ምዕራፍ ፲
የመፅሐፈ ሞርሞን ምስክርነት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይመጣል—ለታማኞች የመንፈስ ስጦታዎች ይሰጣቸዋል—መንፈሳዊው ስጦታዎች ዘወትር እምነትን ይከተላል—የሞሮኒ ቃላት ከምድር ይናገራሉ—ወደ ክርስቶስ ኑ፤ በእርሱም ፍፁማን ሁኑ፣ እናም ነፍሳችሁን አንፁ። ፬፻፳፩ ዓ.ም. ገደማ።
፩ አሁን እኔ ሞሮኒ፣ መልካም የመሰለኝን በመጠኑ እፅፋለሁ፤ ለወንድሞቼ ለላማናውያንም እፅፋለሁ፤ እናም ስለክርስቶስ መምጣት ምልክት ከተሰጠ አራት መቶ ሃያ ዓመት ማለፉን እንዲያውቁ እፈልጋለሁ።
፪ እናም እናንተን በጥብቅ በመምከር ጥቂት ከተናገርኳችሁ በኋላ እነዚህን መዛግብት አትማቸዋለሁ።
፫ እነሆ፣ እነዚህን ነገሮች በምታነቡበት ጊዜ፣ ይህን እንድታነቡ በእግዚአብሔር ጥበብ ከሆነ፣ ጌታም ለሰው ልጆች ከአዳም መፈጠር ጀምሮ እነዚህን ነገሮች እስከምትቀበሉአቸው ጊዜ ድረስ ምን ያህል መሃሪ እንደነበረ እንድታስታውሱ በጥብቅ እመክራችኋለሁ፣ እናም በልባችሁ ይህን አሰላስሉ።
፬ እናም እነዚህንም ነገሮች በምትቀበሉበት ጊዜ፣ እነዚህ ነገሮች ሀሰት እንደሆኑ ዘለዓለማዊ አብ እግዚአብሔርን በክርስቶስ ስም እንድትጠይቁት አጥብቄ እመክራችኋለሁ፤ እናም በቅን ልባችሁ፤ ከእውነተኛ ፍላጎት፣ በክርስቶስ አምናችሁ ከጠየቃችሁት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እውነቱን ይገልፅላችኋል።
፭ እናም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሁሉንም ነገር እውነታ ታውቁታላችሁ።
፮ እናም መልካም የሆነ ማንኛውም ነገር ጻድቅ እና እውነተኛ ነው፤ ስለሆነም፣ መልካም የሆነ ማንም ክርስቶስን አይክድም፤ ነገር ግን እርሱ መሆኑን ያረጋግጣል።
፯ እናም እርሱ መሆኑንም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ታውቃላችሁ፤ ስለሆነም፣ የእግዚአብሔርን ኃይል እንዳትክዱ በጥብቅ እመክራችኋለሁ፤ ምክንያቱም እርሱ፣ በሰው ልጆች እምነት መሰረት፣ በኃይሉ ዛሬም እንዲሁም ነገም፣ እናም እስከዘለዓለም በአንድ አይነት ይሰራልና።
፰ እናም በድጋሚ ወንድሞቼ፣ የእግዚአብሔር ስጦታዎች እንዳትክዱአቸው አጥብቄ እመክራችኋለሁ፣ ብዙ ናቸውና፤ እና እነርሱም የሚመጡት ከአንድ እግዚአብሔር ነው። እናም እነዚህ ስጦታዎች የሚገለጡበት የተለያዩ መንገዶች አሉ፤ ነገር ግን ሁሉን በሁሉ የሚያደርገው እግዚአብሔር አንድ ነው፤ እናም ለሰው በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መገለጥ ለጥቅሙ ይሰጠዋል።
፱ እነሆም፣ ለአንዱ የጥበብን ቃል ያስተምር ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ይሰጠዋል።
፲ እናም ለሌላው፣ ለእርሱም በዚያው መንፈስ የእውቀትን ቃል ያስተምር ዘንድ ይሰጠዋል።
፲፩ እናም ለሌላው እጅግ ታላቅ ዕምነት፤ ለሌላውም በዚያው መንፈስ የመፈወስ ስጦታ ይሰጠዋል፤
፲፪ እናም በድጋሚ፣ ለሌላው፣ ታላላቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ ይሰጠዋል፤
፲፫ እናም በድጋሚ፣ ለሌላው ስለሁሉም ነገሮች ትንቢት እንዲናገር ይሰጠዋል፤
፲፬ እናም በድጋሚ፣ ለሌላው፣ መላዕክትን የማየት እናም የመንፈስ አገልጋይነት ይሰጠዋል፤
፲፭ እናም በድጋሚ፣ ለሌላው ሁሉንም ዓይነት ልሳን ይሰጠዋል፤
፲፮ እናም በድጋሚ፣ ለሌላው፣ ቋንቋዎችን እናም የተለያየ ዓይነት ልሳን የተነገሩትን መተርጎም ይሰጠዋል።
፲፯ እናም እነዚህ ሁሉ ስጦታዎች የሚመጡት በክርስቶስ መንፈስ አማካኝነት ነው፤ እናም እነርሱም ለእያንዳንዱ ሰው ለብቻው እያካፈለ እንደፈቃዱ ይመጣሉ።
፲፰ እናም የተወደዳችሁ ወንድሞቼ መልካም ስጦታ ሁሉ ከክርስቶስ እንደሚመጣ እንድታስታውሱ አጥብቄ እመክራችኋለሁ።
፲፱ እናም የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እርሱ ዛሬም እናም ነገም እናም ለዘለዓለም አንድ አይነት እንደሆነ፣ እናም የተናገርኳቸው መንፈሳዊ የሆኑት እነዚህ ስጦታዎች በሙሉ ምድር እስካለች የሰው ልጆች እምነት ካላጡ በስተቀር ፈፅሞ መኖራቸውን እንደማያቆሙ እንድታስታውሱ አጥብቄ እመክራችኋለሁ።
፳ ስለሆነም፣ እምነት ሊኖር ይገባል፤ እናም እምነት ካለ ተስፋም ደግሞ ሊኖር ይገባል፤ እናም ተስፋም ደግሞ ካለ ልግስና መኖር አለበት።
፳፩ እናም እናንተ ልግስና ከሌላችሁ በእግዚአብሔር መንግስት በምንም መንገድ ልትድኑ አይቻላችሁም፤ ወይም እምነት ከሌላችሁ በእግዚአብሔር መንግስት ለመዳን አትችሉም፤ ወይም ተስፋም ከሌላችሁ ለመዳን አይቻላችሁም።
፳፪ እናም ተስፋ ከሌላችሁ በተስፋ መቁረጥ ላይም መሆን አለባችሁ፣ እናም ተስፋ መቁረጥም የሚመጣው በክፋት ነው።
፳፫ እናም ክርስቶስ ለአባቶቻችን በእውነት እንዲህ ሲል ተናግሯቸዋል፥ እናንተም እምነት ካላችሁ ለእኔ አስፈላጊ የሆነውን ለማድረግ ይቻላችኋል።
፳፬ እናም አሁን እስከአለም ጫፍ ላሉት ሁሉ እንዲህ ስል እናገራለሁ—የእግዚአብሔር ኃይልና ስጦታ በእናንተ መካከል መሆኑን የሚያቆምበት ቀን ከመጣ፣ ይህም የሚሆነው እምነት በማጣት ምክንያት ነው።
፳፭ እናም እንዲህ ከሆነ ለሰው ልጆች ወዮላቸው፤ ከእናንተ መካከል አንድም እንኳን ቢሆን መልካም የሚሰራ ምንም የለምና። ከመካከላችሁ መልካምን የሚያደርግ አንድ እንኳን ቢኖር፣ እርሱም በእግዚአብሔር ኃይልና ስጦታ ይሰራል።
፳፮ እናም እነዚህን ነገሮች ለሚያስወግዱት እናም ለሚሞቱ ወዮላቸው፣ ምክንያቱም ከነኃጢአታቸው ይሞታሉ እናም በእግዚአብሔር መንግስት አይድኑምና፤ እናም እኔም የተናገርኩት በክርስቶስ ቃል መሰረት ነው፤ እናም ሀሰትን አልተናገርኩም።
፳፯ እናም እነዚህን ነገሮች እንድታስታውሱ አጥብቄ እመክራችኋለሁ፤ እኔ ሀሰት እንዳልተናገርኩ የምታውቁበት ቀን በፍጥነት ይመጣል፣ በእግዚአብሔር ፍርድ ወንበርም ታዩኛላችሁና፤ እናም ጌታ አምላክ እንዲህ ሲል ይናገራችኋል፥ ከሙታን እንደሚጮህ፣ አዎን፣ አንድ ሰው ከመሬት እንደሚናገር በዚህ ሰው የተፃፉትን ቃላት ለእናንተ አላወጅኩላችሁምን?
፳፰ ትንቢቶች ይፈፀሙ ዘንድ እነዚህን ነገሮች ለእናንተ አውጄአለሁ። እናም እነሆ፣ እነርሱም ከዘለዓለማዊው አምላክ አንደበት ይወጣሉ፤ እናም ቃሉም ከትውልድ ወደ ትውልድ ያፏጫል።
፳፱ እናም እግዚአብሔርም የፃፍኩት እውነት እንደሆነ ያሳያችኋል።
፴ እናም በድጋሚ ወደ ክርስቶስ እንድትመጡ፣ እናም እያንዳንዱን መልካሙን ስጦታ እንድትይዙ፣ እናም ክፉውን ስጦታ ወይም እርኩስን ነገር እንዳትነኩ አጥብቄ እመክራችኋለሁ።
፴፩ እናም እስራኤል ሆይ ንቂ ከመሬት ተነሽ፤ አዎን፣ እናም አቤቱ የፅዮን ሴት ልጅ፣ የሚያምረውን መጎናፀፊያሽን ልበሺ፤ እናም ከዚህም በኋላ እንዳትቀላቀሊ፣ የዘለዓለማዊ አባት ለአንቺ፣ አቤቱ የእስራኤል ቤት፣ የገባው ቃል ኪዳን ይሟላም ዘንድ ካስማዎችሽን አጥብቂ እናም ወሰንሽንም ለዘለዓለም አስፊ፤ ከእንግዲህም አታፍሪም።
፴፪ አዎን፣ ወደ ክርስቶስ ኑ፣ እናም በእርሱም ፍፁማን ሁኑ፣ እናም ኃጢአተኝነትን በሙሉ ለእራሳችሁ ካዱ፤ እናም ለራሳችሁ ኃጢአተኝነትን በሙሉ ከካዳችሁ፣ እናም በሙሉ ኃይላችሁ፣አዕምሮአችሁ እና ጉልበታችሁ እግዚአብሔርን ከወደዳችሁ፣ ፀጋው ለእናንተ ይበቃችኋል፣ በፀጋውም በክርስቶስ ፍፁም ትሆናላችሁ፤ እናም በእግዚአብሔር ፀጋ በክርስቶስ ፍፁም ከሆናችሁ፣ የእግዚአብሔርን ኃይል በምንም መልኩ አትክዱትም።
፴፫ እናም በድጋሚ፣ በእግዚአብሔር ፀጋ በክርስቶስ ፍፁማን ከሆናችሁ፣ እናም ኃይሉን ካልካዳችሁ፣ በእግዚአብሔር ፀጋ፣ ለኃጢአታችሁ ስርየት አብ በገባው ቃል ኪዳን ውስጥ ባለው በክርስቶስ ደም መፍሰስ ያለ እንከን ቅዱስ ትሆኑ ዘንድ በክርስቶስ ትቀደሳላችሁ።
፴፬ እናም አሁን ሁላችሁንም እሰናበታችኋለሁ። መንፈስና ስጋዬም በአንድነት እስኪገናኝ፣ እናም ለህያዋን እና ለሙታን ዘለዓለማዊ ዳኛ በሆነው በታላቁ ያህዌህ አስደሳቹ የፍርድ ወንበር ፊት እናንተን ለመገናኘት ድል አድርጌ ወደ ሰማይ እስከምመጣ ድረስ፣ በቅርብ ወደ እግዚአብሔር ገነት ለማረፍ እሄዳለሁ። አሜን።
ተፈፀመ