አጠቃላይ ጉባኤ
ተነሣ! ይጠራሃል
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


11:22

ተነሣ! ይጠራሃል

ወንጌል ፈተናዎችን እና ችግሮችን ለማስወገድ ሳይሆን እምነታችንን የምናሳድግበት እና እንዴት እንደምንወጣው የምንማርበት ነው።

ከጥቂት ጊዜያት በፊት ባለቤቴን፥ “በህይወታችን ውስጥ እስከማስታውሰው ድረስ ከባድ ችግር ያልደረሰብን ለምን እንደሆነ ልትነግሪኝ ትችያለሽ?” ብዬ ጠየቅኳት።

አየችኝና ፈገግ አለች ከዚያም “ይሁን! ለምን ትልቅ ችግር እንዳልነበረን እነግርሀለሁ፤ ይህም አንተ በጣም አጭር ትዝታ ስላለህ ነው!”

የእርሷ ፈጣን እና ብልህ መልስ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል መኖር ለማደግ አስፈላጊ የሆነውን ህመም እና ፈተናዎችን እንደማያስወግድ እንደገና እንድገነዘብ አደረገኝ።

ወንጌል ፈተናዎችን እና ችግሮችን ለማስወገድ ሳይሆን እምነታችንን የምናሳድግበት እና እንዴት እንደምንወጣው የምንማርበት ነው።

ከጥቂት ወራት በፊት፣ አንድ ቀን በእግሬ ስጓዝ፣ በድንገት እይታዬ ደብዛዛ፣ ጨለማ፣ እና የሚርገበገብ ሲሆን ይህን እውነት አስተምሮኝ ነበር። ፈርቼ ነበር። ከዚያም ሐኪሞች ወዲያው ሕክምና ካልጀመርክ በሳምንታት ውስጥ የማየት ችሎታህን ልታጣ ትችላለህ ብለው ነገሩኝ። ከዚህም የበለጠ ፈራሁ።

እናም እንድሜ ልክህን፣ በየአራት ሳምንቱ በቀጥታ ዓይንህ ላይ መርፌ መወጋት ይኖርብሃል አሉኝ።

ይህ የማይመች የማንቂያ ጥሪ ነበር።

ከዚያም በጥያቄ መልክ አንድ ሃሳብ መጣልኝ። ራሴን እንዲህ ብዬ ጠየቅኩት፥ እሺ! አካላዊ እይታዬ ጥሩ አይደለም፣ መንፈሳዊ እይታዬስ? በዚያስ ሕክምና ያስፈልገኛል? ጥርት ያለ መንፈሳዊ እይታ ማግኘት ሲባልስ ምን ማለት ነው?

በማርቆስ ወንጌል ውስጥ የተገለጸውን በርጠሚዮስ የተባለ ዓይነ ስውር ሰው ታሪክ አሰላሰልኩኝ። ቅዱሳን መፅሀፍት እንደሚሉት፣ “የናዝሬቱ ኢየሱስም እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ፦ ‘የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ፡’” እያለ ይጮኽ ነበር።

በብዙዎች ዘንድ ኢየሱስ የዮሴፍ ልጅ ብቻ ነበር፤ ታዲያ በርጠሚዎስ “የዳዊት ልጅ” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው? ኢየሱስ የዳዊት ዘር ሆኖ እንደሚወለድ ትንቢት የተነገረለት መሲሕ መሆኑን ስለተገነዘበ ብቻ ነው።

ይህ አካላዊ የእይታ ችሎታ ያልነበረው አይነ ስውር፣ ኢየሱስን ማወቁ ትኩረት የሚስብ ነው። እሱ በአካል ሊያየው ያልቻለውን በመንፈስ መመልከት ሲችል፣ ሌሎች ብዙዎች ኢየሱስን በአካል ማየት ቢችሉም በመንፈሳስ ግን ሙሉ በሙሉ ዓይናቸው ታውሮ ነበር።

ከዚህ ታሪክ ጥርት ስላለ መንፈሳዊ እይታ የበለጠ እንማራለን።

“የናዝሬቱ ኢየሱስም እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ፦ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ፡” እያለ ይጮኽ ጀመር”የሚለውን እናነባለን።

በዙሪያው ያሉት ሁሉ ዝም እንዲል ቢነግሩትም ኢየሱስ በእውነት ማን እንደሆነ ያውቅ ስለነበር የበለጠ ጮኸ። እነዚያን ድምፆች ችላ በማለት ድምጹን ከፍ አደረገ።

በሌላው ተፅእኖ እንዳይደርስበት እርምጃ ለመዉሰድ ወሰነ። የእሱ ሁኔታ የሚገድበው ቢሆንም፣ ከአቅሙ በላይ የሆነውን ለማድረግ እምነቱን ተጠቀመ።

ስለዚህ፣ የምንማረው የመጀመሪያው መርህ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ስናተኩርና እውነት መሆኑን ለምናውቀው ነገር ታማኝ ስንሆን ጥርት ያለ መንፈሳዊ እይታ እንደምናገኝ ነው።

ወንድሞችና እህቶች፣ መንፈሳዊ እይታችንን ለመጠበቅ፣ በዙሪያችን ያለውን የዓለምን ድምፅ ላለመስማት መወሰን ይኖርብናል። በዚህ ግራ በሚያጋባ እና ግራ በተጋባ አለም ውስጥ፣ ለምናውቀው ነገር፣ ለቃል ኪዳናችን እና ትእዛዛትን በመጠበቅ ታማኝ ሆነን መኖር ይኖርብናል፣ እንዲሁም ይህ ሰው እንዳደረገው እምነታችንን ይበልጥ በጥንካሬ ማረጋገጥ ይኖርብናል። ለአለም የጌታ ምስክርነታችንን ድምጽ ይበልጥ ከፍ አድርገን ማሰማት አለብን። ይህ ሰው ኢየሱስን አውቆታል፣ ላመነበት ነገር ታማኝ ሆኗል፣ እንዲሁም በዙሪያው ላለው ድምፅ ትኩረት ሳይሰጥ ቀርቷል።

ዛሬ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርነታችን ድምፃችንን ዝቅ ለማድረግ የሚሞክሩ ብዙ ድምፆች አሉ። የአለም ድምጾች እኛን ዝም ለማሰኘት እየሞከሩ ነው፣ ነገር ግን የአዳኛችንን ምስክርነት ድምጻችንን ከፍ በማድረግ በብርታት መናገር ያለብን ለዚህ ነው። በአለም ድምጾች መካከል፣ ጌታ ምስክርነታችንን እንድናውጅ፣ ድምፃችንን ከፍ እንድናደርግ፣ እንዲሁም ድምፁ እንድንሆን በእኔ እና በእናንተ ላይ ይተማመናል። እኛ ካላደረግነው፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ይመሰክራል? ስሙን የሚናገር፣ መለኮታዊ ተልእኮውንም የሚያውጅስ ማን ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቃችን ምክንያት የሚመጣ መንፈሳዊ ሃላፊነት አለብን።

ነገር ግን ከዚያ በኋላ በርጠሚዎስ ምን አደረገ?

ጌታ እንዲነሣ ባዘዘው መሠረት እንደገና በእምነት ተነሳ።

ቅዱሳን መፀሀፍት እንደሚሉት፣ “እርሱም እየዘለለ ተነሣና ልብሱን ጥሎ ወደ ኢየሱስ መጣ።”

ይህ ትሑትና ታማኝ ሰው፣ ኢየሱስ በሰጠው ትእዛዝ የተሻለ ሕይወት መምራት እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር። እሱ ከሁኔታዎቹ የተሻለ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ሲጠራው መጀመሪያ ያደረገው የሚለምንበትን ልብስ አውልቆ መጣል ነበር።

በድጋሚ፣ ዝም ብሎ ከመቀመጥ ይልቅ እርምጃ ለመዉሰድ ወሰነ።

እሱም “አሁን ኢየሱስ ወደ ሕይወቴ ስለመጣ ከአሁን በኋላ ይህ አያስፈልገኝም። ይህ አዲስ ቀን ነው። ይሄ የመከራ ህይወት በቅቶኛል። ከኢየሱስ ጋር አዲስ የደስታ ህይወት፣ በእርሱ እና ለእርሱ ልጀምር እችላለሁ። እና ዓለም ስለእኔ ስለሚያስበው ግድ የለኝም። ኢየሱስ እየጠራኝ ነው፤ አዲስ ሕይወትም እንድኖር ይረዳኛል” ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል።

ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ለውጥ ነው!

የልመና ልብሱን አውልቆ ሲጥል፣ ሁሉንም ሰበብ አስወገደ።

እናም ይህ ሁለተኛ መርህ ነው—ተፈጥሮአዊውን ሰው ትተን፣ ንስሃ ስንገባ፣ እና በክርስቶስ አዲስ ህይወት ስንጀምር ጥርት ያለ መንፈሳዊ እይታ ይኖረናል።

ይህን ማድረግ የምንችለው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አዲስ ህይወት ለመነሳት ቃልኪዳን በመግባት እና በመጠበቅ ነው።

ለራሳችን፣ ለሁኔታችን፣ ለችግሮቻችን፣ በህይወታችን ውስጥ ለሚከሰቱ መጥፎ ነገሮች ሁሉ እንዲሁም ደስተኛ እንዳንሆን ያደረጉን በሚመስሉን መጥፎ ሰዎች ምክንያት ለራሳችን ለማዘን የምንፈጥረውን ሰበብ እስካልተውን ድረስ የልመና ልብስ በትከሻችን ላይ እንለብሳለን። እውነት ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች (ሆን ብለውም ሆነ ሳናውቁ) ይጎዱናል። ነገር ግን ሰበብን ወይም ኃጢያትን ለመደበቅ የለበስነውን የአዕምሮ እና የስሜት ልብስ፣ እርሱ እንደሚፈውሰን በማወቅ አውልቀን በመጣል፣ በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት ለመመላለስ መወሰን አለብን።

“እኔ እንደዚህ የሆንኩት፣ በአንዳንድ አሳዛኝ እና ደስ በማይሉ ሁኔታዎች ምክንያት ነው መለወጥ አልችልም፤ ደግሞም በቂ ምክንያት አለኝ” የሚል ጥሩ ሰበብ በፍጹም የለም።

እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሲኖረን፣ በሌላው ተጽዕኖ እንዲደረግብን እንወስናለን።

የለማኝነትን ልብስ ሳናወልቅ እንቀራለን።

በእምነት መመላለስ ማለት በእርሱ የኃጢያት ክፍያ፣ በእርሱ ትዕዛዝ ከሁሉም ነገር መነሳት እንደምንችል በማመን በአዳኛችን መታመን ማለት ነው።

ሦስተኛው መሠረታዊ ሥርዓት “ወደ ኢየሱስ መጣ” የሚለው የመጨረሻው አራት ቃል ነው።

እርሱ ዓይነ ስውር ስለነበር እንዴት ወደ ኢየሱስ ሊሄድ ይችላል? ብቸኛው መንገድ ድምፁን በመስማት ወደ ኢየሱስ መሄድ ነበር።

እናም ይህ ሦስተኛው መርህ ነው—የጌታን ድምፅ ስንሰማ እና እርሱ እንዲመራን ስንፈቅድ ጥርት ያለ መንፈሳዊ እይታ ይኖረናል።

ይህ ሰው በዙሪያው ባሉት ድምጾች ላይ ድምፁን ከፍ እንዳደረገው ሁሉ፣ በሌሎች ድምጾች መካከል የጌታን ድምፅ ማዳመጥ ችሏል።

ይህም ጴጥሮስ መንፈሳዊ ትኩረቱን በጌታ ላይ በማድረግ እና በዙሪያው ባለው ነፋስ ባለመረበሽ በውኃ ላይ እንዲራመድ ያስቻለው አይነት እምነት ነው።

ከዚያም የዚህ ዐይነ ስውር ሰው ታሪክ “ወዲያውም አየ [ክርስቶስን] በመንገድ ተከተለው” በሚል ቃል ይጠናቀቃል።

በዚህ ታሪክ ውስጥ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ትምህርቶች አንዱ፣ ይህ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እውነተኛ እምነት መለማመዱ እና እርሱን ለመከተል በእውነተኛ ዓላማበእውነተኛ ፍላጎት በመጠየቁ ተአምር እንደተደረገለት ነው።

እናም በህይወታችን የምንቀበላቸው በረከቶች ዋነኛው ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ነው። ይህም እርሱንማወቅ፣ በእርሱ ምክንያት ከእግዚአብሄር ጋር ቃል ኪዳን ማድረግ እና መጠበቅ፣ በእርሱ ተፈጥሮአችንን መቀየር፣ እና እርሱን በመከተል እስከ መጨረሻው ስለመጽናት ነው።

ለእኔ፣ ጥርት ያለ መንፈሳዊ እይታን መያዝ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ማተኮር ነው።

ታዲያ ዓይኔን በመርፌ ስወጋ መንፈሳዊ እይታዬ ጥርት ያለ ሆነ? ይህን ለማለት እኔ ማን ነኝ? ነገር ግን ለማየው ነገር አመስጋኝ ነኝ።

በዚህ ቅዱስ ስራ እና በህይወቴ ውስጥ የጌታን እጅ በግልጽ አያለሁ።

በሄድኩበት ሁሉ የራሴን እምነት የሚያጠነክሩ የብዙዎችን እምነት አያለሁ።

መላዕክትን በዙሪያዬ አያለሁ።

ጌታን በአካል ባማይመለከቱትም ከእርሱ ጋር ቅርበት ስላላቸው በመንፈስ የሚያውቁትን የብዙዎችን እምነት አያለሁ።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁሉም መልስ ነውና ይህ ወንጌል የሁሉም ነገር መልስ እንደሆነ እመሰክራለሁ። አዳኜን ስከተል ላየው ስለምችለው ነገር አመስጋኝ ነኝ።

የጌታን ድምጽ ስንሰማ እና በአዳኝ የቃል ኪዳን መንገድ እንዲመራን ስንፈቅድ በህይወታችን በሙሉ ግልጽ እይታ፣ መንፈሳዊ መረዳት እና የልብ እና የአእምሮ ሰላም እንደምንባረክ ቃል እገባለሁ።

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ መስማት በሚያስፈልገው አለም ውስጥ፣ በዙሪያችን ካሉ ድምፆች የበለጠ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ስለ እርሱ ምስክርነታችንን እናሰማ። አሁንም ለብሰነው ሊሆን የሚችለውን የለማኝን ልብስ እናስወግድ፣ እንዲሁም በክርስቶስ በኩል ወደተሻለ ህይወት ከአለም ከፍ እንበል። ኢየሱስ ክርስቶስን ላለመከተል የምናቀርበውን ሰበብ ሁሉ በማስወገድ፣ ድምፁን ስንሰማ እርሱን ለመከተል በቂ ምክንያቶችን እናግኝ። ይህ ፀሎቴ ነው በእየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።