ቅዱሳት መጻህፍት
፬ ኔፊ ፩


አራተኛው ኔፊ

የኔፊ መፅሐፍ
ከኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት አንዱ የነበረው የኔፊ ልጅ

በእርሱ መዛግብት መሰረት የነበረው የኔፊ ህዝብ ታሪክ።

ምዕራፍ ፩

ኔፋውያን እንዲሁም ላማናውያን ሁሉ ወደ ጌታ ተለወጡ—ሁሉም ነገሮች በጋራ ነበሯቸው፣ ተአምራትን ሰሩ፣ በምድሪቱም ላይ በለፀጉ—ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ፣ መከፋፈል፣ ክፋት፣ ሀሰተኛ ቤተክርስቲያኖች፣ እናም ስደት ተነሳ—ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ፣ ኔፋውያን እንዲሁም ላማናውያን ኃጢአተኞች ሆኑ—አማሮንም ቅዱሳን መጻሕፍቶችን ደበቃቸው። ከ፴፭–፫፻፳፩ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ ሠላሳ አራተኛው ዓመትና፣ ደግሞ ሠላሳ አምስተኛው ዓመት አለፈ፣ እናም እነሆ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት በምድሪቱ ዙሪያ በሁሉም ስፍራ የክርስቶስን ቤተክርስቲያን መሰረቱ። እናም ወደ እነርሱ የመጡት፣ ለኃጢአታቸውም ከልባቸው ንሰሃ የገቡት ሰዎች ሁሉ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፣ እናም ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።

እናም እንዲህ ሆነ በምድሪቱ ገፅ የነበሩት ላማናውያንም ሆኑ ኔፋውያን በሙሉ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት ወደ ጌታ ተለወጡና፣ በመካከላቸው ፀብም ሆነ ጥላቻ አልነበረም፣ እናም እያንዳንዱ ሰው እርስ በርሱ በቅን ይሰራ ነበር።

እናም ሁሉም ነገሮች በጋራ ነበሩአቸው፣ ስለዚህ ድሃና ሃብታም፣ ግዞተኛና ነፃ አልነበረም፣ ነገር ግን ሁሉም ነፃና፣ ሰማያዊውን ስጦታ ተቀባይ ነበሩ።

እናም እንዲህ ሆነ ሠላሳ ሠባተኛውም ዓመት ደግሞ አለፈ፣ እናም በምድሪቱ ሠላም ሰፈነ።

እናም በኢየሱስ ደቀመዛሙርት አማካኝነት ታላቅና ድንቅ ሥራዎች ይሰሩ ነበር፣ ስለዚህ ህመምተኞችን ይፈውሱ፣ እናም ሙታኖችን ያስነሱና፣ ሽባውን እንዲራመድ ያደርጉ፣ እናም ዐይነ ስውር ብርሃን እንዲያገኝና፣ ደንቆሮ እንዲሰማ ያደርጉ ነበር፤ እናም ሁሉንም አይነት ታዕምራቶችን በሰው ልጆች መካከል ያከናውኑ ነበር፤ እናም በክርስቶስ ስም ካልሆነ በቀር በማንም ታምራቶችን አልሰሩም።

እና በዚህ ሠላሳ ስምንተኛው ዓመት አለፈና፣ ደግሞ ሠላሳ ዘጠነኛው፣ እናም አርባ አንደኛውና፣ አርባ ሁለተኛው ዓመት አለፈ፣ አዎን፣ አርባ ዘጠነኛው ዓመት እስከሚያልፍ ድረስና፣ ደግሞ ሃምሳ አንደኛውና፣ ሃምሳ ሁለተኛው፤ አዎን፣ እናም ሃምሳ ዘጠነኛው ዓመትም እስከሚያልፍ ድረስ እንዲህ ሆነ።

እናም ጌታ በምድሪቱ ላይ እጅግ እንዲበለፅጉ አደረጋቸው፤ አዎን፣ በዚህም የተነሳ ከተሞች በተቃጠሉበት ሥፍራ ከተሞችን በድጋሚ አቋቋሙ።

አዎን፣ ያቺን ታላቋን የዛራሔምላ ከተማንም በድጋሚ እንድትገነባ አደረጉ።

ነገር ግን የሰጠሙ ብዙ ከተሞች ነበሩ፣ እናም በቦታውም ውሃ ይፈልቅ ነበር፤ ስለዚህ እነዚህ ከተሞች ሊታደሱ አልተቻላቸውም።

እናም አሁን፣ እነሆ፣ እንዲህ ሆነ የኔፊ ህዝቦች ተጠናከሩ፣ እናም በጣም በፍጥነት ተባዙና፣ እጅግ መልካም እንዲሁም ያማሩ ህዝቦች ሆኑ።

፲፩ እናም ተጋቡና፣ ለጋብቻም ተሰጡ፣ እናም ጌታ በብዙ በገባላቸው ቃል ኪዳኖች ተባረኩ።

፲፪ እናም ከእንግዲህ በሙሴ ህግ ስራዎችና ሥርዓት መሠረት አልተራመዱም፣ ሥርዓቶቹንም አይከተሉም ነበር፤ ነገር ግን ከጌታቸውና ከአምላካቸው በተቀበሉአቸው ትዕዛዛት፣ ያለማቋረጥ በፆማቸውና፣ በፀሎታቸው፣ እንዲሁም በየወቅቱ ለመፀለይና የጌታን ቃል ለመስማት በመሰብሰብ ይራመዱ ነበር።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ በምድሪቱ ህዝቦች መካከል ሁሉ ምንም ፀብ አልነበረም፤ ነገር ግን በኢየሱስ ደቀመዛሙርት መካከል ኃያል የሆኑ ተአምራት ይሰሩ ነበር።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ሰባ አንደኛው እንዲሁም ሰባ ሁለተኛው ዓመት አለፈ፤ አዎን፣ በአጠቃላይ ሰባ ዘጠነኛው ዓመት አለፈ፤ አዎን መቶ ዓመታት አለፉ፣ እናም ኢየሱስ በምድር እንዲቆዩ ከመረጣቸው ከሦስቱ በስተቀር ሁሉም የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ወደ እግዚአብሔር ገነት ሄደዋል፤ እናም በእነርሱም ቦታ የተሾሙ ሌሎች ደቀመዛሙርት ነበሩ፤ እናም ደግሞ የዚያም ትውልድ ብዙዎች ሞቱ።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ በህዝቡ ልብ ውስጥ ባለው የእግዚአብሔር ፍቅር የተነሳ በምድሪቱ ፀብ አልነበረም።

፲፮ እናም ቅናት፣ ቁጣ፣ ሁከት፣ ዝሙት፣ መዋሸትም፣ ግድያም ሆነ ዝሙትን የሚቀሰቅስ ምንም ነገር አልነበረም፤ እናም በእርግጥ በእግዚአብሔር እጅ ከተፈጠሩት ሰዎች መካከል እንደዚህ ያለ ደስተኛ ሊሆን የቻለ ህዝብ አልነበረም።

፲፯ ሌቦችም ሆኑ ገዳዮች፣ ላማናውያንም ሆኑ ማንኛውም ዓይነት በመደብ የተለዩ ሰዎች አልነበሩም፤ ነገር ግን ሁሉም በአንድነት የክርስቶስ ልጆች፣ እናም የእግዚአብሔርንም መንግስት ወራሾች ነበሩ።

፲፰ እናም እነርሱ እንዴት የተባረኩ ነበሩ! ምክንያቱም ጌታ በስራዎቻቸው ሁሉ ባርኳቸዋልና፤ አዎን፣ አንድ መቶ አስረኛው ዓመት እስኪያልፍ እንኳን ተባርከዋል፤ በልፅገዋልም፤ እናም ከክርስቶስ ጉብኝት ጀምሮ የመጀመሪያው ትውልድ አልፎአልና፣ በምድሪቱ ሁሉ ፀብ አልነበረም።

፲፱ እናም እንዲህ ሆነ ይህንን የመጨረሻ መዝገብ ጠብቆ ያቆየው (እናም በኔፊ ሠሌዳዎች ላይ ነበር ያስቀመጣቸው) ኔፊ ሞተና ልጁ አሞፅ በእርሱ ቦታ አስቀመጠው፤ እናም አሞፅም ደግሞ በኔፊ ሠሌዳዎች ላይ ጠበቃቸው።

እናም ለሰማንያ አራት ዓመታት አስቀመጠው፣ እናም በቤተክርስቲያኑ ላይ ከተነሱትና የላማናውያንን ስም ከወሰዱት ጥቂት ሰዎች በቀር በምድሪቱ አሁንም ሠላም ነበር፤ ስለዚህ በምድሪቱ ላይ በድጋሚ ላማናውያን ሆኑ።

፳፩ እናም እንዲህ ሆነ አሞፅም ደግሞ ሞተ (እናም ይህ ክርስቶስ ከመጣ ከመቶ ዘጠና አራት ዓመት በኋላ ነበር) እናም ልጁ አሞፅ በእርሱ ምትክ መዛግብቱን ጠበቀ፤ እናም ደግሞ በኔፊ ሠሌዳዎች ላይ ጠበቃቸው፤ እናም ይህም ደግሞ ይህ መፅሐፍ በሆነው በኔፊ መጽሐፍ ላይ ተፅፈው ነበር።

፳፪ እናም እንዲህ ሆነ ሁለት መቶ ዓመታት አለፉ፤ እናም ከጥቂቶች በስተቀር ሁለተኛውም ትውልድ በሙሉ አለፈ።

፳፫ እናም እንግዲህ እኔ ሞርሞን፣ ህዝቡም እንደተባዙ፣ በምድሪቱ ገፅ ላይ በሙሉ እስከተሰራጩ ና፣ በክርስቶስ ባገኙት ብልፅግናም እጅግ ሀብታሞች እንደሆኑ እንድታውቁ እፈልጋለሁ።

፳፬ እናም አሁን፣ በሁለት መቶ አንደኛው ዓመት በመካከላቸው በኩራት የተወጣጠሩ፣ ይኸውም ውድ ልብሶችንና መልካም ዕንቁ ከሆኑት ሁሉ እንዲሁም የዓለምን መልካም የሆኑ ነገሮችን የሚለብሱ ነበሩ።

፳፭ እናም ከዚያን ጊዜ በኋላ በመካከላቸው የጋራ የሆኑ ዕቃዎች እንዲሁም ንብረቶች አልነበሯቸውም።

፳፮ እናም በመደብ መከፋፈል ጀመሩ፤ እናም ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ቤተክርስቲያን መስራት ጀመሩ፤ እናም የክርስቶስን እውነተኛ ቤተክርስቲያንም መካድ ጀመሩ።

፳፯ እናም እንዲህ ሆነ ሁለት መቶ አስረኛው ዓመት እንዳለፈም በምድሪቱ ብዙ ቤተክርስቲያኖች ነበሩ፤ አዎን፣ ክርስቶስንም እናውቃለን የሚሉ ብዙ ቤተክርስቲያኖችም ነበሩ፤ እናም ይሁን እንጂ የወንጌሉን አብዛኛውን ክፍል ክደዋል፣ በዚህም የተነሳ ሁሉንም ዓይነት ክፋቶች ተቀብለዋል፤ እናም እርሱ ብቁ ባለመሆኑ የተከለከለውን ቅዱስ የሆነውን ሰጥተዋልና።

፳፰ እናም በክፋታቸውም የተነሳና ልባቸውን በተቆጣጠረው በሰይጣን ኃይል የተነሳ ይህች ቤተክርስቲያን እጅግ ተስፋፋች።

፳፱ እናም በድጋሚ፣ ክርስቶስን የሚክድ ሌላ ቤተክርስቲያን ነበር፤ እናም በትህትናቸውና በክርስቶስ ባላቸው እምነት የተነሳ እውነተኛ የሆነችውን የክርስቶስን ቤተክርስቲያን አሳደዱ፤ እናም በመካከላቸው ብዙ ተአምራትንም በመስራታቸው ጠሉዋቸው።

ስለዚህ ከእነርሱ ጋር በቀሩት የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ላይ ኃይልና ስልጣናቸውን ተጠቀሙ፣ ወህኒ ቤትም ጣሉአቸው፤ ነገር ግን በውስጣቸው ባለው በእግዚአብሔር ቃል ኃይል ወህኒ ቤቱ ሁለት ቦታ ተከፈለ፣ እናም በመካከላቸው ኃያል ተአምራትን መስራት ቀጠሉ።

፴፩ ይሁን እንጂ፣ እናም እነዚህ ሁሉ አስደናቂ ነገሮች ቢኖሩም እንኳን፣ ሰዎቹ ልባቸውን አጠጥረው ነበር፣ እናም በኢየሩሳሌም የነበሩት አይሁዶች በቃሉ መሠረት ኢየሱስን ለመግደል እንደፈለጉት ሁሉ እነርሱን ለመግደል ፈለጉ።

፴፪ እናም በእሳት ዓምድም ውስጥ ጣሉአቸውና፣ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ወጡ።

፴፫ እናም ደግሞ በዱር አራዊት ዋሻ ጣሉአቸውና፣ እነሆ ልጅ ከሚጠባ የበግ ጠቦትጋር እንደሚጫወተው ከአውሬዎች ጋር ይጫወቱ ነበር፣ እናም ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከመካከላቸው ወጡ።

፴፬ ይሁን እንጂ፣ ሰዎቹ በብዙ ካህናትና ሃሰተኛ ነቢያት ብዙ ቤተክርስቲያኖችን እንዲሰሩና ሁሉንም አይነት ክፋቶች እንዲሰሩ በመመራታቸው ልባቸውን አጠጥረውት ነበር። እናም የኢየሱስን ህዝቦችንም መቱ፤ ነገር ግን የኢየሱስ ሰዎች መልሰው አልመቱአቸውም ነበር። እናም ከዓመት ዓመት፣ ሁለት መቶ ሰላሳ ዓመት እስከሚያልፍ ድረስ እምነት በማጣትና በክፋቶቻቸው መነመኑ።

፴፭ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ በዚሁ ዓመት፤ አዎን፣ በሁለት መቶ ሠላሳ አንደኛው ዓመት፣ በህዝቡ መካከል ታላቅ የሆነ መከፋፈል ነበር።

፴፮ እናም እንዲህ ሆነ በዚህ ዓመት ኔፋውያን ተብለው የሚጠሩ ሰዎች ተነሱና፣ እነርሱም በክርስቶስ እውነተኛ አማኞች ነበሩ፤ እናም በመካከላቸው በላማናውያን—ያዕቆባውያንና፣ ዮሴፋውያን፣ እናም ዞራማውያን ተብለው የሚጠሩ ነበሩ፤

፴፯ ስለዚህ በክርስቶስ እውነተኛ አማኞች እናም የክርስቶስ እውነተኛ አምላኪዎች (ከእነርሱም መካከል በምድር የቀሩት ሦስቱ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ነበሩ) ኔፋውያንና፣ ያዕቆባውያን፣ እናም ዮሴፋውያንና፣ ዞራማውያን ተብለው ይጠሩ ነበር።

፴፰ እናም እንዲህ ሆነ ወንጌሉን ያልተቀበሉት ላማናውያን፣ ልሙኤላውያንና፣ እስማኤላውያን ተብለው ይጠሩ ነበር፤ እናም እምነት አጥተው አልመነመኑም፣ ነገር ግን በክርስቶስ ወንጌል ላይ በፈቃደኝነት አምፀዋል፤ እናም አባቶቻቸው ከመጀመሪያው ጀምረው እንደመነመኑት፣ እነርሱ ልጆቻቸውን እንዳያምኑ አስተምረዋቸዋል።

፴፱ እናም ይህም የነበረው ከመጀመሪያም እንደነበረው የአባቶቻቸው ክፋትና ርኩስነት ምክንያት ነው። እናም ከጥንት ጀምሮ ላማናውያን የኔፊን ልጆች እንዲጠሉ እንደተማሩት የእግዚአብሔርን ልጆች እንዲጠሉ ተማሩ።

እናም እንዲህ ሆነ ሁለት መቶ አርባ አራተኛው ዓመት አለፈ፣ እናም የህዝቡም ጉዳይ እንዲህ ነበር። እናም ከህዝቡ ይበልጡን ክፉ የነበሩት የበረቱ ሆኑና፣ ከእግዚአብሔር ሰዎች ይበልጥ እጅግ ብዙ ሆኑ።

፵፩ እናም አሁንም ለራሳቸው ቤተክርስቲያንን መስራት ቀጠሉ፣ በከበሩ ነገሮችም አስጌጡአቸው። በዚህም ሁለት መቶ ሃምሳ ዓመት፣ እናም ደግሞ ሁለት መቶ ስልሳ ዓመታትም አለፉ።

፵፪ እናም እንዲህ ሆነ ክፉዎች የሆኑት የጋድያንቶን ቡድኖች ሚስጥር መሃላንና ውህደትን በድጋሚ መገንባት ጀመሩ።

፵፫ እናም ደግሞ የኔፊ ህዝብ ተብለው የሚጠሩት እጅግ ሀብታሞች በመሆናቸው መኩራት ጀመሩ፣ እናም እንደወንድሞቻቸው እንደላማናውያን ከንቱ ሆኑ።

፵፬ እናም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ደቀመዛሙርቱም ስለዓለም ኃጢያት ማዘን ጀመሩ።

፵፭ እናም እንዲህ ሆነ ሦስት መቶ ዓመታት ካለፉ በኋላ፣ የኔፊ እንዲሁም የላማናውያን ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ እጅግ ክፉዎች ሆኑ።

፵፮ እናም እንዲህ ሆነ የጋድያንቶን ዘራፊዎች በምድሪቱ ገፅ ሁሉ ተሰራጩ፤ እናም ከኢየሱስ ደቀመዛሙርት በቀር ፃድቅ የነበረ ማንም አልነበረም። እናም በመጋዘኖቻቸው በርካታ ወርቆችንና ብሮችን አከማችተው ነበር፣ እናም ማንኛውንም ሸቀጦቻቸውን ይገበያዩ ነበር።

፵፯ እናም እንዲህ ሆነ ሦስት መቶ አምስት አመታት ካለፉ በኋላ፣ (እናም ህዝቡ አሁንም በክፋታቸው ቀጥለዋል) አሞፅ ሞተ፤ ወንድሙ አማሮንም መዛግብቱን በእርሱ ምትክ ጠበቀ።

፵፰ እናም እንዲህ ሆነ ሦስት መቶ ሃያኛው ዓመት ካለፈ በኋላ፣ አማሮን በመንፈስ ቅዱስ በመገፋፋቱ፣ ቅዱስ የሆኑትን መዛግብት ደበቀ—አዎን፣ ቅዱሳን የነበሩትን ከትውልድ እስከ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡትን መዝገቦች ሁሉ—ክርስቶስ ከመጣ ከሦስት መቶ ሀያ ዓመት ጀምሮ ያሉትን ጭምር ደበቀ፤

፵፱ እናም በጌታ ትንቢትና ቃል ኪዳን መሰረት በድጋሚ ወደ ያዕቆብ ቤት ቅሪት ይመጡ ዘንድ በጌታ ደበቃቸው። እናም የአማሮን መዝገብ ፍፃሜ ይህ ነው።