ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፩


የኔፊ ሁለተኛ መጽሐፍ

የሌሂ የአሟሟት ታሪክ። የኔፊ ወንድሞች በእርሱ ላይ አመጹ። ጌታ ኔፊን ወደ ምድረበዳ እንዲሄድ አስጠነቀቀው። በምድረበዳ የነበረው ጉዞና የሌሎች ነገሮች መዝገብ።

ምዕራፍ ፩

ሌሂ ስለነፃነቷ ምድር ተነበየ—የእስራኤልን ቅዱስ የሚቃወሙ ከሆነ ዘሮቹ ይበተናሉ እናም ይጠፋሉ—ወንዶች ልጆቹን የፅድቅን የጦር ዕቃ እንዲለብሱ አበረታታቸው። ከ፭፻፹፰–፭፻፸ ም.ዓ. ገደማ።

እና እንዲህ ሆነ እኔ፣ ኔፊ፣ ወንድሞቼን ማስተማሬን ከጨረስኩ በኋላ አባታችን ሌሂም ደግሞ፣ ብዙ ነገሮችን ተናገራቸው፣ እናም ጌታ እነርሱን ከኢየሩሳሌም ምድር በማውጣት ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገላቸው አስታወሳቸው።

እናም በባህር ላይ በነበሩ ጊዜ ስለነበራቸው አመፅና፣ ደግሞ በባህር ውስጥ እንዳይሰጥሙ በማድረግ እግዚአብሔር ስላሳየው ምህረት ነገራቸው።

እናም ደግሞ ስላገኙት የቃል ኪዳን ምድር በተመለከተ፣ ጌታ እኛን ከኢየሩሳሌም እንድንወጣ በማስጠንቀቅ እንዴት መሀሪ እንደነበር ነገራቸው።

እነሆም፣ አለ እርሱ፥ ራዕይን አይቻለሁ፣ በእርሱም ኢየሩሳሌም እንደጠፋችም አውቃለሁ፤ እኛም በኢየሩሳሌም ቀርተን ቢሆን ኖሮ እኛም ደግሞ እንጠፋ ነበር።

ነገር ግን፣ መከራችንን በሙሉ በመቋቋም ከምድር ሁሉ የተመረጠችውን የቃል ኪዳን ምድር፣ ጌታ አምላክ ለእኔ ለዘሮቼ ርስት እንድትሆን ቃል የገባልኝን ምድር አግኝተናል አለ። አዎን፣ ጌታ ይህንን ምድር ለእኔና ለልጆቼ እናም ደግሞ ከሌሎች ምድር በጌታ እጅ ተመርተው ለሚወጡት በሙሉ ለዘለዓለም ቃል ኪዳን ገብቷል።

ስለዚህ፣ እኔ፣ ሌሂ፣ በውስጤ ባለው የመንፈስ ሥራ መሠረት፣ በጌታ እጅ ተመርተው ካልሆነ በቀር ወደ እዚህች ምድር ማንም እንደማይመጣ እተነበያልሁ።

ስለዚህ ይህች ምድር እርሱ ለሚያመጣው ተቀድሳለች። እናም በሰጣቸው ትዕዛዛት መሰረት እርሱን የሚያገለግሉት ከሆነ ለእነርሱ የነፃነት ምድር ትሆናለች፤ ስለዚህ፣ መቼም ቢሆን በምርኮ አይያዙም፤ ከተያዙ ግን በኃጢያት ምክንያት ነው፤ ነገር ግን ኃጢያት ከተስፋፋ ምድሪቷ በእነርሱ የተነሳ የተረገመች ትሆናለች፣ ነገር ግን ለፃድቃን ለዘለዓለም የተባረከች ትሆናለች።

እናም እነሆ፣ ይህች ምድር በሌሎች ሀገሮች ሳትታወቅ ትቆይ ዘንድ ይህ ጥበብ ነው፤ እነሆም፣ ብዙ ሀገሮችም ምድሪቷን ይሞሏታል፣ ለውርስ የሚሆን ቦታ እንኳን አይኖርም።

ስለዚህ፣ እኔ፣ ሌሂ፣ ጌታ አምላክ ከኢየሩሳሌም የሚያወጣቸው በሙሉ ትዕዛዛቱን እስከጠበቁ ድረስ፣ በዚች ምድር ላይ እንደሚበለፅጉ ቃል ኪዳንን ተቀበልኩ፤ እናም ከሌሎች ሀገሮች ይጠበቃሉ፣ ይህችንም ምድር በራሳቸው ይይዟታል። የእርሱን ትዕዛዛት የሚጠብቁ ከሆኑም በዚች ምድር ላይ የተባረኩ ይሆናሉ፣ የሚያስቸግራቸው ወይም የርስት ምድራቸውን የሚወስድባቸውም ማንም አይኖርም፤ እናም ለዘለዓለም በደህንነት ይኖራሉ።

ነገር ግን እነሆ፣ ታላላቅ በረከቶችን ከጌታ እጅ ከተቀበሉ በኋላ ባለማመን የሚመነምኑበት ጊዜ ሲመጣ—የምድርንና የሁሉን ሰዎች አፈጣጠር እያወቁ፣ ከምድር መፈጠር ጀምሮ የጌታን ታላቅና ድንቅ ስራዎች እያወቁ፣ ሁሉን ነገር በእምነት ለማድረግ ኃይል ከተሰጣቸው በኋላ፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሁሉንም ትዕዛዛት ኖሯቸው፣ እናም በእርሱ በማያልቅ ደግነት ወደዚህች የተከበረች የቃል ኪዳን ምድር ከመጡ በኋላ—እነሆ፣ እኔ እላለሁ፣ እነርሱ የእስራኤሉን ቅዱስ፣ እውነተኛውን መሲህ፣ ቤዛቸውንና አምላካቸውን የሚክዱበት ቀን ከመጣ፣ እነሆ፣ ትክክለኛ የሆነው የእርሱ ፍርድ በላያቸው ላይ ይመጣባቸዋል።

፲፩ አዎን፣ ሌሎች ሀገሮችን በእነርሱ ላይ ያመጣባቸዋል፣ ለእነርሱም ኃይልን ይሰጣቸዋል፣ እናም የርስት ምድራቸውንም ይወሰድባቸዋል፣ እንዲሁም እንዲበተኑና እንዲጠፉ ያደርጋል።

፲፪ አዎን፣ አንዱ ትውልድ ወደሌላው ሲተላለፍ ደም መፍሰስ ይኖራል፣ እናም በእነርሱ መካከል ታላቅ ቅጣት ይሆናል፤ ስለዚህ፣ ልጆቼ ሆይ፣ እንድታስታውሱ እፈልጋለሁ፤ አዎን፣ ቃላቶቼን እንድታዳምጡ እፈልጋለሁ።

፲፫ አቤቱ እናንት እንድትነቁ፤ ከከባድ እንቅልፍ እንድትነቁ፣ አዎን፣ ከሲኦል እንቅልፍ እንኳን እንድትነቁ፣ እናም የታሰራችሁበትን የሰው ልጆችን ወደዘለአለማዊ የጉስቁልና የሀዘን ጥልቅ በምርኮ የሚወስደውን ሰንሰለት አውልቁ።

፲፬ ንቁ! ከትቢያም ላይ ተነሱ፣ እናም ማንም ተጓዥ ሊመለስበት ወደ ማይችለው ወደ ቀዝቃዛውና ወደ ዝምተኛው መቃብር በቅርቡ ሊሄዱ ያሉትን የሚንቀጠቀጡትን የወላጃችሁን ቃላት አድምጡ፤ እኔም በተወሰኑ ቀናት ውስጥ ምድር ሁሉ ወደሚሄዱበት እሄዳለሁ።

፲፭ ነገር ግን እነሆ፣ ጌታ ነፍሴን ከሲኦል አድኗታል፤ እኔ የእርሱን ክብር አይቻለሁ፣ እናም እኔ በእርሱ በዘለዓለማዊው ፍቅር ክንዶች ተከብቤአለሁ።

፲፮ እናም የጌታን ስርዓቶችና ፍርዶች መጠበቅን ታስታውሱ ዘንድ እፈልጋለሁ፤ እነሆ፣ ይህ ከመጀመሪያው ጀምሮ ነፍሴን የሚያስጨንቅ ነው።

፲፯ ልቤ ከጊዜ ወደጊዜ በኃዘን ተጨንቋል፣ ምክንያቱም በልባችሁ ጠጣርነት የተነሳ ትለዩና ለዘለዓለም ትጠፉ ዘንድ ጌታ አምላካችሁ በሙሉ ቁጣው እንዳይመጣ እኔ ፈርቻለሁ፤

፲፰ ወይም፣ ለብዙ ትውልድ እርግማን በላያችሁ ላይ ይመጣባችኋል፣ እናም በሰይፉና በርሃብ ትጎበኛላችሁ፣ እንዲሁም ትጠላላችሁ፣ እናም እንደዲያብሎስ ፈቃድ በምርኮ ትመራላችሁ ብዬ ፈርቼ ነበርና።

፲፱ አቤቱ፣ ልጆቼ ሆይ፣ እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ እንዳይመጡባችሁ፣ ነገር ግን እናንተ በጌታ የተመረጣችሁና የተወደዳችሁ ህዝቦች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። ነገር ግን እነሆ፣ የእርሱ ፈቃድ ይሁን፤ የእርሱ መንገዶች ለዘለዓለም ፅድቅ ናቸውና።

እናም እርሱ እንዲህ አለ፥ ትዕዛዛቴን እስከጠበቃችሁ ድረስ በምድሪቱ ትበለፅጋላችሁ፤ ነገር ግን ትዕዛዛቴን ባልጠበቃችሁ ጊዜ ሁሉ ከእኔ ዘንድ ትለያላቸሁ።

፳፩ እናም አሁን ነፍሴ በእናንተ ደስ እንዲላትና፣ ልቤ ይህንን ዓለም በእናንተ ምክንያት በደስታ እንድትለይ፣ እኔ በሀዘንና በመከራ ወደ መቃብር እንዳልሄድ፣ ልጆቼ ሆይ ከትቢያ ላይ ተነሱና፣ ሰዎች ሁኑ፣ እናም በምርኮ እንዳትያዙ በአንድ ሀሳብና በአንድ ልብ ሁኑ፣ በሁሉ ነገሮች ተስማሙ፤

፳፪ በከባድ እርግማን እንዳትረገሙ፤ እንደዚሁም ደግሞ የትክክለኛውን አምላክ ቁጣ እስከሚያጠፋችሁ ድረስ፣ አዎን፣ ዘለዓለማዊ የስጋም የነፍስም ጥፋት በላያችሁ ላይ እንዳታመጡ።

፳፫ ንቁ፣ ልጆቼ፣ የፅድቅን የጦር ዕቃ ልበሱ። የታሰራችሁበትን ሰንሰለት አውልቁ፣ ከጨለማም ውጡ፣ ከትቢያም ተነሱ።

፳፬ ራዕዮቹ ታላቅ በነበሩትና ከኢየሩሳሌም ከወጣን ጀምሮ ትዕዛዛቱን በጠበቀው፤ እናም ደግሞ እኛን ወደ ቃል ኪዳን ምድር በማምጣት በእግዚአብሔር እጅ መሳሪያ በሆነው፣ በወንድማችሁ ላይ አታምፁ፤ በእርሱ ባይሆን ኖሮ፣ ሁላችንም በምድረበዳው በረሃብ ባለቅን ነበርና፤ ይሁን እንጂ፣ እናንተ ልትገድሉት ሞክራችኋል፤ አዎን፣ እናም እርሱ በእናንተ የተነሳ ብዙ መከራን ተቀብሏል።

፳፭ እናም እኔ እርሱ በእናንተ የተነሳ ድጋሚ ይሰቃያል ብዬ በእጅጉ እፈራለሁ፤ እነሆም እናንተ እርሱ በእናንተ ላይ ስልጣንና ኃይልን ይፈልጋል ብላችሁ ወቅሳችሁታል፤ ነገር ግን እርሱ ኃይልንና ስልጣንን በእናንተ ላይ እንዳልፈለገ አውቃለሁ፣ ነገር ግን እርሱ የእግዚአብሔርን ክብርና የእናንተን ዘለዓለማዊ ደህንነት ይፈልጋል።

፳፮ እናም እናንተ እርሱ ለእናንተ ግልፅ በመሆኑ አጉረምርማችኋል። እናንተ እርሱ ቁርጥ ቃል ተናግሯል ብላችኋል፤ ተቆጥቶናል ብላችኋል፤ ነገር ግን እነሆ፣ የእርሱ ኃይለኝነት በእርሱ ውስጥ በነበረው በእግዚአብሔር ቃል ኃይል ነው፣ እናም እናንተ ቁጣ የምትሉትም ሊያቆመው የማይችለው በእግዚአብሔር ውስጥ ባለው መሰረት የእናንተን ኃጢአቶች በግልፅ የሚገልጸው እውነት ነው።

፳፯ እናም እናንተም ያዘዛችሁን መቀበል እስኪኖርባችሁ ድረስ የእግዚአብሔር ኃይል በእርሱ ውስጥ መሆን አለበት። ነገር ግን እነሆ፣ መዝጋት እስኪያቅተው አፉን በመክፈት ያናገረው እርሱ ሳይሆን በውስጡ የነበረው የጌታ መንፈስ ነው።

፳፰ እናም አሁን ልጆቼ፣ ላማንና፣ ደግሞም ልሙኤልና ሳም፣ እናም ደግሞ የእስማኤል ልጆች የሆናችሁ ልጆቼ፣ እነሆ፣ የኔፊን ድምፅ የምትሰሙ ከሆነ አትጠፉም። እናም እርሱን የምታደምጡ ከሆነ በረከቴን እተውላችኋለሁ፣ አዎን የመጀመሪያውን በረከቴንም እንኳን ቢሆን።

፳፱ ነገር ግን እርሱን የማታደምጡ ከሆነ የመጀመሪያውን በረከቴን እወስድባችኋለሁ፣ አዎን፣ እንዲሁም የእኔን በረከት፣ እናም በእርሱ ላይ ያርፋል።

እናም አሁን ዞራም፣ ለአንተ እናገራለሁ—እነሆ፣ አንተ የላባን አገልጋይ ነህ፤ ይሁን እንጂ፣ አንተ ከኢየሩሳሌም ምድር ወጥተሀል፣ እናም አንተ ለልጄ ለኔፊ እውነተኛና የዘለዓለም ጓደኛው እንደሆንክ አውቃለሁ።

፴፩ ስለሆነም አንተ ታማኝ በመሆንህ ዘርህ ከእርሱ ዘር ጋር የተባረከ ይሆናል፣ በዚህች ምድር ላይ ለብዙ ጊዜ በብልፅግና ይኖራሉ፤ እናም ከክፋት በስተቀር በዚህች ምድር ላይ ለዘለዓለም ብልፅግናቸውን የሚጎዳቸው ወይም የሚረብሻቸው ምንም አይኖርም።

፴፪ ስለሆነም፣ እናንተ የጌታን ትዕዛዛት የምትጠብቁ ከሆነ፣ ጌታ ይህችን ምድር ለዘርህ ደህንነት ከልጄ ዘር ጋር ይቀድሳል።