አጠቃላይ ጉባኤ
አምዶች እና ጨረሮች
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


11:17

አምዶች እና ጨረሮች

እኛም የራሳችንን የብርሃን አምድ ቀስ በቀስ ሊኖረን ይችላል።

መልእክቴ፣ ኃያል መንፈሳዊ ተሞክሮዎች ስላላጋጠሟቸው ስለምስክርነታቸው ለሚጨነቁ ነው። የተወሰነ ሰላም እና ማረጋገጫ መስጠት እንድችል እጸልያለሁ።

የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ዳግም መመለስ፣ በድንገተኛ ብርሃን እና እውነት ተጀመረ! በኒውዮርክ ሰሜናዊ ክፍል የሚኖር፣ ጆሴፍ ስሚዝ የተሰኘ የተለመደ ስም ያለው አንድ በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ያለ ልጅ፣ ለመጸለይ ወደ ዛፎች ቁጥቋጦ ገባ። ስለ ነፍሱ እና በእግዚአብሔር ፊት ስላለው አቋም ይጨነቅ ነበር። እሱ ለኃጢአቱ ስርየትን ይፈልጋል። እናም ደግሞ የትኛውን ቤተክርስቲያን መቀላቀል እንዳለበት ግራ ተጋብቷል። ግልጽነትን እንዲሁም ሰላምንም ይሻል—ብርሃን እና እውቀትም ያስፈልገዋል።

ጆሴፍ ለመጸለይ ተንበርክኮ “የል[ቡን] ፍላጎቶች ለእግዚአብሔር መግለጽ” ሲጀምር ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ ከበበው። የሆነ ክፉ፣ ጨቋኝ እና በጣም እውን የሆነ ነገር ሊያቆመው እንዲሁም እንዳይናገር ምላሱን ለማሰር ሞከረ። የጨለማው ኃይሎች በጣም እየጠነከሩ ከመሄዳቸው የተነሳ ጆሴፍ የሚሞት መሰለው። እሱ ግን “[በላዩ] ላይ ከሰለጠነው የጠላት ኃይል እንዲያድ[ነው] ሃይ[ሉን] ሁሉ አሰባስ[ቦ] እግዚአብሄርን [ጠራ]።” ከዚያም፣ “ተስፋ ወደመቁረጥ እና [ራሱን]ም ለጥፋት አሳል[ፎ] ለመስጠት በተዘጋጀ[በት] በዚያች ቅጽበት”፣ ከዚህ በኋላ ጸንቶ መቆየት ይችል እንደሆን ባላወቀበት ሰዓት፣ የከበረ ብርሃን ጨለማውን እና የነፍሱ ጠላት እየበተነ ጫካውን ሞላው።

ከፀሐይ ይልቅ የደመቀ “የብርሃን አምድ” በዝግታ በእርሱ ላይ ወረደ። አንድ ሰው ታየ፣ ከዚያም ሌላ። “ብሩህነታቸውና ክብራቸው ቃላት ከሚገልጹት በላይ” ነበር። የመጀመሪያው፣ የሰማይ አባታችን፣ ስሙን በመጥራት “ወደ ሌላውም በማመልከት—[ጆሴፍ!] የምወደው ልጄ ይህ ነው። እርሱን ስማው!

እናም በዚያ በሚያጥለቀልው የፈነጠቀ ብርሃን እና እውነት ዳግም መመለሱ ተጀመረ። እውነተኛ መለኮታዊ መገለጥ እና የበረከት ጎርፍ ተከትሎ መጣ፥ አዲስ ቅዱስ መፅሃፍ፣ የተመለሰ የክህነት ስልጣን፣ ሐዋርያት እና ነቢያት፣ ስርዓቶች እና ቃል ኪዳኖች፣ አንድ ቀን ምድርን በኢየሱስ ብርሃን እና ምስክርነት የምትሞላው የጌታ እውነተኛ እና ህያው ቤተክርስቲያን ዳግም መቋቋም እንዲሁም ክርስቶስ እና የተመለሰው ወንጌል።

ያ ሁሉና ተጨማሪ ሌሎችም የጀመሩት በአንድ ልጅ የተስፋ መቁረጥ ጸሎት እና የብርሃን ዓምድ ነው።

እኛም የራሳችን አንገብጋቢ ጥያቄዎች አሉን። እኛም ከመንፈሳዊ መደነጋገር እና ከዓለም ጨለማ ነጻ መውጣት ያስፈልገናል። እኛም ለራሳችን ማወቅ ይኖርብናል። ይህም ነቢያችን ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “[ራሳችንን] በዳግም መመለሱ የከበረ ብርሃን እንንከር”ብለው ግብዣ ካቀረቡልን ምክንያቶች አንዱ ነው።

ከዳግም መመለሱ ታላላቅ እውነቶች መካከል አንዱ፣ ሰማያት ክፍት መሆናቸው እና እኛም ብርሃን እና እውቀት ከላይ መቀበል መቻላችን ነው። እውነት መሆኑን እመሰክራለሁ።

ነገር ግን ከመንፈሳዊ ወጥመድ መጠንቀቅ አለብን። አንዳንድ ጊዜ ታማኝ የቤተክርስቲያኑ አባላት አስደናቂ የሆኑ መንፈሳዊ ልምዶች እና የራሳቸው የሆነ የብርሃን አምድ ስላልገጠማቸው ተስፋ ይቆርጣሉ አልፎ ተርፎም ይርቃሉ። ፕሬዘደንት ስፔንሰር ደብሊው ኪምባል “ሁልጊዜም አስደናቂውን ነገር በመጠበቅ የማያቋርጠውን የተገለጠ የግንኙነት ፍሰት ብዙዎች ያጣሉ። በማለት አስጠንቅቀዋል።

ፕሬዘደንት ጆሴፍ ኤፍ. ስሚዝ “ጌታ እኔ [ወጣት ሳለሁ] ድንቆችን ከለከለኝ፣ እናም እውነትን፣ በስርዐት ላይ ስርዐት፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ በማድረግ እውነቱን አሳይቶኛል” ብለው አስታወሱ።

ወንድሞች እና እህቶች፣ ያ የተለመደ የጌታ አሰራር ነው፣ ጌታ የብርሃን አምድ ከመላክ ይልቅ፣ የብርሃን ጨረር ይልክልናል፣ ከዚያም ተጨማሪ ሌላ ይልክልናል ከዚያም ሌላ።

እነዚያ የብርሃን ጨረሮች ያለማቋረጥ በላያችን ላይ እየፈሰሱ ነው። ቅዱሳት መጻህፍት ኢየሱስ ክርስቶስ “የአለም ብርሃን እና ህይወት” እንደሆነ ፣ “መንፈስ ወደዓለም ለሚመጣ [ወንድና ሴት] ብርሃን [እንደሚሰጥ] ፣ እንዲሁም ብርሃኑ “ጠፈርን ለመሙላት [እንደሚሄድ]“ እና “ለሁሉም ነገሮች ህይወትን” እንደሚሰጥ” ያስተምራሉ። የክርስቶስ ብርሃን በዙሪያችን ነው።

የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ከተቀበልን እና እምነትን ለመለማመድ፣ ንስሃ ለመግባት እና ቃል ኪዳኖቻችንን ለማክበር የምንጥር ከሆነ፣ እነዚህን መለኮታዊ ጨረሮች ያለማቋረጥ ለመቀበል ብቁ ነን። በሽማግሌ ዴቪድ ኤ. ቤድናር የማይረሳ ሀረግ፣ “በመገለጥ [እንኖራለን]።”

ሆኖም እያንዳንዳችን የተለያየን ነን። ሁለት ሰዎች የእግዚአብሔርን ብርሃን እና እውነት በተመሳሳይ መንገድ ሊረዱ አይችልም። የጌታን ብርሃን እና መንፈስ እንዴት መለማመድ እንዳለባችሁ ለማሰብ ትንሽ ጊዜ ውሰዱ።

እነዚህን የምሥክርነት ጨረሮች፣ ባሳሰበችሁ ነገር ላይ “በአእም[ሯችሁ] ሰላምን [ሲናገር]” ገጥሟችሁ ሊሆን ይችላል (

ወይም ደግሞ “በአእም[ሯችሁ] እና በል[ባችሁ]” ውስጥ በተቀመጠ እና አንድን ሰው እንደመርዳት ያለ መልካም ነገር እንድታደርግ የሚገፋፋው አይነት አነስተኛ የዝምታ ድምፅ ሊሆን ይችላል።

ምናልባት በቤተክርስቲያን ክፍል ውስጥ ወይም በወጣቶች ካምፕ ውስጥ እያላችሁ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል እና ታማኝ ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ተሰምቷችሁ ይሆናል። ምናልባት ቆማችሁ እውነት ነው ብላችሁ ተስፋ ስለምታደርጉት ነገር ምስክርነት ስታካፍሉ እውነት መሆኑ ተሰምቷችሁ ይሆናል።

ወይም ምናልባት እየጸለያችሁ ሳለ እግዚአብሔር እንደሚወዳችሁ የደስታ ማረጋገጫ ተቀብላችሁ ይሆናል።

አንድ ሰው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመሰክር ሰምታችሁ ልባችሁ ተነክቶ በተስፋ በመሞላት ተነሳስታችሁ ይሆናል።

ምናልባት መፅሐፈ ሞርሞንን ስታነቡ እግዚአብሔር ለእናንተ ብቻ ያስቀመጠው በሚመስል ሁኔታ አንድ ጥቅስ ለነፍሳችሁ ተናግሮ ይሆናል።

ሌሎችን ስታገለግሉ፣ እግዚአብሔር ለእነሱ ያለው ፍቅር ተሰምቷችሁ ይሆናል።

ወይም ምናልባት በድብታ ወይም በጭንቀት ምክንያት መንፈሱን ለመሰማት ስትቸገሩ ወደ ኋላ የማየት እና ያለፉትን “የጌታን የርህራሄ ምህረቶዎች” የማወቅ ስጦታ ሊኖራችሁ ይችላል።

ለማለት የምፈልገው ሰማያዊ የምሥክርነት ጨረሮችን ለመቀበል ብዙ መንገዶች እንዳሉን ነው። በእርግጥም፣ እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው። አስደናቂ ላይሆኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን ሁሉም የምሥክርነታችን አካል ናቸው።

ወንድሞች እና እህቶች፣ የብርሃን አምድ አላየሁም፣ ነገር ግን እንደ እናንተ ብዙ መለኮታዊ ጨረሮችን አግኝቻለሁ። ባለፉት አመታት ለእንደዚህ አይነት ልምዶች ከፍ ያለ ቦታ ለመስጠት ሞክርያለሁ። ያንን ሳደርግ፣ የበለጠ እያወኳቸው እንዲሁም ብዙዎቹን እያስታወስኳቸው ነው። ከህይወቴ የተወሰኑ ምሳሌዎች የሚከተሉት ናቸው። ለአንዳንዶች በጣም አስደናቂ ላይሆኑ ይችላሉ ነገር ግን ለእኔ ውድ ናቸው።

በአስራዎቹ እድሜ ክልል እያለሁ፣ በአንድ የጥምቀት ስርዓት ወቅት እየረበሽኩ እንደነበር አስታውሳለሁ። ስብሰባው ሊጀመር ሲል፣ መንፈስ እንድቀመጥ እና አክብሮት እንዳሳይ ሲገፋፋኝ ተሰማኝ። ተቀመጥኩ፣ ስብሰባውም እስኪያልቅ ድረስ ጸጥ አልኩ።

ከሚስዮኔ በፊት፣ ምስክርነቴ በበቂ ሁኔታ ጠንካራ ስላልመሰለግኝ ፈርቼ ነበር። ከዚህ በፊት በቤተሰቤ ውስጥ በሚስዮን ያገለገለ ማንም አልነበረም፣ ስለዚህም ማገልገል ስለመቻሌ ማወቅ አልቻልኩም ነበር። የበለጠ እርግጠኛ የሆነ የኢየሱስ ክርስቶስን ምስክርነትን ለመቀበል ማጥናቴን እና መጸለዬን አስታውሳለሁ። ከዚያም አንድ ቀን፣ የሰማይ አባትን ሰለም፣ ኃይለኛ የብርሃን እና የሙቀት ስሜት ተሰማኝ። እናም አወቅሁ። እንዲሁ አወቅሁ።

በሽማግሌዎች ቡድን ውስጥ እንዳገለግል እንደምጠራ “በንፁህ የመረዳት” ስሜት አንድ ምሽት ከእንቅልፌ መቀስቀሴን አስታውሳለሁ። ከሁለት ሳምንት በኋላ ተጠራሁ።

አንድ የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ቡድን አባል፣ እንዲሰማ ለፈለግኩት ጓደኛ የነገርኩትን የምሥክርነት ቃል የተናገረበትን አጠቃላይ ጉባኤ አስታውሳለሁ።

ልቡ መምታት ካቆመ በኋላ በትንሽ እና ሩቅ ሆስፒታል ውስጥ እራሱን ስቶ በማሽን እገዛ ለሚተነፍስ ጓደኛዬ ለመጸለይ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ወንድሞች ጋር መንበርከኬን አስታውሳለሁ። ልባችንን አንድ አድርገን ስለ ህይወቱ ስንማፀን፣ ነቃና የመተንፈሻውን ማሽን ከጉሮሮው ጎትቶ አወጣ። ዛሬ የካስማ ፕሬዝዳንት ሆኖ ያገለግላል።

አንድ ያለጊዜው በማለፉ በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ቀዳዳ ትቶ ስለነበረ የምወደው ጓደኛ እና መካሪ ግልጽ የሆነ ህልም ካየሁ በኋላ በጠንካራ መንፈሳዊ ስሜት ከእንቅልፌ መነሳቴን አስታውሳለሁ። በደስታ ፈገግታ እያሳየ ነበር። ደህና እንደሆነም አወቅሁ።

እነዚህ በጥቂቱ የእኔ ጨረሮች ናቸው። የራሳችሁ የምሥክርነት ጨረሮች—የራሳችሁ በብርሀን የተሞሉ ምስክርነት ነበራችሁ። እነዚያን ጨረሮች “[በአንድ ላይ]” ስንሰበስብ፣ ስናውቅ እና ስናስታውስ አስደናቂ ነገር መከሰት ይጀምራል። “ብርሃን ከብርሃን ጋር ይጣበቃል”—“እውነት እውነትን ያቅፋል።” የአንድ የምሥክርነት ጨረር እውነታ እና ኃይል ከሌላው ጋር ይጣመራል፣ ከዚያም ከሌላ ጋር እያለ መጠናከሩን ይቀጥላል። በስርዐት ላይ ስርዐት፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ ፣ እዚህ ጨረር እዚያ ጨረር፣ በአንድ ጊዜ አነስተኛ፣ ውድ የሆነ መንፈሳዊ ቅጽበት በብርሃን የተሞላ፣ የመንፈሳዊ ልምድ በውስጣችን ያድጋል። ምናልባት አንድ ጨረር፣ ሙሉ ምስክርነትን ለመመስረት የሚያስችል ጥንካሬ ላይኖረው ይችላል፣ ነገር ግን አንድ ላይ ሆነው የጥርጣሬ ጨለማ ሊያሸንፈው የማይችለው ብርሃን ሊሆኑ ይችላሉ።

“አቤቱ ይህ እውነት አይደለምን?” አልማ ይጠይቃል። “እኔ እንዲህ እላችኋለሁ፣ አዎን፣ ይህ ብርሃን ነው።”

“ከእግዚአብሔር የሆነው ብርሀን ነው፤ እና ብርሀንን ተቀብሎ በእግዚአብሔር የሚቀጥል፣ ተጨማሪ ብርሀንን ይቀበላል፤ እናም ብርሀኑም ፍጹም እስከሆነው ቀን ድረስም እየጨመረ ይበራል”በማለት ጌታ ያስተምረናል።

ያም ማለት፣ ወንድምች እና እህቶች፣ በጊዜ እና “በታላቅ ትጋት” እኛም የራሳችንን የብርሃን አምድ ቀስ በቀስ ሊኖረን ይችላል። በዚያ አምድ መካከል፣ እኛም ደግሞ በስማችን የሚጠራንን፣ ወደ አዳኛችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጠቁመንን እና “እርሱን ስሙት!” በማለት የሚጋብዘንን አፍቃሪ የሰማይ አባትን እናገኛለን።

ኢየሱስ ክርስቶስ የአለም ሁሉ እንዲሁም የእኔ እና የእናንተ የግል አለም ብርሃን እና ህይወት እንደሆነ እመሰክራለሁ።

እርሱ የእውነተኛው እና ሕያው አምላክ እውነተኛ እና ሕያው ልጅ እንደሆነ እንዲሁም በዚህች እውነተኛ እና ሕያው ቤተክርስቲያን በእውነተኛ እና ህያው ነብያትና ሐዋርያቶች ራስ ላይ እንደቆመ እመሰክራለሁ።

የከበረ ብርሃኑን እንወቅ እንዲሁም ሁሌም እና ለዘላለም እንቀበል፣ ከዚያም ከጨለማው አለም ይልቅ እርሱን እንምረጠው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. የጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥10-13ይመልከቱ።

  2. የጆሴፍ ስሚዝ —ታሪክ 1፧14–16 ይመልከቱ።

  3. See Joseph Smith, Journal, Nov. 9–11, 1835, p. 24, josephsmithpapers.org.

  4. ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥17

  5. የጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1:20ይመልከቱ። ጆሴፍ ስሚዝ ከመጀመሪያው ራዕይ በኋላ ወደ ቤት ሲመለስ እናቱ ደህና እንደሆነ ጠየቀችው። እሱም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ደህና ነኝ። … ፕሪስባቴሪያኒዝም እውነት እንዳልሆነ ለራሴ ተምሬያለሁ።”

  6. ረስል ኤም. ኔልሰን፣ “Closing Remarks፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2019 (እ.አ.አ)፣ 122።

  7. ስፔንሰር ደብሊው ኪምቦል፣ በኮንፈረንስ ሪፖርት፣ ሙኒክ ጀርመን አካባቢ ኮንፈረንስ፣ 1973 (እ.አ.አ)፣ 77፤ ግሬሃም ደብሊው ዶክስይ፣ “The Voice Is Still Small,”፣ ኢንዛይንህዳር 1991 (እ.አ.አ)፣ 25 ላይ ተጠቅሷል።

  8. Teachings of Presidents of the Church: Joseph F. Smith (1998 እ.አ.አ፣ 201፤ “እንደ ወጣት ልጅ መጀመሪያ ማገልገል ስጀምር፣ በተደጋጋሚ ወደ ውጪ እወጣና እና ምስክርነት እንዳገኝ ጌታ ድንቅ ነገር እንዲያሳየኝ እጠይቀው ነበር። ነገር ግን ጌታ ተአምራትን ከለከለኝ እና መስመርን በመስመር፣ ትእዛዝን በትእዛዝ፣ ጥቂት እዚያም ጥቂት እውነትን አሳየኝ፣ እውነትን ከራሴ አክሊል እስከ እግሬ ጫማ እስካውቅ ድረስ። እና ጥርጣሬ እና ፍርሃት ከእኔ ሙሉ በሙሉ እስኪወገዱ ድረስ። ይህን ለማድረግ ከሰማይ መልአክን መላክ አላስፈለገውም ወይም እርሱ የመላእክት አለቃ መለከትን ይዞ መናገር አልተጠበቀበትም። በህያው እግዚአብሔር መንፈስ ትንሽ ድምፅ ሹክሹክታ፣ ያለኝን ምስክር ሰጠኝ። በዚህም መርህና ኃይል ለሰው ልጆች ሁሉ ከእነርሱ ጋር የሚኖር የእውነትን እውቀት ይሰጣቸዋል እግዚአብሔርም እንደሚያውቀው እውነትን እንዲያውቁ የአብንም ፈቃድ እንዲያደርጉ ያደርጋቸዋል። ክርስቶስ ያደርገዋል።

  9. ሞዛያ 16፥9

  10. ትምህርት እና ቃልኪዳን 84፥46፤ ደግሞም ዮሃንስ 1:9 ይመልከቱ።

  11. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፥12-13

  12. ዴቪድ ኤ.ቤድናር፣ “The Spirit of Revelation፣” ሊያሆና፣ግንቦት 2021 (እ.አ.አ)፣7

  13. ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 6፥23

  14. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 8፥2፤ በተጨማሪም ሄለማን 5:30ይመልከቱ።

  15. ሞዛያ 5:2ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 11:12 ይመልከቱ።

  16. 2ኛ ኔፊ 4:21ሄለማን 5:44ይመልከቱ።

  17. ጌታ የሌሎችን ምስክርነት የማመንን ችሎታ እንደ መንፈሳዊ ስጦታ ለይቷል ( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 46፥13-14 ይመልከቱ)።

  18. የዘመናችን መገለጥ የቅዱሳት መጻህፍት ቃላቶች “ለእናንተ የተሰጧችሁ በመንፈሴ ነው፣ እናም በሃይሌም አንዳችሁ ለሌላኛችሁ ልታነቧቸው ትችላላችሁ፣ እናም በሃይሌ ካልሆነ በስተቀር እነሱን ሊኖሯችሁ አይችልም ነበር” በማለት ያስተምራል። “ስለዚህ ድምጼን እንደሰማችሁ እና ቃላቴን እንደምታውቁ መመስከር ትችላላችሁ” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 18፥35–36)።

  19. ሞዛያ 2:17ሞሮኒ 7:45–48ይመልከቱ።

  20. 1 ኔፊ 1፥20። ሽማግሌ ጌሪት ደብሊው ጎንግ “በሕይወታችን ውስጥ ያለውን የጌታን ብዙ ምህረት ለማየት እና ለመደሰት ስለመመልከት ተናግረዋል (“Ministering,” ሊያሆና፣ ግንቦት 2023 (እ.አ.አ)) ብዙውን ጊዜ የኋላ እይታ በጣም ግልፅ ነው” (“Always Remember Him,” ሊያሆና፣ ግንቦት 2016(እ.አ.አ))። በህይወታችን ውስጥ የጌታን እጅ በአመስጋኝነት የማወቅ እና የመቀበል ስጦታ፣ ባናውቀውም ወይም በሰዓቱ ባይሰማንም ኃይለኛ ነው። ቅዱሳት መጻህፍት ብዙ ጊዜ ስለ ማስታወስ መንፈሳዊ ሃይል ይናገራሉ (ሔለማን 5፥9–12ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፥77፣ 79 ይመልከቱ)፣ ይህም ለመገለጥ ቅድመ ሁኔታ ሊሆን ይችላል (ሞሮኒ 10፥3–4 ይመልከቱ)።

  21. ጆሴፍ ስሚዝ እንዲህ አስተምሯል፥ “አንድ ሰው የመገለጥ መንፈስን የመጀመሪያ ፍንጭ በማስተዋል ሊጠቀም ይችላል። ለምሳሌ፣ ንፁህ መረዳት ወደ እናንተ እንደመጣ ሲሰማችሁ (መንፈስ ቅዱስ ሲያናግራችሁ)፣ ድንገት ሀሳቦችን ሊሰጣችሁ ይችላል፣ ስለዚህ ይህን ልብ በማለት፣ በዚያው ቀን ወይም በቅርቡ ተፈጽሞ ልታገኙት እችላላችሁ፤ (ማለትም) በእግዚአብሔር መንፈስ ወደ አእምሮአችሁ የቀረቡት ነገሮች ይፈጸማሉ። ስለሆነም የእግዚአብሔርን መንፈስ በመማር እና እርሱን በመረዳት፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ፍጹም እስክትሆኑ ድረስ በመገለጥ መርህ ልታድጉ ትችላላችሁ።(Teachings of Presidents of the Church: Joseph Smith [2007(እ.አ.አ]፣ 132)

  22. ኤፌሶን 1፥10

  23. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፥40፦ “የመረዳት ችሎታ ከመረዳት ችሎታ ጋር ይጣበቃል፣ ጥበብም ጥበብን ይቀበላል፤ እውነት እውነትን ያቅፋክ፤ በጎነት በጎነትን ያፈቅራል፤ ብርሃን ከብርሃን ጋር ይጣበቃል።”

  24. አልማ 32፥35። እነዚህ በብርሃን የተሞሉ ልምዶች፣ ብዙ ጊዜ ትንሽ ቢሆኑም፣ በየትኛውም መንገድ እውን ስለመሆናቸው አልማ አፅንዖት ሰጥቷል። አንድ ላይ ተጣምረው ሲፈጠሩ እውነታቸው የበለጠ ኃይለኛ ይሆናል።

  25. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50፥24

  26. አልማ 32፥41