ሀቀኝነት፦ የክርስቶስ መሰል ባሕርይ
የሀቀኝነት ህይወትን መኖር ለእግዚአብሔር፣ አንዳችን ለሌላችን እና ለመለኮታዊ ማንነታችን ታማኝ መሆንን ይጠይቃል።
አዳኙ በአገልግሎቱ የመጨረሻዎቹ ሰአታት ላይ፣ ወደ ደብረዘይት ተራራ በመሄድ ጌተሰማኔ ወደሚባል የአትክልት ስፍራ ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንዲጠብቁት ጋበዛቸው። አሁን ብቻውን በሆነበት ወቅት፣ “ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ”ሲል ወደ አባቱ ጸለየ። በከባድ ሥቃይ ውስጥ የነበረ በመሆኑ፣ “የሁሉም ታላቅ የሆነውን እግዚአብሄርን፣ እርሱን [እንኳን]፣ ከስቃዩ የተነሳ እንዲንቀጠቀጥ እናም ከእያንዳንዱ ቀዳዳ እንዲደማ እናም እንዲሰቃይ… እናም መራራውን ጽዋ መጠጣትን እንዳይፈልግ እና እንዲሸማቀቅ” አድርጎታል። “ሆኖም፣ በዚህ ጥልቅ የተሥፋ መቁረጥ ጊዜ፣ “አዳኙ ለሰዎች ልጆች ዝግጅቱን ጨረሰ” እንጂ አላፈገፈገም።
የአብ አንድያ ልጅ እንደመሆኑ መጠን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞት፣ በህመም እና በስቃይ ላይ ሃይል ነበረው ሆኖም ግን አላፈገፈገም። ለአባቱ የገባውን ቃል ኪዳን ፈጸመ፣ ይህንን በማድረግም፣ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ አስፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣውን የክርስቶስ መሠል የሀቀኝነትን ባህሪይ አሳየ። ለእግዚአብሔር፣ ለእያንዳንዳችን እና መለኮታዊ ለሆነው ማንነቱ ታማኝ ሆኖ ቆየ።
ሀቀኝነት
ኢየሱስ ክርስቶስ አርዓያችን ነው። የሀቀኝነት ሕይወትን መኖር፣ ለእግዚአብሔር፣ አንዳችን ለሌላችን እና ለመለኮታዊ ማንነታችን ታማኝ መሆንን ይጠይቃል። ሀቀኝነት እግዚአብሔርን ውደድ ከሚለው ከመጀመሪያው ታላቅ ትዕዛዝ ይመነጫል። እግዚአብሔርን ስለምትወዱት በሁሉም ጊዜያት ለእርሱ ታማኞች ናችሁ። ትክክል የሆነ ነገር እና ትክክል ያልሆነ ነገር እንዳለ እንዲሁም የእግዚአብሔር እውነት የሆነ ፍጹም እውነት እንዳለ ትረዳላችሁ። ሀቀኝነት ማለት ሌሎችን ለማስገረም ወይም በሌሎች ተቀባይነትን ለማጝኘት ከዚህ በፊት የነበሩንን መሥፈርቶቻችንን ወይም ባህሪያችንን ዝቅ አናደርግም ማለት ነው። እናንተ “ትክክል የሆነውን ነገር አድርጉ” ከዚያም የድርጊታችሁ ውጤት ተከትሎ እንዲመጣ ፍቀዱ።” በቅርብ ጊዜ በወንጌሌን ስበኩ የሚሲዮናዊ ማንዋል ላይ በተደረገ ክለሳ ሀቀኝነት የክርስቶስ መሰል ባህርይ በመሆን ተካቷል።
ከብዙ አመታት በፊት፣ ሽማግሌ ኡክዶርፍ ካስማችንን በድጋሚ እንዲያደራጁ ተመድበው ነበር። በቃለ መጠይቃች ላይ፣ ፦“ለማህበረሰቡ እይታ ቢቀርብ አንተን ወይም ቤተክርስቲያኗን የሚያዋርድ ነገር በሕይወትህ ውስጥ አለ?” ሲሉ ከአዕምሮዬ ያልጠፋ ጥያቄ ጠየቁኝ። በመገረም፣ ሳላሳካ የቀረሁበትን ጊዜ ለማስታወስ እየሞከርኩኝ፣ ሌሎች ያደረኩትን ነገር በሙሉ ቢያውቁ፣ ስለእኔ ወይም ስለቤተክርስቲያኗ ምን ሊያስቡ ይችሉ ይሆን? በማለት እራሴን እየጠየኩ፣ በፍጥነት በአእምሮዬ ጠቅላላ ሕይወቴን መመልከት ጀመርኩ።
በጊዜው፣ ሽማግሌ ኡክዶርፍ ስለብቁነት ብቻ እየጠየቁ ያለ መስሎኝ ነበር ነገር ግን ጥያቄው በእርግጥም ስለ ሀቀኝነት እንደሆነ መረዳት ችያለሁ። ተግባራቶቼ ከተናገርኩት ነገር ጋር አብረው የሚሄዱ ነበሩ? ዓለም ቃሌ እና ተግባሬ አብረው እንደሚሄዱ ማየት ይችላል? በባህሪዬ በኩል ሌሎች እግዚአብሔርን ማየት ይችላሉ?
ፕሬዚዳንት ስፔንሰር ደብሊው ኪምቦል ፦ “ሀቀኝነት በምናምንበት ነገር እና ለተሰጠንበት ነገር ለመኖር ፍቃደኛ መሆን ነው”ሲሉ አስተምረዋል።
ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን
የሀቀኝነት ሕይወት በመጀመሪያ እና በዋነኝነት ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆንን ይጠይቃል።
ከልጅነታችን ጀምሮ፣ በአንበሳ ዋሻ ውስጥ ስለነበረው ስለዳንኤል ታሪክ ተምረናል። ዳንኤል ለእግዚአብሔር ሁሌም ታማኝ ነበር። ይቀኑበት የነበሩት እኩዮቹ “[በዳንኤልም] ላይ ሰበብ ይፈልጉ ነበር” እናም ጸሎት ለባዕድ አምላካቸው ብቻ እንዲቀርብ ብርቱ ትዕዛዝ እንዲወጣ ተማከሩ። ዳንኤል ስለ ህጉ ያውቅ ነበር ነገር ግን ወደቤት ሄዶ “መስኮቶቹን ከፍቶ” ለእስራኤል አምላክ በቀን ሶስት ጊዜ ተንበርክኮ ጸለየ። በውጤቱም ዳንኤል ወደ አንበሶች ጉድጓድ ተጣለ። በነጋታውም፣ ንጉሱ የዳንኤል አምላክ ዳንኤልን እንዳዳነው ተመለከተ ከዚያም እርሱ ህያው አምላክ ነው በማለት ሁሉም “በዳንኤል አምላክ ፊት እንዲፈሩና እንዲንቀጠቀጡ አዲስ ትዕዛዝ አወጣ።”
ንጉሱ በዳንኤል ሀቀኝነት በኩል እግዚአብሔርን ወደማወቅ መጣ። ሌሎች፣ እግዚአብሔርን በቃላቶቻችን እና በስራዎቻችን ያውቃሉ። ልክ እንደ ዳንኤል፣ ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን እየጨመረ በሚሄድ ሁኔታ ከዓለም የተለየን ያደርገናል።
አዳኙ ፦ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ሲል ያስታውሰናል። ፕሬዚዳንት ራስልኤም. ኔልሰን፣ ዓለምን ማሸነፍ “ማለት ከእግዚአብሔር ነገሮች ይልቅ ስለዚህ ዓለም ነገሮች እንድናስብ የሚፈትነንን ነገር ማሸነፍ ማለት እንደሆነ፣ ይህም፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ከሰዎች ፍልስፍና በላይ ማመን ማለት እንደሆነ”ምክር ሠጥተዋል። በተመሳሳዩም፣ “በገዛ መንገዳችን ለመሄድ እናም የጣኦት ቁሳቁስ በሆነው አምሳያውም የአለም በሆነው ምስል መንገድ ለመራመድ የሚመጣን ፈተና መቋቋም አለብን።”
የዚህ ዓለም የተቃርኖ ሳቢ ሃይል የእግዚአብሔር የደህንነት እቅድ ወሳኝ ክፍል ነው። ለተቃርኖው ሳቢ ሃይል ምላሽ የምንሰጥበት መንገድ ማንነታችንን ይገልፃል— የሀቀኝነታችን መለኪያ ነው። ዓለማዊ የስበት ሃይል፣ ልክ በትዳር ውስጥ ታማኝነትን እንደማጥፋት ወይም የቤተክርስቲያኗን ትምህርት ወይም ባህል በመቃወስ ስም ባለመስጠት መልእክትን እንደመላክ አይነት ቀጥተኛ ሊሆን ይችላል። ምርጫዎቻችንን ስናደርግ ሀቀኝነትን መለማመድ፣ አዳኙን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ያለን ውስጣዊ ቁርጠኝነት ውጫዊ መገለጫ ነው።
ለሌሎች ታማኝ መሆን
ሃቀኝነት እግዚአብሔርን ውደድ ከሚለው ከመጀመሪያው ታላቁ ትዕዛዝ እንደሚመነጭ ሁሉ እርስ በእርስ ታማኝ መሆን፣ ባልንጀራችንን እንደራሳችን እንድንወድ ከተሠጠን ከሁለተኛው ትዕዛዝ ይመነጫል። የሃቀኝነት ሕይወት የፍፁምነት ሕይወት አይደለም፣ እያንዳንዱን ቀን ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ታማኝ ለመሆን የምንጥርበት ሕይወት ነው። ፕሬዚዳንት ኦክስ፣ “ሁለተኛውን ትዕዛዝ ለመጠበቅ ያለን ቅንዓት የመጀመሪያውን እንድንረሳ ምክንያት መሆን እንደሌለበት” አስታውሰውናል።
አለም በሰዎች እና በተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚቆጣጠሩ የስነምግባር ደንቦችን በማስገደድ በበለጠ ሁኔታ ከሃቀኝነት ጋር እየታገለ ይገኛል። እነዚህ ህጎች ጥሩ ቢሆኑም በአጠቃላይ በፍጹም እውነት ላይ የተመሰረቱ አይደሉም እንዲሁም በባህላዊ እሴት ተቀባይነት በማግኘታቸው ምክንያት የጸደቁ ናቸው። ሽማግሌ ኡክዶርፍ ከጠየቁት ጥያቄ ጋር በሚመሣሠል ሁኔታ፣ አንዳንድ ድርጅቶች የሰራተኞቻቸው ውሳኔዎች ወይም የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት በበይነ መረብ ላይ ወይም በታላቅ ጋዜጣ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ቢታተም ምን እንደሚመስል እንዲያስቡ ያሠለጥናሉ። ቤተክርስቲያኗ ከተደበቀችበት እና ከጨለማ ስትወጣ፣ እኛም ልክ እንደ ዳንኤል የአለምን ተፅእኖዎች ተቋቁመን በማንኛውም ጊዜ እና በማንኛውም ቦታ የህያው እና እውነተኛው አምላክ ወኪል መሆን አለብን።
ተግባራችን ከቃላቶቻችን ጋር የማይሄዱ ከሆነ ሃቀኝነት አለን ማለቱ በቂ አይደለም። በተመሣሣይ መልኩ፣ ክርስቲያናዊ ደግነት ሃቀኝነትን አይተካም። የቃል ኪዳን ሕዝቦች እንደመሆናችን እና የእርሱ ቤተክርስቲያን መሪዎች እንደመሆናችን ከፍ ያለ ብቃት እንዳለን እና ከወቀሳ ነጻ እንደሆንን አለማሰብ እና ጌታ ካስቀመጠው አቋም ጋር የምንስማማ መሆን አለብን።
በሀቀኝነት መተግበር እምነትን ይገነባል እንዲሁም የጌታን ፍቃድ ብቻ ለመፈጸም እንደምንፈልግ ለሌሎች ማረጋገጫ ይሰጣል። በምክር ቤቶቻችን ውስጥ፣ ከእያንዳንዱ ወንድ እና ሴት ሃሳብን እየጠየቅን እና በተቀበልነው ተነሳሽነት ባለው ምክር መሰረት እየተገበርን የተገለጠውን የጌታን ሂደት እየተከተልን የውጭ ተጽእኖዎችን እንቋቋማለን።
ትኩረታችን በአዳኙ ላይ ነው፣ እንዲሁም የራሳችንን ፍላጎት እንደማሟላት፣ ቤተሰባችንን እንደመጥቀም ወይም በሌላው ጉዳት አንድን ሰው እንደምናስበልጥ አስመስለው ሊያሳዩን ከሚችሉ ድርጊቶች እንቆጠባለን። በሰዎች ዘንድ ክብርን እንዲሁም በማህበራዊ ድረ ገጽ ተወዳጅነትን ለማግኘት እንዲሁም በሰዎች ንግግር መሃል ሃሳባችን እንዲጠቀስ ወይም እንዲታተም የምናደርጋቸው እንዳይመስል የተለየ ጥረትን እናደርጋለን።
ለመለኮታዊ ማንነታችን ታማኝ መሆን
በመጨረሻም፣ የሀቀኝነት ኑሮ ለመለኮታዊ ማንነታችን ታማኝ መሆንችንን ይጠይቃል።
ታማኝ ያልነበሩ አንዳንዶችን እናውቃለን። በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚገባው ጸረ-ክርስቶስ የሆነው፣ “ስለስጋ” እንዲያስቡ በማድረግ የብዙዎችን ልብ ያሳተው ቆሪሆር ነው። ሆኖም፣ በሕይወቱ የመጨረሻዎቹ ጊዜያት፦ “ሁል ጊዜም እግዚአብሔር እንዳለ አውቅ ነበር” ሲል ተናዟል። ፕሬዚዳንት ሔንሪይ ቢ አይሪንግ፣ መዋሸት መለኮታዊ ማንነታችን ከሆነው“ከመንፈሳችን ባህርይ ጋር ይጻረራል” ሲሉ አስተምረዋል። ቆሪሆር እራሱን አታለለ፣ እውነትም በውስጡ አልነበረም።
በተቃራኒው ነብዩ ጆሴፍ ስሚዝ በድፍረት እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “እኔ አውቄዋለሁ፣ እናም እግዚአብሔር እንዳወቀው አውቄዋለሁ ፣ እናም ልክደው አልቻልኩም።”
የጆሴፍ ወንድም ሐይረም “በልቡ ሀቀኝነት ምክንያት በጌታ ተወዳጅ ነበር።” እርሱና ጆሴፍ ለመለኮታዊ ማንነታቸው፣ ለተቀበሉት ብርሃን እና እውቀት፣ እንዲሁም ሊሆኑት እንደሚችሉት ለሚያውቁት ሰው እስከመጨረሻው ታማኝ ሆነው ቆዩ።
ማጠቃለያ
እራሳችንን “ከእግዚአብሔር ፍቃድ ጋር ”እናስታርቅ እንዲሁም የሀቀኝነትን ክርስቶስ መሰል ባህሪይ እናዳብር። ለእግዚአብሔር፣ አንዳችን ለሌላችን እንዲሁም ለመለኮታዊ ማንነታችን ታማኝ የሆነን ሕይወት በመኖር እንጂ ባለማፈግፈግ የአለም አዳኝ የሆነውን ምሳሌያችንን እንከተል።
እዮብ እንዳለው፣ “በእውነተኛ ሚዛን ልመዘን፥ እግዚአብሔርም ቅንነቴን ይወቅ።” በተቀደሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን።