ለማገልገል ቀድሞ መመረጥ
የሰማይ አባታችን የእናንተን የግል አስቀድሞ መመረጥ ሊገልጽላችሁ ይፈልጋል፣ እናም የእርሱን ፍቃድ ለመማር እና ለመከተል ስትሹይገልጽላችኋል።
በዚህ ምሽት፣ ለሚቀጥለው ትውልድ ምልክት ተሸካሚ ለሆኑት የትውልዱ ታዳጊ ወጣት ወንድ እና ሴት የቤተክርስቲያኗ ወጣቶች እናገራለሁ፣
ጥቅምት 2013 (እ.አ.አ)፣ ውድ ነብያችን፣ ፕሬዝዳንት ረሴልኤም. ኔልሰን፣ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፣፤ “የሰማይ አባታችሁ በጣም ለረጅም ጊዜ ያውቃችኋል። እናንተ፣ እንደ ወንድ ሴት ልጆቹ፣ በዚህ ወቅት ወደ ምድር መጥታችሁ በምድር ላይ የታላቅ ሥራው መሪዎች እንድትሆኑ በእርሱ ተመርጣችኋል።”
ከሁለት አመት በፊት፣ ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዲህ ሲሉ ይቀጥላሉ፤
“ዛሬ እያንዳንዱ ብቁ የሆነ፣ የሚችል ወጣት ወንድ ልጅ በሚስዪን ለማገልገል እንዲዘጋጅ እና እንዲያገለግል ጌታ እንደጠየቀ አበክሬ አረጋግጣለሁ። ለኋለኛው ቀን ቅዱሣን ወጣት ወንዶች፣ ሚስዮናዊ አገልግሎት የክህነት ሃላፊነት ነው። እናንተ ወጣት ወንዶች ቃል የተገባው የእስራኤል መሰባሰብ እየተከናወነ ላለበት ለዚህ ጊዜ የተመረጣችሁ ናችሁ። …
“እናንተ ወጣት እና የምትችሉ እህቶች፣ ሚስዮን ሃያል የሆነ፣ ነገር ግን በአማራጭነት የቀረበ፣ እድል ነው። ጌታ በሚስዮን እንድታገለግሉ ይፈልግ እንደሆነ ለማወቅ ጸልዩ፣ ከዚያም መንፈስ ቅዱስ በልባችሁ እና በአዕምሯችሁ ምላሽ ይሰጣል።”
በዚህ ጊዜ ላለው የእስራኤል መሰባሰብ ጌታ የዘመናችንን ወጣቶች ማስቀመጡ እና ጌታ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ለማወቅ እንድትጸልዩ ነብያችን መጋበዛቸው፣ በከፊሉ፣ በዚህ ምድር ከመወለዳችሁ በፊት የኖራችሁትን ኑሮ እና ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁትን በረከቶች የሚያመላክት ነው። በዚህ ምድር ላይ የተወለድን ሁላችንም በመጀመሪያ ከሰማይ አባት ጋር እንደ መንፈስ ልጆቹ አብረነው እንኖር ነበር። ጌታ ለሙሴ እንዲህ ሲል ተናግሯል፤ “እኔ፣ እግዚአብሔር አምላክ ነገሮችን ሁሉ ከምድር ፊት በፍጥረታዊ አካል ከመፈጠራቸው በፊት በመንፈሳዊ አካል ፈጥሬአቸዋለሁና።”
በመንፈሳዊ ሲፈጥራችሁ፣ እንደ መንፈስ ወንዶች እና ሴቶች ልጆቹ ወደዳችሁ እንዲሁም በእያንዳንዳችሁ ውስጥ መለኮታዊ ተፈጥሮን እና ዘለአለማዊ ዕጣ ፈንታን አስቀመጠላችሁ።
በቅድመ ምድር ህይወታችሁ፣ “ማንነታችሁን አሳድጋችኋል እንዲሁም መንፈሳዊ አቅማችሁን ጨምራችኋል።” የራሳችሁን ምርጫዎች የማድረግ ችሎታ በሆነው የነጻ ምርጫ ሥጦታ ተባርካችኋል፣ እናንተም፣ ለምሳሌ የሰማይ አባትን የደስታ እቅድ እንደመከተል ያለ ጠቃሚ ውሳኔዎችን ወስናችኋል፣ ያም “የሰውነት አካልን ለማግኘት እና ለማደግ ምድራዊ ተሞክሮን ለማግኘት … እናም እንደ የዘላለም ህይወት ወራሽነታችሁ የመለኮታዊ መዳረሻ[ችሁ]ን እንድትጎናጸፉ ነው።” ይህ ውሳኔ ያኔ በቅድመ ምድር ህይወታችሁ ላይ ተጽእኖ ነበረው፣ እንዲሁም አሁን ህይወታችሁ ላይ ተጽእኖ ማድረጉን ቀጥሏል። በቅድመ ምድር ህይወታችሁ እንደ እግዚአብሔር ልጅ ስትኖሩ፣ እናንተ “በጥበብ አደጋችሁ እና እውነትን በመውደድ አደጋችሁ።
ከመወለዳችሁ በፊት፣ በምድራዊ ህይወታችሁ በምድር ላይ የተለዩ ተልዕኮዎችን እንድትፈፅሙ እግዚአብሔር እያንዳንዳችሁን ሰይሟል። ብቁ በመሆን ከቀጠላችሁ፣ የዚያ የቅድመ ምድር ሕይወት ድንጋጌ በረከቶች፣ በዚህ ምድር ሁሉም ዓይነት እድሎች እንዲኖሯችሁ ያስችላችኋል። እንዲሁም በቤተክርስቲያን ውስጥ የማገልገልን እድሎች ጨምሮ ዛሬ በምድር እየተከናወነ ያለውን እጅግ በጣም ጠቃሚ በሆነው እስራኤልን የመስብሰብ ስራ ላይ መሣተፍን ያካትታል። እነዚያ የቅድመ ምድር ሕይወት ቃልኪዳኖች እና በረከቶች የናንተ ቀድሞ መመረጥ ይባላሉ። “የቀድሞ መመረጥ አስተምሮ ሁሉንም የቤተክርስቲያኗን አባላት ይመለከታል።” ቀድሞ መመረጥ የተለዩ ጥሪዎችን ወይም ሃላፊነቶችን እንደምትቀበሉ ማረጋገጫ አይሰጥም። እነዚህ በረከቶች እና እድሎች በእናንተ የዚህ ህይወት የነጻ ምርጫ ቅዱስ ተሞክሮ የሚመጡ ናቸው፣ ልክ በቅድመ ምድራዊ ህይወት ቀድሞ መመረጣችሁ በቅድስና ምክንያት እንደመጣው ሁሉ። ብቁ መሆናችሁን ስታስመሰክሩ እና በቃልኪዳን መንገዱ ስትጓዙ፣ በወጣት ሴቶች ክፍል ወይም በክህነት ቡድን ውስጥ ታገለግሉ ዘንድ ሃላፊነቶችን ትቀበላላችሁ። በቤተመቅደስ ውስጥ ለማገልገል፣ የአገልግሎት ወንድም ወይም እህት ለመሆን፣ እና እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዝሙር በሚስዮን በማገልገል ትባረካላችሁ።
ስለ ቀድሞ መመረጣችሁ ለማወቅ እና ለመረዳት መሻት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ብዙዎች የእውነተኛ ማንነታቸውን ጥያቄ በማንሳት ለማወቅ በሚሹበት በዚህ ወቅት፣ በዚህ ምድር ላይ ከመወለዳችን በፊት በ”ቅድመ ምድራዊ ህይወት፣ በምድራዊ ህይወት፣ እና በዘላለማዊ ማንነት እና አላማ ልዩ ባሕሪዎች” በእግዚአብሔር መታወቃችን እናም መባረካችን አስደሳች ሰላም እና ማረጋገጫን ወደ አእምሯችን እና ልባችን ያመጣል። ማን እንደሆናችሁ ማወቅ የሚጀምረው በዚህ ምድር ከመወለዳችሁ በፊት እግዚአብሔር የሠጣችሁን ቀድሞ የመመረጣችሁን በረከቶች ከመረዳት ነው። የሰማይ አባታችን የእናንተን የግል አስቀድሞ መመረጥ ሊገልጽላችሁ ይፈልጋል፣ እናም የእርሱን ፍቃድ ለመማር እና ለመከተል ስትሹይገልጽላችኋል።
የፕሬዚዳንት ኔልሰንን የኢንስታግራም መልእክቶች ማንበብ እወዳለሁ። በጣም ከምወዳቸው አንዱ ሐምሌ 20፣ 2022 (እ.አ.አ) የተጠፈውን ነው። እንዲህ ሲሉ ፅፈው ነበር፦
“ጌታ ለእናንተ ቀጥታ እየተናገረ ቢሆን ኖሮ፣ መጀመሪያ እናንተ እንድትረዱ የሚያደርገው እውነተኛ ማንነታችሁን ነው። ውድ ጓደኞቼ፣ እናንተ እውነተኛ የእግዚአብሔር የመንፈስ ልጆች ናችሁ። …
“… አትሳሳቱ፣ አቅማችሁ መለኮታዊ ነው። ተግታችሁ ስትሹ፣ እግዚአብሔር ማን መሆን እንደምትችሉ ያሳያችኋል።”
የእኔን ማንነት እና እግዚአብሔር በህይወቴ ውስጥ ያለውን እቅድ እንዳውቅ ለማድረግ ምድራዊ አባቴ ያስተማረኝን ላካፍላችሁ?
የ13 አመት ልጅ እያለሁ አንድ ቅዳሜ ጠዋት፣ እንደ ሳምንታዊ ተግባሬ ሳር እያጨድኩ ነበር። ስጨርስ፣ ከቤታችን ጀርባ በር ሲዘጋ ሰማሁና ለማየት ስዞር አባቴ ከሱ ጋር እንድሆን ሲጠራኝ ሰማሁ። በጀርባ ወዳለው በረንዳ ተራመድኩ፣ ከዚያም ደረጃው ላይ አብሬው እንድቀመጥ ጋበዘኝ። ውብ የሆነ ጠዋት ነበር። በጣም ቅርብ ለቅርብ ከመቀመጣችን የተነሳ ትከሻችን ሲነካኩ እንደነበር አሁንም አስታውሳለሁ። እንደሚወደኝ በመናገር ነበር የጀመረው። በህይወት ውስጥ አላማዎቼ ምን እንደነበሩ ጠየቀኝ። “በርግጥ፣ ያ ቀላል ነው” ብዬ አሰብኩ። ሁለት ነገሮችን በእርግጠኝነት አውቅ ነበር፤ እረጅም መሆን እፈልግ እንደነበርና፣ በሽርሽር ለመስፈር ይበልጥ ብዙ ጊዜ መሄድ እፈልግ ነበር። ውሥብሥብ ሃሣቦች ወይም ፍላጎቶች ያልነበሩኝ ሠው ነበርኩ። እርሱ ፈገግ አለ፣ ለጥቂት ጊዜ ዝም አለና፣ እንዲህ አለ፤ “ስቲቭ፣ ለእኔ በጣም አስፈላጊ የሆነን አንድ ነገር ላካፍልህ እፈልጋለሁ። የሰማይ አባት፣ አሁን የምለውን መቼም እንዳትረሳ በአእምሮህ እና በነብስህ በማይፋቅ መንገድ እንዲታተም እንዲያደርግ እጸልያለሁ።
በዚያ ጊዜ አባቴ የእኔን ሙሉ ትኩረት አገኘ። ዞረ እና አይኖቼን እያየ እንዲህ አለ፣ “ልጄ፣ በህይወትህ ውስጥ በግል የምታሣልፋቸውን ጊዜዎች ጠብቅ። ትርጉሙ ወደ ልቤ ዘልቆ እስዲንገባ እስኪያደርግ ድረስ ረጅም ዝምታ ነበር።
ከዚያም እንዲህ ሲል ቀጠለ፤ በአከባቢው ያለኸው አንተ ብቻ ስትሆን እና ምን እያደረክ እንደሆነ ማንም የማያውቅበትን እነዚያን ጊዜያት ታውቃለህ? አሁን የማደርገው ነገር ሁሉ ከእኔ በስተቀር ማንም ላይ ተጽእኖ አያስከትልም ብለህ የምታስብባቸውን እነዚያ ጊዜያት?
ከዚያም እንዲህ አለ፣ “ከሌሉቹ የህይወትህ ጊዜያት ሁሉ በበለጠ፣ በግል በምታሣልፋቸው ጊዜያቶች የምታደርጋቸው ነገሮች የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች እና ሃዘኖች በምትጋፈጥበት መንገድ ላይ ታላቅ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል፤ እንዲሁም በግል በምታሣልፋቸው የህይወትህ ጊዜያት የምታደርጋቸው ነገሮች ከሌላ ከማናቸውም ጊዜያት በበለጠ ስኬቶችን እና ደስታን በምታስተናግድበት መንገድ ላይ ታላቅ ተፅዕኖ ያሣድራሉ።”
አባቴ የልቡን ምኞት አገኘ። ድምጹ እና አቀራረቡ፣ እንዲሁም በእርሱ ቃላት ውስጥ የተሰማኝ ፍቅር፣ በዚያ ቀን በአእምሮዬ እና በነብሴ እንዳይፋቁ ሆነው ታተሙ።
በዚያ የልጅነት ቤቴ ደረጃ ላይ የነበረው የዚያ ቀን ታላቅ ተዓምር፣ በህይወቴ በግል የማሣልፋቸው ጊዜያት፣ ራዕይን ለመቀበል በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መሄድ እንደምችል የተማርኩት በዓመታት ውስጥ ነበር። አባቴ፣ እግዚአብሔር የሠጠኝን የቀድሞ መመረጥ በረከቶች እንዴት ማወቅ እንዳለብኝ እያስተማረኝ ነበር። በእነዚያ የግል ጊዜያት፣ መፅሐፈ ሞርሞን የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ተማርኩ። በሚስዮን እንዳገለግል እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደመረጠኝ አወኩኝ። እግዚአብሔር እንደሚያውቀኝ እና ጸሎቴን እንደሚሰማ እንዲሁም እንደሚመልስልኝ ተማርኩ። ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ፣ እንዲሁም አዳኛችን እና ቤዛችን እንደሆነ ተማርኩ።
ከአባቴ ጋር ከነበርኝ ከዚያ ከማይዘነጋው ቀን በኋላ ብዙ ስህተቶችን ሰርቼ የማውቅ ቢሆንም፣ በግል የማሣልፋቸውን ጊዜዎቼን ለመጠበቅ መጣሬ በህይወት ለሚመጡት ማዕበሎች መልህቅ ሆኖ ቆይቷል እንዲሁም በአዳኛችን ፍቅር እና የሀጥያት ክፍያ መሥዋዕት የተነሳ የሚገኙትን የደህንነት እና የፈውስ፣ የሚያጠነክሩ በረከቶችን ሁሉ እንድሻ ረድቶኛል።
ወጣት ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በህይወታችሁን በግል የምታሣልፉትን ጊዜ ስትጠብቁ በብዙ መዝናኛዎች፣ የሚያንፁ ሙዚቃዎችን በመስማት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ፣ እለታዊ ትርጉም ያለው ጸሎት በማድረግ፣ እና የፓትሪያርክ በረከታችሁን ለመቀበል እና በእርሱ ላይ ለማሰላሰል ጥረት በማድረግ፣ መገለጥን ትቀበላላችሁ። በፕሬዚዳንት ኔልሰን ቃላት፣ አይኖቻችሁ “ ለእውነት በደምብ ይከፈታሉ፤ ይሄ ህይወት በእውነት ምን አይነት ህይወት እናንተ መኖር እንደምትፈልጉ የምትወስኑበት ጊዜ ነው።”
የሰማይ አባታችን ጸሎቶቻችሁን ይመልስላችኋል፣ በተለይ በህይወታችሁ በግል በምታሣልፏቸው ጊዜያት የምትጸልዩአቸው ጸሎቶች። የቀድሞ መመረጥ ስጦታችሁን እና ተሰጥኦችሁን ይገልጥላችኋል፣ እናም ከልባችሁ ከጠየቃችሁ እና በእውነት ለማወቅ ካሻችሁ የእርሱ ፍቅር ሲሸፍናችሁ ይሰማችኋል። በህይወታችሁ በግል የምታሣልፏቸውን ጊዜያትስትጠብቁ፣ በቅዱስ ሥርዓቶች እና የወንጌል ቃልኪዳኖች ውስጥ ያላችሁ ተሳትፎ የበለጠ ትርጉም ያገኛል። በምትገቧቸው ቃልኪዳኖች ራሳችሁን የበለጠ ከእግዚአብሔር ጋር ታጣምራላችሁ፣ እንዲሁም ታላቅ ተስፋ፣ እምነት፣ እና በገባላችሁ ቃልኪዳን መተማመኛ እንዲኖራችሁ ትታነፃላችሁ። እግዚአብሔር ለእናንተ ያለውን እቅድ ማወቅ ትፈልጋላችሁ? እናንተ እንድታውቁ እንደሚፈልግ እንዲሁም እያንዳንዳችን እንድንጸልይ እና ይሄን አይን ከፋች ተሞክሮ እንድናገኝ እንዲጋብዙን በአለም ላይ ነብያትን በመንፈስ እንዳነሳሳእመሠክራለሁ። የእግዚአብሔር የሠጠውን ሁሉንም የቀድሞ መመረጥ በረከቶች ለመኖር እና በእነሱ ለመደሰት ሰላስቻለን የአዳኛችን የሀጥያት ክፍያ መስዋዕት እውነት እና ሃያል እንደሆነ የምመሰክረው፣ በኢየሱስ ስም ነው፣ አሜን።