መፅሐፈ ሞርሞን ይኖረን ዘንድ የጌታ ጥበብ ነው።
በዚህ አመት መፅሐፈ ሞርሞንን ማንበባችን ይህን አመት ለእያንዳንዳችን ደስታን እና በረከቶችን እንዲያመጣ እንዲሁም ወደ አዳኙ እንዲያቀርበን ፀሎቴ ነው።
ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ በ ኑ፤ ተከተሉኝአማካኝነት ቅዱሳት መጻህፍትን ለማንበብ ለምታደርጓቸው ጥረቶች አመስጋኞች ነን። ስለምታደርጓቸው ነገሮች ሁሉ እናመሰግናለን። ከእግዚአብሔር እና ከቃሉ ጋር የምታደርጉት የዕለት ተዕለት ግንኙነት ትልቅ ውጤቶችን ያስገኛል። “የታላቅ ሥራን መሠረት እየገነባችሁ ነው። እናም ከትንንሾቹ ነገሮች ታላቅ ነገሮች ይወጣሉ።”
የአዳኙን ትምህርቶች በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ማንበብ ቤቶቻችንን ወደ እምነት መቅደሶች እና ወደ ወንጌል ትምህርት ማዕከላት እንድንለውጥ ይረዳናል። መንፈሱን ወደ ቤቶቻችን ይጋብዛል። መንፈስ ቅዱስ ነፍሣችንን በደስታ ይሞላል እንዲሁም የሕይወት ሙሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ወደመሆን ይለውጠናል።
በእነዚህ ባለፉት በርካታ ዓመታት፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን መጻሕፍት ስናነብ፣ እግዚአብሔር በሁሉም ዋና ዋና የወንጌል ዘመናት ለልጆቹ ያስተላለፈውን ትምህርት ሠፊ ዕይታ ተመልክተናል።
በእያንዳንዱ ዘመን በደምብ የሚታወቅ ንድፍ እይተናል። እግዚአብሄር የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በነቢያቱ አማካኝነት ዳግም ይመልሣል ወይም ይገልጣል። ሕዝቡ ነቢያቱን ይከተላሉ እናም በእጅጉ ይባረካሉ። ሆኖም፣ በጊዜ ሂደት፣ አንዳንድ ሰዎች የነቢያትን ቃል መስማት ያቆማሉ እንዲሁም ራሳቸውን ከጌታ እና ከወንጌሉ ያርቃሉ። ክህደት ብለን የምንጠራው ይህንን ነው። ወንጌሉ በመጀመሪያ የተገለጠው ለአዳም ነበር፣ ነገር ግን አንዳንድ የአዳምና የሔዋን ልጆች ክህደት በመፈፀም ከጌታ ራቁ። በሄኖክ፣ በኖህ፣ በአብርሃም፣ በሙሴ እና በሌሎችም ዘመናት የዳግም መመለስ እና የክህደት ንድፍ ተደጋግሞ ሲከሠት እናያለን።
አሁን፣ ዛሬ፣ የምንኖረው በዘመኑ ፍጻሜ ውስጥ ነው። ይህ በክህደት የማይቋጭ ብቸኛው ዘመን ነው። የአዳኙ የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት እና የሺህ ዓመት ንግስናውን የሚቀበለው ይሄ ዘመን ነው።
ስለዚህ፣ ይህ ዘመን ምን ልዩነት አለው? ወደ አዳኙ እንድንቀርብ እንዲሁም በፍፁም እንዳንተወው በተለይ በእኛ ዘመን የሚረዳን፣ ጌታ ዛሬ ምን ሠጥቶልናል?
ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው አንድ መልሥ ቅዱሣት መፃሕፍት ናቸው—በተለይም መጽሐፈ ሞርሞን፦ ሌላኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት።
እግዚአብሔር ሌላ አጠቃላይ ክህደት እንደማይኖር ቃል የገባ ቢሆንም፣ ከግለሠብ ክህደት ለመራቅ ማስተዋል እና ጥንቃቄ ማድረግ አለብን—ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን “እያንዳንዳችን ለራሣችን መንፈሣዊ ዕድገት ሃላፊነት አለብን” ሲሉ ያስተማሩንም አስታውሱ። በዚህ ዓመት እያደረግን እንዳለነው፣ መፅሐፈ ሞርሞንን ማጥናት፣ ሁልጊዜም ወደ አዳኙ ያቀርበናል—እንዲሁም በእርሱ ዘንድ እንድንቆይ ይረዳናል።
እሱን “ጥናት” ብለን እንጠራዋለን፣ ጥረትን የሚያመለክት በመሆኑም መልካም ነው። ሆኖም ሁልጊዜ የግድ አዲስ እውነት መማር አያስፈልገንም። አንዳንድ ጊዜ መፅሐፈ ሞርሞንን ማንበብ በዚያ ቀን ከእግዚአብሔር ጋር የመገናኘት ሥሜት እንዲሠማን ለማድረግ ብቻ ይሆናል—ነፍስን ለመመገብ፣ አለምን ለመጋፈጥ ከመውጣታችን በፊት በመንፈሳዊ ለመጠናከር ወይም በአለም ውስጥ አስቸጋሪ ነገሮችን ካሳለፍን በኋላ ፈውስን ለማግኘት።
ቅዱሳት መጻህፍትን የምናጠናው፣ ታላቁ አስተማሪ መንፈስ ቅዱስ፣ ወደ ሰማይ አባት እና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የምናደርገውን መለወጥ ለማጠናከር እና ይበልጥ እነርሱን እንድንመስል እኛን ለመርዳት ይችል ዘንድ ነው።
እነዚህን ሃሳቦች በአዕምሯችን ይዘን፣ “በዚህ ሳምንት የመፅሐፈ ሞርሞን ጥናታችን፣ መንፈስ ቅዱስ ምን አስተምሮናል?” እንዲሁም “ይህ ወደ አዳኙ የሚያቀርበን እንዴት ነው?” የሚለውን ልናስብ እንችላለን።
እነዚህ በቤታችን ለምናደርገው የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ጥሩ ጥያቄዎች ናቸው። በቤተክርስቲያን የሚደረግን የሠንበት ትምህርት ለመጀመር እጀግ በጣም ጥሩ ጥያቄዎች ናቸው። በሣምንቱ ውስጥ የቤት የትምህርት አቀባበላችንን በማሻሻል በሠንበት ዕለት በቤተክርስቲያን ትምህርት የምንሠጥበትን መንገድ እናሻሽላለን። በውጤቱም፣ በሠንበት የትምህርት ክፍሎቻችን “የሚሰብከው እና የሚቀበለውም እርስ በርሳቸው ይግባባሉ፣ እና ይተናነጻሉ እና አብረውም ይደሰታሉ።”
በዚህ ሳምንት በነበረው የመጽሐፈ ሞርሞን ጥናት መንፈስ በአዕምሮዬ ላይ ጠንካራ እና ዘላቂ ተፅዕኖ እንዲያሳደሩ ያደረጋቸው ጥቂት ጥቅሶች እነሆ፦
-
ኔፊ እንዲህ ሲል ለያዕቆብ ትዕዛዝን ሰጠው፣ “እነዚህ ሰሌዳዎች ከአንዱ ትውልድ ወደ ሌላው መተላለፍ [ይገባቸዋል]። እናም ቅዱስ የሆነ ሰበካ፣ ወይም ታላቅ የሆነ ራዕይ፣ ወይም ትንቢት፣ ካለ” ያሬድ “በእነዚህ ሰሌዳዎች ላይ … ለህዝ[ባቸው] [ሲል] መጻፍ [ነበረበት]።”
-
በኋላም ያዕቆብ እንዲህ ሲል መስክሯል፣ “[ቅዱሣት መፃሕፍትን] እንመረምራለን፣ …እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ስላሉንም ተስፋን እናገኛለን፣ እናም እምነታችን የማይናወጥ [ይሆናል]”
አሁን፣ እነዚህ ጥቅሶች ኔፊ ቀደም ሲል ስለነሐስ ሰሌዳዎቹ የተናገረውን እንዳስታውስ አድርገውኛል፦
“እናም መዝገቦች አግኝተናልና መርምረናቸዋል፣ አዎን፣ የጌታን ትዕዛዛት ለልጆቻችን ማቆየት እስኪቻለን ያህል ለእኛ ትልቅ ዋጋ ያላቸው እንደሆኑ አግኝተናቸዋል።
“ስለዚህ እኛ ወደ ቃልኪዳኑ ምድር በምድረበዳ ውስጥ ስንጓዝ ከእኛ ጋር ይዘናቸው እንሄድ ዘንድ የጌታ ጥበብ ነበር።”
አሁን፣ ሌሂ እና ቤተሠቡ ቅዱሣት መፃሕፍት ይኖራቸው ዘንድ ጥበብ ከነበረ፣ ለእኛም በዚህ ጊዜ እንዲሁ ጥበብ ነው። ቅዱሳት መጻህፍት ያላቸው ታላቅ ዋጋ እና መንፈሣዊ ሀይል ዛሬም በእኛ ህይወት ውስጥ ሳይደበዝዝ ይገኛል።
ዛሬ ጥቅም እየሠጡን ያሉትን መጽሐፈ ሞርሞንን እና ሌሎች ቅዱሳት መጻህፍትን እንደ እኛ ማግኘት የቻለ ህዝብ በታሪክ ውስጥ አልነበረም። አዎን፣ ሌሂ እና ቤተሠቡ የነሐስ ሰሌዳዎቹን በመያዝ ተባርከዋል፣ ሆኖም ለእያንዳንዳቸው የሚዳረስ ቅጂዎች አልነበሯቸውም! ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆነው የመፅሐፈ ሞርሞን ቅጂ፣ የእራሳችን የግል ቅጂ ነው። የምናነበው ቅጂ ነው።
በሌሂ የሕይወት ዛፍ ራዕይ ውስጥ፣ ሌሂ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር በግለሠብ ደረጃ የመለማመድን አስፈላጊነት አስተምሮናል። ፍሬውን ከበላ በኋላ፣ ሌሂ ሚስቱን ሳርያን፣ እንዲሁም ልጆቹን ኔፊን እና ሳምን ትንሽ ራቅ ብለው አያቸው።
“እነርሱም ወዴት መሄድ እንዳለባቸው እንደማያውቁ ሆነው ቆሙ።
ሌሂ እንዲህ ብሏል፣ “እኔ ጠቆምኳቸው፣ ወደ እኔ እንዲመጡና ከሌሎች ፍሬዎች ሁሉ በላይ መልካም የሆነውን ፍሬ፣ እንዲበሉ በከፍተኛ ድምፅ ነገርኳቸው።
የሌሂን ዓላማ ያለው የወላጅነት ምሳሌ እወደዋለሁ። ሳርያ፣ ኔፊ እና ሳም መልካም የሆነ፣ የጽድቅ ሕይወት ይኖሩ ነበር። ነገር ግን፣ ጌታ ለእነሱ የተሻለ ጣፋጭ ነገር ነበረው። የት ሊያገኙት እንደሚችሉ አያውቁም ነበር፤ ነገር ግን ሌሂ ያውቅ ነበር። ስለዚህም፣ ወደ ሕይወት ዛፉ እንዲመጡና ከፍሬው እራሳቸው እንዲካፈሉ “በከፍተኛ ድምፅ” ጠራቸው። የሠጠው አቅጣጫ ግልፅ ነበር። ምንም አለመግባባት ሊከሠት አይችልም ነበር።
እኔም ዓላማ ያለው የልጅ አስተዳደግ ውጤት ነኝ። ትንሽ ልጅ ሳለሁ፣ ምናልባት 11 ወይም 12 ዓመት ቢሆነኝ ነው፣ እናቴ፣ “ማርክ፣ ወንጌል እውነት እንደሆነ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት፣ በራስህ አውቀሃል?” ስትል ጠየቀችኝ።
ጥያቄዋ አስገረመኝ። ሁልጊዜ “ጨዋ ልጅ” ለመሆን እሞክር የነበረ ሲሆን ያም በቂ ይመስለኝ ነበር። ነገር ግን እናቴ፣ ልክ እንደ ሌሂ ከዚያ የበለጠ ነገር እንደሚያስፈልግ ታውቅ ነበር። ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ እንዲሁም በራሴ ማወቅ ያስፈልገኝ ነበር።
ያ ተሞክሮ ገና እንዳልነበረኝ መለስኩላት። እናም በመልሴ ምንም የተገረመች አትመስልም ነበር።
ከዚያም ልረሳው የማልችለውን አንድ ነገር እንዲህ አለች። ቃላቱን እንስከዚህ ቀን አስታውሰዋለው፦ “የሰማይ አባት ለራስህ እንድታውቀው ይፈልግሀል። ሆኖም ጥረት ማድረግ አለብህ። መፅሐፈ ሞርሞንን ማንበብ እንዲሁም በመንፈሥ ቅዱሥ አማካኝነት ለማወቅ መፀለይ አለብህ። የሰማይ አባት ለፀሎትህ መልስ ይሰጣል።”
መልካም፣ መፅሐፈ ሞርሞንን ከዚያ በፊት አንብቤ አላውቅም ነበር፡፡ ያንን ለማድረግ ዕድሜዬ እንደደረሠ አላሰብኩም ነበር። ነገር ግን እናቴ የተሻለ ታውቅ ነበር።
ጥያቄዋ በውስጤ በራሴ የማወቅ ጉጉትን አጫረብኝ።
ስለዚህ፣ በእያንዳንዱ ምሽት፣ ከሁለት ወንድሞቼ ጋር እጋራው በነበረው የመኝታ ክፍል ውስጥ፣ ከአልጋዬ በላይ ያለውን መብራት አብርቼ የመፅሐፈ ሞርሞንን አንድ ምዕራፍ አነበብኩኝ። ከዚያም፣ መብራቱን በማጥፋት፣ ቀስ ብዬ ከአልጋዬ ውስጥ ወጥቼ በጉልበቴ ተንበርክኬ ጸለይኩኝ። ከመቼውም ጊዜ በላቀ ታላቅ ፍላጎት እና በበለጠ ቅንነት ጸለይኩኝ። የሰማይ አባት የመፅሐፈ ሞርሞንን እውነትነት እንዲያሳውቀኝ በትሕትና ጠየቅሁት።
መጽሐፈ ሞርሞንን ማንበብ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ የሰማይ አባት ጥረቴን ያውቅ እንደነበረ ተሰማኝ። ከዚያም፣ የእኔ ነገር ግድ እንደሚለው ተሰማኝ። እያነበብኩኝ እና እየፀለይኩኝ ስሄድ፣ የሚያጽናኑ፣ ሠላማዊ ሥሜቶች ተሠሙኝ። ከአንዱ ምዕራፍ ወደ ሌላው በተሸጋገርኩኝ ቁጥር፣ የእምነት ብርሃን በነፍሴ ውስጥ ይበልጥ እየበራ በመሄድ ላይ ነበር። በጊዜ ሂደት፣ እነዚህ ሥሜቶች ከመንፈስ ቅዱስ የሚመጡ የአንድን ነገር እውነትነት የሚያረጋግጡ ሥሜቶች እንደነበሩ ተገነዘብኩኝ። መፅሐፈ ሞርሞን እውነት እንደሆነ እና ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም አዳኝ እንደሆነ በራሴ አወቅኩኝ። ለእናቴ በመንፈስ የተነሳሳ ግብዣ እንዴት ታላቅ አመስጋኝ ነኝ።
ይህ ከልጅነት የተገኘ የመፅሐፈ ሞርሞን ንባብ ልምድ፣ እስከ ዛሬ ድረስ እየባረከኝ ያለውን የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ንድፍ አስጀምሯል። አሁንም መፅሐፈ ሞርሞንን አነባለሁ፤ ለጸሎትም እንበረከካለሁ። መንፈስ ቅዱስም ስለእሱ እውነታዎች ደጋግሞ ማረጋገጫ ይሠጣል።
ኔፊ በትክክል አስቀምጦታል። በመላው ሕይወታችን ቅዱሳት መፃህፍትን ይዘን እንሄድ ዘንድ የጌታ ጥበብ ነበር። መፅሐፈ ሞርሞን፣ ይህንን ዘመን ከቀደሙት ዘመናት ሁሉ የተለየ የሚያደርግ “የማእዘን ድንጋይ” ነው። መፅሐፈ ሞርሞንን ስናነብ እና በሕይወት ያለን ነቢይ ስንከተል፣ በህይወታችን ውስጥ የግል ክሕደት አይኖርም።
የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቆ በመያዝ ወደ ህይወት ዛፍ ለመምጣት ያቀረበው ግብዣ ከሌሂ ለቤተሰቡ ብቻ የቀረበ ግብዣ አይደለም፤ እንዲሁም እናቴ መፅሐፈ ሞርሞንን እንዳነብ እና ስለሱ እንድጸልይ ያቀረበችው ግብዣ ከእናቴ የመጣ ግብዣ ብቻ አይደለም። ከነቢያችን ከፕሬዚዳንት ራስል ኤም.ኔልሰን ለእያንዳንዳችን የቀረበ ግብዣም ነው።
“መፅሐፈ ሞርሞንን በጸሎት መንፈስ በየቀኑስታጠኑበየቀኑየተሻሉ ውሳኔዎችን እንደምትወስኑ ቃል እገባለሁ። በምታጠኑት ነገር ላይ ስታሰላስሉ፣ የሰማይ መስኮቶች እንደሚከፈቱ፣ እንዲሁም ለራሳችሁ ጥያቄዎች መልስ እና ለግል ህይወታችሁ መመሪያ እንደምትቀበሉ ቃል እገባለሁ።”
በዚህ አመት መፅሐፈ ሞርሞንን ማንበባችን ለእያንዳንዳችን አስደሣች እንዲሆን እና በረከት እንዲያመጣ እንዲሁም ወደ አዳኙ ይበልጥ እንድንቀርብ ያደርገን ዘንድ ፀሎቴ ነው።
የሰማይ አባት ሕያው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እና ቤዛችን ነው። መፅሐፈ ሞርሞን የእርሱን ቃላት ይዟል እንዲሁም የእርሱን ፍቅር ያስተላልፋል። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልስን ዛሬ በምድር በሕይወት ያለ የጌታ ነቢይ ናቸው። በልጅነቴ መፅሐፈ ሞርሞንን ባነበብኩበት ጊዜ በመጀመሪያ በተቀበልኩት የመንፈስ ቅዱስ የማረጋገጫ ምስክርነት እነዚህ ነገሮች እውነት እንደሆኑ አውቃለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።