አጠቃላይ ጉባኤ
በክርስቶስ አንድ ሁኑ
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


15:5

በክርስቶስ አንድ ሁኑ

ለኢየሱስ ክርስቶስ እና ለሃጢያት ክፍያው ባለን ፍቅር እና እምነት አንድ ሆነናል። የአባልነት ዋናው መሰረት በክርስቶስ አንድ መሆን ነው።

ገና ከልጅነቴ ጀምሮ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ጥልቅ ስሜት ይሰማኝ ነበር፣ ነገር ግን የአዳኙ የኃጢያት ክፍያ እውነታ ወደ ውስጤ የገባው በ25 ዓመቴ ነበር። ከስታንፎርድ የህግ ትምህርት ቤት ተመርቄ ለካሊፎርኒያ የጠበቆች መመዘኛ ፈተና እያጠናሁ ነበር። እናቴ ደውላ በዩታ የሚኖሩት አያቴ ክሮዚየር ኪምባል ሊሞቱ እያጣጣሩ እንደሆነ ነገረችኝ። ላያቸው የምፈልግ ከሆነ ወደ ቤት ብመጣ እንደሚሻለኝ ነገረችኝ። አያቴ የ86 አመት እድሜ የነበራቸው ሲሆን በጠና ታመው ነበር። በጣም አስደናቂ ጉብኝት አደረኩ። እኔን በማየታቸው እና ምስክርነታቸውን በማካፈላቸው በጣም ተደሰቱ።

ክሮዚየር ገና የሦስት ዓመት ልጅ እያለ አባቱ ዴቪድ ፓተን ኪምባል በ44 አመቱ አረፈ። ክሮዚየር አባቱ እና አያቱ ሄበር ሲ. ኪምቦል፣ ለህይወቱ ቦታ እንደሚሰጡ እና ለውርሱ ታማኝ እንደነበር እንደሚሰማቸው ተስፋ አድርጎ ነበር።

አያቴ የሠጡኝ ዋነኛ ምክር፣ በእነዚህ ታማኝ ቅድመ አያቶች ምክንያት ሊገኝ የሚችልን ማንኛውንም የመብት ወይም የይገባኛል ስሜት እንዳስወግድ ነበር። ትኩረቴ በአዳኙ እና በአዳኙ የሀጢያት ክፍያ ላይ መሆን እንዳለበት ነገሩኝ። ሁላችንም የአንድ አፍቃሪ የሰማይ አባት ልጆች ነን ሲሉ ተናግረዋል። ምድራዊ ቅድመ ዓያቶቻችን ማንም ይሁኑ ማን፣ እያንዳንዳችን ትዕዛዛቱን ምን ያህል እንደጠበቅን ለአዳኙ መልስ እንሠጣለን።

አያቴ አዳኙን “መግቢያውን ጠባቂ” 2 ኔፊ 9፡41በማለት ይጠሩት ነበር። ለአዳኙ ምሕረት ብቁ ለመሆን በበቂ ሁኔታ ንስሃ እንደገቡ ተስፋ እንደሚያደርጉ ነገሩኝ።

በጣም ተነካሁ። ጻድቅ ሰው እንደነበሩ አውቅ ነበር። ፓትርያርክ የነበሩ ሲሆኑ በብዙ ሚስዮኖችም አገልግለዋል። ማንም ሰው ከአዳኙ የሀጢያት ክፍያ እርዳታ ውጭ፣ በመልካም ስራ ብቻ ወደ እግዚአብሔር ሊመለስ እንደማይችል አስተምረውኛል። አያቴ ለአዳኙ እና ለኃጢያት ክፍያው የነበራቸውን ታላቅ ፍቅር እና አድናቆት እስከ ዛሬ ድረስ ማስታወስ እችላለሁ።

በ2019 (እ.አ.አ.) በኢየሩሳሌም በተመደብኩበት ወቅት፣ አዳኙ ከሥቅለቱ በፊት የሐዋርያቱን እግር ያጠበበት ቦታ አቅራቢያ ሊሆን የሚችለውን በደርብ ላይ ያለውን ክፍል ጎበኘሁ። በመንፈስ ተነካሁ እንዲሁም ሐዋርያቱ እርስ በርሳቸው እንዴት እንዲዋደዱ እንዳዘዛቸው አሰብኩ።

በእኛ ምትክ አዳኙ ያደረገውን የተማፅኖ የምልጃ ጸሎት አስታወስኩ። በዮሐንስ ወንጌል እንደተመዘገበው፣ ይህ ጸሎት ቃል በቃል በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ሰዓታት ላይ የተደረገ ነበር።

እኛን ሁላችንን ጨምሮ የክርስቶስ ተከታዮችን አስመልክቶ የቀረበ ጸሎት ነበር። አዳኙ አባቱን፣ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፣ … በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፣ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ” በማለት ተማፅኗል። ከዚያም አዳኙ በመቀጠል፣ “እኛም አንድ እንደሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ … የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ”በማለት ተናግሯል። ክርስቶስ አሳልፎ ከመሠጠቱ እና ከመሰቀሉ በፊት የጸለየው ስለአንድነት ነበር። ከክርስቶስ እና ከሰማይ አባታችን ጋር አንድነት ሊገኝ የሚችለው በአዳኙ የሀጢያት ክፍያ አማካኝነት ነው።

የጌታ የማዳን ምሕረት በቅድመ አያቶቻችን፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ ደረጃ ወይም በዘር ላይ የተመሰረተ አይደለም። ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆን እና በትዕዛዛቱ ላይ የተመሰረተ ነው።

ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እና ኦሊቨር ካውደሪ በ1830 (እ.አ.አ) የቤተክርስቲያኗን አደረጃጀት እና አመራር የተመለከተ ራዕይን የተቀበሉት ቤተክርስቲያኗ ከተደራጀች ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ነበር። አሁን ክፍል 20 የሆነው በመጀመሪያው የቤተክርስቲያኗ ጉባኤ ላይ በነቢዩ ጆሴፍ የተነበበ ሲሆን፣ በጋራ ስምምነት የጸደቀ የመጀመሪያው ራዕይ ነበር።

የዚህ ራዕይ ይዘት በእውነት አስደናቂ ነው። የአዳኙን የኃጢያት ክፍያ አስፈላጊነት እና ሚና እንዲሁም ኃይሉን እና በረከቶቹን በኃጢያት ክፍያው ጸጋ አማካኝነት እንዴት ማግኘት እንደምንችል ያስተምረናል። ነቢዩ ጆሴፍ የ24 ዓመት ልጅ በነበረበት ጊዜ ብዙ ራዕዮችን ተቀብሎ የነበረ ሲሆን የመፅሐፈ ሞርሞንን ትርጉም በእግዚአብሔር ስጦታ እና ሀይል አጠናቆ ነበር። ጆሴፍ እና ኦሊቨር የተሾሙ ሐዋርያት ተብለው ተለዩ ስለሆነም ቤተክርስቲያንን የመምራት ስልጣን ነበራቸው።

ቁጥር 17 እስከ 36 የእግዚአብሔርን መኖር፣ የሰውን ልጅ አፈጣጠር፣ ውድቀትን እና በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ አማካኝነት የሚገኘውን የሰማይ አባት የማዳን ዕቅድ ጨምሮ የቤተክርስቲያኗን አስፈላጊ አስተምህሮቶች ማጠቃለያ ይዟል። ቁጥር 37 በጌታ ቤተክርስቲያን ለመጠመቅ አስፈላጊ የሆኑትን መስፈርቶች ይዟል። ቁጥር 75 እስከ 79 በየሰንበቱ የምንጠቀማቸውን የቅዱስ ቁርባን ጸሎቶችን ይዘዋል።

ጌታ በዳግም መመለሱ ነቢይ በጆሴፍ ስሚዝ በኩል ያቋቋመው ትምህርት፣ መርሆዎች፣ ቅዱስ ቁርባን እና ልምምዶች በእውነት ትልቅ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ናቸው።

ለመጠመቅ የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ጥልቅ ቢሆኑም፣ በተለየ ሁኔታ ቀላል ናቸው። እነሱም በዋናነት በእግዚአብሔር ፊት ትህትናን፣ የተሰበረ ልብን እና የተዋረደ መንፈስን፣ለሀጢያት ሁሉ ንስሀ መግባትን፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በላያችን ላይ መውሰድን፣ እስከ መጨረሻው መጽናትን እና የክርስቶስን መንፈስ እንደተቀበልን በሥራችን ማሳየትን ያካትታሉ።

ሁሉም የጥምቀት መመዘኛዎች መንፈሳዊ መሆናቸው ጠቃሚ ነው። ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ስኬት አያስፈልግም። ለሃብታምም ለድሃም ያለው መንፈሳዊ መስፈርት አንድ ዓይነት ነው።

የዘር፣ የጾታ ወይም የጎሳ መስፈርቶች የሉም። መፅሐፈ ሞርሞን፣ሁሉም “ለእግዚአብሔር አንድ ናቸው … ጥቁርም ነጭም፣ ባሪያውና ነፃው፤ ሴትና ወንድ”የጌታን መልካምነት እንዲካፈሉ እንደተጋበዙ ግልጽ አድርጎ ያስቀምጣል። “ሁሉም ሰው እንደሌላው ታድሏል፣ እናም ማንም አልተከለከለም።

በእግዚአብሔር ፊት “ተመሳሳይ” ስለሆንን ልዩነቶቻችንን ላይ ማተኮር ምንም ትርጉም አይሰጥም። አንዳንዶች “ሰዎች ከእኛ እንዲሁም አንዳቸው ከሌላው በጣም የተለዩ እንደሆኑ አድርገን እንድናስብ በተሳሳተ መንገድ አበረታተውናል። [አንዳንዶች] ተጨባጭ ነገር ግን ትናንሽ ልዩነቶችን ወስደው ያገዝፏቸዋል።”

በተጨማሪም አንዳንድ ሰዎች፣ ሁሉም የእርሱን ቸርነት እና የዘላለም ሕይወት ይቀበሉ ዘንድ ስለተጋበዙ ምንም ዓይነት የሥነ ምግባር መስፈርቶች እንደማያስፈልጉ በማሰብ ይሳሳታሉ።

ነገር ግን፣ ቅዱሳት መጻህፍት ሁሉም በተጠያቂነት እድሜ ላይ የደረሱ ሰዎች፣ ለሃጢያታቸው ንስሀ መግባት እና ትዕዛዛቱን መጠበቅ እንዳለባቸው ያረጋግጣሉ። ጌታ ሁሉም የሥነ ምግባር ነጻ ምርጫ እንዳላቸው እና “በሚማልደው አማካኝነት ነጻነትን ወይም ዘላለማዊ ህይወትን ለመምረጥ፣ …እና ታላቅ ትዕዛዛቱን [እንዲሠሙና] የዘላለም ህይወትን …[እንዲመርጡ]”በማለት ግልጽ ያደርገዋል። የአዳኙን የኃጢያት ክፍያ በረከቶች ለመቀበል፣ ክርስቶስን ለመምረጥ እና ትዕዛዙን ለመጠበቅ ያለንን ነጻ ምርጫ በአዎንታዊ ሁኔታ መጠቀም አለብን።

በህይወት ዘመኔ፣ “የነጻ ምርጫ” እና “የነጻ ፈቃድ” ትርጉም በዝርዝር ተጠንቷል እንዲሁም ክርክር ተደርጎበታል። በእነዚህ ርዕሶች ላይ ብዙ ምሁራዊ ክርክሮች ተደርገዋል፣ አሁንም መደረጋቸውን ይቀጥላሉ።

በቅርቡ አንድ ታዋቂ የባዮሎጂ ፕሮፌሰር፣ በአንድ ትልቅ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎች ህትመት ሽፋን ላይ “ለነፃ ፈቃድ የሚሆን ቦታ የለም” በማለት ተከራክረዋል። በማያስደንቅ ሁኔታ በህትመቱ ላይ “እግዚአብሄር የሚባል ነገር የለም፣ … ነጻ ፈቃድም የለም፣ እንዲሁም ይህ ሰፊ፣ ግድ የሌለው፣ ባዶ አጽናፈ ዓለም ነው” እንዳሉም ተጠቅሷል። ፈጽሞ የማልስማማበት ነገር ነው።

የእምነታችን መሰረታዊ አስተምህሮ፣ነጻ ፈቃድን የሚያካትት ነጻ ምርጫ እንዳለን፣ ነው። ነጻ ምርጫ የመምረጥ እና የመተግበር ችሎታ ነው። ለደህንነት ዕቅድ አስፈላጊ ነው። ከሥነ ምግባር ነጻ ምርጫ ውጭ፣ መማር፣ መሻሻል ወይም በክርስቶስ አንድ ለመሆን መምረጥ አንችልም። በሥነ ምግባር ነጻ ምርጫ ምክንያት “ነፃነትን እና ዘለዓለማዊ ህይወትን”ለመምረጥ ነጻ ነን። በሰማይ በነበረው ቅድመ ምድራዊ ጉባኤ፣ ነጻ ምርጫ የአብ ዕቅድ አስፈላጊ አካል በመሆን ተካትቶ ነበር። ሉሲፈር አመፀ እንዲሁም “የሰውን ነጻ ምርጫ [ለማጥፋት ፈለገ]።” በዚህ መሠረት ምድራዊ አካል የማግኘት እድል ለሰይጣንና ለተከተሉት ሰዎች ተነፈገ።

ሌሎች የቅድመ ምድራዊ መንፈሶች የሰማይ አባትን ዕቅድ የመከተል ነጻ ምርጫቸውን ተጠቀሙ። ወደዚህች ምድር በመወለድ የተባረኩ መንፈሶች አሁንም ነጻ ምርጫቸውን ይዘው ይቀጥላሉ። ውጤቱን መቆጣጠር ባንችልም የመመምረጥ እና የመተግበር ነፃነት አለን። “የመልካም እና የጽድቅ ምርጫዎች ወደ ደስታ፣ ወደ ሰላም እና ወደ ዘለዓለማዊ ህይወት፣ እንዲሁም የኃጢአት እና የክፋት ምርጫዎች ደግሞ በመጨረሻ ወደ ልብ ሀዘን እና ስቃይ ይመራሉ።” አልማ እንደተናገረው፣ “ክፋት በፍጹም ደስታ ሆኖ አያውቅም።”

በዚህ እጅግ ፉክክር በሞላበት ዓለም ውስጥ፣ ከሁሉም የተሻሉ ለመሆን የማያቋርጥ ጥረት ይደረጋል። የምንችለውን ያህል ምርጥ ለመሆን መጣር ጻድቅ እና ዋጋ ያለው ጥረት ነው። ከጌታ ትምህርት ጋር የሚሄድ ነው። ሌሎችን ለማሳነስ ወይም ዝቅ ለማድረግ ወይም ለስኬታቸው እንቅፋት ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች ከጌታ ትምህርት ጋር ይቃረናሉ። የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በመፃረር ለተደረገ ውሳኔ ሁኔታዎችን ወይም ሌሎችን መውቀስ አንችልም።

በዛሬው ዓለም፣ በቁሳዊ እና በሙያዊ ስኬት ላይ ማተኮር ቀላል ነው። አንዳንዶች ዘላለማዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የዘለዓለማዊ መርሆች እና ምርጫዎች ዕይታን ያጣሉ። የፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰንን “ስለ ሰለስቲያል አስቡ”የሚለውን ምክር ብንከተል ብልሆች እንሆናለን።

ተሰጥኦዎች፣ ችሎታዎች፣ ዕድሎች ወይም ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ምንም ይሁኑ ምን በጣም ጉልህ የሆኑ ምርጫዎች በሁሉም ሰዎች ሊደረጉ ይችላሉ። የቤተሰብ ምርጫዎችን በማስቀደም ላይ ማተኮር አስፈላጊ ነው። ይህ በመላው ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል። በ1 ኔፊ ያለውን ሌሂ ወደ ምድረ በዳ የሄደበትን ታሪክ አስቡ። “ቤቱን፣ የወረሰውን መሬት፣ ወርቁንና ብሩን፣ ውድና የከበሩ ነገሮቹን ተወ፣ እንዲሁም ከቤተሰቡ [ውጪ]… ከእርሱ ጋር ምንም ሳይወስድ ወደ ምድረበዳ ሄደ”የሚለውን በኔፊ ውስጥ የሚገኘውን ታሪክ አስቡ።

የህይወትን ውጣ ውረዶች ስንጋፈጥ፣ ብዙ ከቁጥጥራችን ውጪ የሆኑ ሁኔታዎች ይከሰታሉ። የጤና እክሎች እና አደጋዎች ያለጥርጥር ወደዚህ ምድብ ሊካተቱ ይችላሉ። በቅርቡ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁሉንም ነገር በትክክል በሚሠሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በጣም አስፈላጊ የሆኑ ምርጫዎችን መቆጣጠር እንችላለን። ወደ ሚሲዮናዊነት ዘመኔ ስመለስ፣ የሚስዮን ፕሬዚዳንታችን ሽማግሌ ማሪዮን ዲ.ሃንክስ፣ ሁላችንም በኤላ ዊለር ዊልኮክስ የተጻፈን ግጥም በከፊል በቃላችን እንድንይዝ አድርጎናል፡-

የቆራጥ ነፍስን ጽኑ ውሳኔ

የትኛውም አጋጣሚ፣ ዕድል፣ እጣ ፈንታ

ሊያሸንፍ ወይም ሊያደናቅፍ ወይም ሊቆጣጠር አይችልም።

መርህን፣ ምግባርን፣ የሃይማኖት ሥርዓት አጠባበቅን እና የጽድቅ አኗኗርን በተመለከተ እኛ ቁጥጥር ማድረግ እንችላለን። በእግዚአብሔር አብ እና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት እና አምልኮ፣ እኛ የምናደርገው ምርጫ ነው።

እባካችሁ እኔ ለትምህርት ወይም ለስራ ያለን አነስተኛ ፍላጎት እየደገፍኩ እንዳልሆነ ተረዱ። እኔ እያልኩ ያለሁት፣ በትምህርት እና በስራ ላይ የሚደረጉ ጥረቶች፣ ከቤተሰብ ወይም ከክርስቶስ ጋር አንድ ከመሆን በላይ ከፍ ሲሉ የሚመጡ ያልተጠበቁ ውጤቶች በጣም ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ ነው።

ትምህርቶች እና ቃል ኪዳኖች 20 ላይ የተቀመጠው ግልጽ እና ቀላል አስተምህሮ፣ የተቀደሱ መንፈሳዊ ፅንሰ ሀሳቦችን ሲያጎላ እና ሲያብራራ ልብ የሚነካ እና የሚስብ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ንስሃ የገቡ ነፍሳትን ሲያጸድቅ እና ሲያነጻ በአዳኙ ጸጋ ምክንያት መዳን እንደሚመጣ ያስተምራል። ለኃጢያት ክፍያው የላቀ ሚና መድረኩን ያዘጋጃል።

ሌሎችን በአንድነት ክበባችን ውስጥ ለማካተት መጣር አለብን። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን፣ በመጋረጃው በሁለቱም በኩል የተበተኑትን እስራኤል እንድንሠበሥብ የሠጡትን ማሣሠቢያ ለመከተል የምናስብ ከሆነ፣ ሌሎችን በአንድነት ክበባችን ውስጥ ማካተት መቻል አለብን። ፕሬዚዳንት ኔልሰን በሚያምር ሁኔታ እንዳስተማሩት፡ “በሁሉም አህጉር እንዲሁም በባህር ደሴቶች ላይ፣ ታማኝ ሰዎች ወደ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን እየተሰበሰቡ ነው። ታማኞች ወደ ቃል ኪዳኑ መንገድ ሲገቡ እና ወደተወደደው ቤዛችን ሲመጡ የባህል፣ የቋንቋ፣ የጾታ፣ የዘር እና የብሔር ልዩነቶች እየጠፉ ይሄዳሉ።”

ለኢየሱስ ክርስቶስ ባለን ፍቅር እና እምነት እንዲሁም የአፍቃሪ የሰማይ አባት ልጆች በመሆናችን አንድ ነን። የአባልነት ዋናው መሰረት በክርስቶስ አንድ መሆን ነው። በ ትምህርት እና በቃል ኪዳኖች 20ላይ የተገለጹት የጥምቀት እና የቅዱስ ቁርባን ሥርዓቶች፣ ከቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖቻችን ጋር በመሆን በልዩ መንገድ እንዲሁም በእያንዳንዱ ለዘላለም ጉልህ በሆነ መንገድ አንድ እንድንሆን እና በሰላም እና በስምምነት እንድንኖር ያስችሉናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፣ እንዲሁም በኃጢያት ክፍያው ምክንያት፣ በክርስቶስ አንድ መሆን እንደምንችል እመሰክራለሁ። በተቀደሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ዴቪድ፣ በ17 ዓመቱ፣ አንዳንድ ቅዱሳን በዋዮሚንግ ከፍ ያሉ ሜዳዎች ላይ ያለረዳት በቆሙ ጊዜ በበረዶ የተሞላውን የስዊትዋተር ወንዝ እንዲሻገሩ ረድቷቸዋል ( ቅዱሳን፤ የኋለኛው ቀን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ታሪክ, መጽሃፍ 2፣ No Unhallowed Hand, 1846–1893 1846-1893 (እ.አ.አ) [2020 (እ.አ.አ)]፣ 237)።

  2. ሞሮኒ 7፥27–28ን ይመልከቱ።

  3. የኖርዌይ ዋና የአይሁድ አስተማሪ፣ ረቢ ሚካኤል ሜልቺር፣ እና እኔ ሰኔ 5፣ 2019 (እ.አ.አ) ላይ በእስራኤል በሚገኘው BYU እየሩሳሌም ሴንተር በተካሄደው የአይሁድ–የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ምሁር ንግግር ላይ ዋና ተናጋሪዎች ነበርን።

  4. ዮሀንስ 17:20ይመልከቱ።

  5. ዮሐንስ 17:21–22

  6. “The Conference Minutes and Record Book of Christ’s Church of Latter Day Saints, 1838–1839, 1844” (commonly known as the Far West Record), June 9, 1830, Church History Library, Salt Lake City; Steven C. Harper, Making Sense of the Doctrine and Covenants (2008), 75.

  7. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20 በቤተክርስትያኗ መጽሄት ለመታተም የመጀመሪያው መገለጥ ሲሆን ለጥምቀት እና ለቅዱስ ቁርባንን ስርዓቶች አስተምህሮት እና አስተዳደር ምስዮናውያን ይጠቀሙት ነበር(ሃርፐር፣ Making Sense of the Doctrine and Covenants፣ 75 ይመልከቱ)።

  8. 2 ኔፊ 2፥7 ይመልከቱ።

  9. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፥37ይመልከቱ።

  10. 2 ኔፊ 26፥33

  11. 2 ኔፊ 26፥28

  12. ፒተር ዉድ Diversity: The Invention of a Concept (2003), 20.

  13. ኔሆር ይህን አቋም ያዘ (አልማ 1:4 ይመልከቱ)።

  14. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 29፥49–50ይመልከቱ።

  15. 2 ኔፊ 2፥27–28

  16. Stanford (publication of the Stanford Alumni Association), Dec. 2023, cover.

  17. ሳም ስኮት “As If You Had a Choice,”Stanford ታህሳስ፣ 2023 (እ.አ.አ)፣ የፊት ገጽ 44። ጽሑፉ ፕሮፌሰር ሮበርት ሳፖልስኪ፣ የስታንፎርድ የባዮሎጂ፣ ኒውሮሎጂ እና የነርቭ ቀዶ ሕክምና ፕሮፌሰር እና የሳይንስ መጽሃፍትን ታዋቂ ደራሲ መሆናቸውን ይገልጻል። በፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ፕሮፌሰር የሆኑት፣ በነጻ ፈቃድ ላይ ትልቁን የጆን ቴምፕልተን ፋውንዴሽን ፕሮጀክትን ይመራ የነበረውን አልፍሬድ ሜሌን ጨምሮ የተቃራኒ አመለካከቶችን ይህ ጽሁፍ ይዟል። “ሳይንቲስቶች ነጻ ፈቃድ—በጉጉት የሚደረጉትንም ጨምሮ—የተሳሳተ እምነት እንደሆኑ አላረጋገጡም” ብሏል (iበስኮት “As If You Had a Choice,” 46)።

  18. ዲ ቶድ ክርስቶፈርሰን “Moral Agency” (Brigham Young University devotional, Jan. 31, 2006).

  19. ትምህርት እና ቃል ኪዳን 58፥27ይመልከቱ።

  20. 2 ኔፊ 2፥27

  21. ሙሴ 4፥3

  22. True to the Faith: A Gospel Reference (2004 (እ.አ.አ))፣ 12።

  23. አልማ 41፥10

  24. ራስል ኤ. ኔልሰን፣ “ስለ ሰለስቲያል አስቡ!፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2023 (እ.አ.አ)፣ 117–20።

  25. 1 ኔፊ 2፥4

  26. Poetical works of Ella Wheeler Wilcox (1917 (እ.አ.አ))፣ 129.

  27. ይህንን በጣም አጭር በሆነ መንገድ የገለጸውን በሽማግሌ ኒል ኤ. ማክስዌል የተነገረውን ጥቅስ ሁል ጊዜም እወድ ነበር፡ “የእግዚአብሔርን መንግስት ካልመረጣችሁ፣ በመጨረሻ በምትኩ የመረጣችሁት ምንም ለውጥ አያመጣም” (ለ18ኛው ክፍለ ዘመን የእንግሊዝ ቄስ ለዊልያም ሎው፣ በኒል ኤ. ማክስዌል፣“Response to a Call,” ኢንዛይን፣ ግንቦት 1974 (እ.አ.አ)፣ 112 የተጠቀሰ)።

  28. ትምህት እና ቃል ኪዳኖች 6፥29–31 ይመልከቱ። የካልቪኒዝም ሥነ-መለኮት፣ የወደቁ ነፍሳትን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ማጽደቅ እና ማንጻት ላይ አጽንዖት ይሰጣል። እግዚአብሔር አስቀድሞ ነፍስን ለማዳን ከወሰነ፣ በኋላ ውጤቱን ምንም ነገር ሊቀይረው እንደማይችል ያስተምራል። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20 ከካልቪኒዝም ጋር ያለንን ልዩነት በግልጽ ያሳያል። “ሰው ከጸጋ ወድቆ ከህያው እግዚአብሄር ለመለየት የሚያስችለው ሁኔታም አለ” ይላል ( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፥32–34፤ በተጨማሪም ሃርፐር፣ Making Sense of the Doctrine and Covenants፣ 74 ይመልከቱ)።

  29. ረስል ኤም. ኔልሰን፣ “Building Bridges ሊያሆና፣ታህሳስ 2018 (እ.አ.አ)፣ 51።