አጠቃላይ ጉባኤ
“ዕረፉ፣ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ”
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


14:43

“ዕረፉ፣ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ”

ልናርፍ እና እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን እንደሆነ፣ እኛም ልጆቹ እንደሆንን እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እንደሆነ ልናውቅ እንችላለን።

አዲስ ለተከፈተ የጌታ ቤት በቅርቡ በተደረገው የሕዝብ ጉብኝት እና የሚዲያ ቀን ዝግጅት፣ የጋዜጠኞች ቡድንን በመምራት ቤተመቅደሡን አስጎብኝቻለሁ። ቤተመቅደሶች በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውሥጥ ያላቸውን ዓላማዎች ገለፅኩኝ፤ ከዚያም እነርሱ ለጠየቋቸው ምርጥ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጠሁኝ።

ወደ ሰለስቲያል ክፍል ከመግባታችን በፊት፣ በጌታ ቤት ውስጥ ያለው ይህ ክፍል በምሳሌያዊ ሁኔታ ከዚህ ህይወት በኋላ ተመልሠን የምንሄድበትን የሠማይ ቤት ሠላም እና ውበት እንደሚወክል አስረዳሁኝ። በሰለስቲያል ክፍል ውስጥ ሣለን እንደማንነጋገር፣ ሆኖም ወደሚቀጥለው የጉብኝት መዳረሻ ከሄድን በኋላ ማናቸውንም ጥያቄዎች በደስታ እንደምመልስ ለእንግዶቻችን ጠቆምኩኝ።

ከሰለስቲያል ክፍል ወጥተን በሚቀጥለው የጉብኝት መዳረሻ በተሰበሰብንበት ጊዜ፣ እንግዶቻችን ሊያካፍሉ የሚፈልጉት ማንኛውም ምልከታ ይኖር እንደሆነ ጠየቅኳቸው። ከጋዜጠኞቹ አንዱ በታላቅ ሥሜት ተሞልቶ እንዲህ አለ፦ “በህይወቴ እንደዚህ ዓይነት ነገር ገጥሞኝ አያውቅም። በዓለም ውስጥ እንደዚያ ያለ ነገር እንዳለ አላውቅም ነበር፤ በቀላሉ፣ እንዲህ ያለ እርጋታ ይኖራል ብዬ አላምንም ነበር።”

በዚህ ሰው የንግግር ቅንነት እና ቅለት ተገርሜ ነበር። እንዲሁም፣ ጋዜጠኛው የሠጠው ምላሽ፣ የውጫዊ አካባቢያችንን ግርግር የመቋቋምን እና ለእነርሱ ትኩረት ያለመሥጠትን የመረጋጋት አንድ ጠቃሚ ጎን አጉልቶ አሳይቷል።

በኋላ ላይ ጋዜጠኛው በሠጠው አስተያየት ላይ ሳሰላስል እና አብዛኛውን ጊዜ አስጨናቂ ስለሆነው የዘመናዊ ህይወታችን ጥድፊያ—የስራ መብዛት፣ ጫጫታ፣ አቅጣጫ መቀየር፣ የሃሳብ መከፋፈል እና ብዙውን ጊዜ ትኩረታችንን የሚሹ ስለሚመስሉት አቋራጮች—ባሰብኩኝ ጊዜ፦ “ዕረፉ፣ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ” የሚለው የቅዱሣት መፃሕፍት ጥቅስ ወደ አእምሮዬ መጣ።

በህይወታችን ውስጥ፣ እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን እንደሆነ፣ እኛም ልጆቹ እንደሆንን እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እንደሆነ እንድናውቅ እና እንድናስታውስ የሚያስችለንን የነፍስ ውስጣዊ እረፍት የሆነውን ከፍ ያለውን እና የተቀደሰውን መረጋጋት ስናስብ፣ መንፈስ ቅዱስ ለእያንዳንዳችን ጥልቅ እውቀትን እንዲሠጠን እጸልያለሁ። “የጌታ የቃል ኪዳን ህዝቦች” ለመሆን በታማኝነት ለሚጥሩ ሁሉም የቤተክርስቲያኗ አባላት ይህ አስደናቂ በረከት ይገኛል።

ዕረፉ

በ1833 (እ.አ.አ)፣ በሚዙሪ የነበሩ ቅዱሳን የተጠናከረ የሥደት ኢላማዎች ነበሩ። የሕገ ወጥ ሠዎች ሥብሥብ እነርሱን በጃክሰን አውራጃ ከነበሩት ቤቶቻቸው አሣደዋቸዋል እንዲሁም አንዳንድ ቅዱሳን ራሳቸውን በአቅራቢያው በሚገኙ በሌሎች አውራጃዎች ውስጥ ለማቋቋም ሞክረው ነበር። ሆኖም ማሳደዱ ቀጠለ፣ እንዲሁም ብዙ የሞት ዛቻዎች ይሠነዘሩ ነበር። በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ፣ ጌታ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ የሚከተለውን መመሪያ በከርትላንድ ኦሃዮ ገለጠለት፦

“ስለዚህ፣ ፅዮንን በሚመለከት ልቦቻችሁ ይፅናኑ፤ ሁሉም ስጋዎች በእጆቼ ውስጥ ናቸውና፤ ዕረፉ እና እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ።”

ጌታ “ዕረፉ” ሲል የሠጠው ማሳሰቢያ፣ ካለመናገር ወይም ካለመንቀሳቀስ የበለጠ ነገርን እንደሚያካትት አምናለሁ። ምናልባት የእርሱ ዓላማ “በሁሉም ጊዜ በሁሉም ነገርና [በምንኖርባቸው] ቦታዎች ሁሉ” እርሱን እና ኃይሉን እንድናስታውስ እና እንድንተማመንበት ለማድረግ ይሆናል። ስለዚህ፣ “ዕረፉ” የሚለው ቃል፣ አዳኙን ሁልጊዜ ከባድ ነገሮችን እንድናደርግ እና እንድንቋቋም ጥንካሬን የሚሠጠን የነፍስ መንፈሳዊ መረጋጋት ታላቅ ምንጭ በማድረግ እንድናተኩርበት የሚያስታውሰን መንገድ ሊሆን ይችላል።

በዓለቱ ላይ ገንቡ

እውነተኛ እምነት ሁል ጊዜ የሚያተኩረው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነው፤ ይኸውም መለኮታዊ እና የዘለዓለማዊ አባት አንድያ ልጅ በመሆኑ ላይ እንዲሁም በፈጸመው የማዳን ተልዕኮ ላይ ነው።

“እርሱም የህጉን ፍፃሜ አሟልቶታል፣ እናም በእርሱ እምነት ያላቸውን በሙሉ የእርሱ አድርጓል፤ እናም በእርሱ እምነት ያላቸው መልካሙን ነገር በሙሉ ይይዛሉ፤ ስለሆነም እርሱም ለሰው ልጆች ጉዳይ ጠበቃ ይሆናል።”

ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛችን፣ አማላጃችን፣ እና በዘለአለማዊ አባት ዘንድ ጠበቃችን እንዲሁም የህይወታችንን መንፈሳዊ መሠረት ልንገነባበት የሚገባን ዓለት ነው።

ሔለማን እንዲህ ሲል አብራርቷል፣ “አስታውሱ፣ አስታውሱ፣ አዳኝ በሆነው የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በክርስቶስ ዓለት መሰረታችሁን መገንባት እንዳለባችሁ፤ ዲያብሎስ ኃይሉን ንፋሱን፣ አዎን፣ በአውሎ ነፋስ እንደሚወረወር ዘንጉን በላከ ጊዜ፣ አዎን በረዶው፣ እናም ኃይለኛው ውሽንፍር በሚመታችሁ ጊዜ፣ እርግጠኛ መሰረት በሆነው ሰዎች ከገነቡበት ሊወድቁበት በማይችሉበት ዓለት ላይ ስለገነባችሁ እናንተን ወደ ስቃይና ወደ ባህር ስላጤና መጨረሻ ወደሌለው ዋይታ ጎትቶ ለመጣል ኃይል አይኖረውም።”

የህይወታችንን መሠረት ልንገነባበት እንደሚገባን “ዓለት” ተደርጎ የቀረበው የክርስቶስ ተምሣሌትነት እጅግ አስተማሪ ነው። እባካችሁ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ክርስቶስ መሠረቱ እንዳልሆነ አስተውሉ። ከዚያ ይልቅ፣ የግል መንፈሳዊ መሠረታችንን በእርሱ ላይ እንድንገነባ ተመክረናል።

መሠረት የሚባለው ህንፃውን ከመሬቱ ጋር የሚያያይዘው የህንፃው አካል ነው። ጠንካራ መሠረት ከተፈጥሮ አደጋዎች እና ከሌሎች ከብዙ አውዳሚ ኃይሎች ይከላከላል። በአግባቡ የተገነባ መሠረትም ከሥሩ ባለው መሬት ላይ ከመጠን ያለፈ ጫና እንዳይፈጠር የህንፃውን ክብደት ሠፋ ወዳለ ቦታ ያከፋፍላል እንዲሁም ግንባታው የሚከናወንበት መሬት ውሃ ልኩን የጠበቀ እንዲሆን ያደርጋል።

በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ ሄት

አንድ ግንባታ በጊዜ ሂደት ጠንካራ እና ባለበት የሚቆይ እንዲሆን ከተፈለገ፣ በመሬቱ እና በመሠረቱ መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ እና አስተማማኝ እንዲሆን ያስፈልጋል። ለተለዩ የግንባታ ዓይነቶች ደግሞ የብሎን መልህቆች እና የፌሮ ብረቶች የህንፃውን መሠረት፣ እንደ አፈር እና ኮረት ካሉ በመሬቱ ሥር ካሉ ጠንካራና ጠጣር ዓለት፣ “የዓለት ንጣፍ” ጋር ለማጣበቅ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ።

ከዓለት ንጣፍ ጋር በመልሕቅ የተጣበቀ ቤት

በተመሳሳይ መንገድ፣ በፅናት እና በታማኝነት ለመኖር ከፈለግን የህይወታችን መሠረት ከክርስቶስ ዓለት ጋር መጣበቅ አለበት። ዳግም የተመለሠው የአዳኙ ወንጌል ቅዱስ ቃል ኪዳኖች እና ሥርዓቶች፣ ህንፃን ከዓለት ንጣፍ ጋር ለማጣበቅ ከሚጠቅሙት የብሎን መልህቆች እና የፌሮ ብረቶች ጋር ሊነፃፀሩ ይችላሉ። የተቀደሡ ቃል ኪዳኖችን በታማኝነት በምንቀበልበት፣ በምንከልስበት፣ በምናስታውስበት እና በምናድስበት ጊዜ ሁሉ፣ መንፈሳዊ መልህቆቻችን ከኢየሱስ ክርስቶስ “ዓለት” ጋር በፅናት እና በማይነቃነቁበት ደረጃ ይጣበቃሉ።

“ስለሆነም፣ በእግዚአብሔር የሚያምን በእርግጥ ለተሻለ ዓለም፣ አዎን፣ በእግዚአብሔር ቀኝ እጅ በኩል ያለውን ስፍራ እንኳ ለማግኘት ተስፋ ይኖረዋል፤ ይኸውም ተስፋ በእምነት የሚመጣ ነው፤ ተስፋም ለሰዎች ነፍስ እንደ መልሕቅ ነው፤ እነርሱንም ፅኑ እና የማይነቃነቁ እንዲሆኑ እናም ሁልጊዜም በርካታ መልካም ነገሮችን እንዲሰሩ፤ እግዚአብሔርንም እንዲያከብሩ ያደርጋቸዋል።”

“ከጊዜ በኋላ፣” ቀስ በቀስ እያደገ እና ያለማቋረጥ በብዛት እየጨመረ በመሄድ፣ “ምግባረ በጎነትም ሳያቋርጥ አስተሳሰ[ባችንን] ያሳምራል፣” “ልበ ሙሉነ[ታችንም] በእግዚአብሔር ፊት እየጠነከረ ይሄዳል፤” እናም “ መንፈስ ቅዱስ የእኛ ቋሚ ጓደኛ” ይሆናል። የበለጠ መሠረት እንይዛለን፣ ሥር ይኖረናል፣ እንቋቋማለን እንዲሁም እንረጋጋለን። የህይወታችን መሠረት በአዳኙ ላይ የተገነባ በመሆኑ እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን እንደሆነ፣ እኛም ልጆቹ እንደሆንን እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እንደሆነ መንፈሣዊ ማረጋገጫ በማግኘት “እንድናርፍ” ተባርከናል ።

የተቀደሡ ጊዜያት፣ ቅዱስ ቦታዎች እና ቤት

ይህንን የነፍሶቻችንን ውስጣዊ መረጋጋት እንድንለማመድ እና እንድናውቅ ለመርዳት፣ ጌታ የተቀደሡ ጊዜያትን እና ቅዱስ ቦታዎችን ሠጥቶናል።

ለምሳሌ፣ ሠንበት አብን በልጁ ሥም አማካኝነት ለማስታወስ እና ለማምለክ፣ በክህነት ሥርዓቶች ለመሳተፍ እና የተቀደሡ ቃል ኪዳኖችን ለመቀበል እና ለማደስ የተለየ የእግዚአብሔር የተቀደሠ ጊዜ ነው። በየሣምንቱ በቤት ጥናታችን እንዲሁም በቅዱስ ቁርባን እና በሌሎች ሥብሰባዎች ወቅት “ከቅዱሳን ጋር ባላገሮች” በመሆን ጌታን እናመልካለን። በእርሱ የተቀደሠ ቀን፣ የሚኖሩን ሀሣቦች፣ ድርጊቶች እና አመለካከቶች ለእግዚአብሔር የምንሠጠው ምልክቶች ሲሆኑ ለእርሱ ያለንን ፍቅር የምናሳይባቸውም ናቸው። በእያንዳንዱ የሠንበት ቀን፣ ከፈለግን ልናርፍ እና እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን እንደሆነ፣ እኛም ልጆቹ እንደሆንን እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እንደሆነ ልናውቅ እንችላለን።

የሠንበት አምልኳችን ዋነኛ መለያ “ወደ ጸሎት ቤት [መሄድ]፣ እናም [በጌታ] ቅዱስ ቀ[ን]ም ቅዱስ ሥርዓቶ[ቻችንን] [ማቅረብ] ነው። በሠንበት ቀናት የምንሰበሰብባቸው “የፀሎት ቤ[ቶች]” የመሠብሠቢያ አዳራሾች እና የተፈቀዱ ሕንፃዎች — የጥልቅ አክብሮት፣ የአምልኮ እና የመማሪያየተቀደሱ ቦታዎች ናቸው። እያንዳንዱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና ሕንፃ፣ የጌታ መንፈስ እንዲኖርበት እንዲሁም የእግዚአብሔር ልጆች “ቤዛቸውን ለማወቅ” የሚሄዱበት ቦታ እንዲሆን የክህነት ሥልጣን ባላቸው የተመረቀ ነው። ከፈለግን በተቀደሡ የአምልኮ ቦታዎቻችን “ልናርፍ” እና እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን እንደሆነ፣ እኛም ልጆቹ እንደሆንን እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እንደሆነ ልናውቅ እንችላለን።

ቤተመቅደሥ እግዚአብሔርን ለማምለክ እና ለማገልገል እንዲሁም ዘለዓለማዊ እውነቶችን ለመማር የተለየ፣ ሌላኛው የተቀደሠ ቦታ ነው። በጌታ ቤት ውስጥ የምናስበው፣ የምንተገብረው እና የምንለብሠው አዘወትረን ከምንገኝባቸው ከሌሎች ከማናቸውም ቦታዎች በተለየ ሁኔታ ነው። በተቀደሠ ቤቱ ውስጥ፣ ከፈለግን ልናርፍ እና እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን እንደሆነ፣ እኛም ልጆቹ እንደሆንን እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እንደሆነ ልናውቅ እንችላለን።

የተቀደሠ ጊዜ እና የተቀደሱ ቦታዎች ዋና ዓላማዎች አንድ ነው፦ በሠማይ አባታችን እና በዕቅዱ ላይ፣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በኃጢያት ክፍያው ላይ፣ በመንፈስ ቅዱስ የማነፅ ሃይል እና ዳግም በተመለሰው የአዳኙ ወንጌል ቅዱሥ ሥርዓቶች እና ቃል ኪዳኖች ጋር በተያያዙ ተስፋዎች ላይ በተደጋጋሚ ማተኮር ነው።

ዛሬ፣ ከዚህ በፊት አፅንዖት ሰጥቼው የነበረውን መርህ እደግመዋለሁ። ቤቶቻችን፣ ግለሰቦች እና ቤተሰቦች “ሊያርፉ” እና እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን እንደሆነ፣ እኛም ልጆቹ እንደሆንን እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እንደሆነ ሊሚያውቁ የሚችሉባቸው የተቀደሠ ጊዜ እና የተቀደሠ ቦታ ታላቅ ጥምረት መሆን አለባቸው። በሠንበት ዕለት እንዲሁም በጌታ ቤት ውስጥ ለማምለክ ከቤታችን መውጣት በእርግጠኝነት አስፈላጊ ነው። ሆኖም ከእነዚያ የተቀደሡ ቦታዎች እና ተግባራት የተገኘውን መንፈሳዊ ዕይታ እና ጥንካሬ ይዘን ወደ ቤታችን ስንመለስ ብቻ ነው ትኩረታችንን በምድራዊ ህይወት ዋና አላማዎች ላይ ማድረግ እና በወደቀው ዓለም ውስጥ ተስፋፍተው የሚገኙትን ፈተናዎች ማሸነፍ የምንችለው።

ዘላቂ የሆኑ የሠንበት፣ የቤተመቅደሥ እና የቤት ልምዶቻችን፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ ከአብ እና ከወልድ ጋር በሚደረግ ዘላቂ የሆነ እና ጠንካራ የቃል ኪዳን ግንኙነት እንዲሁም በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ተስፋዎች “ፍጹም የሆነ የተስፋ ብርሃን” ሊያጠናክሩን ይገባል።

ቤት እና ቤተክርስቲያን በክርስቶስ በአንድ እንደተጠቀለሉ፣ በሁሉ ልንገፋ እንችላለን እንጂ በአዕምሯችን እና በልባችን አንጨነቅም። በሁኔታዎቻችን እና በፈተናዎቻችን እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም። ልንሠደድ እንችላለን እንጂ በምንም ብቻችንን እንደማንሆን እናውቃለን ፅኑ እና እውነተኛ ለመሆን እና ሆነን ለመቀጠል መንፈሳዊ ጥንካሬን ልንቀበል እንችላለን።

የተስፋ ቃል እና ምስክርነት

የህይወታችንን መሠረት በኢየሱስ ክርስቶስ “ዓለት” ላይ ስንገነባ፣ እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን እንደሆነ እኛም ልጆቹ እንደሆንን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እንደሆነ እንድናውቅ እና እንድናስታውስ የሚያስችለንን የነፍስን የግል እና መንፈሳዊ እረፍትን ለመቀበል እንዲሁም ከባድ ነገሮችን ለመፈፀም እና ለመቋቋም በመንፈስ ቅዱስ ልንባረክ እንደምንችል ቃል እገባለሁ።

እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን እንደሆነ፣ እኛም ልጆቹ እንደሆንን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛችን እና የደህንነታችን “ዓለት” እንደሆነ በደሥታ እመሠክራለሁ። እንዲህ የምመሰክረውም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።