አጠቃላይ ጉባኤ
ኢየሱስ ክርስቶስ በህይወታችን መካከል ላይ
የአጠቃላይ ባለስልጣኖች፣ የክልል ሰባዎች እና አጠቃላይ መሪዎች ድጋፍ


ኢየሱስ ክርስቶስ በህይወታችን መካከል ላይ

በጨለመብን ጊዜ እና በትልቅ ፈተናዎቻችን ወቅት የሚመጡ ጥልቅ የነፍስ ጥያቄዎች፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የማይናወጥ ፍቅር አማካኝነት ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

በምድራዊ ህይወት ውስጥ ስንጓዝ፣ አንዳንድ ጊዜ በፈተናዎች እንከበባለን፦ የምንወዳቸውን ሰዎች የማጣት፣ ከባድ ህመም፣ ከበሽታ ጋር የሚደረግ አድካሚ ፍልሚያ፣ የኢፍታዊነት ቁስል፣ የትንኮሳ ወይም የጭቆና አስጨናቂ ገጠመኞች፣ የስራ ማጣት ጥላ፣ የቤተሰብ መከራዎች፣ የብችኝነት የማይሰማ ጩኸት ወይም ልብ የሚሰብሩ የጦር ግጭቶች ውጤት። በእነዚህ ወቅቶች ነፍሶቻችን መሸሸጊያን ይሻሉ። ይህን ለማወቅ በቅንነት እንሻለን፦ የሰላምን ቅባት የምናገኘው የት ነው? በራስ መተማመን እና በጥንካሬ እነዚህን ተግዳሮቶች ለማሸነፍ እንዲረዳን እምነታችንን ማን ላይ ማድረግ እንችላለን? እኛን ለማንሳት እና ለማጽናት ትዕግስት፣ ሁሉን አቀፍ ፍቅር እና ሁሉን ቻይ እጅ ያለው ማን ነው?

በጨለመብን ጊዜ እና በትልቅ ፈተናችን የሚመጡ ጥልቅ የነፍስ ጥያቄዎች፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የማይናወጥ ፍቅር አማካኝነት ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። በእርሱ እና ቃል በተገባላቸው ዳግም በተመለሰው ወንጌሉ በረከቶች አማካኝነት የምንሻውን መልሶች እናገኛለን። ማለቂያ በሌለው የሃጥያት ክፍያው አማካኝነት፣ ስፍር ቁጥር የሌለው የተስፋ፣ የፈውስ እና በሕይወታችን ውስጥ ቋሚ እና ዘላቂ የሆነ የእርሱ መገኘት ስጦታ ተሰጥቶናል። እርሱ በነጻ የሚሰጠውን ሰላም እና ቤዛነት በደስታ በመቀበል በእምነት ለሚጠይቁ ሁሉ ይህ ስጦታ የሚገኝ ነው።

ጌታ የመለኮታዊ ፍቅሩ እና በጎነቱ ትክክለኛ መገለጫ የሆነውን እጁን ለእያንዳንዳችን ይዘረጋል። ለኛ ያለው ግብዣ ከቀላል ጥሪ በላይ ነው፣ በጸጋው ዘላቂ ሃይል የተጠናከረ መለኮታዊ ቃልኪዳን ነው። በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ፣ እርሱ በፍቅር እንዲህ ማረጋገጫ ይሰጠናል።

“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፤ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ።

“ቀንበሬንም በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።

“ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”

“ወደ እኔ ኑ” እና “ቀንበሬን ተሸከሙ” የሚሉት የእርሱ ግብዣ ግልጽነት፣“እረፍት ታገኛላችሁ” የሚለውን ፍቅሩን ያዘለ ሰፊ እና ሙሉ የሆነ ቃል ኪዳንን የከበረ ዋስትና ሃይል ተፈጥሮን ያረጋግጣል።

መንፈሳዊ ምሪትን በትጋት ስንሻ፣ ምስክርነታችንን ወደሚያጠናክርና ጥልቅ ለውጥ ወደሚያመጣ የግል የዕድገት መንገድ ውስጥ እንገባለን። የሰማይ አባታችንን እና የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ፍቅር ሰፊነት ስንረዳ፣ ልባችን በምስጋና፣ በትህትና እና የደቀመዝሙርነትን መንገድ ለመከተል በታደሰ ፍላጎት ይሞላል።

ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳስተማሩ፣ “የህይወታችን ትኩረት በእግዚአብሔር የደህንነት እቅድ … እና በኢየሱስ ክርስቶስና በወንጌሉ ላይ ሲሆን፣ በህይወታችን ከተከሰተውም ወይም ካልተከሰተውም ሁኔታ ባሻገር ደስታ ሊሰማን ይችላል።” ደስታ ከእርሱና በእርሱ ምክንያት ይመጣል።”

አልማ ለልጁ ለሔለማን ሲናገር እንዲህ ብሎ ገልጿል፦ “እናም አሁን፣ ልጄ ሔለማን ሆይ፣ እነሆ፣ አንተ ወጣት ነህ፣ እናም ስለዚህ፣ ቃሌን እንድትሰማና ከእኔም እንድትማር እለምንሃለሁ፤ እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ያደረጉ ሁሉ፣ በፈተናቸውና፣ በችግራቸው፣ እናም በስቃያቸው እንደሚደገፉና፣ በመጨረሻው ቀን ከፍ እንደሚደረጉ አውቃለሁ።”

ሔለማን ለወንድ ልጆቹ ሲናገር አዳኙን የህይወታችን ማእከል የማድረግ ዘለዓለማዊ መርህን እንዲህ ሲል አስተምሯል፦ “እናም አሁን ልጆቼ አስታውሱ፣ አስታውሱ፣ አዳኝ በሆነው የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በክርስቶስ ዓለት መሰረታችሁን መገንባት እንዳለባችሁ።”

ማቴዎስ 14 ውስጥ የመጥምቁ ዮሐንስን ሞት ከሰማ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን መሆን እንደፈለገ እንማራለን። ይሁን እንጂ፣ ብዙ ህዝብ ተከተለው። በርህራሄ እና በፍቅር በመነሳሳት እና ሃዘኑ ከተልዕኮው እንዲያዘናጋው ባለመፍቀድ፣ ኢየሱስ በመካከላቸው የታመሙትን በመፈወስ እነሱን ተቀበላቸው። ምሽቱ ሲቃረብ፣ ደቀ መዛሙርቱ ከባድ ፈተና ገጠማቸው፦ ብዙ ሰዎች እና አነስተኛ ምግብ። ኢየሱስ ህዝቡ ምግብ እንዲገዛ ይልካቸው ዘንድ ሃሳብ አቀረቡ፣ ነገር ግን ኢየሱስ በታላቅ ፍቅር እና ተስፋ ደቀ መዛሙርቱ እንዲመግቧቸው ጠየቃቸው።

ደቀ መዛሙርቱ በአፋጣኙ ችግር ተወጥረው ሳሉ፣ ኢየሱስ ለህዝቦቹ ያለውን የማይወላውል ፍቅር ጨምሮ ለአባቱ ያለውን እምነት እና ፍቅር አሳየ። ህዝቡ በሳር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ እንዲሁም አምስት ዳቦዎችን እና ሁለት አሳ ብቻ በመውሰድ፣ ከእርሱ ስልጣን እና ሃይል ይልቅ፣ ላዘጋጀው ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና መስጠትን መረጠ ።

ምስጋና ከሰጠ በኋላ፣ ኢየሱስ ዳቦውን ቆረሰ፣ ደቀ መዛሙርቱም ለህዝቡ አከፋፈሉ። በሚያስደንቅ ሁኔታ ምግቡ በቂ ብቻ ሳይሆን 12 መሶብ ሞልቶ ተትረፈረፈ። አምስት ሺህ ከሚሆኑ ወንዶች፣ በተጨማሪ ሴቶች እና ልጆችም ተመገቡ።

ይህ ተአምር ጥልቅ ትምህርት ያስተምራል፦ ፈተናዎች ሲገጥሙን፣ በችግሮቻችን ውስጥ መጠመድ ቀላል ነው። ይሁን እንጂ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የችግሮቻችን መፍትሄ ሁል ጊዜ ያለው እኛ ዘንድ ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሚመጣ ስለመሆኑ ምስጋናን በማቅረብ በአባቱ ላይ ትኩረት የማድረግን ሃይል ምሣሌነት አሳይቷል።

ችግሮች ሲያጋጥሙን፣ በተፈጥሮ በሚያጋጥሙን መሰናክሎች ላይ ማተኮር ይቀናናል። ተግዳሮቶቻችን ተጨባጭ ናቸው እንዲሁም ትኩረታችንን ይጠይቃሉ፣ ነገር ግን እነሱን የማሸነፍ መርህ የሚገኘው በትኩረታችን ውስጥ ነው። ክርስቶስን የሃሳባችን እና የተግባራችን ማዕከል በማድረግ፣ እራሳችንን ከእርሱ እይታ እና ጥንካሬ ጋር እናስተካክላለን። ይህ ማስተካከያ ችግሮቻችንን አይቀንስም፤ ከዚያ ይልቅ፣ በመለኮታዊ አመራር ስር እንድናልፋቸው ይረዳናል። ስለሆነም፣ ከፍ ካለ ጥበብ የሚመጡ መፍትሄዎችን እና እርዳታዎችን እናገኛለን። ይህንን ክርስቶስን ያማካለ አመለካከት መያዛችን፣ ከባድ የሚመስለው ችግር ከአዳኙ ጋር የታላቅ መንፈሳዊ እድገት መንገድ መሆን እንደሚችል እያስታወሰን፣ ፈተናዎቻችንን ወደ ድሎች ለመቀየር በጥንካሬ እና በማስተዋል ኃይል ይሰጠናል።

በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የወጣቱ አልማ ታሪክ ስለ ቤዛነት እና የአንድ ሰው ህይወት ክርስቶስን ያማከለ ሲሆን የሚያሣድርበትን ተፅዕኖ አሳማኝ ታሪክ ያቀርባል። በመጀመሪያ፣ አልማ ብዙዎችን ከጽድቅ መንገድ ወደ ተሳሳተ መንገድ በመምራት የጌታ ቤተክርስቲያን ይቃወም ነበር። ይሁን እንጂ፣ በመላዕክት ጉብኝት አማካኝነት በግልፅ የታየው መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ከተሳሳተ ስራው አነቃው።

በጨለመበት ጊዜ፣ በጥፋተኝነት ስሜት እና ከመንፈሳዊ ጭንቀቱ መውጫውን መንገድ ለማግኘት በፍለጋ ሲሰቃይ፣ አልማ አባቱ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ስለ ሃጥያት ክፍያው ሃይል ያስተማረውን ትምህርቶች አስታወሰ። ቤዛነትን ለማግኘት በሚሻ ልብ፣ ከልብ በሆነ ስሜት ንስሃ ገባ እንዲሁም የጌታን ምህረት አጥብቆ ተማጸነ። አልማ ምህረቱን በቅንነት በፈለገ ጊዜ ክርስቶስን ከሃሳቦቹ ሁሉ በፊት ያስቀደመበት ይህ ወሳኝ ሙሉ ለሙሉ እጅ የመስጠት ጊዜ አስደናቂ ለውጥ እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል። ከባዱ ጥፋተኝነት ሥሜት እና የተስፋ መቁረጥ ሰንሰለት ጠፍቶ በአስደናቂ የደስታ እና የሰላም ስሜት ተተካ።

ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋችን እና ለህይወት ታላቅ ህመም መልሳችን ነው። በእርሱ መስዋዕትነት፣ ለኃጢአታችን ዋጋ ከፍሏል እንዲሁም ስቃያችንን፣ ህመማችንን፣ ኢፍትሃዊነትን፣ ሀዘንን፣ እና ፍርሃትን በራሱ ላይ ወስዷል። በእርሱ ስንታመን እና ህይወታችንን በተሻለ ሁኔታ ለመለወጥ ስንፈልግ ይቅር ይለናል እንዲሁም ይፈውሰናል። በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ብዙዎችን እንደፈወሰው ሁሉ እርሱ ፈዋሻችን ነው፣ በእርሱ ፍቅር እና ሃይል አማካኝነት ልባችን ይጽናናል እንዲሁም ይጠገናል። እርሱ የነፍሳችንን ጥልቅ ፍላጎት፣ በእርሱ ቋሚ ፍቅር እና ደግነት የሚሞላ የህይወት ውሃ ነው። ይህ በውሃ ጉድጉዱ ለሳምራዊቷ ሴት ቃል እንደገባው አይነት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ጉድጉድ ነው።”

ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው እንደሆነ፣ ይህችን የተቀደሰች ቤተክርስቲያኑን የኋለኛው ቀን ቅዱሣን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እንደሚመራ በአክብሮት ምስክርነቴን እሰጣለሁ። የአለም አዳኝ፣ የሰላም አለቃ፣ የነገስታት ንጉስ፣ የጌቶች ጌታ፣ የአለም ቤዛ እንደሆነ እመሰክራለሁ። በእርሱ አእምሮ እና ልብ ውስጥ ሁሌም እንደምንኖር በእርግጠኝነት እናገራለሁ። ለዚህም ምስክር ይሆን ዘንድ፣ በዚህ የኋለኛው ቀናት ቤተክርስቲያኑን ዳግም መልሷል እንዲሁም በዚህ ሰዓት ፕሬዚዳንት ረስል ኤም. ኔልሰንን እንደ እርሱ ነብይ እና የቤተክርስቲያኗ ፕሬዚዳንት አድርጎ ጠርቷል። እኛ የዘላለም ህይወት እንዲኖረን ኢየሱስ ክርስቶስ ህይወቱን እንደሰጠ አውቃለሁ።

እርሱን የህይወታችን ማዕከል ለማድረግ ስንጥር፣ ራዕዮች ለኛ ይገለጡልናል፣ የእርሱ ጥልቅ ሰላም ይሸፍነናል እንዲሁም የእርሱ ወሰን የለሽ የሃጢያት ክፍያ ስርየታችንን እና ፈውሳችንን ያመጣል። በእርሱ አማካኝነት ለማሸነፍ ጥንካሬን፣ ለመፅናት ድፍረትን እና አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ ሰላምን እናገኛለን። የመልካም ነገሮች ሁሉ ምንጭ ወደሆነው፣ ወደ ሰማይ አባታችን መገኘት ለመመለስ በምናደርገው ጉዞ ላይ የተስፋ ምልክት ወደሆነው ወደ እርሱ ለመቅረብ በየቀኑ እንጣር። በተቀደሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን።

አትም