አጠቃላይ ጉባኤ
ከፍ ያለ ደሥታ
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


15:37

ከፍ ያለ ደሥታ

ሁላችንም ህይወታችንን ለሰማይ አባታችን እና ለውድ ልጁ በመሥጠት የሚገኘውን ከፍ ያለ ደስታ እንፈልግ እንዲሁም እናግኝ።

ለሦስት አስርት ዓመታት በአጠቃላይ ጉባኤ ላይ የመናገር ታላቅ በረከትን አግኝቻለሁ። በእነዚያ ጊዜያት፣ በአለም ዙሪያ በሚገኙ በብዙ ሰዎች ከእነዚህ መልዕክቶች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ተጠይቂያለሁ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ አንድ የተለየ ጥያቄ ደጋግሞ በመምጣት ላይ ይገኛል። አብዛኛውን ጊዜ ይህን ይመስላል፦ “ሽማግሌ ኡክዶርፍ፣ የመጨረሻውን ንግግርዎን በጥሞና አዳምጫለሁ ሆኖም … ስለ አውሮፕላን በረራ ምንም አልሰማሁም።”

እንግዲህ፣ ከዛሬ በኋላ፣ ያንን ጥያቄ ለተወሰነ ጊዜ ላልሰማው እችላለሁ።

“በፀሐይ ጮራ የተሠነጠቀው በዓየር ላይ የሚንከባለለው ደመና” ላይ [“the Tumbling Mirth of Sun-Split Clouds”]

ዊልበር ራይት እና ኦርቪል ራይት ለመጀመሪያ ጊዜ መሬትን ለቀው ተነስተው በሰሜን ካሮላይና ከምትገኘው ኪቲ ሃውክ አሸዋ በላይ የበረሩት ከ120 ዓመታት በፊት እንደነበረ ለማመን ይከብዳል። በዚያ የታኅሣሥ ቀን የተደረጉት አራት አጫጭር በረራዎች ዓለምን ቀይረዋል እንዲሁም በዓለም ታሪክ ውስጥ ካሉት ታላላቅ ፈጠራዎች አንዱ ለሆነው በር ከፍተዋል።

በእነዚያ የመጀመሪያዎቹ ቀናት አውሮፕላን ማብረር አደገኛ ነበር። ወንድማማቾቹ ይህንን ያውቁ ነበር። አባታቸው ሚልተንም እንዲሁ ያውቅ ነበር። በእርግጥ፣ ሁለቱንም ልጆቹን በአውሮፕላን አደጋ እንደሚያጣቸው በጣም ፈርቶ ስለነበረ በፍፁም አብረው እንደማይበሩ ቃል ገቡለት።

ስለዚህም፣ ከአንድ ጊዜ በስተቀር በጭራሽ ያንን አላደረጉም ነበር። በኪቲ ሃውክ ከነበረችው ከዚያች ታሪካዊ ቀን ከሰባት አመታት በኋላ፣ ሚልተን ራይት በመጨረሻ ፈቃዱን ሰጠ እንዲሁም ዊልበር እና ኦርቪል ለመጀመሪያ ጊዜ አብረው ሲበሩ ተመለከታቸው። አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ፣ ኦርቪል አባቱ የመጀመሪያ ጊዜውን እና ብቸኛውን የአውሮፕላን በረራ እንዲያደርግ እና ምን እንደሚመስል በራሱ እንዲያይ አሳመነው።

የ82 ዓመት ዕድሜ የነበረው ሚልተን፣ አውሮፕላኑ ከመሬት ሲነሳ በበረራው ደስታ ከመዋጡ የተነሣ ፍርሃቱ ሁሉ ለቀቀው። አባቱ “ከፍ በል፣ ኦርቪል፣ ከፍ በል!” እያለ በደስታ ሲጮህ፣ ኦርቪል ሳቀ።

ይህ ሠው የተሠማው እኔን እንደሚሠማኝ ነበር፡፡

ምናልባት አልፎ አልፎ ስለ አውሮፕላን በረራ የምናገርበት ምክንያት፣ የራይት ወንድማማቾች የተሰማቸውን የሆነ ነገር ስለማውቅ ይሆናል። እኔም “ብርማ ክንፎቹ ሣቅን እና ደሥታን እያንፀባረቁ በአውሮፕላን በመብረር ከምድር የስበት ኃይል በማለፍ በሠማይ ላይ ተንሣፍፊያለሁ።”

ከመወለዴ ከ 37 ከማይበልጡ ዓመታት በፊት የተደረገው የራይት ወንድማማቾች የመጀመሪያ በረራ፣ በህይወቴ ውስጥ የጀብድ፣ የድንቅ እና የንጹህ ደስታ በሮችን ከፍቶልኛል።

ያ ደስታ አስደናቂ ቢሆንም፣ ከዚያም የበለጠ ከፍ ያለ የደስታ አይነት ደግሞ አለ። ሚልተን ራይት፣ “ከፍ በል፣ ኦርቪል፣ ከፍ በል!” ሲል ባሠማው የደስታ ጩኸት መንፈሥ፣ ይህ ከፍ ያለ ደስታ ከየት እንደሚመጣ፣ እንዴት ወደ ልባችን እንደሚገባ እና እንዴት በላቀ መጠን ልንለማመደው እንደምንችል ዛሬ ለመናገር እፈልጋለሁ።

የሠው ልጅ አጠቃላይ የህልውና ዓላማ

ሁሉም ሰው ደስተኛ መሆን እንደሚፈልግ ሣይታለም የተፈታ ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰው ደስተኛ እንዳልሆነም እንዲሁ ሣይታለም የተፈታ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ ለብዙ ሰዎች ደስታን ማግኘት አስቸጋሪ የሆነ ነገር ይመስላል።

ያ የሆነው ለምንድን ነው? እኛ ሰዎች ከሁሉም አስበልጠን የምንፈልገው ብቸኛው ነገር ደስታ ከሆነ፣ እሱን በማግኘት ረገድ ያን ያህል ውጤታማ ያልሆንነው ለምንድነው? አንድን የካንትሪ ዘፈን በራሴ አባባል ለመግለፅ ያህል፣ ምናልባት ደስታን በሁሉም የተሳሳቱ ቦታዎች እየፈለግን ሊሆን ይችላል።

ደስታን ማግኘት የምንችለው የት ነው?

ደስታን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ከመወያየታችን በፊት፣ የአዕምሮ ጭንቀት እና ሌሎች ከባድ የአዕምሮ እና የስሜት ተግዳሮቶች እውን ስለመሆናቸው እውቅና እንድሠጥ ፍቀዱልኝ፤ እንዲሁም መፍትሄው እንዲያው በቀላሉ “ደስተኛ ለመሆን ሞክሩ” የሚል አይደለም። የዛሬ አላማዬ የአዕምሮ ጤና ጉዳዮችን ዝቅ ማድረግ ወይም አስፈላጊነታቸውን ማቃለል አይደለም። እንደዚህ አይነት ተግዳሮቶች ከገጠሟችሁ ጋር አብሬያችሁ አዝናለሁ እንዲሁም ከጎናችሁ ነኝ። ለአንዳንድ ሰዎች፣ ደስታን መፈለግ፣ የህክምና ጥበብን ለመለማመድ ህይወታቸውን ካዋሉ የሠለጠኑ የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎች እርዳታን መሻት በጣም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። እንደዚህ ላሉት እርዳታዎች አመስጋኞች መሆን አለብን።

ህይወት የማያቋርጥ የስሜት ከፍታ ፍሠት አይደለም። “ለሁሉም ነገሮች ተቃራኒ መኖር አስፈላጊ ነውና።” ቅዱሳት መጻህፍት እንደሚያረጋግጡት፣ እግዚአብሔር ራሱ የሚያለቅስ ከሆነ፣ ደግሞም፣ በእርግጥ እናንተ እና እኔም እናለቅሳለን። የሀዘን ስሜት መሠማት የውድቀት ምልክት አይደለም። በዚህ ህይወት ውስጥ ደስታ እና ሀዘን ቢያንስ የማይነጣጠሉና በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው። እንደ ሁላችሁም፣ እኔም ተስፋ መቁረጥ፣ ሥቃይ፣ ሀዘን እና ጸጸት ተሠምቶኛል።

ሆኖም፣ መሸከም እስኪያቅት ድረስ በጥልቅ ደስታ ነፍስን የሚሞላ ታላቅ ጎህ እኔንም አጋጥሞኛል። ይህ ሠላማዊ መተማመን የሚመጣው አዳኙን በመከተል እና በመንገዱ በመጓዝ እንደሆነ በራሴ ተረድቻለሁ።

እርሱ የሚሠጠን ሠላም ዓለም እንደሚሠጠው ዓይነት አይደለም። የተሻለ ነው። ከፍ ያለ እና የተቀደሠ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፣ “እኔ ህይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውን መጣሁ።”

የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በእውነት፣ “ታላቅ ደስታ የምሥራች” ነው! አቻ የማይገኝለት የተስፋ መልዕክት ነው! ቀንበርን የመሸከም እና ሸክምን የማቅለል መልዕክት ነው። ብርሃንን የመሠብሠብም። የሠማያዊ ሞገስ፣ የላቀ ግንዛቤ፣ ቅዱስ ቃል ኪዳኖች፣ የዘለዓለማዊ ደህንነት እና የዘለዓለማዊ ክብር!

ደስታ፣ እግዚአብሔር ለልጆቹ ያለው ዕቅድ ዓላማ ነው። ለዚያ ነው የተፈጠራችሁት—“ደስታም [እንዲኖራችሁ] ዘንድ”! የተፈጠራችሁት ለዚህ ነው!

የሰማይ አባታችን ወደ ደስታ የሚወስደውን መንገድ አልደበቀም። ሚሥጥር አይደለም። ለሁሉም ይገኛል!

በደቀመዝሙርነትን መንገድ ለሚጓዙ፣ የአዳኙን ትምህርት እና ምሳሌ ለሚከተሉ፣ ትዕዛዛቱን ለሚጠብቁ እና ከእግዚአብሔር ጋር የገቧቸውን ቃል ኪዳኖች ለሚያከብሩ ቃል ተገብቷል። እንዴት አስደናቂ የሆነ የተስፋ ቃል ነው!

እግዚአብሔር የሚሠጠው ሌላ ተጨማሪ ነገር አለው።

ደስተኛ ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር እንደማያስፈልጋቸው፣ ያለ ሃይማኖት ደስተኛ እንደሆኑ የሚናገሩ ሰዎችን ሁላችንም እናውቃለን።

ለእነዚህን ሥሜቶች እውቅና እሠጣለሁ እንዲሁም አከብራቸዋለሁ። ውድ የሰማይ አባታችን ሁሉም ልጆቹ በተቻለ መጠን ብዙ ደስታ እንዲኖራቸው ይፈልጋል፣ ስለዚህ ይህንን ዓለም “ዓይንን እና … ልብን በሚያስደስቱ” በሚያምሩ፣ ጤናማ በሆኑ የእርካታ ምንጮች እና ደስታዎች ሞልቶታል። ለእኔ አውሮፕላንን ማብረር ትልቅ ደስታን አምጥቶልኛል። ሌሎች ደግሞ በሙዚቃ፣ በሥነ ጥበብ፣ በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ወይም በተፈጥሮ ውስጥ ያገኙታል።

ሁሉንም በመጋበዝ እና የአዳኙን ታላቅ ደስታ የምሥራች በማጋራታችን፣ የአንዳቸውንም የእነዚህን የደስታ ምንጮች አስፈላጊነት አናቃልልም። በቀላሉ እግዚአብሔር የሚሰጠን ተጨማሪ ነገር አለው እያልን ነው። ይህም ዓለም ከሚሠጠው ከማንኛውም ነገር በላይ የሆነ፣ የላቀ ትርጉም ያለው እና ጥልቅ ደሥታ ነው። ይህ ደስታ በልብ ሥብራት ውስጥም የሚፀና፣ ሀዘን ውስጥ ዘልቆ የሚገባ እንዲሁም ብቸኝነትን የሚቀንስ ነው።

በተቃራኒው ዓለማዊ ደሥታ አይዘልቅም። ሊዘልቅ አይችልም። ማርጀት፣ መበስበስ፣ መመንመን ወይም መሻገት የምድራዊ ነገሮች ሁሉ ባህርይ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ በመሆኑ ምክንያት፣ አምላካዊ ደስታ ዘለዓለማዊ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የምድራዊ ህይወት ተፅዕኖዎችን እንድንቋቋም እና የሚበሠብሠውን በማይበሰብሠው ይለውጣል። ይህንን የመሰለ ሃይል ያለው እርሱ ብቻ ነው እንዲሁም ዘላቂ የሚሆነውም ከእርሱ የሚመጣው ደሥታ ብቻ ነው።

በህይወታችሁ ውስጥ እንደዚህ አይነት ተጨማሪ ደስታ ሊኖር እንደሚችል ከተሰማችሁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እና መንገዱን የመከተል ጉዞ እንድትጀምሩ እጋብዛችኋለሁ። ይህም በህይወት ዘመን የሚደረግ እና ከዚያም አልፎ የሚሄድ ጉዞ ነው። በዚህ ሊደከምለት በሚገባው ንፁህ ደስታን የማግኘት ጉዞ ላይ የሚወሰዱ ጥቂት የመጀመሪያ እርምጃዎችን ልጠቁም።

ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰችውን፣ ለ12 ዓመታት በደም መፍሠስ ህመም ስትሠቃይ የነበረችውን ሴት ታስታውሷታላችሁ? ያላትን ሁሉ በህክምና ባለሙያዎች ላይ አባከነች፣ ነገር ግን ነገሮች እየባሱባት ሄደ። ስለ ኢየሱስ ሰምታ ነበር፤ የመፈወስ ኃይሉ በደምብ የታወቀ ነበር። ሆኖም፣ ሊፈውሳት ይችል ይሆን? እንዴትስ ወደ እርሱ ለመቅረብ ትችላለች? በሙሴ ህግ መሠረት ህመሟ “ርኩስ” አድርጓታል፣ ስለዚህም ከሌሎች እንድትርቅ ይጠበቅባት ነበር።

ወደ እርሱ በመቅረብ በህዝብ ፊት ፈውስ መጠየቅ የሚታሰብ አይመስልም።

አሁንም፣ “ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደሆነ እድናለሁ” ስትል አሰበች።

በመጨረሻም፣ እምነቷ ፍርሃቷን እንድትቋቋም አደረገ። የሌሎችን ነቀፋ በድፍረት ተቋቁማ ወደ አዳኙ ተጠጋች።

በመጨረሻም ልትነካው በምትችልበት ርቀት ላይ ደረሰች። እጇን ዘረጋች።

ከዚያም ተፈወሰች።

ሁላችንስ ብንሆን በተወሰነ መልኩ እንደዚህች ሴት አይደለንምን?

ወደ አዳኙ ለመቅረብ የምናመነታባቸው ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ሌሎች ሊሳለቁብን ወይም ሊያወግዙን ይችላሉ። በኩራታችን ምክንያት አንድ በጣም ቀላል የሆነ ነገር ትልቅ ዋጋ ያለው የመሆን እድሉን ልናሳጣው እንችላለን። ያለንበት ሁኔታ እርሱ ለሚሠጠው ፈውስ ብቁ እንዳንሆን ያደርገናል ርቀቱ በጣም ሠፊ ነው ወይም ኃጢአታችን ብዙ ነው ብለን ልናስብ እንችላለን።

ልክ እንደዚች ሴት፣ ወደ እግዚአብሔር ከቀረብን እና እሱን ለመንካት እጃችንን ከዘረጋን፣ በእርግጥ ፈውስ፣ ሠላም እና ደስታ እንደምናገኝ ተምሬአለሁ።

ፈልጉት።

ኢየሱስ፣ “ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ” ሲል አስተምሯል።

ይህ ቀላል ሐረግ፣ መንፈሳዊ ተሥፋ ብቻ ሣይሆን የእውነት መግለጫ እንደሆነ አምናለሁ።

ለመናደድ፣ ለመጠራጠር፣ መራር ወይም ብቸኛ ለመሆን ምክንያቶችን ከፈለግን እናገኛቸዋለን።

ሆኖም፣ ደስታን ከፈለግን—ለመደሰት እና አዳኙን በደስታ ለመከተል ምክንያቶችን ከፈለግን እናገኛቸዋለን።

የማንፈልገውን ነገር አናገኝም።

ደስታን እየፈለጋችሁ ነውን?

ፈልጉ እናም ታገኙማላችሁ።

እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም።

ኢየሱስ፣ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሠጥ ብፁዕ ነው” በማለት አስተምሯል።

በደስታ ፍለጋችን ላይ፣ እሱን ለማግኘት ከሁሉም የተሻለው መንገድ ለሌሎች ደስታን ማምጣት ሊሆን ይችል ይሆን?

ወንድሞች እና እህቶች፣ እንደ እንደማውቀው እናንተም ይህ ውነት እንደሆነ ታውቃላችሁ! ደስታ እንደ ማድጋው ዱቄት ወይም እንደ ማሰሮው ዘይት ፈጽሞ አያልቅም። እውነተኛ ደስታ ለሌሎች በሚካፈልበት ጊዜ ይጨምራል።

ታላቅ ወይም ውሥብሥብ የሆነ ነገርን አይጠይቅም።

ቀላል ነገሮችን ማድረግ እንችላለን።

ለአንድ ሰው በልባችን በሙሉ እንደመጸለይ።

ልባዊ ምሥጋና እንደ ማቅረብ።

አንድ ሰው መልካም አቀባበል እንደተደረገለት፣ እንደተከበረ፣ ዋጋ እንደተሠጠው እና የሚወደድ እንደሆነ እንዲሰማው መርዳት።

ተወዳጅ ጥቅስን እና ለእኛ ያለውን ትርጉም ማካፈል።

ወይም በማዳመጥ ብቻም እንኳን ቢሆን።

“እናንተ ሰዎችን በምታገለግሉበት ጊዜ እግዚአብሔርን ብቻ እያገለገላችሁ [ነው]” እናም እግዚአብሔር ስለደግነታችሁ በልግስና ይከፍላችኋል። ለሌሎች ያመጣችሁት ደሥታ፣ “[በ]ተጨቆነና [በ]ተነቀነቀ [በ]ተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ” ወደ እናንተ ይመጣሉ።

“እንግዲህ ምን እናድርግ?”

በሚቀጥሉት ቀናት፣ ሳምንታት እና ወራት የሚከተሉትን እንድታደርጉ ልጋብዛችሁ፦

  • ወደ አምላክ ለመቅረብ በቅንነት፣ በሙሉ ልብ ጥረት በማድረግ ጊዜ አሳልፉ።

  • የዕለት ተዕለት የተስፋ፣ የሰላም እና የደስታ ጊዜያትን በትጋት ፈልጉ።

  • በዙሪያችሁ ላሉት ለሌሎች ደሥታን አምጡላቸው።

ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ውድ ጓደኞች፣ የእግዚአብሔርን ዘለአለማዊ እቅድ በጥልቅ ለመገንዘብ የእግዚአብሔርን ቃል ስትፈትሹ፣ እነዚህን ግብዣዎች ስትቀበሉ፣ እና በመንገዱ ለመራመድ ስትጥሩ፣ በሀዘን መካከልም “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም” ያጋጥማችኋል። እጅግ የላቀ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችሁ ውስጥ ሲያድግ ይሰማችኋል። የሰለስቲያል ጎህ ብርሀን የፈተናችሁን ዳመና ዘልቆ ይገባል፣ እንዲሁም የማይታየውን፣ ፍጹም የሆነውን፣ የሰማይ ክፍል ሊነገሩ የማይችሉ ክብሮች እና አስደናቂ ነገሮች ማጣጣም ትጀምራላችሁ። መንፈሳችሁ ከዚህ አለም አሉታዊ ተፅዕኖዎች በላይ ከፍ ሲል ይሰማችኋል።

እንዲሁም ልክ እንደ መልካሙ ሰው እንደ ሚልተን ራይት፣ ምናልባት እናንተም ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ በደስታ “ከፍ በል፣ አባ፣ ከፍ በል!” እያላችሁ ትጮላችሁ።

ሁላችንም ህይወታችንን ለሰማይ አባታችን እና ለውድ ልጁ በመሥጠት የሚገኘውን ከፍ ያለ ደስታ እንፈልግ እንዲሁም እናግኝ። ይህ ልባዊ ፀሎቴ እና በረከቴ ነው፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ጆን ጊሌስፒ ማጊ ዳግማዊ፣ “High Flight,” poetryfoundation.org.

  2. ክሪስቶፈር ከሌን፣ “10 Things You May Not Know about the Wright Brothers [ስለራይት ወንድሞች ያላወቋችኋቸው አስር ነገሮች],” History፣ መጋቢት 28፣ 2023 (እ.አ.አ)፣ history.com ይመልከቱ።

  3. ማጊ፣ “High Flight.”

  4. ከሁለት ሺህ አራት መቶ ዓመታት በፊት፣ አርስቶትል የሰው ልጆች ሁሉ ከሁሉም አስበልጠው የሚፈልጉት አንድ ነገር ቢኖር ደስታ እንደሆነ ተገንዝቧል። Nicomachean Ethics፣ በተሠኘው ፅሁፉ በህይወታችን ውስጥ ከሁሉም ትልቁ መልካም ነገር ሌሎች ነገሮችን የሚያሳኩ ነገሮችን ከመከተል ይልቅ የመጨረሻውን ግብ መከተል እንደሆነ አስተምሯል። ከሌሎች ከሁሉም ነገሮች በላይ፣ ደስታ ልክ እንደዚህ ያለ ነገር ነው። “እኛ ሁል ጊዜ ደስታን የምንመኘው ራሱን ፈልገነው እንጂ በእርሱ አማካኝነት ሌላ ነገርን ለማግኘት በፍጹም አይደለም” ብሏል (The Nicomachean Ethics of Aristotle ትርጉም) J. E. C. Weldon [1902], 13–14).

  5. ሃሪ ኤንተን “American Happiness Hits Record Lows,” CNN, Feb. 2, 2022, cnn.com፤ በተጨማሪም ታማራ ለሽ “Americans Are the Unhappiest They’ve Been in 50 Years,” Associated Press, June 16, 2020, apnews.com; “The Great Gloom: In 2023, Employees Are Unhappier Than Ever Ever. Why?” ይመልከቱ። BambooHR, bamboohr.com.

  6. ዋንዳ ማሌት፣ ቦብ ሞሪሰን፣ እና ፓቲ ራያን፣ “Looking for Love (in All the Wrong Places)” (1980) ይመልከቱ።

  7. 2 ኔፊ 2፥11

  8. ዮሃንስ 11፥35ሙሴ 7፥28–37 ይመልከቱ።

  9. 2 ኔፊ 2፥11ን ይመልከቱ።

  10. ዮሀንስ 14፥27ን ይመልከቱ።

  11. ዮሀንስ 10፥10

  12. ሉቃስ 2፥10፣ አዲሱ የተከለሰ መደበኛ ዕትም፡፡

  13. ማቴዎስ 11፥28–30ን ይመልከቱ።

  14. 2 ኔፊ 2፥25

  15. የሰማይ አባታችሁ ይቀበላችሁ እንደሆነ እንዲሁም እርሱ ለእናንተ ያለውን ደስታ ትቀበሉ ዘንድ ይፈቅድላችሁ እንደሆነ የሚያሳስባችሁ ነገር ካለ፣ ክርስቶስ ስለአባካኙ ልጅ የተናገረውን ምሳሌ በጸሎት መንፈሥ እንድታነቡ እጋብዛችኋለሁ (ሉቃስ 15፥11–32 ተመልከቱ)። ከዚያ ምሳሌ፣ የሰማይ አባታችን ስለ ልጆቹ ያለውን ስሜት እና ከእሱ ከራቅን በኋላ ተመልሰን መምጣታችንን እንዴት እንደሚጠብቅ እና እንደሚያከብር እንማራለን! ወደ ልባችን ከምንመለስበት (ቁጥር 17 ተመልከቱ) እና ወደ ቤታችን ጉዟችንን ከምንጀምርበት ቅፅበት አንስቶ ቆሞ የሚጠብቀን ስለሆነ፣ ያየናል። ማንን ነው የሚጠብቀው? እኛን! ወደ እርሱ ስንቀርብ፣ ተመልሰን በመምጣታችን ይደሠታል እንዲሁም ልጆቼ ብሎ ይጠራናል።

  16. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 59፥18። ይህ ራዕይ እንደሚገልጸው፣ “እናም እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለሰው ስለሰጠ እግዚአብሔርን ያስደስተዋል፤ … እንደዚህ እንዲጠቀሙባቸው ነውና የተፈጠሩት” (ቁጥር 20)።

  17. ወደ እግዚአብሔር ለሚቀርቡት የሚከተለውን ታላቅ ተስፋ ሰጥቷቸዋል፦“ወደ እናንተም [እቀርባለሁ]” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፥63፤ በተጨማሪም ያዕቆብ 4፥8 ይመልከቱ)።

  18. ማርቆስ 5፥24–34ን ይመልከቱ።

  19. Bible Dictionary፣ “Clean and Unclean [ንጹህ እና ርኩስ]” የሚለውን ይመልከቱ።

  20. ማርቆስ 5፥28

  21. ማቴዎስ 7፥7

  22. እያንዳን[ዳችን] የአንዱን ሸክም [በመሸከም] “የክርስቶስን ህግ [እንፈጽማለን]” (ገላትያ 6፥2፤ ደግሞም ሞዛያ 18፥8 ይመልከትቱ)።

  23. የሐዋርያት ስራ 20፥35

  24. 1 ነገሥት 17፥8–16ን ይመልከቱ።

  25. ሞዛያ 2፥17

  26. ለሮሜ ሰዎች በፃፈው መልዕክት ጳውሎስ “እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤ በበጎ ሥራ በመፅናት ምሥጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ህይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ህይወት ይሠጣቸዋል” (ሮሜ 2፥6–7፣ 10)።

  27. ሉቃስ 6፥38። ደህንነታችን እና ዘለዓለማዊ ደሥታችን ለሌሎች ባለን ርህራሄ እና ደግነት ላይ የሚመካ ሊሆን ይችላል (ማቴዎስ 25፥31–46 ይመልከቱ)።

  28. ሉቃስ 3፥10

  29. ፊልጵስዮስ 4፥7