አጠቃላይ ጉባኤ
ተዓምራት፣ መላዕክት እና የክህነት ሀይል
የአጠቃላይ ባለስልጣኖች፣ የክልል ሰባዎች እና አጠቃላይ መሪዎች ድጋፍ


ተዓምራት፣ መላዕክት እና የክህነት ሀይል

ተአምራትን እና የመላእክትን አገልግሎት ጨምሮ የክህነት በረከቶችን የምትፈልጉ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ባዘጋጀልን የቃል ኪዳን መንገድ ተጓዙ።

በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች ተዓምራት ከእንግዲህ ወዲህ የሉም ይላሉ፣ መላእክት የልብ ወለድ ታሪክ እንደሆኑና ሰማያት እንደተዘጉ ይናገራሉ። እኔ ተዓምራት እንዳልቆሙ፣ መላዕክትም በመካከላችን እንዳሉ እና ሰማያት በእውነት ክፍት እንደሆኑ እመሰክራለሁ።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለዋና ሐዋርያው ለጴጥሮስ የክህነት ቁልፎችን ሰጥቶት ነበር። በእነዚህ ቁልፎች አማካኝነት ጴጥሮስ እና ሌሎቹ ሐዋርያት የአዳኙን ቤተክርስቲያን መርተዋል። ነገር ግን እነዚያ ሐዋርያት ሲሞቱ፣ የክህነት ቁልፎች ከምድር ላይ ተወሰዱ።

የጥንት የክህነት ቁልፎች እንደተመለሱ እመሰክራለሁ። ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና ሌሎች የጥንት ነቢያት ከሞት እንደተነሱ አካላት ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ተገልጠው ጌታ “የዘመኑ ፍጻሜን ወንጌልንና የመንግስቱን ቁልፎች” ያለውን ሰጥተውታል።

እነዚህ ቁልፎች እስከ ዛሬ ድረስ ከነቢይ ወደ ነቢይ ተላልፈዋል። እንደ ነቢያት፣ ባለራእዮች፣ እና ገላጮች የምንደግፋቸው 15 ሰዎች የአዳኙን ቤተክርስቲያን ለመምራት ይጠቀሙባቸዋል። እንደ ጥንቱ ሁሉ፣ ሁሉንም የክህነት ቁልፎች የሚይዝ እና የተፈቀደለት አንድ የበላይ ሐዋርያ አለ። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን፣ በኛ ዘመን የተመለሰችው የክርስቶስ ቤተክርስቲያን፡ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን፡ ነቢይ እና ፕሬዚዳንት ናቸው።

በአዳኛችን ቤተክርስቲያን በኩል፣ የክህነት በረከቶችን እንዲሁም ለህይወታችን የሚረዳንን የእግዚአብሄር ሀይል እንቀበላለን። በክህነት ስልጣን ቁልፎች ስር፣ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን እና በእርሱ ፊት ለመኖር የሚያዘጋጁንን ቅዱስ ሥርዓቶች እንቀበላለን። በጥምቀት እና ማረጋገጫ በመቀበል በመጀመር፣ ከዚያም፡ በቤተመቅደስ ውስጥ ወደ እርሱ በሚወስደን የቃል ኪዳን መንገድ ወደፊት እንገሰግሳለን።

እጆች በራሳችን ላይ ሲጫኑ፣ ምሪትን፣ መጽናናትን፣ ምክርን፣ ፈውስን እና ኢየሱስ ክርስቶስን የመከተል ሀይልን ጨምሮ የክህነት በረከቶችንም እናገኛለን። በሕይወት ዘመኔ ሁሉ በዚህ ታላቅ ኃይል ተባርኬአለሁ። በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተገለፀው፣ ይህንን የቅዱስ መልከ ጼዴቅ የክህነት ኃይል እንለዋለን።

በወጣትነቴ ለዚህ ኃይል ትልቅ አክብሮት አገኘሁ፣ በተለይ በክህነት በረከቶች የተገለጠ ስለነበር። እኔና ጓደኛዬ በቺሊ ወጣት ሚስዮናዊ ሆነን እያገለገልን ሳለ ተይዘን ታሰርንና ተለያየን። ለምን እንደሆነ ፈጽሞ አልተነገረንም ነበር። ይህ ወቅት ከፍተኛ የፖለቲካ አለመረጋጋት የተፈጠረበት ወቅት ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ በወታደራዊ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች፣ ከዚያ በኋላ የገቡበት አይታወቅም ነበር።

ምርመራ ከተደረገብኝ በኋላ፣ የምወዳቸውን ሰዎች ዳግመኛ ልያቸው አልያቸው ሣላውቅ በእስር ቤት ክፍል ውስጥ ብቻዬን ቁጭ አልኩ። ወደ ሰማይ አባቴ ዞር አልኩኝና፣ አጥብቄ ተማጸንኩ፣ “አባት ሆይ፣ ሚስዮናውያኖችህን እንደምትጠብቅ ሁልጊዜ ተምሬያለሁ። እባክህ አባቴ፣ እኔ ልዩ አይደለሁም፣ ነገር ግን ታዛዥ ነበርኩ እናም ዛሬ ማታ የአንተ እርዳታ ያስፈልገኛል።”

ከብዙ አመታት በፊት የዚህ እርዳታ ዘር ተተክሎ ነበር። ከተጠመቅሁ በኋላ፣ የቤተክርስቲያን አባልነትን ማረጋገጫ ተሠጠኝ፤ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታም ተቀበልኩ። ብቻዬን፣ በወኅኒው ቤት ጀርባ ስጸልይ፣ መንፈስ ቅዱስ ወዲያው ወደ እኔ መጣና አጽናናኝ። ከፓትርያርክ በረከቴ በጣም የተለየ ጥቅስ ወደ አእምሮዬ አመጣ፣ ይህም ሌላው የክህነት በረከት ነው። በውስጡም፣ እግዚአብሔር በታማኝነቴ ምክንያት ከውብ፤ በጎ እና በፍቅር ከተሞላች ሴት ጋር በቤተመቅደስ ውስጥ ለዘመናት እና ለዘለአለም እንደምታተም፣ የከበሩ ወንድና ሴት ልጆች ወላጆች እንደምንሆን፣ እናም በእስራኤል ውስጥ እንደ አባት እንደምባረክ እና ከፍ ከፍ እንደምደረግ ቃል ገብቶልኝ ነበር።

ስለ ወደፊቱ ሕይወቴ የሚናገሩት እነዚህ አነሳሽ ቃላት ነፍሴን በሰላም ሞሏት ። ሁሌም ቃል ኪዳኖቹን ከሚጠብቀው ከአፍቃሪው የሰማይ አባቴ እንደመጡ አውቅ ነበር። በዚያች ቅጽበት፣ እንደምለቀቅ እና እነዚህን ተስፋዎች ሲፈጸሙ ለማየት በሕይወት እንደምኖር ማረጋገጫ አገኘሁ።

ከአንድ አመት በኋላ፣ የሰማይ አባት ውበ፡ በጎ እና ፍቅር በተሞላች ሚስት ባረከኝ። እኔና ሊኔት በቤተ መቅደስ ውስጥ ታተምን ። በሦስት ውድ ወንዶች እና አራት ውድ ሴቶች ልጆች ተባርከናል። የ17 አመት ልጅ ሳለሁ በተቀበልኩት የፓትርያሪክ በረከት እግዚአብሔር በሰጠኝ ተስፋ መሰረት አባት ሆንኩኝ።

“ስለሆነም፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ [እና እህቶቼ]፣ ክርስቶስ ወደ ሰማይ በማረጉ ተዓምራት ቆመዋልን? …

“… እነሆ አልቆሙም እላችኋለሁ፣መላዕክቶችም ቢሆኑ የሰው ልጆችን ማገልገላቸውን አላቆሙም።”

ተዓምራት እና አገልግሎት አብዛኛውን ጊዜ የክህነት ሀይል ቀጥተኛ ውጤት በመሆን በህይወታችን ውስጥ በተደጋጋሚ እንደሚከሰቱ እመሰክራለሁ። አንዳንድ የክህነት በረከቶች እኛ ማየት እና መረዳት በምንችልባቸው መንገዶች ወዲያውኑ ይፈጸማሉ። ሌሎቹ ደግሞ ቀስ በቀስ እየተገለጡ የሚመጡ ሲሆኑ በዚህ ህይወት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እውን ሊሆኑ አይችሉም። ነገር ግን እግዚአብሔር የገባውን ቃል ሁል ጊዜ ይጠብቃል፣ ከቤተሰባችን ታሪክ በዚህ ዘገባ ላይ እንደተገለጸው፡-

ወንዱ አያቴ ግራንት ሪሴ ቦወን ታላቅ እምነት ያለው ሰው ነበር። የራሱን ፓትርያርክ በረከት እንዴት እንዳገኘ ሲተርክ የሰማሁትን በደንብ አስታውሳለሁ። በማስታወሻው ላይ፣ “ፓትርያርኩ የፈውስ ስጦታን ቃል ገብቶልኛል። ‘ድውዮች ይድናሉ። አዎን፣ ሙታን በእጅህ ይነሳሉ’” ብሏል።

ከዓመታት በኋላ፣ አያቴ ሳር እየከመረ በነበረበት ሰዓት ወደ ቤቱ መመለስ እንዳለበት ተሰማው። አባቱ ወደ እሱ ሲመጣ አገኘው። አባቱም “ግራንት፣ እናትህ አሁን ከዚህ አለም በሞት ተለየች” አለው።

ከአያቴ የግል ማስታወሻ እንደገና እጠቅሳለሁ፡- “አልቆምኩም ነገር ግን በፍጥነት ወደ ቤት ገብቼ በአልጋ ላይ ተኝታ ወዳለችበት የፊት በረንዳ ላይ ወጣሁ። ተመለከትኳት እናም በእሷ ውስጥ ምንም የህይወት ምልክት እንደሌለ አየሁ። በእምነቴ ታማኝ ከሆንኩ በሽተኞች እንደሚፈወሱ እና ሙታንም እንደሚነሱ በፓትርያሪክ በረከቴ የተገባልኝን ቃል አስታወስኩ። እጆቼን ጭንቅላቷ ላይ በመጫን፣ ጌታ በፓትርያርኩ የገባልኝ ቃል እውነት ከሆነ፣ በዚህ ጊዜ እናቴን ወደ ህይወት እንደገና እንድትመለስ ነገርኩት። ይህን የሚያደርግልኝ ከሆነ፣ የእርሱን መንግስት ለመገንባት የምችለውን ሁሉ ከማድረግ በፍጹም እንደማላመነታ ቃል ገባሁኝ። እየጸለይኩ እያለ፣ አይኖቿን ገልጣ፣ ‘ግራንት: እባክህ አንሳኝ። በመንፈስ አለም ውስጥ ነበርኩ አንተ ግን መልሰህ ጠራኸኝ። ይህ ምን ጊዜም ለአንተም ሆነ ለተቀሩት ቤተሰቦቼ ምስክርነት ይሁንላችሁ’” አለች።

ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን ተዓምራትን እንድንፈልግና እንድንጠብቅ አስተምረውናል። ክህነት ስለተመለሰ፣ የእግዚአብሔር ሀይል እና ስልጣን በምድር ላይ እንዳለ እመሰክራለሁ። በጥሪ እና ምክር ቤቶች አማካኝነት፣ ወንዶች እና ሴቶች፣ ወጣት እና አዛውንቶች፣ በክህነት ስራ መሳተፍ ይችላሉ። መላእክት የተሳተፉበት፣ የተዓምራት ሥራ ነው። የሰማይ ሥራ ነው፡ እናም የእግዚአብሔርን ልጆች ሁሉ ይባርካል።

በ1989 (እ.አ.አ) ሰባት አባላት የነበረው ቤተሰባችን ከአጥቢያው የውጪ እመዝናናት ጉዞ እየተመለስን ነበር። ጊዜው ረፍዶ ነበር ። ስድስተኛ ልጃችን የሆነችው ሊኔት ነፍሰጡር ነበረች። ማድረግ የረሳችውን የመቀመጫ ቀበቶዋን የመታጠቅ ጠንካራ ስሜት ተሰማት። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በመንገዳችን ላይ አንድ ጠመዝማዛ ቦታ ደረስን፤ አንድ መኪናም መስመሩን አቋርጦ ወደ መንገዳችን ገባ። በሰዓት 112 ኪሎ ሜትር ያህል እየተጓዝኩ ሳለሁ፡ እየመጣ ያለውን መኪና ላለመምታት ብዬ ወደ ጎን ዞርኩኝ። የኛ መኪናም አውራ ጎዳናው ላይ ተንከባለለ፣ ከመንገዱ ወጥቶ በስተመጨረሻ ተንሸራተተና ቆመ፤ እናም በተሳፋሪው ጎን በአፈር ላይ አረፈ።

ቀጥሎ የሰማሁት ነገር “ሼን፣ ባንተ በር አርገን መውጣት አለብን” የሚል የሊኔትን ድምፅ ነበር። በመቀመጫ ቀበቶዬ ተንጠልጥዬ በአየር ላይ ነበርኩ። አቅጣጫውን ለማወቅ ጥቂት ሴኮንዶች ፈጀብኝ። ልጆቻችንን እያንዳንዳቸውን አሁን የመኪናው ጣሪያ በሆነው በእኔ መስኮት በኩል ማውጣት ጀመርን። እነርሱም ምን ተፈጠረ ብለው እያለቀሱ ነበር ።

ብዙም ሳይቆይ የ10 ዓመቷ ልጃችን ኤሚሊ እንደጠፋች ተገነዘብን። ስሟን ጮኸን ጠራን ፤ ሆኖም ምንም ምላሽ አልነበረም ። ወደ ቤት እየተጓዙ የነበሩት የአጥቢያው አባላት፣ በቦታው ላይ እርሷን በጭንቀት በመፈለግ ላይ ነበሩ። በጣም ጨለማ ነበር። እንደገና መኪና ውስጥ የእጅ ባትሪዪን ይዤ ስመለከት የኤሚሊ ትንሽ አካል ከመኪናው ስር ተይዞ አየሁ። “ከኤሚሊ ላይ መኪናውን ማንሳት አለብን” ብዬ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ጮኽኩ። ጣሪያውን ያዝኩና ወደ ኋላ ጎተትኩት። የሚያነሱት ጥቂት ሰዎች ብቻ ቢሆኑም በተዓምራዊ ሁኔታ መኪናው ወደ ታች በጎማዎቹ ላይ ቆመ፡ የኤሚሊ በድን አካልም ታየ።

ኤሚሊ እየተነፍሰች አልነበረም። ፊቷ ሐምራዊ ቀለም ይመስል ነበር። እኔም “በረከት ልንሰጣት ይገባል” አልኩ። ውድ ጎደኛዬ እና የአጥቢያ አባል ከእኔ ጋር ተንበረከኩ እና በመልከ ጼዴቅ የክህነት ስልጣን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ በህይወት እንድትኖር አዘዝናት። በዚያች ቅጽበት ኤሚሊ በሚሰቀጥጥ ድምጽ በረጅሙ ተነፈሰች።

ከሰዓታት ከሚመስል ጊዜ በኋላ አምቡላንሱ ደረሰ። ኤሚሊ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ተወሰደች። ሳንባዋ ተጎድቶ እና የጉልበቷ ጅማት ተቆርጦ ነበር። ያለ ኦክስጅን በቆየችበት ጊዜ ምክንያት የአንጎል ጉዳት የመከሠቱ ዕድል አሳሳቢ ነበር። ኤሚሊ ለአንድ ቀን ከግማሽ ያህል ኮማ ውስጥ ነበረች። ስለ እሷ መጸለያችንን እና መጾማችንን ቀጠልን። ሙሉ በሙሉ በማገገም ተባረከች። ዛሬ፡ ኤሚሊና ባለቤቷ ኬቨን የስድስት ሴቶች ልጆች ወላጆች ናቸው።

ተዓምራዊ በሆነ ሁኔታ የተቀሩት ሰዎች ተራምደው ሊሄዱ ችለዋል። ሊኔት በማህጸኗ የተሸከመችው ሕፃን ታይሰን ነበረ። እሱም ቢሆን ከማንኛውም ጉዳት ተርፎ በቀጣዩ የካቲት ወር ተወለደ ። ምድራዊ ሥጋውን ከተቀበለ ከስምንት ወራት በኋላ፣ ታይሰን ወደ ሰማይ አባት ቤት ተመለሰ። እርሱ ጠባቂው መልአክ ልጃችን ነው። በቤተሰባችን ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ይሰማናል፣ እንደገናም ከእሱ ጋር ለመሆን እንናፍቃለን።

ከኤሚሊ ላይ መኪናውን ያነሱት ሰዎች መኪናዋ ምንም ክብደት እንደሌላት ሆኖ ተሰምቷቸው ነበር። በሰማይ ያሉ መላእክት ከምድራዊ መላእክት ጋር በመሆን ተሽከርካሪውን ከኤሚሊ አካል ላይ እንዳነሱ አውቅ ነበር። ኤሚሊ በቅዱስ የክህነት ኃይል ወደ ሕይወት እንደተመለሰችም አውቃለሁ።

ጌታ ይህንን እውነት ለአገልጋዮቹ ገልጦላቸዋል፡- “በፊታችሁ እሄዳለሁ። በቀኝህና በግራህ እሆናለሁ፥ መንፈሴም በልባችሁ ይሆናል፥ እናንተንም ለመሸከም መላእክቶቼ በዙሪያችሁ ይሆናሉ”

“እንደ እግዚአብሔር ልጅ ሥርዓት ቅዱስ ክህነት የሆነው ” የመልከ ጼዴቅ የክህነት ሥልጣን፣ ቁልፍ እና ሀይል በእዚህ በኋለኛው ቀናት ወደ ምድር እንደተመለሱ እመሰክራለሁ። ምንም እንኳን ሁሉም ሁኔታዎች እንደምንመኘው እና እንደምንጸልየው ባይሆንም፣ የእግዚአብሔር ተዓምራት ሁሌም በፈቃዱ፣ በጊዜው፣ እና በእቅዱ መሠረት እንደሚመጡ አውቃለሁ።

ተዓምራትን እና የመላእክትን አገልግሎት ጨምሮ የክህነት በረከቶችን የምትፈልጉ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ባዘጋጀልን የቃል ኪዳን መንገድ እንድትመላለሱ እጋብዛችኋለሁ። የሚወዷችሁ የቤተክርስቲያን አባላት እና መሪዎች ቀጣዩን እርምጃ እንድትወስዱ ይረዷችኋል።

የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የክህነት ቁልፎችን በሚይዙ እና በሚለማመዱ በሕይወት ያሉ ነቢያት አማካኝነት ቤተክርስቲያኑን እንደሚመራ እመሰክራለሁ። መንፈስ ቅዱስ እውን ነው። አዳኙ እኛን ለመፈወስ፣ መልሶ ለማግኘት፣ እና ወደ ቤት ለመመለስ ህይወቱን ሰጥቷል።

እኔ ተዓምራት እንዳልቆሙ፣ መላዕክትም በመካከላችን እንዳሉ እና ሰማያት በእውነት ክፍት እንደሆኑ እመሰክራለሁ። እናም አቤቱ፡ ሰማያት እንዴት ተከፍተዋል! በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

አትም