ቤተመቅደሶች፣ ምድርን እየሞሉ ያሉ የጌታ ቤቶች
በብቂነት እና በጸሎት ወደ ቅዱስ ቤቱ ስትመጡ፣ በሀይሉ ትታጠቃላችሁ።
አሁን የዘመርነውን የሚያስደስቱ ቃላትን አትወዱምን? “አጠናክርሀለሁ፣ እረዳሃለሁ፣ እንዲሁም እንድትቆም አደርግሀለሁ፣ … በጻድቅ፣ ሁሉን ቻይ እጄ ተደግፈህ።” ጌታ በሁሉም እድሜ ስር የሚገኙት ቅዱሳኖቹ ወደ እርሱ ቅዱስ ቤት ሲመጡ ያጠነክራቸዋል። ከኪንሻሳ እስከ ዞሊኮፍን እስከ ፉኩዎካ እና ኦክላንድ፣ ወጣቶች፣ በራሳቸው ተነሳሽነት፣ የቤተምቅደስ ጥምቀት ቦታዎችን እየሞሉ ነው። በፊት፣ አብዛኛው ውድ የቅዱስ ስርአት አገልጋዮች ሽበት ነበራቸው- አሁን ግን ያ ቀርቷል። የተጠሩ ሚስዮናውያን፣ የአገልግሎት ሚስዮናውያን፣ እና ከሚስዮን የተመለሱ በየ እያንዳንዱ ጥግ ይገኛሉ። በአለም ዙሪያ እኛን ወደ ጌታ ቤት የሚያቀርብ እየጨመረ ያለ ስሜት አለ፡፡
ከአንድ አመት በፊት፣ ከሚስዮናዊያን ለ70 አመታት ሲማሩ የቆዩ 95 አመት የሆናቸው በአሜሪካ ምስራቅ ዳርቻ የሚኖሩ ውድ የቤተሰብ ጓደኛ፣ ለሴት ልጃቸው “አብሬሽ ቤተመቅደስ መሄድ እፈልጋለሁ” አሏት።
ልጃቸው እንዲህ ስትል መለሰች፣ “እንግዲህ እናቴ፣ መጀመሪያ መጠመቅ ይኖርብሻል።”
“እሺ”፣ በማለት መለሡ፣ “ከዚያም፣ መጠመቅ እፈልጋለሁ።” ተጠመቁ። ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ በቤተመቅደስ ማጥመቂያ ውስጥ ተራቸውን ይዘው ገቡ። ከዚህ አንድ ወር በፊት፣ ለእራሳቸው ቡራኬ እና ለመታተም በቤተመቅደስ ተገኙ። “የእግዚአብሔር እውቀት እና ሃይል እየተስፋፋ ነው፤ በምድር ላይ ያለው መጋረጃ መከፈት እየጀመረ ነው።”
ጌታ፣ አሁን ምድርን የእርሱ በሆኑት ቤተመቅደሶች፣ በቅዱስ ቤቶቹ፣ እንዲሞላ ነቢዩን የሚመራው ለምን እንደሆነ አስባችሁ ታውቃላችሁን? ለቃል ኪዳን ህዝቦቹ የሚያስፈልገውን ብልጽግና ሰጥቶ፣ በእነርሱ የተቀደሱ አሥራቶች አማካኝነት፣ በዚህ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጌታ ቤቶች እንዲገነቡ የሚያደርገው ለምንድን ነው?
በዚህ ማለዳ፣ ፕሬዝዳንት ዳለንኤች.ኦክስ ለመገንባት የሚታሰብባቸውን አስደናቂ የቤተመቅደስ ስዕሎች አሳዩ። ካቲ እና እኔ በቅርቡ ፊሊፒንስ ነበርን። ይህን ተአምር አስቡ፦ የማኒላ ቤተመቅደስ የተመረቀው በ1984 (እ.አ.አ) ነበር። ሁለተኛው ቤተመቅደስ በሴቡ ከተማ በ2010 (እ.አ.አ) ከመጠናቀቀቁ በፊት 26 አመታት አልፈው ነበር። አሁን፣ ከ14 አመታት በኋላ፣ 11 ቤተመቅደሶች ወይ እየተገነቡ ነው፣ ወይ ንድፍ ወቶላቸዋል፣ ወይም ለመመረቅ ተዘጋጅተዋል። ከሰሜን ተነስተን እስከ ደቡብ፦ ላኦአግን፣ ቱጌጋራሮን፣ ሳንቲያጎን፣ ኡርዳኔታን፣ አላባንግን፣ ናጋን፣ ታክሎባንን ሲቲን፣ ኢሎይሎን፣ ባኮልድን፣ ካጋያን ደ ኦሮን፣ እና ዳቫኦን እናገኛለን። የእግዚአብሔርን ድንቅ ስራዎች መመልከት የሚያስደንቅ ነው!
በአለም ዙሪያ፣ የጌታ ቤቶች ወደ እኛ እየቀረቡ ናቸው። ለምን በእኛ ቀናት?
የመጨረሻ ቀናት
በመጨረሻው ቀናት፣ በህቦች መሃል ጭንቀት እንደሚኖር፣ ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ” እንደሚሆኑ፣ “ሁሉም ነገሮች በሁከት ውስጥ እንደሚሆኑ፣” ግራ መጋባት እንደሚሆን እና ፡”የሰዎች ልብ በፍርሃት [እንደሚደክም]” ጌታ አስጠንቅቋል። በእርግጥ፣ የወንዶች እና የሴቶችን ልብ በአለም አማላይነት፣ ትኩረትን በሚስቡ አሰናካይ ድምጾች፣ መንፈሳዊ ምግብን ችላ በማለት እንዲሁም የደቀመዝሙርነት ጥሪ በሚጠይቀው ነገር ሲዳከሙ አይተናል። ምናልባት በአንድ ወቅት በእውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ስላላቸው እምነት ከልባቸው ሲናገሩ የነበሩ፣ ስለ መጽሐፈ ሞርሞን የመሰከሩ፣ እና የእግዚአብሔርን መንግስት በጉጉት የገነቡ የምትወዷቸው ሰዎች፣ አሁን በድንገት እምነታቸን ትተው ከቤተክርስቲያን ፈቀቅ በማለታቸው አዝናችሁ ይሆናል። ለእናንተ የምሰጠው ምክር ይህ ነው፣ አትጨነቁ! ሁሉም ሰላም ነው። በእግዚአብሔር ዘንድ የማይቻል ነገር የለምና።
በዚህ በተተነበየው የአለም ግርግር እና የእምነት ማጣት፣ በጉጉት የእርሱን መመለስ የሚጠባበቁ፤ በቅዱስ ቦታዎች የሚቆሙ እና ከቦታቸው የማይነቃነቁ፣ የቃል ኪዳን ህዝቦች እንደሚኖሩ ጌታ ቃል ገብቷል። የጠላትን ቀስቶች ስለሚቋቋሙ፣ እምነታቸውን ስለሚያሳድጉ፣ ስለ ሰለስቲያል በማሰብ በአዳኙ በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ስለሚተማመኑ ጻድቃን ሰዎች ተናግሯል።
ጌታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተመቅደሶቹን አሁን ወደ እኛ እያቀረበ ያለው ለምንድነው? አንደኛው ምክንያት በዓለም ግርግር እና ፈተናዎች መካከል፣ የቃል ኪዳኑን ቅዱሳን እንደሚያጠናክር እና እንደሚባርክ ቃል ገብቷል።
በከርትላንድ ቤተመቅደስ ውስጥ የተሰጡ ቃል ኪዳኖች
እነዚህ ቅዱስ ቤቶች የሚያጠናክሩን፣ የሚያጽናኑን እና የሚጠብቁን እንዴት ነው? በከርትላንድ ቤተመቅደስ ምረቃ ላይ፣ ነብዩ ጆሴፍ ስሚዝ ባደረገው ተማጽኖ ውስጥ ምላሹን እናገኛለን። ”ከሰማይ ሰራዊቶች ጋር እንዘምራለን እንዲሁም እንጮሃለን” የሚለውን መዝሙር ቅዱሳን የዘመሩት በዚያ ቤተመቅደስ ውስጥ ነበር። እንዲሁም ተጨማሪ የክህነት ቁልፍን ዳግም ወደተመለሰው ወንጌል ለማምጣት፣ አዳኙ እራሱ ተገለጠ፣ የጥንት ነብያትም ተመለሱ።
በከርትላንድ ቤተመቅደስ ውስጥ በነበረው በዚያ ቅዱስ ሁኔታ ላይ፣ ነብዩ፣ በጌታ ቅዱስ ቤት ውስጥ፣ ቅዱሳን በእግዚአብሔር ሃይል የታጠቁ እንዲሆኑ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእነርሱ ላይ እንዲሆን፣ መላእክቱን ስለእነሱ እንዲያዝላቸው፣ እና በጌታ እንዲያድጉ እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ሙሉነትን እንዲቀበሉ ጸለየ። እኛ በጌታ ቤት ውስጥ በታማኝነት ስናመልክ፣ እነዚህ ሃያል ልመናዎች በህይወታችን ይፈጸማሉ።
የሃይል መሳሪያን መታጠቅ
በእርሱ ቤት ውስጥ፣ ቃል በቃል በሰማይ ሃይል በቀጥታ ተባርከናል። በኢየሱስ ክርስቶስ ያለን እምነት እና ለእርሱ ያለን ፍቅር የተረጋገጡ እና የተጠናከሩ ናቸው። ስለ እውነተኛ ማንነታችን እና ስለ ህይወት አላማ በመንፈሳዊ ሁኔታ ይረጋገጥልናል። ታማኞች ስንሆን፣ ከፈተናዎች እና መሰናከያዎች በመጠበቅ እንባረካለን። በችግራችን እና በሃዘናችን ወቅት ሲረዳን የአዳኙ ፍቅር ይሰማናል። በእግዚያብሔር ሃይል ታጥቀናል።
የእርሱ ስም በላያችን ላይ
በእርሱ ቅዱስ ቤት፣ ስሙን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ በእራሳችን ላይ እንወስዳለን። ስንጠመቅ፣ በእርሱ ያለንን እምነት እንዲሁም ትእዛዛቱን ለመጠበቅ ያለንን ፍላጎት እናሳያለን። በቤተመቅደስ ውስጥ፣ በቃል ኪዳኖቻችን አማካኝነት እርሱን ለዘለአለም እንደምንከተል በቅድስና ቃል እንገባለን።
የዚህ ቤተክርስቲያ ወጣቶች አስደናቂ ናቸው። በአስቸጋሪ አለም ውስጥ፣ የክርስቶስን ስም በላያቸው ላይ ይወስዳሉ። በሂበር ሲቲ፣ ዩታ፣ እንዲገነባ ስለታቀደው ቤተመቅደስ ዝርዝር ነገሮች ለመወያየት ለሕዝብ ክፍት የሆነ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። ለታቀደው ቤተመቅደስ ድጋፋቸውን ለማሳየት መናፈሻ ቦታውን ሶስት መቶ ወጣቶች ሞሉት። አንድ ወጣት ወንድ፣ በክፍት የሕዝብ ውይይት የመንግስት አመራሮችን ሲያናግር ብርታትን ተሞልቶ እንዲህ ሲል አብራርቷል፣ “እኔ እዚህ ቤተመቅደስ ውስጥ አገባለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። [ቤተመቅደሱ] እራሴን ንጹህ አድርጌ እንድጠብቅ ይረዳኛል።” ሌላኛው ደግሞ ቤተመቅደስን እንደ ብርሃን እና ተስፋ ምልክት ገለጸው። በአለም ዙሪያ ያሉ የቤተክርስቲያኗ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ለመቀበል ፍላጎታቸውን እያሳዩ ነው።
መላዕክቶች ከእኛ ጋር
በከርትላንድ ቤተመቅደስ፣ ነብዩ ጆሴፍ ስሚዝ “መላዕክትም ይጠብቋቸው ዘንድ እንጠይቅሃለን” በማለት ጸልዩአል። ለቅድመ ዓያቶቻችን ቅዱስ ሥርአቶችን በመፈጸም ቀጣይ ጊዜን በቤተመቅደስ ውስጥ ማሳለፍ፣ ከመጋረጃው ጀርባ ህይወት እንደሚቀጥል ጣፋጭ እና ጽኑ ማረጋገጫን ያመጣል።
በጌታ ቤት ውስጥ ያሚኖሩንን አብዛኞቹን ተሞክሮዎቻችንን በግልጽ ለሌሎች ለማካፈል እጅግ ቅዱስ ቢሆኑም፣ አንዳንዶቹን ማካፈል እንችላለን። ከአርባ አመታት በፊት፣ በፍሎሪዳ ስንኖር፣ ካቲ እና እኔ ወደ አትላንታ ጆርጂያ ቤተመቅደስ ተጓዝን። እሮብ ምሽት፣ ግንቦት 9፣ 1984 (እ.አ.አ)፣ በቤተመቅደስ ውስጥ አንድ ክፍለ ጊዜን እንደጨረስን፣ የቅዱስ ሥርአት አገልጋዩ ወደ እኔ ቀረበ እናም አንድ የማዘጋጃ ሥርአት ለመፈጸም ጊዜ እንዳለኝ ጠየቀኝ። እኔ የወከልኩት ሰው ስም የተለመደ አልነበረም። ስሙ ኤሊያዛር ሰርሲ ነበር።
በሚቀጥለው ቀን፣ ቤተመቅደሱ በቅዱሳን ተሞልቶ ነበር። የቀኑን ሁለተኛ ቡራኬ ለመቀበል እየተዘጋጀሁ ሳለሁ፣ የምወክለው ሰው ስም ተሰጠኝ። በሚደንቅ ሁኔታ፣ ባለፈው ምሽት የወከልኩት ሰው ስም ነበር፣ ኤሊያዛር ሰርሲ። ቡራኬው ሲካሄድ የጌታ መንፈስ ተሰማኝ። ከዚያ ከሰአት በኋላ፣ በቤተመቅደስ ውስጥ እያለን ካቲ፣ እህት ዶሊ ፈርናንዴዝ የሚባሉ አሁን በአትላንታ የሚኖሩትን በዕድሜ ገፋ ያሉ የቤተስባችንን ጓደኛ አየቻቸው። ወንድ የቤተስባቸው አባል አብሯቸው ባለመኖሩ፣ አባታቸውን ከአባታቸው ቤተሰቦች ጋር ለማተም እንዳግዝ ጠየቁኝ። እኔም ይህን ለማድረግ ክብር ተሰምቶኝ ነበር።
ለዚህ ቅዱስ ሥርአት በመሰዊያው ዳር ስንበረከክ፣ በአዕምሮዬ የተጻፈውን የእርሳቸው አባት ስምን በድጋሜ ሰማሁት፣ ኤልያዛር ሰርሲ። ከዚህ ሕይወት በኋላ፣ በምድር ህይወቱ ኤልያዛር ሰርሲ የተባለውን ሰው እንደማገኝ እና እንደማቅፈው ሙሉ እምነት አለኝ።
በጌታ ቤት ውስጥ የምናገኛቸው አብዛኛዎቹ ልምዶቻችን ከአስደናቂ ጣልቃገብነት የበለጠ አስደሳች ሰላም እና ጸጥ ያለ መገለጥ ያመጣሉ። ነገር ግን እርግጠኛ ሁኑ፦ መላእክት በእኛ ላይ ስልጣን አላቸው!
የመንፈስ ቅዱስ ሙሉነት
የቤተክርስቲያኗ አባል ሆነን ማረጋገጫ ስንቀበል የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተሠጥቶናል። አዳኙን ለማስታወስ ዳቦውን እና ውሃውን በየሳምንቱ ስንካፈል፣ መንፈሱ ሁልጊዜም ከእኛ ጋር እንደሚሆን ቃል ተገብቶልናል። በምድር ላይ ዋነኛ ቅዱስ ቦታ ወደሆነው ወደ ጌታ ቤት ፈቃደኛ በሆነ ልብ ስንመጣ፣ በጌታ አድገን “የመንፈስ ቅዱስን [ታላቅ] ሙሉነት እንቀበላለን።” በመንፈስ ቅዱስ ሃይል አማካኝነት፣ በሰላም እና በደስታ እንዲሁም በማይነገር ተስፋ ተሞልተናል። ከቅዱስ ቦታዎች እራሳችንን በምናገኝበትም፣ የእርሱ ደቀመዛሙር ለመሆን ጥንካሬ እንቀበላለን።
ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን፣ “አዳኛችን እና ቤዛችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አሁን እና ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜያት መሃል ታላቅ ከሆኑት ስራዎቹ ውስጥ አንዳንዱን ያከናውናል። እግዚአብሔር አብ እና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በግርማ ሞገስ እና በክብር በዚህች ቤተክርስቲያን ላይ ስልጣን እንዳላቸው ተአምራዊ ምልክቶችን እናያለን” በማለት አውጀዋል። በጌታ ቤቶች ምድርን መሙላት ድንቅ ሥራ እና ተአምራዊ ምልክት ነው።
ውድ ጓደኞቼ፣ የምንችል ሆነን፣ ነገር ግን የቤተመቅደስ ተሳትፏችንን ቁጥር ከፍ ካላደረግን፣ በጌታ ቤት ለማምለክ በቋሚነት ተጨማሪ ጊዜን እንፈልግ። ለተዋወቁት ቤተመቅደሶች—ንብረቶች እንዲገዙ፣ መንግስታት እቅዶችን እንዲያጸድቁ፣ ተሰጥኦ ያላቸው ሰራተኞችም ችሎታቸው እንዲበዛ እና የተቀደሰ ምረቃቸውም የሰማይን ፍቃድ እና የመላእክቶችን ጉብኝት እንዲያመጣ እንጸልይ።
ቃል ኪዳኖች
ቤተመቅደስ ቃል በቃል የጌታ ቤት ነው። በብቁነት እና በጸሎት መንፈሥ ወደ እርሱ ቅዱስ ቤት ስትመጡ፣ በእርሱ ሃይል እንደምትታጠቁ፣ ስሙ በእናንተ ላይ እንደሚሆን፣ የእርሱ መላእክት እንደሚጠብቋችሁ፣ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ በረከት እንደምታድጉ ቃል እገባላችኋለሁ።
ጌታ “ኃጢአቶቹን የሚተውና ወደ እኔ የሚመጣ፣ እና ስሜን የሚጠራ፣ እና ድምጼን የሚያከብር፣ እና ትእዛዛቴን የሚያከብር እያንዳንዱ ነፍስ ሁሉ ፊቴን የሚያይበት እና እኔ እንደሆንኩም የሚያውቅበት ጊዜ ይመጣል” በማለት ቃል ገብቷል። የጌታን ፊት የማየት ብዙ የተለያዩ መንገዶች አሉ፣ ነገር ግን ከእርሱ ቤት ውጪ ሌላ የተሻለ ምንም ቦታ የለም።
በዚህ ግራ የመጋባት እና የግርግር ጊዜ፣ ቤተመቅደስ የእርሱ ቅዱስ ቤት እንደሆነ እናም እንደሚጠብቀን እንዲሁም ከሁሉም ቅዱስ መላእክቱ ጋር፣ አዳኛችን በሞገስ፣ በሃይል እና በታልቅ ክብር እስከሚመለስበት ታላቅ ቀን ድረስ እንደሚያዘጋጀን እመሰክራለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።