የተሰወረ የእሳት እንቅስቃሴ
እግዚአብሔር የምናቀርበውን እያንዳንዱን ጸሎት እንደሚሰማ እና ለእያንዳንዱም ለፍጹምነታችን በዘረዘረው መንገድ ምላሽ እንደሚሰጥ እመሰክራለሁ።
ወንድሞችና እህቶች፣ በጥቅምት 2022 (እ.አ.አ) ይህን መድረክ ለመጨረሻ ጊዜ ከያዝኩት ጊዜ አንስቶ አንድ የሚያሳምም ትምህርት ተምሬያለሁ። ያም ትምህርት፦ ተቀባይነት ያለው ንግግር ካልሰጠህ፡ በቀጣዮቹ በርካታ ጉባኤዎች ላይ እገዳ ሊጣልብህ ይችላል። በዚህ በመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ ማለዳ ላይ እንደተመደብኩ ማየት ትችላላችሁ። ልታዩት የማትችሉት ነገር ቢኖር፣ ልዩ መቆለፊያ ባለው የወጥመ በር ላይ መቆሜን ነው። ይህ ንግግር በጥሩ ሁኔታ ካልሄደ፣ ለሚቀጥሉት ጥቂት ጉባኤዎች አላያችሁም።
እነዚያ ደስ የሚሉ መዘምራን በዘመሩት በዚያ ቆንጆ መዝሙር መንፈስ ውስጥ፣ በቅርቡ የተወሠኑ ትምህርቶችን ተምሬአለሁ፣ በጌታ እርዳታ፣ ዛሬ ላካፍላችሁ እመኛለሁ። ያም ይህንን ንግግሬን በጣም የግል ያደርገዋል።
ከእነዚህ ሁሉ የቅርብ ጊዜ ገጠመኞች በጣም ግላዊ እና ከባድ የነበረው የምወዳት ባለቤቴ የፓት ህልፈተ ሕይወት ነው። እስከ ዛሬ ከማውቃቸው ሁሉ በላይ ታላቅ ሴት ነበረች። ከንጹህነቷ፣ ሀሳቧን የመግለጽ ችሎታዋ፣ እና መንፈሳዊነቷ በተጨማሪ ፍጹም ሚስት እና እናት ነበረች። በአንድ ወቅት “የተፈጠራችሁበትን ዓላማ ማሣካት” የሚል ርዕስ ያለው ንግግር አቅርባ ነበር። ማንም ሰው ሊያልመው ከሚችለው በላይ እርሷየተፈጠረችበትን ዓላማ በተሳካ ሁኔታ የፈፀመች መስሎ ይታየኛል። እርሷ ፍጹም የእግዚአብሔር ሲት ልጅ ነበረች፣ የክርስቶስ አይነት ሴት ምሳሌ። 60 አመታት ያህል ከእርሷ ጋር ለመኖር በመቻሌ ከወንዶች ሁሉ እድለኛ ነበርኩኝ። ብቁ መሆኔን ካረጋገጥኩኝ፣ በመታተማችን ምክንያት ከእሷ ጋር ለዘለአለም ማሳለፍ እችላለሁ ማለት ነው።
ባለቤቴ ከተቀበረች ከ48 ሰዓታት በኋላ ሌላ የመማር ተሞክሮ ተጀመረ። በዚያን ወቅት፣ ከባድ የጤና እክል ገጥሞኝ በአጣዳፊ ሁኔታ ወደ ሆስፒታል ተወስጄ ነበረ። ከዚያም ከስድስት ሳምንታት ቆይታዬ ውስጥ የመጀመሪያዎቹን አራት ሳምንታት አልፎ አልፎ በፅኑ ሕሙማን እንክብካቤ ክፍል ውስጥ ስገባ እና ስወጣ ብሎም ራሴን በመሣት እና በመንቃት ውስጥ አሳልፌያለሁ።
በመሠረቱ፣ በዚያ ወቅት በሆስፒታል ውስጥ መጀመሪያ ላይ ያጋጠመኝ ነገር ሁሉ ማስታወስ አልችልም። ያልጠፋ ነገር ቢኖር፣ ከሆስፒታል ውጪ ያደረግሁት ወደዘለዓለማዊነት ጠርዝ የሚመስል የጉዞ ትዝታዬ ነው። ስለዚያ ተሞክሮ አሁን ሙሉ ለሙሉ መናገር አልችልም፣ ነገር ግን ከተቀበልኩት ውስጥ አንዱ ክፍል መመርያ እንደነበር መናገር እችላለሁ፤ ይኸውም፣ በበለጠ ቅድስና፣ በአዳኝ ላይ የበለጠ ትኩረት በማድረግ እና በቃሉ የበለጠ በማመን በፍጥነት ወደ አገልግሎቴ እንድመለስ የተሠጠ ማበረታቻ ነበር።
ከ200 አመት በፊት ለአስራ ሁለቱ ከተሰጠው ራዕይ፤ የራሴን የራዕይ ቅጂ እየተቀበልኩ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር።
“ስለስሜ ትመሰክራለህ፤ …[እና] ቃሌን ወደ ምድር ዳርቻዎች ትልካለህ። …
“… ስለዚህ ጠዋት በየማለዳው፣ በየቀኑ የማስጠንቀቂያህ ድምፅህ ይሂድ፤ እና ሲመሽም፣ በንግግርህ ምክንያት የምድር ነዋሪዎች ያንቀላፉም ዘንድ አትፍቀድ። …
“ተነሳ፣… መስቀ[ልህን] አን[ሣ]፣ እና ተከተ[ለኝ]
የተወደዳችሁ እህቶቼ እና ወንድሞቼ፣ ከዚያ ተሞክሮ ጀምሮ፣ መስቀሌን ለማንሳት፣ በጠዋት፣ በቀን፣ እና በሌሊት የሐዋርያዊ ድምጽን ለማንሳት የምችልበትን ቦታ ለማግኘት የበለጠ ጥረት አድርጌያለሁ።
ይህም በእነዚያ በሐዘን፣ በበሽታና በጭንቀት ወራት ወደመጣው ወደሦስተኛው እውነት ይመራኛል። ይህም ተጠቃሚ ስለሆንኩባቸው የእናንተ የቤተክርስቲያን ትሑት የግል ጸሎቶች ውጤታማነት አዲስ ምስክርነት እና ማለቂያ የሌለው ምስጋና ነው። ተግታ እንደለመነችው መበለት፣ እኔን ወክለው የሰማያትን ጣልቃ ገብነት ደጋግመው ለፈለጉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ልመና ዘለአለማዊ ምስጋና አቀርባለሁ። የክህነት በረከቶችን ተቀብያለሁ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጓደኞቼ ለእኔ ብለው ሲፆሙ አየሁ፣ ልክ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ያሉ በርካታ ሌሎች አጥቢያዎች እንዳደረጉት። እናም ስሜ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ባሉ በሁሉም ቤተመቅደሶች የጸሎት ጥቅል ውስጥ ሣይገባ አይቀርም።
ለዚህ ሁሉ ላለኝ ጥልቅ ምስጋና፣ ከጂ ኬ ቼስተርተን ጋር እቀላቀላለሁ፣ እርሱም አንድ ጊዜ፣ “ምስጋና ከሁሉ የላቀ ሀሳብ ነው፤ እና … ምስጋና ደስታን በአስገራሚ እጥፍ ይጨምረዋል።” ብሏል። በራሴ “በአድናቆት በእጥፍ በጨመረ ደሥታ”፣ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ እናም ጸሎታችሁን የሰማውን እና ህይወቴን የባረከውን የሰማይ አባቴን አመሰግናለሁ።
ወንድሞች እና እህቶች፣ እግዚአብሔር የምናቀርበውን እያንዳንዱን ጸሎት እንደሚሰማ እና ለእያንዳንዱም ለፍጹምነታችን በዘረዘረው መንገድ ምላሽ እንደሚሰጥ እመሰክራለሁ። በዚሁ ጊዜ ውስጥ ብዙ ሰዎች ጤንነቴ እንዲመለስ ይጸልዩ እንደነበር ተገንዝቤያለሁ፣ እኔን ጨምሮ ተመሣሣይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የባለቤቴ ጤንነት እንዲመለስም እየፀለዩ ነበር። ለፓት የቀረቡት ጸሎቶች እኔ በምፈልገው መንገድ ባይመለሱም እንኳ ሁለቱም ጸሎቶች እንደተሰሙ እና በመለኮታዊ ርኅሩኅ በሆነው የሰማይ አባት እንደተመለሱ እመሰክራለሁ። ፀሎቶች እኛ ተስፋ ከምናደርግባቸው በተለየ መልኩ ምላሽ የሚያገኙት ለእግዚአብሔር ብቻ በታወቁ ምክንያቶች ነው፤ ነገር ግን ይሰማሉ፣ እንከን የለሽ በሆነ ፍቅሩ እና ለአፅናዓለሙ ባለው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መልስ ያገኛሉ።
“[ሣንነቅፍ ከለመንን]” መቼ፣ የት ወይም ስለምን መጸለይ እንዳለብን ገደብ የለውም። በራዕይ እንደተገለጠው፣ “ሁልጊዜ መጸለይ” አለብን። አሙሌቅ እንዳለው፣ “የጻድቅ [ሰዎች ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች” እኛም በማመን “በዙሪያችን ላሉት” መጸለይ አለብን። ብቻችንን ሆነን ጸሎት ስናደርግ ድምጽ አውጥተን መሆን ይኖርበታል። ያንን ማድረግ የማይቻል ከሆነ በልባችን ውስጥ ድምፅ አልባ ቃል ሆነው ሊወሰዱ ይገባል። ጸሎቶች፣ ሁልጊዜም አዳኙ ባስቀመጠው ምሣሌ መሰረት፣ በአንድያ ልጁ ስም ወደ ዘላለማዊ አባት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ “የተሰወረ የእሳት እንቅስቃሴ” እንደሆኑ በጋለ ሥሜት እንናገራለን።
የተወደዳችሁ ጓደኞቼ፣ ጸሎቶቻችን በጣም ጣፋጭ ሰዓታችን፣ እጅግ በጣም “ቅን ፍላጎታችን”፣ እጅግ ቀላል፣ ንጹህ የአምልኮ አይነት ናቸው። በግላችን ፣ በቤተሰባችን እንዲሁም የተለያየ ስፋት ባላቸው በሁሉም ስብሠባዎች ላይ መጸለይ ይኖርብናል። ጸሎትን ፈተናን እንደሚከላከል ጋሻ መጠቀም አለብን፣ መጸለይእንደሌለብን የሚሰማን ጊዜ ካለ፣ ይህ በማንኛውም ጊዜ ከልጆቹ ጋር ለመነጋገር ከሚናፍቀው ከእግዚአብሔር እንዳልመጣ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። በእርግጥም ፀሎት እንዳንፀልይ የሚደረጉ አንዳንድ ጥረቶች በቀጥታ ከጠላት ይመጣሉ። ደግሞም እንዴት ወይም ስለምን እንደምንፀልይ በማናውቅበት ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ ልናቀርበው ወደሚገባን ጸሎት እስኪመራን ድረስ መፀለይ መጀመር እና መቀጠል አለብን። ይህ አቀራረብ፣ ለጠላቶቻችን እና በሚያበሳጭ መንገድ ለሚጠቀሙብን ሰዎች ስንጸልይ የምንማፀንበት ሊሆን ይችላል።
በዋነኝነት፣ በጣም፣ በጣም ብዙ ጊዜ የጸለየውን የአዳኙን ምሳሌ መመልከት እንችላለን። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሊፀልይ እንደሚገባው መረዳቱ ሁልጊዜ ትኩረቴን ይስበው ነበር። ፍጹም አልነበረምን? ስለ ምን መጸለይ ያስፈልገዋል? እርሱም ከእኛ ጋር፣ “የአብንን ፊት መፈለግ፣ ቃሉን ማመን እና በጸጋው መታመን” እንደሚፈልግ ተረድቻለሁ። በየጊዜው፣ ሰማይን በጸሎቱ ለማስከፈት ከማንኳኳቱ በፊት ብቻውን ለመሆን ከኅብረተሰቡ ፈቀቅ ይል ነበር። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ከጥቂት ጓደኞቹ ጋር ሆኖ ይጸልይ ነበር ። ከዚያም ተራራን የሚሸፍኑ ብዙ ሰዎችን ወክሎ የሰማይን እርዳታ ይፈልጋል። አንዳንዴ ጸሎት ልብሱን እንደ ብርሃን ነጭ ያደርገው ነበር። አንዳንዴ ገፅታውን እንደፀሃይ ያበራው ነበር። አንዳንድ ጊዜ ለመጸለይ ይቆም ነበር፣ አንዳንዴም ለመጸለይ ይንበረከክ ነበር፣ እናም ቢያንስ አንድ ጊዜ ለፀሎት በፊቱ ይወድቅ ነበር።
ሉቃስ፣ የኢየሱስ ስለሃጢያታችን መሠቃየት እና ጭንቀት መሠማት ”ይበልጥ አጥብቆ እንዲጸልይ እንደሚጠይቅበት” ገልጿል። ፍጹም የሆነ አንድ ሰው ይበልጥ አጥብቆ የሚጸልየው እንዴት ነው? ሁሉም ጸሎቶቹ ከልብ የመነጩ እንደነበሩ እናምናለን፣ ነገር ግን የኃጢያት ክፍያን በመፈፀም እና ለእያንዳንዱ ሠው በሚሆነው በተሠሙት ህመሞች ውስጥ፣ የመሥዋዕቱ ህመም በመጨረሻ ደሙም ከእያንዳንዱ የሰውነቱ ቀዳዳ ሲፈስ፤ ከምን ጊዜውም በላይ በፀሎት መማጸን አስፈልጎት ነበር።
ክርስቶስ በሞት ላይ ድልን በማግኘቱ እና በምድር ላይ ለጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት በምድር እንድኖር በቅርቡ ለእኔ በሰጠኝ ስጦታ፣ የዘለአለማዊ ህይወትን እውነተኝነት እና እሱን ስናቅድ በቁም ነገር ማድረጋችን አስፈላጊ እንደሆነ ንጹህ ምስክርነቴ ነው።
ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ፣ —በደበዘዘ የጥምቀት መዝገብ ላይ እንደተዘረዘሩ የአባላት ሥም ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ፣ ታማኝ አማኞች፣ ቃል ኪዳንን የምንጠብቅ ደቀ መዛሙርት እንደሆንን ሊገነዘበን ይገባል። ይህ ለሁላችንም አስቸኳይ ጉዳይ ነው፦ አለበለዚያ “በጭራሽ አላውቃችሁም”፣ ወይም፣ ጆሴፍ ስሚዝ ያንን ሀረግ እንደተረጎመው፣ “[አንተ] በጭራሽ አታውቀኝም”የሚለውን ቃል በሚሠብር ፀፀት እንሠማለን።
እንደ እድል ሆኖ፣ ለዚህ ተግባር እርዳታ አለን—ብዙ እርዳታ። በመላእክት እና በተአምራት እንዲሁም በቅዱስ ክህነት ተስፋዎች ማመን አለብን። በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ፣ በጥሩ ቤተሰቦች እና ጓደኞች ተጽእኖ እንዲሁም በክርስቶስ ንጹህ ፍቅር ሀይል ማመን አለብን። በመገለጥ እና በነቢያት፣ በገላጮች እና በፕሬዚዳንት ራሰል ኤም. ኔልሰን ማመን አለብን። በጸሎታችን እና በተማፅኗችን እንዲሁም በግል ፅድቃችን አማካኝነት፣ እነዚያ መላእክት ወደ “…ፅዮን ተራራ፣ እናም ከሁሉም በላይ ቅዱስ ወደሆነው ሰማያዊ ስፍራ፣ ወደ ህያው እግዚአብሔር ከተማ” ሊመሩን እንደሚችሉ ማመን ያስፈልጋል።
ወንድሞች እና እህቶች፣ ለኃጢአታችን ንሰሀ ስንገባ እና በድፍረት ወደ “ጸጋው ዙፋን” ስንመጣ፣ ምጽዋታችንን እና ልባዊ ልመናችንን በፊቱ ትተን፣ በዘላለም አባታችን እና በታዛዡና ፍጹም ንጹህ በሆነው ልጁ በኩል ምህረት እና ይቅርታ እናገኛለን። ከዚያም፣ ከኢዮብ እና ከተጣሩት ታማኞች ሁሉ ጋር፣ ለመረዳት “ድንቅ ነገር” የሆነውን አለም እናያለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።