ምዕራፍ ፬
[ሰኔ–ጥቅምት ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.)]
እንዴት ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ—ሰይጣን ሔዋንን ፈተነ—አዳምና ሔዋን ወደቁ፣ እናም ሞት ወደ ምድር መጣ።
፩ እና እኔ እግዚአብሔር አምላክም ለሙሴ እንዲህ አልኩት፤ በአንድያ ልጄ ስም ያዘዝከው ያ ሰይጣንም ከመጀመሪያው ጊዜ የነበረ ነው፣ እና በፊቴም እንዲህ በማለት መጣ፣ እነሆ፣ አለሁ፣ እኔን ላከኝ፣ ልጅህም እሆናለሁኝ፣ እና አንድም ነፍስ እንዳይጠፋ፣ የሰውን ዘር አድናለሁ፣ እና በእርግጥም ይህን አደርጋለሁ፤ ስለዚህ ክብርህን ስጠኝ።
፪ ነገር ግን እነሆ፣ ውዱና ከመጀመሪያ ጊዜ ጀምሮ የተመረጠው ተወዳጁ ልጄም እንዲህ አለኝ—አባት ሆይ፣ ፈቃድህ ይፈጸም፣ እናም ክብርም ለዘለአለም ያንተ ይሁን።
፫ ስለዚህ ሰይጣን ስለዐመፀብኝና እኔ እግዚአብሔር አምላክ የሰጠሁትን የሰው ነጻ ምርጫ ለማጥፋት ስለፈለገ፣ እና ደግሞም የራሴን ሀይል ለእርሱ እንድሰጠው ሰለፈለገ ዘንድ፣ በአንድያ ልጄ ሃይል እንዲጣል አደረግሁኝ፤
፬ እና እርሱም ሰይጣን፣ አዎን፣ እንዲሁም ድምጼን የማያደምጡትን ሁሉ የሚያታልለው እና ሰዎችን እንዳያዩ አድርጎ በፈቃዱም እንደ እስርኞች የሚመራቸው፣ እንዲሁም የሀሰት አባት ዲያብሎስ ሆነ።
፭ እና እኔ እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠርኳቸው ከምድር አውሬዎች ሁሉ ይልቅ እባብም ተንኮለኛ ነበር።
፮ እና (ብዙዎችን ወደ ራሱ ስለወሰደ) ሰይጣን በእባቡ ልብ ውስጥ ይህን አደረገ፣ እና እርሱም ሔዋንን ለማሳሰት ፈለገ። የእግዚአብሔርንም ሀሳብ አያውቅምና፣ ስለዚህ ምድርን ለማጥፋት ፈለገ።
፯ እና ሴቲቱንም እንዲህ አላት፥ አዎን፣ እግዚአብሔር—ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ ብሏል? (እና በእባቡ አፍ ነበር የተናገረው።)
፰ እና ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፥ በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤
፱ ነገር ግን በገነት መካከል ከምትመለከቷቸው ከዛፉ ፍሬ፣ እግዚአብሔር እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም ብሏል።
፲ እና እባብም ለሴቲቱ አላት፥ በእርግጥም አትሞቱም፤
፲፩ ከእርሱም በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።
፲፪ እና ሴቲቱም ዛፉን ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፣ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፣ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።
፲፫ እና የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፣ እና ራቁታቸውን መሆናቸውንም አወቁ። እናም የበለስ ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።
፲፬ እነርሱም ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔር አምላክን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ፤ አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ።
፲፭ እና እኔ እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቼ፣ የት ነህ? አልኩት።
፲፮ እርሱም አለ፥ ድምጽህን በገነት ሰማሁ፤ ራቁቴን ስለሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም።
፲፯ እና እኔ እግዚአብሔር አምላክም ለአዳም እንዲህ አልኩት፥ ራቁትህን እንደሆንህ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ፣ ከበላህም መሞት አለብህ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህ?
፲፰ አዳምም አለ፥ የሰጠኸኝ እና ከእኔ ጋር እንድትሆን ያዘዝከኝ ሴት፣ እርስዋ የዛፉን ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ።
፲፱ እና እኔ እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን፥ ይህ ያደረግሽው ነገር ምንድን ነው? አልኳት። እና ሴቲቱም አለች፥ እባቡ አሳተኝና በላሁ።
፳ እና እኔ እግዚአብሔር አምላክም እባቡን እንዲህ አልሁት፤ ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ፤ በሆድህም ትሄዳለህ፣ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ።
፳፩ በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እና እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሽኰናውን ትቀጠቅጣለህ።
፳፪ ለሴቲቱም እኔ እግዚአብሔር አምላክም እንዲህ አልኳት፥ በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ። በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ እና ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል።
፳፫ ለአዳምም እኔ እግዚአብሔር አምላክ አልኩት፣ የሚስትህን ቃል ሰምተሀል፣ ከእርሱ አትብላ ብዬ ያዘዝኩህን ዛፍ በልተሀልና፣ ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ።
፳፬ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ።
፳፭ ከምድር ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ—በእርግጥም ትሞታለህና—ከዚህም ስለመጣህ፥ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህና።
፳፮ አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፣ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና፤ እንደዚህም ነው እኔ እግዚአብሔር አምላክ ከብዙዎቹ ሴቶች ሁሉ የመጀመሪያዋን የጠራኋት።
፳፯ እኔ እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረግሁላቸው፣ እና አለበስኳቸው።
፳፰ እና እኔ እግዚአብሔር አምላክም ለአንድያ ልጄ እንዲህ አልኩት፥ እነሆ ሰውም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፣ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፤
፳፱ ስለዚህ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድእኔ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከዔድን ገነት አስወጣዋለሁ፤
፴ እኔ እግዚአብሔር አምላክ ህያው እስከሆንኩኝ ድረስ፣ ቃላቶቼ ውጤት የሌላቸው መሆን አይገባቸውም፣ ከአፌ እንደወጡ መከናወን አለባቸውና።
፴፩ ለዚህ ሰውን አስወጣሁት እና ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጥኩኝ።
፴፪ (እነዚህ ለአገልጋዬ ሙሴ የተናገርኳቸው ቃላት ነበሩ፣ እና እውነተኛ እንዲሁም እንደፈቃዴ ናቸው፤ እና ለእናንተም ነግሬአቸዋለሁ። ከሚያምኑት በስተቀር፣ እስከማዝህ ድረስ ከሚያምኑት ሌላ ለማንም ሰው አታሳይ። አሜን)