ስላየኋቸውና ስለሰማኋቸው ነገሮች ታሪክ መዝገብ
የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል ለመሆን ከዛሬ የተሻለ ጊዜ እንደሌለ እመሰክራለሁ።
ከህግ ትምህርት ቤት ከተመረቅኩ በኋላ ባለቤቴ ማርሲያ እና እኔ ወደ ፍርድ ቤት በሚላኩ የህግ ጉዳዮች የተካነ የሕግ ድርጅትን ለመቀላቀል መረጥን። የሥራ ላይ ሥልጠናዬን ስጀምር፣ ብዙ ጊዜዬን በችሎት ላይ ቃል የሚሰጡ ምስክሮችን በማዘጋጀት አሳለፍኩኝ። ምስክሮች ቃለ መሃላ በመፈፀም ያዩትና የሰሙትን እውነትነት ሲመሰክሩ፣ እውነት በፍርድ ቤት ውስጥ እንደሚወሰን ወዲያውኑ ተረዳሁኝ። ምስክሮች ሲመሰክሩ፣ ቃላቶቻቸው ይመዘገባሉ ከዚያም ይቀመጣሉ። የታማኝ ምስክሮች አስፈላጊነት በዝግጅቴ ሁልጊዜ ቀድሞ የሚመጣው ነገር ነበር።
በየእለቱ እንደ ጠበቃ የምጠቀምባቸው ተመሳሳይ ቃላት በወንጌል ውይይቶቼ ውስጥ የምጠቀምባቸው ቃላት መሆናቸውን ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልወሰደብኝም። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እውነትነት ያለንን እውቀት እና ስሜቶች ስናካፍል የምንጠቀምባቸው “ምስክር” እና “ምስክርነት” የሚሉት ቃላት ናቸው።
አዲስ የአካባቢ ሰባ ሆኜ ድጋፍ በተሠጠኝ ጊዜ ስላሉብኝ ሃላፊነቶች ለማወቅ ቅዱሳት መጻህፍትን ከፈትኩኝና፣ “ሰባዎቹ፣ ለአህዛብና በአለም ሁሉ ልዩ ምስክሮች እንዲሆኑ ተጠርተዋል” የሚለውን በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 107፥25 ውስጥ አነበብኩኝ። ልትገምቱ እንደምትችሉት፣ ዓይኖቼ “ልዩ ምስክር” ወደሚለው ቃል ተሳበ። በአለም ዙሪያ በሄድኩበት ቦታ ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም የመመስከር ሃላፊነት እንዳለብኝ ግልፅ ሆነልኝ።
የዓይን እማኞች የነበሩ እንዲሁም ስላዩት እና ስለሰሙት የመሰከሩ የብዙ ሰዎች ምሳሌዎች በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ይገኛል።
የጥንቱ ነቢይ ሞርሞን መዝገቡን ሲጀምር እንዲህም ሲል ጽፏል፣ “እናም እንግዲህ እኔ ሞርሞን፣ ስላየኋቸውና ስለሰማኋቸው ነገሮች ታሪክ ፃፍኩ፣ እናም መፅሐፈ ሞርሞን ብዬ ጠራሁት።”
የአዳኙ ሐዋርያት የሆኑት ጴጥሮስ እና ዮሐንስ አንድን ሰው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ፈወሱ። በኢየሱስ ስም እንዳይናገሩ በታዘዙ ጊዜ፣ እንዲህ ብለው መለሱ፦
“እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤
“እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም።”
ሌላኛው አሳማኝ ምስክርነት የመጣው የአዳኙን የኢየሱስ ክርስቶስን ጉብኝት ከተመለከቱት የመፅሐፈ ሞርሞን ቅዱሳን መካከል ነው። እነርሱ በምስክርነት የገለጹትን አዳምጡ፦ “እናም በዚህም ሁኔታ መስክረዋል፦ ከዚህ በፊት ዐይን ያላየውን፣ ጆሮም ያልሰማውን፤ ኢየሱስ ወደ አብ ሲናገር ያየናቸው እናም የሰማናቸው ነገሮች ታላቅና አስደናቂ ነገሮችን ነው።”
ወንድሞች እና እህቶች፣ ዛሬ ምስክርነቴን እሠጣለሁ እንዲሁም የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰባ አባል እንደመሆኔ በተቀደሰው አገልግሎት ውስጥ ስላየኋቸውና ስለሰማኋቸው ነገሮች እመዘግባለሁ። ይህንንም በማድረግ ስለ አፍቃሪው የሰማይ አባት እና ለእግዚአብሄር ልጆች የዘለዓለም ሕይወትን ለመስጠት መከራን ስለተቀበለው፣ ስለሞተው እና ከሞት ስለተነሣው ስለቸር ልጁ ስለኢየሱስ ክርስቶስ እመሰክርላችኋለሁ። ስለ “ታላቅ እና ድንቅ ሥራ” እንዲሁም ጌታ በሕይወት ባሉ ነቢያቱ እና ሐዋርያት በኩል ወንጌሉን በምድር ላይ ዳግም ይመልስ ዘንድ እጁን እንደገና እንደዘረጋ እመሰክራለሁ። ባየሁት እና በሰማሁት መሠረት፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል ለመሆን ከዛሬ የተሻለ ጊዜ እንደሌለ እመሰክራለሁ። ይህንንም የማውቀው ከሌላ ምንጭ ሳይሆን፣ ካየሁትና ከሰማሁት ካለኝ እውቀት በመነሣት ነው።
በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጨረሻ ዓመት ላይ እያለሁ፣ ከሴሚናሪ ለመመረቅ፣15ቱንም የቤተክርስቲያኗን ቤተመቅደሶች ማወቅ ነበረብኝ። የእያንዳንዱ ቤተመቅደስ ምሥል በክፍላችን ፊት ለፊት ነበር፣ እናም እያንዳንዱ የት እንደሚገኝ ማወቅ ነበረብኝ። አሁን፣ ከዓመታት በኋላ፣ 335 በስራ ላይ ያሉና የተዋወቁ ቤተመቅደሶችን እያንዳንዳቸውን ማወቅ ትልቅ ፈተና ነው። እኔ በግሌ እነዚህን ብዙዎቹን የጌታ ቤቶች አይቻለሁ እንዲሁም ጌታ በረከቶቹን እና ሥርዓቶቹን በዓለም ዙሪያ ላሉ ለበርካታ ልጆቹ እንደሚያቀርብ እመሰክራለሁ።
በFamilySearch ውስጥ የሚሰሩ ጓደኞቼ በየቀኑ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ስሞችን ወደ FamilySearch እንደሚያክሉ አስተምረውኛል። ትናንት ቅድመ አያታችሁን ለማግኘት ካልቻላችሁ ነገ ደግማችሁ እንድትመለከቱ እጋብዛችኋለሁ። ከመጋረጃው በስተጀርባ ያለውን እስራኤል መሰብሰብን አስመልክቶ፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል ለመሆን ከዛሬ የተሻለ ጊዜ እንደሌለ እመሰክራለሁ።
ልጆቻችንን በትዊን ፎልስ፣ አይደሆ ስናሳድግ፣ ስለ ዓለም አቀፉ ቤተ ክርስቲያን ያለን አመለካከት ውስን ነበር። አጠቃላይ ባለሥልጣን እንድሆን በተጠራሁ ጊዜ እኔና ማርሲያ ሄደንበት በማናውቀው በፓስፊክ አካባቢ እንድናገለግል ተመደብን። በ1958(እ.አ.አ) የተመረቀውን ቤተ መቅደስ ጨምሮ በኒው ዚላንድ ከላይ ጫፍ እስከ ታች ካስማዎችን በማግኘታችን ተደሰትን። በሴሚናሪ ውስጥ ማስታወስ ከነበረብኝ ከ15ቱ ቤተ መቅደሶች አንዱ ነበር። በሁሉም የአውስትራሊያ ትልቅ ከተሞች ውስጥ ቤተመቅደሶችን አገኘን፣ በዚያም አህጉር ውስጥ ካስማዎች በየቦታው ነበሩ። 25 ካስማዎች ባሉበት ሳሞአ፣ እና ግማሽ ያህሉ ህዝብ የቤተክርስቲያኗ አባላት በሆኑበት በቶንጋ የሥራ ምደባ ተሠጥቶን ነበር። በኪሪባቲ ደሴት እንድናገለግልም የሥራ ምደባ ተሠጥቶን ነበር፣ በዚያም ሁለት ካስማዎችን መሰረትን። በማርሻል ደሴቶች ውስጥ በሚገኘው ኢቤዬ እና በፓፑዋ ኒው ጊኒ የሚገኘውን ዳሪን የመጎብኘት የሥራ ምደባ ተሠጥቶንም ነበር።
በፓስፊክ ደሴቶች ካገለገልን በኋላ በፊሊፒንስ እንድናገለግል ተመደብን። ይግረምህ ብሎ፣ በፊሊፒንስ የምትገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ከተገነዘብኩት በላይ እያደገች ነው። አሁን 125 ካስማዎች፣ 23 ሚስዮኖች እና 13 የተተዋወቁ ቤተመቅደሶች አሉ። በዛ ሀገር ውስጥ ከ850,000 በላይ አባላት ያሏትን ቤተ ክርስቲያን ተመልክቻለሁ። በዓለም ዙሪያ ያለውን የክርስቶስ ቤተክርስቲያን መስፋፋት እንዴት አላወኩም?
በፊሊፒንስ ሶስት አመት ካሳለፍኩኝ በኋላ፣ በሚስዮን ክፍል እንዳገለግል ተጠየቅኩኝ። የስራ ምድቤ በዓለም ዙሪያ ወዳሉ ሚስዮኖች ወሰደን። የአዳኙን አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን በተመለከተ ያለኝ እይታ በፍጥነት አደገ። እኔና ማርሲያ በእስያ ሚሲዮኖችን እንድንጎበኝ ተመደብን። በሲንጋፖር ውስጥ አስደናቂ እና ታማኝ አባላት ያሉት የሚያምር የካስማ ማዕከል አገኘን። በኮታ ኪናባሉ፣ ማሌዥያ በሚገኘው የጸሎት ቤት አባላትን እና ሚስዮናውያንን ጎበኘን። በሆንግ ኮንግ ከሚስዮናውያን ጋር ተገናኘን እንዲሁም ከታማኝ ቅዱሳን ጋር በሚያስደንቅ የካስማ ኮንፈረንስ ላይ ተሳተፍን።
በመላው አውሮፓ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በካሪቢያን እና በአፍሪካ ካሉ ሚስዮናውያን እና አባላት ጋር ስንገናኝ ይህንን ተሞክሮ ደጋግሞ ይከሠት ነበር። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በአፍሪካ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበች ነው።
በመከናወን ላይ ያለውን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ዳግም መመለስ እና የጌታ ነቢይ፣ “የእግዚአብሔር እውነት በድፍረት፣ በግርማ፣ በገለልተኝነት፣ በሁሉም አህጉራት ዘልቆ እስኪገባ፣ ሁሉንም ድንበር እስኪጎበኝ፣ ሁሉንም አገራት እስኪጠርግ፣ እናም እያንዳንዷ ጆሮ እስክትሰማ ይጓዛል፡፡” ሲል የተናገረው ትንቢት ስለመፈፀሙ የዓይን ምስክር ነኝ፡፡
አሁን ዓለምን የሚሸፍኑት ድንቅ ሚስዮናውያን 74000 ብርቱዎች ናቸው። ከአባላት ጋር በመተባበር በየወሩ ከ20,000 በላይ ሰዎችን ያጠምቃሉ። በቅርብ ጊዜ፣ በጌታ እርዳታ ይህንን ታላቅ የመሰብሰብ ተዓምር የፈጠሩት የ18፣ የ19 እና የ20 ዓመት ወጣት ወንዶች እና ወጣት ሴቶች እነርሱ ናቸው። እነዚህን ወጣት ሴቶች እና ወጣት ወንዶች በቫኑዋቱ ትናንሽ መንደሮች እና እንደ ኒውዮርክ፣ ፓሪስ እና ለንደን ባሉ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ እናገኛቸዋለን። በፊጂ ውስጥ በሚገኙ ሩቅ በሆኑ መሠብሠቢያዎች እንዲሁም በአሜሪካ ውስጥ እንደ ቴክሳስ፣ ካሊፎርኒያ እና ፍሎሪዳ ባሉ ትላልቅ ቦታዎች ስለ አዳኙ ሲያስተምሩ ተመልክቻለሁ።
ሚስዮናውያን 60 የተለያዩ ቋንቋዎችን በመጠቀም፣ በማቴዎስ 28 ላይ የተጠቀሰውን “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው” የሚለውን የአዳኙን ታላቅ ተልዕኮ በሁሉም የምድር ማዕዘን እየፈፀሙ ታገኟቸዋላችሁ። የቀድሞዎቹን እና የአሁኖቹን የቤተክርስቲያኗን ሚስዮናውያን አከብራለሁ እንዲሁም ታዳጊው ትውልድ እንዲመጣ እና እስራኤልን እንዲሰበስብ ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን ያቀረቡትን ግብዣ አስታውሳለሁ።
ይህንን ታላቅ የሆነውን የአዳኙን ወንጌል ዳግም መመለስ በዓይኔ እንዳየሁ እና በጆሮዬ እንደሰማሁ ዛሬ እመሰክራለሁ። እኔ በመላው አለም የሚከናወነው የእግዚአብሔር ሥራ ምስክር ነኝ። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል ለመሆን ከዛሬ የተሻለ ጊዜ እንደሌለ እመሰክራለሁ።
ምናልባት፣ እኔ ካየሁት በጣም የሚያነሣሣው የዳግም መመለሱ ተዓምር እናንተ በሁሉም አገር የምትኖሩት ታማኝ የቤተክርስቲያኗ አባላት ናችሁ። እናንተ፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን፣ ኔፊ ዘመናችንን አይቶ ፣“እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ በበጉ ቤተክርስቲያን ቅዱሳንና በምድር ገፅ ላይ ሁሉ በተበተኑት የጌታ የቃልኪዳን ህዝቦች ላይ የእግዚአብሔር በግ በኃይል ሲወርድ ተመለከትኩ፤ እናም እነርሱ ፅድቅንና የእግዚአብሔርን ኃይል በታላቅ ክብር የታጠቁ ነበሩ።”ሲል በመሠከረ ጊዜ በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ተገልጿችኋል።
ኔፊ ያየውን በዓይኔ እንዳየሁ እመሰክራለሁ—እናንተ፣ በሁሉም ምድር ያላችሁ የቃል ኪዳን ቅዱሳን፣ በጽድቅ እና በእግዚአብሔር ኃይል ታጥቃችኋል። ከእነዚህ ታላላቅ የአለም አገራት በአንዱ በመድረክ ላይ ሳለሁ፣ ንጉስ ቢንያም በመፅሐፈ ሞርሞን በሞዛያ 2 ውስጥ ያስተማረውን አንድ ነገር ጌታ በአእምሮዬ አስቀመጠ። ብረንት፣ “የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁትን የተባረከና አስደሳቹን ሁኔታ እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ። እነሆም እነርሱ በሁሉም ነገሮች፣ በጊዜያዊም ሆነ በመንፈሳዊው፣ የተባረኩ ናቸውና።”
በአለም ዙሪያ ትእዛዛትን የምትጠብቁ የእግዚአብሔር ታማኝ ቅዱሳን እናንተን ባገኘኋችሁ ጊዜ ይህን በራሴ አይቼ በጆሮዬ እንደሰማሁ እመሰክርላችኋለሁ። እናንተ የአብ የቃል ኪዳን ልጆች ናችሁ። እናንተ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት ናችሁ። እኔም ይህንን እንደማውቅ ታቃላችሁ ምክንያቱም ዳግም ስለተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እውነትነት የግል ምስክርነትን ተቀብላችኋል። አዳኙ እንዳስተማረው፣ “ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናችሁ።”
በጌታ እና በነቢያቱ እንዲሁም በሐዋርያቱ መሪነት ሚስዮናውያንን ማዘጋጀታችንን እንቀጥላለን፣ የተቀደሡ ቃል ኪዳኖችን እንፈፅማለን፣ የክርስቶስን ቤተክርስቲያን በአለም ዙሪያ እንመሰርታለን እንዲሁም የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ስንጠብቅ የሚመጡትን በረከቶች እንቀበላለን። እኛ አንድ ነን። የእግዚአብሄር ልጆች ነን። እናውቀዋለን እንዲሁም እንወደዋለን።
ጓደኞቼ፣ እነዚህ ነገሮች እውነት መሆናቸውን ከእናንተ ጋር በአንድነት እመሠክራለሁ። ስላየናቸውና ስለሰማናቸው ነገርች እንመዘግባለን። አናንተ እና እኔ የአይን እማኝ ምስክሮች ነን። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በወንጌሉ ላይ እምነት ይዘን ወደፊት የምንገፋው በዚህ የተባበረ ምስክርነት ሃይል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው እንደሆነ እመሰክራለሁ። እሱ አዳኛችን እና ቤዛችን ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።