በክህነት ቁልፎች ስጦታ ደስ ይበላችሁ
የክህነት ቁልፎች፣ የጌታን ዓላማዎች ለማሣካት እና ዳግም የተመለሰውን ወንጌል የሚቀበሉትን ሁሉ ለመባረክ፣ የእግዚአብሔርን ክህነት የመጠቀምን መንገድ ያስተዳድራሉ።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ዛሬ ለእኔ እና ለፕሬዚዳንት ዳልን ኤች. ኦክስ ታሪካዊ ቀን ነው። ከ40 ዓመታት በፊት፣ ሚያዝያ 7 ቀን 1984 (እ.አ.አ)፣ የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ቡድን አባላት ተደርገን የተጠራንበት ቀን ነበር። ይህንንም ጨምሮ እስከ ዛሬ በተደረገው በእያንዳንዱ ጠቅላላ ጉባኤ ተደስተናል። በተቀደሰ የመንፈስ ፍሰት መትረፍረፍ በድጋሚ ተባርከናል። በሚቀጥሉት ወራት፣ የዚህን ጉባኤ መልዕክቶች ደጋግማችሁ እንደምታጠኑ ተስፋ አደርጋለሁ።
እኔ በተወለድኩበት ጊዜ፣ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ በሥራ ላይ የነበሩ ስድስት ቤተመቅደሶች ነበሩ። እነርሱም በሴንት ጆርጅ፣ በሎጋን፣ በማንቲ፣ እና በሶልት ሌክ ሲቲ፣ ዩታ እንዲሁም በካርድስተን፣ በአልበርታ ካናዳ እና በሌይ፣ ሁዋዪ በእያንዳንዳቸው ውስጥ አንዳንድ ነበር። ሁለት ቀደምት ቤተመቅደሶች በከርትላንድ፣ ኦሃዮ እና ናቩ፣ ኢሊኖይ ለአጭር ጊዜ በአገልግሎት ላይ ነበሩ። ዋናው የቤተክርስቲያኗ አባላት ቡድን ወደ ምዕራብ ሲሄድ ቅዱሳኑ ሁለቱን ቤተመቅደሶች ትተው ለመሄድ ተገደዱ።
አንድ ሰው እሳት በማስነሣቱ ምክንያት የናቩ ቤተመቅደስ ወደመ። በኋላም እንደገና የተገነባ ሲሆን የተመረቀውም በፕሬዚዳንት ጎርደን ቢ. ሂንክሊ ነበር። የቤተክርስቲያኗ ጠላቶች የከርትላንድ ቤተመቅደሥን አረከሡት። በኋላም የከርትላንድ ቤተመቅደሥ ለብዙ ዓመታት በCommunity of Christ ባለቤትነት ይዞታ ሥር ነበር።
ባለፈው ወር፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በናቩ የሚገኙትን በርካታ ታሪካዊ ቦታዎች ጨምሮ የከርትላንድ ቤተመቅደስን መግዛቷን አስታውቀናል። ወደዚህ ሥምምነት ላይ እንድንደርስ ያደረጉንን ከCommunity of Christ [የክርቶስ ህብረተሰብ] መሪዎች ጋር በጨዋነት የተደረጉ እና ሁሉንም የሚጠቅሙ ውይይቶች በጣም እናደንቃለን።
የከርትላንድ ቤተመቅደስ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ዳግም መመለስ ላይ የተለየ ጠቀሜታ አለው። በዚያ ተከሥተው የነበሩት በርካታ ክንውኖች፣ ከሺህ ዓመታት በፊት የተተነበዩ ነበሩ እንዲሁም ዳግም የተመለሰችው የጌታ ቤተክርስቲያን የኋለኛውን ቀን ተልዕኮዋን እንድታሣካ አስፈላጊ ነበሩ።
ከእነዚህ ክስተቶች ውስጥ ከሁሉም የላቀ ጠቀሜታ የነበረው ሚያዝያ 3 ቀን 1836 (እ.አ.አ) እሑድ፣ የፋሲካ ዕለት የተከናወነው ነው። በዚያን ቀን፣ ጆሴፍ ስሚዝ እና ኦሊቨር ካውድሪ ተከታታይ የሆኑ አስደናቂ ጉብኝቶች አጋጥመዋቸዋል። በመጀመሪያ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ነበር። ነቢዩ፣ የአዳኙ “ዓይኖ[ች]ም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤ የራሱ ጠጕርም እንደ ንጹህ በረዶም ነጭ ነበሩ፤ ፊቱም ከብርቱ የጸሀይ ብርሀን በላይ የሚያበራ ነበር፤ ድምፁም እንደሚወርዱ ታላቅ ውኃዎች ድምፅ [እንደበረ]” መዝግቧል።
በዚያ ጉብኝት ወቅት፣ ጌታ ስለማንነቱ ማረጋገጫ ሠጥቷል። “እኔ ፊተኛውና ኋለኛው ነኝ፤ እኔ ህያውም ነኝ፣ የተገደልኩትም እኔ ነኝ፤ እኔም በአብ ዘንድ አማላጃችሁ ነኝ” ብሎ ነበር።
ከዚያም ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ መቅደሱን የራሱ ቤት አድርጎ መቀበሉን ተናገረ እንዲሁም ፦ “እነሆ፣ ይህን ቤት ተቀብዬዋለሁ፣ እና ስሜም በዚህ ይሆናል፤ እና በምህረትም ራሴን ለህዝቤ አሳያለሁና”በማለት ይህን አስደናቂ ቃል ገብቶ ነበር።
ይህ ጉልህ ቃል ኪዳን ዛሬ ላለው ለእያንዳንዱ የተመረቀ ቤተመቅደስ ይሠራል። የጌታ ቃል ኪዳን በግለሰብ ደረጃ ለእናንተ ምን ትርጉም እንዳለው እንድታሰላስሉ እጋብዛችኋለሁ።
ከአዳኙ ጉብኝት በኋላ ሙሴ ተገለጠ። ሙሴም፣ እስራኤልን የመሠብሠብ እና አሥሩ ነገዶችን የመመለስን ቁልፎችን ለጆሴፍ ስሚዝ ሰጠው፡፡
ይህ ራዕይ ሲያልቅ፣ “ኤልያ መጣ፣ እና የአብርሃም ወንጌል የዘመን ፍፃሜን [ለጆሴፍ] ሠጠው፡፡”
ከዚያም ነቢዩ ኤልያስ ተገለጠ፡፡ የእርሱ መገለጥ፣ ከዳግም ምፅዓት በፊት ጌታ ኤሊያስን እንደሚልክ፣ “የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች እንደሚመልስ” የተናገረውን የሚልኪያን ቃል ኪዳን ፈፅሟል። ከዚያም ኤልያስ የዕትመት ኃይል ቁልፎችን ለጆሴፍ ስሚዝ ሰጠው።
በጌታ አመራር፣ የእነዚህ ቁልፎች በሦስት ሰማያዊ መልዕክተኞች ወደ ምድር የመመለሣቸው ጠቀሜታ ተጋኖ ሊገለጽ አይችልም። የክህነት ቁልፎች የአመራሮችን ስልጣን እና ሃይል ያካትታሉ። የክህነት ቁልፎች፣ የጌታን ዓላማዎች ለማሣካት እና ዳግም የተመለሰውን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የሚቀበሉትን ሁሉ ለመባረክ፣ የእግዚአብሔርን ክህነት የመጠቀምን መንገድ ያስተዳድራሉ።
ቤተክርስቲያኗ ከመደራጀቷ በፊት፣ ሰማያዊ መልዕክተኞች የአሮናዊ እና የመልከ ጼዴቅ ክህነትን ለነቢዩ ጆሴፍ ሠጥተውት እንደነበር እና የሁለቱንም ክህነቶች ቁልፎች ሠጥተውት እንደነበር ማስተዋል ያስፈልጋል። እነዚህ ቁልፎች፣ ጆሴፍ ስሚዝ ቤተክርስቲያኗን በ1830 (እ.አ.አ) ያደራጅ ዘንድ ስልጣን ሰጡት።
ስለዚህ የእነዚህ ሶስት ተጨማሪ የክህነት ቁልፎች ማለትም፣ እስራኤልን የመሰብሰብ ቁልፎች፣ የአብርሃም ወንጌል ቁልፎች እና የዕትመት ሃይል ቁልፎች በ1836 (እ.አ.አ) በከርትላንድ ቤተመቅደስ ውስጥ መሰጠቱ አስፈላጊ ነበር። እነዚህ ቁልፎች፣ በመጋረጃው በሁለቱም ወገን ያለውን እስራኤልን እንዲሰበስቡ፣ ሁሉንም የቃል ኪዳን ልጆች በአብርሃም በረከቶች እንዲባርኩ፣ በክህነት ሥርዓቶች እና ቃል ኪዳኖች በኩል የማጽደቅ እትመትን እንዲያደርጉ እና ቤተሰቦችን ለዘለዓለም አንድ ላይ እንዲያትሙ ለጆሴፍ ስሚዝ እና ከእርሱ በኋላ ለመጡት ለሁሉም የጌታ ቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንቶች ሥልጣን ሠጧቸው። የእነዚህ የክህነት ቁልፎች ኃይል ወሠን የለውም እንዲሁም አስደናቂ ነው።
የክህነት ቁልፎች ዳግም ወደ ምድር ባይመለሱ ኖሮ የእናንተ ህይወት እንዴት የተለየ ሊሆን ይችል እንደነበረ አስቡ። የክህነት ቁልፎች ባይኖሩ ኖሮ በቤተመቅደስ ቡራኬ አማካኝነት የእግዚአብሔር ኃይል ሊሰጣችሁ አይችልም ነበር። የክህነት ቁልፎች ባይኖሩ ኖሮ ቤተክርስቲያኗ ወሳኝ የትምህርት እና የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ብቻ ከመሆን የዘለለ ብዙ ጠቀሜታ ሊኖራት አይችልም። የክህነት ቁልፎች ባይኖሩ ኖሮ ማናችንም ብንሆን ከቤተሠብ አባላቶቻችን ጋር ለዘለዓለም የሚያስተሳስሩንን እና በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ጋር እንድንኖር የሚፈቅዱልንን አስፈላጊ ሥርዓቶች እና ቃል ኪዳኖች ማግኘት አንችልም ነበር።
የክህነት ቁልፎች፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን በምድር ላይ ካሉ ከሌሎች ከማናቸውም ድርጅቶች የተለየች ያደርጓታል። ሌሎች ብዙ ድርጅቶች በዚህ ምድር ላይ ህይወታችሁን የተሻለ ሊያደርጉላችሁ ይችሉ ይሆናል፣ በርግጥም ያደርጋሉ። ነገር ግን ማንኛውም ሌላ ድርጅት፣ ከሞት በኋላ በሚኖራችሁ ህይወት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል እንዲሁም የሚያሳድር አይሆንም።
የክህነት ቁልፎች፣ ለአብርሃም ቃል የተገቡትን በረከቶች ሁሉ፣ ለእያንዳንዱ ቃል ኪዳኑን ለሚጠብቁ ወንዶች እና ሴቶች እንዲገኙ የማድረግ ሥልጣንን ያጎናፅፉናል። የቤተመቅደስ ሥራ፣ የኖሩበት ቦታ ወይም ጊዜ ግምት ውስጥ ሣይገባ፣ እነዚህ ድንቅ በረከቶች ለሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች እንዲገኙ ያደርጋል። የክህነት ቁልፎች እንደገና በምድር ላይ ስላሉ ደስ ይበለን!
በሚከተሉትን ሦስት ዓረፍተ ነገሮች ላይ በአፅንዖት እንድታስቡባቸው እጋብዛችኋለሁ፦
-
የእስራኤል መሰብሰብ፣ እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ የሚኖሩትን ሁሉንም ልጆቹን እንደሚወድ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
-
የአብርሃም ወንጌል፣ እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ የሚኖሩትን ሁሉንም ልጆቹን እንደሚወድ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ሁሉም ወደእርሱ እንዲመጡ ይጋብዛል—“ጥቁርም ነጭም፣ ባሪያውንና ነፃውን፤ ወንድን እና ሴትን፤ … በእግዚአብሔር ፊት ሁሉም አንድ ነው።”
-
የዕትመት ኃይል እግዚአብሔር ምን ያህል ሁሉንም ልጆቹን እንደሚወድ እና እያንዳንዳቸው ወደ ቤት፣ ወደ እርሱ መመለስን እንዲመርጡ እንደሚፈልግ የሚያሳይ መለኮታዊ ማስረጃ ነው።
በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል ዳግም የተመለሱት የክህነት ቁልፎች፣ ቃል ኪዳናቸውን የሚጠብቁ ወንዶች እና ሴቶች ሁሉ በግለሠብ ደረጃ የሚሠጡ አስደናቂ መንፈሳዊ መብቶች እንዲኖሯቸው ያስችሏቸዋል። እዚህም እንደገና፣ ከከርትላንድ ቤተመቅደሥ ቅዱስ ታሪክ የምንማረው ብዙ ነገር አለ።
የጆሴፍ ስሚዝ የከርትላንድ ቤተመቅደሥ የምረቃ ፀሎት፣ ቤተመቅደሥ፣ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ የህይወት ፈተናዎችን መቋቋም እንችል ዘንድ፣ ለእኔ እና ለእናንተ መንፈሳዊ ሃይልን እንዴት እንደሚሰጠን ያስተምራል። በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ክፍል 109 ውስጥ የተመዘገበውን ያንን ፀሎት እንድታጠኑት አበረታታችኋለሁ። ያ በራዕይ የመጣ የምረቃ ፀሎት፣ ቤተመቅደሥ “የጸሎት ቤት፣ የጾም ቤት፣ የእምነት ቤት፣ የመማሪያ ቤት፣ የክብር ቤት፣ የሥርዓት ቤት፣ የእግዚአብሔር ቤት” እንደሆነ ያስተምራል።
ይህ የባህርያት ዝርዝር ከቤተመቅደሥ ምንነት መግለጫነት የበለጠ ነው። በጌታ ቤት ውስጥ የሚያገለግሉ እና የሚያመልኩ ሠዎች ሊያገኙ ስለሚችሏቸው ነገሮች የተሠጠ የተሥፋ ቃል ነው። ለጸሎት መልሶችን፣ የግል መገለጥን፣ ላቅ ያለ እምነትን፣ ጥንካሬን፣ መጽናኛን፣ ተጨማሪ እውቀትን እና ተጨማሪ ኃይልን እንደሚቀበሉ መጠበቅ ይችላሉ።
በቤተመቅደሥ ውስጥ የምታሣልፉት ጊዜ፣ስለሰለሥቲያል እንድታስቡ እንዲሁም ስለእውነተኛ ማንነታችሁ፣ ወደፊት ማን መሆን እንደምትችሉ እና ለዘለዓለም ልትኖሩት ስለምትችሉት ህይወት እይታ እንድታገኙ ይረዳችኋል። የዘወትር የቤተመቅደሥ አምልኮ ራሳችሁን የምታዩበትን እንዲሁም ከእግዚአብሔር አስደናቂ እቅድ ጋር ተስማምታችሁ መኖር የምትችሉበትን መንገድ ያጎለብታል። ያንን ቃል እገባላችኋለሁ።
በቤተመቅደሥ “የመንፈስ ቅዱስን ሙላት እንደምንቀበል” ቃል ተገብቶልናል። ያ የተስፋ ቃል፣ ዘለዓለማዊ እውነትን በቅንነት ለሚፈልግ ለእያንዳንዱ ግለሠብ ስለ ሰማያት መከፈት አስመልክቶ ምን ማለት እንደሆነ አስቡ።
በተጨማሪም በቤተመቅደሥ ውስጥ የሚያመልኩ ሁሉ በእግዚአብሔር ሃይል ታጥቀው እና የመላዕክት “ጥበቃ” ተሠጥቷቸው እንደሚወጡ ትምሕርት ተሰጥቶናል። የእግዚአብሔር ሃይል የታጠቃችሁ የቤተመቅደሥ ቡራኬን የተቀበላችሁ ሴት ወይም ወንድ በመሆናችሁ፣ ህይወትን ለብቻችሁ መጋፈጥ እንደሌለባችሁ ማወቃችሁ ምን ያህል በራስ መተማመናችሁን ይጨምራል? በእርግጥ መላዕክት እንደሚረዷችሁ ማወቃችሁ ምን ዓይነት ድፍረት ይሰጣችኋል?
በመጨረሻም፣ በጌታ ቤት ውስጥ በሚያመልኩ ሰዎች ላይ “የክፋት ሴራ” እንደማይሠለጥን ቃል ተገብቶልናል።
በቤተመቅደሥ ውስጥ ማግኘት የቻልናቸውን መንፈሳዊ መብቶች መረዳታችን ዛሬ ለእያንዳንዳችን ወሳኝ ነው።
ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ የሚከተለውን ቃል እገባላችኋለሁ። ሁኔታችሁ በሚፈቅድላችሁ መጠን በቤተመቅደሥ አዘወትራችሁ የማምለክን ያህል በበለጠ ሁኔታ የብረቱን በትር አጥብቃችሁ ለመያዝ የሚረዳችሁ ምንም ነገር የለም። የዓለም የጨለማ ጭጋግ ሲያጋጥማችሁ የበለጠ የሚጠብቃችሁ ምንም ነገር የለም። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን እና የእርሱን የኃጢያት ክፍያ ምሥክርነት የበለጠ የሚያጠናክርላችሁ ወይም የእግዚአብሔርን ድንቅ ዕቅድ የበለጠ እንድትገነዘቡ የሚረዳችሁ ምንም ነገር የለም። በህመም ጊዜ የበለጠ መንፈሣዊ ማፅናኛን የሚሠጥ ምንም ነገር የለም። ሠማያትን ይበልጥ የሚከፍት ምንም ነገር የለም። ምንም!
ቤተመቅደሥ፣ ለአብርሃም የተገቡለትን በረከቶችሁሉ ልንቀበል የምንችልበት በምድር ላይ ያለ ብቸኛው ቦታ ስለሆነ፣ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ያለው ታላቅ በረከቶች የሚገኙበት ቦታ ነው። ለዚህ ነው የቤተመቅደሥ በረከቶችን ለቤተክርስቲያኗ አባላት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በጌታ አመራር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ የምናደርገው። ስለዚህም፣ በሚከተሉት 15 ቦታዎች አዳዲስ ቤተመቅደሶችን ለመገንባት ያለንን ዕቅድ ስናስታውቅ ደሥተኞች ነን፦
-
ዩቱሮአ፣ የፈረንሳይ ፖሊኔዢያ
-
ቺዋዋ፣ ሜክሲኮ
-
ፍሎሪያኖፖሊስ፣ ብራዚል
-
ሮሳሪዮ፣ አርጀንቲና
-
ኤዲንበርግ፣ ስኮትላንድ
-
ብሪስቤን፣ የደቡብ አውስትራሊያ አካባቢ
-
ቪክቶሪያ፣ ቢሪቲሽ ኮሎምቢያ
-
ዩማ፣ ኤሪዞና
-
ህዩስተን፣ ደቡብ ቴክሳስ አካባቢ
-
ደ ሞይን፣ አዮዋ
-
ሲንሲናቲ፣ ኦሃዮ
-
ሆኖሉሉ፣ ሃዋኢ
-
ዌስት ጆርዳን፣ ዩታ
-
ሊሃይ፣ ዩታ
-
ማርሲያቦ፣ ቬኔዙዌላ
ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ይህች የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ናት። እርሱም የቤተክርስቲያኗ እራስ ነው። እኛ የእርሱ ደቀ መዛሙርት ነን።
እኔ እና እናንተ ልንቀበላቸው ፍቃደኛ እና ብቁ በሆንንባቸው ሁሉንም መንፈሳዊ በረከቶችን እንድናገኝ በሚያስችሉን ዳግም በተመለሡት የክህነት ቁልፎች እንደሰት። ይህንን የምመሰክረው ቅዱስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።