አጠቃላይ ጉባኤ
ሁሉም ነገሮች ለእኛ መልካም
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


14:14

ሁሉም ነገሮች ለእኛ መልካም

በዚህ ምድር እና በዘለአለም፣ የፍጥረት አላማ እና የእግዚአብሔር ተፈጥሮ ሁሉንም ነገር ለበጎ ማድረግ ነው።

ዛሬ ሚያዝያ 6 ቀን (እ.አ.አ)፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የኋለኛው ቀን ቤተክርስቲያኑን ዳግም የመለሰበት አመታዊ በዓል ከመሆኑም በተጨማሪ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ህይወት፣ የኃጥያት ክፍያ መስዋዕትነት እና የክብር ትንሳኤን በደስታ የምንመሰክርበት የትንሳኤ ወቅት አካል ነው።

አንድ የቻይና ታሪክ፣ የአንድ ሰውዬ ወንድ ልጅ ቆንጆ ፈረስ ባገኘ ጊዜ ይጀምራል።

ጎሬቤቶቹም፣ “እንዴት አይነት እድለኛ ነው” አሉ።

ሰውየው ደግሞ፣ “የሚሆነውን እናያለን” አለ።

ከዚያም ልጁ ከፈረሱ ላይ ወድቆ በቋሚነት ይጎዳል።

ጎሬቤቶቹም “እንዴት ያልታደለ ነው” ይላሉ።

ሰውየው ደግሞ፣ “የሚሆነውን እናያለን” አለ።

ለግዳጅ ውትድርና የሚመለምል ጦር ይመጣል ነገር ግን የተጎዳውን ልጅ ሳይወሰድ ይቀራል።

ጎሬቤቶቹም፣ “እንዴት አይነት እድለኛ ነው” አሉ።

ሰውየው ደግሞ፣ “የሚሆነውን እናያለን” አለ።

ይህ ተለዋዋጭ ዓለም፣ ብዙ ጊዜ በዐውሎ ነፋስ የተወዛወዘ፣ እርግጠኛ ያልሆነ፣ አንዳንድ ጊዜ መልካም አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ አሳዛኝ ይመስላል። ሆኖም ግን በዚህ መከራ በተሞላ አለም ውስጥ፣ “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት … ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሚደረግ እናውቃለን።” በእርግጥም፣ በቅንነት ስንራመድ እና ቃል ኪዳኖቻችንን ስናስታውስ፣ “ሁሉም ነገሮች ለበጎ አብረው ይሰራሉ።”

ነገር ሁሉ ለእኛ መልካም ይሆናል።

አስደናቂ የሆነ ተስፋ ነው! ከራሱ ከእግዚአብሔር የመጣ የሚያፅናና ማረጋገጫ! በተአምራዊ መንገድ፣ የፍጥረት ዓላማ እና የአባታችን የእግዚያብሔር እና የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጥሮ፤ ለእኛ የሚጠቅመውን ሁሉ ማድረግና በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የኃጢያት ክፍያ የነጻን እና ቅዱሳን እንድንሆን ዘንድ እኛን ለማዳን እና ከፍ ከፍ ለማድረግ መጀመሪያን እና መጨረሻን ማወቅ ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ሊያድነን እና ከኃጢአት ሊቤዠን ይችላል። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ስቃይ፣ መከራ፣ ህመም፣ሀዘን እና መለየያየት በጥልቀት ይረዳል። በዚህ ምድር እንዲሁም ለዘለአለም፣ በሞት እና በገሃነም ላይ ያደረገው ድል ሁሉንም ነገር ማስተካከል ይችላል። የተሰበረውን እና የተናቀውን ይፈውሳል፣ የተቆጣውን እና የተከፋፈለውን ያስታርቃል፣ ብቸኛ የሆኑትን እና የተገለሉትን ያጽናናል፣ እርግጠኛ ያልሆኑትን እና ፍጹምነት የጎደላቸውን ያበረታታል፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የሚቻሉ ተአምራትን ያደርጋል።

ሀሌሉያ እንዘምራለን እናም ሁሳዕና ብለን እንጮሀለን። በዘለአለማዊው ኃይል እና ወሰን በሌለው ቸርነት፣ በእግዚአብሔር የደስታ እቅድ ነገር ሁሉ ለበጎ ሊሆን ስለሚችል ነው። ህይወትን ያለፍርሀት እና በልበ ሙሉነት እንጋፈጣለን፡

በራሳችን ስንቀር የራሳችንን በጎነት ላናውቅ እንችላለን። “እኔ ራሴን ስመርጥ፣” የራሴን ውስንነቶች፣ ድክመቶች፣ ብቁ አለመሆንንም ጭምር እየመረጥኩ ነው። በመጨረሻ፣ መልካምን ሁሉ ለማድረግ እኛው እራሳችን መልካም መሆን አለብን። ከእግዚአብሔር በቀር መልካም የሆነ ስለሌለ፣በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹምነትን እንፈልጋለን። እውነተኛ የሆንን፣ ከሁሉ የተሻለ ማንነት የሚኖረን፣ ፍጥረታዊውን ወንድ ወይም ሴት ስናስወግድና በኢየሱስ ክርስቶስ ስራ፣ ምህረት እና ጸጋ አማካኝነት በእግዚአብሔር ፊት እንደ ልጅ ስንሆን ነው።

በእግዚአብሔር ላይ ባለን እምነት፣ ፈተናዎች እና መከራዎች ለጥቅማችን ሊቀደሱ ይችላሉ። በግብፅ ለባርነት የተሸጠው ዮሴፍ ከጊዜ በኋላ ቤተሰቡንና ህዝቡን አዳነ። የነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በሊበርቲ እስር ቤት መታሰር፣ እነዚህ ነገሮች “[ለእሱ ልምድ እንደሚሰጡ[ት] እና [ለእሱ] ጥቅም እንደሆኑ” አስተምሮታል። በእምነት የተጋፈጥናቸው ፈጽሞ የማንመርጣቸው ፈተናዎች እና መስዋዕትነቶች፣ እኛንም ሆነ ሌሎችን ባልገመትነው መንገድ ሊባርክ ይችላል።

ሁሉም ነገር ለበጎ እንደሚሆን ዘለአለማዊ እይታን በምናገኝበት ጊዜ በጌታ ላይ እምነትን እንዲሁም ታማኝነትን እንጨምራለን፤ ፈተናዎቻችን “ለትንሽ ጊዜ ብቻ” እንደሆኑ እንረዳለን፤ መከራ ለጥቅማችን ሊቀደስ እንደሚችል እንገነዘባለን፤ አደጋዎች፣ ያለጊዜው የመጣ ሞት፣ ከባድ ህመም እና በሽታ የምድራዊ ኑሮ አካል እንደሆኑ እንገነዘባለን፤ እንዲሁም አፍቃሪው የሰማይ አባታችን ፈተናዎችን ለመቅጣት ወይም ለመፍረድ እንደማይሰጥ እናምናለን። እንጀራ ለሚለምን ድንጋይን፣ ዓሣ ለሚለምን ደግሞ እባብን አይሰጥም።

ፈተናዎች ሲመጡብን፣ ብዙ ጊዜ አጥብቀን የምንፈልገው አንድ ሰው እንዲሰማን እና ከእኛ ጋር እንዲሆን ነው። ለጊዜው፣ ዓላማቸው ለማጽናናት ቢሆንም፣ ሳይታሰቡ የሚሰጡ የተለመዱ መልሶች የማይጠቅሙ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ከእኛ ጋር የሚያዝን፣ የሚታመም እና የሚያለቅስ፤ ህመምን፣ ብስጭትን፣ ቁጣን እንኳን እንገልጽ የሚያደርጉን፤ እንዲሁም የማናውቃቸው ነገሮች እንዳሉ ከእኛ ጋር እውቅና የሚሰጥ ሰውን እንፈልጋለን።

እግዚአብሔርን እና ፍቅሩን ስንታመን፣ የእኛ ታላቅ የልብ ስብራት እንኳን በመጨረሻ ለበጎ ሊሆን ይችላል።

የምወዳቸውን ሰዎች ላይ ከባድ የመኪና አደጋ እንደደረሰ የተነገረኝን ቀን አስታውሳለሁ። እንደዚህ ባሉ ጊዜያት፣ በጭንቀት እና በእምነት፣ ከኢዮብ ጋር “እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን” ማለት ብቻ ነው የምንችለው።

በአለም አቀፍ ደረጃ የቤተክርስቲያኗ፣ ወደ 3,500 የሚጠጉ ካስማዎች እና አውራጃዎች እንዲሁም ወደ 30,000 የሚጠጉ አጥቢያዎች እና ቅርንጫፎች መሸሸጊያ እና መጠለያ ይሰጣሉ። ነገር ግን በካስማዎቻችን እና በአጥቢያዎቻችን ውስጥ፣ ታማኝ የሆኑ ቤተሰቦች እና ግለሰቦች፣ ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሚሆን እያወቁ እንኳን (እንዴት እንደሚሆን ባያውቁም) ብዙ ከባድ ፈተናዎችን ይጋፈጣሉ።

በኸደርስፊልድ፣ እንግሊዝ ውስጥ፣ ወንድም ሳሙኤል ብሪጅስቶክ አዲስ የካስማ ፕሬዚደንት እንዲሆን ከመጠራቱ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ ደረጃ አራት ካንሰር እንዳለበት ታወቀ። በተነገረው ከባድ የምርመራ ውጤት ምክንያት፣ ለምን ለቃለ መጠይቅ መሄድ እንዳለበት ባለቤቱ አናን ጠየቃት።

እህት ብሪጅስቶክም፣ “ምክንያቱም አንተ የካስማ ፕሬዚዳንት ሆነህ ስለምትጠራ ነው” አለችው።

የብሪጅስቶክ ቤተሰብ

በመጀመሪያ አንድ ወይም ሁለት ዓመት እንደቀረው የተነገረው ቢሆንም፣ ፕሬዚዳንት ብሪጅስቶክ (አሁን በዚህ ይገኛሉ) በአገልግሎት ላይ አራተኛ ዓመቱ ላይ ነው። መልካም እና አስቸጋሪ ቀናት አሉት። የእሱ ካስማ በእምነት፣ በአገልግሎት እና በደግነት እየተሰበሰበ ነው። ቀላል አይደለም፣ ነገር ግን ሚስቱ እና ቤተሰቡ በእምነት፣ በአመስጋኝነት እና ለመረዳት ቀላል በሆነ ሀዘን በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ፣ ዘለአለማዊ ደስታ ይሆናል ብለው በማመን እየኖሩ ነው።

ረጋ ስንል፣ ተቀባይ ልብ ሲኖረን እና አክባሪ ስንሆን፣ ጌታ የሚያቀርበው ቃል ኪዳን አባልነት ውበት፣ አላማ እና የመንፈስ እርካታ ሊሰማን እንችላለን። በተቀደሱ ጊዜያት፣ የእለት ተእለት ህይወታችን አካል የሆነበትን፣ ትናንሽ እና ቀላል ነገሮች ለሰጪዎች እና ተቀባዮች ጥቅም በጋራ የሚሰሩበትን ትልቁን ዘለአለማዊ እውነታ በጨረፍታ እንድንመለከት ያስችለናል።

የመጀመሪያው የሚስዮን ፕሬዚዳንቴ ልጅ የሆነችው ረበካ፣ መጽናናትን ለማግኘት ስትጸልይ ባልተጠበቀ አጋጣሚ የሌላ ሰውን ጸሎት በመመለስ እንዴት ጸሎቷን ጌታ እንደመለሰላት አካፈለች።

ረበካ የእናቷ የነበረውን የኦክስጅን ማሽን ሰጠቻቸው።

አንድ ቀን ምሽት ላይ፣ ረበካ እናቷ በቅርቡ በመሞቷ አዝና እያለች፣ ለመኪናዋ ነዳጅ እንድትገዛ ግልጽ የሆነ ስሜት ተሰማት። የነዳጅ ማደያው ቦታ ስትደርስ አንዲት አሮጊት ትልቅ የኦክሲጅን ማጠራቀሚያ ጋን ይዘው ተቸግረው ሲተነፍሱ አገኘቻቸው። በኋላ፣ ረበካ የእናቷ የነበረውን ተንቀሳቃሽ የኦክስጅን ማሽን ሰጠቻቸው። እኚህ እህት በአመስጋኝነት “ነፃነቴን መለስሽልኝ” አሉ። ልክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ስናገለግል ነገሮች የተስተካከሉ ይሆናሉ።

ከአንድ ልጅ ጋር እንደ አገልግሎት አጋር የተመደበ አንድ አባት፣ “አገልግሎት ማለት ጣፋጭ ምግቦችን ከሚያመጣ ጎረቤትነት ወደ ታማኝ ጓደኛና፣ የመንፈሳዊ ድንገተኛ አደጋ እርዳታ ሰጪ ወደመሆን መለወጥ ነው“ በማለት አብራርቷል።” በኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ኪዳን አባል መሆን ያጽናናል፣ ያገናኛል፣ ይቀድሳል።

በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ስንሆን እንኳን፣ መንፈሳዊ ዝግጅት ደካማ የነበርንበትን እና ብቸኝነት የተሰማንን ጊዜ የሰማይ አባት ያውቅ እንደነበር ሊያስታውሰን ይችላል። ለምሳሌ፣ ልጃቸው ወደ ሆስፒታል የተወሰደበት ቤተሰብ በኋላ ምን እንደሚጠብቃቸው መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ ነግሯቸው እንደነበር በማስታወስ ተፅናንተዋል።

አንዳንድ ጊዜ ጌታ እንዲሰማን ከሚያደርገው ትልቁ ዘለአለማዊ እውነታ ከመጋረጃው በስተጀርባ ያለን ቤተሰብን ያካትታል። አንዲት እህት ዳግም ወደተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በመቀየሯ ደስታን አግኝታለች። ነገር ግን ሁለቱ ሰቆቃዎች—የጀልባ አደጋን መመልከቷ እና በአሳዛኝ ሁኔታ እናቷ ራሷን ማጥፋቷ ህይወቷ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል።

እህት ፍርሃቷን አሸነፈች እናም ተጠመቀች።

ሆኖም ይህች እህት የውሃ ፍራቻዋን አሸንፋ በመጥለቅ ተጠመቀች። እና በጣም አስደሳች በሆነ ቀን፣ ለሟች እናቷ አንዲት ግለሰብ በቤተመቅደስ ውስጥ ስትጠመቅላት ለመመልከት በቃች። ይህች እህትም “የቤተመቅደስ ጥምቀት እናቴን ፈወሳት፣ እኔንም ነፃ አወጣኝ” በማለት ተናገረች። “እናቴ ከሞተች በኋላ ሰላም የተሰማኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው” አለች።

የእኛ የተቀደሰ መዝሙር ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሚሆን የእርሱን ማረጋገጫ ያስተጋባል።

ነፍሴ ሆይ፣ እረፊ፥ አምላክሽ ያከናውነዋል

ቀድሞ እንዳደረገው መጪውን ይመራል።

ተስፋሽ፣ መተማመንሽ ከቶ አይናወጥ፤

አሁን ምስጢር የሆነ ሁሉ በመጨረሻ ብሩህ ይሆናል።

ኑ፣ ኑ፣ ቅዱሳን፣ ልፋትን ወይም ስራን አትፍሩ

ግን በደስታ መንገዳችሁን ቀጥሉ።

ይህ ጉዞ ከባድ ቢመስላችሁም፣

ጸጋ እንደቀናችሁ ይሆናል።

ጉዞአችን ከማለቁ በፊት ብንሞት፣

አስደሳች ቀን! ሁሉም መልካም ነው!

መፅሐፈ ሞርሞን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ እና እግዚአብሔር ትንቢቶቹን እንደሚፈጽም በእጃችን ልንይዘው የምንችለው ማስረጃ ነው። ዘመናችንን ባዩ በመንፈስ የተነሳሱ ነቢያት የተጻፈው መፅሐፈ ሞርሞን፣ ጥልቅ በሆነ ልዩነት እየተቸገረ ባለ ቤተሰብ ልብ የሚነካ ታሪክ ይጀምራል። ነገር ግን፣ ከ1ኛ ኔፊ ምዕራፍ 1 እስከ ሞሮኒ ምዕራፍ 10 ድረስ ስናጠና እና ስናሰላስል፣ እዚያ ቦታ እና በዚያን ጊዜ የሆነው፣ እዚህ ላይ አሁን እንደሚባርከን ጠንካራ ምስክርነት እየሰጠን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንሳባለን።

በህይወት ባለ ነቢይ በኩል ብዙ የጌታ ቤቶችን በብዙ ቦታዎች ጌታ ሲያቀርብ፣ የቤተመቅደስ በረከቶች ለጥቅማችን አብረው ሲሰሩ እናያለን። በግላዊ መንገድ፣ ወደ እግዚአብሔር አባታችን እና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል ኪዳን እና ስርአት እንመጣለን እንዲሁም ስለ ምድራው ህይወት ዘለአለማዊ እይታን እናገኛለን። አንድ በአንድ፣ በስም፣ የተወዱ የቤተሰብ አባላትን—የአያቶቻችን—የማዳን ስርዓቶችን እና የቃል ኪዳን በረከቶችን በጌታ የአዳኞች ምሳሌ በጽዮን ተራራ ላይ እናቀርባለን።

ቤተመቅደሶች በብዙ ቦታዎች ወደ እኛ ሲቀርቡ፣ ልናቀርበው የምንችለው የቤተመቅደስ መስዋዕት በጌታ ቤት ውስጥ ቅድስናን በተደጋጋሚ መፈለግ ነው። ለብዙ አመታት፣ ወደ ቤተመቅደስ ለመምጣት አጠራቅመናል፣ አቅደናል እና መስዋዕት ሰጥተናል። አሁን፣ ሁኔታዎች በሚፈቅዱት መሰረት፣ እባካችሁ ዘወትር ወደ ጌታ ቅዱስ ቤቱ ኑ። የዘወትር የቤተመቅደስ አምልኮ እና አገልግሎት እናንተን እና ቤተሰባችሁን—ያላችሁትን ቤተሰብ እና የሚኖራችሁን እና አንድ ቀን ሊኖራችሁ የሚችለውን ቤተሰብ—ይባርክ፣ ይጠብቅ እና ያነሳሳው።

አያት ከቤተመቅደስ ውጪ

እንዲሁም፣ ሁኔታችሁ በሚፈቅድበት ጊዜ፣ እባካችሁ የቤተመቅደስ ልብሶች ባለቤትነት የመሆን በረከት እንዲኖራችሁ አስቡበት። የትሁት ቤተሰብ አባል የሆኑ ሴት አያት በዓለም ላይ ካለው ማንኛውም ነገር በላይ በጣም የሚፈልጉት የራሳቸው የቤተመቅደስ ልብሶች እንደሆኑ ተናግረዋል። ወንዱ የልጅ ልጃቸውም እንዲህ አለ፣ “አያቴ በሹክሹክታ፣ ‘የራሴ የቤተመቅደስ ልብስ ለብሼ አገለግላለሁ፣ ስሞትም ለብሼው እቀብራለሁ’” ብለው ተናግረዋል አለ። ጊዜአቸውም በደረሰ ጊዜ፣ ይህንኑ አደረጉ።

ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ “የምናምነው ሁሉ እና እግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ህዝብ የገባው ቃል ኪዳን ሁሉ በቤተመቅደስ ውስጥ አንድ ላይ ይሰባሰባሉ።”

በዚህ ምድር እና በዘለአለም፣ የፍጥረት አላማ እና የእግዚአብሔር ተፈጥሮ ሁሉንም ነገር ለበጎ ማድረግ ነው።

ይህ የጌታ ዘለአለማዊ አላማ ነው። ይህ የዘለአለም እይታው ነው። ይህ የዘለአለም ቃል ኪዳኑ ነው።

ህይወት ሲዘበራረቅ እና ዓላማውም ግልጽ በማይሆንበት ጊዜ፣ የተሻለ ህይወት ለመኖር ስትፈልጉ ነገር ግን እንዴት እንደምታደርጉት በማታውቁበት ጊዜ፣ ወደ እግዚአብሔር አባታችን እና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኑ። እነርሱ ህያው እንደሆኑ፣ እንደሚወዷችሁ፣ እና ሁሉም ነገሮች ለእናንተ ለበጎ እንዲሆኑ እንደሚፈልጉ እመኑ። ይህን ፍጻሜ በሌለው እና ዘለአለማዊ መንገድ እንደሚያደርጉ የምመሰክረው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ዮሐንስ 16፥33ን ይመልከቱ።

  2. ሮሜ 8፥28

  3. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 90፥24። “ሁሉም መልካም ነው” የሚለው ታዋቂው ሀረግ፣ ለእኛ ለመልካም ይሆናል ሳይሉ በአብዛኛው ጊዜ ነገሮች ደህና እና በትክክል የተገኙ እንደሆኑ ያስመስላል።

  4. ሙሴ 1፥3ን ይመልከቱ።

  5. አልማ 7፥11ን ይመልከቱ።

  6. 2 ኔፊ 9፥10-12ን ይመልከቱ፡፡ አንዳንዴም የሎሎች ጻድቅ ያለሆነ ስራ እኛን እንዲነካን በመፍቀድ፣ እግዚአብሔር የነጻ ምርጫን ያከብራል። ነገር ግን እኛ ለማድረግ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ በፈቃደኛነት ስንፈልግ፣ የኢየስይስ ክርስቶስ ጸጋ እና የእርሱ የኃጢያት ክፍያ ሀይል ሊያጸዱን፣ ሊፈውሱን፣ ቁስልን ሊሸፍኑልን፣ እና ከራሳችን እና ከመጋረጃው በሁለቱም በኩል ከሚገኙት ሌሎች ጋር ሊያስታርቁን ይችላሉ።

  7. ሞሮኒ 7፥6፣ 10–12ን ይመልከቱ። ፕሮፌሰር ቴሪ ዎርነር በዚህ ርዕስ ላይ በአስተያየት ፅፈውል።

  8. ሮሜ 3፥10ሞሮኒ 10፥25ን ይመልከቱ።

  9. ሞሮኒ 10፥32ን ይመልከቱ።

  10. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 122፥4፣ 7ን ይመልከቱ።

  11. በምንም በማንመርጣቸው አጋጣሚዎች እንማራለን። አንዳንዴ ሸክሞችን በጌታ እርዳታ መሸከም እነዚያን ሸክሞች ለመሸከም ያለንን ችሎታ ያሳድጋል፤ ሞዛያ 24፥10–15 “በመከራቸው ጊዜ ህዝ[ቡ]ን እንደ[ሚ]ጎበኝ” እና “ሸክማቸውን ማቅለል እንዲችሉ … ብርታትን [እንደሚሰጣቸው]” ጌታ ቃል የገባውን ያሳያል። አልማ 33፥23 እንደሚያስተምረው፣ “በልጁም ደስታ አማካኝነት ሸክማችሁ [ይቀልላችኋል]።” ሞዛያ 18፥8 “አንዳችሁ የአንዳችሁን ሸክም … ለመሸከም ፈቃደኞች [ስትሆኑ]” እነርሱም “ቀላል እንደሚሆኑ” ያስታውሰናል።

  12. ነቢዩ ኢሳይያስ ስለመሲህ እንዲህ ተናግሯል፦ “የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ … የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ … እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድ ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ” (ኢሳይያስ 61፥1–3)። እንደዚሁም፣ የመዝሙር ጸሀፊው የቃል ኪዳን አስተያየቱን እንዲህ አቅርቧል፦ “ለቅሶ ማታ ይመጣል፥ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል” (መዝሙር 30፥5) ይህም ለጻድቃን የተሰጠው ግርማዊውን የማለዳውን የመጀመሪያ ትንሳኤ ቃል ኪዳንን ያካትታል።

  13. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 122፣4። ፈተናዎች በዘለአለም አስተያየት “ትንሽ ጊዜ” ናቸው ማለት በዚህ ህይወት ውስጥ ከቀን ወደ ቀን ሊደርስብን የሚችለውን አሰቃቂ ህመም ወይም ስቃይ፣ ሊቋቋሙት የማይችሉት እንቅልፍ የሌላቸው ምሽቶች፣ ወይም በሚመጡት አዲስ ቀናት እርግጠኞች አለመሆንን ማቃለል ወይም አስቸጋሪነትን ወይም ፈተናዎችን ማስቀነስ አያመለክትም። ከእግዚአብሔር ርህራሄ እና ዘለአለማዊ እይታ አንጻር ወደ ኋላ ለመመልከት እና ምድራዊ ስቃያችንን ለማየት የምንችልበት ቃል ኪዳን ስለ ምድራዊ ህይወት ያለን ግንዛቤ እና በእምነት እስከ መጨረሻው በእርሱ ለመታመን ያለንን ተስፋ አንዳንድ እይታን ይጨምራል። በተጨማሪም፣ ለማየት ዓይኖች ሲኖሩን፣ ብዙ ጊዜ በዛሬ ጥሩ አለ፤ መልካም ነገር ለማየት ለወደፊቱ ጊዜ መጠበቅ የለብንም።

  14. 2 ኔፊ 2፥2 ይመልከቱ።

  15. ማቴዎስ 7፥9–10ን ይመልከቱ። እግዚአብሔር በህይወታችን እንዲያሸንፍ መፍቀድ የሚመጣውን ሁሉ በጸጥታ በመቀበል ብቻ አይደለም። የሰማይ አባት እና አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ የሚበጀንን ብቻ ሁልጊዜም እንደሚፈልጉ ማመን ነው። አሳዛኝ ሁኔታ ሲከሰት፣ “በእኔ ላይ ለምን?” ብለን ሳይሆን “ምን መማር እችላለሁ?” በማለት በእምነት መጠየቅ እንችላለን። እናም በእርሱ ጊዜ እና መንገድ፣ የካሳ በረከቶች እና እድሎች እንደሚመጡ እያወቅን በተሰበረ ልብ እና በተዋረደ መንፈስ ማዘን እንችላለን።

  16. ከሚያዝኑት ጋር ለማዘን እና መፅናናትን ለሚሹ መጽናናትን ለመስጠት ቃል ገብተናል (ሞዛያ 18:9)።

  17. ኢዮብ 1፥21

  18. ትምህርት እና ቃል ኪዳን 115፥6 ይመልከቱ።

  19. በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለ እምነት መፅሐፈ ሞርሞን “እግዚአብሔርን [በመርገም] እና መሞት ለሚፈልጉ፣” ነገር ግን “ይሁን እንጂ ለህይወታቸው በህይወት ለመቆየት በጎራዴአቸው [ስለሚታገሉት]” ከገለጸው ሰዎች የህልውና ጭንቀት እና ተስፋ መቁረጥ ጋር ተቃራኒ ነው (ሞርሞን 2፥14)።

  20. “Be Still, My Soul [ጸጥ በይ፣ ነፍሴ]” Hymns [መዝሙሮች]፣ ቁ. 124።

  21. “Come, Come, Ye Saints [ኑ፣ ኑ፣ ቅዱሳን]፣” Hymns [መዝሙር]፣ ቁጥር 30። ይህንንም አስቡበት፦

    እንዴት ታላቅ ጥበብ እና ፍቅር ነው። …

    የቤዛነት ታላቅ ንድፍ፣

    ፍትህ፣ ፍቅር፣ እና ምህረት የሚገናኙበት

    በመለኮታዊ ስምምነት!

    (“How Great the Wisdom and the Love [እንዴት ታላቅ ጥበብ እና ፍቅር ነው]” መዝሙር፣ ቁጥር 195።)

    በህይወት ጥርጣሬዎች መካከል፣ የቤዛነት ታላቅ ንድፍ ፍትህን፣ ፍቅርን እና ምህረትን ለጥቅማችን እንደሚያመጣ እናውቃለን።

  22. አብድዩ 1፥21ን ይመልከቱ። ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንዳስተማረው፦ “እነርሱ [የኋለኛው ቀን ቅዱሳን] እንዴት በጽዮን ተራራ ላይ አዳኞች ይሆናሉ? ቤተመቅደሶቻቸውን በመገንባት፣ የጥምቀት ገንዳዎችን በመገንባት፣ እና በመውጣት እና ለሞቱ አባቶቻቸው ሁሉ በመወከል ሁሉንም ስርዓቶች በመቀበል ነው” (Teachings of Presidents of the Church: Joseph Smith [የቤተክርስቲያኗ ፕሬዚዳንቶች ትምህርት፦ ጆሴፍ ስሚዝ] [2017 (እ.አ.አ)]፣ 473)።

  23. በቤተመቅደስ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳተፍ የሚሄዱ አባላት የቤተመቅደስ ልብስን በታላቅ ቅናሽ ዋጋ መግዛት ይችላሉ።

  24. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “The Temple and Your Spiritual Foundation [ቤተመቅደስ እና መንፈሳዊ መሰረታችሁ]፣” ሊያሆና፣ህዳር 2021 (እ.አ.አ)፣ 94።