አጠቃላይ ጉባኤ
ጸልዩ፣ እርሱ አለ
የአጠቃላይ ባለስልጣኖች፣ የክልል ሰባዎች እና አጠቃላይ መሪዎች ድጋፍ


ጸልዩ፣ እርሱ አለ

የሰማይ አባት እንዳለ ለማወቅ እንድትጸልዩ፣ እርሱን ለመምሰል ለማደግ እንድትጸልዩ እና ለሌሎች ፍቅሩን ለማሳየት እንድትጸልዩ እጋብዛችኋለሁ።

ወንድሞች እና እህቶች፣ ከልጆች ጋር እንድነጋገር ላነሳሳኝ ስሜት ምላሽ ስሰጥ ደስታ ይሰማኛል።

ሴት እና ወንድ ልጆች፣ በየትም አለም ብትገኙ፣ ለእናንተ አንድ ነገር ማካፈል እፈልጋለሁ።

የሰማይ አባታችን ይወዳችኋል! እናንተ የእርሱ ልጆች ናችሁ። ያውቃችኋል። እናንተን መባረክ ይፈልጋል። የእርሱ ፍቅር እንዲሰማችሁ በሙሉ ልቤ እጸልያለሁ።

ስጦታዎችን መቀበል ትወዳላችሁ? የሰማይ አባት እናንተን ለመርዳት ስለሰጣችሁ ልዩ ስጦታ ላናግራችሁ እፈልጋለሁ። ይህም የጸሎት ስጦታ ነው። ጸሎት እንዴት ያለ በረከት ነው! በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ የሰማይ አባትን ማነጋገር እንችላለን።

ምስል
ኢየሱስ ከህጻናት ጋር

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እንድንፀልይ አስተምሮናል። “ለምኑ፣ ይሰጣችሃል” በማለት ተናግሮናል።

ምን ዓይነት ስጦታዎችን ለማግኘት ልትጸልዩ ትችላላችሁ? ብዙ አሉ፣ ዛሬ ግን ሶስቱን ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ፦

  1. ለማወቅ ጸልዩ።

  2. ለማደግ ጸልዩ።

  3. ለማሳየት ጸልዩ።

ስለ እያንዳንዱ እንነጋገር።

መጀመሪያ፣ ለማወቅ ጸልዩ።

ማወቅ የሚያስፈልጋችሁ ምንድን ነው?

በዓለም ዙሪያ የመጀመሪያ ክፍል ልጆች ስለ ጸሎት የሚዘምሩት አንድ መዝሙር አለ። በጥያቄ ይጀምራል። የትኛው መዝሙር እንደሆነ ታውቃላችሁ? ደፋር ብሆን ኖሮ፣ እዘምርላችሁ ነበር!

“የሰማይ አባት፣ በእርግጥ አለህን? የሁሉንም ልጅ ጸሎት ትሰማለህ እና ትመልሳለህን?” የሚል ነው።

እርሱን ማየት ባትችሉም እንኳን የሰማይ አባት በእውነትም እንዳለ እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ?

ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ልባችሁን ለሰማዩ አባታችሁ አፍስሱ።… ከዚያም አዳምጡ!” በማለት ጋብዘዋችኋል። በልባቹሁ ውስጥ የሚሰማችሁን እና ወደ አእምሮአችሁ የሚመጡ ሀሳቦችን አዳምጡ።

የሰማይ አባት የከበረ የስጋና አጥንት አካል አለው እንዲሁም የመንፈሳችሁ አባት ነው። የሰማይ አባት ሁሉም ሀይል ስላለው እና ሁሉንም ነገሮች ስለሚያውቅ፣ ልጆቹን ሁሉ ማየት ይችላል እንዲሁም እያንዳንዱን ጸሎት መስማትና መመለስ ይችላል። እርሱ እንዳለ እና እንደሚወዳችሁ እራሳችሁ ማወቅ ትችላላችሁ።

የሰማይ አባት እንዳለና እርሱ እንደሚወዳችሁ ስታውቁ በድፍረት እና በተስፋ መኖር ትችላላችሁ! “ጸልዩ፣ እዚያ አለ፤ ተናገሩ፣ እያዳመጣችሁ ነው።”

ብቸኝነት ተሰምቷችሁ ያውቃል? አንድ ቀን የልጅ ልጃችን አሽሊ የስድስት ዓመት ልጅ እያለች፣ በትምህርት ቤት መጫወቻ ሜዳ ላይ የሚያጫውታት ጓደኛ ያልነበራት እሷ ብቻ ነበረች። እዚያ ቆማ፣ አስፈላጊ እንዳልሆነች እና በሌሎች የማትታይ እንደሆነች እየተሰማት ሳለ፣ “ቆይ! ብቻዬን አይደለሁም! ክርስቶስ አለኝ!” የሚል አንድ የተለየ ሀሳብ ወደ አእምሮዋ መጣ። አሽሊ በመጫወቻ ሜዳው መሃል ላይ ተንበርክካ እጆቿን አጣምራ ወደ ሰማይ አባት ጸለየች። ዓይኖቿን በከፈተችበት ቅጽበት፣ በእርሷ ዕድሜ የምትሆን አንዲት ልጅ እዚያ ቆማ መጫወት የምትፈልግ ከሆነ ጠየቀቻት። አሽሊ “ለጌታ አስፈላጊ መሆናችንን እና መቼም በእውነት ብቻችንን እንዳልሆንን ተምሬአለሁ” ስትል ጽፋለች።

አንዳንድ ጊዜ በህይወታችሁ ውስጥ ከባድ ነገር ለምን እየተፈጠረ እንደሆነ ወይም የጸለያችሁለትን በረከት ለምን እንዳልተቀበላችሁ ማወቅ ትፈልጉ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ የሰማይ አባትን ለመጠየቅ የተሻለ ጥያቄ የሚሆነው ለምን ሆነ የሚለው ሳይሆን ምን ማድረግ አለብኝ የሚለው ነው።

ኔፊ እና ቤተሰቡ በምድረበዳ ውስጥ እየተጓዙ እያለ ተርበው እንደነበር ታስታውሳላችሁ? ኔፊ እና ወንድሞቹ፣ ምግብ ፍለጋ ለማደን በሄዱ ጊዜ፣ ኔፊ ቀስቱን ቢሰበርም ለምን ብሎ አልጠየቀም።

ምስል
ኔፊ ምግብ የት ማግኘት እንደሚችል ሌሂን ጠየቀ።

ኔፊ አዲስ ቀስት ሰራና ምግብ ለማግኘት የት መሄድ እንዳለበት አባቱን ሌሂን ጠየቀው። ሌሂ ጸለየ፣ እናም ጌታ ኔፊ የት መሄድ እንዳለበት አሳያቸው። የሰማይ አባትን ምን ማድረግ እና ምን መማር እንዳለባችሁ ስትጠይቁት፣ እርሱ መመሪያ ይሰጣችኋል።

ሁለተኛ፣ ለማደግ ጸልዩ

የሰማይ አባት እናንተ እንድታድጉ ሊረዳችሁ ይፈልጋል! በጣም ይወደናል ስለዚህም የህይወትን መንገድ እንዲያሳየን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ልኮልናል። ከኃጢአታችን ይቅር እንድንባል እና እርሱንም ወደመምሰል እንድናድግ ኢየሱስ ተሰቃይቷል፣ ሞቷል እንዲሁም ከሞት ተነስቷል።

በትዕግስት ወይም በታማኝነት ማደግ ትፈልጋላችሁ? በችሎታ ማደግ ትፈልጋላችሁ? ምናልባት ዓይናፋር ስለሆናችሁ ደፋር መሆን ትፈልጉ ይሆናል። “ጸልዩ፣ እርሱ እዚያ አለ!” በመንፈሱ በኩል፣ ልባችሁ ሊቀየር ይችላል፣ እንዲሁም ጥንካሬን መቀበል ትችላላችሁ።

አዲሱ ጓደኛዬ ጆና እንዲህ ሲል ጽፏል፣ “ብዙ ጊዜ ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ፍርሃት ይሰማኛል። ማርፈድ፣ የሆነ ነገር መርሳት፣ እና ፈተና መፈተንን የመሰሉ ነገሮች ያስጨንቁኛል። የ10 ዓመት ልጅ እያለሁ፣ ከእናቴ ጋር ወደ ትምህርት ቤት በመኪና እየሄድኩኝ በነበረ ጎዜ መጸለይ ጀመርኩ። ስለሚያስፈልገኝ እርዳታ ጠየኩኝ፣ ለቤተሰቤም ጸለይኩ። አመስጋኝ ስለሆንኩባቸው ነገሮችም አሰብኩኝ። [ወደ ሰማይ አባት መጸለይ] ረድቶኛል። አንዳንድ ጊዜ ልክ ከመኪናው እንደወረርድኩኝ እፎይታ አይሰማኝም፣ ነገር ግን ክፍል ውስጥ ስገባ ሰላም ይሰማኛል።”

ጆና በየቀኑ በመጸለይ ወደ ፊት ሲቀጥል እምነቱ እያደገ ሄዷል።

ሶስተኛ፣ ለማሳየትጸልዩ

የሰማይ አባትን ፍቅር ለሌሎች ለማሳየት ለእርዳታ መጸለይ እንችላለን። የሰማይ አባት ያዘነን ሰው ማጽናናት እንድትችሉ በመንፈሱ በኩል ያንን ሰው እንድትለዩ ይረዳችኋል። አንድን ሰው ይቅር በማለት ፍቅሩን እንድታሣዩ ሊረዳችሁ ይችላል። አንድን ሰው እንድታገለግሉ እና የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆናችሁ ለእነርሱ እንድታካፍሉ ድፍረትን ሊሰጣችሁ ይችላል። ይህንን ስታደርጉ፣ ሌሎች ልክ እንደ እናንተ ኢየሱስን እና የሰማይ አባትን እንዲያውቁት እና እንዲወዱት መርዳት ትችላላችሁ።

አባቴ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል እንዲሆን በህይወቴ ሙሉ እጸልይ ነበር። ገና ወጣት ልጅ እያለሁ እንኳን፣ እርሱ ምን ያህል በረከቶችን ሊያገኝ እንደሚችል አውቅ ነበር። የእኛ ቤተሰብ ለዘለአለም የመታተም በረከቶችን ማግኘት ይችል ነበረ። እኔ፣ ቤተሰቤ እና ጓደኞቼ ደጋግመን እንጸልይለት ነበር፣ ነገር ግን እርሱ ቤተክርስቲያኗን አልተቀላቀለም። የሰማይ አባት ማንም ምርጫ እንዲያደርግ አያስገድድም። የጸሎቶቻችንን መልሶች ግን በሌላ መንገድ ሊልክልን ይችላል።

ምስል
ፕሬዘዳንት ፖርተር ከወላጆቿ እና ከወንድምና እህቶቿ ጋር

እድሜዬ ሲደርስ፣ የፓትርያርክ በረከቴን ተቀበልኩ። በፓትርያርክ በረከቴ ውስጥ ቤተሰቦቼ በሰማያት እንዲኖሩ ለመርዳት ማድረግ የምችለው ትልቁ ነገር የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ምሳሌ መሆን እንደሆነ ፓትሪያርኩ ነገረኝ። እኔ ማድረግ የምችለው ያንን ነው!

አባቴ 86 አመት እሲኪሞላው ድረስ ኖረ። እርሱ ከሞተ ከአምስት ቀናት በኋላ የተቀደሰ የደስታ ስሜት ተቀበልኩ። የሰማይ አባት አባቴ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በረከቶች መቀበል እንደሚፈልግ በመንፈሱ አሳውቀኝ! ከወላጆቼ ጋር ለመታተም ከእህቴ እና ከወንድሞቼ ጋር በቤተመቅደስ ውስጥ ባለው መሠዊያ ዙሪያ የተንበረከኩበትን ቀን መቼም አልረሳም። ለዚህ በረከት መጸለይ የጀመርኩት በመጀመሪያ ክፍል በነበርኩበት ጊዜ ነበረ፣ መልሱን የተቀበልኩት ግን አያት ሆኜ ነው።

ምናልባት ቤተሰባችሁ እና ሌሎች የምትወዷቸው ሰዎች በረከቶችን እንዲቀበሉ እየጸለያችሁ ይሆናል። ተስፋ አትቁረጡ። የሰማይ አባት ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ያሳያችኋል

በልባችሁ ያለውን ለሰማይ አባት አካፍሉ። የእርሱን እርዳታ በቅንነት ስትጠይቁ እንዲመራችሁ መንፈሱን ትቀበላላችሁ። በየቀኑ መጸለይ በሰማይ አባት እና በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እንድትሞሉ ያደርጋችኋል። ይህ እድሜ ልካችሁን እነሱን ለመከተል እንድትፈልጉ ይረዷችኋል!

በአፍሪካ፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በእስያ፣ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በአውስትራሊያ ያሉ ልጆች ሁሉ በየቀኑ ቢጸልዩ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡ? መላው ዓለም ብዙ በሆነ የእግዚአብሔር ፍቅር ይባረካል!

ምስል
በአለም ዙሪያ ያሉ ልጆች እየተጫወቱ

የሰማይ አባት እንዳለ ለማወቅ እንድትጸልዩ፣ እርሱን በመምሰል ለማደግ እንድትጸልዩ እና ለሌሎች ፍቅሩን ለማሳየት እንድትጸልዩ እጋብዛችኋለሁ። እርሱ ህያው እንደሆነ እና እንደሚወዳችሁ አውቃለሁ። “ጸልዩ፣ እርሱ አለ።” በተቀደሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

አትም