በሁሉም ነገሮች ተቃርኖ
ነጻ ምርጫችንን ለመጠቀም እንድንችል ግምት ውስጥ የምናስገባቸው ተቃራኒ አማራጮች ሊኖሩን ይገባል።
በቅርብ ጊዜ፣ በማናውቀው ከተማ ውስጥ በመኪና እየነዳን እያለ ሳላስበው ወደተሳሳተ አቅጣጫ ተጠመዘዝኩኝ፣ ይህም እኔን እና ባለቤቴን ደግሞ መዞር በማይቻልበት ወደማያልቅ ፈጣን ዋና መንገድ መራን። በጓደኛችን ቤት በጎ ግብዣ ተደርጎልን ነበር ሆኖም አሁን መድረስ ከነበረብን ጊዜ በጣም ዘግይተናል ብለን ተጨነቅን።
በዚህ ዋና መንገድ ላይ ሆኜ እንደገና መውጫ መንገድ በመፈለግ ላይ ሳለሁ፣ አቅጣጫ ለሚሰጠን ሲስተም(ጂፒኤስ) የተሻለ ትኩረት ባለመስጠቴ ራሴን ወቀስኩኝ። ይህ ተሞክሮ በህይወታችን ውስጥ አንዳንድ ጊዜ የተሳሳቱ ውሳኔዎችን እንዴት እንደምንወስድ እና አካሄዳችንን እንደገና መቀየር እስክንችል ድረስ ውጤቱን በትህትና እና በትዕግስት እንዴት መኖር እንዳለብን እንዳስብ አድርጎኛል።
ሕይወት ምርጫዎችን ስለማድረግ ብቻ ነው። የሰማይ አባታችን ትክክል ከሆኑት እና ሥህተት ከሆኑትበመምረጥ እንማር ዘንድ የመምረጥ መለኮታዊ ስጦታን ሠጥቶናል። ንስሐ ስንገባ የተሳሳቱ ምርጫዎቻችን እናስተካክላለን። እድገት የሚከሰተው እዚህ ላይ ነው። የሰማይ አባት ለሁላችንም ያለው እቅድ ስለ መማር፣ ስለማደግ እና ወደ ዘለአለማዊ ህይወት ስለመሻሻል ነው።
ከብዙ አመታት በፊት እኔና ባለቤቴ በሚስዮናውያን ትምህርት ከተሰጠን እና ቤተክርስቲያኗን ከተቀላቀልን ጀምሮ፣ በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ሌሂ ለልጁ ለያዕቆብ በሰጠው ጥልቅ ትምህርት ሁሌም እደነቃለሁ። “ጌታ እግዚአብሔር ሰው በራሱ እንዲያደርግ ሰጠው” እናም “ለሁሉም ነገሮች ተቃራኒ መኖር አስፈላጊ ነው” በማለት አስተምሮታል። ነጻ ምርጫችንን ለመጠቀም እንድንችል ግምት ውስጥ የምናስገባቸው ተቃራኒ አማራጮች ሊኖሩን ይገባል። ይህንንም በማድረግ፣ መፅሐፈ ሞርሞን “በበቂ ሁኔታ እንደተማርን” እና “የክርስቶስ መንፈስ” እያንዳንዳችን “መልካሙን ከክፉ እንድናውቅ” እንደተሰጠን ያስታውሰናል።
በህይወት ውስጥ፣ ያለማቋረጥ ብዙ አስፈላጊ ምርጫዎች ይገጥሙናል። ለምሳሌ፦
-
የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመከተል ወይም ላለመከተል መምረጥ።
-
እምነት እንዲኖረን እና ተአምራት ሲፈጸሙ ለመገንዘብ መምረጥ ወይም ለማመን ከመምረጥ በፊት የሆነ ነገር እስኪከሰት በጥርጣሬ መጠበቅ።
-
በእግዚአብሔር ላይ እምነት ለማዳበር መምረጥ ወይም በሚቀጥለው ቀን ሌላ ፈተና እንደሚመጣ በፍርሃት መጠባበቅ።
በዚያ ዋና መንገድ ላይ ወደተሳሳተ መንገድ እንደዞርኩት ሁሉ፣ በራሳችን ደካማ ውሳኔዎች ምክንያት በሚከሠቱ ውጤቶች ስንሰቃይ ህመሙ በተለይ ከፍ ያለ ይሆናል፣ ምክንያቱም ለስህተታችን የምንወቅሰው እራሳችንን ብቻ ስለሆነ ነው። ቢሆንም፣ ሁልጊዜ መለኮታዊ በሆነው የንስሃ ሂደት መጽጽናናትን መቀበል፣ የተሳሳቱ ነገሮችን እንደገና ማስተካከል እና ይህን በማድረግ ህይወትን የሚቀይሩ ትምህርቶችን ለመማር መምረጥ እንችላለን።
አንዳንድ ጊዜ ከቁጥጥራችን ውጭ ከሆኑ ነገሮች ተቃውሞ እና ፈተናዎች ሊደርሱብን ይችላሉ፣ ለምሳሌ፦
-
የጤንነት እና የሕመም ጊዜያት፡፡
-
የሰላም እና የጦርነት ጊዜያት።
-
የቀን እና የሌሊት ሰዓታት እና የበጋ እና የክረምት ወቅቶች።
-
የስራ ጊዜያት እሱን ተከትሎም የእረፍትን ጊዜያት።
ምንም እንኳን ሁኔታዎች በራሳቸው ስለሚከሰቱ ከእነዚህ መካከል አዘውትረን መምረጥ ባንችልም ለእነሱ እንዴት ምላሽ መስጠት እንዳለብን የመምረጥ ነፃነት አለን። ይህንን ማድረግ የምንችለው በአዎንታዊ ወይም በአሉታዊ የአስተሳሰብ ዝንባሌ ነው። ከተሞክሮ ለመማር መሻት እንዲሁም የጌታችንን እርዳታ እና ድጋፍ መጠየቅ እንችላለን፣ ወይም በዚህ ፈተና ውስጥ ብቻችንን እንደሆንን እና በራሳችን መወጣት እንዳለብን ማሰብ እንችላለን። ከአዲሱ እውነታ ጋር “የመርከብ መቅዘፊያ ሸራዎቻችንን ማስተካከል” እንችላለን ወይም ምንም ነገር ላለመቀየር መወሰን እንችላለን። በምሽት ጭለማ፣ ብርሀናችንን ማብራት እንችላለን፡፡ በክረምት ብርድም፣ ሙቀት የሚሰጡ ልብሶችን መልበስ እንችላለን፡፡ በህመም ጊዜ፣ ህክምናን ወይም መንፈሳዊ እርዳታን እንሻለን፡፡ ለእነዚህ ሁኔታዎች እንዴት ምላሽ መስጠት እንዳለብን እንመርጣለን።
“ማስተካከል”፣ “መማር”፣ “መፈለግ” እና “መምረጥ” ሁሉም የድርጊት ግሦች ናቸው። እኛ መራጮች እንጂ እቃዎች እንዳልሆንን አስታውሱ። እየሱስ “የህዝቡን ህመምና በሽታ በራሱ ላይ እንደሚወስድ … እንዲሁም እንደሚረዳ” ወይም ወደሱ ስንዞር እንደሚረዳን በፍጹም አንርሳ። ዐውሎ ነፋስ ሲመጣ “በእኛ ላይ ሥልጣን እንዳይኖረው” ዓለት በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መሠረታችንን ለመገንባት መምረጥ እንችላለን። “ወደ እርሱ የሚመጣን ሁሉ እርሱን እንደሚቀበለው” ቃል ገብቷል። “ወደ እርሱ የሚመጡም ብፁዓን ናቸው።”
አሁን፣ ከሁሉም የበለጠ አስፈላጊ የሆነ አንድ ተጨማሪ መርህ አለ። ሌሂ እንዲህ ብሏል “ ለሁሉም ነገሮች፣ “ተቃራኒ መኖር አስፈላጊ ነውና።” ይህ ማለት ተቃራኒ ነገሮች ተለያይተው አይኖሩም ማለት ነው። እንዲያውም እርስ በርስ ሊደጋገፉ ይችላሉ። የሆነ ጊዜ ሀዘንን ካላየን በስተቀር ደስታን ማወቅ አንችልም ነበር። አንዳንድ ጊዜ የረሃብ ስሜት ሲሰማን በቂ ምግብ ባገኘን ጊዜ አመስጋኞች እንድንሆን ይረዳናል። እዚህም እዚያም ያሉትን ውሸቶች ባናይ ኖሮ እውነትን ማወቅ አንችልም ነበር።
እነዚህ ተቃራኒዎች ሁሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ሁለቱም ወገኖች ሁል ጊዜ ይገኛሉ። ቻርልስ ዲከንስ “በጣም ጥሩ ወቅት ነበር፣ እንዲሁም በጣም መጥፎ ዘመን ነበር” ብሎ በፃፈበት ጊዜ ለዚህ ሃሳብ ምሳሌ እያቀረበ ነበር።
ከራሳችን ህይወት አንድ ምሳሌ ልስጥ። ማግባት፣ ቤተሰብ መመስረት እና ልጆች መውለድ በህይወታችን ካየናቸው ታላላቅ የደስታ ጊዜያትን አምጥቶልናል፣ ነገር ግን በማናችንም ላይ የሆነ ነገር ተከስቶ በነበረ ጊዜ በጣም ጥልቅ የሆነ ህመም፣ ጭንቀት እና ሀዘን አምጥቶብናል። ከልጆቻችን ጋር የነበረን ወሰን የሌለው ደስታ እና ሃሴት አንዳንድ ጊዜ በሚያገረሹ በሽታዎች፣ ሆስፒታል በመተኛት እና በጭንቀት የተሞሉ እንቅልፍ አልባ ምሽቶችን በማሣለፍ ፣ እንዲሁም በጸሎቶች እና በክህነት በረከቶች እፎይታ በማግኘት ይከተላሉ። እነዚህ ተቃራኒ ገጠመኞች በመከራ ጊዜ ብቻችንን እንዳልሆንን አስተምረውናል፣ እንዲሁም በጌታ እርዳታ እና እገዛ ምን ያህል መሸከም እንደምንችልም አሳይተውናል። እነዚህ ተሞክሮዎች በሚያስደንቅ ሁኔታ እኛን በመቅረፅ ረድተዋል፣ እንዲሁም ሁሉም ነገር በጣም ጠቃሚ ነበር። ወደዚህ የመጣንበት ምክንያት ይህ አይደለምን?
በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥም አንዳንድ አስደሳች ምሳሌዎችን እናገኛለን።
-
ሌሂ በምድረ በዳ የደረሰበት መከራ የእግዚአብሔርን ታላቅነት እንዲያውቅ እንደረዳው እና “[እግዚአብሄር] [መከራውን] ወደ [ጥቅሙ] እንደለወጠለት”ለልጁ ለያቆብ አስተምሮታል።
-
ጆሴፍ ስሚዝ በሊበርቲ እስር ቤት ባሣለፈው የጭካኔ የእስራት ጊዜ፣ ጌታ፣ “ይህ ሁሉ [ለእሱ] ልምድ እና ጥቅም”እንደሆነ ነግሮታል።
-
በመጨረሻም፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ማለቂያ የሌለው መስዋዕት በእርግጥ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የህመም እና የስቃይ ምሳሌ ነበር፣ ነገር ግን የእሱን የኃጢያት ክፍያ አስደናቂ በረከቶች ለሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች አምጥቷል።
ፀሀይ ባለበት ቦታ፣ ጥላም እዚያ መኖን አለበት። የጎርፍ መጥለቅለቅ ጥፋት ሊያመጣ ይችላል፣ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ህይወትንም ያመጣል። የሐዘን እንባ አብዛኛውን ጊዜ ወደ እፎይታ እና የደስታ እንባ ይለወጣል። የምንወዳቸው ሰዎች ሲለዩን የሚሰማን የሐዘን ስሜት በኋላ እንደገና በመገናኘት ደስታ ይካሳል። በጦርነትና በጥፋት ጊዜ፣ “የሚያይ አይን እና፣ የሚሰማም ጆሮ” ላላቸው ሰዎች ብዙ ትናንሽ የደግነትና የፍቅር ድርጊቶች ይፈፀማሉ።
የወደፊቱ ጊዜ ምን ሊያመጣብን እንደሚችል በመፍራት፣ ዛሬ የዓለማችን መገለጫ ብዙውን ጊዜ ፍርሃትና ጭንቀት ሆነዋል። ነገር ግን ኢየሱስ ግን እንድንታመን፣ እናም “ባሰ[ብነው] ነገር ሁሉ ወደ [እርሱ] [እንድንመለከት]፣ [እንዳንጠራጠር]፣ [እንዳንፈራ]” አስተምሮናል።
በህይወታችን የተመደበልንን የእያንዳንዱን ሳንቲም ሁለቱንም ጎኖች ለማየት ያለማቋረጥ በጣም ነቅተን እንስራ። ምንም እንኳን ሁለቱም ወገኖች አንዳንድ ጊዜ ለእኛ ወዲያውኑ ላይታዩን ቢችሉም፣ ሁልጊዜም እዚያ እንዳሉ ማወቅ እና ማመን እንችላለን።
ችግሮቻችን፣ ሀዘኖቻችን፣ ስቃያችን እና ህመማችን ማንነታችንን እንደማይገልጹ እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ይልቁንም እንድናድግ እና ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ እንዴት እንዲረዱን እናደርጋለን የሚለው ነው። ከችግራችን በተሻለ ሁኔታ የሚገልጹን አመለካከቶቻችን እና ምርጫዎቻችን ናቸው።
በጤንነታችሁ ጊዜ፣ ተንከባከቡት እንዲሁም ለእያንዳንዱ ጊዜ አመስጋኝ ሁኑ። በህመም ውስጥ ስትሆኑ ከእርሱ በትዕግስት መማርን ፈልጉ እንዲሁም ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንደገና ሊለወጥ እንደሚችል እወቁ። በሐዘን ውስጥ ስትሆኑ፣ ደስታ ጥግ ላይ እንደሆነ እመኑ፤ እኛ ብዙውን ጊዜ ገና ያንን ማየት አንችልም። ሆነ ብላችሁ ትኩረታችሁን ቀይሩ እንዲሁም ሃሳቦቻችሁን ወደ ችግሩ አወንታዊ ገጽታዎች አሳድጉ፣ ምክንያቱም እነሱ ያለጥርጥር ሁልጊዜም እዚያው ናቸው! አመስጋኝ መሆንን ፈጽማችሁ አትርሱ። ማመንን ምርጡ። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት እንዲኖራችሁ ምረጡ። ሁሌም በእርሱ ለመታመን ምረጡ። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን በቅርብ ጊዜ እንዳስተማሩን፣ ”ስለሰለስቲያል አስቡ!”
የሰማይ አባታችን ለእኛ ያለውን አስደናቂ እቅድ ሁሌም እናስታውስ። እሱ ይወደናል እንዲሁም በፈተናዎቻችን ውስጥ እንዲረዳን እና ወደ እሱ የምንመለስበትን በር እንዲከፍትልን የሚወደውን ልጁን ልኳል። ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው ነው እንዲሁም በሁሉም ጊዜ እዚያ ቆሞ እርዳታን፣ ጥንካሬን እና ደህንነትን ለመስጠት እሱን መጥራትን እንድንመርጥ እየጠበቀን ነው። ስለእነዚህ ነገሮች የምመሰክረው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።