ ነበር። ሰላምታ በሰጠኋት ጊዜ የሆነ ችግር እንደገጠማት መናገር ችዬ ነበር። እንዲህ አለች “ፕሬዚዳንት ኦልሰን ይህን ማድረግ እችል እንደሆነ አላውቅም። መቼም ቢሆን ለዚህ ብቁ እንደምሆን አላውቅም። ጌታ እንድሆን የሚፈልገውን ዓይነት ሚስዮናዊ መሆን ስለመቻሌ እርግጠኛ አይደለሁም።”
አስደናቂ ሚስዮናዊ ነበረች። በሁሉም መንገድ ምርጥ ነበረች። አንድ የሚስዮን ፕሬዚዳንት የሚያልማት ዓይነት ነበረች። እንደሚስዮናዊ ባላት ችሎታ ምንም አልተጨነቅኩም ነበር።
ባዳመጥኳት ጊዜ ምን ልላት እንደምችል ተቸገርኩኝ። በዝምታ እንዲህ ጸለይኩኝ፦ “ሰማያዊ አባት ሆይ ይህች ድንቅ ሚስዮናዊ ናት። የአንተ ናት። ሁሉንም ነገር በትክክል እያደረገች ነው። ይህንን ማበላሸት አልፈልግም። አባክህ፣ ምን እንደምላት ማወቅ እንድችል አርዳኝ።
ቃላቶቹ ወደ እኔ መጡ። እንዲህ አልኩኝ “ሄርማና፣ እንዲህ ስለተሰማሽ በጣም አዝናለሁ። አንድ ጥያቄ ልጠይቅሽ። እንዲህ የሚሰማት የምታስተምሪያት ጓደኛ ቢኖርሽ ምን ትያታለሽ?
አየችኝና ፈገግ አለች። በማያሻማ የሚስዮናዊ መንፈስ እና ጠንካራ እምነት እንዲህ አለች “ፕሬዚዳንት፣ ያ ቀላል ነው። አዳኙ በደንብ እንደሚያውቃት እነግራታለሁ። እርሱ ህያው እንደሆነ እነግራታለሁ። ይወድሻል። ብቁ ነሽ እንዲሁም ገብቶሻል!”
ትንሽ ሳቅ ብላ እንዲህ አለች፣ ”ይህ ለጓደኞቻችን የሚሰራ ከሆነ፣ ለእኔም ይሰራል ብዬ እገምታለሁ።”
ጥያቄዎች ወይም ጥርጣሬዎች በሚኖሩን ጊዜ መፍትሄዎቹ በጣም ውስብስብ እንደሆኑ ወይም መልስ ማግኘት በጣም ግራ የሚያጋባ እንደሆነ ሊሰማን ይችላል። የሃሰትም ሁሉ አባት የሆነው ጠላት የመደናገር መሐንዲስ መሆኑን እናስታውስ።8
አዳኙ ነገሮችን የማያወሳስብ ጌታ ነው።
ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፦
“ጠላት ብልህ ነው። ለሺህ አመታት፣ እርሱ መልካምን ክፉ እና ክፉውን መልካም እያስመሰለ ነው። መልእክቱም የጎላ፣ ደፋር እና ኩራተኛ ነው።
“ነገር ግን፣ ከሰማይ አባታችን የሚመጣው መልእክት በጣም የተለየ ነው። እርሱ የሚያነጋግረው በቀላል፣ በጸጥተኛ፣ እና በሚያስደንቅ ግልፅነት ግራ ለመጋባት በማንችልበት መንገድ ነው።”9
እግዚአብሄር ስለወደደንና ልጁን ስለላከ ምንኛ አመስጋኞች ነን። እርሱ መልስ ነው።
ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን በቅርቡ እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፦
“የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የዛሬን ያህል አስፈላጊ ሆኖ አያውቅም።…
“… ይህ ጌታ ለደቀመዛሙርቱ የሰጣቸውን ‘ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ’ የሚለውን መመሪያ የመከተልን አጣዳፊ አስፈላጊነት አጉልቶ ያሳያል።”10
ለማገልገል ለሚመርጡ፣ የነቢይን ጥሪ ሲሰሙ፣ የሚመጡትን በረከቶች ማረጋገጥ እችላለሁ። የማገልገል ጉዳይ ስለአናንተ ሳይሆን ስለአዳኙ ነው። በአንድ ቦታ እንድታገለግሉ ትጠራላችሁ፣ በይበልጥ ግን ወደ ሰዎች ትጠራላችሁ። አዳዲስ ጓደኞች መልሱ ኢየሱስ መሆኑን እንዲያውቁ የመርዳት ትልቅ ሃላፊነት እና በረከት ይኖራችኋል።
ይህች የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ናት እኛም የእርስዋ አካል ነን። ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንድናደርግ በፍቅር የሚያበረታቱን ነገሮች ሁሉ ወደ አዳኝ ወደመቅረብ ይመሩናል።
ለአስደናቂ ወጣቶቻችን —የወንድሜን ልጅ ናሽን ጨምሮ— በህይወታችሁ ሁሉ፣ ፈተናዎቹ የቱንም ያህል ከባድ ወይም ግራ የሚያጋቡ ቢሆኑ መልሱ ሁልጊዜ ቀላል እንደሆነ ማስታወስ ትችላላችሁ፤ ሁሌም ኢየሱስ ነው።
ነቢያት፣ ገላጮች እና ባለራዕዮች አድርገን የደገፍናቸው ብዙ ጊዜያት ሲናገሩ እንደሰማሁት እኔም እንወዳችኋለን፣ እናመሰግናችኋለን፣ እንዲሁም እንፈልጋችኋለን እላለሁ። የእናንተ ቦታ ይህ ነው።
አዳኙን እወደዋለሁ። ስለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ምስክርነቴን እሰጣለሁ። አዳኙ “የእምነታችንንም ራስ እና ፈጻሚ”11 እንዲሁም ነገሮችን የማያወሳስብ ጌታ መሆኑን እመሰክራለሁ። መልሱ ኢየሱስ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።